ኧረ ፋኖ! ፋኖ!
እንደ ዝንብና እንደ ክፉ መንፈስ ግንቦትን የሚወዱት ደደቢታውያን (ደብረጽዮን እና አቢይ አህመድ)፣ ፋኖን ለማጥፋት ግንቦት ላይ ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል። ግንቦት ሦስት። አማራ ፋኖ ያለውን ያህል ባንም ሁሌ ስለማያጣ ቆሻሻውን ሥራ የሚሠራ የባንዳ ሹምባሽ ባሕርዳር ከረመ ተብሏል። የት? አቫንቲ ሆቴል። የስሙም ሥምረት የሚደንቅ ነው። ለባንዳ መኝታ የሰላቶ ስም ያለው ሆቴል! አቫንቲ! በጣልያንኛ ወደፊት? ቀጥል? ግፋ! ግባ! እንደማለት ነው። የጣልያን ባንዳ ኦሮሞም አማራም ትግሬም የሆንክ ሁላ ወደፊት ግፋ! ሀገር አጥፋ! ወገን አውድም! የተባለ ይመስል በአቫንቲ ሆቴል ሰፍሮ ሲያሴር፣ ሲያደራጅ ሰንብቶ አሁን ለግንቦት ቀጠሮ ይዟል። የመንፈስ መመሪያው ከጣልያን የወረደለት ስለሆነ ትውልድም ተሻግሮ አቫንቲ! የሚለውን ነው የሚያደምጠው።
የፋኖ ምርጫ
1 በላይ ዘለቀ (የሶማው) በስሙኒ ገመድ ተንጠልጥሎ መሞት
2 ደርበው አየለ (የዱር ቤቴው) አሥሩን ባንዳ ደራርቦ መሄድ
3 እሸቴ ሞገስ (የይፋቱ) ዘጠኙን ባንዳ አራግፎ መሄድ
4 ደመቀ ዘውዱ (ወልቃይቴው) ባንዳውን ረፍርፎ በወገን ታጅቦ ትግሉን መቀጠል
እነዚህ ናቸው የፋኖ መንገዶች። ትናንትም ዛሬም። ምሳሌው ብዙ ስለሆነ ያታክታልና እነዚህን ለናሙና መርጠናል። ፋኖን ማዳን የፋኖ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም ግዴታ ነው። ላንተ ነጻነት ለሚሞትልህ ፋኖ መቆም ከተሳነህ የደህንነትህ ዘብ የሆነውን ፋኖን ካስወገዱ በኋላ ሰንሰለቱን፣ ሜንጫውን ወይም የመቅበሪያውን ዶዘር ይዘው እደጅህ ድረስ ይመጡልሃል።
የአማራ ሕዝብ ሶሥት ዐይነት ነው። ፋኖ፣ ባንዳና ባርያ። ምርጫውም እንግዲህ ሦስት ነው ማለት ነው። አቅም፣ ወኔ፣ አባት፣ ያለው ፋኖ ይሆናል። ሆድ ያለው ባንዳ ይሆናል። ጀግናውን የሚያስገድል ቆሞ ተመልካች ደግሞ ባርያ ይሆናል።
ምርጫ በምርጫ ነው። ቡፌው ቀርቧል የሚስማማህን መርጠህ አንሳ። የመጨረሻው ምሽግ ላይ ቆመሃል፣ መሸሻ መጠጊያ የለህም። ከተኛህም ጅራፉ ቀስቅሶ ወይም ወደ ወህኒ ወይም ወደ መቃብር ያወርድሃል። ባንዳም ብትሆን ፋኖ ሲያልቅ የመሳደድ ተራው ያንተ ነው። ግንቦቴው ካልጠፋ ሰላም አይኖርህም። እንቅጩን ስንነጋገር።
ከላይ የተጠቀሱትን ዝነኛ ስሞች ለማያውቁ መጠነኛ ማብራሪያ
በላይ ዘለቀ። ጣልያንን በአምስት አመቱ ትግል የመከተ ስመጥር አርበኛ፣ የጎጃም ተወላጅ። ጣልያን ከተባረረ በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስቅላት የገደሉት።
ደርብ አየለ። ወያኔ በውደቀቷ ዋዜማ ተቃውሞ ስለበዛባት እንደዛሬው አቢይ አህመድ ባንዶችን ልካ ትጥቅ ልታስፈታው ስትል አሥራ ምናምኑን አቁስሎ ወደ ሰባቱን ባንዳዎች ረፍርፎ የተሰዋ የዱር ቤቴ፣ ጎጃም ተወላጅ።
እሸቴ ሞገስ። የይፋት ተወላጅ ከልጁ ጋር ሆኖ ወያኔ በዳግም ወረራዋ ወደ ደብረ ብርሃን የምታደርገውን ግስጋሴ የመከተ ዘጠኝ ባንዳ ረፍርፎ የተሰዋ።
ደመቀ ዘውዱ። ወያኔ የወልቃይትን ጥያቄ ለማሰናከል አፋኝ የትግራይ ልዩ ኃይል እቤቱ ድረስ ብትልክበት፣ መሣሪያ አንስቶ አጥቂዎቹን ያወደመ፣ ሕዝቡም ደርሶ ያስጣለውና ትግሉን ለማስቀጠል የቻለ የጎንደር ዘመናዊ አርበኛ። የወያኔ ውድቀት ዋና ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ።