ዉይይታቸዉ እንዲያተኩር የፈለጉት አሜሪካ በምትባል ሀብታም ሉዓላዊ ሀገር ያሉ ሴኔተሮች ኢትዮጵያ በምትባል ደሀ ሉዓላዊ ሀገር ላይ ባወጣዉ አስር ምክረ ሐሳብና ማስፈራሪያ ላይ ያተኩራል። በነገራችን ላይ እነኚህ ምክረ ሐሳቦች (SR97) ወይም ትዕዛዞች በሙሉ መጥፎ ናቸዉ ባይባልም የተወሰኑት ግን ኢትዮጵያን ያፈርሱ ወይም ያተራምሱ ዘንድ ኃይል ያላቸዉ ናቸዉ። ለምሳሌ ያህል ‘የፖለቲካ እስረኞችን ፍቱ’ የሚለዉ ትዕዛዝ እስክንድር ነጋን እንደሚያካትት ሁሉ ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባን ይጨምራል። አሜሪካ የሕግ ሂደቱን አቋርጣችሁ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጫፍ ድረስ ተጉዘዉና ለብዙ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑትን ወንጀለኞች ፍቱና ስልጣን አጋሯቸዉ ማለቷ ሉዓላዊነትን መዳፈር ብቻ ሳይሆን ሀገርን ለትርምስ መጋበዝ መሆኑ እንዴት ሊገባን አይችልም? ይህ ግን ሰሎሞን ሹምዬና አያልቅበት ዓደም ለተባሉ ሰዎች የሚሰጠዉ ትርጉም ‘ተስማሙ’ ብቻ ነዉ።
ጃዋርንና በቀለ ገርባን ያለ ዳኛ በነፃ የምትለቅ ሀገር ምን ዓይነት ሀገር እንድትሆን ተፈልጎ ነዉ? …. መንግስትስ ይህን የአሜሪካ ትዕዛዝ አለመቀበሉ እንዴት ሊያስወቅሰዉ ይችላል? …ቄሮ በዓለም ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ተብሎ ይፈረጅልኝ ሲል የነበረዉ ኤርሚያስና ኢትዮ360 ምን ልዩ ነገር ተገኝቶ ነዉ የአሜሪካ ትዕዛዝ ቅዱስ ነዉ ስለዚህም እስረኞች ይፈቱልን የሚሉን? … ወይስ እነሱ እስረኞች የሚሉን የእነሱን ጓደኞች ብቻ ነዉ? የአማራ ልዩ ኃይልስ ከሀገሩ ኢትዮጵያ ምድር ወዴት እንዲሄድስ ስለተፈለገ ነዉ የአሜሪካ ትዕዛዝ ተከብሮ ከትግራይ ክልል የሚወጣዉ? …. ወይስ ይህን የአሜሪካ ትዕዛዝ ለአማራ ሕዝብ ቆመናል የሚሉን ሚዲያዎች አልተመለከቱትም? … ይህ አስቆጥቷቸዉ ‘ብሔራዊ ክብር – በሕብር!! በማለት ለሀገር ክብር መቆማቸዉን ለመመስከር ወደፊት የመጡ ኢትዮጵያዊያንንስ ማዋረድ ከምን የመጣ ነዉ?
ሰሎሞን ሹምዬ የተባለዉ ሰዉ ንግግሩን ሲጀምር በአሜሪካ ሴኔት ዉሳኔ የተቆጡ ኢትዮጵያዊያንን መንጨርጨር ግራ እንዳጋባዉ በመግለፅ ነዉ። ሰዉዬዉ አስሩንም የአሜሪካ ትዕዛዞች ማንበቡን በመግለፅ ምንም ስዕተት እንደሌለዉና ምንም ጣልቃ የገቡበትን ሁኔታ አለማየቱን ይመሰክራል። ለነገሩ ሴኔቱ እስረኛ ፍቱ እና ምርጫዉን ትታችሁ ወደ ጋራ መንግስት ምስረታ ሂዱ ብሎ ትዕዛዝ መስጠቱ ጣልቃ ካልተባለ ምን እንበለዉ? … ለምን ቻይና ወይንም ራሺያ ተመሳሳዩን አላሉንም? …
በንፁሐን ላይ የሚደርስ ማንኛዉም ጥቃት፣ የሚቻለዉን እርዳታ በጊዜዉ አለማቅረብ፣ እና ጥፋተኞችን ለፍርድ አለማቅረብ መንግስትን ሊያስጠይቀዉ ይገባል። ከዚህ አልፎ ግን ሁሉም ኃይሎች ተኩስ አቁመዉ ወደ ድርድር መምጣት አለባቸዉ ማለት ምን ማለት ነዉ? … ወያኔን ከተበተነበት ሰብስቦ ለስልጣን መደራደር? … ይህ የሃያ ሰባት ዓመታት ሰቆቃችንን መዘንጋት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም እንድትበታተን መተባበር ነዉ። ምክንያቱም የህወኣት ዓላማ ኢትዮጵያን መበተን ነዉ።
ሰሎሞን ሹምዬ ሞኝ ሰዉ አይመስለኝም። የሞኞች ተረት ደጋግሞ ሲተርት ግን ሰምቼዋለሁ። “አሜሪካኖች ያሉን ተስማሙ ነዉ። እነሱ ይህን እስኪሉን መጠበቅ አልነበረብንም፤ ይልቁንስ እኛዉ እራሳችን ቀድመን በድርድር መስማማት ነበረብን።” ብሏል። ለአርባ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያኅን ለመበታተን ካሴረና አማራ የሚባል ብሔርን ታሪካዊ ጠላቱ አድርጎ ከተንቀሳቀሰ ቡድን ጋር ምን ልትደራደርና ምን ልታተርፍ ነዉ? መንግስትስ የአሜሪካ ሴኔትን ትዕዛዝ እሺ ብሎ ከእነ ጌታቸዉ ረዳና ኬሪያ ኢብራሂም ጋር ልወያይ ቢል የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀበላል?…. እኔ የማዝነዉ ተመሳሳዩን የብልጣብልጥ ጩኸት ርዕዮት ሚዲያ፣ ኢትዮ 360 ሚዲያ እና እነ ሰሎሞን ሹምዬ መሰሎች ሲቀባበሉት የአማራ ሕዝብ ታግሶ መስማቱ ነዉ። የጠቀስኳቸዉ በሙሉ ግን ለኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ ጥላቻ ስላላቸዉ ብሔርተኛዉ ቀርቶ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረዉ የኦሮሞ ሕዝብ ለደቂቃ አይቀበላቸዉም።
ለማንኛዉም እናንተ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ለምን ሊገለፅላችሁ እንዳልፈለጋችሁ ከመጠርጠር ዉጪ የምናዉቀዉ ባይኖርም ለእኛ ግን ተገልፆልናል። ግብፅ የጠነከረችና አባይ ወንዝን እንደፈለገች የምታደርግ ኢትዮጵያን ማየት ፈፅሞ አትፈልግም። አሜሪካ ደግሞ ከበግብፅ በኩል አብዛኛዉ ዓረብ አገራትን ስለምትቆጣጠርና በስዊዝ ካናል አካባቢም ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን በማዳከም ግብፅን ማገዝ ግዴታዋ ነዉ። ኢትዮጵያ የምትዳከመዉ ደግሞ ወያኔን እና ኦነግን የመሳሰሉ በታኝና ተላላኪ ኃይሎች ፖለቲካዉን መዘወር ሲችሉ ነዉ። ይህ ሊገባችሁ አይችልም ማለት ይከብዳል ቢሆንም ግን ተረዱት።
በነገራችን ላይ ‘ግብፅ ጠላታችን ምን አመጣዉ?’ ለሚለዉ መልስ ይሆን ዘንድ በቅርቡ ፅፌዉ ከነበረ አንድ ፁሑፍ ቀንጨብ ላድርግ። ……
ዘጠነኛዉ የግብፅ ባሕሪ ማምልኩ ሱልጣን በ 1320 ክርስትያኖችን እያሳድደ መሆኑን የሰማዉ የአቢሲኒያዉ ንጉስ ዓምደ ፂዮን አንደኛ ወደ ግብፅ መልህክተኞችን ይልካል። በመልህክቱም ሱልጣኑ ክርስትያኖችንን ማሳደድ ካላቆመ የአባይን ዉሃ በመጥለፍ ግብፅን በዉሃ ጥም እንሚቀጣ ብሎም በሚያስተዳድረዉ ምድር የሚገኙትን የይፋትን ሙስሊም ሱልጣን ግዛቶች በርሃብ እንደሚቀጣ የታሪክ ተመራማሪዉ ሪቻርድ ፓንክረስት ፅፈዋል (Richard Pankhurst The Ethiopian Borderlands: Essays in Regional History from Ancient times to the End of the 18th Century, 1997)።
ይህን መሰሉ ቁጣና መልህክት ግብፅን ሁሌም ትቃዥ ዘንድ ያደርጋታል። የኢትዮጵያ እጆች ፈርጥመዉ አባይ ወንዝ ላይ ሙሉ ለሙሉ ማዘዝ ከቻሉ ግብፅን መዳፋቸዉ አስገቡ ማለት ነዉና ከግብፅ ጋር የሚኖረን ጠባችን ዘለዓለማዊ ነዉ።
ኢትዮጵያ ትቅደም።
ዶ/ር መኮንን ብሩ