አባ መላዎችን ለማብዛት ከፈራን ፣ አባ ዱላዎች እየበዙ ይመጣሉ። ይኽንን ለሰከንድ እንኳን መጠራጠር ታላቅ ጅልነት የወለደው ውድቀት ያስከትላል። ፀሐፊው ቀጥሎ ያለውን ቀጥተኛ እውነት ለመፃፍ የተነሳውም ፤ አባ ዱላዎች ዳግም እያንሰራሩ ሥለመጡና የተከፈተውን የዴሞክራሲ በር ሊዘጉብን ዳር ፣ ዳር ፣ እያሉ መሆኑንን በማስተዋሉ ነው ። ፀሐፊው በማሥተዋል ውሥጥ ሆኖ ” ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሥፈልገው የዱላ ወይሥ የመላ አሥተዳደር ነው ?” ብሎ ይጠይቃል። ጥያቄውንም በተቀዳሚነት በትህትና የሚያቀርበው ለገዢው ለብልፅግና ፓርቲ ነው። ገዢው ብልፅግና የካሮትና የልምጭ ተደጋጋፊ ና ተገቢ የሆነና በዓለም ቅቡልነት ያለው ፤ አሥተዳደርን በወጉ ና በሥርዓቱ በተቋሞቹ አማካኝነት እንዲሥተናገድ ማድረግ ሲገባው ፣ በተቋሞቹ ዳተኝነት ና ሙሥና የተነሳ የህዝቡን እና የአገርን በደል ፣ በፖለቲካ ውሳኔ መሻር ከጀመረ ፤ ” ጥቂት “የማይባል ህዝብ ለመንግሥት ጀርባውን መሥጠቱ አይቀርም ና ገዢው ፓርቲ ይኽንን እውነት በቅጡ ሊረዳ እና ለወደፊቱ ከውሳኔዎቹ በፊት በህዝብና በመንግሥት መሐል ቅራኔ እንዳይከሰት ፣ የብዙሃኑን ህዝብ ፍላጎት ( እውነተኛ ፍትህ መሻቱን…) ቀድሞ መገንዘብ ይኖርበታል ። ህዝብ ዛሬና አሁን ፍትህ ፣ እኩልነት ፣ ነፃነት ፣ መልካም አሥተዳደርና ያለወገነ ንፁህ ዴሞክራሲ ነው የሚፈልገው ። አራት ነጥብ ።
ህዝብ ፍትህ እንደ ሰማይ እየራቀው ከሄደ ፤ ህዝብ እንደ ዜጋ በአገሩ ላይ የመኖር ነፃነቱ ከተገፈፈ ፤ ህዝብ እንደ ዜጋ በየክልሉ በእኩልነት አሥተዳደራዊ አገልግሎት ካላገኘ ፤ ህዝብ በሠላም ወጥቶ መግባት አዳጋች ከሆነበት ፤ ህዝብ ተፈጥሯዊ እና ሰብዓዊ መብቱ ካልተከበረለት ። ወዘተ ። አገራችን ወደ ባሰ ትርምስ ፣ ሁከት ፣ ለቅሶ ና ዋይታ ውሥጥ ልትገባ እንደምትችል ከወዲሁ መገንዘብ ወይም መረዳት ፣ እጅግ አሥፈላጊ ነው ።
ለዚህ ነው ፤ ከዱላ ይልቅ በመላ የተሞላ ፣ የካሮትና የልምጭ አሥተዳደር በአገር ይስፈን የምለው ።የመላ አሥተዳደር ከታች ጀምሮ እሥከላይ ከሰፈነ ፣ በዱላ የሚያምኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ቦታ ሥለማይኖራቸው አገር ከላይ ከጠቀስኳቸው አደጋዎች ትድናለች ብይም አምናለሁ ። በነገሬ ላይ ፣ ” የልምጭና የካሮት አስተዳደር በህግ የበላይነት ላይ መመሥረቱን አትዘንጋ ! ” ለማለት እፈልጋለሁ ። እንኳን መንግሥት ይቅርና መልካም ወላጅ ልምጩን እየደበቀ ልጁን በሥርዓት ማሥተዳደር እንደማይችል በቅጡ ያውቃል ። መብትና ግዴታ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደሆነም ለልጁ የሚያሥተምረው ልጁ ሲያድግ ” ሥድ ” እንዳይሆን ነው ። ” አሳዳጊ የበደለው ። ” ተብሎም እንዳይሰደብ ።
ዛሬ ፣ ዛሬ አሳዳጊ ከበደላቸው ይልቅ የወያኔ ሥርዓት በዘረኝነት ኮትኩቶ ያሳደጋቸው እና የሌላቸውን እውቀት በሥልጣን አማካኝነት ያጎናፀፋቸው ፤ ወይም በወያኔ የሥልጣን አረቄ ያበዱ ሰዎች ፣ እንዳሉ አትዘንጉ ። … እነዚህ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ና ጥቂት የማንላቸው ግለሰቦች ፣ ከ2010 ህዝባዊ ለውጥ ከወለደው ከጠ/ሚ አብይ አህመድ አመለካከትና አስተሳሰብ ጋራ የተቃረኑ ናቸው ። “ያለምንም ደም ኢትዮጵያን ለማበልፀግ ከተወጠነው ለውጥ ጋር አስተሳሰብና አመለካከታቸውን ያላሥተካከሉ ናቸው ። ዛሬ ና አሁን ፣ ከታች እሥከላይ በሥልጣን ላይ ያሉ በእኩልነት ፤ በሰዎች ተፈጥሯዊ አንድነት ፣ በምድራችን ተፈጣሪነትና በራስዎ አንድ ፍጥረትና የሰው ልጅ ያልፈጠራት መሆኗን እሥካላመኑ ጊዜ ድረስ ፣ በአገራችን የተሻለ ና በዓለም ህዝብ ቅቡልነት ያለው ርዕዮት ሊነግሥ አይችልም ።
ታሪክ የሚዘግባቸው መሪዎችም ሆኑ ተራ ሟቹ ፤ መገንዘብ ያለበት ፣ ኢትዮጵያ ውሥጥ የምንኖርና በኢትዮጵያ ምድር የተወለድን ሰዎች ሁሉ ፣ በአጋጣሚ ፣ ኢትዮጵያ ተወለደን የዜግነት መብት በዓለማዊው ሥርዓት ተሰጠን እንጂ ፣ ራሳችን ወደንና ፈቅደን ኢትዮጵያ አልተወለድንም ። ማንም ሰው የአምላክን ሚና የሚጫወት ባለመሆኑ ፍጥረቱ የአጋጣሚ ውጤት ነው ። ( እርግጥ ነው ሰውን እግዜር ፈጥሮታል ። እናም ፣ ሰው ሁሉ የፈጣሪ ውጤት ነው ። ተፈጣሪ ነው ። ፍጡር ነው ። …)
ሁላችንም መረዳት ያለብን ፣ ገና በጨቅላነታችን እራሳችን ወደን እና ፈቅደን ፣ ኦሮምኛ ፣ አማርኛ ፣ ትግሪኛ ፣ ሱማሊኛ ፣ ሲዳምኛ ፣ አኘዋክኛ ፣ ጉምዝኛ ፣ ወላይታኛ ፣ ጋሞኛ ፣ ሽናሽኛ ፣ ከንባትኛ ፣ ኃድይኛ ፣ ቅማንትኛ ፣ ጉራጊኛ ፣ ሥልጢኛ ፣ ወዘተ ። አልተናገርንም ። ሁሉም ነገር ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ነው ። መፀነሳችንም ፤ መወለዳችንም ።…
ከመወለድ ውጪሥስንቶቻችን፣ ሥለትውልድ ሐረጋችን እናውቃለን ? ከ14 ትውልድበኋላ ያለውን የትውልዱን ሐረግ የሚያቅ ካለ ” አለሁ እዚህ ” ይበለን ። ካለ መቼም ይኽ ድንቅ ነገር ይሆናል ። በመፀሐፍ ቅዱስ እንኳን በተመዘገበ ታሪክ የእየሱስ የትውልድ ሐረግ እሥከ 12 ትውልድ ብቻ ነው የሚቆጠረው ።
እኛም የትውልድ ሐረጋችንን እሥከ 14 ትውልድ ድረስ ለመጥራት አንችልም ። ( እንዳልኩት ” እችላለሁ ” የሚል ካለ እሥቲ በሚዲያ ይውጣና ያሥገርመን ። ) ይኽንን እውነት ግን ብዙዎቻችን አንገነዘብም ።
በአገራችን ሰው ሆነንን ሣለ ሰውነታችንን የሚያሥክድ ፣ በማንኛውም ዓለም የሌለ ቋንቋን ምሰሶ ያደረገ ሥርዓት ተተክሏል ። በአገሬ የተተከለው የጎሣ ፣ የነገድ ፣ የዘውግ ፣ የቋንቋ ንግሥና ሥርዓት አገራችንን ከአንዱ ሁከትና ብጥብጥ ወደሌላው ውድመት ፣ ሁከትና ብጥብጥ ከመዶሉ እና በትርምስ ውሥጥ ወደኋላ እንድትራመድ ከማድረግ ውጪ ፣ ለተርተው ህዝብ ያመጣለት አመርቂ ትሩፋት የለም ። በ 27 ዓመት ውሥጥ ከሥርቆት ተርፎ በመላው አገሪቱ ፣ በተለይም በአማራ ፣ በትግራይ ና በአፋር የተገነቡት መሠረተ ልማቶች እንኳ ባለፉት 13 ወራቶች ወድመዋል ። ዛሬም ውድመቱ አላባራም ።
ይህንን ውድመት ለመቀልበሥ እንደሌሎቹ ዘመነኛ አገሮች ፣ ዘመነኛ ርዕዮት ና ዘመነኛ አሥተዳደር በአገራችን መተከል ያሥፈልጋል ። መነቀል ያለበትን ነቅለን ። የብልፅግና ፓርቲም ፣ ከምር ራዕዩ ኢትዮጵያዊያንን ማበልፀግ ከሆነ የዜጋ እኩልነትን ያረጋገጠ ርዕዮትን መመሪያው ማድረግ ይጠበቅበታል ። ( የምክክረ ጉባኤውም የዛሬውን የመላ ዓለምን የመንግሥት ሥርዓት ያገናዘበ ወቅታዊውን የዓለምን የንቃተ ህሊና ደረጃ የተረዳ መሆን ይኖርበታል ። እውነትን የፈራ ሊሆን አይገባውም ። የዓለም የፖለቲካ ሥርዓትን የደፈጠጠ ። በ18 ኛውና በ19 ኛው ክ/ዘ የሚዋኝ ከሆነ ፤ ዛሬም ፣ ነገም ፣ ከነገወዲያ ሥራችን ጥርሥን ማፋጨት ይሆናል ። የምክክር ጉባኤው ፣ ከሥግብግብነት እና ከሥግብግቦች የፀዳ ፤ እንዲሁም በዕውቀት ላይ በተመሠረተ እውነት የተቀነበበ መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ ። )
እንደሚታወቀው ፣ ያለፈው ሥርዓት ና የአሁኑ ሥርዓት ማዋቅር ፣ በፊደራል ደረጃ ቢለወጥም ፣ በክልል ደረጃ ያው ነው ። የኢትዮጵያ የአሥተዳደር ሥርዓት ፣ ከደርግ ጀምሮ ጠርናፊና ” ቀበሌ መር ” (ካቢኔ መር ) መሆኑንን እናውቃለን(የማዘጋጃ ቤት ሥርዓት ፣ በቀኃሥ ጊዜ ነው የቀረው ።) ። ትላንትም ሆነ ዛሬ ቀበሌዎች በማንኛውም ጉዳይ ለህዝባዊ ውይይት የሚያሳትፉት ጥቂት ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ነው። ይኽ መንገድ ትላንትና ኢህአዴገን ጠልፎ እንደጣለውም መዘንጋታቸው ብቻ ነው የሚደንቀኝ ። እንዴት በአጭር ጊዜ ውሥጥ ያንን ህዝባዊ አመፅ ፈፅሞ ለመዘንጋት በቁ ? ? ። ወይሥ ዝንጋታ አይደለም ። እንዲህ ከሆነ ጉዳዩ ፣ እኛም ” ዛሬም በኢህአዴግ የሚያምኑ ብልፅግና ተባሉ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም ። ” ለማለት እንገደዳለን ። በአሥተሳሰብ ደረጃ ከቀድሞው ኢህአዴግ ጋር የውና አንድ ነን የሚሉትን ብልፅግና ከታች እሥከላይ ፈትሾ መንጥሮ እሥካለወሰገደ ጊዜ ድረሥም ፣ ” ከራስ በላይ ነፈስ ” በሚሉ ሥግብግብ ግለሰቦች እጅና አግሩ ታሥሮ አፉ ብቻ እንደቀረ ይወቀው ። እነዚህ ሰዎች ከሰውነት ይልቅ ለግል ጥቅማቸው ብቻ ሲሉ
“ ቋንቋ ወይም ሞት “ የሚሉ ናቸውና እንደ ወያኔ መሪዎች የአገር ህልውና ፀር መሆናቸው መታወቅ አለበት ።
ወዳጄ የፈለከውን ቋንቋ ተናገር ፤ አንተ ሰው ነህ እንጂ ቋንቋ አይደለህም ።የኢትዮጵያ ፣ የአሜሪካ ፣ የሩሲያ ፣ የጃፓን ፣ የቻይና ፣ የጀርመን ። ወዘተ ። ዜጋ ልትሆን ትችላለህ ። ግን አንተ ሰው ነህ ። ትግሪኛ፣ አማርኛ ፣ ሱማሊኛ፣ ኦሮምኛ ልትናገር ፣ ትችላለህ ሆኖም ሰው እንጂ ቋንቋ ልትሆን አትችልም ። እናም ለአንተ የሚገባህ ሰው መሆንህን በሚገባ ማወቅ ና መብትና ግዴታህን በእኩል ደረጃ አውቀህ ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር መኖር ነው ። ሰውን ሁሉ የሚያሥከብረውና ህይወቱ በሥቃይ የተሞላ ብቻ እንዲሆን የማያደርገው ይኽ ብቻ ነው ።
መንግሥትም ቢሆን የሰዎች ስብስብና መሆኑንን ተረዳ ።እንደ ማንኛችንም ተፈጥሯዊ ድርጊቶች ና እራሷ ተፈጥሮ ለኑሮው እንደምታሥፈልገው ተረዳ ። ” መንግሥት እንደኔ ሰው መሆኑንን ብገነዘብም ፣ ጠመንጃ ፣ ታንክ ና ባንክ እንዲሁም እሥር ቤቶችን ፣ ስለሚያዝባቸውና ሥለሚቆጣጠር ፣ እፈራዋለሁ ። ” ። ካልክ ይኽ ፍራቻኽ ጤነኛ ቢሆንም ፤ ፍርሐት በራሱ ” የህይወት ድንክ ” እንደሚያደርግም እወቅ ።
እናም መንግሥትእውነተኛ ዴሞክራት እንዲሆን ታገል ። መንግሥትህ ፣ለመረጠውም ፣ ላልመረጠውም የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ መብቱን ና ግዴታውን በማሳወቅ ፣ ካሮት እንዳለ ሁሉ ልምጭ መኖሩን በወጉ ማስገንዘብ እንደሚችል ንገረው ። መንግሥትህን ከእውነተኛው የፍትህ መንገድ ፣ ቅቡልነት ካለው የዴሞክራሲ መንገድ ሲወጣ መውቀሥ ና መሄየሥህን የፍራት ቆፈን አይከልክለው ።መንግሥትም ዜጎችን በመልካም ሥራቸው ማመሥገን ፣ በመጥፎ ሥራቸው ደግሞ መኮነን እና ፣ መውቀሥ እንዲሁም በህግ አግባብ እንዲቀጡ ማደረግን ለአፍታ እንኳን መግታት የለበትም ። በህግ አግባብ ፈጣን ተመጣጣኝ ቅጣት በመቅጣት አጥፊዎች ቀጪ ህግ እንዳለ እንዲያውቁ ማድረግ ፤ ህብረተሰቡንም ማሥተማር የመንግሥት የ24 ሰዓት ሥራ እንደሆነ ይታወቃል ።
መልካም ፤ ቅን እና ሰው መሆኑንን በሚገባ የተረዳ መንግሥት ፣ በመላ እንጂ በዱላ እንደማያምን የዘመናችን ዴሞክራሲ ይነግረናል ። እንዲህ አይነቱ በሰዎች ተፈጥሯዊ መብት ና ሰብዓዊ መብት የሚያምን መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው ፤ በአገራችን ሠላም የሚሰፍነው ። እናም ዛሬ ና አሁን ለእኛ ለጫዋዎቹ ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገን የመላ አገዛዝ እንጂ የዱላ አገዛዝ አይደለም ። ልምጭ ና ካሮት ። ( carrot and stick Approach ) በወጉ መከተል ነው የሚያስፈልገን ። ከዱላ ይልቅ በመላ እና በጥበብ የሚያሥተዳድር መንግሥትም የተረጋጋች አገር እንዲኖረን ማድረግ አይሳነውም ።
ከታሪክ እና በየመንግሥታቱ የአገዛዝ ጉዞ አብረን በመጓዛችን ፣ የተረዳነው ፣ የዱላ አገዛዝንበአገር ሰፍነው እንደነበር ነው ። በቀኃሥ ዘመን ዓፄያዊ ዱላ ነበር ። በአብዮታዊት ፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያም ደርጋዊ ዱላ ነበር ። በኢህአዴግም ወያኒያዊ ዱላ እጅግ በዝቶ ነበር ። ማሥፈራራት ፣ ማሰቃየት እና ወግሮ መግደል ብቻ ሣይሆን ፣ ወያኔ /ኢህአዴግ በአሰቃቂ ሁኔታ ራሱ ገድሎ ፣ እውነትን ለመቅበር ድራማዊ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ፣ ጣቱን ወደሌላ እየጠቆመ ሲያወዛግብን ነበር ።
ይኽ እውነት ነው ። ዛሬም ይኽ ሁሉ ተወግዷል ብለን ለመመሥከር አንደፍርም ። የሰው የንግግር ነፃነት በዱላ እየታፈነ እየተመለከትን እንዴት ነው የዴሞክራሲ ምሰሶ የጠበቀ ነው የምንለው ? በዚች አገር ሰው ሁሉ ያሻውን ለመናገር የግድ ሠካራምና እብድ መሆን አለበት እንዴ ?!
ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ አንድ አጋጣሚ አለኝ ። የልጅነት አጋጣሚ ። (10 ወይ 11 ዓመት ቢሆነኝ ነው ። )
የወታደር ልጅ በመሆኔ ካምፕ ውሥጥ ነው ያደኩት ። እዛ ከምፕ ውሥጥም የኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን አለች ። እዛ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ፣ ተዋቂ ቄስ ነበሩ ። በእውቀታቸው ማለቴ ነው ። ቄሥ ሥሜ ይባላሉ ። ሲሰክሩ ግን የልባቸውን ይናገሩ ነበር ። ከካምፑ ጎን ካለው አራዳ ከተማ ጥተው ወደ ካምፑ ሲገቡ ፣ ቤተክርሥቲያኑ መገቢያ አሥፖልት ላይ በሠልፍ ወታደሮች ሲጎዙ አዩ ። እናም ጮክ ብለው ” እናንተ የኃይለሥላሴ ባሮች ! …” እያሉ እየሳቁ ደጋግመው ሲናገሩ እንደ አጋጣሚ አጠገባቸው ሆኚ ሥምቻለሁ ። በህፃን ጆሮዬ ። በወቅቱ እኔም ሥቄለሁ ። ይሁን እንጂ በመናገራቸው ማንም የተቆጣቸው ። የመታቸው ። ያሰራቸውም የለም ። ዘመኑ 1965 ነው ። እና በዛ በቀኃሥ ዘመን ” እናንተ የኃይለሥላሤ ባሮች ። ” ሥላሉ ማን ሊከሳቸው ፣ ሊቆጣቸው ፣ ወዘተ ። ይችላል ? ( የአምበርብር ጎሹን ሞት ምክንያት ከአብዬ መንግሥቱ ግጥም ተረዳ ። በር ዘግታ አላሥገባ ያለችውን ሴትኛ አዳሪ ለንጉሡ በመመኘቱና ነኸው ንግግሩ ፣ በነጭ ለባሽ ተጠቆሞበት አርባ ጅራፍ እንዲገረፍ ተፈርዶበት ፣ ግርፊያው 30ም ሣይሞላ ፍግም ያለው ። )
በነገራችን ላይ ፣ ፀሐፊው ሃሳብና ሃቅ ላይ የተመረኮዘ ፅሑፉን ነው ለአንባቢ ለማካፈል የሚፈልገው ። አንተ ሁሌም በነጭ ወረቀት ላይ ጥቁር ነጥብ የምትፈልገው ሰውዬ ፣ እሥቲ ወደ ቀልብህ ተመለስ ። ሰውን በሐሰት በመክሰስ አታሥገርፍ ። አታሣሥር ። አባ ዱላ ማላት የዱላ አባት ማለት ነው ። አባ መላ ደግሞ የመላ አባት ነው ።ሃሳቤ ሽፍንፍን አይደለም ግልፅና ግልፅ ነው ። ( ከኦሮምኛ ፍቺ ጋር አታገናኘው ። እርሱ ላላ ተደርጎ ነው የሚነበበው ። የጦርነት አባት ማለት ነው ። የጦር መሪ እንደ ማለት ) በበኩሌ ፣ ገሃነም እሥቲቀዘቅዝ መጠበቅ ሞኝነት መሆኑንን እረዳለሁ ። ገሃነም እሥከወዲያኛው አይቀዘቅዝም ። እናም አንድ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ፀሐፊ ፣ ለሚወዳቸው ኢትዮጵያን ነፃነት ፣ እኩልነት ፣ ሠላም ፣ ዴሞክራሲ እና ብልፅግና ማበብ ሲል ዱላውን ሳይፈራ ፣ ባለሥልጣናቱ ቢመራቸውም በህዝቡ ውሥጥ ያለውን እውነተኛ ሃሳብ በግልፅ መናገር አለበት ።…. ።
እውነቱ ምንድነው ? እውነቱ ፣ ዛሬም እንደትናንቱ አባ ዱላዎች ይፈራሉ ። አባመላ የሆኑትን ምሁራን ፣ ማህበራዊ አንቂዎች እና ጋዜጠኞችን በደፋር ብዕራቸው ፣ በእውነተኛ አንደበታቸው ፣ ምክንያት ከግል ፍራቻቸው የተነሳ ለእሥር እና ለእንግልት ይዳርጓቸዋል ። ባለሥልጣናቱ ” ዛሬሥ በአይኔ መጣ ! ” በማለት ብቻ የአይናቸው ቀለም ያላማራቸውን ሁሉ ለማሳሰር እንደሚችሉ እያሥተዋልን ነው ።
በዱለኝነታችን ተፈርተን ፣ ከህግ በላይ ሆነን ፣ አንድ ዜጋ ፣ በሰብዓዊ መብቱ ፣ ተፈጥሮ በለገሰችው አንደበቱ በመናገሩ ብቻ ፣ በአንድ የክልል ባለሥልጣን ቀጭን ትዕዛዝ ማጅራቱን ይዘን ወደ እሥር ቤት መወርወር አግባብ አይደለም ። ፀረ ዴሞክራሲ አካሄድ ነው ። አምባገነንነት ነው ። አምባገነንነት ነው ፤ ሥንል የጋዜጠኞችን መታሰር ቤተሰብ ቢያውቅም ፣ የት እንደታሰሩ እንኳን ለማወቅ ወራት የፈጀበት እውነትን በዋቢነት ይዘን ነው ።ይኽንን አሥገራሚ እውነት ተመልክተንም ፣ ” ወያኔ በየት ዞረሽ መጣሽ ? ” ብለናል ። …
ይህ የኢፍትሐዊነትና ፣ የማን አለብኝነት አካሄድ ፣ ከታዲዎስ ታንቱ ፣ እሥከ ታምራት ነገራ እሥር መሥተዋሉም ፣ ብልፅግና ወዴት እየሄደ ነው ? ወይሥ እንደ ፓርቲ በአንድ የድርጅት ማዕቀፍ ፣ የሚመራ አይደለምን ? በማለት ብልፅግና የሥም እንጂ የግብር ፓርቲ ላለመሆን በአእምሮም መበልፀግ ያሥፈልገዋል ። ብለን እንመክራለን ። የቁሥ ብልፅግና ያለአእምሮ ብልፅግና ከንቱ ነው ። እንዴ ምን ማለታችሁ ነው ፤ ደጋግመው የነገሩንን የጠቅላይ ሚኒሥቴሩን የእውነት ፣ የቅንነት ና የሃሳብ ነፃነትን መርህ የጣሰ ድርጊት ሲፈፀም ጆሮ ዳባ ልበሥ ማለት ለምን አስፈለጋችሁ ? ሰው ተፈጥሮ የሰጠችውን አንደበት ተጠቅሞ ሃሳቡን በመሰንዘሩ ፣ ሃሳብ እንደዱላ መቆጠር አለበትን ? …ብለንም እጠይቃለን ።
ሰዎች ሆይ ! የአውሮፖና የአሜሪካ ዴሞክራሲም የሚያሥቀናን ከዚህ እውነት አንፃር ነው ። እሥቲ የአሜሪካ ቀልደኞችን ተመልከቷቸው ። እንዴት ነው ፤ በየመድረኩ ፣ እያዋዙ ና ተመልካቹን እያሳቁ ፣ ፕሬዝደንቶቻቸውን እና ሹማምንቱን ሁሉ የሚያብጠለጥሉት ? የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንትንም ሆነ የአሁኑንን በግልፅ ሲተቿቸው ተመልክተናል ። ትራምፕን ከአፍሪካ አበገነን መሪ እኩል አደርገው በመሣል ፣ በግዙፍ መድረክ ላይ ተሣልቀውባቸዋል ።
ዛሬና አሁን በኢትዮጵያ ፀረ _ዴሞክራሲ ተግባር ሲያቆጠቁጥ እያየን ነው ። ሰው በግልፅ በአደባባይ ፣ ያውም የአገሬ መሪ ትችት ና ሂስን አይፈራም ብሎ ፣ ከሥደት ወደ አገር ውሥጥ ገብቶ ፣ እርሱ እና ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የሚያምኑበትን ሂሥ ፊት ፣ ለፊት በመናገሩ ሲታሰር ፣ ሥናይ ፣ ” አይ የእኛ ፖለቲካ ! ዛሬም ይላል ባለሥልጣንን አትንካ ! ” ለማለት እንገደዳለን ።
አይ እኛ ! ለምን ይሆን፣ የሰውንተፈጥሯዊ የመናገር መብት ለማፈን የምንተጋው ? ደንቆሮና መሐይም ሥለሆንን ይሆንንን? ወይሥ ከመብላትና፣ ከመጠጣት ና ከምቾት ኑሮ ብዛት የትላንቱ የራቁት ውልደታችን ተዘንግቶን ?
እሥቲ ወደኋላ ልውሰዳችሁ፣ ጠቅላይ ሚኒሥቴር አብይ ሥልጣን ከያዙበት ከመጋቢት 24/ 2010 ዓ/ም ባሉት አንድ ዓመት ከመፈንቅ ጊዜ ውሥጥ በኢትዮጵያ ውሥጥ ፣ ” ተአምር ” ለመሰኘት የሚበቃ እውነተኛ ዴሞክራሲ መከሰቱን ትክዳላችሁን ? ተከታታዮቹን የኢትዮጵያውያንን ልብ ያሞቁ ንግግራቸውን ትዘነጋላችሁን ? ለዓመታት በአምባገነኑ ወያኔ / ኢህአዴግ ታሥረው የነበሩ ፣ የበዙ የፖለቲካ እሥረኞች መፈታት እና እሳቸውም ከእንግዲህ የአንድ ግለሰብን ህግ ጥሰት ወይም በህግ የተከለከለን ተግባር መፈፀም ሣናረጋግጥ አናሥርም ። ” ማለት ተግባራዊ ሲሆንም ቆይቷል ። አሁን እና ዛሬ ግን መንግሥታቸው ውሥጥ ከታሸገበት ጠርሙሥ የወጣ ጂና የገባ ይመስላል ። ይህን ጂኒ መልሶ ወደጠርሙሱ ለማሥገባት የሙሴ በመላ የታጀበ የአመራር ጥበብን መከተል ያሥፈልጋል
።
ዛሬም ከሙሴ የአመራር ጥበብ ብዙ ብልሃትን መማር ይቻላል ። ሙሴ አሥርቱን ትዕዛዝና እርሱን ተከትሎ ያወጣቸው ህጎች የህግ መሠረቶች እንደሆኑ ፣ ግጭትን ፣ አመፅን ፣ ጉልበተኝነትን ፤ ወዘተ ። እንደገደቡ ይታወቃል ። የመናገር መብትን ግን ያፈኑ አልነበረም
። …
ወዳጄ ማወቅ ያለብህ ነገ ሟችነትህን እና ሁሉም ሰው እንደ አንተ ሟች መሆኑንን ነው ። እናም ሰው በህይወት እሥካለ ድረሥ በተቻለው አቅም ህይወቱን አጣፍጦ እንዲኖር መተጋገዝ ግዴታው ነው ። አንተ እህል ገጠር ሆነህ ብታመርት ፣ ጨው ፣በርበሬ ፣ ዘይት ፣ ወዘተ ። ከከተማ ያሥፈልግሃል ። ይኽ በአጭሩ ፣ ሰው በዚች ዓለም የሚኖረው በመደጋገፍ እንጂ ፣ በመነጣጠል ህይወቱን ማጣፈጥ እንደማይችል ያሥተምርሃል ። እናም ሰው እሥከ ጊዜ ሞቱ ፣ ከአቋቋመው መንግሥት የሚሻው ፣ ፍትህን ፣ እኩልነትን
፣ ነፃነትን እና ዴሞክራሲያዊ
መብትን ብቻ ነው ። ይኽንን መሻቱን አንድ መንግሥት የሚያሟላለትም ጠንካራ የመከላከያና የፖሊሥ ሠራዊት ሲኖረው ብቻ ነው ።
በዘውግ ላይ ያልተመሠረተ ፣ አንዳችም ኮታ የሌለበት ፣ በሁሉም የአገረ መንግሥቱ አሥተዳደራዊ ግዛቶች ወይም ክፍለ አገሮች ውሥጥ ህግን ለማሥከበር የሚንቀሳቀሥ የፖሊሥና የሚሊተሪ ኃይል ያለው መንግሥት ፤ የህዝቡን ወጥቶ መግባት አሥተማማኝ ሥለሚያደርግ
፣ አገርን በቀላሉ ባለፀጋ ለማድረግ ይችላል ።
ዜጎች ያለገደብ በመከላከያም ሆነ በፖሊስ የመቀጠር መብት ሊኖራቸው ካልቻለ እና አንድ ወጥ ከዘውግ አመለካከትና ከዘረኝነት አስተሳሰብ የፀዳ ሠራዊት እሥከሌለን ጊዜ ድረስ ፣ ነገም በኦሮሚያ ፣ በአማራ ፣ በሱማሊያ ፣ ወዘተ ፣ ልዩ ኃይል ና ፖሊሥ አማካኝነት ሠላማችን መደፍረሱ አይቀርም ።
በሁሉም ክልሎች የሚፈጠሩ አመራሮች ፣ በከተማና በገጠር በግልፅ የህዝብ ድምፅ ፣ ወደ ህዝብ አሥተዳዳሪነት መምጣት ይጠበቅባቸዋል ። በየከተማው የሚኖር ዜጋ ሁሉ ፍትህን ሳይሸራረፍ በእኩልነት ማግኘት ና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ መከበር አለበት ።
ሥለሰብዓዊ መብት ሳነሳ የታምራት ነገራ መታሰር ግርም ይለኛል ። በተፈጥሮ በተሰጠው አንደበት ሃሳቡን ሥላቀረበ ለምን ይታሰራል ? የክልል ፕሬዝዳንቶች ራሳቸውን እንደ ህዝብ አገልጋይ ሳይሆን እንደ ንጉሥ የሚቆጥሩ ሥለሆኑ ይሆንን ? ወይሥ ለሙገሳ እና ሹመት ለማግኘት የሚፈልጉ የፖሊሥ ባለሥልጣናት ናቸው እንደ በግ ሰውን ማሰር የጀመሩት ? ለሥዩም ተሾመ የተሰጠው የመናገር መብት ለታምራት ነገራ የተከለከለው ለምንድነው ? መቼ ይሆን በሃሳብ ደረጃ መሟገት የምንጀምረው ? መቼ ይሆን በዱላ ሳይሆን በልምጭ መጠቀም የምንጀምረው ? በብዕር ሸንቆጥ ማድረግ ፣ በሃሳቡ ዙሪያ የውይይት መድረክ መክፈት ። ህዝብን ማወያየት እና በህዝብ ፈቃድ መመራት መቼ ነው የምንጀምረው ??? ታምራት ነገራ በሚሊዮኖች ቤት በጎዳ የሚነገረውን በአደባባይ በመናገሩ መታሰር አለበት ወይ ? ደሞስ ኦሮሚያ የሚል ቃል የፈጠረው አንድ ግለሰብ ነው ፤ ተብሎ ይታመናልን ? ይኽሥ ሥያሜ ጤናማ መልዕክት ያለው ነው እንዴ ? ሌሎች ክልሎች ለምን” ያ ” ን አልተጠቀሙም ? ለምሳሌ ለምን ሶማሊያ ፣ ሲዳሚያ፣ጋቤሊያ፣ ቤንሻንጉሊያ ፣ አማርያ ወዘተ ። አልተባለም ። የዚህን ጥያቄ መልሥ ፣ የቀድሞው ወያኔ /ኢህአዴግ ይመልስልሃል ። በዘውግ ና በቋንቋ ፣ የአጠቃላይ እውቀት ደሃ የሆነውን ፣ የየዘውጉን ኢሌት ና ባለሀብት በጥቅም በመደለል ፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ለቋንቋው ተናጋሪ ብቻ እንዲወግን ያደረገው እርሱ ነበርና !? ከፋፋይ ሃሳብ ያጨቀውን ህገ መንግሥት ፣ ዘረኛነት ህጋዊ ሽፋን እንዲኖረው ያደረገውን ህገመንግሥት ፤ እንካችሁ ብሎ እሥከ ዛሬ እያጨራረሰን ያለው ሰውነትን ያሥካደ ፣ የወያኔ የተረገመ የዘውግ ና የቋንቋ ንግሥና አይደለምን ?
የወያኔንን የ27 ዓመት ድርሳን ብታነብ ዜግነት በወረቀት ብቻ እንጂ በተግባር እንዳይኖር ማድረጉን በቅጡ ትረዳለህ ። እንሆ ዛሬም ትግራይ ህዝብ ውሥጥ መሽጎ ፣ ለሆድ አደሮች የዘረፈውን እየበተነ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ዜጋ ፣ በግፍ እንዲገደሉ ና እንዲሰደዱ እያደረገ መሆኑንም አሥታውሥ ። ” የአፋር ህዝብ ለምን ለሞትና ለሥደት ተዳረገ ? ” ብለህም ጠይቅ ። ( ” ኢትዮጵያ ወይም ሞት ! ” በማለቱ አይደለምን ? ይኽንን ደግሞ የባንዶቹ አለቆች ና የምዕራቡ ዓለም ዘረኞች መሥማት አይፈልጉም ። ሥለዚህ ነው በአፈር ህዝብ ላይ ዱላቸውን ያበረቱት ። ለብዝበዛቸው ግብ መምታት ሲሉ ። )
ዛሬ እና አሁን ወያኔዎች ፣ የጌቶቻቸውን የቤት ሥራ ለመጨረስ ፣ ከሁሉም ዘውግ ጋር ( ብሔር ብሔረሰብ ጋር በሉት ።) ተጋብቶ እና ተዋልዶ የሚኖረውን የኦሮሞ ህዝብ ፣ ጥቂቶች ለሚቀባረሩበትና እና ሚሊዮን ዶላር ለሚያገኙበት እኩይ ሴራ ሲሉ ፤ ከሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ሰው ገር ( በተለይም አማርኛ ቋንቋ ብቻ ከሚናገረው ሰው ጋር …) ደም በማቃባት አገሪቱን ወደማያባራ የእርስ በእርስ መተላላቅ እየመሯት ነው ።የእጅ አዙሩን የብዝበዛ መንገድ እየጠረጉ ነው ። በቋንቋቸው ብቻ ፣ የአማራ ህዝብ አካል ናችሁ ። በማለት ለዘመናት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተደባልቀው የኖሩትን ፣ በነ ግብፅ ጃሥ ባይነት ( በሥውር ፣ ቢሊዮን ዶላር በጀት መድበው እንደሚቀሳቀሱ ይታወቃል ። ) እየጨፈጨፉና ቤታቸውን እያቃጠሉ ፣ ያሉትም ለጌቶቻቸው ዓላማ ሲሉ መሆኑንን ተገንዘብ ። ግንዛቤህንም ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑትን የሳተላይት ቴሌቪዢኖችን መብዛት ይጨምርልሃል ። በነዚህ የቴሌቪዢን ጣቢያዎች ለኦሮሞ እና ለትግራይ ደሃ ህዝብ ከድህነት መላቀቅ ዜሮ አምሥት ሣንቲም አሥተዋፆ ያላደረጉ ምሁራን ናቸው ጥላቻን ሲዘሩ ዘወትር የምትሰማው ። እነዚህ የተማሩ ሰዎች ፣ የዳርዊንንም ሆነ የሙሴን መፅሐፍ ያነበቡ ሆነው ሣለ ፣ ሰው ከፍጥረቱ ጀምሮ ፣ ከአንድ ዘር የተገኘ መሆኑንን ሆዳቸው አሥክዷቸው ፣ ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ ፣ በዘውግና በነገድ ለመከፋፈል ብቻ ሣይሆን ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው በአማርኛ ተናጋሪው ላይ ቢላዋ አንስቶ እንዲያርደው የሚቀሰቅሱ ፤ ” እኛ ንፁህ የመለአክት ዘር ነን ። ሌሎች ደሞ ሰው ሳይሆኑ በረሮዎች ናቸው
። ” ብለው በድፍረት የሚናገሩ የሂትለርን እና የሞሶሎኒን አእምሮ የወረሱ እብድች ናቸው ። ከእጅ ወደአፍ ኗሪውን ምሥኪን ህዝብ ሠርቶ ከመብላት ይልቅ ፣ ገድሎ ፣ አርዶ ና ዘርፎ እንዲበላ ፤ ወገን በወገኑ ላይ ዘላለማዊ ጥላቻን እንዲያፈራ ዛሬም እያደረጉ ነው ።
ዛሬም አንድ ጨዋ ና ሠላማዊ አርሶ አደር ዜጋን ፣ ከመሬት ተነሥቶ ፣ በአውሬነት መንፈስ መግደል ና ማረድን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል ። ይህንን እኩይ ድርጊት በቅጥረኝነት እንዲፈፅሙ በገንዘብ ፣ በትጥቅና ሥንቅ መደገፍ ምን ማለት እንደሆነ ፤ ሰው ና የሰው ክብርን ለሚያውቅ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ግልፅ ነው ።
ኢትዮጵያዊው ሰው ሆይ ! ጥቂቶች ራቁታቸውን የዘነጉ ፣ ለዘመናት ከህይወት የተማሩትን ትምህርት የማያሥተውሉ ፣ የኮሌጅ ና የዩኒቨርስቲን ቆየታቸውን ለቆዳ ማዋደድ የሸጡ ። ሰው መሆናቸውን ክደው ፣ ለእኩይ ዓለማ በቋንቋቸው የወገኑ ። በወጣትነታቸው ና በድህነታቸው ሰበብ የነጮችን ሴራ ለማሥተዋል የተሳናቸው ። በኢምፔሪያሊዝም ና በሶሻሊዝም አቀንቃኝ የውጪ ኃይሎች ሴራ ተጠልፈው ፣ ለእነሱ ዓላማ የሞቱ ። ሌኒንን ፣ ማርክስን እና ኤንግልሥን እንደ ሦሥቱ ሥላሤዎች የቆጠሩ ። “አሜሪካና መንግሥተ ሠማይ አንድ ናቸው ። ” በማለትም የአሜሪካንን መንግሥት እንደ እጊዜር መንግሥት የቆጠሩ ነበሩ ፤ የትላንት ወድቀታችን መንስኤዎች እነሱ ነበሩ ። የዛሬ ውድቀታችን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ኪሳራ ውሥጥ አገርን ያሥገቡ እነዚሁ ጭቅላተ ቢሥ ሆዳሞቹ ወያኔዎችና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው ።
እነዚህ ሆድ ብቻ የሆኑ ቡድንች ፣ ዛሬም ህዝብ ሳይወክላቸው ፣ በጠመንጃ ፣ ህዝቡን ፣ ጨዋ ዜጋውን ፣ ሠርቶ ለመለወጥ የሚጠረውን ሰው ፣ እያስፈራሩ በህዝብ ሥም የነግዳሉ ። ህዝብ በመራቡ ፣ የሚላሥ የሚቀመሥ በጎጆው በመጥፋቱ ፣ ሳይወድ በግዱ ለመሰንበት ብሎ የሚለሥ የሚቀመሥ ሥለሌለው ፣ ሁሉ በአጃቸው ና በደጃቸው ካለ ፤ ዱላ እንጂ መላን ከሚጠየፉ ሥግብግብ ና አይጠረቄውች ጋር ሳይወድ በግዱ ይወግናል ።
ወገኔ ልብ ብለህ አሥተውል ፣ የእርዳታ እህል አከፋፋዮች እነሱ ናቸው ። የእርዳታ እህሉ ለነሱ ልክ እንደ ወታደራዊ ሎጀሥቲክ ነው ። እናም ልጁን ያላዘመተ ወላጅ እርዳታውን እንደማያገኝ የታወቀ ነው ። ይኽ እውነት ይሁን እንጂ ተርታው ህዝብ በነጋ በጠባ ቁጥር የወያኔ ካድሬዎችን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ስለሚሰማ ፣ አብዛኛው የትግራይን ህዝብ ፣ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ ሊያጠፋው እንደተነሰ ከልቡ አምኖ ነው ፣ ወደ ጦርነት የገባው ። ዘላለም አለሙን በጥርነፋና በግምገማ በመኖሩ ባለው አንድ ለአምሥት አደረጃጀት የተነገረውን ” እውነት ነው ። ” ብሎ ከእኛዎቹ ሞሶለኒዎች ና ሂትለሮች ጋር ቢተባበር ምን ያስገርማል ?
ህዝብ እንደ ህዝብ አይጠላላም ። አንዱ ሰው ለሁሉም ሰው ጠላት መሆን አይችለልም ። ቡድናዊ ና የዘረኝነት ህሊና ነው ጥላቻን የሚፈጥረው ። ይኽንን እውነት ቢታወቅም ፣ ባለው ንቃተ ህሊና እና ለዘረኛ ቡድኑ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ በመሆኑ ፣” ለምንድነውምንም ካልበደለኝ ፣ ከራሴ ዜጋ ጋር የምገዳደለው ? ” ብሎ ለመጠየቅ ከቶም አይችልም ።
እወቅ ፣ እጅግ የበዛው ትግራዋይ በወያኔ ተጠርንፎል ። አብዛኛው ህዝብ እኮ በእነደብረ ፅዮን መዳፍ ውሥጥ ነው ። አይደለም ትግራይ የሚኖረው ትግራዋይ በመሐል አገርና በውጪ አገር የሚኖር ትግራዋይ አፉ ሳይቀር የተለጎመ ነው ። እውነተኛ አሥተያየት መሥጠት ፣ የወያኔንን ጥፋት እያየ መቃወም አይችልም ።ከተቃወመ ፣ መገለልና እሥከ ህይወት መጥፋት በገዛ ወንድሙ ፣ እንደሚደርስበት ያውቃልና !! ( ሳያጣሩ ማሰር አንዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆነ እና ይኽንን አድራጎት ፣ አምርሬ ብቃወምም ፤ በየክልሉ በጥርጣሬ ከታሰሩት የትግራይ ተወላጆች አብዛኞቹ በፍራቻ ቆፈን ተይዘው ወያኔንን ለማወደሥ የተገደዱ እንደሆኑ እሙን ነው ። ነገ ወያኔ ተመልሶ መንገሱ አይቀርምና ” የመጀመሪያዎቹ ሠለባዎች እኛነን “ብለው ሥለሚያምኑ ነው ። ከጳጳሱ የበለጠ ሰባኪ እና ለወያኔ ተቆርቋሪ ሆነው በመገኘታቸው የታሰሩ ዜጎች ብዙ ነበሩ ። እርግጥ ዛሬ ተፈተዋል ። ግን ግን ፣ ዛሬም ይኽ ፍራቻን ያሰፈነ ሥልጣንን ከህግ በላይ የማደረግ እና አምባገነንነትን የማስፈን አዝማምያ በገዢው በብልፅግና ፖርቲ ውሥጥ መኖሮ ይታወቃል ። “ በላቤ ና በድካሜ ጥረት እንጀራ አገኛለሁ ። እውነትን ተናግሬም የመሸበት አድራለሁ “ ከሚል ይልቅ “ ከራስ በላይ ነፋስ “ በማለት ፣ ተገቢ ለልሆነ የግል ጥቅም ጓደኞቹን ሳይቀር መሰዋት የሚያደርግ የበዛ ሰው በመሞዳሞድ ፣ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ በየክልሉ እየተስተዋለ ነው ።ይኽንኑ የገዢውን የብልፅግና ባለሥልጣናትን ግልፅ ሙሥና እና የዘረኝነት ልክፍት ጦስ ጥንቡሳስ ፣ በአደባባይ ካሰጣህ ፤ እንዲሁም ዛሬ ና አሁን የምንሄድበት መንገድ ፤ ቁልፉ በህሊና ቢሥ ሥግብግቦች የተያዘ ፣ በጊዜው የሚፈነዳ ፈንጂ የሞላበት ነው ። “ ብለህ ካስጠነቀቅህ ፣ ይኽ ትሁት ና ለአገር መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ ያለው ሃሳብህ ፣ ያለመብላትና መጠጣት እንዲሁም ያለሴት ሌላ ዓለም ያለ በማይመሥላቸው ሥለማይወደድ ፣ የውድቀት ጎዳናውን ለማፅዳት ፣ በንሥሐ ወደ ቀልባቸው ከመመለሥ ይልቅ ፣ አንተን በማጥፋት እውነትን ማጥፋት ያለ ይመሥል ግልፅና ሥውር ማሳደድ ፣ እሥርና እንግልት ያደርሱብሃል ። ” …
ወዳጄ ! የነ ደብረፅዮንን መፈራት ከእዚህ አንፃር ብትቃኘው የአምባገነንነት አሥጠሊ ገፅታ ፍንትው ብሎ ታይሃል ። በትግራይ ክልል ዛሬና አሁን ህዝቡን የሚያሥተዳድሩት አምባገነኖች ናቸው ። በሚሊዮን ለሚቆጠረው ህዝብ ሥንቅ አቅራቢ ፣ መድሃኒት አዳይ ፤ እነ ደብረፅዮን መሆናቸውን ተረዳ ። በመሆናቸውም አንዳችም አማራጭ የሌለው ህዝብ እነ ደበረፅዮንን ፣ ምንም ነገር የማይሳናቸው ” ልዕለ ሰብ ” አድርጎ ነው የሚመለከታቸው ። ምክንያቱም እነሱ የዛ ደርግን የገረሰሰው የታላቁ ወያኔ ልጆች ናቸዋ ።
እውነታው ግን የትግራይ ህዝብ ከሚያሥበው ውጪ ነው ። ትላንት ደርግን የገረሰሰው አሜሪካ ነው ። ታላቋ ሶሻሊስት አገር ሶቬት ህብረት ሥትፈረካከሥ ሶሻሊዝም አብሮት መቀበሩን እወቅ ። እናም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ነው ደረግ መፈረካከስ እና ወደ ኋላ መሸሽ የጀመረው ። ከዛም በኸርማን ኮሆን ቀጭን ትዕዛዝ ፣ እነ አሻግሬ ይግለጡ ድርድር ላይ እያሉ ወያኔ ሚኒሊክ ቤተ መንግሥት ገባ ። እውነቱ ይኽ ነው ። የወቅቱ ብቸኛዋ ልዕለ ኃያል መንግሥት አሜሪካን ነበረች ። ተዋግቼ ! አቸንፌ ! ወይም አሸንፌ ! እውነታውን አይገልፅም ። ወያኔንን ያለ አንዳች ህዝባዊ ድጋፍ ሆነ ተቃውሞ ፣ ሚኒሊክ ቤተ መንግሥት የተከለችው አሜሪካ ነበረች ። ዛሬም አብይን ” ነቅልሃለሁ ! ” በማለት የምታሥፈራራው አሜሪካ ናት ። ሲአይ ኤ በተሰኘው የሥለላ ተቋሟ አማካኝነት ። ለሲአይኤ የሚሳነው እንደሌለ ከተከታታዩ የጀምስ ቦንድ ፊልም መገንዘብ ትችላለህ ። ወዳጄ ከአንተ ይልቅ ፣ ትላንት ዛሬ እንዳልሆነ ፣ ሲአይኤ ጠንቅቆ ያውቃል ። የዓለም የኃይል አሰላለፍ እንደልቡ እንዳላራመደውም በመገንዘቡም ወጥመዱ የሚሆኑት የአፍሪካ የመንግሥት ባለሥልጣናት ና ጀነራል መኮንኖች ናቸው ። ( ….የሚሰማ ይስማ ። የማይሰማ አይስማ ።)
ደሞም ከሰማህ ልንገርህ ፣ ሲአይኤም ሆነ ኬጂቢ ዛሬ የሚጠቀሙት ዘመናዊውን ቴክኖሎጂ በመሆኑ ሤራቸውን እንዲህ በቀላሉ አትደርስበትም ። ኬጂቢ የሲአይኤን ሴራ እግር በእግር ተከታትሎ የሚደርስበት በቴክኖሎጂው ረቂቅነት ነው ። አቻ ቴክኖሎጂ አለዋ ። የእኛ አገር ገና አዳጊ አገር በመሆኑ የነሱን እገዛ ይሻል ። ደሞም ሁለቱም ከዓለም የደበቁት የረቀቀ የመረጃ መሰብሰቢያ የቴክኖሎጂ መሣሪያ ሊኖራቸው እንደሚችል ተረዳ ። “እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ ” ነው ። ነገሩ ። በአገራችን ምን እየተከናወነ እንደሆነ
፣ ሲአይኤም ፣ ኬጂቢም ፣ ሞሳድም በሚገባ ያውቃሉ ።
ወደ ሰማይ ቀና ብለህ ተመልከት ። ምንም አይታይኽም ? አዎ አይታይኽም ። እኔም የሚታየኝ ነገር የለም ። ሣተላይቶቹ እኮ በጨረቃ ሙሐር ውሥጥ ነው ያሉት ። እንዴት ልታያቸው ትችላለህ ። ነገሩ ያለው በምድር መቀበያ መሣሪያው ውሥጥ ነው ። እሱን ደሞ ለአንተ አይሰጡኽም ። የፔንታጎን ፣ የክሪሚሊን ፣ የቴልአቪቭ ጉዳይ ነው ። እነሱ እኮ በመላ ና በጥበብ እንጂ በዱላ የሚመካ መንግሥታዊ መዋቅር የላቸውም ። እናም ለአገራቸው ጥቅም ሲሉ እያንዳንዶን እርምጃ ፣ በጥንቃቄ ና በሰጥቶ መቀበል ነው ፣ የሚጓዙት ።