March 19, 2022
15 mins read

ሰው ሆይ! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ ([email protected])

መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን” ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና አይምሮን ተጠቅሞ የሃይማኖቱን ምስጢር ይመረምር ዘንድ “ሰው ሆይ!!” ሲሉ ዛሬም ይማጸናሉ፡፡

እንኳን ኮምፒዩተር ጥንታዊው ታይፕ ማድረጊያም እምብዛም ባልነበረበት ዘመን በበብዕር መድሎተ አሚንን የመሳሰሉ መጻሕፍትና ታሪካዊ የመንፈሳዊና የአካላዊ አርበኝነት አሻራ ትተው ያለፉ ሰዎች ልሳኖች ስለማይዘጉ የመልአከ አድማሱ ጀምበሬ መንፈስና አንደበቶች ዛሬም “ሰው ሆይ!” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ሰው ሆይ! ያለንበት ዘመን እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ ከተጸጸተበት የኖህ ዘመንም የከፋ ይመስላል፡፡ ዘፍጥረት 6፡5-7 እንደሚያስተምረው “እግዚአብሔርም የሰውን ክፋት በምድር ላይ እንደበዛ፣ የልቡ አሳብ፣ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ፡፡ እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ፡፡” ይላል፡፡  በእውነቱ በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች ክፋት በኖህ ዘመን ከነበሩት ክፋት በሺህ እጥፍ ሳይበዛ ይቀራል?

እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች እግዚአብሔር “በአንድ አምላክ አምልክ፤ አምላክህ እኔ ነኝ፡፡ ከኔ በቀር ሌሎች አማልክት አታምልክ” የሚለውን ሽረን አምላኮቻችንን ገንዘብና ስልጣን አድርገናል፡፡ ገንዘብና ስልጣን አምላኮቻችን ስለሆኑም ሳጥናኤል በእነዚህ መቅቡጦቹ እየደለለ የእርሱን እርኩስ ፍላጎት እንድንፈጥም ይገፋፋናል፡፡

ከስልጣን ኮርቻ ለመንጠልጠልና ገንዘብ ለማካበት ሕዝብን እንፈጃለን፣ እናስፈጃለን፣ እናፋጃለን፡፡ ተስልጣን ለመውጣት በለስ ያልቀናንም ፍርፋሪ ለመልቀም ሕዝብ ፈጅና አስፈጅ ባለስልጣኖችን ተእግራቸው ሥር ወድቀን እንደ ቃልቻ እናመልካለን፡፡ ለገንዘብ ወይም ለሆዳችን ስንል በሌላው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በወላጅ፣ በልጅ፣ በወንድም፤ በእህትንና በጓደኛ እሬሳም ሳይሰገጥጠን እንረማመዳለን፡፡

የገንዘብ ውቃቢ ተማምለካችን የተነሳ በተራበና በታርዘ ሕዝብ ሥም ብር፣ ዩሮ፣ ፓውንድና ዶላር ሰብስበን ለራሳችን ቅንጦት እናውላለን፡፡ መለኮትን ገፍትረን ለገንዘብ ጣኦት ከመስገዳችን ብዛት “ለሕዝብ ድርጅቶች፣ ለሕዝብ ልሳን፣ ለልማት፣ ለትምህርት ወዘተርፈ” እያልን የበጎ አድራጊን ሕዝብ ኪስ አውልቀን እንደ ኖህ ቁራ እንጠፋለን፤ ገንዘቡን ቆርጥመን ስንጨርስ ደሞ ዓይናችንን አፍጠንና ምላሳችንን አትብተን ለዳግም ዘረፋ ጆፌውን ገላችንን የእርግብ ላባ አልብሰን እንመለሳለን፡፡

“በባለእንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር ” የሚለውን ቃል ፍቀን የሐሰት ምስክር በ”ፍርድ ቤት” ጓዳ እንደ ትያትረኛ አሰልጥነን በጲላጦስ ችሎት በንፁሐን እናስመሰክራለን፡፡ ለገንዘብ ወይም ለስልጣን ስንል እንደ ይሁዳ የጓደኞቻችንንና የአጋሮቻችንን ጉንጪ “እምጱዋ” አርገን ሥመን አሳልፈን እንሰጣለን፡፡ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ለእውነትና ለህሊናቸው በቆሙ ብሩክ ሰዎች ላይ በሐሰት መስክረን አሳስረን ወይም አሰውተን በእነሱ መቃበር ላይ ፎቅ ሰርተን፣ ንብረት አካብተንና ስልጣን አግኝተን ለመኖር እንጥራለን፡፡ የሳጥናኤልን ድምፅ ማጉያ ባትሪ አጉርሰን በጉርብትና፣ በእድር፣ በእቁብ፣ በጋብቻና በሌሎችም ማህበራዊ መረቦች ተሳስሮ የኖረን ሕዝብ በአንደበቱ፣ በሃይማኖቱ፣ በጎጡና በሰፈሩ እየለያዬን እርስ በርሱ ስናናክስና ስናጫርስ እንውላለን፡፡

“አትስረቅ!’ የሚለውን ቃል በላፒስ ፍቀን ሕዝብ በበሽታና በችጋር እያለቀ የሕዝብ ንብረት፤ የአገር ሐብትና ቅርስ ዘርፈን በዓለም ገበያ እየቸበቸብንና ገንዘብ በባንክ እያደለብን ወይም ተመኝታችን ሥር እየቀበርን ሞትን ድል ነስተን ተንደላቀን  ለዘላለም ለመኖር እንወጣጠራለን፡፡ ሰው ሰራሽ ችጋር ባመደየው፣ በሽታ ባሰቃየው፣ በጦርነትና በአረመኔዎች በተፈናቀለ፣ ፍትህ በተራበና ቤተሰቡን ባጣ ሕዝብ ሥም ገንዘብ ሰብሰበን እንደ ጩልሌ ሞጭልፈን ተአገር አገርና ተሆቴል ሆቴል እያማረጥን የቅንጦት ኑሮ እንኖራለን፡፡ ለማኝ ወይም ድሃ ተመቀነቷ ወይም ተቀዳዳ ኪሱ የከፈለውን የቤተ ክርስትያን አስራትም ዘርፈን ለመክበርና በድሎት ለመኖር መነኩሴ፣ ካህንና የበቃ መእመን መስለን በየደብሩና ገዳሙ የተወቀጠ ኑግ እንደ ሸተታት አይጥ እንልከሰከሳለን፡፡

“አትግደል” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ገጥ ቀደን መለኮት በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ጎረቢቱን ጎረቢቱ በቋንቋ ቆንጨራ ወይም በካራ እንዲያርድ የሰይጣን ጥሩንባ ይዘን እንቀሰቅሳለን፡፡ ነፍሰ ገዳይን ነፃ ለቀን እንዲያውም በእጅ የማይነሳ ሹመት ሰጥተን አትገደል ያለን ወይም ገዳዩን ያጋለጠን እናስራለን ወይም እናሰድዳለን፡፡ ይቅርታ የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ለስልጣን ማደላደያና ለገንዘብ ማግበስበሻ በመጠቀም ሕዝብ የጨፈጨፈን ወይም ያስጨፈጨፈን ነፍሰ ገዳይ ያለ ንስሃ፣ ሱባዔና ፍትህ በይቅርታ ሥም ለቀን መቃብር በገባ ሰማእታት ሥጋ ውስጥ ስራችንን ሰደን እንደ ባድማ ሙጃ ለማገፍገፍ፣ በነፍሳቸውም እቃ እቃ ጨዋታ ለመጫወት እንደፍራለን፡፡ “እስተንፋስ ያለው ሁሉ ይጩህ” የሚለውን የመለኮት ቃል ተከትለው በሰማእታት ስም ለፍትህና ለእውነት የጮሁትን እንደ እስጢፋኖስና ሳሙኤል አወቀ በድንጋይ እንወግራለን፣ እንደ ቅዱስ ጳውሎስና ጴጥሮስም ዘቅዝቀን እንገርፋለን፡፡

ሰው ሆይ! እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች ክፋታችን በምድር ላይ በዝቷል፤ የልባችን አሳብ፣ ምኞታችንም ክፋት ሆኗል፡፡ መለኮት በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው በአንደበት፣ በእምነት፣ በመንደርና በሌሎችም የሚያናክሱ የሰይጣን መሳሪያዎች ከፋፍለን አፋጅተናል፡፡ ዓለምንና ሰይጣንን ወደን መለኮትን ክደናል፡፡ ሞትን እረስተናል፡፡ ቀኑ መሽቶ በነጋ ቁጥር ወደ ሞት እየሄድን፤ የሞት ገደልም እየቀረበን የሚሄድ መሆኑን የገንዘብ፣ የስልጣንና የሌሎችም ምድራዊ ጥቅማጥቅሞች ሞራ ዓይናችንን ሸፍኖታል፡፡ ዘርፈን፣ አጪበርብረን፣ እርስ በርሱ በድድ አናክሰንና በችጋር አመድይተንና በበሽታ አስለክፈን በገደልነው ሕዝብ መቃብር ውስጥ የምንገባ መሆናችንን ዘንግተናል፡፡ በልሳንና በሃይማኖት ገጀራ አርደን ወይም አሳርደን ደሙን ባፈሰስነው ሕዝብ መቃብር ውስጥ እኛም ነገ ተጋድመን ምስጥና ጉንዳን የሚውጠን ከንቱ ፍጡሮች መሆናችንን ማስተዋል ተስኖናል፡፡

ሰው ሆይ! ተፊታችን የቆመውን ነገ የምንገባበትን መቃብር ለማየት ታውረን ከአውሬ በከፋው ባህሪያችን በራሳችንና በመለኮት አምሳል የተሰራን የሰው ዘር እየፈጀንና እያስፈጀን እግዚአብሔርን ዳገመኛ ሰውን በመፍጠሩ ከማጸጸት ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡ በመለኮት አምሳል የተሰራ ሰው ማለትም አእምሮውን ለመንፈስ ልዕልና፣ ለህሊናና ለሃይማኖት ሚዛንነት የሚጠቀም ለእውነትና ለፍትህ የቆመ መሆኑን መገንዘብ ተስኖናል፡፡ ከእውነትና ከፍትህ ያፈነገጠን እርጉም እግዚአብሔር በአምሳሉ እንደሰራው መቁጠር ህፀፅ መሆኑን ማጤን አልሻ ብለናል፡፡

ሰው ሆይ! የሚዛን ትርጉምም እውነትን ተውሸት፣ ፍሬን ተገለባ፣ ብርሃንን ተጨለማ፣ የመለኮትን ባህሪ ተሳጥናኤል ድንበር የለሽ ቅንዝንዝ ፍላጎት የሚለይ በእግዚአብሔር አምሳል የተሰራ ሰው መለኪያ መሆንኑን ማመን ትተናል፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል የተሰራ ሰው ሚዛን በእነ ኤፍሬም ይስሃቅ ስንኩል እጅ ተሚንጠለጠለው የምእራባው የጥቅም ማስጠበቂያ ሰባራ ሚዛን ወይም ድርድር (mediation) እጅግ የተለየ መሆኑን መረዳት ተስኖናል፡፡

ሰው ሆይ!  በእግዚአብሔር አምሳል የተሰራ ሰው እውነትን ተአፈር እንደወጣ ወርቅ አጥቦ ተውሸት የሚለይ፣ የገንዘብና የስልጣን ጣኦት የማያመልክ፣ ባለእንጀራውንም ሆነ ሕዝብን መንጠላጠያ ታደረገ በኋላ እንደ ይሁዳ የማይክድ ወይም ቃሉን እንደ ቆሎ ቆርጥሞ የማይበላ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል የተሰራ ሰው መለኮት በአምሳሉ የሰራውን ሕዝብ በጭካኔ የማይገፋና የማያጠፋ፣ በጆሮው ውሸትን ሰምቶ የማያምን፣ በእጁ የማይሰርቅ፣ በምላሱ የማያታልል፣ በዓይኑ የሌላውን ንብረት የማይመኝ መሆኑን ማመን ይኖርብናል፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል የተሰራ ሰው በምዳራዊ አጭር ህይወት ተቀይዶ ዘላለማዊ የሰማይ ህይወቱን እንደ ተነቀለ አረም የማያበሰብስ፣ ሊፋቅ የማይችል ታሪክንና ተከታታይ ትውልድንም ተአዛባ እንደወደቀ ልብስ የማያቆሽሽ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሰለዚህ ሰው ሆይ! ነገ እንደጤዛ የሚረግፈውን ይኸንን ሰፍሳፋ ገላችንን በሳጥናኤል ፍላጎቶች ለማርካት ስንክለፈለፍና ስንሽሎኮሎክ እግዚአብሔርን እንደገና እኛን በመፍጠሩ እንዳናጸጽተው በየደቂቃው ህሊናችችንን መኮርኮርና ግብራችንንም  መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ አሜን፡፡

 

መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አራት  ዓ..

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop