•የኮሚቴው መሪ ዕቅድ የጸደቀው በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ መመሪያ መሠረት አይደለም
•በዕጩዎች ላይ የሕዝብ አስተያየትና ጥያቄ የማስተናገጃው ጊዜ 15 ቀን አይሞላም
•የኮሚቴው ሰብሳቢ ከመግለጫው ቀን በፊት በኮሚቴው ስብሰባዎች አልተገኙም
የስድስተኛውን ፓትርያሪክ ምርጫ እንዲያስፈጽም የተሠየመው ኮሚቴ፣ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው መግለጫ የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡንና ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ የሰጠውን መመሪያ የጣሰ መኾኑ ተገለጸ፡፡
‹‹፮ኛው ፓትርያሪክ የሚሾሙበትን ቀንና የምርጫውን ሂደት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ግልጽ ለማድረግ›› በሚል ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ÷ ምርጫውን የሚያስፈጽምበትን መሪ ዕቅድ ለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ አቅርቦ እንዳጸደቀ ጠቅሶ ነበር፡፡ ይኹንና የመንበረ ፓትርያሪኩ ሐራዊ ምንጮች ዘግይተው እንዳስታወቁት፣ የኮሚቴው መሪ ዕቅድ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 2/ሀ መሠረት÷ ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማሰናዳት የሚገባውን ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ለቅዱስ ሲኖዶሱ አቅርቦ ሊታይና ሊወሰንበት ይገባ ነበር፡፡ በዚህም አገባብ ተፈጻሚ እንዲኾን ኮሚቴው በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ መመሪያ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ነገር ግን ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በኮሚቴው ይፋ የተደረገው መሪ ዕቅድ በሕገ ደንቡ መሠረት ቅ/ሲኖዶሱ ያላየውና ያልወሰነበት እንደኾነ ነው ምንጮቹ የሚያስረዱት፡፡
መግለጫው በተሰጠበት ዕለት ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሌላ ከመግለጫው ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው አምስት ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአዳራሹ ተገኝተዋል፤ የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ግን በአካባቢው ጨርሶ አልታዩም፤ ይህም የኮሚቴው የድርጊት መርሐ ግብር እና አካሄድ ከቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ዕውቅናና ቁጥጥር ውጭ ለመኾኑ በአስረጅነት ተጠቅሷል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣንና ለአስመራጭ ኮሚቴው በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ በተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት (የኮሚቴውን ሊቃነ መናብርት የመሠየም፤ የዕጩ ፓትርያሪኮችን የማጽደቅ፤. . .) ዙሪያ በኮሚቴው አባላት መካከል ክርክሮች ተነሥተው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ምንጮቹ የሚያቀርቡት ተጨማሪ አስረጅ፣ የምርጫው ሂደት ዕዝና ቁጥጥር በሌላ እጅ ስለመውደቁ ይጠቁማል፡፡ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በሕገ ደንቡ መሠረት በቅ/ሲኖዶሱ ውሳኔ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ኾነው ተመርጠዋል፡፡ በተሰጣቸው ሓላፊነት መሠረት ግን የኮሚቴውን ስብሰባዎች በመንበረ ፓትርያሪኩ ተቀምጠውና በጽ/ቤቱ ተገኝተው አልመሩም፡፡ በመግለጫው ላይም ተገኝተው ጋዜጣዊ መግለጫውን ያነበቡት ከሀገረ ስብከታቸው ዕለቱኑ ተጉዘው እንደገቡ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው በመንበረ ፓትርያሪኩ እንዲገኙና መግለጫውን እንዲያነቡ የተደረገው ‹‹በወረደላቸው ቀጭን ትእዛዝ ነው›› ይላሉ የዜናው ምንጮች፡፡ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ግን በውሳኔያቸው የጸኑ ይመስላሉ – ከሀ/ስብከታቸውም ንቅንቅ አላሉ፡፡
በሌላ በኩል፣ የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ባወጣው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም በኮሚቴው በሚያቀርብለት ዕጩዎች ላይ ተስብስቦ በመወያየት የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለዕጩ ፓትርያሪክነት የታመነባቸውንና ይኹንታ ያገኙትን አምስት አባቶች ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፤ ከሦስት ቀናት በኋላ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ይህ የምርጫ መርሐ ግብር በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ 2/ሰ ከተጠቀሰው የጊዜ ሰሌዳ ጋራ የሚጣረስ ነው፡፡
በሕገ ደንቡ መሠረት÷ አስመራጭ ኮሚቴው ለፓትርያሪክነት ይበቃሉ ያላቸውን ዕጩዎች ስም ዝርዝር ከትምህርት ደረጃቸው፣ ችሎታቸውና ልምዳቸው ጋራ ለ15 ቀናት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፤ በእነዚህ ቀናት ውስጥም በዕጩዎች ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ካሉ ይቀበላል፡፡ በዚሁ ንኡስ አንቀጽ ፊደል ተራ ቁፅር (ሸ) እንደተመለከተው÷ ኮሚቴው ለፓትርያሪክነት ለመመረጥ ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ዕጩዎች የመጨረሻ ስም ዝርዝር ከትምህርት ደረጃቸው፣ ችሎታቸውና ልምዳቸው ጋራ ለሕዝብ የሚገልጸው፣ የምርጫውን ቀንና ቦታም የሚያስታውቀው ከሕዝብ የሚቀርቡለትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከቅ/ሲኖዶስ ጋራ መርምሮና አጣርቶ የሚቀበለውን ከተቀበለ፣ የማይቀበለውን ከጣለ በኋላ መኾን ይገባው ነበር፡፡
ኮሚቴው ጥር 30 ቀን ይፋ ባደረገው የምርጫ መርሐ ግብር ግን፣ ዕጩዎቹን ለቅዱስ ሲኖዶሱ ከማቅረቡ በፊት የ15 ቀናት ይፋዊ ጊዜ በመስጠት በዕጩዎቹ ላይ ከካህኑና ምእመኑ ጥያቄና አስተያየት እንደሚቀበል የሚያመለክት የሥራ ዕቅድ የለውም፡፡ በምትኩ እንዲሁ በደፈናው ‹‹ስድስተኛው ፓትርያሪክ ሊኾን ይገባል የምትሉትን በአካል በመቅረብና በፋክስ በመላክ ጠቁሙ›› ብቻ በማለት ነው ያስታወቀው፡፡ ይህም ኾኖ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የታዩ ጥቂት አስተያየቶች፣ በአንድ በኩል ዕጩ ለመጠቆም የተሰጠው የስምንት ቀናት ጊዜ በቂ እንዳልኾነ ሲተቹ በሌላ ወገን ደግሞ ለፓትርያሪክነት ብቁ ናቸው ያሏቸውን የራሳቸውን ዕጩዎች ዝርዝር በማቅረብ እገሌን ወይም እገሌን ብንመርጥ ማለት ጀምረዋል፡፡ በነገሩ ሁሉ ‹‹የገዘፈ ግፍ››ና በርካታ እንከን እንዳለ ከሚያምኑቱ ወገን እንኳ ‹‹ጥሩ አባት ለማስመረጥ ታሪካዊ አጋጣሚው አይለፈን›› በሚል ይኾናል፤ ይበጃል ላሉት አባት ግልጽ የምርጫ ዘመቻ ውስጥ የገቡም አሉ፡፡
የኾነው ኾኖ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የካቲት 16 ቀን የሚወያይባቸው ዕጩዎች÷ ካህኑና ምእመኑ እንደ ዕጩ ፓትርያሪክ ለይቶ የማያውቃቸው፣ በጥያቄና አስተያየት ያልተቻቸው ሊኾኑ ነው እንግዲህ፡፡ በምርጫ ሕገ ደንቡ አንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ 2 እና 3 እንደተደነገገው ግን የሕገ ደንቡ ዓላማዎች፡- ‹‹በካህናትና ምእመናን ዘንድ አመኔታ የሚኖረው ቋሚና ወጥ የኾነ የቅዱስ ፓትርያሪክ ምርጫ ሥርዐት›› ስለማስፈን፤ ካህናትና ምእመናን በግልጽ የሚያውቁትና በመተማመን የሚሳተፉበት የምርጫ ሂደት እንዲኖር›› ስለማድረግ ነበር፡፡
ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት በዓለም ዙሪያ የሚሰማው የዕርቁ ይቅደም አቤቱታ እንዳለ ኾኖ የገዛ ሕገ ደንቡን እንኳ ያላከበረው የምርጫ አስፈጻሚዎች ጥድፊያ ጥቂት የማይባሉ ታዛቢዎችን÷ የምርጫው ሂደት እንዲያው ለአጃቢነት የሚካሄድና ስድስተኛው ፓትርያሪክ አስቀድሞ የተወሰነ መኾኑን ክፉኛ እንዲጠረጥሩ፣ መጠርጠር ብቻ ሳይኾን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ‹‹የተያዘው ማስመረጥ ሳይኾን ማስቀመጥ ነው›› ይላሉ አንድ ሓራዊ አስተያየት ሰጪ፡፡
ምንጭ፡ ሐራ ተዋሕዶ