በቁማቸው ከሞቱ ወገኖቼ መካከል አንድም ሰው ቢሆን ወደኅሊናው እንዲመለስ ማድረግ ብችል ብዬ ዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2014ዓ.ም ይህን ጻፍኩ፡፡ የምጽፈውም እውነት ነው፡፡ ያለአንዳች ጥቅም ራሱን ደብቆ የሚጽፍ ሰው ሳያውቅ ካልሆነ በስተቀር አውቆ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ሰውን አያጭበረብርም፤ የሚዋሽበት ምክንያትም የለውም – የሚጽፈው ለምንም ጥቅም ብሎ አይደለምና፡፡
ዓለማችን በታሪኳ ካስተናገደቻቸው አስመሳዮችና ጨካኞች ውስጥ ከአቢይ አህመድ (ዳግማዊ ካሊጉላ) ይበልጥ አስመሳይና ጨካኝ እንደሌለ በአሥር ጣቶቼ እፈርማለሁ፡፡ ይህች ምድር ከጥንታውያን እነካሊጉላንና (በዋና ስሙ Gaius Caesar Augustus Germanicus) እነኔሮን (Nero Claudius Caesar) የመሳሰሉ ዐረመኔዎችን ተቀብላ እንደቅደም ተከተላቸው ለ28 እና ለ31 ዓመታት ከነዚህም ውስጥ አሁንም እንደቅደም ተከተላቸው ለ4 እና ለ14 ዓመታት በገዢነት ወንበር አስቀምጣ ተሰቃይታለች፡፡ በነዚህ ሰዎች የሥልጣን ዕድሜ ምን ያህል ሰው በቁሙ ይነድ እንደነበር ታሪክ መዝግቦ አስቀምጦታል፡፡ ልክ እንደአቢይ ሁሉ እነዚህን መሰል አስተዳደግ የበደላቸውና የሥነ ልቦና ደዌ የተጠናወታቸው ዕብዶችና ወፈፌዎች ሥልጣን ሲይዙ ምን ሊከሰት እንደሚችል ለመረዳት ወደመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን መሄድ አያስፈልግም፡፡ እዚሁ አገራችን ውስጥ መጋቢት 10 ቀን 2010ዓ.ም በልዩ የማጭበርበር ሥልት የኢሕአዲግን ሥልጣን የተረከበው የኛውን ካሊጉላ አሰግድ አህመድን ማየት በቂ ነው፡፡ የአእምሮ በሽተኛ ገዢዎች ሰውን በማሰገድና በማስደግደግ እርካታን ስለሚያገኙ ነው አቢይን “አሰግድ” ያልኩት፡፡
የሮማው ወጣቱ ንጉሥ ካሊጉላ በ25 ዓመት ዕድሜው ገደማ ንጉሥ ሆኖ ተሾመ፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ ልክ እንደኛው ጉድ አንዳንድ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ የብዙዎችን ቀልብ ገዛና ተወዳጅነትን አተረፈ፡፡ ነገር ግን “ዕብድ ቢጨምት እስከኩለ ቀን ነው” እንዲሉ ከሕጻንነቱ የለከፈው የአእምሮ በሽታው ተነሳበትና የጭቃ ጅራፉን ማንጓት ጀመረ፡፡ በአራት ዓመታት አገዛዙም ሮምንንና ሮማውያንን ቁም ስቅላቸውን አሳይቶ በ28 ዓመት ዕድሜው በሰው ተገደለ፡፡ በዚያን አገዛዙ ያደረገው ሁሉ ትንግርት ነው፡፡ እህቶቹንና ሌሎች የቅርብ ሴት ዘመዶቹን ሳይቀር ተኛቸው፤ ተገናኛቸው ማለቴ ነው፡፡ የባለሥልጣናትን ሚስቶች ከባሎቻቸው ፊት እየመረጠ ወደመኝታ ቤቱ በማስገባት አነወራቸው፤ በዚያም ተግባሩ ሁሉንም ጀግና ነኝ ባይ አዋረደ፡፡ የኛውንም ጉድ በአራተኛው ዓመቱ እንዲገላግለን መመኜቴን ያዙልኝና ያ ካሊጉላ የተባለ ዕብድ ሥልጣን በያዘ በአራኛው ዓመት አንዱ የጦር ጀግና በሠይፍ አንገቱን በጥሶ ሮምን ከተጨማሪ ኪሣራ ገላገላት፡፡ አሥር ዓመታት ገደማ ቆይቶ የነገሠው ኔሮም እንዲሁ ክፉ ነበር፡፡ በራሱ አምሳል ከእንደገና ለመገንባት ብሎ በሥውር ሰው ልኮ ሮምን አቃጠላት፡፡ ሮም ስትነድም ሠገነቱ ላይ ቆሞ እየተዝናና ተመለከታት፡፡ እሱም የሠራውን ግፍ ሁሉ ቆጥሮ ፈጣሪ ወሰደው – በ68ዓ.ም በተወለደ በ31 ዓመቱ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ አድርጎ፡፡ የኛው ጉድ በምን እንደሚሰናበት ጥቂት ወራትን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ያ ዓይነት ክስተት እንደማይቀር ግን ማንም አይጠራጠር፡፡ የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀር ጌታ ይህንን የሰውን በተለይም የአማራን ደም መጣጭ እንዲሁ አይተወውም፡፡
ዕብድ መሪዎች ዕብድ የሚሆኑባቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡ ዋናው ግን በልጅነታቸው የሚገጥሟቸው አስተዳደግ ነክ የሆኑ ችግሮች ናቸው፡፡ የብዙዎቹን ዐረመኔ ነገሥታትና የሀገር መሪዎች ታሪክ ስንመረምር የበርካታዎቹ ተመሳሳይ ነው፡፡ የነሂትለርም ሆነ የነሙሶሊኒ፣ የነመንግሥቱም ሆነ የነአቢይ አህመድና አባቱ መለስ፣ የነሣዳምም ሆነ የነኢዲያሚን መነሻቸው የድህነት አስተዳደግና የመጨቆን ስሜት በአእምሯቸው ጥሎ የሚያልፈው ጠባሳ ለአእምሯዊ ጉስቁልና እንደሚዳርጋቸውና ጊዜ ሲያገኙ ያን ሥነ ልቦናዊ ዕድፍ ለማጠብ ሲሉ በሚያደርጉት ያልተገባ እንቅስቃሴ ሀገርን እስከማውደም ሕዝብንም እስከመጨረስ እንደሚያደርሳቸው እንገነዘባለን፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለውም ይሄው ነው፡፡ አሰግድ አህመድ ማለትም አቢይ አህመድ ብዙው ሰው አልገባውም እንጂ ስለልጅነቱ ሲደሰኩር ከተናገረው – እጠቅሳለሁ – “ከልጅነቴ ጀምሮ መኪና ተለይቶኝ አያውቅም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ በአንሶላ ነው የምተኛው” እያለ ከወሻከተው ብዙ ቁም ነገር መቅሰም እንችላለን፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ሰውዬው ከሕጻንነቱ ጀምሮ በማስመሰልና ራሱን በማታለል የተዋጣለት መሆኑን ነው፡፡ መኪና ያለው የሽቦ መኪናውን ሲሆን አንሶላ ያለው ያቺን አንዲት ብርድ ልብስ እያጠፈ በመሀሏ በመተኛት በምናቡ የላይኛውን እንደላይው አንሶላ፣ የታችኛውን ደግሞ እንደታችኛው አንሶላ የሚቆጥር እንደነበር ከተናገረው የተረዳነው ነው፡፡ ይህን መሰል ድህነት ቤቱን ሠርቶበት ተሰቃይቶ ያደገ ሰው ሥልጣን ሲይዝ ምን ሊያደርግ እንደሚችል በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሚገባ እየታዘብን ነው፡፡ ትንሽ ሰው ሥልጣን አይያዝ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ በተለይ የአስተሳሰብ ድህነት እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ይህ ሰው ኢትዮጵያን አባቱ እንዳወረሱት የጓሮ አትክልት፣ እኛን ዜጎቿን ደግሞ ታላቅ እሀቱ እንዳወረሰችው አሻንጉሊቶች ሳይቆጥረን አልቀረም፡፡ እንዳሻው እኮ ነው እያደረገን ያው፡፡ እንደልብ የሚጋልቡትን ሕዝብ ማግኘት ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን መታደል ነው፡፡ አልጋለብም ካልክ ደግሞ መጨረሻህ ቃሊቲ ነው – ልክ እንደነአስቴር (ቀለብ) ሥዩም፡፡
ይህ ሰው ትንሽ ባይሆን ኖሮ ካለብዕር ምንም የሌለውን እስክንድር ነጋንና ጓደኞቹን አስሮ በዚያም ላይ በቀጠሮ ቀን እንዳይቀርብ ደብድቦና አስደብድቦ የኦሮሙማ መንግሥቱን እንዲህ መሣቂያ መሣለቂያ ባላደረገው ነበር፡፡ እንደአቢይ ያሉ ካሊጉላዎች ፈሪዎች ወይም ቦቅቧቃዎች ናቸው፤ ጥላቸውን ሳይቀር ይጠራጠራሉ፡፡ ሁሉም ጠላታቸው እንደሆነ ስለሚቆጥሩ የቅርብ ሰዎቻቸውን ሳይቀር ይገድሏቸዋል፡፡ አቢይን ሳስብ ሁሌም በአእምሮየ የሚመጣ ሌላ የአንድ ኮሜዲ ፊልም ገጸ ባሕርይ አለ – እሱም የዲክቴተር ፊል ተዋናዩ ጄኔራል አላዲን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ያንን ፊልም ልጋብዛችሁና እባካችሁን ፈልጋችሁ እዩት – እየሣቃችሁ ትጨርሱታላችሁ፡፡ አቢይና አላዲን ቁርጥ ቁምጥ አንድ ናቸው፡፡ አምባገነኖች ከፍርሀታቸው የተነሣ በንጹሓን ላይ ያልተጠበቀ ግፍና በደል በማድረስ የሀገር አለኝታዎችን በከንቱ ይጨርሷቸዋል፡፡ የኛም ሰውዬ በዚህ ሁኔታ ስንቱን እንዳሳጣን ብዙዎቻችን የምናውቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ሲችሉ በጥይት ሳይችሉ በመርዝና በመሳሰሉት የሤራ ግድያዎች ለሥልጣናቸው ያሰጉናል የሚሏቸውን ሁሉ ድራሻቸውን ያጠፏቸዋል፤ የእናታቸው ልጅም ቢሆን አይራሩለትም፡፡ በነሱ ቤት ፍቅርና መዋደድ ብሎ ነገር አይሠራም፡፡ ቋሚ ወዳጅም የላቸውም፡፡ ለነገሩ ሀብታምና ባለሥልጣን ባሕርይው ተለዋዋጭ ስለሆነ ቋሚ ጠላት እንጂ ቋሚ ወዳጅ ሊኖረው አይችልም፡፡ ለሥልጣን የሚጓጉና ለገንዘብ የሚንሰፈሰፈ ሰዎች ዋና ዘመዳቸው ሥልጣንና ገንዘብ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኛም አምባገነን ባሥልጣኖች ሁሌም ፊታቸው ላይ ድቅን የሚልባቸው ሥልጣናቸውና በሥልጣናቸው ሰበብ የሚያገኙት ዝና ብቻ ነው፡፡ የሚገርሙ ፍጡራን ናቸው፡፡
እንግዲህ ሁሉንም ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና የዛሬን የመጨረሻ መልእክቴን ተናግሬ ጅምሬን ልቋጭ፡፡ በነገራችን ላይ ባለፈው ሰሞን የላክሁትን አንድ ጽሑፍ ብዙ የማውቃቸው ሰዎች ከአንድ ዩቲዩብ እንደሰሙት በመጠቆም እኔም እንድሰማው ጠቆሙኝና ሰማሁት (ሰዎቹ እኔ እንደምጽፍ የማያውቁ ናቸው)፡፡ በጥሩ ሁኔታ ነው ያ ባሮቲዩብ የተባለ ዩቲዩበር ያቀረበው፡፡ እሱም ሳይሆን አይቀርም የልብ ልብ ሰጥቶኝ ሳልጽፍ ብዙ እቆያለሁ ያልኩትን ሰው በቶሎ ብቅ እንድል ያደረገኝ፡፡
ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ!
አንድን ሰው ከሰውነት ተራ ከሚያስወጡት ዓለማዊ ነገሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ሥልጣን፣ ገንዘብና ወሲብ እንደሆኑ የብዙዎቻችን የወል ዕውቀት ነው፡፡ ከነዚህ ሦስት ነገሮች በአንዱ ወይ በሌላው የተማረኩ ወንድምና እህቶቻችን የትና የት ይደርሳሉ ሲባሉ አልባሌ ቦታ በመገኘት ነፍስና ሥጋቸውን ያጣላሉ፤ ለትዝብትና ለአሉታዊ ትችትም ይጋለጣሉ፡፡ የገንዘብን ፈተና ስታልፍ የሥልጣኑ ያጓጓህና ትጠለፋለህ፤ የወሲቡን ስታልፍ የገንዘቡ ይማርክህና ትወድቃለህ፡፡ የዓለም ፈተና ብዙና ከባድም ነው፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ፈተና ላለመውደቅ ጠብቆ መጸለይና ራስን በንባብና በሥራ በማድከም ከፈተና ለማምለጥ መሞከር ይገባል፡፡ በመሠረቱ ፈተና አያጋጥም አይባልም፤ ግን አንዴ ወድቄያለሁና በዚያው ወድቄ ልቅር ማለት ተገቢ አይደለምና በቻልን ጊዜ ሁሉ ነቅተን ወደሁነኛው መንገድ እንግባ፡፡ ይህም ያለና የነበረም ነው፡፡ ቢቻለን ሦስተኛውን ዐይናችንን እንክፈት፡፡ አዱኛ ብላሽ መሆኑንም እንገንዘብ፡፡ አዱኛ ካላወቁበት አጥፊ ነው፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፉ “ዓለምን ሁሉ የሚገዛ ሀብትና ሥልጣን ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል የሀብትንና የገንዘብን እንዲሁም የዓለማዊ ሥልጣንን ከንቱነት ቀድሞ ያስታወቀው፡፡ ሀብት ንብረት ለማግኘት አትጣሩ እያልኩ አይደለም፤ ባግባቡ ለማግኘት ግን እንሞክር፡፡
ብዙ ወንድሞቻችን ወድቀዋል፡፡ ባለፈው ጽሑፌ ለመጠቆም እንደሞከርኩት አቢይ አህመድ በአማላይ ንግግሩና እንደፈለገው በሚያሽቃንጥበት የሀገራችን አንጡራ ሀብት ሁነኛ ሰዎቻችንን እየደለለና እየገዛ ሰው አልባ ሊያደርገን ሩብ ሐሙስ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ሀገራችን ነጻ መውጣቷ አይቀርም፤ ያኔ ታዲያ መሪ እንድናጣ ወያኔና ኦነግ እያደረጉት ያለው ሁለንተናዊ ተንኮልና ሸፍጥ ቀላል አይደለም፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ብንጠቅስ ይሄ ኢትዮጵያዊ ኔሮና ካሊጉላ አብንን የተቀቀለ ፓስታ አድርጎታል፡፡ “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ቤት ሲልከሰከስ ታዬ” እንዲሉ ብዙዎች ተስፋ ጥለውበት የነበረው አብን (በበኩሌ ስሙን አልወደውም) አሁን ላይ በሥልጣን ሾኬ ተመትቶ ድምጹ አይሰማም፡፡ ኦነግና ወያኔ በቆፈሩትና ቆሻሻቸውን በሞሉበት ጉድጓድ አማራው ካለውድ በግዱ ገብቶ አንገቱ ድረስ ጠልቆ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ጣር ላይ እያለ የአብን ትንታጎች ለፍርፋሪና ለማይሠሩበት የማይረባ የሥልጣን ፍርፋሪ ብለው ዐይናቸውን በጨው አጥበው ይቃወሙት ለነበረው ህገ መንግሥት ልዕልና ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ አስገራሚ የነገሮች መለዋወጥን ከማሳየቱም በላይ የምናምነውን እንድናጣ የሚያደርግ ክፉ አጋጣሚ ነው፡፡
ሀገር በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ብዙው ሰው የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ይመሻል፤ ይነጋል፡፡ ሦዶምና ገሞራ በድኝ እሳት ከመመታታቸው በፊት የነበረው ዳንኪራና ጮቤ ረገጣ አሁንም በአዲስ አበባና በታላላቅ ከተሞች ይታያል፡፡ በኖኅ ዘመን ዓለም በውኃ ንፍር ከመጥፋቷ በፊት የነበረው ድልቂያና ጭፈራ አሁንም በጦርነትና በርሀብ እየተጠበሰች ባለችዋ በኛዋ ሀገርም እየተደገመ ነው፡፡ ሦርያና የመን፣ ሶማሊያና አፍጋኒስታን፣ ዩጎዝላቪያና ሊቢያ … ከመፈረካከሳቸው በፊት በነዚህ ሀገሮች ይታይ የነበረው የዜጎች ቸልተኝነትና ለሽ ያለ ዕንቅልፍ በኛም ሀገር እየታዬ ምንም ነገር የሌለ ያህል የሚሰማው ዜጋ ብዙ ሆኗል፡፡ … የዜጎች ንቃት መውረድ ከኦሮሙማው መንግሥታችን ብልጠት ባልተናነሰ እጅጉን ያሰጋል፡፡ ሰው ሠራሹ የኑሮ ውድነት ከጦርነቱ በተጓዳኝ ሕዝቡን ራቁቱን እያስኬደው ነው፤ አንድም የመንግሥት አካል ይህንን የተገነዘበ አይመስልም፡፡ ለምን ቢባል የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስናና በጉቦ እንጂ በደሞዛቸው አይኖሩምና፡፡ ኩንታል ጤፍ ስድስት ሽህ ብር፣ አንድ ሊትር የምግብ ዘይት 120 ብር እየተገዛ… አጭሩ የታክሲ ደርሶ መልስ ጉዞ ሃያ ብር ሆኖ…. የአንድ ሽህ ብር ደሞዝተኛ ማየት ያሳቅቃል፡፡ በሕይወት መኖራችን ራሱ ከተዓምርም በላይ ነው፡፡ ባጭሩ መንግሥት የለንም፤ ያ ብቻውን ባልከፋ፡፡ ያለን መንግሥት ገዳይ፣ አስገዳይ፣ አጋዳይ፣ አገዳዳይና አስራቢ ሆኖ ነው የተቸገርነው፡፡ ያለ መንግሥት በጥሩ ሁኔታ መኖር ስንችል በተተካኪ ገዳይ ጁንታዎች በዳርና በመሀል ታጥረን አሳራችንን እንበላለን፡፡ በወሎ፣ በትግራይና በወለጋ በእህል ምትክ ጥይት እየተዘራ ሚሊዮኖች በርሀብም በመትረየስና በቆንጨራም እያለቁ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ድራማ ዋና ገጸ ባሕርይ የሆነው አቢይ ይህን ሁሉ ትያትር መሰል አሳዛኝ ትዕይንት አያውቅም አንልም፤ እነኢዜማና ሌሎች አጨብጫቢ ፓርቲዎችም አቢይን አያውቁትም አንልም፡፡ የአቢይ አምላኪዎች ምናልባት ሃይማኖት እንዳይቀይሩ ይሉኝታና ጥቅም ይዟቸው እንጂ የአቢይ ኢትዮጵያ ወዴት እየከነፈች እንደሆነ እውነቱን አያጡትም፡፡ ግን በካፈርኩ አይመልሰኝ ተሸብበው በአቢይዝም እምነት ሀገርን በትብብር እያወደሙ ይገኛሉ – ጊዜውን ጠብቆ ግን ዋጋቸው ይሰፈርላቸዋል፡፡ በመጠለያ ካምፖች የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ብዙዎች በርሀብ እየረገፉ መሆናቸውን ለንግሥናው ወደ ሦስት ቢሊዮን የሚጠጋ ብር አውጥቶ ደጋፊዎቹን በስካር ያስፈነደቀውና በቁንጣን ያስጨነቀው አቢይ በደምብ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ካሊጉላውያን በሰው ሀዘን የሚደሰቱ፣ በሰዎች ጭንቀት ጮቤ የሚረግጡ፣ በሰው ሞት የሚረኩ ሀዘን አምላኪዎች (ሳዲስቶች) በመሆናቸው ለነሱ የሚሊዮኖች ማለቅ የሃሴታቸው ምንጭ እንጂ የሚያሳስባቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ ለማን ጀቴ ብለው ይነቃሉ! ደግሞስ ያልፈጠረባቸውን!
በዚህ የአቢይ አስጨናቂ ቡድን ውስጥ ያላችሁ ወገኖች በአስቸኳይ ውጡ፡፡ ይህች ዓመት ላወቀባት የንስሃ ዓመት ናት፡፡ የአማራ ሆዳሞች ከከርስ አምልኮት ባፋጣኝ ውጡ፡፡ ሆድ ገደል ይከታል፤ አውቃለሁ፡፡ ግን ጠግባችሁ ገደል ከምትገቡ ተርባችሁ የኅሊና ነጻነት ብታገኙ ይሻላችኋል፡፡ ፈጣሪ ሰፊ ዕድል ሰጣችሁ፡፡ ግን እስካሁን አልተጠቀማችሁበትም፡፡ ሌሎች ወገኖቼም ከዚህ ሰውዬ አንደርብ በአፋጣኝ ውጡ፡፡ ከተላመዱት የሀሰት ዓለም ለመውጣት አስቸጋሪነቱ ግልጽ ነው፡፡ ግን ሞክሩ፡፡ ነገ ጊዜ አይኖራችሁም፡፡ አሁን ነው ጊዜው፡፡ በወራት ውስጥ ሁኔታዎች በፍጥነት ይለዋወጣሉ፡፡ ዛሬ የተሸነፈ የሚመስል ኃይል ባልታወቀ ቅጽበት – ለራሱ ሳይቀር ትንግርት በሚሆንበት የሁኔታዎች መለዋወጥ – አሸናፊ ሆኖ ይወጣና ኢትዮጵያን ከሞት አፋፍ ይታደጋታል፡፡ እናም ከዛሬ አሸናፊ ጋር የምታሽቃብጡ አማሮችም ሆናችሁ ሌሎች ወገኖቼ መስመራችሁን ፈትሹ፡፡ ነገ ማቄን ጨርቄን የለም፡፡ የዛሬ ሥልጣናችሁና የሀብት ክብረታችሁ ነገ ጧት ከዐመድ አንድ ነው፡፡ ዛሬ ልለምናችሁ ግዴለም፡፡ የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ አይደለምና ከዚህ ሰውዬ አፍዝ አደንግዝ ባፋጣኝ ውጡ፡፡ ፈጣሪ ምን ጊዜም ከተበዳዮችና የግፍን ጽዋ ከሚጎነጩ ጋር እንጂ ከበዳዮችና ከዕብሪተኞች ጋር አይደለምና ወገኖቼ እባካችሁን ብዙም ሳይመሽ ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ የወያኔን ነገር ተውት፡፡ ሲፈልጉ ደብረ ብርሃንን አልፈው ሸኖ አጠገብ ወደምትገኘው ጫጫም ይድረሱ፡፡ አቢይና ሽመልስ እያሉ ከዚያም በላይ ይሆናልና በዚህ ብዙም አንጨነቅ፡፡ የወገኖቻችን መሞትና መራብ እርግጥ ነው ለጊዜው ያንገበግበናል፡፡ መጨረሻው ግን ከአሁኑ የተለዬና ተቃራኒም በመሆኑ በጥጋብ ተወጥራችሁ የምትሠሩትን ያጣችሁ ሰዎች እደግመዋለሁ አሁን ከዚህም በከፋ ሳይጨልም በቶሎ ተመለሱ፡፡ “ሲስሟት ቀርታ ሲስቧት” እንደሚባለው እንዳይሆን ፈጣሪ የሰጣችሁን የማሰብ ኃይል አሁንና ዛሬ ተጠቀሙበት፡፡ ጨለማው ጠንክሯል፤ ግን የንጋት ምልክት ነው፡፡ አበቃሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ፤ አሜን፡፡
https://youtu.be/1mfoZDprRCs