ይድረስልኝ ላንተ በቁምህ ለሞትከው
በደም ተጨማልቀህ ገምተህ ለሸተትከው
ክቡር አልልህም ክብር የት ታውቅና
ዶክተር አልልህም ምኑን ተማርክና
ሃገር ሞተች እንጂ ባንተ ድድብና
እስኪ ልጠይቅህ ማነው ያለህ በርታ
እንደዚህ አርክሶ ያጣላህ ከጌታ
እንዳሻህ ገደልከን እንደጉድ ሞትንልህ
ቤተ እምነት አቃጠልክ አልቅሰን ዝም አልንህ
በርሃም ቀጣኸን ላንተም ጸለይንልህ
ማን አይዞህ ብሎህ ነው አሁን የለየልህ
ባንተ ዘመን እኮ
አባቱን ያልሰዋ ወንድም ያልቀበረ
እህቱ ተደፍራ ቅስሙ ያልተሰበረ
እናቱ ታርዳበት በደም ያልሰከረ
በጦቢያዬ ምድር ሰው የለም ነበረ
ግን…
ሁሉንም አልፈናል አዝነን ብናለቅስም
ያሁኑ ድፍረት ግን አያለሳልስም
ቤተ እምነቷ ሲነድ ይሁን ያልፋል ባለች
ሃገር ሲተራመስ ምህላ በያዘች
ካንተ ክፉ እንዲርቅ ጾማ በጸለየች
ልጆቿን ሰብስባ ይቅር በሉ ባለች
ፍቅር ባስተማረች
ምኗ ቀሎህ ይሆን ባንተ የተደፈረች
አላወክም እንጂ
ኦርቶዶክስ መሆን የሃይማኖት ጥጉ
ለእምነቱ መሞት ነው ወግ እና ማረጉ
የአቡነ ጴጥሮስ የእየሱስ ልጆች ነን
በሞት ውስጥ ነው ትንሳኤን ያገኘን
ስለዚህ አንፈራም እመነን አንተ ሰው
ረጋ በል ሰከን ሞትክን አታርክሰው።
“የመጨረሻው ደብዳቤ”
ፀጋየ ወልኪቴ