“የመንፈሥ ኩራት እና የሞራል ልእልና ያለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአገራችን ጉዳይ ያገባናል።“
“ በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ፤ ተነካናኪም ነኝ ። “
“ በልጅ እያመካኙ አንጉተው ሲበሉ እያየሁ ለምን ዝም እላለሁ ?! “ እንላለን ።
በአገረህ ጉዳይ ያገባኛል ካልክና በተለያየ መንገድ ግለሰብን ፤ ህዝብ ና አገርን ከሚጎዶት ህሊና ቢስ የገዛ አገርህ ጥቂት ህሊና ቢሥ ሰዎች ጋር ፣ ተነካናኪ ሥትሆን ፣ “ምን ያገባዋል ? ለምን ከሁሉም ሰው ጋር ይጋጫል ? ተነካናኪ ፣ አጋላጭ ና አሣጪ ለምን ይሀ ይሆናል ? ስህተቶችን አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ይልቅ ( የሚጠቁማቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ላያርሙት ፤ እራሳቸውም ላይታረሙ … ) በዘመናት ሂደት የተገነባውን ፣ ህጋዊነትን ጠብቆ የግል የአገርን ና የመንግሥት ሀብት ወደራሥ ኪስ የማሥገባት አሰራርን ፣ ለምን ለሚመለከታቸው የበላይ አካላት በማሳወቅ የአገር እና የህዝብ ሀብት እየተመዘበረ ለምን ባላየ ታልፋላችሁ በማለት ይሟገታል ? ለምንስ ያለማቋረጥ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲሰሙ ይጮኻል ? ለምን ደርሶ አትርሱኝ __ ይላል ? _ የኢትዮጵያ ህዝብ የግለሰቦች ና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተቀናጀ የደላላ አሰራር ይወገድ ዘንድ ፣ ግልፅና ተጠያቂ የሆነ የንግድ ና የአገልግሎት ተቋምና አሰራር ይዘርጋ …ይላል ?
” የሚገርመው ደግሞ አንዳንዴም ‘ የውሸቱን ያንቀላፋ ቢቀሰቅሱት አይሰማም እና የእውነትና የውሸት እንቅልፍ ለዩ … ‘ማለቱ ነው ። አያሌ ጥያቄዎችን በሙሥና ዙሪያ በማንሳት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ተጎጂው ግለሰብ ና ህዝብ እንዲገነዘብ በማደረግ እኛን ለምን ያሳጣል ? እርሱ ማን ሥለሆነ ነው ከሁሉም ሰው ጋር ተናካናኪ ና ተጋጪ የሚሆነው ? እንዴ ! አናውቀውም እና ነው ? ምን ሥልጣን አለው ? የእኔ የሚላት ደሳሳ ጎጆ የሌለው መናጢ አይደል እንዴ ?! (… ) ” መዝረፍያ ቀዳዳ ሥላጣ እኮ ነው ፤ እንዲህ ገበናችንን በማሥጣት የሚያሳጣን ። ምቀኛ … ። _ …የማያልፍለት የለየለት እዬቻ ! …” ይሉሃል ።
እንዲህ የሚሉህ ሌብነታቸውን በመጠየፍ ፣ ግልፅ የሆነ ፀረ _ሌብነት አቋምህን በማሳየትህ ፣ የእነሱ ሰርቆ መክበር፣ የእነሱ ሙሥና ፣ የነሱ ከህግ በላይ መሆን ፣ የእነሱ‘ በልጅ አመካኝቶ አንጉቶ መብላት ‘ ተገቢ እንዳልሆነ እና ትውልድና ሀገርን ገዳይ መሆኑንን ፤ ህሊና ላለው ዜጋ ሁሉ ፣ ዘመኑ በለገሰህ የመገናኛ አውታር በማሳወቅህ ነው ።
አሁን እና ዛሬ ደግሞ መንግሥት ና የክልል መንግሥታት ጠንካራ ና ንፁህ ህሊና ያለቸው ባለስልጣናት እንብዛም ሥለሌላቸው ፣ በልጅ እያመካኙ አንጉተው የሚጎርሱ እንደሚበዙም ህዝብና ከመንግሥት የተሰወረ አይደለም ። አገርን ከመበታተን ለመታደግ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረትን ከማገዝ ይልቅ ፣ ሥንቅና ትጥቅ (ወይም ፣ የሎጀሥቲክ ደጋፍ ከማቅረብ ይልቅ) እንዴት እንደሚቀርብ ፣ የት ና መቼ የከተተውን ሠራዊት እየመገቡ በአጭር ሥልጠና ለወታደራዊ ግዳጅ ለማብቃት እንደሚቻል ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከመምከር ይልቅ ፤ እንዲሁም ባልተቋረጠ የሞራል ግለት ለአገሩ ክብር ና ለህዝቧ ልእልና ለመሞት የተዘጋጀውን በሚዲያቸው ከማበረታታት ይልቅ ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ፣ በዘፈን እና በከንቱ ውዳሴ የቴሌቪዢን የአየር ሰዓታን የሚገድሉ አሉ ። ወዳጄ ያለህበት ወቅትን አንተ ባለሥልጣኑ በዋዛ ካየኸው ሌለው ተራው ሰው ባላሰለሰ የወያኔ ፕሮፖጋንዳ ቢደነባበር በበኩሌ አይገረመኝም ።
የመንግሥት ሚዲያ የፕሮፖጋንዳ ማሽን የአሸባሪውን ትህነግ አፍራሽ ድርጊት እግር በእግር እየተከታተሉ ወዲያውኑ ለህዝቡ እውነተኛውን ዜና ለህዝቡ ከዛው ከጦርነቱ አውድማ ማሳወቅ ነበር ። ደግሞምም ” ለአገር መከላከያ የሚቀርበውን ሎጀሥቲክ እየዘረፉ ፣ በዝርፊያ መክበር ልማዳቸው ለሆነ ነጋዴዎች ፣ በደላሎች አማካኝነት የሚሸጡ ወይም በሥውር ረብጣ ዶላር ህሊናቸው ታውሮ ሥንቅና ትጥቁን ለጠላት የሚሸጡ ፣ በዚህም እኩይ ድርጊት ሚሊዮነር ለመሆን ያሰፈሰፉ አሉና ተጠንቀቁ ። ” ማለት የአንተ ሥራ ነበር ።
የአንተ ሥራን ግን ተነካናኪው አገር ወዳድድ ሥለተገበረው ፤ ” ምን ያገባዋል ? እየተባለ ይብጠለጠላል ። በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ለሃቅ ሲል ባገኘው ሚዲያ ከአገር ብልፅግና ጠሮች ጋር የሚጋጨውን ሁሉ በተነካናኪነቱ መረግም የተለመደ ሆኗል። የሚረግሙትም ለገንዘብ ፣ ለምቾትና ለድሎት እንጂ ፣ ለሰው ሁሉ የደስታ ኑሮ ቅንጣት ያህል የማይገዳቸው ፣ ፈጣሪን የማይፈሩ ዳቢሎሶች እንደሆነ ተነካናኪው ይገነዘባል።
ውድ አንባብያን ሆይ ፣ ተነካናኪ በመሆን ይኽ ፀሐፊ ፣ ከለውጡ ጀምሮ ፣ በአብዛኛው በለውጥ ኃይሉ መንግሥት ቅቡልነት ያለው ሃሳብ ቢያቀርብም ፣ ያቀረባቸው ሃሳቦች በሙሉ በአንድ ቀን ጀንበር ይተገበራሉ የሚል የሞኝ እምነት አልነበረውም ። በአገሩ ጉዳይ ተነካናኪ በመሆኑ እና በኢትዮጵያ ውሥጥ ያለውን እሥከ ዛሬ ያልታረመ፣ ከገንዘብ ጋር ቀጥታ የሚገናኙ አገልግሎት ሰጪዎችን እና በአጠቃላይ የክልል መንግሥታትን የቁጥጥር ሥርዓት ደካማነትን ዛሬም አፅኖት በመሥጠት የፌደራሉ መንግሥት በሂደት መፍትሄ እንዲያበጅለት ግን ይሻል። በተለይም ዛሬ ና አሁን መንግሥት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የእርስ በእርስ ጦርነትን ፋይል ለመዝጋት የፍፃሜ ጦርነት ሲያደርግ ፣ ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት የትህነግ ( ወያኔ) የመንግሥት አወቃቀርን እና የኔት ወርክ የሙሥና አሰራሩ ፣ ሙሉ ለሙሉ ያለተበጠሰ መሆኑንም መዘንጋት የለበትም ። በዚኽች አገር አያሌ ያልተፈነቀሉ ሆኖም ጊዜ ሳይሰጣቸው መፈንቀል ያለባቸው የሙሥና ድንጋዮች አሉ ።
ዛሬም በልጅ አመካኝተው አንጉተው የሚበሉ ያልተፈነቀሉ ድንጋዮች ናቸው። በህግ ሽፋን ፣ ህገወጥ ብዝበዛን የሚያቀላጥፉ ፣ ከለውጥ ኃይሉ ዐይን ያልተሰወሩ ሆኖም ግን በበቂ መረጃና ማሥረጃ እጦት ያልተያዙ እና ተገቢውን ቅጣት ያላገኙ አገርን ያቆረቆዙና በማቆርቆዝም ላይ ያሉ ሌቦች አሉ ። ከእነዚህ የማይረቡ አገርን እና ትውልድን እየገደሉ ያሉ ሌቦች ለአንዴ ና ለመጨረሻ ጊዜ አገር እሥካልተፋታ ጊዜ ድረሥ የግለሰቦች ኪስ እንጂ ፣ የሰርቶ በሌው ( የላብ አደሩ ፤ የአርሶአደሩ ና የአርብቶ አደሩ ) የህዝብ ኪሥ አያብጥም ። እናም ዛሬ እያቆጠቆጠ ያለው ደቡብ አፍሪካዊ እድገት ሥለሚሆን የተረጋጋ ሠላምና ቀጣይነት ያለው ብልፅግናንን አይወልድልንም ።
ይህንን እውነት በመረዳት ፤ “ የለውጡ ኃይል ከመሥከረም 30/2014 ዓ/ም በፊት ፣ በጥቅም አሳዳጆቹ ና ለአፍሪካዊያን ህይወት ደንታ ቢሥ በሆኑት ፣ በአሜሪካ ና በአንዳንድ የአውሮፖ መንግሥታት ድጋፍ በአሸባሪው ትህነግ እየተካሄደብን ያለውን ጦርነት ፣ በኩሩው ና ለክብሩ ሟች በሆነው በብልፅግና ናፋቂው የኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ክንድ ድል በመንሳት ፣ ፊቱን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ወደሚያሥተሳስር የፖለቲካ ውይይትና የጋራ መፍትሄ ማዞር ይኖርበታል ። ሁሉም ጎሣ ና ቋንቋ የአብሮነቱን ጠላት ለማጥፋት እንደዘመተ ሁሉ ፣ የሁሉም ክልል አመራር ወያኔያዊ የአጥር አሥተሣሠቡን ከህሊናው ጠርጎ በማሶገድ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ መሆኖን በተግባር ማሥመሥከር አለበት ። በተለይም እንደ መምህር ፣ የህክምና ባለሙያ ፣ የሂሳብ ሰራተኛ ፣ ቴክኒሻን ፣ መካኒክ ፣ ሹፊር ፣ የምግብ ባለሙያ ፣ ወዘተ ። የክልሉን ቋንቀበ ካላወቀ አይቀጠርም ማለት አፓርታይዳዊ መሆኑ መታወቅ አለበት ። ። በቀጥታ የክልሉን ቋንቋ ካላሥተማረና የቋንቋ አሥተማሪ እሥካልሆነ ጊዜ ድረስ አንድ የእንግሊዝኛ መምህር ሱማሊኛ ተናጋሪ በመሆኑ ብቻ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የመንግሥት ት/ቤቶች እንዳያሥተምር ለምን ይከለከላል ?
በየክልሉ ያሉ የተማረባቸው ዩኒቨርሥቲዎቹ የፊደራል እንደሆኑ ሁሉ በየክልሉ ያሉ መንግሥታዊ ተቋማት በሙያው ሊቀጥሩት ይገባል ።በሥራ ሰበብ ከእነሱ ጋር ሲኖር ቋንቋቸውን በቶሎ ያውቃልና ጥቅሙ ለራሱ ብቻ ሣይሆን ለአገርም ይሆናል ። “ ይልኻል ተነካናኪው ።