ዜጎች ከጭቆና ወደ ፍትህ የሚሸጋገሩበት ታሪካዊ ጉዞ ቤተ-መንግስት በተቀመጠው ሰመመን ተስተጓጉሏል።ለለውጥ ብለው የተሰቃዩ፣የታሰሩ ታጋዮችና መተኪያ የሌላትን ህይወት የሰጡ ሰማእታት ገድል ግለሰብን በማግዘፍ አባዜ ደብዝዞ ቢቆይም አልጠፋም።ራስን በራስ በማግነን ከገሃዱ አለም ባፈተለከ «ሰመመናዊ» መሪ ስር ወገን አሳሩን አየ።በነቂስ መፈናቀል፣ መታሰርና መሞት የመለመድ ገጽታን መያዛቸው አስጊ ነበረ። የአብይ አስተዳደር ተብሎ ነገን ማየት በማይቻልበት ፈታኝ ወቅት ላይ ነን።ከአብይ በሗላስ? የሚለው እውነታ ፈጦ መጥቷል።
ህዝብ በመስዋእትነት ለውጥን ዋጅቷል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ በእርቅና በድርድር ትገነባለች የሚለው ተስፋ የንግስና ቅዠትን ባነቆረ መንታፊ ተሰረቆ ቆይቷል።አሁን ያ ተስፋ ባለቤት ወደ ሆነው ህዝብ ለመመለስ የተቃረበ ይመስላል።ወገን የ50 አመታት የለውጥ ጥሙን ይቆርጣል ቢባልም «አሻግሬ ተብዬው» ወደ ዘመነ መኳንንት የኋልዮች መጓዝ ዳዳውና አገርን ፈተና ላይ ጣለ።ጨቋኝ የሆኑ ሙታን ሐውልቶችን በቤተ-መንግስት ተክሎ ትላንትን ቋመጠ።
አለም ከአብይ በኋላ የ110 ሚሊዮን ህዝቦች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል በሚለው መነጋገር ቢጀምርም የአራት ኪሎው ሰመመን ከወደቀችበት የማትነሳ ኢትዮጵያን ፈጥሮ ለማለፍ የሚያኮበኩብ ይመስላልና እንጠንቀቀው።
ጦርነቶች እንዴት ተጀመሩ የሚለው እሳቤ ጋር ቆሞ መቅረቱ ተገቢ አይደለም። ጦርነቶች እንዴት ይቁሙ? ከጦርነቶች በኋላ ህዝብ ወደ ቀድሞ የተረጋጋ ህይወቱ እንዴት ይመለስ? የሚለውን ማሰቡ ነው ብልህ የሚስብለው።
የይስሙላ ህጋዊነትን ካገኘ አንድ ወር የሞላው ሰመመኑ መሪ ነገሮችን ‹ከሳት ወደ ረመጥ› የሚቀይር እንጂ መፍትሔን የሚያመጣ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል።ህዝብ «ለዞረበት» ግለሰብ ብሎ መሰቃየቱና መሞቱ መብቃት አለበት።
ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ እስከ ሐያላንና ሌሎችም ወዳጅ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ከበባዎችን አጧጥፈዋል።የምጣኔ ሐብት ጫናው ተጠናክሮ ቀጥሏል።ጦርነቱ ካልቆመ የመንግስታቱ ድርጅትም ይሁን ሌሎች አለም-አቀፋዊ ተቋማት ቀፍዳጅ ህጎችን ያሳልፋሉ።ሰላም እስካልወረደ፣አገሪቷ ለገባችበት አጣብቂኝ ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተፈለገና እርቅ እስካልሰፍነ ነገሮች አይሻሻሉም።
110 ሚሊየን ህዝብ የሰፋ የአመለካከት ልዩነት ቢኖረው አይደንቅም።የሚደንቀው ግን ነገ ለሚፈረጥጡ ወይም አለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ለሚቀርቡ ወንጀለኞች መተኪያ የሌላትን ህይወት የሚገብር ከሆነ ነው።ግዜው እነዚያን የአመለካከት ልዩነቶች ጋብ የሚደረጉበት ነው።ሰላምና እርቅ የተነፈጋቸውን አትኩሮት ይሻሉ።የፈጣሪ ምህረት እንዲመጣ ሁሉ እንደየ እምነቱ የሚማጸንበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው ያለነው።
እነ «ቼ በለውና ዘራፍ» ኪሳራን እንጂ ውጤት አላመጡም።ጦር ግንባር የማይሔዱት አታሞ ደላቂዎችና የከተማ ተንደላቃቂዎች እነ «ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር» ድምጻቸውን የሹክሹክታ ያደርጋሉ።ነገሮች መቀየራቸው አይቀሬ ነው።እናሸንፋለን የሚል የሐሰት ተስፋን የሚዘሩ ፖለቲከኞች፣ህዝብን ለማፍዘዝ የተሰማሩ ካድሬዎችና ሚዲያዎች አገሪቷ ውስጥ ያለውን ቀውስ የሚያባብሱ መሆናቸውን ህዝብ አውቆ በዙሪያው ባለው እውነታ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ወደ ነገ መሻገሩና ብስሉን ከጥሬው መለየቱ ወሳኝ ሆኗል።
ሰመመኑ ሰሞኑን «አለም አልደወለልኝም» ሲል የዋሁን ህዝብ በአፍዝዝ-አደንግዙ ሊያሞኝ ይሻል።አለምማ «ንክ» ነገር አርጎ ቆጥሮት ከርሱ በኋላ ስላለችው ኢትዮጵያ መዘየድ ጀምሯል።ጽሁፌን ወይም የሚዲያ ስራዎቼን የሚከታተል በተደጋጋሚ ስለ አምባገነናዊያን የምለውን ነገር ያስታውሳል «አዳዲሶቹም ይሁኑ የሰነበቱት አንባገነናውያን ቤተ-መንግስታቸው ተከቦ እንኳ አገርን የሚመሩ ይመስላቸዋልi»…ከአብይ በኋላስ?… ሁሉም ነገር ወደ ጠረጴዛው ግንባር!
ልብ ያለው ልብ ይበል!