በላይነህ አባተ ([email protected])
ኪነ-ፋኖ ተኢትዮጵያ መንጭቶ መላው አፍሪካን፣ መካከለኛው ምስራቅን፣ ኤስያንና ላቲን አሜሪካን ያጥለቀለቀ የነፃነት ሃይማኖት ነው፡፡ ኪነ-ፋኖ ሳይነኩ ያለመንካትን፣ ነፃነትን አሳልፎ ያለመስጠትን፣ የሎሌነትና የባንዳነት እድፍ መፀየፍን፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለሕፃናትንና ለሰላማዊ ሰዎች እንክብካቤ ማድረግን፣ የአገር ሐብትንና ድንበር የማስጠበቅ ጥበብን የሚያስተምር ሃይማኖት ነው፡፡
ይህንን የነፃነት ሃይማኖት የማይቀበል ሎሌነት የማይሰለቸው ባርያና ባንዳ ብቻ ነው፡፡ ሎሌነት የማይሰለቸው ባርያና ባንዳ እንኳን ይኸንን የነፃነት ሃይማኖት ሊቀበል ፋኖ የሚለውን ሲሰማም አቴቴው አንቀጥቅጦ እንደሚያስጎራው የታወቀ ነው፡፡ ሎሌነት የማይሰለቸው ባርያና ባንዳ የኪነ-ፋኖ ነፃነት ሃይማኖት ሲበላ በትንታ፣ ሲተኛም በቅዥት ስለሚያሰቃየው ፋኖ እንዲጠፋለት ዲያቢሎስ የሚተኛበትን አመድ ሲቅም የሚያድር ከንቱ ፍጡር ነው፡፡
ታሪክ እንደሚያውቀው በኢትዮጵያውያን ልብ፣ ዓይምሮና በዘር ሰንሰለታቸው (ዲ ኤን ኤ) ሥር ሰዶ የኖረው ኪነ-ፋኖ የተስፋፊዎችና የቅኝ ገዥዎች ወሽመጥ በተደጋጋሚ ሰብሮ ወደ አፍሪካ፣ ኤስያና ደቡብ አሜሪካ በመስፋፋት የቀጥታ ቅኝ ተገዥነትን እርኩስ መንፈስ ጠራርጎ ያስወገደ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡
ኪነ-ፋኖ በፍረንጅ አቆጣጠር በ1952 ዓ.ም ወደ ኬንያ ተዛምቶ የነፃነት ሰራዊት የፈጠረ መንፈስ ነው፡፡ ኪነ-ፋኖ ወደ ደቡብ አፍሪካ ነጉዶ እነ ፋኖ ማንዴላንና ስቲቭ ቢኮን ያጠመቀ ፀበል ነው፡፡ ኪነ-ፋኖ ወደ ዝምባቡዌም ተጉዞ ወህኒ ቤት እያሉ 6 ዲግሪዎች የተቀበሉትን ፋኖ ሙጋቤን ኮትኩቶ ያሳደገ ብርቱ ኃይል ነው፡፡ ኪነ-ፋኖ ወደ አሜሪካም በሮ እነ ፋኖ ማልካም ኤክስንና ማርቲን ሉተርን ኪንግን ያጠመቀ ሃይማኖት ነው፡፡ የኪነ-ፋኖ ሃይማኖት ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ኤስያና ላቲን አሜሪካ ተስፋፍቶ በቢሊዮን የሚቆጠርን ሕዝብ ተቀጥታ ባርነት ያላቀቀ የነፃነት እስተንፋስ ነው፡፡
በሃያኛው ክፍለ ዘመን ኪነ-ፋኖ ዓለም አቀፍ የነፃነት ሃይማኖት ለመሆን ስለበቃ በዩኔስኮ ተመዝግቦ እንንክብካቤ ሊደረግለትና ሊስፋፋ ይገባል፡፡ በትውልድ አገሩ በኢትዮጵያ ደግሞ በየዓመቱ የሚከበር በዓል፣ ገድሉን የሚዘክር ሐውልት፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ጤና ተቋም፣ መንገድ፣ ከተማና መንደር ሊሰየምለት ይገባል፡፡ ኪነ-ፋኖ የነፃነት መንፈስንና ሃይማኖት ሰለሆነ እረኛው በዋሽንቱ፣ ዘፋኙ በክራሩና በመሰንቆው፣ ዘማሪው በከበሮና በጸናጽል ሊያወድሰው ይገባል፡፡ ኪነ-ፋኖን ልጃገረዶች በአንገታቸው፣ ጎበዛዝትም በክንዳቸው ሊነቀሱት ይገባል፡፡
ኪነ-ፋኖ በሳጥናኤል የሚመራውን የቅኝ ግዛት ውቃቤ አርክሶ አብዛኛውን የዓለም ሕዝብ የነፃነት አየር እንዲተነፍስ ያደረገ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህ ኪነ-ፋኖ እንደ ጥምቀት በቅርስነት ተመዝግቦ በእየዓመቱ በእልልታና በደስታ በዓለም መከበር ያለበት የነፃነት ሃይማኖት ነው፡፡
ጥር ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.