June 20, 2021
ጠገናው ጎሹ
አዲስና የሚያስገርም ነገር ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) እና ህሊናቸውን የሸጡ ቅጥረኞቻቸው የሚተውኑት እጅግ ርካሽ እና አደገኛ የፖለቲካ ድራማ ከምር ካላሳሰበንና የሚበጀውን እናደርግ ዘንድ ካላነሳሳን ነፃነትና ፍትህ የሚረጋገጥበት ሥርዓት ፈላጊነታችን ከተምኔታዊነት (ባዶ ተስፋነት) በፍፁም አያልፍም ።
እራሳቸው በአስከፊ ሁኔታ የደፈሩትን ወይም ሽባ ያደረጉትን የአገር (የህዝብ) ልኡላዊነት በውጭ ሃያላን መንግሥታት ተደፍሯል በሚል እራሳቸውን አሳልፈው ለርካሽ የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ቅጥረኝነት (ግብረበላነት) በሰጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ተባባሪነት የመከረኛውን ህዝብ ስሜት ለመቆጣጠር እና የትኩረት አቅጣጫውን ለማስቀየር የሄዱበት መንገድ ምን ያህል አስቀያሚ እንደሆነ ታዝበናል ። እየታዘብንም ነው።
የግፍ ሥርዓታቸውን የተቀባይነት (legitimacy) ካባ ለማልበስ ይጠቅመናል የሚሉትን እጅግ የለየለት ርካሽና አደገኛ የምርጫ ቁማር ለማሳካት እና “የድል ብሥራት ለማብሰር” የቀራቸው ጊዜ በቀናት ሳይን በአንድ ቀን ወይም በሰዓታት የሚቆጠር ነው። ይህ አይነት እጅግ ርካሽ ግን ደግሞ አደገኛ የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ በነዚያው የበግ ለምድ ለባሽ አሽቃባጭ (አድርባይ) ወገኖች አጃቢነት በመጧጧፍ ላይ ይገኛል።
እርግጥ ነው ቤተ መንግሥቱን በተረኝነት ከተቆጣጠረው እና ዓላማውና ግቡ ግልፅ ከሆነው የኢህአዴግ አንጃ ቡድን (junta) ከዚህ የከፋ እንጅ የተሻለ ነገር መጠበቅ አይቻልም። እጅግ አስቸጋሪና አሳዛኝ የሚሆነው የመከራው ፖለቲካ ማብቂያ እንዳይኖረው የሚያደርጉ የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮዎች በቁጥር ፣ በዓይነትና በአስከፊነት እየጨመሩ የመሄዳቸው መሪር እውነት ነው። ከኢዜማው መሪ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ (የትምህርት ደረጃ ማእረግ ሰብእናን ከክፉ ልክፍት አለመታደጉ አሳዛኝ መሆኑ ሳይዘነጋ) ከሰሞኑ የሰማነው የአደባባዩን ምሥጢር ጨርሶ የመካድ የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት የሚነግረን ይህንኑ እጅግ ግዙፍና መሪር እውነት ነው።
የበሰበሰውንና የከረፋውን ኢህአዴጋዊ (ብልፅግናዊ) ሥርዓት እንደ ሥርዓት በማስወገድ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደውን መሸጋገሪያ ድልድይ በጋራ (ቀጥተኛ የወንጀል ተጠያቂ ያልሆኑ ኢህአዴጋዊያንን ጨምሮ) ከመዘርጋት ይልቅ በሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች እጅግ አሳሳች አንደበት (ዲስኩር) ተጠልፈን በመውደቃችን ይኸውና የመከራና የውርደቱን ዘመን ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችላቸውን የ6ኛ ዙር “ታሪካዊ ምርጫ ድል አድራጊነት” ልንሰማ በሰዓታት የሚቆጠር ጊዜ ቀርቶናል።
ይህንን እኩይ የተረኛ ገዥ ቡድኖች የፖለቲካ ቁማር ድራማ የሰመረ (የተሳካ) ለማድረግ በግል ተወዳዳሪነት ስም የዋና ተዋናይነት ሚና የተሰጣቸው የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮዎችም የተሰጣቸውን ሚና በታማኝነት በመወጣት ቀድመው ያወቁትን የድል ብሥራት በይፋ ለመስማት ያለምንም የሞራል ሃፍረት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ።
እንደ ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ አይነት ትውልድን ቀርፆ ለመልካም ዜግነት የማብቃት እጅግ ከፍተኛ ሚና ያለው የመማርና ማስተማር ባለሙያዎች ነን የሚሉ ወገኖች “የምንወዳደረው በግል ቢሆነም የምንስፈፅመውና የምናስፈፅመው ዓላማና ግብ ግን የኢህአዴግ (የብልፅግና) ነውና ምረጡን” በሚል በመከረኛው ህዝብ መሠረታዊ የማገናዘብ ችሎታ (አቅም) ላይ ሲሳለቁበት ከመስማትና ከማየት የከፋ ህሊናን የሚያቆስል ነገር የለም። ቅን እና ሚዛናዊ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው።
ይህ ትውልድ በክፍል ውስጥ የሚያነበንቡትን ንድፈ ሃሳብ በሚችሉት አቅምና ሁኔታ በገሃዱ ዓለም በአርአያነት ለማሳየት አለመቻላቸው አልበቃ ብሎ እራሳቸውን ለለየለት የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ አሻንጉሊትነት አሳልፈው የሚሰጡ ወገኖችን “ነፃነትና ፍትህ በሚሰፍንባት አገር ውስጥ ሠርቶና ኮርቶ የመኖር እጣ ፈንታየን እያበላሻችሁብኝ ነውና አደብ ግዙ ” ለማለት የሚሳነው ከሆነ የተሻለ ነገን መመኘቱ ከባዶ ምኞት አያልፍም። ይህን ክፉ አዙሪት በመስበር የሚበጀውን ሁሉ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ለማድረግ ከተሳነው ከእራሱ መካከል የሚወጡና በተመሳሳይ የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮነት የሚለከፉ ወገኖች በሚተራመሱበት አስከፊ ሥርዓት ሥር መከራውን ሲቆጠር ይኖራል (ኑሮ ከተባለ)።
የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን አኮላሽተው ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን እኩይ ሥርዓተ ፖለቲካ ብልፅግና በሚል ስያሜ ቀይረው ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ያስቀጠሉት ተረኛ የኢህአዴግ አንጃዎች (juntas) አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ በእውን የሚያሳስበን ከሆነ እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ዓይነት ወገኖችን እጅግ አሳሳችና አደገኛ የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮነት ከነውርነት አልፎ ወንጀል መሆኑን በቀጥታና በግልፅ መንገር የግድ ነው።
ዲያቆን ዳንኤልን በግል አላውቀውም ። ያወቅሁትና ይበልጥ ለመከታተል የሞርኩት ከብዙ ዓመታት ጀምሮ የሚፅፋቸውን ፅሁፎችና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚደሰኩራቸውን ዲስኩሮች መከታተል ስጀምር ነው። ስከታተል ግን በአንፃራዊነት ችሎታውን ያሳየባቸውን ብእሩንና አንደበቱን ለምን አይነት ዓላማና ግብ ያውላቸው ይሆን? ለምድሩም ሆነ ለሰማያዊው ቤት ከሚበጅ (ከእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ሃይል) ጋር በፅእኑ መርህ ላይ ፀንቶ በመቆም የመልካም ዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ይጠቀምባቸው ይሆን? በአንፃራዊነት የጠንካራ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ሰብእና መገለጫነትን ከሚያንፀባርቁት የብእር እና የአንደበት ችሎታዎቹ ጋር በማያወላዳው የገሃዱ ዓለም ሠርቶ የማሳየት ፈተና ሲፈተን በፅእናት ፈተናውን ያልፍ ይሆን ወይስ የህወሃት የበላይነት መወገድን እንደ ጥሩ የመሽሎኪያ አጋጣሚ በመጠቀም ልፍስፍስና አሳሳች ( clumsy and disingenuous ) ሰበብ በመደርደር ፈተናውን ይወድቅ ይሆን? ከሚሉ ጥያቄዎችና ሂሳዊ እይታዎች ጋር እንጅ በስሜት በሚነዳ አቀራረብ አልነበረም ። ዛሬም አይደለም። ወደ ፊትም አይሆንም።
ለዚህም ነው ምንም እንኳ ፅሃፎቹና ዲስኩሮቹ ግልፅ፣ ቀጥተኛና ጠቃሚ የሆኑ አካደሚክና አጠቃላይ ፅንሰ ሃሳቦችን የሚያንፀባርቁ የመሆናቸው ጉዳይ ባይካድም ከፖለቲከኞች ጋር ያለመላተምና መስወእትነትን ያለመክፈል “ጥበብ” የተካነ ብእርና አንደበት ያለው ሰው መሆኑንም በሚገባ ለመረዳት ብዙም ያልተቸገርኩት ።
የሩብ ምእተ ዓመቱ እኩይ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ያስከተለውና የሚያስከትለው አስከፊ ውጤት አሳሳስቧቸው ድምፃቸውን ያሰሙ እጅግ አያሌ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ወገኖች ለግፍ ግድያና ለቁም ስቃይ ሲዳረጉ ዲያቆን ዳንኤል ግን ምንም አይነት የከፋ ሥጋት ወይም ጥቃት ሳይደርስበት “ታሪካዊውን የኢህአዴጋዊያንን (የብልፅግናዊያንን) የተሃድሶ ለውጥ” በታማኝ አማካሪነት እንዲቀላቀል የረዳውም ይኸው በአሉታዊነት እጅግ መሰሪ (cynical) የሆነው የፖለቲካና የሞራል ሰብእናው መሆኑን በግልብ ስሜት ወይም በሌላ የቲፎዞነት ፖለቲካ ካልታወርን በስተቀር ለመረዳት ጨርሶ አንቸገርም።
ከሰሞኑ በአንድ ሚዲያ (ባልሳሳት EBC) ላይ ቀርቦ ምርጫ ተብየውንና እና አማካሪነት ከሚሠራበት ገዥ ፓርቲ (ብልፅግና) ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሠራ መሆኑን በገለፀበትን ቃለ ምልልስ በትእግሥት ተከታትየዋለሁ ። ምንም እንኳ ባለፉት ሦስት ዓመታት በቅጥረኛ አማካሪነት ከሠራበትና አሁን ደግሞ ለፓርላማ አባልነት እያዘጋጀው ካለው የኢህአዴግ ግልባጭ ከሆነው ብልፅግና የተለየ ነገር ያወራል የሚል እምነት ባይኖረኝም መከረኛውንና የዋሁን ህዝብ ለቅጥፈት (ለማታለያነት) ባሰለጠነው አንደበቱ ምን ያህል እንደሚያታልለው ሳስብ ባይገርመኝም አዘንኩ።
የእራሱን የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮነት ፣ በአማካሪነት እያገለገለው ያለውንና ለደረሰው እጅግ አሰቃቂ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በዋናነት ተጠያቂ የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመከላከል የሄደበት የሃተታ ድሪቶ ህሊናን በእጅጉ ይፈታተናል። በግልብ ስሜታዊነት ቲፎዞነት ያልተጠመደ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው።
የግል ተወዳዳሪ የሚል ስም ቢሰጠውም የገዥው ፓርቲ የቅርብ ትብብር እንዳልተለየው በምሳሌ ሲያስረዳ ብልፅግና እርሱ በሚወዳደርበት አካባቢ ሌላ አባል ሳያቀርብ እርሱን ብቻ ለተወዳዳሪነት እንዲቀርብ ማድረጉን በኩራት ይነግረናል። መጀመሪያ ሊወዳደር ያሰበበት አካባቢ ከብልፅግና ጋር ጋብቻ መፈፀሙ እንደማይቀር የሚነገርለት የኢዜማ ተወዳዳሪ ለሆነው ለአንዱዓለም አራጌ በምክክር መልቀቁንም ይነግረናል ። ይህም የበግ ለምድ ለባሽነቱን ልክፍት ስፉትና አስከፊነት ይነግረናል።
እዚህ ላይ “አንዷለምን ለቀቅ” የሚሉ ወገኖች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ለዚህ ያለኝ መልስ አዎ! አንዱዓለም መስዋእትነት የከፈለ መሆኑን መካድ አይቻልም። ነገር ግን አሁን እየተነጋገርን ያለነው ስለ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እና ግለሰቦች ማበርከት ስለሚገባቸው በፅዕኑ ዓላማና መርህ ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ እንጅ ባለፈው ያስመዘገቡትን አስተዋፅኦ አሁን ለገቡበት የተሳሳተ የፖለቲካ ጨዋታ ማካካሻነት እየመነዘሩ እንዲጠቀሙበት አይደለም የሚል ነው። የትናንቱን ልማት በዛሬው ስህተት (ጥፋት) እንደ ክፍልፋይ ሂሳብ ስሌት (fraction) እያጣፉ የነፃነትና የፍትህ ትግል ብሎ ነገር የለም።
ዲያቆን ዳንኤል የእውነተኛ ሽማግሌና ሽምግልና እጥረትን (ድርቀትን) ለማስረዳት በወቅቱ በነበረው የዘውዳዊ አገዛዝ ለተሃድሶ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ከነበሩት ሁለት የዓለም የርእዮተ ዓለም ጎራዎች አንዱን በመውሰድ የተሻለ ለውጥ ያመጣ መስሎት ሲታገል የተገደለውንና የተገዳደለውን 1960ዎች ትውልድን ወደ ማብጠልጠል የተለመደ ትርክት የሄደበት አካሄድ አሁን እራሱም ለተዘፈቀበት እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት ማወዳደሪያ ሊሆን አይችልም።ከኢህአዴግ (ከብልፅግና) በባሰ በዓላማና መርህ ላይ በመቆም አገርን ለመታደግ የሚችል ሽማግሌ (ሽምግልና) እንዳይኖረን ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ እኩይ ሥርዓት ያለ ይመስል ሽማግሌ (ሽምግልና) አሳጡን እያሉ በደምሳሳው ማላዘን ፈፅሞ ቅንነትና መፍትሄ ፈላጊነት አይደለም።
ቅርስና ታሪክ ከሚያፈርሰው የሸፍጠኛ ሴረኛ ሥርዓት ጋር እየተላላሱ ብመረጥ ቅርስ አስጠብቃለሁ እያሉ መቀለድ ከቅንና ገንቢ የፖለቲካ ሰብእና የሚመነጭ አይደለም።
ችግሩ የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት እና የአንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች የሞራልና የመንፈሳዊነት ዝቅጠት እንጅ የመሥሪያ ቤት እጥረት ወይም አለመኖር ይመስል ብመረጥ የሃይማኖቶች ሚኒስቴር መ/ቤት እንዲቋቋም አስደርጋለሁ የሚል አይነት አስተሳሰብ ማራመድ ምን ይሉታል?
እራሱን በበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮነት ለሸፍጠኛና ለሴረኛ ገዥ ቡድኖች አሳልፎ መስጠቱ ለገንዛ ልጆቹ ሊያስተላልፍ የሚችለው አስቀያሚ መልእክት አሳስቦት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ወኔ የሌለው ሰው ስለ ሌሎች ልጆች ግራ መጋባት ተቆርቋሪ መስሎ መቅረብ ትርጉም ያለው ስሜት አይሰጥም ። በአጠቃላይ መሬት ላይ ካለው መሪር እውነት ጋር ጨርሶ የማይገናኝ የትርክት ድሪቶውን ከልብ ለሚታዘብ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓቱ ፍፃሜ ከባድና ረጅም ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት አይቸገርም።
ዲያቆኑ ይገጥምልኛል በሚለው ተረትና ምሳሌ እያስደገፈ በሰላ አንደበቱ ስለሚተርከው ትርክት ብዙ ማለት ይቻላል ። በግልብ ስሜትና በግልብ ቲፎዞነት ምክንያት ቀልባችን እያጣን ተቸግረን ነው እንጅ የእንዲህ አይነት ወገኖችን አስተሳሰብና አካሄድ ፈፅሞ ማስቆም ባይቻልም ብዙ እርቀት ሳይሄዱና ይበልጥ ጉዳት ሳያስከትሉ አንፃራዊ አደብ እንዲገዙ ለማድረግ በተቻለን ነበር።
እናም ይህ ትውልድ እየኖረበት ላለው ዘመን የሚመጥን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን መሥርቶ እንደ ዜጋ ተከብሮ፣ ተካባብሮና በልጽጎ የሚኖርባትን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ካለበት መንበረ ሥልጣኑን እየተፈራረቁ ከሚቆጣጠሩ ሸፍጠኛ ባለጌ ገዥ ቡድኖች ጋር እየተገለባበጡ የመከራና የውርደት ሥርዓትን የሚያራዝሙ የበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮዎችን ጨርሶ ማስወገድ ባይችልም በንቃት እየተከታተለ አደብ እንዲገዙ ማድረግ ይኖርበታል።
ይህ እንደሚሆን ተስፋና ምኞቴን እየገለፅሁ አበቃሁ!