መሪዎች በድግስ የሚምነሸነሹባት፤ ሕዝብ በርሃብ፣ በጦርነት፣ በስደትና በኑሮ ውድነት የሚለበለብባ አገር፤ ኢትዮጵያ።
ቅዱስ መጽሐፍ ላይ “የግፉአን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው!” ይላል። አዎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፉአን ናቸው። የመጣ፣ የሄደው ሁሉ እስከሚችለው ጥግ የሚገፋው፣ የሚደፋው፣ የሚዘርፈው፣ የሚያዋርደው፣ የሚያረክሰው፣ እርስ በርሱ የሚያባላው፣ የሚበላው። ግን ጊዜውን ጠብቆ ግፈኞችን ወደ ጥልቁ ጉርጓድ የመጨመር አቅምም ያለው ተአምረኛ ሕዝብ ነው። ከቅርብ ትውስታችን፤ ወያኔ የገባችበትን ጥልቅ ጎርጓድ ልብ ይለዋል። ችግሩ ግፈኞች አይማሩም። ግፋአንም አያስተምሩም። አድፍጠው ይቆዮና ግፈኞችን ይውጣሉ እንጂ። አዙሪቱ የሚቀጥለውም ለዛ መሰለኝ።
የኢህአዴግ የበኩር ልጅ የሆነው ብልጽግና ከፈጠረው ድርጅት የሚብሰው ለድግስና ለገጽታ ግንባታ የሚሰጠው ትኩረት ነው። ሕዝብ ቢራብ፣ ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለው ያለመጠለያ በየሜዳው ቢወድቁ፣ የኑሮው ውድነት በፈጠረው ማህበራዊ ቀውስ ሕዝብ ቢራቆት፣ ቢጠማ ከብልጽግና ደጃፍ መሪዎቹን የሚያረሰርስ ድግስ፣ ፈንጠዝያ፣ እርስ በርስ መሸላለም፣ መወዳደስ፣ መሽቀርቀር ግን አይነጥፍም። ይሸታል ዶሮ ዶሮ፣ ይሸታል ጠጅ ጠጅ … ከብልጽግና ደጅ።
ምክር፤ ምክር ለማትሰሙት ገዥዎቻችን
– እጃችው ላይ የወደቀችው ኢትዮጵያ እናንተ እና የትላንት ባልንጀሮቻችሁ ወያኔዎች ጋር መግባባት አቅቷችሁ በከፈታችሁት ጦርነት ሳቢያ ክፋኛ ተጎድታለች። ጦርነቱ አገሪቱን ብዙ አመት ወደኋላ መልሷታል። ተቋማቶች ፈርሰዋል፣ ትግራይ de facto state ሆናለች፣ ትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልል በጦርነቱ ደቀዋል፣ ኦሮሚያ በሽኔ ጦር ተወጥራለች፣ ቤኒሻንጉል የማያባራ ቀውስ ውስጥ ገብቷል።
– እናንተ እና የወያኔ ሹሞች ተዛዝታችሁ ይዋጣልን ብላችሁ በገባችሁበት ጦርነት ምኑንም የማያውቁ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የድሀ ልጆችን ገብራችሁ እናንተ እንዳማረባችሁ በመንበራችሁ ጸንታችኋል።
– በሰላም አርሶ የሚበላውን ሰላም ወዳድ ደሀ ገበሬ ለጦርነት ዳርጋችሁ ብዙ ሺዎች የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል፣ ቤት ንብረቱ ተዘርፏል፣ ገበሬው ተራቁቷል፣ ሚሊዮኖች በጦርነቱ ተፈናቅለው በየሜዳው ወድቀዋል።
– በአገሪቱ የሰሜን ክፍል ብቻ 7 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ የተባበሩት መንግስታት ካስታወቀ ሳምንት አይሞላውም።
– በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል በርካታ አካባቢዎች ታጣቂዎች ሕዝቡን መውጫና መግቢያ ነስተውታል።
– በሱማሌ ክልልና ኦሮሚያ ቦረና አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ ሚሊዮኖች በውሀ እጥረት እየተሰቃዮ እና ከብቶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑን እየተዘገበ ነው።
ይህ ሁሉ በሚሆንበት አገር እናንተ በድግስ ላይ ድግስ፣ ምርቃት፣ ሽልማት እያላችሁ ትምነሸነሻላችሁ። ይህ የጤናም አይመስለኝም። የምትመሩትን ሕዝብ አንድም ንቃችሁታል፤ አለያም ስለነጋችሁ ተስፋ ቆርጣችኋል። በእርግጥ በዚህ ድግስ ላይ በጠቅላዩ ምክር መሰረት ‘ሺፈራሁ’ የተባለውን ቅጠል በፈላ ውሀ ዘፍዝፋችሁ ጨው ጣል አርጋችሁ ከሆነ የምትቋደሱት የሕዝቡን ሰቆቃ በከፊልም ቢሆን እየኖራችሁት መሆኑን ስለሚያሳይ ይህ ቸር ሕዝብ ይራራላችሁ ይሆናል። ግን አይመስለኝም። እንዲያ ከሆነ ዘንዳ እውነት እውነት እላችኋለው ህውሀት ከ27 ዓመት በኋላ ከገባበት ጥልቅ ጉድጓድ ጫፍ ላይ መሆናችሁን ልብ በሉ። የግፉአን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው። የገባ አይወጣም።