በኢትዮጵያችን ላይ የተደፋው ርኩስ የመጠፋፋትና የጥላቻ ፣ የጭካኔና የዘረኝነት መንፈስ መገለጫው ዓይነቱና መከሰቻው ስፍራ ከጎንደር እስከ ባሌ ከቤንሻንጉል እስከ ሐረር የዘለቀ ሲሆን ፤ ከሰውነት እሳቤና ርህራሄ ውጪ በመሰል ኢትዮጵያዊ ወገንና አካል ላይ ሳያባራ ላለፉት አራት ዓመታት ቀጥሏል። መራሄ መንግሥቱ መገዳደሉ መፈናቀሉና ውድመቱ በራሱ ጊዜ ሲበቃው ይቆማል ሲል እጁን ከታጠበ ሰንብቷል።
አእላፍ ግን ህይወታቸውን አጥተዋል፣ እያጡም ናቸው። በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ንብረት መውደሙ ቀጥሏል። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብም በገዛ ሃገሩ ስደተኛና ተፈናቃይ ሆኗል። ረሃብና በሽታ ስር ሰደዋል። አሸንፈናል የተባለው የሰሜኑ ጦርነት ትርጉም አጥቶ እና እንደ ዱቄት በትነነዋል የተባልነው ናዚስት ወያኔ በተደራጀና በጎለበተ ወታደራዊ ቁመና የአማራና የአፋር ክልልን በመሰረተ ልማትና በዕድገት 30 ዓመት የኋሊት መልሷቸው ህዝቡን አፈናቅሎ ዘርፎና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሞ ወደ ጎሬው ሲመለስ ያልተቋጨው ጦርነት ለአፋርና ለአማራው ህዝብ ማባሪያ ያጣ ሰቆቃ እንዲሆን ሆን ተብሎ ተትቷል። ዱቄት ሆኗል የተባልነው የኢህአዴግና ኢህአዴጋውያን አባት ናዚስት ወያኔ ከነሙሉ አቅሙ ከነዘግናኝ ወንጀሉ ከብልፅግና መንግሥት ጋር ለእርቅና ለሥልጣን በአንድ እጁ መትረየስ በሌላ እጁ አንቀፅ 39ኝን ይዞ ለድርድር ሽርጉድ እየተባለ ነው ። ያለ ጦርነት መኖር የማይችለውና ህልውናም የማይኖረው ናዚስት ወያኔ በአማራና በአፋር ላይ ዳግማዊ የምፅዐት ጦርነት መጀመሩ ደግሞ አይቀሬ ነው። ትህነግ በይፋ በአማራና አፋር ህዝብ ላይ በሚከፈተው ድጋሚ ጦርነት የብልፅግና መንግሥት ካለፉት ተደጋጋሚ ስህተቶቹ ተምሮ በወያኔ ላይ የማያዳግም ሁለገብ እርምጃ ካልተወሰደ አማራና አፋር የእልቂትና የውድመት መናኸሪያ ይሆናሉ።
ናዚስት ህወሓት ከተንቤን ገደል ወጥቶ ከሞት ወደ ህይወት ትንሣዔ ለማግኘቱ የብልፅግና መንግሥት መሰረታዊ ስህተት ውጤት ነው። ይህ ሳያንስ የዘር ማፅዳትና የህወሃት አርኪቴክት አቦይ ስብሃትንና ናዚስት ወንጀለኞችን በስተርጅና ዘመናቸው አስሮ ማቆየት በእግዜር ዘንድ ያስጠይቀኛል ሲል ብልፅግና በቴሌቪዥን የሚያሰቅቅ ንግግር አሰምቷል። ቀንደኞቹን ናዚስቶች ከእስር ፈትቶና ነፃነት ሰጥቶ በብዕር የሚተቹትን ጋዜጠኞች እያሳደደ ያስራል፣ ደብዛቸውንም ይሰውራል።
በዚህ ሁሉ ሀገራዊ ሰቆቃ ፣ ረሀብና ጦርነት መኻል የብልፅግና ፓርቲ መንግሥት ከበርቻቻው ግብዣውና ብልጭልጠጭ ብልፅግናው (በተለይ በአዲስ አበባ) ቅጥ አጥቷል። ፖለቲካው ባለፉት አራት ዓመታት በሂደት እጅግ እየጎመዘዘ ከመምጣት አልፎ ለሀገርና ለኢትዮጵያዊነት ህልውና እጅግ አደገኛ ሆኗል። የእርጉዝ እናት ሆድ በስለት ተተልትሎ ጨቅላ ሲገደል ፣ ህፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ በዘረኞች በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ከሚታረደውና ከቀዬው ከሚፈናቀለወ ህዝብ በላይ በአረንጓዴ አሻራ ለመከነ ወይም ተረግጦ ለሞተ ችግኝ በብዙሃን መገናኛ የሚንገበገብ መንግሥት ፣ በህዝብ ረሀብና የምግብ ጠኔ በኑሮ ውድነትም ሰቆቃ ለሚሰቃይ ህዝብ ‘ጎመን በጨው ፣ ሙዝ በዳቦ’ በአማራጭ ምግብነት የሚሰብክ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ በለውጡ(?) ማግሥት ይከሰታል ብሎ የገመተ አልነበረም። ለውጡ ከዘመነ ወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዐተ አገዛዝ የቅርፅ እንጂ የይዘት ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። አልሸሹም ዞር አሉ ሆኗል የብልፅግና ሥርዐተ መንግሥት ሁለገብ ተግባር። ሚሊዮናት ህፃናትን ይዘው ተፈናቅለውና መጠለያ አጥተው ብልፅግና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያወጣ ህንፃ ያድሳል። የቢሮ ጌጣጌጥ ይቀያይራል። በግብዣ ላይ ግብዣ እየጠራ ደረቅ ዳቦ ለናፈቀው ሕዝብ የትረፈረፈ መስተንግዶውን በቴሌቪዥን ያሳያል።
ኢህአዴግንና ኢህአዴጋውያን ሁሉ አቅፎ በብልፅግና ፓርቲ መታወቂያ ሥልጣን የያዘው መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ለተከታታይ አራት ዓመታት የዘለቀውን የዘረኝነት መጠፋፋት፣ መፈናቀል ፣ ወደር ያጣውን ግፍና ሰቆቃ ‘በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ክስተት ነው’ ሲል ያለ አንዳች ሀገራዊና መንግሥታዊ ሀላፊነት በአደባባይ ከመግለፅ በዘለለ መንግሥታዊ ግዴታውንና ሀላፊነቱ ሲወጣ አልታየም። ብልፅግና ህግንና ሥርዓትን ማስጠበቅም ሆነ ማስፈን እስካሁን አልቻለም። በገፍና በግፍ ለጠፋው የህዝብ ህይወትና ለወደመው ንብረት ሀላፊነትንም ተጠያቂነትንም እንደ መንግሥት ሲወስድ አልታየም፣ አይታይምም።
ብልፅግና ለአራት ኪሎ መቀመጫው አስጊ ሁኔታ የተፈጠረ ሲመስለው ግን በእጁ የሚገኙትን የፀጥታ ሃይላት የሚያሰማራበትና ርህራሄ አልባ እርምጃ የሚወስድበት ፍጥነትና ቅልጥፍና አስገራሚ ነው። ለአብነት፤ ሀ/ አብዲ ኢሌ መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርግ ነው ብሎ በብርሃን ፍጥነት ሐረር ተገኝቶ አብዲን የፊጥኝ አስሮና ሴራውን አክሽፎ ተመልሰሷል። ለ/ ባህር ዳር ላይ በነጄኔራል አሳምነው ፅጌ የሚመራ ሀይል መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርግ ተንቀሳቅሷል ሲል ባህር ዳር በቅፅበት ተከስቶ ከጄኔራሉና ቁጥራቸው በውል ካልተገለፀ የአማራ ልዩ ሀይሎች ዘግናኝ እልቂት በኋላ ሙከራውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ለህዝብ ገልጿል። ሐ/ በዘፋኝ ሀጫሉ ሞት ማግሥት ከሶስት ዓመት በላይ እንኮኮ አድርጓቸው የቆዩት እነ ጃዋር መፈንቅለ መንግሥት ሊያደርጉ ነው ሲል ከያሉበት ሰብስቦ ወህኒ ዶሏቸዋል። መ/ ናዚስት ወያኔ የአማራና የአፋር ክልልን ወርሮና እጅግ አሰቃቂ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ሲፈፅም ብዙ ትችትን ያስተናገደው ብልፅግና ወያኔ ወደ አዲስ አበባ ሲቀርብ ወታደራዊ ልብሱን አጥልቆ በመዝመት ናዚስቶችን አማራና ትግራይ አዋሳኝ ላይ ለቋቸው ‘ጦርነቱን አሸንፌያለሁ’ ብሎ ወደ መንበሩ ተመልሷል። አማራና አፋር ዛሬ ፍዳቸውን እየቆጠሩ አዲስ አበባ ግን ሰርግና ምላሽ ነው – ብልፅግና መንደር። የኢትዮጵያ ብልፅግና መንግሥት ወደ መንበሩ ለሚጠጋ በህግና ደንብ ማስከበር አርማ ሥር ሲዘምትና ወንበሩን ሲጠብቅ አስደናቂ ቅልጥፍና አለው። ሕዝብ ከዓመት ዓመት መጤ እየተባለ ከሚኖርበት ሲፈናቀልና ኢሰብዐዊ ጭካኔ ሲፈፀምበት፣ አብያተ ክርስቲያናትና መስጂዶች ከዐመት ዐመት ሲነዱ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ለህግ መጓደል ለሥርዐት መጥፋት ለፍትህ አለመኖር ሀላፊነት ሲወስድ ፣ የተሰደዱትን ሲጎበኝና ተገቢውን እርዳታም ሲያደርግ አይታይም።
ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና ፓርቲነት የተቀየረው መንግሥት በኢትዮጵያ ህግንና ሥርዐትን በማስፈን የኢትዮጵያውያንን በሀገራቸው በሠላም የመኖር በነፃነት ሰርቶ የመግባት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል በኢትዮጵያዊነት የመንቀሳቀስ እና የመኖር የዜግነት መብታቸውን ማስጠበቅ ከቶም አልቻለም ወይም አይፈልግም።
ብልፅግና የቀደመ የኢትዮጵያን አኩሪ የነፃነትና የሉዐላዊነት ታሪክ ከዚህ ቀደም በዘመነ ወያኔ ኢህአዴግ አገዛዝ ተሰምቶ በማያውቅ ስሜትና ቋንቋ በውደሳና ፉከራ ያሸበረቀ ዲስኩር በየጊዜው በየመድረኩ በማድረግ የሚስተካከለው ባይኖርም በተግባር ግን፤ ሀ/ እኒያ ጥንታውያን በአድዋም ይሁን በማይጨው፣ በካራማራም ይሁን በባድመ ከጠላት ጋር ሲተናነቁ ከፍ አድርገው የተሰዉላትን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ንፁህ ሠንደቅ ዓላማ እንደ ናዚስት ህወሃት ሁሉ በአሸባሪነትና በህገ ወጥነት ፈርጆ በየክብረ በዓሉ ላይ ሲያሳድዳትና በፀጥታ ሀይላቱ ከሕዝብ እጅ እየነጠቀ በየሜዳው ሲያዋርዳትና ሲወረውራት ማየት እጅግ የሚያበሳጭና የሚያስቆጭ የአራት ዓመት ተደጋጋሚ የብልፅግና ተግባር ሆኗል። ህገ ወጥ ሰንደቅ ዓላማ ይዛችኋል እያለ ስንቶች በፀጥታ አስከባሪዎች ተደብድበዋል?! ስንቶችስ ለእስር ተዳርገዋል?! ብልፅግና ያደባባይ አማላይ ዲስኩሩ ለፓለቲካ ፍጆታ ፓለቲካዊ ገፅታ ግንባታ ከመሆን በቀር መንግሥታዊ ሠንደቅዓላማን የማሳደድና ከኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የማገድና የማውረድ አስነዋሪ ተግባሩ እንደ ወያኔ ዘመን ሳያባራ እንደ ቀጠለ ነው።
ለ/ በዘመነ ብልፅግና ብሔራዊም ሆነ ሕዝባዊ ክብረ በዓላትን በሰላምና በነፃነት ማክበር ከቶም አልተቻለም። የብልፅግና ባለሥልጣናት ለምሳሌ የዐድዋ በዓልን ለማክበር ከሚያወጡት ተንኳሽና እብሪተኛ ፀረ ታሪክ ፀረ ሠንደቅ ዓላማ መመሪያ የተነሳ በየጊዜው ዐድዋ ክብረ በዓል የታሪክና የሠንደቅ ዓላማ የፍልሚያ በዓል ሆኗል። ዐድዋ ላይም ሆነ ማይጨው ካራማራም ሆነ ባድማ ለሉዓላዊነት የተውለበለበችው ባንዲራ የመጀመሪያ የክብረ በዓሉ የብልፅግና ሰለባ ሆና ትሳደዳለች። ትጋዛለች። ትዋረዳለች። ለጥምቀት ክብረ በዓልም ይኸው ድርጊት ተደጋግሞ ተከስቷል። መመሪያው መንግሥታዊ ነውና !!!
ናዚስት ወያኔ አራት ኪሎን ከለቀቀ ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት ተተኪው ብልፅግና የመልካም አስተዳደር፣ የሰላም የፍትህና የሀገር ሉዐላዊነትን በሂደት ያሰፍን ይሆናል የሚለው ተስፋችን ከመሟጠጡም በላይ ይነጋል ያልነው እየጨለመ፣ ህግና ሥርዓት፣ ሰላምና ደህንነት ለሥርዓተ መንግሥቱ ወንበር ህልውና እንጂ ለህዝብና ለሀገር ህልውና እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አሳይቷል።
አዎ ኢትዮጵያ ላይ ህዝብ ድምፄን ከሰጠሁት ከቀደመ ስህተቱም ሆነ ዳተኝነቱ ወይም ከፋፋይነቱና ጥምቀተ ኢህአዴጋዊነቱ ተላቆ እንደ መንግሥት ሀላፊነቱን ይወጣል በሚል ተስፋ የቀድሞው ኢህአዴግ የአሁኑ ብልፅግናን በመንግሥትነት አስቀምጦታል። አዎ ይህ መንግሥት በዓለም መንግሥታት በኢትዮጵያ ህጋዊ መንግሥትነት ይታወቃል። ይሁን እንጂ ብልፅግና በድህረ ወያኔ የአራት ዓመት መንግሥትነቱ ሲመዘን ፤ የጠፋው ህይወት፣ የተፈናቀለውና መጠጊያ ያጣው ህዝብ ብዛት፣ የሰላምና የዜግነት ነፃነት እጦት ፣ የወደመው ንብረትና፣ የተጣሰው ሀገራዊ ሉዓላዊነት ፣ የተሸረሸረው ኢትዮጵያዊነትና አብሮነት የደረሱበት ጡዘት፣ የብልፅግና ዳተኝነት፣ ሁሉን አዋቂነትና ከፈረስ ጋሪ የማስቀደም ተግባራት ኢትዮጵያን እጅግ አደገኛ ወደ ሆነ ምዕራፍ ላይ አድርሷታል።
አዎ ዛሬ በ2014 ዓ/ም ሀገራችን የምትገኝበትን ሐምሌያዊ ድባብ ሰባት ሚሊዮን ህዝብ የያዘው የናዚስት ወያኔ ተግባር ወጤት ነው ብለን አንድ መቶ አስር ሚሊዮን ህዝብን ከሚመራው ፣ የትየለሌ ባጀት፣ መንግሥታዊ መዋቅርና የጦር ሀይል ካለው ብልፅግና ትከሻ ላይ ማውረድ ከቶም አይቻልም። ግን ዛሬም ለኢትዮጵያ አልመሸም። ብልፅግና ሆይ ይህ ምዕራፍ ለአንተም ህልውና ሆነ ለኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ነውና ከኢህአዴጋዊ ርዕዮትህና ከኔ በላይ ለኢትዮጵያ አዋቂ ላሳር ከሚለው መንግሥታዊ ደዌህ ተላቀህ ድምፅ የሰጠህን ህዝብ ልብ ሰጥተህ ስማ፣ የሕዝብ መንግሥት እንድትሆን እንጂ ድምፅ የተሰጠህ የፉክክር ቤት የምትመራ መንግሥት እንድትሆን አይደለም። የየክልል መንግሥታት ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ መንግሥታት እስኪመስሉ ድረስ የታበዩት በአንተ አመራር ምክንያት ነውና የኢትዮጵያውያን ሁሉ መንግሥት መሆንህን ከዲስኩር ይልቅ መሬት ላይ በሚታይ ግብርህ አስመስክር። በግልፅ ከሚታይብህ የተደጋጋመ የስህተት አረንቋም ራስህን አፅድተህ ውጣ። ቅድሚያ የሚሰጠው መሰረታዊ ሀላፊነትህ ላይ ሥራ – እንደ ህዳሴው ግድብ!!! መንግሥታዊ ኃላፊነትህንና ግዴታህንም ተወጣ። ይህ ይሆን ዘንድ አልመሸብህምና ሳይመሽ አይምሽብህ!! ውስጣዊ ሰላሟ የተረጋጋ፣ ህግና ሥርዐት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ለትንሳኤዋ መነሻና መድረሻ ብቻ ሳይሆን ለአንተም ህልውና አልፋና ኦሜጋ ነውና። ኢትዮጵያ ከአንተ በፊትም ነበረች ከአንተም በኋላ ትኖራለችና !!! አዎ ነገ ሌላ ቀን ነውና – በበኩሌ በሀገሬ በኢትዮጰያ ግን ከቶም ተስፋ አልቆርጥም!!!
[ መስፍን ማሞ ተሰማ ግንቦት 2014 ዓ/ም ሲድኒ አውስትራሊያ ]