የብሔራዊ ምክክር እንዲካሄድ ገና በጠዋቱ ህውሀት መራሹ ኢህአዴግ መንገዳገድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በብልጽግና እስከ ተተካበት ጊዜ ድረስ መንግስትን ሲወተውቱ ከነበሩ ጥቂት ሰዎች አንዱ ነበርኩ። የእኔ ውትወታና ምኞት የብሔራዊ ምክክር ጉባዔው ከምርጫው በፊት እንዲካሄድ ነበር። ምክንያቴም ግልጽ ነው፤ ያንጃበቡ አደጋዎች ስለነበሩ አገሪቱን ከከፋ እልቂትና መጠፋፋት ሊታደጋት ይችላል ከሚል ቅን እሳቤ ነበር። ይሁንና ብልጽግና መራሹ ኢህአዴግ ቅድሚያ የመቀመጫዮን ስላለ ትኩረቱን ወደ ምርጫ አደረገ። ያ እንደ ጥቁር ደመና በላያችን ላይ አንጃቦ የነበረው አደጋም በዶፍ ዝናብ መልክ ወርዶ አገሪቱን ወደ ለየለት ጦርነት ዶላት። በዚህ ከአንድ አመት በላይ በቆየ ጦርነት ኢትዮጵያ ብዙ ሺ ልጆቿን አጣች። በልመና ገንዘብ የተቋቋሙ ጤና ጣቢያዎች፣ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ተቋማት ዶግ አመድ ሆኑ። ባጭሩ በፖለቲከኞች እብደት ኢትዮጵያ ተዋረደች፣ ዜጎቿ ተሰቃዮ፣ የአገሪቱም ኢኮኖሚ በብዙ አሥርት አመታት ወደኋላ ተቀለበሰ።
ዛሬ መቀመጫውን በምርጫ ያደላደለ የመሰለው ብልጽግና የብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ሕግ ቀርጾ እና አስፈጻሚውን አካል በኮሚሽን መልክ ለማቋቋም ደፋ ቀና እያለ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት ይህ ምክክር የዛሬ ሁለት አመት ጀምሮ ቢካሄድ ኖሮ ብዙ ልናተርፍበት እንችል የነበረ ቢሆንም ‘ከቀረ የዘገየም’ ቢሆን ይሻላል በሚል ሂደቱን በጥንቃቄ እና በቅርብ ከመከታተል ባለፈ ሀሳብ ከመስጠት ተቆጥቤ ነበር። አሁን ግን መንግስት ጉዳዩን የያዘበት አግባብ ከወዲሁ ጥላ እያጠላበት መሆኑን ሳይ ይህን ምክረ ሀሳብ አዘል አጭር ጽሑፍ ለመጫር ተገደድኩ።
መሠረታዊ ሀሳብ፤
በአንድ ሀገር ውስጥ የብሔራዊ ምክክር የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? እና መቼስ ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ መንግስትን ጨምሮ በብዙዎች የሚታየውን ግራ መጋባት ወይም የተምታታ ሀሳብ ያጠራው ይሆናል። በአንድ አገር ውስጥ ብሔራዊ የመግባቢያ ምክክር – National Dialogue የሚያስፈልገው በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፤
1ኛ/ በአገሪቱ ያሉ ግጭቶችን እና የግጭት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ትርጉም ያለው ውይይት ለማካሄድ፣
2ኛ/ መሠረታዊ የሆነ እና ሕገ መንግስታዊ ይዘት ያለው የፖለቲካ አቅጣጫ ለውጣ ለማድረግ – ለምሳሌ ከጎሣ ፌደራሊዝም ወደ ሌላ ቅርጽ ያለው ፌደራሊዝም መሸጋገር፣
3ኛ/ ከፖለቲካ ልሂቁ ባለፈ በጠቅላላ በማህበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት ሲያጋጩ የቆዩ ቁርሾዎችን በግልጽ ውይይት፣ እውቅና በመቸርና በይቅርታ ለማከም፣
4ኛ/ ለተፈጸሙ በደሎችና የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማስረጽ፤ ናቸው
ከላይ የተጠቀሱትን የብሔራዊ ምክክር አስፈላጊ የሚያደርጉ አመክኒዎች ለማሳካት ሂደቱ ከዚህ በታች በምጠቅሳቸው መርሆዎች ሊደገፍ ይገባል።
የብሔራዊ መግባባት ወይም ምክክር መድረክ ዋና ዋና መርሆዎች፤
– ሁሉ አቀፍ (inclusion) እና አሳታፊ ወይም አቃፊ መሆን አለበት። የሂደቱ መነሻ ግጭት ስለሆነ በግጭቱ ዙሪያ ያሉ አካላት እና በግጭቱ ምክንያት ጥቅማቸው የሚነካባቸው አካላት ሁሉ በሂደቱ እኩል ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል፣
– ግልጽነት (transparency) የተሞላው መሆን አለበት። ሂደቱ ውጤቱን ከወዲሁ ስለሚያመላክት ከጅምሩ ጀምሮ እያንዳንዱ እርምጃና እንቅስቃሴ ግልጽ በሆነ መልኩ መካሄድ አለበት፣
– አሳታፊነት (public participation)፤ ሕዝብን፤ በተለይም ባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሂደት መሆን አለበት፣
– ለሀገራዊ መግባባቱ ወሳኝ የሆኑ የመወያያ አጀንዳዎችን በዝርዝር እና በበቂ ሁኔታ የያዘ መሆን አለበት ( a far reaching agenda)፣
– የአፈጻጸሙን ሂደቱን በተመለከተ አግባብነት ባላቸው እና ግልጽ በሆኑ መመሪያዎች ሊመራ ይገባል፣
– በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ አመኔታ የሚጣልበትና የሚከበር አወያይና አደራዳራ አካል ( Credible Convener) ያስፈልጋል፣
– ሙሉ ሂደቱ በዝርዝር በተቀመጠ የረዥምና አጭር ጊዜ እቅድ (implementation plane) መመራት ይኖርበታል፣
– የመጨረሻው ወሳኝ እና የብሔራዊ ምክክር እንዲሳካ የሚያደርገው ነገር ቁልፍ የሆኑ ባለድርሻ አካላት በቅን ልቦና የተሞላ ተሳትፎና ለሂደቱ መቃናት የሚያሳዩት ቀና ትብብር ነው።
የብልጽግና አስተዳደር ዘግይቶም ቢሆን አገሪቱ ወደ አገራዊ መግባቢያ መድረክ መምጣት አለባት ብሎ መንገድ መጀመሩ መልካም ነው። ይሁንና ሂደቱ ከወዲሁ ባለድርሻ አካላትን ስጋትና ጥርጣሬ ውስጥ የጣለ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ቀደም ሲል ኦፌኮን ጨምሮ ሦስት የኦሮሞ ፓርቲዎች፤ አስከትሎም በርካታ ፖርቲዎችን ያቀፈው የፖለቲካ ፖርቲዎች ምክር ቤት ሂደቱ እንዲቆም ጠይቀዋል። ስጋታቸውንም ገልጸዋል።
ይህ ነገር እንደተራ ተቃውሞ መታለፍ የለበትም። የአብይ አስተዳደር ይህ ሂደት ከመበላሸቱ እና የሌላ የፖለቲካ ቅራኔ ምንጭ ከመሆኑ በፊት የእነዚህን ባለድርሻ አካላት ቅሬታ በአግባቡ ሊያስተናግድ ይገባል። አዎ እስካሁን ባለው ሂደት ላይ ጥርጣሬን የሚያጭሩ ጉልህ ስህተቶች ታይተዋል። ሂደቱን በቅርብ እንደሚከታተል ሰው ከታዩት ጉልህ ስህተቶች መካከል፤
– በኮሚሽን አመራረጥ ለይ ከሕዝብ የቀረበው ጥቆማ የሚቀበለው አካል ገለልተኛነት፣
– ቀጠቅላላ ከተጠቆሙት ሰዎች ውስጥ በቅድመ ማጣሪያ የሚለዩ ሰዎችን የመለየቱ ሂደት፣
– 638 ሰዎች ተጠቁመው 42 ተለይተው የተመረጡበት መስፈርት፣
– ከ42ቱ የመጨረሻ 11 ሰዎች የሚመረጡበት ሂደት፣
እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ከወዲሁ ግልጽነት በጎደለው መልኩ ነው የተያዙት።
በመሆኑም መንግስት ይህን ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ሊኖረው የሚችል ጉዳይ ከወዲሁ ግልጽነት በጎደለው መልኩ የሚገፋበት ከሆነ የመጨንገፍ እድሉ ሰፊ ነው። ያ ደግሞ አገሪቱን ወደ ሌላ ዙር የፖለቲካ ቀውስ ሊከት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።
የአብይ አስተዳደር ከሚፈተንባቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ እና ወሳኙ ይህን አገራዊ የመግባቢያ መድረክ ከተራ የፖለቲካ ፍጆታ እና የፖርቲ ህልውና በላይ አገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው ማድረግ ሲችል ነው። ወያኔ ገና በጠዋቱ ሥልጣን በያዘ ማግስት ሞክሮት የከሸፈው አገራዊ የመግባቢያ መድረክ መዘዙ ይሄው እስከ ዛሬ አለቀቀንም። ብልጽግና ከወያኔ ስህተት መማሩን በተግባር ማሳየት ካልቻለ መዘዙ ከከሸፈው የ1983ቱ የሰላም ጉባዮ እጅግ የከፋ ይሆናል። ያኔ የብሔር ፖለቲካም ሆነ አክራሪ ብሔረተኝነት ጥርስ አላወጡም ነበር። የዛሬዋ ኢትዮጽያ ግን ከገዢ እስከ ምንዝር የሾለ ጥርስ ባወጡ፣ የአገርነት ስሜት በሚሰማቸው እና አፍንጫቸው ድረስ በታጠቁ ብሔር ተኮር ክልሎች የተከፋፈለችበት፣ ታጥቀውና የተወሰነ የአገሪቱን ክፍል እንደልባቸው የሚያምሱ የሽኔ አይነት ታጣቂዎች ያሉባት፣ የአገሪቱን የሰሜን ክፍል እስከ ሸዋ ድረስ በጦርነት ማመስ የቻለ የትግራይ ህይል አሁንም ለጸብ እየተንደረደረ ያለበት እና መገንጠልን አማራጭ ያደረጉ ቡድኖች የተፋጠጡባት አገር ነች።
ከዚህ በኋላ የገዢው ፖለርቲ እርምጃዎች ወሳኞች ናቸው። አስተውሎ ከተጓዘ እና ሂደቱን ከላይ በተጠቀሰው አግባብ እንዲሄድ ከፈቀደ አገሪቱ የመታደግና የማረጋጋት፣ ግጭቶችን የመቀነስ፣ የፖለቲካ ውጥረቱም የመርገብ እድል ይኖረዋል። ብልጽግና የወያኔን ስህተት ከደገመ ግን እንደ ሀገር መክረማችን ያሰጋል።
ሂደቱ እንዳይደናቀፍ ሁሉም በቅን መንፈስ ድርሻውን ይወጣ። በተለይ መንግስት ብዙ እርቀት መሄድ ይጠበቅበታል።
ቸር እንሰንብት!