ፍቅር ይበልጣል ([email protected])
ከዚህ በታች ያለውን መጣጥፍ የጻፍኩትና በዚይን ጊዜ ለተከፈቱ ድረገፆች ልኬ ለንባብ የበቃው የዛሬ 11 ዓመት በ2003 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ድረገፆችን ስጎበኝ በአንደኛው ላይ አየሁትና አነበብኩት፡፡ አንብቤም ልተወው አልፈለግሁም፡፡ ያኔ ምን እንዳልኩና መጣጥፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ነጥቦች አኳያ ከዚያን ጊዜ ወዲህ እስካሁን ድረስ በሀገራችን ምን ምን እንደተከናወነ ማገናዘብ ለሚፈልግ ሰው አንዲትም ቃ
ሳልጨምር ሳልቀንስ አሁን ደግሜ ላክሁት፡፡ ምንም ነገር እንዳልጨመርኩና እንዳልቀነስኩ ለማረጋገጥ በርዕሱ ገብቶ የዱሮውን ከዚህኛው ቅጂ ጋር ማመሳከር ይቻላል፡፡ ጊዜ ያለው ሰው ያንብበው፤ ባያተርፍበት አይከስርም፡፡ መልካም ንባብ፡፡
እንዴት እንደከረማችሁ እያወቅሁት ‹እንዴት ከረማችሁ› ብዬአልጠይቅም። ሲዳሩማ ልቀስወግመሆኑእዬቀረ እንደመምጣቱ ሁሉሲገናኙ ሰላምታ መለዋወጥም እንደዚያው እየሆነነው። ምንአዲስነገርአለና? ጊዜማጥፋትብቻ! ሁሉም ነገር ያውነውብቻ ሳይሆንያውመሆንም እያቃተው ከሴከንድወደሴ ከንድ እየባሰበት ነው የሚሄደው- በኢትዮጵያውስጥየሚታየውነባራዊሁኔታበተለይ- በዓለምዙሪያደግሞባጠቃላይ።ተግባባን?
‹ዘመኑ ነው› ብለን ብቻ የምንተወው ጉዳይ ግን አይደለም። እኛም ነን። ለአንድ ጥትፋም ሆነ ልማት የተራ ዜጎች አስተዋፅዖ ቀላል እንዳልሆነ የዐረብን ምድር የለውጥ ንፋስና ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መመልከት ይገባል።
መልካም ነገር ልጽፍ አለመነሳቴን በመግቢያዬ ሳትረዱ አትቀሩም – መልካም ነገር የሚባል ስለሌለ ሳይሆን በተለይ በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ክፉው ነገር አመዝኖ ስለሚገኝ ነው። አጻጻፌ የሥነ ጽሑፍን ውበትና ሥርዓት የተከተለ አይደለም። እንዲያ ቢሆን ቦታም ጊዜም አይበቃኝም። ስለዚህ በወፍ በረር ዕይታ ወደአእምሮየ ጓዳ የሚገባልኝን፣ ነገር ግን በተለይ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ የሚመለከታቸው ወገኖች ቢቃኙት ይጠቅማቸው ይሆናል ብዬ የምገምተውን ሃሳብ እንደወረደ ማስቀመጥን መርጫለሁ። አነሳሴ ለማንም ምክር ለመለገስ አይደለም። ምክር ዱሮ ቀረ። በዘመነ ዲያብሎስ ጥሩ ምክርን መካሪም ሆነ ምክርን ተቀብሎ ተግባር ላይ እሚያውል ሰው እንደሚያጥጥ መጽሐፉም ቀድሞውን ተንበዮታል። ስለዚህ ቀኑ እስኪደርስ ‹ጉድ ነው› እያሉ ከመቀመጥ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ያህል በትዝብት ዐምድ ሥር ተጠልሎ ቀኑን መጠበቅ ነው – ለቀኑ ለሚያበቃው። እንዲያም ቢሆን ከተለያዬ አቅጣጫ ሲታይ ቀኑ የደረሰ ስለመሆኑም መጠቆም አይገድም።
በአንድ ወይ በሌላ መልክ – በዓለማዊነት (Secularism) ወይም በሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት (Religious Fanatism/Fundamentalism) – አጠቃላዩ ዓለም የደረሰበት የሞራል፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሥነ ልቦና፣ የማኅበራዊና ሌሎች ፈርጀ ብዙ የጤናማ ማኅበረሰብ መገለጫ አውታሮች ከዘመን ወደ ዘመን በከፍተኛ ፍጥነት እየተበጣጠሱ መምጣት በሩቅም በቅርብም እየታዘብን በመሆናችን ያን ለጊዜው አንገባበትም። የሀገራችንን ሁለንተናዊ ክስረት ግን አሁን ትንሽ እንገርብ። አዲስ ነገር ስለማልናገር ነው ‹እንገርብ› ያልኩት በጫት ቃሚዎች የጫትን ዕጥረት መግለጫ ቋንቋ።
‹ዘመኑ የቅሌትና የውርደት ነው› ነው መነሻዬ። በመጀመሪያ አንድ ትውስታ ልናገር። የዛሬ አሥራ ስምንት ዓመት ገደማ ወደ አንድ በጊዜው የታወቀ የጠበል ቦታ እግሬ ወስዶ ይጥለኛል። መነኩሴው ከዙሪያ ጥምጥሙ ታማሚ ሠልፈኛ ተራው ደርሶት የሚገባውን ተጠማቂ በጠበሉም በመስቀላቸውም እያስለፈለፉ ሲያጠምቁ በአንደኛዋ ‹ሀ ሁ›ን የማያውቁ ማይም አሮጊት ላይ ሠፍሮ ሲጮህና ሲያስጮህ የታዘብኩት የአጋንንት መንፈስ እስከመቼውም አይረሳኝም። ሌላ ሌላውን ትቼ የመሰጠኝን ክፍል ብቻ ልግለጽ።
አሮጊቷ ላይ የሠፈረው መንፈስ፤ ይቺን አገር ለማጥፋት ከአሜሪካና ከአውሮፓ ተጠራርተን መጥተናል። ዕወቁት ከእንግዲህ ማንም አይችለንም። … ክርስትና ሃይማኖት በየሌሊቱ በደወልና በቃጭል በዜማና በጸሎት አላስቆም አላስቀምጥ አለን። ስለዚህ ተሰባስበን መጥተንባችኋል። ዕድሜ ለልጆቻችን- እነሱ የልባችንን ያደርጉልናል። ይታዘዙናል እንታዘዛቸዋለን። ከቃላችን ዝንፍ አይሉም።
አጥማቂ መነኩሴ፤ እነማን ናቸው ልጆቻችሁ?
አሮጊቷ ላይ የሠፈረው መንፈስ፤ የሾምናቸው ልጆች አሉን። እንደልባችን ያሻንን እናዛቸዋለን። የፈለግነውን ያደርጉልናል። እኛም እንደፈለጉ እንዲሆኑ ሁሉንም ነገር ሰጥተናቸዋል።
አጥማቂ መነኩሴ፤ ምንድን ነው የሰጣችኋቸው? ምንስ ሥልጣን አላችሁ ለመስጠት?
አሮጊቷ ላይ የሠፈረው መንፈስ፤(መንፈሱ በማሾፍ ዓይነት ይስቃል) ሥልጣን አለን። ለኛ ለተገዛ ዓለምን ሁሉ እንሰጠዋለን፤ [እንዲያዝባት እንዲናዝባት- ይቺኛዋ የኔ ሐረግ ናት] ሥልጣንና ሀብት እንሰጣቸዋለን። የሚቃወሟቸውን እናጠፋላቸዋለን፤ የሚሸረብባቸውን ሤራ አስቀድመን እየተከታተልን እናከሽፍላቸዋለን። ከውጭም ዕርዳታና እገዛ እንዲያገኙ ወዳጆቻችንን ከጎናቸው እናሰልፍላቸዋለን። … አትጨቅጭቀኝ አቦ … በፈጠረህ አታቃጥለኝ፤ ሸኘኝ። እንደልማዴ ጮሄ ልሂድበት፤ መልቀቁን አልለቅም። ያሳደግሁዋትን? እንዴት ብዬ? ልቧ ላይ ከሕጻንነቷ ጀምሬ ቤቴን ሠርቻለሁ – የኔ ናት አልለቃትም። ባታውቅ ነው እንጂ ሁሉም በድብቅም በግልጽም እኛኑ አምላኪ ነው። ያንተ ማርያም ምን ትሰጣቸዋለች መሰለህ? ሥልጣኑም ሀብቱም የኛው ነው። በርግጥ አንተ እምታመልከው አምላክ የኛም ፈጣሪ መሆኑን እናውቃለን። ግን በሰማይ እንጂ እዚህ አንዳችም ነገር አያደርግልህም። ታቦት እሚስመው ሁሉ ከአንጀቱ እንዳይመስልህ። ብዙው ሰው ማተብ የለውም። ቢኖረውም የውሸት ነው፤ ከልቡ እግዜርን አያመልክም። ስለዚህ መጠቀሚያችን እናደርገዋለን። … ለዓላማችን መሣካት ሦስት ሰዎችን ሾመናል። ቄሱም ጳጳሱም የኛኑ ተልዕኮ አስፈጻሚ ናቸው። ቢጠመጥሙም አትመናቸው። የእናንተ እንዳይመስሉህ…
አጥማቂ መነኩሴ፤ እነሱ የሾማችኋቸው እነማን ናቸው?
አሮጊቷ ላይ የሠፈረው መንፈስ፤ታውቃቸዋለህ፤ ለምን ታደርቀኛለህ? ዋናው ልጃችን መለስ ዜናዊ ነው፤ሁለተኛም ሕዝቡን በሃይማኖቱ በኩል ገብቶ እንዲይዝልንና በቁሙ እንዲያበክትልን የሾምነው አባ ጳውሎስን ነው፤ ሦስተኛው ሀብታሙ ሰውዬ አላሙዲን ነው።…
አጥማቂ መነኩሴ፤ መቼ ነው ሰንኮፋችሁን ነቅላችሁ ከኢትዮጵያ የምትወጡት?
አሮጊቷ ላይ የሠፈረው መንፈስ፤ አሄሄሄ… የምን መውጣት፣ ድራሹዋን ነው የምናጠፋት። አሰቃይታናለች። እናሰቃያታለን። የምንወጣው ቀስ ብለን ነው። ማንስ ሊያስወጣን ቀድሞ ነገር? ሕዝቡን በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በኑሮ ዘይቤ ለያይተነዋል፤ እስከወዲያኛው ከፋፍለነዋል። ዕድሜ ለልጆቻችን። … እንዲያው ለወደፊቱ ብንወጣም በቀላሉ እንደማይሆን ዕወቅ፤ ሀገሪቱን የደም አበላ ውስጥ ከትተናት ነው ወደልጆቻችን ሥፍራ ወደ… የምንሄደው። እዚያ ለልጆቻችን መኖሪያ እያዘጋጀን ነው። እዚህ አላስቀምጥ ካሏቸው መሀል አገሩን አበጣብጠን በደም እያስዋኘን ልጆቻችንን በኛው ምሪት ባዘጋጁት ቦታ በሰላም እናኖራቸዋለን። የክፉ ቀን ባለዉለታዎቻችን ናቸው። እነሱን ባናገኝ ይህችን ሀገር ለማጥፋት በፍጹም አይቻለንም ነበር።… የምንወጣበትን ጊዜ ደግሞ ይህ ነው ብዬ አልነግርህም። በመጨረሻው ሁሉም ሲነቃብንና ሆ ብሎ ሲያምጽብን ግን መውጣታችን አይቀርም። ያ ጊዜ ታዲያ በቅርቡ ይሆናል ብለህ አታስበው። ገና ብዙ አሣር አለባችሁ…
ልጆቼን ጨምሮ ከምወደው ነገር ሁሉ ይለየኝ – ይህ ቃል በጆሮዬ የሰማሁት እንጂ ድርሰት እንዳይመስላችሁ። ጊዜው በመራቁ ምክንያት ቃል በቃል ላላስታውስ እችል ይሆናል፤ ከዚያች ማይም ሴት አንደበት ይወጣል ተብሎ በፍጹም የማይጠበቅ አነጋገር ስሰማ የተደገሰልን ድግስ ክፉኛ የሚያስጨንቅ እንደነበር ያኔውን ገብቶኛል። እስከዚህ ዘመን ይራዘማል ብዬ ግን አልገመትኩም ነበረ። ይሄውና ግፍና በደሉ ተጠናክሮ ከቀጠለ ሃያ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው።
ዘመኑ የቅሌትና ውርደት መሆኑን ማንም አያጣውም። መለስ ዜናዊ በአንድ ቃለ መጠይቅ ‹በመሠረቱ እኔ ሃይማኖት የለኝም፤ ሃይማኖት እንዲኖረኝ ብፈልግ ግን ጴንጤ ብሆን ደስ ይለኛል።› ብሎ መናገሩ ተዘግቦለታል። ይህ አነጋገሩ እንደኢትዮጵያዊ የሚያሳፍር ይመስለኛል። የዘቀጠው ትውልድ፣ በቁሙ የሞተው ትውልድ፣ በሞራል የላሸቀው ትውልድ፣ ከሀገሩ ባህልና ወግ የወጣውና ሀገርና ባህል አልባ ሆኖ አየር ላይ የተንሣፈፈው ትውልድ … ወደሥልጣን መውጣቱን በገሃድ የሚያውጅ የዕብሪትና የትምክህት አነጋገር ነው። ሃይማኖት የሌለው ሰው እንደባህላዊው ግንዛቤያችን ልጓም የሌለው ፈረስ ነው – አውሬ ነው- የሚፈራው ነገር ስለሌለው ልቅ ነው። መለስም እንደዚሁ ስድና መረን የለቀቀ ዋልጌ የሆነው ለዚህ ነው ማለት ይቻላል። እርግጥ ነው ሃይማኖት ያላቸው እየመሰሉ ከሃይማኖታቸው ቀኖና ውጪ የሚጓዙ እጅግ ብዙዎች አሉ – ብፁዕ አባታችንንና ብፀዓን ንዑዳን አባቶቻችነን ጨምሮ። (በወግ በማዕረግ ሳይሆን) ከቃለ ዐዋዲው ውጪ በሥነ ሥርዓቱ ሚስት አግብተው ልጅ እየወለዱ የሚኖሩ ሊቃነ ጳጳሳት አሉን እኮ! ስም እየጠራሁ መናገር እችላለሁ – ከቅርብ ጎረቤቴ እስከ ሩቅ ሐሳዩ መሲሕ አባቴ። ቅሌት ነው፤ ውርደት ነው። ስለዚህም ነው ሃይማኖት የጠፋችው። መለስ በአንድ ፊቱ ትክክል ነው። በሃይማኖት ስም ከሚያጭበረብር ከነአካቴው ‹ሃይማኖት የለኝም› ማለቱ ከነዚህ ጠፍተው ከሚያጠፉ – ማስነው ከሚያማስኑ – ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የተሻለ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም። ከውስጥ አርበኛ የለየለት ጠላት የተሻለ ነውና።
የዝቅጠታችን ደረጃ ለከት የለውም። የመለስ ዜናዊ ንግግር በአብዛኛው ከአንድ የሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር መሪ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ተራ ዱርዬና ማጅራት መቺም አይጠበቅም – እንደኢትዮጵያዊው የቀደመ ጨዋ የአነጋገር ባህል። ይህ ሰውዬ – መለስ ዜናዊ- እስካሁን በግልጽ ሲናገር ያልሰማሁት ብቸኛ ቃል(ከጓደኞቹ ጋር ሲሆን በዚያ ቃል እንደሚሰድበን አልጠራጠርም) ያቺን ከወደ ሐረርና ድሬዳዋ በኩል በምር ሳይሆን እንደአንደበታዊ የአካባቢ ልማድ የምንሰማትን ስብሃታዊ ቃል ብቻ ነው። ነፍሱን ይማርና ስብሃት ገ/እግዚአብሔርን ማለቴ ነው።
ስብሃት ስል ትዝ ያለኝ ነገር አለ። ብፁዕ አባታችን ሥርዓተ ቀብሩን የመሩበት አገባብ አልገባኝም። ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሪያሊዝም አቀንቃኝ ሆነች እንዴ? ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሄዶኒዝምና ኒሂሊዝም አጋፋሪ ሆነች እንበል? ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ብላ ብላ የናቹራሊዝም ጠበቃ ሆነች እንዴ? ዐድዋነትንና ከዚያ ጋር ሊያያዝ የሚችለውን ቀጭን የዝምድናም ይሁን ሌላ የትስስር ገመድ ለአሁኑ ስለማያስፈልግ እንዘንጋውና – አንድ የሃይማኖት ቁንጮ ሊመራው የሚገባው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዴት ዓይነቱን ነው? በኔ በኩል ሁሉንም ቀብሮች ቢሆን ደስ ይለኛል – የስብሃትንም ጭምር። ግን ያ ስለማይቻል በሀገር ደረጃ በጣም የታወቁና ለሀገርም አንዳች አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ዜጎች ሲያርፉ ፓትርያርክ ሥርዓተ ጸሎቱን ሲመራ ይታያል- እንደስካሁኑ። ጥያቄው ታዲያ ታዋቂነት ብቻ ሳይሆን በምን ታወቀ የሚለውም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ። አለበለዚያ አሣፋሪ ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል።
ጳጳሱ በመካነ መቃብሩ ሲገኝ በትልቁ እግዚአብሔርን እንደሚወክል ሲያንስ ደግሞ መሬት ላይ በሰው አምሳል በመካከላችን እየተመላለሰ ‹ቀኝ ዐይንህ ብታሳስትህ አውጥተህ ጣላት፤ ከሁለት ዐይኖችህ ጋር ወደሲዖል ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደገነት ብትገባ ይሻልሃል፤ ሴትን ዐይቶ በልቡ የከጀለ አመነዘረ…› እያለ የሰበከውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚወክል የታወቀ ነው። … እርቃንነትን፣ ዘማዊነትንና ሴሰኝነትን በደምሳሳው የመንግሥተ ሰማይን በር ጠርቅመው ከሚያዘጉ ታላላቅ ኃጢያቶች ውስጥ ቀንደኛ ቀንደኛ የሆኑት የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ እንደነ ቢዮንሴ ያሉ የጠፋቸው ዓለም ምሣሌ ሰዎችን እየጋበዘ ቤተ ክርስቲያንን፣ንዋየ ቅድሳትንና አልባሳትን የሚያረክስ ጳጳስ የተወለደባትና አድጎም ሃይማኖትን ሊያጠፋ የተሾመባት ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት – እንደፖፕ ሮደሪጎ የ15ኛው ክፍለ ዘመን የቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ጉደኛ የሆነ ሰውዬ።
ዘር ከልጓም ይስባል እንዲሉ የዚህ አስገራሚ ፍጡር አነጋገርም ልክ እንደ (አጎቱ ልጅ?) እንደመለስ ዜናዊ መሆኑ የቅጣታችን ጽናት እንዴቱን ያህል የገረረ እንደሆነ ፈጣሪም ሊቀጣን የሰነዘረብን ዱላ ምን ያህል ምሕረት የለሽ እንደሆነ ያሳያል። ትግሬነትን፣ አማራነትን ወይም በጥቅሉ ዘውገኝነትን ከዚህ የስሌት ማዕቀፍ ውስጥ አታስገቡብኝ አደራ። ይቺ ይቺ የወያኔ የማነጣጠያ ሥልት ናት። በበኩሌ እንኳንስ የሃይማኖታችን በር ከሆነችው ከትግራይ ይቅርና ክርስትና እምብዝም ካልተሰበከባቸው ከሙርሲና ከሐመር ነገዶች ፓትርያርክ ቢሾምልኝ ግድ የለኝም ብቻ ሳይሆን በደስታ ነው የምቀበል – ሕግን አክብረው የሚገቡትንም ቃል ሳያዛንፉ በተግባር እስካሳዩ ድረስ።
የመለስንና የባሕርይ አባቱን የወንበዴውን ጳጳስ (የሰውን ሚስት ዘርፎ ለይምሰልም አመንኩሶ በአጠገብ በማስቀመጥ የግቢ አዛዥ ናዛዥ ከማድረግ ያለፈ ውንብድና ሊኖር አይችልም) የአነጋገር ዕብሪተኝነትና አጠቃላይ ግብራዊ ዋልጌነት ዘርዝሮ መጨረስ በፍጹም አይቻልም – በነገራችን ላይ ኃጢያትን ሁሉም ያደርጋል – ‹ሁሉም በኃጢያት ሥር ወድቋል› የመባሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል በተግባራችን የምናረጋግጠው እውነት ነውና። በነሱ ግን አያምርም ብቻ ሳይሆን ያስጠላል። አርአያ መሆን ሲገባቸው እንደዚያ ሲሞላፈጡ – ወንጀልና ኃጢያትንም የዕለት ተለት ግብራቸው አድርገው በዚያም ዕኩይ ግብራቸው ሲኮፈሱ ስናይ ፈጣሪን ከማመን ይልቅ ልንከዳ የሚዳዳን አንጠፋም። ግን አሁንም ቢሆን እነሱና ፈጣሪ ለዬቅል መሆናቸውን መረዳት ለማይቸግረን ሰዎች እግዜርንና እነሱን በአንድ ሚዛን እንደማናስቀምጥ ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባል። እነሱ ግን አደራቸውን አለባበሳቸውንና አነጋገራቸውን ዐይተን የፈጣሪን ቦታ የምንሰጣቸው እንዳይመስላቸውና በትዕቢት እንዳያብጡ – ለማያውቃቸው ይታጠኑ።
አንድ ነገር ታወሰኝ። አንድ አዲስ ሙሽራ አማቶቹ ቤት ለቅልቅል ተጠርቷል አሉ። ለግልጽነቴ ይቅርታ። እናቱ ታዲያ የልጃቸውን እንደመለስ ወጳውሎሳዊ ዘርፍጤነት ያውቁ ነበርና ‹ አደራህን ልጄ – እንዳታዋርደኝ። ንግግርህ እንትን እንትን ስለሚል አማቶችህ ፊት ምንም ነገር እንዳታወራ› ብለው ያስጠነቅቁታል። ልጁም ቅልቅሉ ላይ ቃላቸውን ጠብቆ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን ጸጥ ይላል። አማት ይጨነቃሉ። ‹ተጫወት እንጂ ልጄ? ይሄም እኮ ቤትህ ነው – እኔም እናትህ ማለት ነኝ። …› እያሉ ቢወተዉቱት ጊዜ የተጣለበትን ማዕቀብ ለማሳወቅ በጅሎች የአነጋገር ዘይቤ እንዲህ ይላቸዋል፤ እንዲህ – ‹እማዬ ንግግርህ እንትን እንትን ይላል ስላለችኝ አልናገርም› ይላቸዋል። አማትም ወዲያው ‹ውይ የኔ ልጅ! ለኔስ ንግግርህ ማር ነው፤ ግዴለህም ተጫወትልኝና እንግዶቻችንም ደስ ይበላቸው› በማለት እንዲጫወት ያበረታቱታል። ሞኙ አማች የእናቱን ምክር ዘንግቶ ጨዋታውን ቀጠለ። አሁንም በጅሎች የአነጋገር ‹ለዛ› ነው፤ ‹እማዬ› ‹አቤት፣ አፌ ቁርጥ ይበልልህ!›። ‹ያ እዚያ ጋ ያለው ልጅ የማነው?› ‹ የኔ› ። ‹እዚያ ወዲያ ያለውስ?› ‹የኔ›። ‹እነዚያኞቹስ?› ‹የኔ›። እነዚህ ሁሉ ቤት ሙሉ ልጆች የርስዎ ልጆች ናቸው?› ‹አዎ፣ የኔ ናቸው።› …. በመጨረሻው ግን አስቀየማቸውና ‹እውነትም ከእንትንም እንትን› አሉት ይባላል። ዝርዝሩን ከሚያውቅ ሰው ጠይቃችሁ ተረዱ፤ እኔ የራሴ እንጂ የስብሃት ግርፍ አይደለሁም።
በነገራችን ላይ የስብሃት ተቃዋሚ አይደለሁም። አንድ ሰው ሌላን ሰው እስካልጎዳ ድረስ ምርጫዎቹን አከብራለሁ። መጥፎው ነገር ምርጫዬን ካልወደድክልኝ አጠፋሃለሁ የሚለው አምባገነናዊ የመለስና ቢጤዎቹ አካሄድ ነው። የተቃወምኩት ግን የሃይማኖት አባት የሚገኝበትንና የማይገኝበትን መቼታዊ ሥርዓት ማወቅ አለመቻሉ ላይ ነው – በኔ የግንዛቤ አድማስ መሠረት። በጥላሁን ገሠሠ ቀብር ላይ የመገኘታቸውን አግባብነት ለማጠየቅ ዕንባውን በመንታ በመንታ እያወረደ ያቀነቀነበትን የወሎን ርሀብ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው – ለአቃቂረኞች ክፍተት ላለመፍጠር ማሰቤን በሹልክታ ለመጠቆም ነው።
ቅሌትና ውርደት ቀለባችን ከሆነ ዋል አደር አልን እሚለው አይደል መነሻችን? አዎ፣ ከረምን እንጂ የምን ዋል አደር ብቻ።
የቅሌት መነሻው ሀፍረትንና ይሉኝታን ማጣት ነው። ሀፍረትና ይሉኝታ ከሀገራችን ከተሰደዱ እጅግ ቆዩ። ዘረኝነትም በሉት፣ ጎሠኝትም በሉት፣ ዘውገኝነትም በሉት በአሁኑ ሰዓት ዐይኑን አፍጥጦ ሊጨርሰን የተነሳ አውሬ እሱ ሆኗል። ለጠላቶቻችን ግርድፍ የደረጃ ሠንጠረዥ ማውጣት ካስፈለገ ቀጥሎ የሚመጣው የሃይማኖት ጉዳይ ይመስለኛል። ቀጥሎም ሙስናና ንቅዘት። እንደእውነቱ ከሆነ የሃይማኖት መጥፋትና ትክክለኛ እረኞች ሊሆኑ የሚጠበቁ አባቶች በሰይጣን ወጥመድ እየተጠለፉብን መጥተው መንጋው በተኩላዎችና በቀበሮዎች መነዳቱ ዋነኛው የመጥፋታችን መሠረት ነው። በጥፋት መርከብ ውስጥ የተሳፈረ ሰው ደግሞ እንኳንስ ለሌሎች መብት መከበር ሊታገልና ጥረት ሊያደርግ የራሱንም መብት ለማስከበር ቃል ሊተነፍስ አይችልም። ለዚህ ነው ሁሉም ተነካክቶ በመለስ አማርኛ ተጨመላልቆ በዝምታ ባሕር እየዋኘ የሚገኘው። በተለይ በዘር የመጠቃቀሙ ነገር ‹እግዜር መንበሩን ለወንበዴዎች አስረክቦ ተሠወረ እንዴ?› በሚያስብል ሁኔታ የሀገሪቱ የጥቅም ቦታዎች ሁሉ ለወያኔዎች ብቻ ተመድቧል። ይሉኝታ ብሎ ነገር አይሠራም።
ዐይናቸውን በጨው አጥበው በተጋቦት ወያኔ የሆኑ ወገኖችም ፍርፋሪ አላጡም። ነገር ግን ዘወትር በክትትል ቀለበት ውስጥ ናቸው- አይታመኑምና። የሥቃያችን ሁሉ መንስኤም አለመተማመን ነው። ነገሩ ‹የነብርን ጭራ አይዙም ፤ ከያዙም አይለቁም › እንደሚባለው ነው። ወያኔ የሁሉንም ጭራ ይዛለች፤ መልቀቋ ግን አይቀርም – ያኔ እርሷን አለመሆን ነው። የአሁኑ አያያዟ ሌልኛ ነውና። የሚገርማችሁ በጣም ትንሽዬ ነገር – በኢትዮጵያ ዘፈኑ ሁሉ ወያኔያዊ ሆኗል፤ ማንም ሳይገደድ ወያኔን የሚያስደስት የሚመስለውን ዘፈን ነው በየትምህርት ቤቱ፣ በየቡና ቤቱ/ሆቴሉ፣ በየመዝናኛ ቤቱ፣በየቲቪው፣ በየኤፍ ኤሙ፣ በየፋና ሬዲዮው፣ በየሱፐርማርኬቱ… የሚከፍተው። መለስንና ካድሬዎቹን ላለማስከፋት/ለማስደሰትም የሚዳክረው ወገን ያሳዝናችኋል። ራስን ያለመሆን አባዜ አዳሜን እግር ከወርች ጠፍንጎ ይዞት በየሠርጉና በየጭፈራ ቤቱ በቅጡ የማያውቅበትን ሥልት ለመጨፈር ሲፍገመገም ታያላችሁ – ለመምሰል። ነገ ደግሞ የዝንጀሮ ወይም የጦጣ ቅኝት ቢመጣ ማስመሰሉም ቅኝቱን ለውጦ ይቀጥላል። ከዚህ እንውጣ። ወደራሳችን እንግባ – ሳይመሽ።
መለስና አባቱ ጳጵሎስ ሰውን እንዴት ማኖ እንደሚያስነኩ ያውቁበታል። ወደቄራ እንደሚነዳ የዕርድ ከብት አሽከሮቻቸውን ጨውና ስኳር እያላሱ – የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ለራሳቸው የሥልጣን ማቆያነት በመጠቀም ማለት ነው – እንዴት ዕድሜያቸውን መቀጠል እንደሚችሉ፣ እንዴት ሀብትና ንብረት ማግበስበስና ማከማቸት እንደሚችሉ ተክነውበታል። ሃይማኖት ለጳውሎስ የሚፈልገውን ማድረጊያ መሣሪያ እንጂ ሌላ ማለት አይደለም። እንዲያውም ጳውሎስ በርህራሄያዊ አገላለጽ ‹ኤቲይስት›፣ ጨከን ባለ ተግባራዊ አገላለጽ ደግሞ‹ሴቴኒስት› ይመስለኛል። የገነትና የሲዖል ሰው በምግባሩ ያስታውቃል። ጣፋጭ ፍሬ በዛፉ ላይ እንዳለ ያስታውቃል እንዲል አስተምህሮ ክርስቶስ።
ጠፍተናል ጎበዝ! በሀገር ውስጥ ያለን ዜጎች ይህን በደንብ እናውቃለን። በሁሉም ረገድ ጠፍተናል። አጭበርባሪው በዝቷል። አላጭበረብርም የሚል ወገን ካለ እሱ በቁሙ እየሞተ ነው። ባጭሩ ይራባል፤ ይጠማል፤ ይታረዛል። ከዚህ ያነሰ ሞት ደግሞ የለም። በእምነት ጥንካሬህ፣ በሃይማኖት ጽናትህ፣በ‹አልሰርቅም› ባይነት አቋምህ የምትበላውና የምትለብሰው ቤተሰብህንም የምታኖርበት አንዳች ቁሣዊ ሀብት እስከማጣት ደረጃ መውረድ ደግሞ ከኪሣራዎች ሁሉ የሚከፋው ኪሣራ ነው። በንግድም ይሁን በፖለቲካና በሃይማኖት ካላጭበረበርክ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት አትኖርም፤ አራት ነጥብ(በገዢው ኃይል ቋንቋ)። ገዢው መደብ ሁሉንም ተቆጣጥሮ የሀገሪቱን ሀብትና ንብረት እንደፈለገው እያደረገ ነው።
ሕግና ሥርዓት የለም – አንድን ሰው ለማሰር በአንድ ቀን አዳር ሕግ ወጥቶ የይስሙላው ሕገ መንግሥት ሣይቀር ተሽሮ እንደሚያድር ሁሉ አንድ ሰው ወይም ቡድን ለመጥቀምም በቅጽበት ሕግ ቢጤ ሊወጣና ሊታወጅ ይችላል – ፓርላማ ብሎ ነገር የለ፤ የሚኒስትሮች ካቢኔ ብሎ ነገር የለ፤ የዳኞች ጉባኤ ብሎ ነገር የለ፤ ኅሊና ብሎ ነገር የለ… ሁሉም ነገር ለመለስና ከመለስ ጋር ሆኗል፤ ጫትና ሀሽሽ፣ ህልምና ቅዠት፣ ዊስኪና በጮማ የተደፈነ ባልጩት ቅንጭላት ሀገር እየመሩ በ‹ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሰዎች›ም ‹አይዟችሁ፤በርቱ፤ የክፍለ ዘመኑ የአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ ዴሞክራት መሪዎች ናችሁ…› ተብለው እየተሞካሹ … እኛም ለቁርጥ ቀን ያኖርናትን የለበጣ ሣቅ የሞት ሞታችንን አሟጥጠን በማውጣት እንደምንም በፍገት እየሳቅን አለን፤አሉ። አዜብና መለስ በሥልክ የሚያስተዳድሯት ሀገር ሆናለች – ይህች ትልቅ ትባል የነበረች ሀገር። ይገርማል። መለስ የፈለገው ነገር ሁሉ ይሆናል። ለይምሰል ያህል ሲባልም እንኳን በሕግ መግደልም ቀርቷል። ግድያው ሳይቀር በጠፍ ጨረቃና በሥውር ነው። የውሸት ችሎትም መሰየም ሳያስፈልግ እንደሰሞኑ የአቤ ቶክቻው ወንድም የትም ተገድለህ ተጥለህ ብትገኝ ጠያቂም ሆነ ተጠያቂ የለም።
አይ ሞኝነት! ሰው እንዴት ሰውን ከሜዳ ተነስቶ ይገድላል? ኧረ ይሄ ነገር ይታሰብበት። ሟች ኅያዋንን መግደሉን አሁኑኑ ያቁም። ለሚሸና መጠጥና ለ… የሞተ እህል ሲባል የእግዜርን ክቡር ፍጡር ሳያገባ ገብቶ ገድሎ መጣል ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ስንት ሺህ ዓመት ሊኖር? አንድ ዜጋ የሥልጣንም ይሁን የሀብት ሥጋት ከሆነ ሳያሰቃዩ አሥሮ ማኖር ሲቻል የምን ግድያ ነው? ፖለቲከኞች ወደታች ማደጋቸውን ትተው ወደላይ ማደግ እሚጀምሩት መቼ ይሆን? ሕግ አልባና መደዴ ይሁኑ – ግዴለም። ነገር ግን የላይኛውን ጫፍ- ሊታሰብ የማይገባው የመግደሉን ጫፍ ለምን ይይዛሉ? ነግ በኔን እንዴት አጡት? ‹በሠይፍ የሚገድሉ በሠይፍ ይገደላሉ›ን እንዴት ይረሱታል? ወይ ቂልነት!! ምን ይሻለን ይሆን? ሰው ማደግ ባይችል በነበረውና ባለው መኖር እንኳን ያቅተው? የመንግሥቱ በቀለማት ያሸበረቁ ሽብሮች – 69 እና 70 – በየት በኩል ዞረው በ21ኛው ክፍለ ዘመን አሁን መጡብን ጃል? በውነት መረገም ነው። ትልቅ መረገም!
ሀገር ውስጥ ሕይወት ደመ ነፍሳዊና በዕድል ሆንዋል። በአጭሩ በስግብግቦችና በሆድ አምላኪዎች ምክንያት ኢትዮጵያ የሲዖል አብነት ሆናለች። ሲዖልን መጎብኘት የሚፈልግ የውጪ ሀገር ሰው ካጋጠማችሁ ወደኢትዮጵያ ሂድ በሉት። ገዢም ተገዢም ልባምነትን የተነጠቁባት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት እያላችሁ ለዓለም ስበኩ። እውነቱ ይህ ነው። ሆዳምነት ነግሦ ወንድም ወንድሙን፣ እህት እህቷን፣ ልጅ ወላጅን፣ ጓደኛ ጓደኛን በቁም የሚገሸላለጡባት – የቀን ጅብ የወረራት ሀገር ኢትዮጵያ ናት ብላችሁ ዐውጁ – ኩነኔ የለባችሁም፤ እውነትን በመናገር ኩነኔ የለም። በሕዝብ ብዛትና በበሳል የሀገር ልጅ አመራር ዕጦት የምትሰቃይ፣ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ እሚልሰውና እሚቀምሰው አጥቶ በርሀብና በርዛት፣ በበሽታና በድንቁርና በስደትና በተለያዬ እንግልት በሚሰቃይበት ሁኔታ በጉቦ፣ በሙስናና በዝርፊያ ባለሥልጣኖቿን ቢሊዮኔር የምታደርግ ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ አለችላችሁ ብላችሁ ንገሩና መጥተው ይጎብኟት።
እንደአይቮሪያዊው ቲከን ጃህ አንድ አለሁልሽ የሚል አርቲስት፣ እንደበርማዋ ሳን ሱቺ አንድ በቅርብ ሆኖ አለሁልሽ የሚል የነጻነት አርበኛ፣ እንደኢራናዊቷ አዛር ናፍሲ አንድ ብሶቷንና እንግልቷን ገሃድ የሚያወጣ ደራሲ፣እንደቻይናዊው አይዌዌ በሥንክን እውነትን የሚገልጽላት ከያኒ፣… አጥታ የነበሯትን በሞት እዬተነጠቀች ምትኮች እንዳይኖሯትም ከመጸነሳቸውና ከመወለዳቸው በወያኔው የጥፋት ጀሌ የሚታረዱባት ቀፎዋን የቀረች ሀገር፣ ነፍሰ ሥጋዋ በኤሎሄ እየተንጠራወዘ የምትገኝ የድምጽ አልባ ሚልዮኖች ሀገር መሆንዋን ለዓለም ንገሩ – በኋለኛው ዘመን ምሥክርም እንዳይጠፋ። በጥቂት ወሮበሎች መቅኖ አጥታ ሁሉንም ነገሮቿን በሃያ ዓመታት ውስጥ የተነጠቀችና ከሕንጻዎችና ከጥቂት አስፋልት መንገዶች ውጭ ባድማ የቀረች ባዶ ሀገር መሆንዋን ሳታፍሩ ተናገሩ። ሰዎቿ ሕይወት የሌላቸው ግዑዝ ተንቀሳቃሽ ሆነው በቀን እንቅልፍ ድቃት የሚሰቃዩ ሀገር መሆንዋን ለሰማይም ለምድርም ለፍፉ። አንድ ሕግ ግን አለ – ሁሉም ሊያስታውሰው የሚገባ፤ በማንም በምንም የማይለወጥና የማይሠረዝ፤ እሱም ‹ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ› የሚለው ነው። ነገም ሌላ ቀን ነው – ቻው።