ሆዳ አደር እና ከራስ በላይ ነፋስ ባይ ምሁራንን ( ሊሂቃንን ) ፣ የፖለቲካ ተዋንያኑንና ባለሥልጣናቱን ፣ የኃይማኖት አባቶችን ጭምር ፣ እንደ መለሥ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን ሁሉ ፣ በዘመነ አብይ አገዛዝ ዘመንም ፣ በዓለማዊ ና በመንፈሣዊ የሰው ልጅ ህይወት የተወገዘ የዘረኝነት ፖለቲካ በእጅጉ አሳብዷቸዋል ። ብዙዎቹ ቱባ ባለሥልጣናት እና የኃይማኖት መሪዎች ፣ በዘረኝነት ካባ ውሥጥ ተወሽቀው ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች በእጅ አዙር ፣ በገፍ በሚያቀርቡላቸው ልዩ ፣ ልዩ የቅንጦት ቁሥ የተነሳ የቁሥ ሰቀቀን ጠርንፏቸዋል ። የቁሥ ሰቀቀኑን ተከትሎ በነገሰባቸው የልብ መታወር የተነሳ ፣ ዓለማዊያኑም ሆኑ ፣ መንፈሳዊያኑ ባለሥልጣናት ፣ ህሊናቸውን በመሸጥ ቀውሰዋል ። ህሊና ቢስ በመሆናቸውም ፤ ዜጎች በችጋር እየተሰቃዩ ፣ እነሱ በሚዘርፉት የደሃ አገር ሃብት ያለቅጥ እየቸንዘባነኑ ነው ። ከጥጋባቸው የተነሳ ሰማይን በእርግጫ በማለት ፣ የግብዝነታቸውን ለከት አለባነት ያለሐፍረት እያሳዩን ነው ። …
ይኽ ሰማይን በርግጫ የመምታት ድርጊት ከግብዝነት የሚመነጭ ነው ። ፤ ትላንት የንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤን ውደቀት አሥከትሎ ፣ ያለህግ ፤ የመኮንንቶችን ፣ የሚኒሥተሮችን ፣ የከፍተኛ ጦር መኮንኖች ና ባለሥልጣናትን ህይወት ፣ ፍፁም ሳያስቡት እንዲቀጠፍ ያደረገው ይኼው ግብዝነት ነው ።
ከ1953 ዓ/ም የነመንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት መክሸፍ በኋላ እንኳ ፣ ንጉሡ ለለውጥ ዝግጁ ባለመሆናቸው ፤ ሁሉንም የመንግሥት ሥልጣን ጨምድደው በመያዝ ፣ በፈላጭ ፣ ቆራጭነታቸው በመቀጠላቸው ፤ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካዋ መዲና አዲስ አበባ ፣ የግብዝ ፊውዳሎች መፈንጫ እንድትሆን በማድረግ አልጋቸው በቀላሉ እንዲገለበጥ አድርገዋል ።
በቁሥ ሰቀቀን ውሥጥ ሰምጦ ፣ ነጋ ጠባ አሥረሽ ምቺው ማለትን የመረጠ ። የጭሰኛውን ህይወት እጅግ መራር ያደረገ ። በመሣፍንትነቱ ፤ በመኳንንትነቱ ና በባላባት ልጅነቱ ብቻ በመመፃደቅ ፣ ያልደከመበትን እያጋበሰ ና ፣ በፈረንጅ ሱፍ ደምቆና ተውቦ ፣ በሐር ጨርቅ ና በሱፍ ካቦርታ ከተዋቡ ወዛዝርቶች ጋር ፣ በፈረንሳይ ሽቶ ታውዶ ፣ “ ማነህ ባለሣምንት ? “ እያለ ፤ ባለሣምንት እየተባባለ ፣ “ ፓርታ “ በማድረግ “ አሼሼ ገዳዋ … ! “ እያለ በውሥኪና ሻምፓኝ ሲራጭ ነው ። ዓለሙ እንደዋዛ ያለፈችበት ።
መሣፍንቱና መኮንንቱ የደሃ አገር መሪ መሆናቸውን ዘንግተው በተጋነነ ድግሥ አቅላቸውን ሥተው ፣ “ …ሸረቡሽ ! ውሥኪ _ ጀነኑሽ ! “ እያሉ በጥለሁን ገሠሠ ዘፈን ፣ ቡጊ ውጊውን ፣ ሣምባውን ፣ ታንጎና ማሪጌውን ሲያቀልጡ ፤ በአያሌው መሥፍን “ እንዴነሽ ገዳዎ …” ሲውረገረጉ ፤ በመሐሙድ አህመድ ጉብልዬን እያዜሙ ጥንድ ፣ ጥንድ ሆነው በሐላፊ ሐሴት ፣ “ በሻፓኝና ውሥኪ እየተራጩ “ ዓለም በጎኔ አለፈች ! “ በማለት ሲመፃደቁ ነበር ፤ ሣያሥቡት የየካታቱ 1966 ዓ/ም ፣ የተቀጣጠለው አብዮት ነው ወስጥ ውስጡን ተፋፍሞ ፣ በ1967 ዓ/ም አንድዶ አመድ ያደረጋቸው ።
ዛሬም መሠል ክሥተቶች ፣መሠል “ አሼሼ ገዳዎዎች “ እየታዩ ነው ። ሣናውቅ በሥህተት ፤ አውቀን በድፍረት …” እንዲሉ በየክልሉ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን የማይመገብ ህዝብ እያሥተዳደሩ ፣ ይኸው ዜጋ ከሌለው ላይ ቀንሶ ታክሥ በመክፈል ፣ ደሞዝ ቆርጦ እያበላቸው ፤ እነሱ ግን ከደሞዛቸው ውጪ በህግ ሽፋን በሚደረግ ዘረፋ ፣ ዘወትር ቁርስ ምሣና ራታቸው በመንግሥት ወጪ ፣ የሚሸፈንላቸው ፣ከወር እሥከወር “ አሥረሽ ምቺው “ ወይም “ ዙሩን አክርልን ! “ ባዮች ሆነዋል ። ይኽንን “ሰማይን በእርግጫ የመምታት የጥጋብ ህይወት በማየትም የፖለቲካ ተንታኞች “ እንሆ ሣይደወል ቅዱስ ተብሎ ፣ የብልፅግና የቁልቁለት ጉዞ ተጀመረ “ ይሉናል ።
ይኽ ፣ አሥደንጋጭ “ ሳይደወል ቅዱሥ ( ሀ ሳይሉ ፐ ) “ አይነት ፤ የብልፅግና የቁልቁለት ጉዞ እንዴት ተጀመረ ? “ በቋንቋ ና በጎሣ ሥም በየክልሉ ፣ “ ተፋቅሮ የሚኖረውን ህዝብ ፣ በዘር የሚያቦድኑ ፣ ግብዝና ከአፍንጫቸው ርቀው የማያሰቡ ዘረኛ ባለሥልጣናትን እንደ ዘመነ ወያኔ ፣ በመላው ኢትዮጵያ እንዴት በዚች አራት ዓመት ውሥጥ እንደ አሸን ፈላ ?! ብለን ብንጠይቅ መልሱን የምናገኘው ብልፅግና ተንኮታክቶ ከወደቀ በኋላ ነው እንጂ ዛሬ በሚያረካ መልኩ መልሱን የሚሰጠን አይኖርም ። ኢህአዴግ ተንኮታክቶ ሲወድቅ “ የኢህአዴግ የቁልቁለተ ጉዞ “ ብሎ ፤ ብርሃነ ፅጋብ የወያኔንን ተንከባሎ ወደ ገደል መግባት ፣ በ519 ገፅ እንዳሳወቀን ና ከ2005 እሥከ 2010 ዓ/ም የነበረውን ፣ ሸፍጥ ፣ አድርባይነትና ከእውነት ጋር ያለመቆም ያሥከተለውን ጦሥ ፣ ጥንብሳስ ከሥር ከመሠረቱ እንዳወሳልን ሁሉ ፣ ሌላ ኃቀኛ ነብልፅግና የውሥጥ ሰው ፣ የማናውቀውን የብልፅግናንን ገመና በማሥጣት እውነታው ይኼ ነበር ሊለን ይችላል ። ዕድሜ ከሰጠን “ ወይ ጉድ ! “እያልን “ ለካ እንዲህ ነበር ! ይገርማል ! “ እያልን የቁልቁለት ጉዘውን በመገረም እናነብ ይሆናል ። እሥከዛው ግን እያንዳንዱ አገር ወዳድ ይኽ አውዳሚ ና እድገታችንን ገች የጥላቻ የቀለበት ጉዞ ለምን ተደጋገመ ? ብሎ በመጠየቅ ከዚህ አሣፋሪ የሞኝ ጉዞ ለመውጣት የሚያሥችለንን የአንድነት ፣ የትብብር ፣ የፍቅር ፣ የእኩልነት ፣ የነፃነት ፣ የፍትህ መንገድን ለመገንባት የሚረዳ ጠንካራ ሐሳብ ሊያዋጣና ለተግባራዊነቱም ተሣትፎ ሊያደርግ ይገባዋል ። ያ መፅሐፍ ላይፃፍም ይችላልና !
በነገራችን ላይ ፣ ከቀኃሥ በኋለ ፣ ዘረኝነትን ከመለሥ ዜናዊ አገዛዝ ጀምሮ መንገሱ ይታወቃል ። ነጭ እባቦች ና ግብረ አበሮቻቸው ምን ያህል በኢትዮጵያ ጓዳ “ ሽር ብትን “ ፣ እንደሚሉ ጥቂት የማይባል አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በቅጡ ታዝቧል ። እነዚህ በህቡ የሚያሤሩ ፣ በሲአይ ኤ እና በሞሳድ ሠላዮች የሚጠቀሙ ፤ የምንተራረድበትን ቢላ አቀባዮች ዘሬም እንዳልተኙልን ማሥተዋል ከብልፅግና የቁልቁለት ጉዞ አደጋ ሊያድነን እንደሚችል መገንዘቡ መልካም ነው ። በመንግሥት እና በኃይማኖት ውሥጥ ተወሽቀው ፤ “ ህሊና ቢሦቹ እብዶች “ በረቀቀ መንገድ በየቀኑ የሞት ሤራ እንደሚደግሱልን ማወቅ ፣ ራሳችንን እና አገራችንን ከጥፋት ለመታደግ እንደሚረዳን ከወዲሂ መገንዘብ መልካም ነው ። ቢያንስ በሚሰጡን አውዳሚ አጀንዳ ላለመጠመድ የጠላቶቻችንን ተንኮል ዘሬ ላይ ማወቅ ይበጀናል ።
የዛረው የፖለቲካ መንገዳችን በራሱ ፣ በህዝብ ሥም ለጥቂት ጥቅመኛ ቡድን አምበሎች ” በገፍ ” የሚያሳብድ የደም ገንዘብ አቀባይ መሆኑንን ማወቃችንም በሥሜት ፣ ግለሰባዊ ፍረጃ ከማድረግ እንድንቆጠብ አድርጎናል ። ሥለ ማህበራዊ ኑሮ ና ሥለፖለቲካ ያለን ግንዛቤ ማደጉም በእጅጉ ጠቅሞናል ።
ማህበራዊ ኑሮ ልክ እንደ ሸማኔ ድር ያቆላለፈን እና ምንም ቢመጣ የማይለያየን እሥከ መቃብር ድረሥ የሚያቆራኘን ነው ። ቀብራችን እንኳን ከማህበራዊ ኑሯችን ጋር የተሣሠሰረ ነው ።
ፖለቲካ ደግሞ በመንግሥት እና በዜጎች መካከል ዘወትር የሚከናወን ዕለታዊ ድርጊት መሆኑን ተገንዝበናል ። ፖለቲካ ፣ የዜጎችና የመንግሥት ኮንትራት ሆኖ ሣለ ፣ የሁለቱ በህግ ላይ የተመሠረተ ጨዋታ ሆኖ ሣለ ፣ ፖለቲካውን ያለሣይንሱ ከህዝብ ለመነጠል “ በአያገባንም ! አይመለከተንም ! ወዘተ ። “ መሸወጃ ቃላት ማለፍም አይቻልም ። ኃይሌን ና መንጌን ፣ ወያኔ / ኢህአዴግንም ያንኮታኮተው ፖለቲከ እንደሆነ እናውቃለን ።
ዛሬ በገሃድ የሚታየውን ፣ በግልፅ እየተፈፀመ ያለውን ፤ ፖለቲካው ሸፍጥ ለመሸፋፈን መሞከር ፣ ከቶም ከዜጎች ጋር የሚያኗኑር አይደለም ። በዜጎች እና በመንግሥት መካከል የሚደረገውን ፖለቲካዊ ጫወታም “ ፌር “ አያደርገውም ። “ የፖለቲካውን የፊር ፕሌይ ህጎችን መንግሥት በውል የሚያቃቸው ይመሥለኛል ። “
ፍትህ ፣ እኩልነት ፣ ነፃነት ዋናዎቹ የህዝብ አሥተዳደር አመራር ፤ የመንግሥት ና የህዝብ የፖለቲካ ጫወታ ህጎች ናቸው ። እናም ማንኛውም ዜጋ ፣ አዲስ አበባ ኖረ ጋምቤላ በአንደበቱ የመናገር ነፃነት አለው ። ሃሳቡንም በፅሑፍ የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው ። ገዢው ፖርቲ ብልፅግና ከፋውም ደስ አለውም ፤ በህሊናው ውሥጥ የሚተራመሠውን ፣ ለህዝብ ና ለሀገር ይበጃል የሚለውን ሐሳብ ይዞ ወደ መቃብር ከመውረድ ይልቅ እያንዳንዱ ዜጋ ፣ ሃቅን ተናግሮ የመሸበት ማደር ከፈለገ መብቱ ነው ። በአፍሪካ መቼም እውነት የሚናገር አዳሩ የት እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም ይኽንንም ለአርነት ብሎ መቀበሉ ወደ ፅድቅ የሚያደርስ መንገድ ነው ።
ከዘህ እውነት አንፃር ፣ “ የጠቅላይ ሚኒሥቴር አብይ አህመድን ( ዶ/ር ) ፣ ሥህተት መፃፍ የምትችለው አብይ ከህመድ ከሞተ ወይም ከሥልጣን ከወረደ በኋላ ነው ። ከሞተ በኋላ እንጂ በቁሙ ልትወቅሰው ፣ ልትሄይሰው አትችልም ። “ በማለት ፣ የዜጎችን አፍ በጠመንጃ ኃይል መዝጋት ማንም አይችልም ። የህዝብን አንደበት መዝጋት እንዴት ይቻላል ???
ይኽንን ተፈጥሯዊ የንግግር መብት ፣ ማፈን ከቶም አይቻልም ። መንግሥትን የቋቋመው ህዝብ እኮ ነው ። “ ኑሮዬን አጣፍጥለኝ ፤ በወጉ አሥተዳድረኝ ፤ ሰባዊ መብቴ ና ህልውናዬን በተገቢው ሁኔታ እንዲጠበቅ ፣ በሃቅ የማያገለግሉኝን ተቋማት ገንባልኝ ። መሠረታዊ ፍላጎቶቼ እንዲሞሉ ለማድረግ ፣ የሀብት ክፍፍሉን ሚዛናዊ ና ፍትሃዊ አድርግልኝ ። ወዘተ ። “ በማለት ፣ ለዚህ የሰዎች ስብስብ የኮንትራት ውል የሰጠው ህዝብ ነው ።
መንግሥት የሰው ስብስብ መሆኑ በውል መታወቅ ይኖርበታል ። መንግሥት ተሰደብኩ ብሎ ዜጎችን ሊያንገላታ ፣ሊያሰቃይና ፣ ሊገድል ከሞከረ ፣ ይኽ መንግሥት ፣ በፍትህ ፣ በእኩልነት ፣ በነፃነት ና በዴሞክራሲ አያምንም ማለት ነው ። ራሱንም ንጉሥና አገዛዙም ንጉሳዊ መሆኑንን በተግባሩ አረጋግጦል ማለት ነው ። እንደ ሠለሞናዊ ዘር ፣ ከእግዜር በታች እኔ ነኝ በህይወታችሁ ጭምር ፈላጭ ና ቆራጩ ፣ “ ህዝቦች ፣ ብሔር ብሔረሰቦች “ ከእኔ በታች ናችሁ በይ መሆኑንን በአምባገነንነት በሚፈፅመው እኩይ ተግባሩ ካጋገጠልን ፣ “ አውጣን ! “ ብለን ወደ ፈጣሪ ከመጮኽ ውጪ ምን እናደርጋለን ??? …
( ሌሎች የክልል መንግሥታትም “ እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ ። “ ካሉ ያው ግብዞች ናቸውና “ አሥቀድማችሁ ከፈሪሣዊያን እርሾ ተጠበቁ ፣ እርሱም ግብዝነት ነው ።… “ በማለት የሉቃስን ምክር ከወንጌል በመጥቀስ እንሆ በረከት እንላቸዋለን ። )
ግን ፣ ግን ፣ ገዢው ፖርቲ ብልፅግና ፣ ዜጎች በየቤታቸው ጓዳ ፣ እኔ ከምፅፈው እውነት በአሥር እጥፍ በሚያሥከነዳ መልኩ ፣ በየክልሉ የሚሥተዋለውን የሹማምንቱና እና የባለሥልጣናቱን አሥጠሊ ገበና እያነሱ ፣ እንደሚወያዩበት መገንዘብ መንግሥትን ከቁልቁለት ጉዞው በመግታት ፣ ቶሎ ወደ ቀልቡ እንዲመለሥ በማድረግ ከውድቀት እንደሚታደገው አምናለሁ ።
ግን ፣ ግን ፣ እንዲህ በአጭር ጊዜ መንግሥት ያወራውን መልካም ነገር ሁሉ እንዴት ሊዘነጋው ቻለ ? እንዴት ? መንግሥትን ያህል አገር አሥተዳዳሪ ፣ እንደ አንድ ህሊናውን እንዳጣ ምንግዴ አባወራ “ በልጅ ቆዳ የተቀበረ የለም ። “ በሚል የግብዞች ተረት ፣ የቁልቁለት ጉዞን እንዴት በአራት ዓመት ውሥጥ ሊጀምር ቻለ ? ለዓመታት የገነባውን ቤተሰብ በአንድ ቀን ውሥጥ ፣ ለውድቀት እንደሚዳርገው አባወራ መሆንን ለምን መረጠ ? ይኽንን ጥያቄ ለመመለስ ፤ መንግሥት ፣ ሣይረፍድበት ፣ ቆም ብሎ ብቻ ሣይሆን ፣ ቁጭ ብሎ ፣ ተረጋግቶ ፣ በሠከነ መንፈሥ ከራሱ ጋር ቢመክር መልካም ነው ። በአደባባይ ባለሥልጣኖቼ ተሰደቡብኝ በማለት አካኪ ዘራፍ ከማሐት ይልቅ ፣ ጅምር የቁልቁለት ጉዞውን መፈተሽና ማሥተካከል ለአገርም ሆነ ለራሱ ለብልፅግና የሚበጅ ይመሥለኛል ። ( በአማራ ምክር ቤት የታየው እውነትን መሻት ፣ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያሥደነቀ ነው ። ደጋግሜ እንዳልኩት የብልፅግና አዲስ ወይን ጠጅ የተከተተው በአሮጌ አቁማዳ ውሥጥ ነው ፤ እንሆ በ11ኛው ሰዓት ወደ ቀልቡ ተመልሶ ፣ አዲስ አቁማዳ ለአዲሱ ወይን ጠጅ እሥካላገኘለት ጊዜ ድረሥ ወይኑንን የያዘው አሮጌ አቁማዳ መፈንዳቱ አይቀርም … )
በነገራችን ላይ ፣ ስድብ እንደ ተግፃሥ የሚቆጠርበት ሁኔታም እንዳለ ማወቅ መልካም ነው ። ንጉሥ ምኒልክ ለምጣም መሆኑ ፤ ጠ/ሚ መለሥም መላጣ መሆኑ የታወቀ ነው ። ( ለምን የቀድሞውን ጠቅላይ ፣ አንተ ትላለህ ? ካልከኝ ፣ ፈጣሪዬንም “ አንተ “ ሥለምል አታካብድ እልሃለሁ ። ) እናም ፣ ዜጎች በአደባባይ መለሥን መላጣ ሥላሉ እውነትን ጮክ ብለው ሥለተናገሩ በዘመኑ ያሰራቸው አልነበረም ። ( በፖርላማ እነ ቡልቻ ፣ መራራ ፣ ሻለቃ አድማሴ ፣ ራሱ መለሥ ተገቢ ያልሀነ ንግግር ይናገሩ እንደነበርም አትዘንጋ ። የቅርቡን የነጃዋር የየቴሌቪዢኑ ዲስኩርን በአናቱ ጨምርበት ። ) ዛሬ ግን ከነሱ ያነሰ መልዕክት የአዲሥ አበባ ወጣት በማሰማቱ ለእሥር ተዳርጓል ። ( ድሬደዋ ሄደህ “….” ተብለህ ብትሰደብ በሥልጣንህ ተመክተህ ምን ልታደርግ ነው ? … ) ህዝብ በአጋጣሚ በጎዳ የሚነገረውን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ፣ በአደባባይ እንደሚናገር አትዘንጋ ! አጭር ትውሥታ ከሌለን በሥተቀር ለቲም ለማ ፣ ለአብይ ና ለደቀመዘሙሮቹ ከአሣምነው ፅጌ ጀምሮ በአደባባይ ፣ መወድስ ቀርቦ ነበር ። ዛሬ ደግሞ አብይ መራሹ ብልፅግና ከዴሞክራሲና ከአገር ሉአላዊነት አንፃር ፣ የቁልቁለት ጉዞ በመጀመሩ እርግማን እየወረደበት ነው ። ህዝቡ ግራ መጋባቱን በወጣቶቹ አማካኝነት መግለፁ ምን ክፋት አለው ? ከላይ ለመግፅ እንደሞከርኩት ፣ በየቤቱ ጎዳ ሲነገር የሰማውን ነው ወጣቱ በአደባባይ የተናገረው … እናም “ ለምን ይህንን የጎዳ የአዲስ አበቤን የነጋ ጠባ መወያያ አጀንዳ ፤ ልጆቹ በሠገነት ላይ ወጥተው ተነገሩ ? “ በማለት ያልተገባ ዱላ መሰንዘር ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ፣ በሺ የሚቆጠር አዲሥ ጠላት መግዛትም ነውና ሊታረም ይገባዋል ። ። እንዲህ አይነቱ ክሥተት ተረጋግቶ ፣ ጉዳዩን ወደራሥ ጥፋት ወሥዶ እንደ ህዝብ አሥተዳዳሪ ፣ ቁጭ ብሎ ፣ ተረጋግቶ ፣ ከራሥ ጋራ በብርቱ ተማክሮ ፣ በቂ ጥናት አድርጎ ያለሸፍጥ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመሥጠት የሚፈታ እንጂ ፤ “ ምን ያመጣል ?! “ ብሎ ፤ በግብዝነት ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ፣ ወጣትነት በፍላሎት የተሞላ መሆኑንን ባለመገንዘብ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ከእናቶቻቸው ጉያ እየነጠቁ ለእሥር መዳረግ ፣ የቀደመውን የኢሀአዴግ የቁልቁለት ጉዞ መድገም ነው ።
ዛሬ እና አሁን ብልፅግና የቁልቁለት ጉዞ ጀምሯል ። ይኽንን የምንገነዘበውም እያንዳንዱ በደም ገንዘብ ያበደ ፣ የዘርና የጎሣ ቡድን አምበል ፣ በሥውር የተቀበለውን ገንዘብ እየረጨ ፣ እዛና እዚህ እሳት ሲለኩሥና ሰላማማዊ ዜጎችን ከመሬት ተነሥቶ ሲያነድ በመመልከታችን ነው ። ይኽንን የእሣት ጫወታ በመሐል አገር ሳይቀር ታዝበናል ። እንቦቃቅላዎች በሣቅ ፣ በጫወታ ላይ እንዳሉ በክላሽ እንደተረፈረፉም በኢቲቪ ዜና ሣይቀር ሰምተናል ። ይኽ የሆነው ለጥፋት የተመቻመቸ ጥርጊያ መንገድ አብይ መራሹ አሥተዳደር ልብ ሣየለው እንዲደላደል በማድረጉ ነው ።የትም የሚታየው ዜጎችን በቋንቋ እየለየ ሥራ የሚሰጥ በዘረኝነት ያበደ ፣ ጥቅመኛ ፣ በሥቁንቁንነት ና በድንቁርና ላይ የተመሠረተ ቡድናዊ አሠራራ እሥካልተወገደ ጊዜ ድረሥ የብልፅግና የቁልቁለት ጉዞ እንደሚቀጥል ፤ ዛሬ እጅግ ተንሰራፍቶ ከምናሥተውለው ግልፅ የዘር መድሎ አሠራር በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን ።
የዘር መድሎው ፣ እጅግ ፅነፍ የወጣ ፣ ጠርዝ ረገጥ ሆኖ በኃይማኖት ውሥጥም ገብቷል ። የቁልቁለት ጉዘው በኃይማኖት ቤት ውሥጥ ያውም በኃይማኖት አባት ተንፀባርቋል ። ከቤተ ክህነቱ ፣ ለመንገጠል ያሰቡትን ፣ በራሳቸው ሥር ያሉትን የእምነቱን አባቶች ሣይገፅሱ “ በመቶሺ የሚቆጠሩ የትግራይ ሴቶች ተደፍረዋል ። “ በማለት ሐሰተኛ የፖሊቲካ ካድሬ ፕሮፖጋንዳ በማራገብ ፣ የመላው ኢ/ ኦ/ቤ አባትነታቸውን ክደው ፣ የአንድ ዘረኛ ፓርቲ ተጠሪ የሆኑ መንፈሳዊ አባት እንደሆኑ ራሳቸው መመሥከራቸው ፣ በታሪካችን ትልቁ አሣፋሪ ኃይማኖታዊ ጠባሳ ሆኖ በታሪክ የሚመዘገብ ነው ። ወቅቱ ፈጣሪን የየምንማፀንበት ፣ የፆለትና የምልጃ ወቅት በመሆኑም ለፀያፍ ድርጊታቸው ፈጣሪ ይቅር ይበላቸው ከማለት የተሻለ እኝህን አባት በዘረኝነት በደም የተጨማሐቀ ባህር የሚያወጣ የተሻለ መፍትሄ ልናገኝላቸው አልቻልንም ። …
ዛሬ አለቃቸው እግዜር የሆነው ለሰማይና ለምድሩ የከበዱ ትላልቅ ሰዎች እና የት ይደርሳሉ የተባሉ ፣ የትላንትናዎቹ የለውጥ ኃይሎች ፣ እጅግ በሚያሥጠላውን ፤ በደም የተጨማለቀውን የዘረኝነት ባህር እያቦጫረቁት ነው ።
ሰው ልጅ ፣ በዘረኝነት የደም ባህር ውሥጥ ፣ በተዝናኖት እያቦራጨቀ አልያም በተዝናኖት እየዋኘ ፣ በደም ገነዘብ ሠክሮ ፣ ሰው መሆኑንን ዘንግቶ ፤ ሰውን እንደሰው ያለመቁጠሩ አያሥገርምም ። ሰው ማለት “ ትግሬ ብቻ ነው “ በማለት ለትግራይ ሰው ደረቱን ሲደቃ ፣ ተመሳሳይ ግፍ ለደረሰበት ከሱ ቋንቋ ውጪ ለሚናገረው ሰው ሥቃይና ሞት በደስታ ሰክሮ የሃሴት ዋንጫውን ከፍ አድርጎ በማንሳት ከግብረ አበሮቹ ጋር ሲያጋጭ ሥናሥተውል ፣ ይኽ ሰው በግፍ በተጨፈጨፉት ንፅሐን የደም ባህር ውሥጥ እየዋኘ ነውና ፈጣሪ ይቅር ይበለው ብሎ መፀለይ የአንድ ኃይማኖተኛ ምግባር እንደሆነም እናምናለን ። ከኃይማኖተኛው ህሳቤ ውጪ ሌላ ህጋዊ ህሳቤ እንዳለ ግን መዘንጋት የለበንም ። በአለም ህሊናውን ያጣ ፣ ሞራለ ቢስ ሰው ፣ ሰውን እንደ ሰው ያለመቁጠሩ የሚያሥገርምና የሚያሥደንቅም ባይሆንም ቅሉ… አንዳንድ ግብዝ ሰው ፣ የእኔ ህዝብ ፤ የእኔ ኃይማኖት እያለ ” በሰፊው ህዝብ ሥም ” እንደቀደመው ጊዜ ፣ ቢሸቅጥ ታሪክን ለሚያቅ ህዝብ ከቶም አሥገራሚ አይሆንም ። በህዝብ ሥም መሸቀጥ የተጀመረው እኮ ከቀዳማዋ ኃይለሥላሤ ውድቀት በኋላ ነው ።
ቀኃሥ በፈጣሪ እያመካኙ ነበር የሚሸቅጡት ። በፈጣሪያችን ሥም ሲሸቅጡ በህዝባዊ ማዕበል ተገርስሰው በሳቸው እግር ፣ ማርኪሲስቱ ደርግ ተተካ ። የማርኪሲዝም ሥርዓት ፈጣሪን የካደ ሥርዓት በመሆኑ ህሊናን አቃውሶ ማሳበዱ ብዙም አይገርምም ። በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አይዶሎጂ መሥመር ፣ ላባደራዊ መንግሥት መመሥረትና በማጭድና መዶሻ ታግዞ ብልፅግናንን ማንበር ነበር ። እግዜርን የማያቅየኮሚኒሥት ርዕዮት ነበር ( የማርክሰኢዝምና የሌኒንኢዝም ርእዮት )
በዚህ በ “ ማሌ “ ርእዮት “ አብዮተኞቹ “ ያለህዝብ ቀጥተኛ ውክልና ፣ አንድ ዓይነት ሙያ ያላቸው ፣ ጥቂት ግለሰቦች ተጠራርተው በሰፊው ህዝብ ሥም ሥልጣን ይዘው ሲያበቁ ፣ ሥልጣኑ እየጣማቸው ሲመጣ ሥልጣንን ለማራዘም ሲሉ ሸፍጥ እና “ የፍየል ወጠጤ “ ፉከራና ፍትህን ደፍጣጭ ፣ “ ነፃ እርምጃ “ መውሰድ ጀመሩ ። ከዚህ የታሪክ እውነት አንፃር ፣ “ የደርጉ “ የፖለቲካ ሥርአት ያበደ ነበር ፡፡ ዛሬም ” ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ” እየተባለ ፣ ሰፊው ህዝብ ራሱ ነፃነቱን ያጣል ። ያለፍርድ በፈጣጣ የሰው ህይወት እንደሚገድለው ደርግ ፣ አንድ አንድ ፖለቲከኞችም በህዝብ ስም አጥፊ የሆነውን ፖለቲካ አልሚ እንደሆነ በመስበክ ” ያበደው የዘር ፖለቲካ ” እንዲቀጥል በመሻት ፣ ራሳቸው ተገልለው እየኖሩ ፣ ዜጎች ፤ ከማህበራዊ መሥተጋብር ውጪ ተገልለው በአንድ ደሴት የሚኖሩ ይመሥል ፣ “ ለዚህ ዘር ቆሚያለሁ ፣ የዚህ ጎሣ ወኪል ነኝ ። የእኔ ዘር ብቻ በአዲስ አበባ መንግሥታዊ ሥራ ማግኘት አለበት ። ወዘተ ። “ በማለት ፣ ነጋችንን የሚያጨልም ኢትዮጵያ እንደኢትዮጵያ እንደትቀጥል የማያደርግ ቦንብ በአዳስ አበባ እያጠመዱልን ነው ። እነዚህ ሰዎች እንደ ትላንትናዎቹ የወያኔ አመራሮች ፣ በቆሰለው ፣ በደማው ፣ አይኑ በጠፋው እጁ ፣ እግሩ በተቆረጠው ፣ የኢትዮጵያ ልጅ እያሾፉ ነው ። ምናልባትም በከፍተኛ ብዝበዛ ላይ በመሠማራት ወርቅ ና መአድኑንን በመሸጥ ፣ ዶላርና ፓውንድ በውጪ አገር እያከማቹ ይሆናል ። ማን ያውቃል ?!
እነዚህ ህሊና ቢሶች፤ ዛሬ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም የሚለው የማጭበርበሪያ መንገድን ፣ “ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ፣ ለጎሳችን እና ለቋንቋችን ሥንል ማንኛውንም መስዋትነት እንከፍላለን ። “ በሚል ተክተው ብዝበዛቸውን እያጧጦፉት ነው ። የውሸት ሥብከቱም ተጧጡፏል ። ፖለቲካዊ እብደቱም ተፋፍሞ ቀጥሏል ፡፡ “ ቅንጦት አሥገኚው የጎሣ ፖለቲካ ወይም ሞት ! ” በሚል መፈክርም አገሪቱ እየተናጠች ነው ። አብሶ በአዲስ አበባ ይኽ የዘር ፖለታካ ከፍቶ ይታያል ። ያልተነጣጠለውን ፣ በፍቅር የሚኖረውን ህዝቦ በጣት ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል በመሥጠት ዜጎች የጎሪጥ እንዲተያዪ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው ። በአንዳንድ ፊደራል መሥሪያ ቤት የቅጥር ማሥታወቂያው የግድ ኦሮምኛ ቋንቋ ማወቅ አለብህ ። ይልሃል ። ይኽንን ከፋፋይ የሥራ ህግ የሚያወጣልህ ፣ የሰው ልጅ እኩልነት የማይታየው ፣ በባለአምስት ኮኮብ ላይ ተምነሽናሹ የሚኖረው ፣ በየቀኑ አሮስቶ የሚቀርብለት ፣ አዛኝ ቅቤ አንጓቹ የጊዜው ወይም ተረኛው ፖለቲከኛ ነው ። ይኽ ህሊና ቢሱ ፣ ሆድ ብቻ የሆነ ባለሥልጣን ( የጊዜው ሰው ) እብድ ፣ እብድ እየተጫወተ እንደሆነ ግን አላሥተዋለውም ። ይህንን ፖለቲከኛ ይህ ፀሐፊ እንደ ገለባ ነው የሚቆጥረው ። የኢትዮጵያ ህዝብ እሳት ነው ። ያንቀላፋ መሥሎት በአሉታዊ ሁኔታ እየቆሰቆሰው ነው ። እንዲህ አይነቱ የጥፋት ጫወታ ግን ቢቀርበት ይሻላል ። …
ህሊና ቢሱ ፖለቲከኛ እሳቱን የኢትዮጵያ ህዝብ በመናቅ ከእሳት ጋር እሰጥ አገባ ከጀመሩ ግን ፤ መለሥ ዜናዊ “ ጣት በመቁረጥ “ ፣ በዘግናኝ የማሰቃያ መንገድ ፣ ሊያሥቆመው ያልቻለውን የህዝብ የፍትህ ፣ የእኩልነት ፣ የፃነት ፣ የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ ፣ ዛሬ ብልፅግና በዚሁ መንገድ ሊያፍነው ከቶም አይችልም ። ዜጎችን በቋንቋ በመከፋፈል፣ በአንድ አገር ውሥጥ እየኖሩ ” ይሄ መሬት የዚህ ጎሣ በቻ ነው ፡፡ ያ ደግሞ የአንተ ዘር ብቻ ነው፡፡ ” እያሥባለ ሰውን እና ዜጋን “ፈርጆ” በባላንጣነት እንዲተያይ ማድረጉን ከቀጠለበትም የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞታልና መጨረሻው እንጦረጦስ ይሆናል ፡፡
ይህ በዘር እና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፊደራሊዝም ከሰው ልጅ የዛሬ አኗኗር ጋር ፍፁም የሚቃረን እንደሆነም አላሥተዋለምና ወደ ቀልቡ ተመልሶ መንገዱን ካልመረመረ ውድቀቱ እጅግ የከፋ ይሆናል ።
ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ ለለውጥ በእጅጉ ያነሳሳንን ፣ ከፋፋይ የተገንጣይ አስተሳሰብን ዛሬም ማራመድ ለኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ አይበጅም ፡፡ የዘር እና የቋንቋ ፖለቲካዊ አሥተዳደር ፣ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጋጭ ነው ። እያንዳንዱ ክልል በተከለለት ክልል ሳቢያ ራሱን እንደ አንድ ነፃ አገር የሚቆጥረው በዚህ ያልጠራ ፌደራሊዝም ሰበብ ነው ።
ጥቂት ድሎተኛ ህሊና ቢሥ የክልል እና የፊደራል ሹም ና ፓርቲና ደርጅት መስርቻለሁ ባይ ፣በህዝብ ስም የሚነግድ ሁላ፣ ያለሀፍረት በአደባባይ ውህዱን ኢትዮጵያዊ እንደዜጋ እንደማይቆጥር ይታወቃል ። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ የዛሬ ሰው ውህድ ነው ። ማንም ዛሬ በህይወት ያለ ፣ የነገ አፈሩ ሰው ፣ ዘርህን ቁጠር ቢሉት እስከ አስር ቤት በትክክል ለመጥራት አይችልም ።
እርግጥ ነው ይህ ዘር ቆጠራ ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላ መሆኑን እነዚህ እብድ ፖለቲከኞች አይገነዘቡም፡፡ አንዳንዶቹማ ኃይማኖተኛ ነን ቢሉም እንደሚሞቱ እንኳ ፈፅሞ የዘነጉ ናቸው ፡፡ ጭፍን ደጋፊያቸውም በየእምነቱ ሲታይ ኃይማኖተኛ ይመስላል እንጂ ፈፅሞ በፈጣሪ እንደማያምን የጥላቻ ተግባሩ ያሳብቅበታል ፡፡ ሁሌም ለሥጋው ጥቅም ብቻ ነው ጥላቻን ሰንቆ ሆዱን ለመሙላት ብቻ ሲባዝን የሚታየው ።…
ዛሬ ፣ ዛሬ የሚታይ እምነት በታላላቅ የኃይማኖት ሊቃውንት ዘንድ እየደበዘዘ ነው ፡፡ ኃይማነተኞቹ ለሰማይ አባታቸው ከመገዛት ይልቅ የፖለቲከኞች ተገዢ ሆነዋል ። በሚያደርጉት ሰውን በዘር የመከፋፈል እኩይ ድርጊትም ፈፅሞ እምነት እንደሌላቸው እያረጋገጥን ነው ፡፡
እምነት ቢኖራቸውማ ” ኢትዮጵያ አገሬ ናት ። ” ብሎ ፣ በዜግነቱ ኮርቶ የሚኖረውን ዜጋ ፣ በህሊና ቢስነት ” በነፍሥህ ጭምር የማዘው እኔ ነኝ።” በማለት ፣ ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ና ህጋዊ መብቱን በየክልሎቹ ፖለቲከኞች ሲገፈፍ እና እንደውሻ በየሜዳው ሲደፋ ዝምታን አይመርጡም ነበር ።
ዛሬ በምእራብ ወለጋ ፣ በምሥራቅ ና ምእራብ ሸዋ ፣ በደቡብ ፣ በቤንሻጉል ፣ በትግራይ አጎራባች ክልሎች ሁሉ እየተፈፀመ ያለው በሰው ዘር ላይ የሚፈፀምና እየተፈፀመ ያለ አረመኔያዊ ድርጊት ነው ። በዘረኝነት ከባ ውሥጥ ግለሰቦች ተደብቀው በቅጥረኝነት እየፈፀሙት ና እያሥፈፀሙት ያሉት የአሸባሪነት ድርጊት ነው ።
ከየአካባቢው የክልሉ የመሥተዳድርና የፀጥታ አካላት ይህንን እኩይ ድርጊት ለማሥቆም ያልቻሉት ለምንድነው ? ተብሎ ቢጠየቅ ፣ ምላሹ ፣ “ የዘር ፖለታካ እጅና እግራቸውን ሥላሰራቸው ነው ። ደግሞም ሥለነፃነት ፣ እኩልነት ና ፍትህ በቂ እውቀት ኖሮት ፣ ዜጎችን በእኩልነት የሚያገለግል ፖሊሥ እና የፀጥታ ኃይል በየትኛውም ክልል ባለመኖሩ ነው ። ሙያውን በውል የሚያውቅ እውነተኛ ፖሊስ ፣ እውነተኛ የፀጥታ አሥከባሪ በየክልሉ የለም ። ለህግና ለህግ ተገዢ ፣ ፍትህን የሚያሰፍን የፀጥታ ኃይል ሳይሆን ፣ የፖለቲካውን ትኩሳት እያየ ለእንጀራው ሲል ከፖለቲካው የዛሬ እውነት ጋር ወግኖ በየዕለቱ እርምጃውን የሚያሥተካክል ኃይል ነው በየክልሉ ያለው ።
እንዲህ አይነት ፤ ህግን ባለማወቁ በህግ የማይገዛ ኃይል ደግሞ ፤ ለፊደራሉ መንግሥት እጅግ አደገኛ ነው ። የፊደራሉ መንግሥት የተደገሰለትን የጥፋት ድግሥ እንዳለ እንኳን ሣይገነዘብ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ኃይል ያልታሰበ ጥቃት በዘግናኝ ሁኔታ ሊጠፋ ይችላል ። “ ቆም ብሎ ንዋይ ያሳበዳቸውን ጉያው ውሥጥ ያሉ ያራሱን እኩያን በቅጡ መርምሮ እሥካላሶገደና የመለሥ ዜናዊን ጫወታ ከመደገም ካልታቀበ በሥተቀር የቁልቁለት ጉዞው ፍፃሜ አያምርም ። “
ይህንን ተገንዝቦ ፣ ቆም ብሎ ሳይሆን ቁጭ ብሎ ፣ በሠከነ መልኩ ማሰብ የዛሬው የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ለነገ የማያሥቀምጠው ፣ የቤት ሥራው መሆን አለበት ። ራሱንም ሆነ ፣ አገሩን ከውድቀት ለማዳን የሚችልበት አሥራአንደኛው ሰዓት ዛሬ ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጋዜ ይልቅ ፣ ዛሬ የብልፅግና ድራማና የመለሥ ዜናዊ የአንድ ጎሣ ፈላጭ ቆራጭነት ና የአውራ ፓርቲ መንገድ መከተል በቅጡ ገብቶታል ። …
ይህ የመለሥ ዜናዊ መንገድ ፣ ፍቅርን ጠል መንገድ ነው ። ሰው ጠል መንገድ ነው ። ኢትዮጵያን ና ኢትዮጵያዊነትን የሚጠላ በመሆኑ ፣ ሰውን በሌለው የተለየ ዘር ፈርጆ ፣ እንዳይደማመጥ ፣ እንደይፋቀር ፣ እንዳይስማማ በማድረግ የማያባራ እልቂትን ፈጥሮ የሚያጫርሥ መንገድን ቀያሽ ነው ። ህብረት ጠል መንገድ ነው ። የጥላቻን ሰንኮፍ የተሸከመ ጥዩፍ መንገድ ነው ። ይኽ መንገድ ዜጎችን በመከፋፈል ፣ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ተንበርካኪ የሚያደርግ መንገድ በመሆኑ ያልታሰበ መዘዝ ከማሥከተሉ በፊት በአሥቸኳይ ከዚህ አውዳሚ መንገድ ያለ ፍርሃት ከእውነት ፊት ለእውነት ቆመን መታገል ይኖርብናል ።