September 10, 2022
16 mins read

 የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል! – አገሬ አዲስ

ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓም(10-09-2022)

የሰው ልጅ የሚመዘነው በጭንቅና ክፉ ወቅት ነው። በደህናው ቀንማ ሁሉም ደግ፣ሁሉም አዛኝ ይሆናል፣ውስጣዊ ማንነቱ አይታወቅም።።በክፉ ቀን ክፉ ሰሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ጉርብትናና ግንኙነት በዝምድናም ሰንሰለት ሳይቀር አብረው የኖሩ ሰዎች ይከፋሉ፤አንዱ በሌላው ላይ ይጨክናል።በስቃይና መከራው ሊጠቀምበት ይሻል።ሌላውን አሳልፎ በመስጠት አንደኛው ሊሾም ሊሸለምበት ይሽቀዳደማል። ይህንን ያመጣሁት እንደው የለለና ያልሆነ ነገር ፈጥሬ አይደለም ።ከታሪክ በመነሳት ማስረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ነው።ክፋትና ጭካኔ ዘርና ቦታን፣ጾታንና ዕድሜን አይለይም።በሁሉም ዘንድ የሚንጸባርቅ ድክመት ነው።

ይህንን ድክመት ሁለንተናዊ ለማድረግ ከዓለም ጦርነቶቹ በአንዱ በናዚዎች ጊዜ የሆነውን መነሻ ባደርግ ዘርና ቦታን አይለይም በሚለው አባባሌ ወደ አገራችን በምመለስበት ጊዜ ትስስሩን ግልጽ ያደርገዋል።የናዚዎችን አነሳሁ እንጂ በሌሎቹም ወቅቶች በተከሰቱ ጦርነቶችና ጉዳቶች ጊዜ የሰው ልጆች ክፋት ገንፍሎ የወጣባቸውን ሁሉ ላንሳ ብል ቦታና ጊዜ አይበቃኝም።

በናዚ ጀርመኒ ጊዜ የአውሮፓ አገራት ሁሉም በሚባል ደረጃ በጦርነት እሳት ተለብልበዋል ብቻም ሳይሆን አመድ ሆነዋል።ቀድሞ እጁን ያልሰጠና ለናዚዎች ያልተንበረከከ ከናዚዎች የክፋት እርምጃ አላመለጠም።በተለይም በዋናነት ጠላቶቼ ናቸው ብሎ የሚያሳድዳቸው የይሁዲ ተወላጆች የሚኖሩባቸው አገሮች የጥቃቱ ዒላማ ነበሩ።በዚህ ጥቃት ከያገሩ እዬተለቀሙ በቦታው ከተገደሉት ይበልጡን ወደ ጀርመን ተወስደው በማቃጠያ ምድጃ አመድ የሆኑት ከ6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መሆናቸውን ታሪክ መዝግቦታል።

የናዚዎችን ክፋትና ጭካኔ ተቀብሎ አጋር የሆነ የዬአገራቱ ተወላጅ ቁጥሩ ቀላል አልነበረም።የራሱን ወገን አሳልፎ እዬሰጠና ለናዚዎቹ እዬሰለለ ባገርና በወገኑ ላይ በደል የፈጸመ ባንዳው ከናዚዎቹ የበለጠ ናዚ ነበር ቢባል ስህተት አይደለም።ለቁራሽ ዳቦ ሲል ዘመዱን፣ጎረቤቱንና ጓደኛውን አሳልፎ የሰጠው ቁጥሩ ቀላል አልነበረም።ከዚህም ጎን ለጎን እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለተቸገሩት መደበቂያ ፣ጥላ ከለላ የሰጡም ደጋጎች ነበሩ።እነሱም በከሃዲዎች ከተጋለጡ ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰድባቸው ነበር።ያንን ቢያወቁም  ግን መልካም ነገር ከመሥራት አላፈገፈጉም።በዚህም የብዙ ሰው ሕይወት አድነዋል።

ሌላው በጦርነት ጊዜ ሁሉም ነገር መጥፋቱ የተለመደ ነው።በመጥፋቱም የዋጋ ጭማሪ ይኖራል።ይህንንም ተቋቁመው ያላቸውን ከሌላው ጋር ተካፍለው ክፉ ቀኑን ያሳለፉ ደጋጎችም ነበሩ።አንዳንዶቹ ጨካኞች ችግርን መሣሪያ አድርገው ባልጠፋ ነገር ላይ ከፍተኛ ዋጋ እዬጨመሩ በሚሰቃዬው ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ስቃይ ያደርሱበት እንደነበር በሁኔታው ያለፉ ሰዎች ይመሰክራሉ።በደህናው ቀን አንድ ቁምጣ ድንች ስሙኒ የነበረውን በጦርነቱ ጊዜ በወርቅ የአንገት ሃብልና ቀለበት የሸጡ አረመኔ ገበሬዎች እንደነበሩ፣እርሃብ የተፈታተናቸው ሰዎች ካለፈ በዃላ እምባቸው እያቀረረ ሲናገሩ መስማት አንጀት ይበላል። ክፉ ቀን አልፎ ሰላም ሲሰፍን ደጎችም ክፉዎችም እንደዬሥራቸው ማህበረሰቡ በታሪክ መድቦ አስቀምጧቸዋል።ክፉ የሠሩት በመልካም ጊዜ የነበሩበትን ቦታ ቀይረው ወደ ማይታወቁበት ቦታ የሸሹም አልጠፉም።ግን ቦታ ቢቀይሩም ጊዜው ቢረዝምም ታድነው ቅጣታቸውን አግኝተዋል።ያልተያዙት ጥቂቶቹ አብሯቸው የሚጓዘው ህሊናቸው የሚቆረቁር ቁስል ፈጥሮባቸው ግማሾቹ በጸጸት እራሳቸውን ሲገሉ አብዛኞቹም ከሰው ተነጥለው በባዶ ቤት ሞተው ለመገኘት በቅተዋል።ቢሞቱም ግን ልጅና የልጅ ልጆቻቸው የዛ ከሃዲና ጨካኝ ልጆች እዬተባሉ ለመሸማቀቅ መዳረጋቸው አልቀረላቸውም።የአባት ዕዳ ለልጅ፣የፊት እድፍ ለእጅ እንዲሉ!

በሌሎቹ አገሮች የሆነውን ካዬን በዃላ ወደ አገራችን ስንመለስ ቦታውና ጊዜው ቢለያይም ተመሳሳይ ድርጊቶ መካሄዳቸውን ካለፉት ታሪኮቻችንና አሁንም ከምናዬውና  ከምንሰማው ለማውቅ እንችላለን።በጣልያን ወረራ ጊዜ ባንዳ የተባሉት ከሃዲዎች ብዙ አርበኞችንና ንጹሃንን በግል በቀልና ጥላቻ ለጣሊያን ፋሽሽቶች አሳልፈው በመስጠት የብዙ ወገኖቻችን ህይወት እንደጠፋ አይካድም። ከጣልያኖች በዃላም በነበሩት  በዘውድና በወታደር አምባገነኑ  አገዛዞች ስርዓቱን ይቃወሙ የነበሩ አገር ወዳዶችን ጎረቤትና ጓደኛ ከዚያም ባለፈ ቤተዘመድ አሳልፎ በመስጠት እንጀራውን እንደጋገረባቸው የድርጊቱ ሰለባ የሆኑትና ከሞት የተረፉት ይመሰክራሉ።

በዚህ  ወገንን ወይም አንዱን የሰው ልጅ ሸጦ የመኖር ወይም በመከራው የመነገድና የመጠቀም ልክፍት አሁንም በኛ ጊዜ በስፋት ሲካሄድ ይታያል።ላለፉት 32 ዓመታት ለሰፈነው የጎሰኞች ሥርዓት ሰላይና አገልጋይ  በመሆን ለራሱ ነጻነትና መብት፣ለአገሩም አንድነት የሚከራከሩና የሚታገሉትን፣ስለ እውነት የሚመሰክሩና የቆሙ ደጋግና ደፋር ዜጎች አሳልፎ የሚሰጠው ጨካኝ ቁጥሩ ቀላል አይደለም።ክህደትና ጭካኔ የመተዳደሪያ ሙያ ሆኖል ማለት ይቻላል። ካለእነዚህ ክፉዎች ክፉ መንግሥታት አቅምና ዕድሜ አይኖራቸውም።

በወታደራዊው አምባገነን አገዛዝ ወጣቶችን እዬጠቆመ ያስጨረሰው አብሮ አደግና የሚያውቅ ጎረቤትና  የቅርብ ዘመድ ነበር።በአሁኖቹም ተከታታይ የጎሰኞች ስርዓት በወያኔና በኦነግ ኦሕዴድ ብልጽግና ዘመን ተቃዋሚዎችን የሚያሳርደው ያው ጎረቤት፣ጓደኛና ቤተዘመድ ነው። ጠላት ከሩቅ አይመጣም የሚባለውም ለዚያው ነው።

ሌላው የሕዝቡን ስቃይና መከራ መጠቀሚያ የሚያደርጉት ደግሞ በንግድና ባገልግሎት መስኩ የተሰማሩት ናቸው።በደህናው ቀን ብዙ መልካም ነገር ተካፍሎ አብሯቸው የኖረውን ሕዝብ በክፉ ቀን ለመጉዳት ሲሯሯጡ ማዬትን የመሰለ የሚያም ህመም የለም።

ክፉን ቀን ተሳስቦ ከመኖር ይልቅ በክፉ ቀን ስቦ ገደል መክተት ትልቅ እውቀትና ችሎታ ሆኗል።በገበያው ላይ የሚታዬው ክፋትና ስግብግብነት ከሰው ደረጃ አውጥቶ ከአውሬ ደረጃ የሚያሰልፍ ሆኗል። አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ዳቦ ከሁለት ብር ስድስት ብር ገባ ሲባል እንዴት ያልን ሰዎች፣ይኸው ዳቦ በደሴ ከተማ 30 ብር መሸጡን ስሰማ  እኔ የማቃት ደሴ ፣እኔ በአምስት ሳንቲም አንድ ፍርኖ ዳቦ በበላሁባት ደሴ የሆነ አልመስልህ አለችኝ፤ወይስ ሌላ ፕላኔት ላይ ስላለች  ደሴ ነው የምሰማው ብዬ ግራ ገባኝ።በዚችው የደጋጎች ከተማ በነበረችው ደሴ የሚካሄደውን ጭካኔና ራስ ወዳድነት ስሰማ ጭራሽ ማመን አቃተኝ።ወያኔ አዋክቦት ከመኖሪያ ቀዬው ያባረረው ወደ ቤቱ ወይም ህይወቱን ለማትረፍ ከደሴ ወልድያ፣ወይም ከወልድያ ደሴ ልሂድ ቢል ከ2500-3000 ብር ለነጠላ ጉዞ መጠዬቁን ስሰማ ይህ ክፉ ቀን አልፎ ደህና ቀን ሲመጣ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች በኩራት በደሴ ከተማ፣በፒያሳ አስፋልት ላይ  ዳግም መኪናቸውን ያሽከረክሩ ይሆን ብዬ እራሴን ስጠይቅ በእግራቸውም ለመራመድ መቻላቸውን ተጠራጠርኩ።ለሚመጣው ጊዜ ፈራሁላቸው። ሌላ ሌላውማ አይነሳ ይቅር ማለቱ ይሻላል።እንዲህ ጭካኔና ክፋት በዋጣት የደሴ ከተማ ከወለጋና ከሌላው ክልል ከሞት ተርፈው ተፈናቅለው የመጡት ዜጎች የሚገፉትን ኑሮ ሲያስቡት ይዘገንናል። መንግሥት ለነዚህ ሰዎች የሚፈልጉትን ከማሟላት ይልቅ በችግኝ ተከላ ጊዜውንና ገንዘቡን ያባክናል።ዱሮስ ቢሆን ከጎሰኞች መንግሥት ምን ይጠበቃል? አስጨፍጫፊውና አፈናቃዩ ማን ሆነና?ይኸው መከረኛ ሕዝብ መንግሥት ባለበት ከተማ  ሕግ ይኖራል ብሎ ወደ አገሩ ዋና ከተማ ወደ አዲስ አበባ ልግባ ቢልም እንደባዕድ ወራሪ ተቆጥሮ እንዳይገባ በፖሊስ ሃይል ይከለከላል።ታድያ ዬት ይግባ?ምን ይሁን?ዬት ይድረስ?

ግፍ መሥራት የማይታክትህ አምባ ገነን መንግሥት ሆይ!

በወገኖችህ መከራና ችግር ሃብት የምትሰበስብ ጨካኝ ነጋዴ ሆይ!

ለትንሽ ጥቅም ብለህ ሌላውን ሃቀኛና ለእውነት የቆመ፣አገር ወዳድ አሳልፈህ የምትሰጥ ከሃዲና አድርባይ ሆይ!

የሌሎቹ ስቃይና መከራ ባንተላይ ቢደርስ ምን ይሰማህ ይሆን?ሌላው ቢቀር ለምን ለልጅ ልጆችህና ለታሪክህ አታስብም?

የዛሬውን ቦታህን ዘለዓለማዊ አድርገህ ካሰብክ ተሳስተሃል።ከአንተ በፊት አንተ አሁን በተቀመጥክበት ቦታ ላይ ተቀምጠው እንዳንተ በሕዝብ ላይ ግፍ የሠሩ መናጢዎች የት እንዳሉና ምን እንደደረሰባቸው አስተውል።ፍትህ ከሰጣቸው ቅጣት ይበልጥ በሕብረተሰቡ የተሰጣቸው መለያ ሞተውም ቢሆን ከመቃብራቸው በላይ እንደሚኖር ተገንዘብ።የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል የምልህም ለዚያ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!ሌላው ቢቀር በሃይማኖትህ የምትሰማውን ደግ ነገር ሁሉ ለማድረግ ቢሳንህ እንኳን፣እንደ ሰው ለሌላው ወገንህ ብትራራለት በክፋት ከምታገኘው ጥቅም የበለጠ ልባዊ ደስታ ታገኛለህ።ቤት አከራይ ስለሆንክ በተከራዬው ላይ አትጨክን፣ቤትህ ጊዜያዊ እንጂ ዘለዓለማዊ አይደለም፤ሊፈርስ፣በእሳት ሊወድም ወይም፤ልትቀማ ትችላለህ።በርካሽ የገዛኸውን ከሚያስፈልገው ትርፍ በላይ ጠይቀህ ብትሸጠው የገዢው ልባዊ ሃዘን እንደሚጎዳህ አስብ! በደህና ቀን ቋሚ ደንበኛህን እንዳታጣ በክፉ ቀን ተንከባክበህ ያዘው።እዘንለት፣አስብለት!ከገንዘብ ትርፍ በላይ የሰው ፍቅርና ክብር ታተርፋለህ። የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል የምልህም ለዚያ ነው።

የመከራ ቀን ጥሩ መስተዋት፣

ደግና ክፉ የሚታይበት፤የሚለይበት።

አገሬ አዲስ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop