ቀን፡ 01/10/2013
ባለፈው ሳምንት-ሐሙስ ‹‹የዓለም ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ እንዴት ይፈፀማል?›› በሚል፤ ጥቂት መረጃዎችን ተለዋውጠን ነበር፤ ከነዚህም ውስጥ ‹‹ከኢራቁ ዘመቻ መልስ!›› በሚለው ንዑስ ርዕስ፤ ትንሹ ቡሽ የሳዳም ሁሴንን ኑክሌር ታጣቂነት በአሜሪካን ኮንግረስ አሳምኖ የገባበት ጦርነት፤ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኪሣራ እንዳስከተለ፤ ‹‹የልዕለ ኃያልነት ክፍተቶች!›› ንዑስ ርዕስ ስር ድግሞ በፕሬዚደንት ባራክ፣ ትረምፕና በአሁኑ ፕሬዚደንት ባይደን አማካኝነት፤ ሲፈፀሙና እየተፈፀሙ ያሉ ክፍቶች ተደማሪ ሆነው፤ አሜሪካንን ‹‹የልዕለ-ኃያልነት ማብቂያ›› ላይ እያደረሷት እንደሚገኝ ተጨዋውተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ‹‹የዓለም ልዕለ-ኃያልነት›› ርክክቡን የተሟላ ሊያደርጉ የሚያስችሉ፤ ተጨባጭ መረጃዎች አካተን አብረን የምናረካክብ ይሆናል!! እነሆ፤
ዴሞክራቶቹ አይመቿትም!
እሥራኤል፤ ከእሥራኤልም ‹‹ናታንያሁ እና ተከታዮቻቸው››፤ የአሜሪካኖቹ ዴሞክራቶች ሁኔታ ብዙውን ጊዜ አይመቻቸውም፤ አሜሪካን በባራክ አስተዳደር ስር በነበረችበት 2015 ናታንያሁና ዴሞክራቶቹ፤ ካለመመቻቸት ወደመደባበር ከመደባበር ወደመካረር ተዳርሰው ነበር፤ ይህን ላስታውሳችሁ! በአሜሪካን የተመራው የተ.መ.ድ. የፀጥታው ምክር ቤት /P5+1/፤ በ2015 ከኢራን ጋር ባደረገው ‹‹ኑክሌር-ተኮር ስምምነት››፤ ዴሞክራቶቹ! እሥራኤል በማትፈልገው መንገድ መፍትሄ ሰጥተውበታል፤ ዴሞክራቶቹ! የእሥራኤል ‹‹አገር አቀፍ ምርጫ›› ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት ሞክረዋል /ልክ አሁን በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ተግባር ዓይነት ነው/፤ ዴሞክራቶቹ! ‹‹በፍልስጥኤም የይገባኛል ቦታ ላይ›› እሥራኤል የምታከናውነውን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንድታቆም ያስጠነቅቃሉ-ያስተባብራሉ፤ ዴሞክራቶቹ! ፍልስጥኤማውያን በተ.መ.ድ. ውስጥ የነበራቸውን ‹‹ተቀምጦ የማዳመጥ ብቻ መብት›› አሳድገው ‹‹አስተያየት የመስጠት መብት›› ያጎናፅፋሉ፤ ዴሞክራቶቹ! New-York በሚገኘው የተ.መ.ድ. ግቢ ውስጥ የፍልስጥኤም ሰንደቅ-ዓላማ ከሌሎች አገሮች እኩል እንዲውለበለብ ‹‹ድጋፍና እውቅና ይሰጣሉ››፤ ቤንጃሚን ናታንያሁ በነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ! ‹‹እሥራኤል ከዚህ በላይ በአሜሪካንና በዴሞክራቶቹ ምን እስክትሆን ትጠብቃለች?›› የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ የተገደደበት ጊዜ ነበር 2015!!
ከላይ የተጠቀሱትን ተጨባጭ መረጃዎች ስትመረምሯቸው፤ ‹‹ዴሞክራቶቹ ምን አጠፉ ታዲያ?›› ልትሉ ትችላላችሁ፤ ይህን የናንተን ጥያቄ የሚመልሰው ቤንጃሚን ናታንያሁ ራሱ ነው! ምክንያቱም እኔ የተነሳሁበት ዓላማ ለዓለም ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ የሚያበቁ ግብአቶችን መሰብሰብና ስዕል መስጠት ስለሆነ ነው፤ ለምሣሌ ናታንያሁ ‹‹ዴሞክራቶቹ ትክክል አልሰሩም›› ብሎ ‹‹ከመደባበር እስከ መካረር›› ከደረሰባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፤ የ2015 ውጤታማ ድርድር የተባለውና ኢራን ኑክሌርን ለጦር-መሣሪያ እንዳታበለፅግ የተደረሰበት ስምምነት ነው፤ ናታንያሁን ‹‹በዚህ ለምን ተከፋህ?›› ብላችሁ ስትጠይቁት “Cash-Bonanza!” ብሎ ይመልስላችዃል፤ የናታንያሁን Cash-Bonanza! ምንነት ስትመረምሩ ደግሞ ኢራን ከP5+1 የደረሰችበት ስምምነት፤ የንግድና የጉዞ ማዕቀቦቸ እንዲነሱላት የሚያስችል ነው፤ ቀጣዩን ከናታንያሁ ይልቅ እኔ ግልፅ ባደርግላችሁ ይሻላል! UN-Security Council እና ምዕራባውያን በግላቸው በኢራን ላይ የጣሉባት ማዕቀብ ሲነሳላት፤ ለዓመታት አምርታ ያከማቸችውን 157,530,000,000 በርሜል ነዳጅና ወደፊት የምታመርተውን ነዳጅ ሳትሳቀቅ ለዓለም ትሸጣለች! በረብጣ-ገንዘብም ትንበሸበሻለች!! /የቁጥር ምንጭ፡-worldometer/፤ ባይገርማችሁ እኔ ራሴ Cash-Bonanza ከኑክሌር በላይ እንደሚያስፈራራ ያወኩት ከቤንጃሚን ናታንያሁ ድንጋጤ ነው፤ ቤንጃሚን ናታንያሁ ከላይ ከተገለፁት ‹‹የማይቀበላቸው ድርጊቶች›› በዃላ፤ ከድንጋጤና የአሜሪካን ዴሞክራቶችን ከማኩረፍ ባለፈ፤ በእሥራኤል ሥም ‹‹እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ›› ያደርጋል!!
ናታንያሁ በዚህ ‹‹እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ››! ነሸጥ ሲያደርገው በሰርጓጅ ጀልባ እባሕር ውስጥ እየገባ፤ K-19 የተሰኘውና ኑክሌር ጦር-መሣሪያ የተገጠመለት ባሕር ሰርጓጅ መርከብ፤ በ1960ዎቹ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የነበረውን ጀብደኛ ተግባር፤ በትዝታ የሚያጣጥም ሰው ከሚገኝበት ሩሲያ ፌዴሬሽን ሄዷል፤ ፑቲንን ለማግኘት!! ናታንያሁ ወደሩሲያ በተደጋጋሚ ቢሄድም የሄደበትን ጉዳይ እስካሁን ማንም በዝርዝር ሊያውቀው አልቻለም፤ ከሩሲያ ‹‹ሄድ መለስ፤ ደሞ ጎርደድ መለስ›› በዃላ ከታዩ ኩነቶች ግን መረዳት ይቻላል፤ ያም የዶናልድ ጄ. ትረምፕ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ሆኖ መከሰት ነው!! የትረምፕ መከሰት ‹‹ለልዕለ-ኃያልነት ርክክብ መቃረብ›› እንዴት ግብአቶችን እንዳበረከተ አሁን እንመለከታለን!! እንሆ፤
የትረምፕ አበርክቶ!
ትረምፕ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ሆኖ ሲከሰት፤ ፈጥኖ ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ Multi-lateral የነበሩትን የንግድ ስምምነቶች ወደ Bi-lateral ስምምነት መቀየር ነበር፤ ከነዚህም ውስጥ ከTrans Pacific Partnership-TPP እና ከNAFTA ስምምነት አሜሪካንን በማግለል፤ የተናጥል ስምምነት እንድታደርግ የወሰደው እርምጃ ሲሆን፤ ይህ የትረምፕ ተግበር ቻይና ጎልታ እንድትወጣ በር የከፈተ እንደነበር ባለፈው ተጨዋውተናል፤ ትረምፕ Make American Great Again-MAGA በሚለው መሪ-ቃል፤ ካካተታቸው ፖሊሲዎች ውስጥ ‹‹አሜሪካን በበርካታ አገራት ያሏትን የማኑፋክቸሪንግ ካምፓኒዎቻን ነቅላ ወደአገሯ ታስገባ›› የሚል ነው፤ ይህ የትረምፕ እቅድ ተግባራዊ ቢሆን! አሜሪካን በተለያዩ አገራት በማኑፋክቸሪንግ ካምፓኒ ልትፈጥር የነበረውን ክፍተት፤ ቻይና፣ ሩሲያና ሕንድን የመሰሉ አገራት ክፍተቱን እንዲሞሉ የሚያስችላቸው ነበር /ምንም እንኳ ይህ እርምጃ ቻይናን የሚጨምር ቢሆንም/፤ የልዕለ-ኃያልነት ርክክቡንም ሊያፈጥነው በቻለ ነበር! ምን ዋጋ አለው! ይህ የትረምፕ ፖሊሲ ተግባራዊ አልሆነም!!
ፕሬዚደንት ትረምፕ በአራት ዓመታት የሥልጣን ቆይታው አንድ ሊነገርለት የሚገባ ስኬት አስመዝግቧል፤ ይኸውም አሜሪካን I.S.I.S. የተባለውን የሽብር ቡድን ለማጥፋት ፍላጎት የላትም እየተባለች፤ ከፖለቲካ ተመልካቾች ዘንድ ወቀሳ ይቀርብባት ነበር፤ ለዚህ ወቀሳ እነባራክ ‹‹ሽብርተኛው ቡድን ላይ ከሁሉም የበለጠ ቦንብ የጣልነው እኛ ነን›› ሲሉ መልስ ሰጥተውበታል፤ ነገር ግን የነባራክን ዲፕሎማሲያዊ የማድበስበሻ ቃላት ትረምፕ አይቀበለውም! ‹‹ኢሄ የፖለቲከኞች የሤራ ጨዋታ ነው›› እያለ ይነቅፋቸዋል! በርግጥም ኢራን I.S.I.S. የተባለውን የሽብር ቡድን እንድታጠፋ ከኢራቅ ግብዣ ሲቀርብላት፤ ባጭር ጊዜ ሽብርተኛውን እየጠራረገች ከኢራቅ ምድር ስታስወጣ ተመልክተናል፤ ይህን እውነታ ባስተዋሉ የፖለቲካ ተመልካቾች ዘንድ ‹‹አሜሪካን ምን-ነክቷት ነበር›› አስብሏል፤ ችግሩ የኢራን ጦር ከኢራቅ ለቆ ሲወጣ ሽብርተኛው ቡድን መልሶ ቦታውን ይቆጣጠራል፡፡ ፕሬዚደንት ትረምፕ ሽብረተኛ ቡድኑን ለማጥፋት የተከተለው መንገድ ሁለት ነበር፤ ‹‹ሽብርተኛው የተቆጣጠራቸውን የነዳጅ ቦታዎች ማስለቀቅ›› እና ‹‹የሽብርተኛውን የገቢ ምንጮች ማድረቅ›› የሚል!! ትረምፕ የሽብርተኛውን የገቢ ምንጭ ለማድረቅ በዋናነት ያነጣጠረው አንዲት አገር ላይ ነበር! ሳዑዲ አረቢያ!! የወሰደው እርምጃ የሳዑዲ ባለሀብቶችን ሰብስቦ ማሰር ወይም ባለ 5 ኮከብ Ritz Carlton ሆቴል ውስጥ ሰብስቦና እንዳይወጡ አርጎ ማዝናናት ነው፤ ትረምፕ በዚህ ዘዴ የሽብርተኛውን የገቢ ምንጭ ማድረቅና ቡድኑን ማዳከም ችሏል!!
ግን ፕሬዚደንት ትረምፕ ይህን ውጤታማ ተግባሩን ሊያስረሳ የሚችል አንድ ጉልህ ስህተት ሠራ! December 26, 2018 የኢራቅ ባለሥልጣናት ሳያውቁ በድንገት ኢራቅ ተገኝቶ! የአሜሪካንን (የራሱን) ወታደሮች ጎበኘ! ይህ የፕሬዚደንት ትረምፕ ተግባር በኢራቅ ምክር ቤት ውስጥ ቁጣ ቀስቅሶ፤ ባስቸኳይ ወታደሮቹን ከኢራቅ እንዲያስወጣ ባለሥልጣናቱ ትዕዛዝ እንዲሰጡ አስገድዷል፤ ትረምፕ በዚህ ጉልህ ስህተቱ ‹‹ለዓለም ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ የሚጠቅም አበርክቶ›› ጥሎ አልፏል፤ እንቀጥል!
ሌላው ፕሬዚደንት ትረምፕ ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ፤ በDecember 20, 2018 አፍጋኒስታን የሚገኘው የአሜሪካን ጦር በከፊል ለቆ እንዲወጣ፤ ለፔንታጎን /Pentagon/ መመሪያ የሰጠበት ተጠቃሽ ነው፤ ይህ የትረምፕ መመሪያ ‹‹የልዕለ-ኃያልነት ርክክብ ፍንጭ›› መሆኑን የምንረዳው፤ በNovember 9, 2018 የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹ሰርጌ ላቭሮቭ››፤ ከአፍጋኒስታን መንግስት እና ከታሊባን ልዑኮች ጋር አስቀድሞ በሞስኮ ካደረገው ውይይት ነው፡፡
ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት!
እንደአንድ የፖለቲካ ተመልካች እንደተረዳሁት፤ ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት›› ከተጀመረ 5 (አምስት) ዓመታት አልፎታል፤ ጅምሩም የሚከተለውን ይመስል ነበር! ብዙ ጊዜ እንደተመለከትነው የዓለም ልዕለ-ኃያልነቷን በገዛ እጇ ጥያቄ ውስጥ የከተተችው አሜሪካን፤ ከዓለም-አቀፍና ከቀጠና ሽብርተኞች ጋር ልፊያ ስታካሂድ /ስትዋጋ/ ‹‹ስራሽ ያውጣሽ የሚሏት››፤ እንዲሁም ከአገራት አመራሮች ጋር በሚኖራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አለመግባባቶች፤ መንግስትን ወይም ሥርዓትን ለመቀየር በምትወስደው የጦር እርምጃ፤ ‹‹ፅኑ የተቃውሞ ውሳኔ›› የሚያስተላልፉባት፤ አሜሪካን ግብታዊ ጦርነቷን ጀምራ እስክትጨርስ ወይም ደክሟት እረፍት እስክትወስድ፤ እግር-በግር እየተከታተሉ የሚያጋልጧትና የሚያሸማቅቋት፤ ሁለት የዓለማችን ኃያላን አገራት አሉ! ‹‹የሩሲያ ፌዴሬሽን›› እና ‹‹የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ››!!
ላለፉት 5 ዓመታት ለተቀሰቀሰው ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት›› ተግባራዊ ምላሽ የሰጠችው የሩሲያ ፌዴሬሽን ናት! በ2003 አሜሪካን በሳዳም ላይ የወሰደችውን እርምጃ እየተቃወመች የተመለከተችው፤ በ2011 የሙሀመር ኤል-ቃዳፊ አገር ሊቢያ ሰትደበደብ እንዲሁ ቅሬታ እያቀረበች ብቻ የተመለከተችው፤ ቀስ-በቀስ ወዳጅ አገር እና መሪ እያጣች መሆኑ ተሰምቷት! ‹‹የፕሬዚደንት በሽርን መደብደብ እንኳ ቆሜ አልመለከትም አሻፈረኝ!›› በማለት፤ September, 2015 በሶሪያ ጦርነት ውስጥ ጣልቃ ገብታ የተዋጋች እና የአሜሪካንን ፍላጎት ያከሸፈችው አገር ሩሲያ ናት!! በመሆኑም ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት›› የተጀመረው፤ ‹‹ልዕለ-ኃያልነቴን አስጠብቄ መዝለቅ ይገባኛል›› በምትለው አሜሪካን እና ‹‹አሜሪካን ኃያልነቷን በፍትሀዊነት አልተጠቀመችበትም›› በምትለው ሩሲያ! ‹‹በሽርን ለማስወገድ እና ለመታደግ›› ሶሪያ ምድር ላይ ባደረጉት ትንቅንቅ ነው፡፡
ከዛሬ 5 ዓመታት በፊት በሶሪያ ምድር የተጀመረው! ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት ነው›› ለማለት የሚያስደፍረን፤ አሜሪካን በቀጠናው የነበረውን ጦርነት ለማስፋት የሄደችበት ርቀት እና ሩሲያ ይህን የአሜሪካን ‹‹ያልተገባ ፍላጎት››፤ ጥንቃቄ በተመላበት ብልህ መንገድ የተወጣችበትን ኩነት ስንቃኝ ነው፤ ኢሄን ላስታውሳችሁ! ሩሲያ ፕሬዚደንት በሽርን ለመታደግ ያደረገችው ማጥቃት አይሎ በታየበት ጊዜ፤ በNATO እቅፍ ውስጥ የምትገኘው ቱርክ የሩሲያን የጦር ጄት በጦር-መሣሪያ መታ-እንድትጥል ተደረገ /November 24, 2015/፤ ይህ የቱርክ ተግባር ሩሲያ ያፀፋ-መልስ እንድትሰጥ የሚያስገድድ ‹‹ትንኮሳ›› ነበር!! ሩሲያ ከዚያው የሶሪያ ጦር ሰፈር ሆና ለቱርክ የአፀፋ መልስ ሰጥታ ቢሆን ኖሮ! በምላሹ የሚጠብቃት የቱርክ ጦር ሳይሆን የ27 አገራት ጥምረት የሆነው የNATO የጦር ድብደባ ነበር፤ ሩሲያ በዚህ የNATO ውርጂብኝ እንኳን ፕሬዚደንት በሽርን ልትታደግ! በሶሪያ የሚገኘውን የራሷን ጦር-ሠራዊት ዳግመኛ አታገኘውም ነበር!! ስለዚህ የሩሲያ መንግስት ለዚህ ‹‹የቱርክ የትንኮሳ ጥቃት›፤› ገንዘባቸውን የሚረጩ ሩሲያዊ ቱሪስቶች ከቱርክ እንዲወጡ አድርጋ፤ ሌላውን ሕመሟን ቻል ማድረግ መርጣለች፤ በመጨረሻም ሩሲያ ‹‹ኢሄ የአሜሪካን ተንኮል ነው›› ብላ ቱርክን ታርቃ፤ ቱርክን በአሜሪካን ላይ እንድትነሳ አድርጋታለች፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን! ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት›› በዚህ መልኩ ተጀምሮ፤ ‹‹ቀዝቃዛውን ርክክብ›› ከጎን አድርጎ እየቀጠለ የሚገኝ መሆኑን ነው!! እባካችሁ ለዚህ ጉዳይ አፍሪካ ቀንድና ቀይ-ባሕር ላይ የተመሠረተ ቀጭን መጠቅለያ እናብጅለት፡፡ እንሆ፤
ቀጭን መጠቅለያ!
አሁን በቀጠናችን የሚገኘው ‹‹ቀይ-ባሕር ተኮር›› ፍጥጫ! ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት›› መቋጫውን በአፍሪካ-ቀንድ ላይ የሚያደርግ መስሎ ይታያል፤ ለዚህ ሀሳብ ፍንጭ ከሰጡን ኩነቶች ውስጥ፤ ሩሲያ በቀይ-ባሕር ቦታ ለማግኘት በማሰብ ከሱዳን ጋር የገባችው ውል፤ ተፈፃሚ እንዳይሆን በሱዳን በኩል ሊያዝ የታሰበው አቋምና ከሩሲያዋ ክሬምሊን የሚወጡ የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች፤ ኢትዮጵያ በቀይ-ባሕር ላይ የያዘችው ግልፅ አቋምና የኤርትራ ትብብር፤ አሜሪካን የራሷንና የአረብ አገራት ወዳጆቿን በቀይ-ባሕር ላይ አለን የሚሉትን ጥቅም ለማስከበር በማሰብ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን ችግር እንደክፍተት ለመጠቀም መሞከር፤ የግብፅ መንግስትና የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት በጋራ ሆነው፤ ኢትዮጵያ እያጠናቀቀች በሚገኘው የህዳሴ ግድብ ‹‹ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ድርድር›› ላይ የያዙት የተዛባ አቋም፤ የሱዳን ወታደሮች ወደኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ መግባት፤ እንዲሁም ሩሲያና ቻይና በጋራ ሆነው ልዕለ-ኃያሏን አሜሪካን ለመገዳደር እያሳዩት ያለው አሰላለፍ፤ እነዚህ ሁሉ ነባራዊ እውነቶች ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት›› መቋጫውን በአፍሪካ-ቀንድ ላይ እንደሚያደርግ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ‹‹የቀዝቃዛው ጦርነት ፍፃሜ›› አውዳሚ እንዳይሆን ወይም ውድመት የቀነሰ እንዲሆን መስራት፤ የአፍሪካ-ቀንድ አገራት አመራሮች ኃላፊነት ነው! በመሆኑም ‹‹ሁለተኛው ቀዝቃዛ ጦርነት ገና አልተጀመረም›› ወይም ‹‹ገና ይመጣል›› ብለን እየተዘናጋን ከሆነ! በመዘናጋታችን ልክ ዋጋ የሚያስከፍለን ይሆናል!! ጤና ይስጥልኝ፡፡
ማስታወሻ፡-
- የተከበራችሁ አንባቢያን ‹‹የዓለም ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ›› የተሟላ ግብአቶችን ለማስቃኘት ባደረኩት ሙከራ ስለረዘመብኝ፤ ከይቅርታ ጋር ርክክቡን በሚቀጥለው ፅሁፍ አከናውነን እንቋጫለን፤ በፈጣሪ ፈቃድ!!
ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ
ቴዎድሮስ ጌታቸው /የፖለቲካ ተመልካች/
ድሬዳዋ