አንድ መንግሥት፤ እንደ መንግሥት አገረ መንግሥት የሚያሰኘው ሁሉንም ማሟላት ባይችል እንኳ’ መሰረታዊ የህዝብን ደህንነትና የአገርን ልዕልና ማስከበር ሲችል ነው። ያለያ በተለምዶ የከሸፍ መንግስት (ፌልድ ስቴት) ይባላል። ለዚህ እንደ ምሳሌ ሱማሌ የምትጠቀስ ሲሆን፤ የመን፣ አፍጋኒስታንና ሊቢያ ደግሞ አሁንም በሁለት እግራቸው መቆም ያቃታቸው ሲሆኑ የእኛዋ ኢርትራ ደግሞ በምዕራቡ ዓለም እይታ የከሸፈች ናት። ታዲያ አገሮችን ለመክሸፍ የሚያበቃቸው ዋና ምክንያት ማዕከላዊ መንግስት መዳከምና ህግና-ሥርዓት ሲጠፋ ነው። ከዚህ ላይ መጤን ያለበት የሰው ልጅ መሰረታዊ መብቱ በገዥዎች ተረግጦና ታፍኖ፤ ህዝብ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ከዋለና ያለነጻነት ከተገዛ፤ ብሎም የአገር ሃብትና ገንዘብ የአምባገነኖች የግል ኪስ ከሆነም እንደ ከሸፈ አገር-መንግሥት ይቆጠራል።
በወያኔ-ኢህአዲግ ላይ የተደረተው የኦህዲድ-ብልጽግና ለመሰረታዊ ለውጥ የተደረገውን ትግል ጠልፎ አራት ኪሎን ይቆጣጠር እንጅ፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ አንድ አገረ-መንግሥት፤ መንግሥት የሚያደርገውን አንዱንም አሟልቶ አያውቅም። አገር ማስተዳደር የተሳነውና ራሱን ብልጽግና ብሎ የሚጠረው የጎሳ ስብስብ፤ አሁን ደግሞ ወያኔ የጋጣትንና በጦርነት ያዳከማትን አገር፤ በተረው መጋጡ ሳያንሰው፤ ”ሌባ ሲከፋፈል እንጅ ሲሰርቅ አይጣላም ” እንደሚባለው ሆነና ፤ ፤ ‘ርስ በርሱ እየተባላ ከተደረተበት ወያኔያዊ ስፌት እየተተረተረ፤ በጠ/ሚ የሚሰበኩት የኢትዮጵያዊነት ”ማስክ”’እርቃኑን እየውጣ፤ አገርና ህዝብ ይዞ ሊጠፋ እየተደረደረ ነው።
ዋናው ጥያቄው ግን የኦህዲድዊ ብልጽግና መፈራረስም ሆነ ህግና ስርዓት ማሰከበር አልመቻሉ ፤ እንደ ወያኔ አወዳደቅ ሁሉ፤ ካለፈው በባሰ ዳፋው ለአገርና ለህዝብ እንዳይተረፍና የአገርና የህዝብ አንድነት እንዲቀጥል ማድረጉ ላይ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ሃቁን እንቀበልና፤ አገራችን እንታደግ የምንል ከሆነ ፤ በርግጥም የምንገዛው በከሸፈ የጎሳ ፓለቱካና ተላላኪ ካድሪ ነው። ከከሸፋ ገዥዎች የምንማረው ደግሞ ህዝብን ከፋፍለውና ኃይል አሳጥተው ፤ ከጋጡት የአገር አንጡራ ሃብት የተረፈም ካለ ቋጥረውና ለ’ርስ-በርስ ጦርነት አመቻችተው መሸሽ ነው።
ኦነጋዊ-ኦህዲድ ብልጽግና ከወያኔ ማዕከላዊ አስተዳደሩን ተረከብኩ ካለ ግዜ ጀምሮ፤
1/ ህግና ሥርዓት አለመኖሩ ብቻ አይደልም፡ የሰው ልጅ በማንነቱ እንደ ከብት የሚታረድብተና የሚሳደድበት፤ በየግዜው የዘር-ማጽዳት ወንጀል አስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ የሚፈጸምባት አገር ኢትዮጵያ ነች።
2/ ወያኔ ትግራይን ከማዕከላዊ መንግሥት መገንጠሉ ሳይበቃ፤ እንደ ሚታወቀው ህልቁ መሳፍርት የሌለው እልቂት የተካሄደበት ጦርነት አሁንም መቀጥሉ ብቻ ሳይሆን፤ ወያኔ የበለጠ ተደራጅቶና ታጥቆ መከረኛውን ህዝብ ለመውረር ትእዛዝ እየተጠባበቀ ነው። በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ኦነጋዊ-ብልጽግና የወያኔን ነገር ወደ ጎን ትቶ ትጥቅ በማስፈታትና “ጉባኤ አይሉት ሱባኤ'” ራሱ በሚፈጥረው አጀንዳና አሉባልታ ወሬ ተጠምዷል።
3/ ኦነግ – ሸኔ በኦርሙማ እየተመራ ዜጋን በማንነቱ ከማረድና ከማሳደድ አልፎ፤ የወረዳ ቀበሌዎችን እየተቆጣጠረ ብቻ ሳይሆን፤ ከሽምቅ ተዋጊነት ወደ መደበኛ ተዋጊነት በራሱ በብልጽግና መሪዎች እንዲያድግ ተደርጓል።
4/ የኑሮ ውድነት ጣራ ከመድረሱ የተነሳ ብዙሃኑ ህዝብ ራስን መመገብ ተስኖት በርሃብ አየተሰቃየ ብቻ ሳይሆን፡ በድርቅ እየተመካኘ በተለይም በሱማሊ፣ በቦረ እና እንዲሁም በጉጅ አካባቢዎች የሚላስ የሚቀመስ ከጠፋ ውሎ አድሯል። በጦርነቱ የተፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም መፍትሄ አልተሰጣቸውም።
5/መንግሥት አለበት በሚባልበት የአገር ልዕልና ተደፍሯል፤ ሱዳን ግዛታችን ወራ ከያዘችና የጦር ሰፈር ከመሰረትች ዓመታት አሰቆጠረች።
6/የውጭ ግንኙነታችን ከመበላሸቱና አቅመቢስ ከምሆናችን የተነሳ፤ የምናወጣውና የምንከተለው አገራዊ መርህ፤ ብሎም ከወያኔ ጋር ለሚደረገው ጦርነት በውጭ ሃያላን አገራት ፍላጎትና ጥቅም ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፤ ነገ በአገራችን ምን ሊደረግ እንደሚችል ማወቅ ቀርቶ መገመት አይቻልም።
ከላይ ለማንሳት የሞክርኩት አገራችን ያለችበት ሁኔታ ጸሃይ የሞቀው የየዕለት ኑሯዋችን የአደባባይ ሃቅ ነው። ነገር ግን አሁን-አሁን በህዝብና በአገር ላይ ሊፈጸሙ ወይም ሊሆኑ የማይገባቸው ነገሮች፤ ሲከናወኑ ደጋግመን በማየታችንና በመላመዳችን፤ ከዚህም አልፎ በየቀኑ አዳዲስ አጀንዳ እየተወረወረልን ስንቧጨቅ፤ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባንን ህልውናችን የማስጠብቅ ትግል ዘንግተን፤ ጎሰኝነት አገራችንና አድነታችን እያሳጣን ነው።
በእውነቱ ብልጽግና ”ርስ-በርሱ እየተባላ ያለው ፤ ወያኔንና ኦነግ-ሸኔን በሚመለከት ለህዝብና ለአገር እንደነት በመቆርቆር የተፈጠረ የመርህ ልዮነት ሳይሆን፤ የተረኝነትና ኦነጋዊ -ብልጽግና የወያኔን ቦታ በመወረሱ እንጅ፤ የተደራጀ የፓልቲካ ፓርቲ ወይም ህዝባዊ እንቅስቃሴ አስገድዷቸው አይደልም።
ለኢትዮጵያዊነትና ለአንድነታችን ይቆማሉ ያልናቸው እንደ ኢዜማ ያሉትም “ከዳግማዊ መኢሶን” በባሰ የስልጣን ፍርፋሪው በልጦባቸው ሲያወግዙት በነበረው የጎሳ ፓለቱካ ውስጥ ተቀርቅረው የህዝብን ትግል ለግዜውም ቢሆን አመከኑት።
ራሱን እንኳን መመራት ያቃተውን ኦነጋዊ -ብልጽግና ቢፈራርስ፤ እንደ ትላንቱ እንደ ወያኔ አወዳደቅ ሁሉ አሁንም አንደም ክፍተቱን የሚተካ ኢትዮጵያዊ የተቃውሚ ወይም የህዝብ መሪና የፓለቲካ ድርጅት እለመኖሩ ነው። ይህም ኦነጋዊ-ብልጽግና ሲደናበር፤ የአገር ህልውና በወያኔዎችና በኦነግ-ሸኔዎች እጅ እንድትወድቅ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፤ ሊከተል የሚችለውን የዘር ማጽዳት—-በ”ርግጥም ማሰብ አልፈልግም።
ከሆሆታ፣ ከበለው በለው፣ ከሽለላ፡ ከፍከራና ከቀረርቶ ወጥተን፤ በጎሳና በመንደር መናቆራችን አቁመን ከማንኛውም ግዜ በበለጠ በሰከነ መንፈስ’፤ ከተራ ዜጋ ጀምሮ ለአገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ ነኝ እስከ ሚል ድረስ ቆም ብሎ፤ በአገርና በህዝብ ላይ የተደቀነውን አደጋ ተገንዝቦ ለመፍትሄ መኳተን የእያንዳንዳችን የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል። ምክንያቱ አሁን ያለው አገዛዝ ትላንት ከተነሳበት አንስቶ አሁን እስከ አለበት ደረጃ ያደረግው ጉዞ፤ በአጭር አገላለጽ፤ ራሱ ከሽፎ አገርና ህዝብን እያከሸፈ ነው።
ከራሴ ልጀምርና ፤ ሌላውም ያቅሙን የድርሻውን እንደሚወጣ ተስፋ በማድረግ ፤ እንደ አንድ ዜጋ መፍትሄ የምላትን መናኛ ሃሳብ ልስጥ።
መፍትሄ ብየ በዚህ ሰዓት የማቀርበው ቀጥታ ለጠ/ሚ አብይ አህመድ ነው። ጠ/ ሚኒስትረ ከዚህ በፊት የቀረበላቸውን የሽግግር መንግሥት መመስረት አልተቀበሉትም ፤ አሁንም ይህ ጥሪ ተደርጎላቸው አልተቀበሉትም እንጅ እንደ እኔ ከመላው አገሪቱ በተውጣጡ አባቶችና እውነተኛ ምሁራን፤ ከማንኛውም ወገን ያልሆኑ የባላደራ የሽግግር መንግሥት ቢያቋቁሙ ይመረጥ ነበር። ” አገራዊ ምክክር” የተባለውም ሳይጀመር ተቀባይነት ያጣ ነውና ሳይወለድ ተጨንግፋል።
ስለዚህም ለጠ/ ሚ አብይ አህመድ አሁን ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆን እንደ መፍትሄ ብየ የማቀርብለዎት፤ በኢትዮጵያ ስም ስለ ሚምሉና ስለሚገዘቱ ፤ በዚህም ምክንያቱ ብዙ ዜጎች ስለተወናበዱ እንጅ፤ በወያኔና በኦነግ-ሸኔ ላይ እስከ አሁን ድረስ ባለዎት አቋም አለመሆኑን ማስመር እፈልጋለሁ። እናም፤
1/ በመላው አገሩቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ላልተወሰነ ግዜ ያውጁና ህገ-መንግሥቱን ያግዱ።
2/ ለኢትዮጵያ ህዝብ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ አፍረጥርጠው ሃቁን ይናገሩና ከህዝብ የሚፈልጉትን ይጠይቁ።
3/ በውስጠዎት የተሰገሰጉትን የጎሳ ጥገኛ ባለስልጣኖች በተለይም ኦነግ-ሸኔን የሚያስታጥቁትንና የሚመሩትን በይፋ መንጥረው ያውጡ። በ’ ርግጥ እርሰዎ አፍቅሮ ኦነግ-ሸኔ ከሌለዎት በውስጠዎ ያሉት ኦነጋዊያን ‘ርስዎንም ከሥልጣነዎ ከማባረር ወደ ኋላ አይሉም።
4/ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሰ’ተዎ በወያኔና በኦነግ-ሽኔ ላይ የማያዳግም ‘ርምጃ ይውሰዱ። የትግራይንም ህዝብ ከወያኔ መንጋጋ ያላቁ። ልብ ያድርጉ ‘ርስዎ ከቆረጡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎነዎት ነው። ይኽን ደግሞ በተግባር እፕስመስክሯል።
5/ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ወ’ቶ ፣ ስርቶ፣ መግባቱኑና ደህንነቱን ያረጋግጡለት። እንዲሁም የአገራችን አንድነት በማስከበር በተግባር ያስመስክሩ።
6/ የህዝብን ሰላምና አንድነት ካረጋገጡና ካረጋጉ በኋላ የሽግግር መንግሥት አቋቁመው፤ በህዝብ አዲስ ህግ-መንግሥት አስረቅቀው ያፀድቁ።
ከዚህ ላይ ላረጋግጥለዎት የምፈልገው፤ ራስዎን ከጎሳ ፓለቱካ በተግባር አፅድተው፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እስቀድመው እስከ መሩ ድረስ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር -እስከ ዳር ድጋፍ ማድረግ አይደለም ፤ የህይወት መሰዎአትነም ለመክፈል ዝግጁ ነው። ነገር ግን እንዳለፈው ግዜ ህዝብ የሚፈልገውን እየተናገሩ ፤ በተግባር ግን ተረኝነትን እያነገሱ፤ አሁን ባለው የጎሳ ህገ-መንግሥት እገዛለሁ ብለው ካመኑ፤ “እርመዎትን” ያውጡ። በአጋጣሚም ይሁን በምንም ምክንያት እጀዎ ላይ ያለችውን እናት ኢትዮጵያን እዲታደጓት እግዚአብሔር ይምራዎ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!
——–//———ፊልጶስ
————————-
ንጉሥ ሆይ ፋኖን ማሣደድ ያቁሙ ዕዳው ለርሥዎ ነዉ