October 9, 2021
ጠገናው ጎሹ
እ.ኢ.አ “አዲስ መንግሥት” ተመሠረተበት ከተባለው ካሳለፍነው መስከረም 24/2014 በፊት በዋናነት ከሁለት ተፃራሪ የፖለቲካ ካምፖች (ጎራዎች) የሚመነጩ (የሚነሱ) የመከራከሪያ ሃሳቦችና አስተያየቶች ሲንሸራሸሩ እንደነበር ይታወሳል። ከምሥረታው በኋላም ቀጥለዋል ።
አንደኛው የመከራከሪያ ሃሳብ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ፈላጊ ወገኖች የሚቀርብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሁለቱ የኢህአዴግ አንጃዎች ማለትም ከሥልጣን ሽሚያ በስተቀር መሠረታዊ ልዩነት ከሌላቸው ቡድኖች (ህወሃት እና ብልፅግና) የሚነሳ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ነው።
ብአዴኖች የሚባሉና ከአገላጋይነት ወይም ከተቀጣሪነት ወይም ከወራዳነት የፖለቲካ ረድፍ (ደረጃ) ለመላቀቅ ጨርሶ የተሳናቸው እና የአማራን ማህበረሰብ ፍፃሜ ላልተገኘለት መከራና ውርደት የዳረጉ ፖለቲከኞች ለዚሁ ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ መቀጠል ያላቸው ሚና እጅግ ጉልህ ነው።
በነገራችን ላይ ገዱ አንዳርጋቸው ከሰሞኑ” ስለ ህገ መንግሥቱ ነፃ አውጭነትና ፍትህ አጎናፃፊነት እና ስለ ዴሞክራሲ ማበብ” ደሴ ላይ የደሰኮረውን (ያስታወከውን ማለት ይሻላል) ሸፍጠኛና ርካሽ ፕሮፓጋንዳ በጥሞና ላዳመጠ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው ብአዴን/የአማራ ብልፅግና ተብየዎቻችን በተለይም የአማራን ማሀበረሰብ እና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ምን ያህል የርካሽ ፖለቲካቸው መጫወቻ እንደረጉትና እያደረጉት እንደሆነ ለመገንዘብ አይቸገርም። ይህ ትውልድ ለማንም ብሎ ሳይሆን ለእራሱ ሲል ከምር በመቆጣት በቃ ብሎ ለመነሳት እስካልቻለ ድረስ ይህ የአገልጋዮች (የወራዶች) ጥርቅም የሆነው ብአዴን የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ በተረኝነት ከተቆጣጠረው የኦሮሙማ/ኦነግ ቡድን የሚሰጠውን ትእዛዝ ያለምንም ማንገራገር እየተቀበለ ማስተጋባቱንና ማስፈፀሙን ይቀጥላል። “ከአዲሱ ምእራፍ ብሥራት” ማግሥት ይበልጥ ግልፅና ግልፅ ሆኖ የሚታየውና የሚዳሰሰው መሪር እውነ ይኸው ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ አብይ አህመድ አገኘሁ ተሻገር የሚባለውን ቅዠታምና እጅግ ወራዳ ካድሬ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር – የምሁርነት እውነተኛ ትርጉምና እሴት ከተጎሳቆለ ብዙ ዓመታት ሆኖታል ) በሚባል ሌላ አሻንጉሊት እንዲተካ ማድረጉን ታዝበናል። መላ አገሪቱ በተለይ የሰሜኑ አካሏ በተለይም ደግሞ የአማራ ማህበረሰብ በሁሉቱ የኢህአዴግ አንጃዎች (ህወሃትና ብልፅግና) የሥልጣን ሽሚያ ጦርነት እና በኦነግ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መካከል ለመግለፅ የሚያስቸግር ግፍና መከራ እየተቀበለ ባለበት በዚህ እጅግ መሪር እውነታ ወቅት የተለዋጩን አሻንጉሊት (ይልቃል ከፋለ) ትክሻ እያሻሸ “ልማት እንጅ ጦርነት አይጠቅምም” ብሎ ሲሳለቅበት ህይወት አልባ ከሆነ ፈገግታ ጋር ሲታገል ከማየት የከፋ ውርደት የለም። የዚህ ቡድን የወራዳነት ታሪካ ተነግሮ የሚያልቅ ባይሆንም እውተኛ አገርና ወገን ወዳድ ምሁራን ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድ መማሪያነት በሚሆን መልኩ እንደሚያቀርቡት ተስፋ አለኝ ።
እነዚህ ሸፍጠኛ ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ያስቀጠሉትን ወንጀለኛ የፖለቲካ ሥርዓት ህሊናቸውን በሸጡ የምርጫ ቦርድ ባለሥልጣናት ትብብርና አፅዳቂነት ባካሄዱት የሸፍጥና የሴራ ምርጫ አሸናፊነት “አዲስና ታሪካዊ ምእራፍ” ሲሉን “ትልቅ ነውር ብቻ ሳይሆን በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ መሳለቅ ነውና ከቻላችሁ አደብ ግዙ ካልሆነ ግን ሌላ የ30 ወይም የ50 ዓመታት መከራና ውርደት መሸከም ጨርሶ አይታሰብም” በማለት የሚሞግቱ ወገኖች ቁጥር ብዙ አለመሆኑ በእጅጉ ያሳሰባል። እናም እውነተኛና ትክክለኛ ታሪክን ለትውልድ የማሳወቁ ሥራና ሃላፊነት አንድ ታላቅ ሥራና ሃላፊነት ሲሆን ይህ የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ፍፃሜ ያገኝ ዘንድ የሚደረገው የአንገዛም ባይነት ትግል ግን የዛሬ እንጅ የነገ የቤት ሥራ መሆን የለበትም።
በአምሳሉ የፈጠራቸውና ሲያስፈልገው እንደ ደመ ነፍሱ አጋሰስ እየጫነና ሲያሻው ደግሞ በገዳይነት እያሰማራ ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በላይ ሲጠቀምባቸው የኖረውን የህወሃት ገዥ ቡድን ከቤተ መንግሥት የፖለቲካ ዙፋኑ ላይ በማስወገድ መሠረተ ሥርዓቱን ግን ይበልጥ አስከፊ በሆነ የአገዛዝ ተረኘነት እንዲቀጥል ካደረጉት የጎሳና የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ((ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን) “አዲስና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይወለዳል” ብሎ መጠበቅ የለየለት የፖለቲካ ቂልነትና የሞራል ዝቅጠት ነው ።
በጋራ አስተሳሰብ፣ በማይናወጥ ዓላማና ግብ፣ በፅዕኑ መርህ፣ ከምር በሆነ የተግባር ውሎ ፣ ወዘተ ላይ ቆሞ እነዚህ ሸፍጠኛ ፣ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ኢህአዴጋዊያንን (ብልፅግናዊያንን) በቃችሁ የሚል እና እየኖረበት ላለው ዘመን የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አምጦ መውለድ የሚቸል ትውልድ እስከሚገኝ ድረስ ነገም የባሰ እንጅ ከቶ የተሻለ ነገር ጨርሶ አይኖርም።
ሸፍጠኛና ጨካኝ በሆኑ ተረኛ የኦህዴድ/የኦሮሙማ/የብልፅግና ፖለቲከኞች የበላይነት፣ በወራዳነት የፖለቲካ ልክፍትና በአስከፊ የሞራል ጉስቁልና በተለከፉ የአማራ ገዥ ቡድኖች፣ ታገልንለት በሚሉት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ዓላማና መርህ ላይ የበረዶ ውሃ ቸልሰውበት የታዛዥነት (የአሽከርነት) ፖለቲካን በተቀላቀሉ የተቀዋሚ ፖለቲካ መሪ ተብየዎች ፣ እና ህሊናቸውን ለአደርባይነት ክፉ ደዌ አሳልፈው በሰጡ ምሁራን ተብየዎች አጃቢነት እየተካሄደ ያለውን እጅግ ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ “አዲስና ብሩህ ምእራፍ“ ብሎ ለመቀበል ፈቃደኛና ዝግጁ ሆኖ ከመገኘት የከፋ በህዝብ መከራና ውርደት ላይ የመሳለቅ አባዜ ከቶ የለም። አይኖርምም።
በእጅጉ ህሊናን የሚያቆስለው ደግሞ ርካሽና አደገኛ አስተሳሰባቸውንና አካሄዳቸውን ሲሆን አምነን እንድንቀበላቸው ካልሆነ ግን አርፈን እንቀመጥ ዘንድ ከእነርሱና ከቀድሞ አሳዳሪያቸው (ሀወሃት) በላይ ጁንታ (አሁን ደግሞ ጉጅሌ ይሉታል) ያለ ይመስል በጁንታነት ሊያስፈራሩንና ሊከሱን የመሞከራቸው እብደት ነው። እንዲህ አይነት እጅግ ጋግርታምና ወራዳ የፖለቲካ ሰብእናቸው በአንዳንድ ድህረ ገፆች ( ዘሃበሻን በምሳሌነት) ላይ የሚወጡ ትችታዊ ሃሳቦችን እንዲወርዱ እስከማስደረግ ወራዳነት አውርዷቸዋል ። የድንቁርናቸው፣ የፍርሃታቸው፣ የፀረ ዴሞክራሲያዊነታቸው፣ የጨካኝነታቸውና የአደገኝነታቸው መጠንና ስፋት ይህን ያህል አስከፊ ነው።
ያነቁኛል ፣ ያደራጁኛል ፣ያታግሉኛል እና ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያበቁኛል በሚል በጉጉት ይጠብቃቸው የነበሩ እንደ ኢዜማ እና አብን አይነት ፖለቲካኞች በሥልጣን ፍርፋሪ (በለየለት የፖለቲካ አድርባይነት ወይም ልክስክስነት) ተሽመድምደው ሲወድቁ ማየት ህሊናውን የማያቆስለውና ከዚህ አይነት አስከፊ የፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት የሚችለውን ሁሉ የማያደርግ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
ይህ ከሦስት ዓመታት በላይ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ አሁን ይፋ የተደረገው የተረኛ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) እና የወራዳ ግብረ በላዎቻቸው የጫጉላ ሽር ጉድ የሚነግረን ቀጣይነት ያለውንና የሚኖረውን አስቀያሚና አደገኛ የፖለቲካ ተውኔት እንጅ የዴሞክራሲን ባህሪና ገፅታ ከቶ አይደለም።
ይልቁንም ይህ እንኳንስ የዴሞክራሲያዊነት ባህሪና ገፅታ የዴሞክራሲ ጠረንም (ሽታም) የሌለው የሸፍጠኞች፣ የሴረኞችና፣ የፈሪዎችና የጨካኞች የፖለቲካ ተውኔት የሚነግረን ግዙፍና መሪር እውነታ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ የሚጠይቀን ሥራ እጅግ ፈታኝ መሆኑን ነው። ህወሃት አልባ የሆነ የህወሃት የፖለቲካ አስተሳሰብንና ሥርዓትን ይበልጥ አስከፊ በሆነ የተረኝነት ፖለቲካ ቁማር እያስቀጠሉ “አዲስና ታሪካዊ ምእራፍ” በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ የመሳለቁ ጨዋታ በቃ መባል ያለበት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው።
ከዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት ሥልጣነ መንበሩን ሲረከብ የካድሬ አሻንጉሊቶች ስብስብ ለሆነው ፓርላማ ተብየ ያደረገውን እጅግ አማላይ ዲስኩሩን (ድርሰቱን) የፃፈበት የብእር ቀለም በቅጡ ሳይደርቅ ኢትዮጵያ የአያሌ ንፁሃን ዜጎች የምድር ሲኦል የመሆኗንና እየሆነች የመሆኗን መሪር ሃቅ መካድ የሚቃጣው ጤናማ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኘም ። ያ ሁሉ ሲሆን ሃላፊነቱን መወጣት ቀርቶ ለመወጣት ያልሞከረ እና ይባስ ብሎ የፓርክ ፣ የችግኝ፣ የመንገድ ፅዳት፣ የውጭ አገር ጉብኝት ተውኔተ ፖለቲካ ሲተውን የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር አሁን ደግሞ “በምርጫ አሸናፊ” በመሆን ስለመሠረተው “አዲስና ታሪካዊ መንግሥት” ያለምንም ሃፍረት ሊሰብከን ሲሞክር ጨርሶ ህሊናውን አይጎረብጠውም። አዎ! እንዲህ አይነት እጅግ አስቸጋሪና አደኛ የፖለቲካ ሰብእና እና የሞራል ዝቅጠት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ናቸው ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ “አገረ ሰላምና አገረ ብልፅግና ልናደርጋት ነውና እልልል እያላችሁ ተደመሩ ፤ ካልሆነ ግን አርፋችሁ ተቀመጡ” ሊሉን የሚቃጣቸው።
ይህ በአስከፊ ሸፍጥ፣ ሴራ ፣ የግል ሥልጣን ፣ ውሸት ፣ አታላይነት ፣ ወዘተ ክፉ ልክፍት የተለከፈው ጠቅላይ ሚኒስትር “በሁሉን አቀፍ አገራዊ ጉባኤ የመከራዎችና የውርደቶች ሁሉ ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት ተብየ በአዲስና ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግሥት ተተክቶ አዲስና እውነተኛ ፌደራላዊ ሥርዓት እውን ይሁን” የሚለው ጥያቄ መክኖ ይቀር ዘንድ ለዚህ እታገላለሁ ይል የነበረውን ወራዳ ተቀዋሚ ተብየ ሁሉ በፍርፋሪ ሥልጣን አፉን አዘግቶታል ።
በአቋማቸው የፀኑትን ደግሞ የማጎሪያ ቤቶቹ እና የፖለቲካ ድራማ የሚተወንባቸው አቃቤ ህግና ፍርድ ቤት ደንበኞች አድርጓቸዋል። በዚህ መሪር ሃቅ ውስጥ ነው “አገራዊ ውይይት አዘጋጃለሁና የፈለጋችሁትን መተንፈስ ትችላላችሁ” በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ ሲደሰኩርና ሲሳለቅ የሰማነውና የምንሰማው ። እናም ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን ሥርዓተ ፖለቲካ ይበልጥ አስከፊ በሆነ የተረኝነት አገዛዝ ካስቀጠሉትና እያስቀጠሉት ካሉት ሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች አዲስና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምእራፍ እውን ሆነ ብሎ ከማመን የባሰ የፖለቲካ ድንቁርና እና የሞራል ዝቅጠት ከቶ የለም ።
ለመሆኑ አዲስ አበቤ ኢትዮጵያዊያንን የትኛውም ጤናማ አእምሮ ያለው የአገሬ ሰው እንኳን ደፍሮ ሊጠቀምበት ለመስማት እንኳ በእጅጉ በሚፀየፋቸው ቃላት (የሴት አዳሪና የሸርሙጣ ዲቃላዎች ) በሚል በአደባባይ የዘለፈውና እወክለዋለሁ የሚለውን የኦሮሞ ማህበረሰብ ጨምሮ ያዋረደ ግለሰብ የተከበሩ የፓርላማ አባል የሆነበት መንግሥት እንዴት ሆኖ ነው የአዲስ ምእራፍ አብሳሪ የሚሆነው? ከዚህ በላይ የባለጌነት ድፍረት ይኖራል?
ለመሆኑ ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነትና ስለ ባንዲራዋ ሲነሳ በሃሰት የተጋተው ትርክት አቅሉን (ሚዛናዊ ህሊናውን አሳጥቶ ) የሚያሳብደው የጎሳ ወይም የመንደር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ አባል የሆነበት የመንግሥት መዋቅር እንዴት ሆኖ ነው የትብብር፣ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና አራማጅ የሚሆነው?
ለመሆኑ በምሁርነት ፣ በእድሜና በህይወት ተሞክሮ አንቱ የምንላቸው ወገኖች ሳይቀሩ ይህን የገሃዱ ዓለም የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ከሰማያዊው ዓለም የተቀባ ወይም የተላከ በሚል እራሳቸውን ከአንድ ካልተማረ አስተዋይ ያገሬ ሰው በታች ያወረዱ ወገኖች በአሽቃባጭነት በተሰየሙበት ሥርዓተ ፖለቲካ ውስጥ ስለ ምን አይነት “አዲስ ምእራፍ” ነው የምናወራው?
ለመሆኑ መንፈሳዊ (ሃይማኖታዊ) ህይወቱ የተሳካ አንዲሆን ያግዙታል የሚባሉ የሃይማኖት መሪዎች የመከረኛውን ህዝብ ዓለማዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ህይወቱንም የተመሰቃቀለ እንዲሆን ባደረጉ ፖለቲከኞች ቤተ መንግሥት ተገኝተው በቅጡ መናገርና ማገናዘብ በተሳናቸው የሃይማኖት አባት ስም ( ጨርሶ አያቁትም ነበር እንዴ? የሚለው ጥያቄ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) “ክቡር ጠ/ ሚኒስትር ሆይ! ኢትዮጵያዊነትን እንደ ክርስቶስ መስቀል ከተቀበርበት ቆፍረው በማውጣት ያስገኙት በረከት ተዝቆ አያልቅም” የሚል አይነት ውዳሴ በሚያቀርቡ ወገኖች የሚታጀብ መንግሥት እንዴት “የአዲስ ምእራፍ ድል አብሳሪ” ሊሆን እንደሚችል እንኳን ለመቀበል ለማሰብም አይከብድም እንዴ?
እናም ከላይ በጠቀስኳቸው ሁለት ጎራዎች (ካምፖች) መካከል የነበረው የሃሳብ ጦርነት ቀጥሏል። ከምር እውነተኛ ነፃነትንና ፍትህን የምንፈልግ ከሆነ የሦስት አሥርተ ዓመታት ኢህአዴግ/ብልፅግና መራሽ የመከራና የውርደት ፖለቲካ ቁማር ፍፃሜ ማግኘት ይኖርበታል። የሥርዓት ለውጥ አስፈላጊነትን እየሳትን ስለ ግለሰቦችና ስለ ቡድኖች ተክለ ሰውነትና ባህሪ የትንታኔ ድሪቶ የመደረቱን ክፉ ልማድ ከምር ልናጤነውና ልናስተካክለው ይገባል።
አዎ! ከእውነትና እውነት ጋር ብቻ ቆሞ ለእውነተኛ ዜግነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚሟገተው ወገን ድል እስጊጎናፀፍ ድረስ የሃሳብ ጦርነቱ አስፈላጊ በሆነ ሰላማዊ የአልገዛም ባይነት ትንቅንቅ እየታጀበ መቀጠል ይኖርበታል!
ፅዕኑ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት አርበኛ የሆነው እስክንድር ነጋ እንደሚለው “ድል ለዴሞክራሲ” እስኪሆን ድረስ የሃሳብ ጦርነቱ እና ማነኛውም አስፈላጊና ውጤታማ የሆነ ሰላማዊ ትግል ሁሉ መቀጠል ይኖርበታል!
አዎ! ልኩን የሳተው የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነታችንን ፣ የሞራል ውድቀታችንን ፣ የመንፈሳዊነት (የሃይማኖታዊ እምነት) ጉስቁልናችንን ፣ ስለፍትህ አጥብቀን እያወራን የፍትህ አልባ አገር ሰዎች የመሆናችንን፣ እውነተኛ ፓርላሜንታሪ ዴሞክራሲ ጨርሶ በሌለበት የህዝ ተወካዮዎች በሚል የተለምዶ አነጋገር መከረኛውን ህዝብ ጨምረን ግራ የማጋባታችንን፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ፖለቲከኞችን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተርና ክቡራን ሚኒስትሮች እያልን መከራና ውርደትን የመለማመዳችንን ፣ የመልካም ሽምግልና እሴት ድህነታችንን ፣ ትውልዳዊ ክፍተቶቻችንና ቀውሶቻችንን ፣ የእለት ጉርስ ሳይቀር ተመፅዋችነታችንን ፣ የበሽታና የድንቁርና ሰለባነታችንን ፣ የጥንተ ሥልጣኔ ትርክት እየተረክን የዘመናችን ሥልጣኔ ጭራዎች የመሆናችንን፣ የእራሳችን የቤት ሥራ ሳንሠራ የውጭ ሃይሎች የምንላቸውን ለውድቀታችን ሁሉ ተጠያቂ እያደረግን የማላዘናችንን ፣ ወዘተ አስከፊ ልማድ ከምር ተገንዝበን ለዚሁ የሚመጥን የጋራ ትግል እስካላደረግን ድረስ ነፃነትና ፍትህ መናፈቅ ጨርሶ ትርጉም የለውም ።
አዎ! ለዘመናት ከዘለቀውና አሁንም ከቀጠለው የሸፍጠኞች፣ የሴረኞች፣ የፈሪዎችና የጨካኞች ሥርዓተ አገዛዝ ካስከተለውና እያስከተለ ካለው መከራና ውርደት ተምሮ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የጋራ እድገት ሥርዓትን እውን ከማድረግ ይልቅ ከትግል መርከቧ እየተንጠባጠብን በመጣንበት አዙሪት ተመልሰን ለምን እንደምንዘፈቅ የየራሳችንን ህሊና ከምር መጠየቅ ይኖርብናል።
ይህንን እንደምናደርግ ያለኝን ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!