አንዱ ዓለም ተፈራ፤ ረቡዕ ጥቅምት ፲ ፯ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም.
ዕርቅ ትርጉም የሚኖረው፤ መታረቂያ ጉዳዩ ላይ ታራቂዎቹ ሲስማሙ ነው።
ዕርቅ ማለት፤ በአንድ ጉዳይም ሆነ በሌላ ተፋጥጠው ያሉ ወይንም በግጭት የተጠመዱ አካላት፤ በመካከላቸው ካለው ውጥረት ይልቅ፤ ውጥረቱን ማርገቡ የተሻለ መሆኑን በሌሎች ግፊት ወይንም በራሳቸው መነሳሳት ተረድተው፤ የሚቀራረቡበት ሁኔታ ነው። ለዕርቅ መጀመሪያውና መጨረሻው፤ የተለያዩበትን በግልጥ አንስተው መነጋገርና፤ ለተከተለው ሂደቱ ተጠያቂው የሚለይበትና ካሣ የሚጣልበት እውነታ ነው። አደባብሶ ወደፊት ለመሄድ መሞከር፤ ለነገ ሌላ ውጥረት መደገስ ነው።
አሁን ላለንበት ውጥረት መነሻው፤ በቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድነት ተነስቶ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አገዛዝን በቃን! ያለበት ሀቅ ነው። በዚህ ሕዝባዊ መነሳሳት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሲከተል የነበረውን የፖለቲካ ፍልስፍናም ሆነ የአስተዳደር መመሪያ፤ ሕዝቡ ውድቅ አደረገው። በርግጥ ለውጡን መምራት የነበረበት ሕዝባዊ ክፍሉ በቦታው ባለመገኘቱ፤ በቦታው መሪነቱን የወሰዱት፤ ለውጡን ከሥሩ እንዲሆን አልመሩትም። ይህ በዚህ እንዳለ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከአገራዊ ሥልጣኑ ሲወገድ፤ ራሱን ትግራይ ውስጥ መሸገ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያስወግደው የተነሳውን ሕገ-መንግሥት፣ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር ዘይቤ፤ “ምን ሲደረግ!” በማለት ይሄው ቡድን አሻፈረኝ አለ። ይሄን በአገራችን ላይ መልሼ አስቀምጣለሁ! ብሎ መዘጋጀት ጀመረ። እጅግ አሰቃቂ የሆነው የኮቪድ ወረርሺኝ በሺታ አገራችንን እና ዓለምን በሙሉ ባስጨነቀበት ወቅት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባርን አስወግጃለሁ ብሎ፤ መሠረታዊ ለውጡን ለማሳካትና የጎደለውን ለመሙላት የፖለቲካ ሂደቱን ቀጠለ። ከፋም በጀም ምርጫ አካሄደ። ይሄ ሁሉ በኢትዮጵያ እየተካሄደ እያለ፤ ይሄ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ አገሪቱን በመውረር የተጠላውን አገዛዙን መልሶ ለማስፈን ዝግጅቱን ማካሄድ ያዘ።
እንግዲህ አዚህ ላይ፤ ይሄ ቡድን የሠራውን ሁሉ መዘርዘሩ፤ አንባቢ ያውቁታልና፤ አልገፋበትም። በአሁን ሰዓት ዕርቅን በተመለከተ እየተናፈሰ ወዳለው ጉዳይ ልግባ። አቶ ገለታው ዘለቀ፤ እንታረቅ! የሚል ጽሑፍ በዘሃበሻ ላይ አስፍሮ፤ ትናንት ማክሰኞ፣ ጥቅምት ፲ ፮ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. አነበብኩ። ጸሐፊውን ከዚህ ቀደም በሚለጥፋቸው ጦማሮቹ እውነተኛ ወገንና አገር ወዳድ መሆኑን አውቃለሁ። በተረፈም በነዚህ በጽሑፎቹ አማካይነት ልውውጦች ስላደረግን፤ ከየት እንደተነሳ ለኔ ግልጥ ነው። የሱን ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ፤ ይሄ አመለካከት በሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዘንድ መኖሩ ተሰማኝ። እናም አጥጋቢ መልስ ካላገኘ፤ ይሄ አመለካከት ተቀባይነት ያለው ተብሎ መወሰዱ አሰጋኝ። እናም መልስ መሥጠት ፈለግሁ። የኔ አመለካከት፤ ከአቶ ገለታው ሃሳብ ይለያል። አቶ ገለታው ዘለቀ፤ ነገሩን ሰፋ አድርጎና ትኩረት ሠጥቶ፤ በሱ እምነት ተገቢ ጥናት አካሂዶ የጻፈው ነው። ያቀረበው ሃሳብ ብዙ የጎደለውና ቋሚ ሰላምን የማያመጣ መሆኑን አዚህ አሳያለሁ።
አቶ ገለታው ዘለቀ እንዳቀረበው፤ ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወረራና በዚህ ቡድንና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል እየተካሄደ ያለ ጦርነት ነው። ስለዚህ፤ ባሁኑ ሰዓት ዕርቅ ስንል፤ በነዚህ ሁለት አካላት የሚካሄድ ማለታችን ነው። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወይንም የመከላከያ ሠራዊት፣ ወንም የአማራ መንግሥትና የአማራ ልዩ ኃይል የግል ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው! የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወረራ ባካሄደባቸው ቦታዎች እየተሰቃየ ያለው። ከዚህ ክፍል ጋር ነው! ዕርቅ ይደረግ እየተባለ ያለው። ዕርቁ፤ ለሁለቱ ታረቁ ለሚባሉት አካሎች፤ የተለያየ ትርጉም አለው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕርቅ ማለት፤ ወንጀለኛ ለፍርድ ይቅረብ፣ የከሰረ አስተዳደር ይወገድ፣ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ይከበር ነው። ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ደግሞ፤ ወደ ነበርንበት እንመለስ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በፈለግሁት መንገድ ልግዛው፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያስቀመጥኩት ሕገ-መንግሥት፣ የክልል አስተዳደር፣ እና ለያንዳንዱ ክልል የሠጠሁት ሰንደቅ ዓላማ አይነካ ነው! ይሄን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል። በተጨማሪ ደግሞ፤ ይሄ መደረግ አለበት ብሎ፤ ይሄ ቡድን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን ከቦ ጨፍጭፏል። ይሄው ቡድን እኔ የምፈልገውን ካላደረጋችሁ፤ ካላችሁበት ድረስ መጥቼ እጨርሳችኋለሁ ብሎ፤ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ፈጽሟል።
አቶ ገለታው ዘለቀ ለዕርቁ አስፈላጊነት ዋና አድርጎ ያቀረበው፤ ይህ የርስ በርስ ጦርነት ነው፣ ብዙ ጉዳት አድርሷል፣ የሚሊቴሪ መፍትሔ አይገኝለትም፣ ኢትዮጵያን ለዕርቅ እንድትንበረከክ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች አሉ፣ ጦርነቱ የሲቪል ነው፣ ጦርነቱ በማንነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ ጦርነቱ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ፣ የሚሉ ናቸው። ዕርቅን ግድ የሚለው፤ ጠቡ ያደረሰው ውጤት ሳይሆን፤ ጦርነቱ የተነሳበት ሀቅ ነው። አቶ ገለታው ዘለቀ ያቀረበው ሃሳብ፤ የጎደለው ብዙ ነው። መጀመሪያ የሁለቱን አካላት መነሻና ዓላማ አመሳስሎ፤ እኩልና አንድ አድርጎ ማቅረቡ ነው። በርግጥ የትግሬዎች ነጻ አውጪ ግንባር በትግሬዎች ስም ነግዶ የተነሳና ጦርነቱን በትግሬዎችና በአማራዎች፣ በትግሬዎችና በአፋሮች፣ በትግሬዎችና በኦሮሞዎች ለማድረግ የሚጥር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፤ በአንድነት ተነስቶ፤ ይህ ጦርነት፡ ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረገው ወራራ ነው! ብሎ ነው መከላከል የያዘው። ታዲያ እንዴት ነው ተመሳሳይና የዓላማ አንድነት ያላቸው አድርጎ ሁለቱን አካሎች ማቅረቡ! ለማሳየት፤ አቶ ገለታው ዘለቀ፤ “ጦርነቱ . . . የአካባቢ ማንነትንና የብሄር አርበኝነትን ስሜት በታጠቁ በማንነት ስሜት በሰከሩ ሃይሎች መካከል በመሆኑ በእውነት ኢትዮጵያን እሳት ላይ ጥዷታል።” ይሄ ፍጹም የተሳሳተ አቀራረብ ነው።
ለምን እንደኔ ያሉ ሰዎች ድርድሩን እንዳልፈለጉ ከመጠየቅና ካቀረቡት ሃሳብ ከመረዳት ይልቅ፤ አቶ ገለታው የሚከተለውን አስፍሯል። “በሃገራችን ውስጥ ድርድር አንዳይኖር አጥብቀው የሚሹ ሃይሎች አሉ። እነዚህ ሃይሎች የተለያየ ዝንባሌ አላቸው። አንደኛው ድርድርና እርቅ ጠል የሆነው ሃይል ገንጣይ ነው። ነገሮች እንዲካረሩ ይፈልጋል። ነገሮች ሲካረሩና ዘርማጥፋት ሲመጣ በዚህ ምሬት ላይ የተለያዩ ትናንሽ ሃገራት የመፍጠር ህልም ያላቸው አሉ። ሌሎች ደግሞ የኢትዮጵያን ሰላም ከማይሹ ጋር ተመሳጥረው ሃገር ሲበጠብጡ የሚኖሩ ሃይሎች ናቸው።” ይሄ ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያ ጠላቶች የሉም እያልኩ አይደለም። ነገር ግን፤ አንድ ሰው የማይፈልገውን ሃሳብ የሚሰነዝሩትን በሙሉ አጠቃሎ፤ አስቀድሞ ወንጀለኞች ካደረገ፤ ይህ ሰው ለውይይት አይደለም ሃሳቡን ያቀረበው፤ ዝም ብላችሁ ተቀበሉኝ! እያለ ነው። ለኔ ይሄን ውይይት ከዚህ በበለጠ መዘርዘሩና ለምን ዕርቁ እንደማይሠራ ማስፈሩ የሚጨምረው የለም ብዬ ስለማምን፤ እዚህ ላይ ሃሳቤን እቋጫለሁ።