የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ (ቃላቱ ያስቁኛል) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ጉባኤ [ኮሚሽን] ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265 /2014 ማጽደቁን ተከትሎ ለዕጩነት የሚቀርቡ ማሟላት የሚገባቸውን ዘጠኝ መስፈርቶች አስፍሯል። የኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት [Ethiopiawinnet Council for the Defense of Citizen Rights] እንዳካፈለን መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው።
1/ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፤
2/ ሁሉንም ሃይማኖቶች፣ የተለያዩ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን በእኩል ዐይን የሚያይ፤
3/ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ፤
4/ ለአገራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋፅዖ ሊያበረክት የሚችል፤
5/ መልካም ሥነ-ምግባርና ሰብእና ያለው፤
6/ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው፣
7/ በከባድ ወንጀል ተከስሶ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያልተላለፈበት ፤
8/ የኮሚሽኑን ሥራ በአግባቡ ለመሥራት የሚያስችል የተሟላ ብቃት ያለው፤
9/ ሙሉ ጊዜውን ለኮሚሽኑ ሥራ ለማዋል ፈቃደኛ የሆነ።
የሚሉ ናቸው፡፡
በነዚህ እላይ በተዘረዘሩት በያንዳንዱ መስፈርት ብዙ ሊባል ይቻላል። እኔ ግን በሁለት ብቻ ላተኩርና የቀሩትን ለሌሎች ልተዋቸው እወዳለሁ። ካልሆነም ሌላ ጊዜ እመለስባቸዋለሁ። እነዚህ ቀልቤን የሳቡት ሁለቱ መመዘኛዎች በቁጥር አንድና ሁለት የተዘረዘሩት ሲሆኑ፣ ሁለቱም ልዩ ትኩረት ይገባቸዋልና ቢሻሻሉ ይመረጣሉ ብዬ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እንዲያስብበት በሚል መንፈስ ወደዚህ ድምዳሜ ያደረሱኝን ምክንያቶች በአጭሩ አቀርባለሁ።
አንደኛ፣ “የተለያዩ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና፣ ሕዝቦችን በእኩል ዐይን የሚያይ” የሚለውን አገላለጥ ይመለከታል። እነዚህ ቃላት ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)” የተወረሱ የቃላት ቅርሶች እንደሆኑ አያጠራጥርም። ኢሕአዴግ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው፣ አሁን አሸባሪና ጁንታ በተባሉ ቅጽሎች የሚጠራው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ [ሕወሓት}፣ በአጭሩ የ”ወያኔ” ሥራ አስፈጻሚ አካል በመሆኑ ሲሆን፣ እኔም በተለያየ ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ተችቼበታለሁ። ወያኔ በበኩሉ፣ በምንም መልክ ሳይረዳቸው፣ ከሺዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹና ሰባዎቹ የከፍተኛ ተቋማት ግራዘመም ተማሪዎች የወረሳቸው ቃላት ናቸው። ተማሪዎቹም ቢሆኑ ምንም በቅጡ ሳይገነዘቡትና ሳይገባቸው ከሩሲያኖቹ ከሌኒንና ከእስታሊን የቀዱት እንደሆነ መርሳት የለብንም። በኔ ዕይታ፣ ይኸንን ዐዋጅ የጻፈ አካል፣ የወያኔን ርእዮተ ዓለም እያራመደ እንዳለ፣ አለበለዚያም የአስተሳሰቡ ሰለባ ሁኖ እንደቀረ አያጠራጥርም። እነዚህን ወቅታቸውና ጥቅማቸው ያለፈባቸውን ቃላት ማንበብ የሚያገናዝበን ነገር ቢኖር፣ ወያኔን በጦር ሜዳ እየተፋለመ ያለው መንግሥት፣ ከድርጅቱ አስተሳሰብ መላቀቅ የቻለም የሚፈልግም አይመስልም ቢባል ከሐቅ የራቀ አስተያየት ነው ማለቱ ያስቸግራል። ወያኔ እንደግዙፍ ኀይል ከምድረ ገጽ አካትቶ ቢጠፋም፣ አስተሳሰቡ ሕያው ሁኖ ከቀጠለ፣ የማታ ማታ ድሉ ዋጋቢስ እንደሚሆን እምብዛም መመራመር አይጠይቅም።
“ሞኝ የተከለውን ብልህ አይነቅለውም” የሚል ብሂል አለ። ሕወሓት በብድር ያመጣቸው ብዙ የቃላት ቅራቅንቦ የየቀኑ ንግግራችን አካል ሁነው እንደምንመገበው ምግብ ከአሳባችን ጋር ተዋህዷል። ትርጉሙ ምን እንደሆነ እንኳን ከማያውቀው ከተራው መሃይምን እስከአገሪቷ የከፍተኞች ተቋማት የቋንቋ መምህር ሳይቀሩ፣ እነዚህን ቃላት እንደበቀቀን ሲያንቦቀቡቋቸው ይታያሉ። የአገሩ ጠቅላይ መሪና ከፍተኞች ባለሥልጣኖች ጭምር ቀን ተሌት ይደጋግሟቸዋል። ሐሰተኛ አሳብ ገና በእንቦቃቅላነቱ ካልተቀጨና ካልከሰመ በስተቀር፣ ለአገር ጠንቅ ብቻ ሳይሆን ከጦር የከፋ ውድመት ሊያደርስበት እንደሚችል ታሪክ በተደጋጋሚ ያስረዳናል። ስለዚህ ወያኔ ባወረሰን ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች በሚሉት ቃላት ሕዝባችንን የመከፋፈል አባዜ በቅጽበት ካልተስተካከሉ፣ የጠነሰሳቸው ድርጅት ከሥረመሠረቱ ጠፍቷል ተብሎ ቢታመንም፣ ጊዜውን ጠብቆ ዐመድ ከሆነበት እንደፍንቅስ ወፍ ሕይወት ዘርቶ በመነሣት አገሪቷንና ሕዝቧን በማያባራ ጦር እንደሚያተራምስ አያጠራጥርም።
የሚገርመው ደግሞ ዐዋጁን ያወጣው አካል የዐረፍተነገሩ የርስበርስ መጣረሱን ለመገንዘብ አለመቻሉ ነው። ዐዋጁ ባንድ በኩል የኢትዮጵያን ሕዝብ በሦስት ማለትም፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና፣ ሕዝቦች በሚባሉት፣የጐሣ ደረጃዎች በተፋሰስ ይደረድራቸዋል። ሁላችንም እንደሚናውቀው፣ ሦስቱ አካላት እኩል አይደሉም። ምክንያቱም “ብሔሮች” የመጀመርያውን ከፍተኛ ማማ ሲይዙ፣ ቀጥለው “ብሔረሰቦች”፣ በመጨረሻም “ሕዝቦች” በዝቅተኛው በሦስተኛ ዕርከን ይመደባሉ። ዐዋጁ በዚህ መልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ በግልጥና በጭፍኑ እየከፋፈለ እያለ፣ በሌላው በኩል ለምክክር ቤቱ በእጩነት የሚቀርብ ግለሰብ፣ እነዚህን ሦስቱን ማለትም “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን”፣ “በእኩል ዐይን የሚያይ” መሆን አለበት የሚል መስፈርት አስቀምጧል። ማንኛውም አስተዋይ አንባቢ አመራሩ እየተዋጋ ካለው ወያኔስ የሚለየው በምንድር ነው፤ የገዢነቱን ሥልጣን በእጁ በመያዙ ካልሆነ በስተቀር ሲል ሊጠይቅ ይገደዳል።
ለባለጤናማ አእምሮ ሰው፣ ቊጥሩ ምንም ያህል አነስተኛ ይሁን የሚናቅ ሕዝብ የለም። ሁሉም እኩል ነው። ርግጥ ነው ወንጀለኛ ሕግ አንዱን አናሳ፣ ሌላውን አብላጫ አድርጎ ያያል፣ ይከፋፍላልም። ይኸ ዐይነት ክፍፍል ውጤቱ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ደግሞ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በአገራችን በወያኔና በአንዳንድ ክልሎች የተፈጸሙት አሰቃቂና ኢሰብኣዊ ድርጊቶች ምስክር ናቸው።
በግልጥ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር የበላይነትና የንቀት መንፈስ የተጠናወተው ብቻ ነው አንዱን ሕዝብ ከሌላው የሚያተናንሰው። የሰው ትንሽ እንደሌለ ሁሉ፣ የሕዝብም አናሳ የለምና። ስለዚህ የቃላቱ ባላቤት የሆነው ወያኔ እንኲትኲቱ ከወጣ በኋላ፣ ድርጅቱን ሽብርተኛ ብሎ በፈረጀው በአገሪቷ ሸንጐ አፍ ተመልሰው ሲደገሙ ምን ይባላል። እየተሰበከ ያለውስ ለውጥ የይስሙላ ነው ከማለት ውጭ እንዴት ሊገለጥ ይችላል። የኢትዮጵያን ሕዝብ በተዋረድ በሦስት ደረጃ እየከፋፈለ፣ የምክክር ቤቱ ዕጩ ሁሉንም “በእኩል ዐይን የሚያይ” መሆን አለበት ማለትስ ለስብከትና ለወግ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳው ምንድር ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው በማለት አንደኛውን ነጥቤን አበቃለሁ።
ሁለተኛው ነጥቤ፣ የተመራጭ “ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ” መሆን አለበት የሚለው ነው። አሁን ባለው ሕገመንግሥት መሠረት፣ ይኸ ነጥብ የኢትዮጵያ ግዩራንን (በፈረንጆች ቋንቋ “ዲያስጶራ”) የሚያካትት አይመስልም። በታሪክ መነጽር ስንመለከት፣ ግዩራን ከአገራቸው ፈልሰው ማንነታቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ናቸው። በዚህም ማንነታቸውን ትተው ጥገኝነት የሰጣቸውን አገር ዜግነት ከወሰዱት ስደተኞች ይለያሉ። ይሁንና አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን አጣምረው የያዙት ሁለቱንም እንደሆነ ይታመናል። ልክ ዐሥራሁለቱን ነገዶች እንደሚያቅፈው እንደአይሁድ ግዩራን፣ የኢትዮጵያም እንደዚሁ የመላዋ አገሪቷን ጐሳዎችንና ነገዶችን ያጠቃልላል።
ከነዚህም መካከል፣ ለውጡን ተከትሎ ማንነታቸውን ይዘው የቈዩት ወደአገርቤት ሲመለሱ፣ የቀሩት አብዛኞቹ ስደተኞች [ዜጎች] ሲሆኑ፣ እነሱም በያሉበት የኢትዮጵያ አገራቸው አምባሳደሮች ሁነው ስሟን እያስጠሩና እየተከላከሉላት፣ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው እየረዷት ይገኛሉ። በቅርቡ በመላው ዓለም የታየው “ያብቃ” የተባለው እንቅስቃሴ፣ የኢትዮጵያ ግዩራንን ከፍተኛ ተፅዒኖና ሚና ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ አገራቸው ጋር ያለው ትስስር ከመንፈስ ዐልፎ የአካልም እንደሆነ ያሳያል። በኢትዮጵያ የሚደርሰው ደስታም ሆነ ጥቃት በቀጥታ እነሱንም እንደሚነካቸውና እንደሚያስተሳስባቸው ያረጋግጣል።
ይሁንና፣ አሁን ባለንበት ወቅት ግዩራን በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ ለጥቅም ብቻ እንደሚፈለጉ ጥገቶች ሁነው ከመታየት በዘለለ ሌላ ፋይዳ የላቸውም። ሁሉም ባይባል በርካታው ግዩር የትውልድ አገሩ ዜጋ አይደለም። ይኸም ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያን ባለፉት ዐምሳ ዓመታት የገዟት መሪዎች የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ የተራቈቱ በመሆናቸው ነው ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያዊነት በታሪክ የሚታወቀው፣ በአገሩ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመንና ባሕር ተሻግሮ፣ በባሕርዩ ሁሉንም በማቻቻል አቅራቢ፣ ዐቃፊና አስተናጋጅ በመሆኑ ሲሆን፣ ባለፉት ዐምሳ ዓመታት የታየው ግን ከዚህ መንፈስ ባፈነገጠ መለዮው ነው። ይኸንን ለመረዳት ሕገመንግሥታቱን ማየቱ ብቻ ይበቃል። ከቅድመደርግ የነበረው የንጉሠነገሥታቱ ሕገመንግሥታት “በንጉሠነገሥቱ መንግሥት ውስጥ ወይንም በውጭ አገር በዜግነት የሚኖር የኢትዮጵያ ተወላጅ ሁሉ በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” ሲል፣ ግዩራንም በአገር ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ ጋር እኩል ዜግነት እንዳላቸው ያረጋግጣል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ደግሞ እስካሁን ከታዩት ሕገመንግሥታት ሁሉ የተሻለ ነው ማለት የሚቻለው ከወታደሩ መንግሥት ግልበጣ ዋዜማ ላይ በሕገመንግሥታዊ ጉባኤ የተረቀቀው የሺዘጠኝመቶ ስድሳስድስት (1966) ዓ.ም. መሆኑ አይካድም። በዚህ ሕገመንግሥት የአገሩን ታሪክ፣ የሕዝቡን ባህል፣ ችግርና እሮሮ በቅጡ የሚረዱት እጅግ በርካታ ዐዋቂዎችና የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት ስለነበር፣ ከፍተኛ ጥንቃቄና ዐላፊነት በተመላበት መንፈስ የተዘጋጀ እንደሆነ ይታወቅል። የሥልጣን ጥመኛው ደርግ ባያጨናግፈው ኖሮ፣ ለአገር ልማት፣ ለሕዝብ ዕድገት፣ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር በማለት በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የሕገመንግሥትነት ብርሃን ሳያይ፣ በረቂቅነቱ ቢቀጭም፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የአገሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን መሆኑን ያረጋገጠው እሱ ብቻ ነው።
ይኸ በጉባኤው የተረቀቀው ሕገ መንግሥት፣ ዜጋ “በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” ይላል። ደርግ ይኸንን የተካው በተለመደው በኮሙኒስቶች ማማለያ ሕዝቡን በሁለት መደብ ከፍሎ፣ አንዱን ሠርቶ ዐደር፣ ሌላውን መዥገርት/አቈርቋዥ ብሎ ሲያበቃ፣ ዜግነቱን አጠቃልሎ ያስረከበው ለሠርቶ ዐደሩ ብቻ ነበር። ከደርግ ሥልጣኑን የተረከበው ወያኔ በበኩሉ የደርግ ሕገመንግሥት እሱ ለቆመበት ዓላማ እንደማያዋጣው ሲያውቅ፣ ጨዋታውን ቀይሮ፣ የኮሙኒስቶቹን ሌላውን አጉል መፈክር በመጠቀም፣ የአገሪቷ ሥልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ናቸው ይለናል። አገርወዳድ የሆነ ማንኛውም ኩሩ ኢትዮጵያዊ፣ በዚህ ከባሕርማዶ ከተበደረ የቃላት ጨዋታ መቀጠል ያለበት አይመስለኝም። የ“ያብቃ’ (No More) ክተት ዐዋጅ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁኝ።
የወያኔና የኦነግ ፊታውራሪዎቹ የነበሩት ግራዘመም ተማሪዎችም ሆኑ እነዚህ ሁለቱ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ያመጡት ከፍተኛ ዕዳ በማንነታችንም ሆነ በታሪካችን እንዳንኮራ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንድናፍርበትም ጭምር ነው። የተፈጠሩበት ዘመን ምዕራባውያንን ያማከለ ነጭዘር-ተኮር ስለነበር፣ እነዚህን ቃላት ከነሱ ቢዋሱ ምንልባትም ብዙዎቻችንን አይገርምም። የሚያሳፍረው አሁን መላው ዓለም ከአውሮጳ ተኮር የአስተሳሰብ ቅኝ ግዛት ራሱን ነፃ እያወጣ ባለበት ወቅት፣በነዚህ ድርጅቶች ዘንድ አለኀፍረት መቀጠሉ ነው። የኛም ቢሆን ከፍተኛ ችግራችን በዚህ በወያኔና ኦነግ ርእዮተ ዓለም ትረካ ዙርያችን በሙሉ መከበቡ ነው። ስለዚህም ቅርሳቸውን ከአእምሯችን ፍቀን እስካልጣልን ድረስ ራሳችንንና ታሪካችንን በሚዛናውነትና በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ዐይነ ልቦና ልናየው ልንቀርበውና ልንፈርደው እንቸገራለን ብቻ ሳይሆን አንችልምም።
የደርግም ሆነ የወያኔ ሕገመንግሥት፤ ሁለቱም የኢትዮጵያዊነት ተጻራሪዎች ናቸው። የወያኔ ግን ከደርግም የከፋ ነው ማለት ይቻላል። የደርግን መንግሥት የገረሰስነው እኛ ነን ባዮቹ እነዚህ ሁለቱ ማለትም ወያኔና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር [ኦነግ]፣ የኢትዮጵያን መሬትና ሕዝብ ተቃርጠው አላንዳች ዕፍረት የአንበሳውን ድርሻ ለራሳቸው ወስደው ሲያበቁ፣ ያደረጉት ነገር ቢኖር ይዞታቸውን በሕግ ማረጋገጥ ነበር። ስለዚህ አሁን ያለን ሕገመንግሥት ቅርጫቸውን ለመጠበቅ ሲሉ፣ ወያኔ በደደቢት በረኻ አርቅቆት፣ ኦነግ ያጸደቀው እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሳተፈበት ወይንም እንደሕዝበ እስራኤሉ በደብረ ሲና ላይ ከሰማይ የተገለጠ በእብነበረድ የተቀረጸ ጽላተ ሙሴ አይደለም። ሁላችን እንደምንረዳው፣ ሕግ የተፈጠረው የሰውን ልጅ ለማገልገል ሁኖ ሳለ፣ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት የቆመበት ዓላማ፣ ሁለቱ የኢትዮጵያ አንድነት ጠላቶች ማለትም ወያኔና ኦነግ ለጠነሰሱት ደባ ማመቻቻ ነው። ስለዚህም ነው አወናባጆች ቃላትን በመጠቀም፣ የኢትዮጵያ ባለቤት አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን፣ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ናቸው እያለ ያለው። በነዚህ ቃላት መሠረት ባለቤቶቹ ብዙዎች ቢሆኑም፣ በርግጥ ግዩራን በነዚህ ውስጥ አልተካተቱም።
የሚቋቋመው ብሔራዊ ምክክር ጉባኤ (ኮሚሺን) ከሺ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ስድስቱ ሕገመንግሥታዊ ጉባኤም ሆነ ከፊተኞቹ ብዙ ነገር እንደሚማር ይጠበቃል። ከነዚህም አንዱ የግዩራን ዜግነት ጉዳይ መሆን ይገባል ባይ ነኝ። አብዛኞቹ ግዩራን አገራቸውን ሊለቁ የበቁት ተገድደው እንጂ ወድደው እንዳልሆነ አያጠራጥርም። አሁን እየተካሄደ ባለው ለውጥም ከፅንሰቱ እስከምልዐቱ፣ ከልደቱ እስከዕርገቱ ግዩራን ከፍተኛ ሚና ተጫውተበታል። ስለዚህ የአገራቸውንም የወደፊት ዕድልና ዕጣፈንታ በመወሰንና ፈሩን በመተለም ድርሻቸውንና ግዴታቸውን እንዲወጡ ተገቢ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባልና በጥኑ ቢታሰብበት መልካም ነው።
ግዩራንም በበኩላቸው፣ለዘመናት የኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መለዮ የሆነውን ብርቅ ቅርስና ውርስ የነበረውን የዜግነት መብታቸውን እንዳይነፈጉ የማረጋገጥ ዐላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው መርሳት የለባቸውም። የግዩራን የዜግነት መብት በበርካታ አገሮች የተከበረ እንደሆነ እናውቃለን። ከብዙዎቹ በጥቂቱ እንደእሥራኤል፣ ፈረንሳይና፣ ግኒ የመሳሰሉትን አገሮች እንደአብነት መጥቀስ ይቻላል። ይሁንና ከሁሉም በፊት ፈርቀዳጇ አገራቸው ኢትዮጵያ መሆኗን በመገንዘብ፣ የኢትዮጵያ ግዩራን ከዜግነት ዝቅ ያለ ማንኛውንም መደራደርያ ከትውልድ አገር መንግሥታቸው ላይቀበሉ ዐብረው በመቆም መብታቸውን ለማስከበር መታገል ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ።
መንግሥትም የአገራቸውን ታሪካዊ መብት የመንፈግ ሥልጣን እንደሌለው በመገንዘብ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ርስበርስ በሚጣረኑ አንጃዎች መከፋፈል አቁሞ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖር ሁሉ በአንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ” መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ መደንገግ እንደሚጠበቅበት ይረሰዋል ብዬ አላምንም። ይኸንን ዐላፊነቱን ካልተወጣ፣ ነገሩ ታጥቦ ጭቃ እንደሚባለው እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሲመቸው ወያኔንና ሕጉን እንደሚያቆለጳጵስ፣ ካልተመቸው ደግሞ ሲያወግዝ እንደሚታይ ሁሉ፣ ግዩራንንም በተመሳሳይ መልኩ ሲበርደው ዕቀፉኝ፣ ሲሞቀው ልቀቁኝ እያለ ለፖለቲካ ቁማሩ እየተጠቀመ እንዳለ አይካድም። ይኸም ከትዝብትና ከማወናበድ ውጭ ምንም ለማንም የሚበጅ አይመስለኝም። የሚከበረው ወያኔና ባልደረቦቹ ያጠፉትን ኢትዮጵያዊነት መልሶ ለማቋቋም ቢተጋ፣ የግዩራንንም ታሪካዊ ዜግነታቸውን ሳያመነታ ቢያጸድቅላቸው ነው።
ኘሮፌሰር ኀይሌ ላሬቦ