መሰረት ተስፉ ([email protected])
ባሁኗ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ገዥ የሆነው አስተሳሰብ የብሄር ፖለቲካ እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ብሄር ብሄረሰቦች ከአንድ በላይ የሆኑ የየራሳቸውን ብሄራዊ አደረጃጀቶች ፈጥረው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። በነዚህ ብሄራዊ አደረጃጀቶች ውስጥም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የየብሄሩ አባላት እየተሳተፉባቸው ይገኛሉ ቢባል ስህተት አይሆንም። አማራን እንወክላለን በሚል የተደራጁት ግን ብዙውን ጊዜ ውጤታማ ሲሆኑ አይታዩም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ አማራዎች ኢትዮጵያዊ በሚለው ስነልቦና የተቃኙ በመሆናቸውና በአማራነት ቢደራጁ ከዚህ ስነልቦና የሚያፈነግጡ መስሎ ስለሚሰማቸው ነው ብየ አስባለሁ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜስ ራሳቸው በአማራነት ተደራጅተው ለአማራ ህዝብ ፍትሃዊ ጥቅሞች ከመታገል ይልቅ የተደራጁትንም ሲያጣጥሏቸውና ለማዳከም ጥረት ሲያደርጉ የሚስተዋሉበት ጊዜ በርካታ ነው ማለት ይቻላል። አለፍ ሲሉም በአማራ ስም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ያዳከሙ መስሏቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ግን የአማራን ህዝብ መሰረታዊ መብቶች ሲፃረሩና ህልውናውን ሲጋፉ ማየት የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ የአማራ ህዝብ በቅርቡ መገደልና መፈናቀል ይብቃኝ ብሎ ሆ ብሎ ተነስቶ ያካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ከአንድ ፓርቲ ጋር ለማቆራኘት ሲንደፋደፉ የታዘብናቸውም አሉ። ሌሎቹ ደግሞ በኦነግ የጥላቻ አስተሳሰብ እየተመራ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረግን ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀልና ንብረት ማውደም ከማውገዝና ከመኮነን ይልቅ ምክንያቶቹ “የአማራ ሙሾ አውራጆች” ናቸው እያሉ ጥፋተኝነትን misplace በሚያደርግ መልኩ የሚሳለቁና በአማራ ህዝብ ቁስል ላይ ሚጥሚጣ የሚነሰንሱም አልጠፉም። ከዚህ ጎን ለጎንም ለአማራ ህዝብ ቀና አመለካከት ለሌላቸው ሃይሎች ፈረስ ሆነው የሚያገለግሉ እንዳሉም መካድ አይቻልም። ብልፅግና ውስጥ ያሉ አማራዎች ደግሞ የአማራን ህዝብ ጥቅም የምናስከብረው ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመሆነ ነው የሚለው መንገዳቸው ትክክለኛና አዋጭ ቢሆንም በተግባር ግን የሚናገሩትን እየተገበሩት ነው ለማለት የሚያስችል ማስረጃ ብዙም የለም። በመሆኑም ከሌሎች የሚመጣን ጫና መክቶ ስርዓትና መልክ እንዲይዝ በማድረግ ረገድ መሰረታዊ የሆነ ችግር ይታያል።
በዚህ ሁኔታ ለአማራ ህዝብ እቆረቆራለሁ የሚል የአማራ ሃይል መፈጠሩ ተፈጥሯዊ ነው ብየ አምናለሁ። የአብን አፈጣጠር መታየት ያለበትም ከዚህ አንፃር ነው። አብን ወደ መድረክ ብቅ ያለው የአማራ ህዝብ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ እየተጠቃ ነው፤ እንዲሁም አሁን ያሉት የአማራ አደረጃጀቶች ህዝቡን በሚገባ ከጥቃት አልተከላከሉትም ከሚል እሳቤ ተነስቶ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ አብን ከምስረታው ጀምሮ ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ በግልፅና በአደባባይ የአማራ ህዝብ ድምፅ ሆኖ ለመንቀሳቀስ ጥረት በማድረጉ ምክንያት የመጡ ለውጦች እንዳሉ መረዳት ይቻላል። ቢያንስ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ አማራዎችን ከእንቅልፋቸው እየቀሰቀሳቸው እንደሚገኝ ለመረዳት አይከብድም።
በነዚህና በመሰል መንገዶች የሚገለፁ የአብን በጎ ጎኖች እንዳሉ ለመናገር ባይከብድም በርካታ ችግሮች እንዳሉበት አለመግለፅ ደግሞ የአማራ ህዝብ እጣ ፋንታ እንዲወሳሰብ ከሚደረግ ጥረት ተለይቶ አይታይም ባይ ነኝ። ስለዚህ አብን አሉበት ብየ የማስባቸውን ችግሮች በተወሰነም ቢሆን በሚከተለው መንገድ ለመግለፅ እወዳለሁ።
አብን ያለበት አንድ ችግር አባላቱን በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ያለማሸትና ያለመቅረፅ ግድፈት ነው ብየ አምናለሁ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ አባላቱ የሰዎች መሰረታዊ የእኩልነት መብትን የሚፃረሩ ንግግሮችን ሲያደርጉ ይደመጣሉ። ይህ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ሂደት ላይ የራሱ የሆነ ተፀእኖ ማሳደሩ አይቀርም።
ሁለተኛ “አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን” የሰሩት ስራ ሁሉ እንከን አይወጣለትም የሚል አቋም መያዛቸው ችግር ነው ብየ አስባለሁ። በዚህ ረገድ አገር በመገንባት ሂደት የጎላ ድርሻ የነበራቸው አያቶችና ቅድመ አያቶች የፈፀሟቸው አስደማሚና ምሳሌያዊ የሆኑ ተግባራት የነበሩትን ያህል ይከተሉት ከነበረው ፊውዳላዊ ስርዓት ባህሪያት ተነስተው የፈፀሟቸውን ድክመቶች አለመቀበል ግን ግመስል ስርቆ አጎንብሶ አይነት ድርቅና ነው የሚሆነው።
ሶስተኛው የአብን ችግር ከአደረጃጀት ጋር የተያያዘ ነው ብየ አስባለሁ። እስካሁን ባለኝ ትዝብት የአብን ትኩረት ከተሞች ላይ እንደሆነ ተረድቻለሁ። የአማራ ህዝብ ደግሞ በብዛት የሚኖረው ገጠር ውስጥ ነው። ይህን ህዝብ ያላንቀሳቀሰ የአማራ ነኝ የሚል ፖለቲካ ፓርቲ ለስኬት እንደማይበቃ አብን ሊረዳ ይገባል ባይ ነኝ።
ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ሌላው የአብን ችግር በፌዴራል መንግስት ደረጃ የስልጣን ተጋሪ የሚሆነው በምን መንገድ እንደሆነ የቀየሰው ታክቲክና ስትራቴጅ ግልፅ አለመሆን ነው። በሌላ አነጋገር አብን ፌዴራል መንግስቱን ለመምራት የሚያስችል ቁመና ላይ ነኝ ይበል እንጅ በምን መንገድ እንደሆነ ግልፅ አድርጎ ያስቀመጠው እቅድ መኖሩን አልሰማሁም። እንደሚታወቀው የፌዴራል መንግስቱን ለመምራት ቢያንስ 274 የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ድምፅ ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በሁለት መንገዶች ነው። አንደኛው ሃገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ በሁሉም ወይም በብዛኛዎቹ ምርጫ ክልሎች እጩዎችን አቅርቦ በመመረጥ አብላጫ ድምፅ ማግኘት ከተቻለ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የብሄር ድርጅቶች (እጩ የሚያቀርቡት በየሚንቀሳቀሱበት ክልል ቢሆንም) ተዋህደው ወይም ተጣምረው ካልሆነም ቅንጅት ፈጥረው አንድ ላይ ለመስራት በመስማማት በምርጫ ተወዳድረው በሃገር አቀፍ ደረጃ አብላጫ ድምፅ ማግኘት ሲችሉ ነው።
አብንን ስንመለከት ግን ከላይ የተቀመጡትን ሁኔታዎች የሚያሟላ አይመስልም። ሲጀመር ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ላይ እጩዎችን አላቀረበም። ሌላው ቀርቶ አማራ ክልል እንኳ በሁሉም አከባቢዎች እጩዎችን ያቀረበ አልመሰለኝም። ሁለተኛ ከሌሎች ክልላዊ ፓርቲዎች ጋር ተዋህዶ፣ ተጣምሮ ወይም ተቀናጅቶ አገር ይመራል እንዳይባል እንኳ ከባልደራስ ውጭ ካሉ ሌሎች ብሄራዊ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ሁኔታዎችን ሲያመቻች አልታዘብኩም።እንበልና አብን አማራ ክልልን፤ ባልደራስ ደግሞ አዲስ አበባንም ሆነ ድሬዳዋን ሙሉ በሙሉ ቢያሸንፉ እንኳ የፌዴራል መንግስቱን ለመምራት የሚያስችል ድምፅ ሊያገኙ አይችሉም። ታዲያ በዚህ ሁኔታ በምን መመዘኛ ነው አብን ፌዴራል መንግስቱን ስለመምራትና ኢትዮጵያን ስለማስተዳደር የሚያወራው??? እንኳንስ ብቻውን ከባልደራስ ጋር ሆኖስ በፌዴራል ደረጃ ያለውን የፖለቲካ ስልጣን እንዴት ሊጋራ ይችላል??? ይህ ካልሆነ ታዲያ በየት በኩል አድርጎ ነው ህገመንግስቱ እንዲሻሻል እንዲሁም ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የአማራ መብት እንዲጠበቅ አሁን ከሚያደርገው የላቀ ሚና ሊኖረው የሚችለው???
ከነዚህ ጥያቄዎች ተነስቸ አብንን ስገመግመው የአማራ ክልልን መንግስታዊ ስልጣን የመቆጣጠር እድል ቢኖረው እንኳ በፌዴራል ደረጃ የተወሰኑ መቀመጫዎችን አግኝቶ የአማራን ህዝብ ጥያቄዎች ከማስተጋባትና የተለያዩ ሰላማዊና ህጋዊ ትግሎችን ከማድረግ ውጭ በፌዴራል መንግስቱ ደረጃ ስልጣን ሊጋራ የሚችልበት እድል ይኖረዋል ብየ አላምንም። ይህ ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ በፌዴራል ደረጃ ባለው የአማራ ህዝብ ጥቅም ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም። በፌዴራል ደረጃ መንግስታዊ ስልጣኑን መጋራት የማይችል ከሆነ ደግሞ ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ አምራዎችን ጥቅም ለማስከበርና ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል መዋቅራዊ ክህሎትም አይኖረውም። ህገ መንግስቱ እንዲሻሻል መጠየቅና መታገል መብቱ ቢሆንም አቻ ከሆኑ ሌሎች ፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ወይም በመጣመር የሚያስፈልገውን አብላጫ ድምፅ ማግኘት ካልቻለ ሃሳቡና ፍላጎቱ እውን የሚሆንበት ሁኔታ ጠባብ እንደሆነም ለመገመት አይከብድም።
ስለዚህ እንደኔ ፍላጎት ምኞት ቢሆን አብን በዚህ ምርጫ አማራ ክልል ላይም ሆነ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውስጥ የተወሰኑ መቀመጫዎችን አግኝቶ የአማራ ብልፅግናዎች እንዳይተኙና መንግስታዊ መዋቅሩን ህጋዊ በሆነ መንገድ ተጠቅመው የአማራን ህዝብ ፍትሃዊ መብቶች እንዲያስከብሩ የሚጎተጉትና የሚያነቃ ሃይል ሆኖ ቢቀጥል እመርጣለሁ። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለሚቀጥለው ምርጫ የአማራን ህዝብ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ሊወክል ይችል ዘንድ ሙሉ ቁመና ይዞ እንዲቀርብ የአደረጃጀትና የፖለቲካ ብቃቱን ማዳበር ይገባዋል ባይ ነኝ። ይህ በዝርዝር ሲታይ የሚከተሉትን ያካትታል።
- ውስጣዊ አደረጃጀቱን በማጠናከር በከተሞች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ገጠሮች ውስጥ መኖሩንም ማረጋገጥ ለምርጫ የሚተው አለመሆኑን ማጤን ያስፈልገዋል።
- በሰው ልጆች እኩልነትና በመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች እንዲሁም መርሆዎች ላይ ተመስርቶ አባላቱን መገንባት ይጠበቅበታል።
- በሌሎች ክልሎች ካሉ አቻ ፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ወይም ተጣምሮ በፌዴራል መንግስቱ ደረጃ ስልጣን ሊጋራ የሚችልባቸውን መንገዶች የሚተልም ስልትና ስትራቴጅ በመንደፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።
አብን በሚቀጥሉት አምስት አመታት እነዚህን ካሟላ ክልሉን መምራት ብቻ ሳይሆን በፌዴራል መንግስት ደረጃም የፖለቲካ ስልጣን ተጋርቶ የአማራን ህዝብ ፍትሃዊ ጥቅሞች ሊያስከብር የሚችል የፖለቲካ ሃይል እንደሚሆን ለመገመት የግድ ትንቢት ተናጋሪ መሆንን አይጠይቅም።
ቸር እንሰንብት!!!