መሰረት ተስፉ ([email protected])
ይህን ፅሁፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ ዋናው ነገር እርስ በእርስ ለመግባባት በመቸገራችን ምክንያት ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ማየቴ ነው። በአንድ በኩል ብልሹ አስተዳደርን ለመጋፈጥና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት እንዲሰፍን ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ያለው ፍላጎትና ተነሳሽነት እየጨመረ መምጣቱ ተስፋ ያጭርብኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ተስፋ የሚያጨልሙና የሃገሪቱን ፖለቲካ እየበከሉ ያሉ በርካታ ችግሮችን እየታዘብኩ ነው። በዚህ ረገድ የአምባገነንነት ዝንባሌ፣ ሴራ፣ ፖለቲካዊ ቁማር፣ ድለላ፣ ሽንገላ፣ መርህ አልባነት፣ ማታለል፣ ማስፈራራት፣ ሙስናና ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው።
በምክንያት ሳይሆን በመንጋ የማሰብ፣ አለመደማመጥ፣ አለመተማመን፣ የአብሮነት መጓደልና እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚሉ ችግሮችም` እየገነኑ መጥተዋል። እነዚህ አለመተማመኖች፣ ሽኩቻዎች፣ አለመደማመጦች ባጠቃላይም አለመግባባቶች ሌላው ይቅርና አገር እየመራሁ ነው በሚለው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ሳይቀር ጎልተው መደመጥ ጀምረዋል። የማንግባባባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች በርካታ ቢሆኑም ለዛሬ የተወሰኑትን መርጨ እንደሚከተለው ላቀርብላችሁ ወድጃለሁ።
አንደኛው መሰረታዊ ጉዳይ የመገንጠል መብትን ጨምሮ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀሩን በተመለከተ የሚነሳው ክርክር ነው። በዚህ ዙሪያ ሁለት ፅንፎች ላይ የተቸከሉ ጎራዎች አሉ። በአንዱ ጎራ ያሉ አካላት ኢትዮጵያ ወደ አሃዳዊ የመንግስት ስርዓት መመለስ አለባት የሚል ክርክር ያነሳሉ። እነዚህ አካላት የኢትዮጵያ የወሰን አከላለል መልክዓ-ምድርን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን አለበት የሚል ሃሳብንም ያንፀባርቃሉ። ይህን ሃሳብ የሚያቀነቅኑ ሃይሎች መገንጠል የሚል መብትን በፍፁም አይቀበሉም። ለዚህ የሚያነሱት ምክንያትም ደግሞ የመገንጠል መብት ሀጋዊ እውቅና የሚሰጠው ከሆነ ኢትዮጵያ እንደዮጎዝላቪያ ተበጣጥሳ ስሟ ከአለም ካርታ ላይ ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋትን ነው። በሌላኛው ጎራ ያሉት ደግሞ አሁን ያለው አወቃቀር የመገንጠል መብትን ጨምሮ እንዳለ መቀጠሉ ዋስትና ስለሚሰጥ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር ወሳኝ ነው የሚል አቋም ያራምዳሉ።
ሁለተኛው ጉዳይ ከማንነት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ውዝግብ ነው። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ማንኛውም በማንነት ላይ የተመሰረተ የወሰን ስሪት ቋንቋን፣ ባህልን/ወግን፣ ስነልቦናዊ ትስስርን እና የቦታ አቀማመጥን መሰረት አድርጎ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። በተግባር ሲፈፀም ግን የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም። ምክንያቱም ቅሬታዎቹ ሲቀርቡና ጥያቄዎቹ ሲነሱ የተፈቱባቸው መንገዶች ተመሳሳይነት የሚጎድላቸው ስለነበሩ ነው። ይህም ማለት በአንዳንድ አከባቢዎች ተከስተው የነበሩ ችግሮች የተፈቱት በህዝበ-ውሳኔ ሲሆን በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ የተመረጠው የችግር አፍተታ ዘዴ አስተዳደራዊ ነበር። ለአስተዳደራዊዩ የችግር አፈታት ዘዴ ገፊ ምክንያት የነብረው ደግሞ በህወሓት ሰዎች ስግብግብነት ላይ የተመሰረተ የግዛት መስፋፋት ስለነበር አሁን ላይ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መነሻ ሆኗል። ለዚህ እንደምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉት የወልቃይትና የራያ አከባቢዎች ናቸው።
ከሰንደቅ አላማ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ውጥንቅጥም ሌላው ጉዳይ ነው። እስካሁን ባለው ልምድ የሚታወቀው ሰንደቅ አላማ አንድ አገር በውስጥም ሆነ በውጭ የሚመሰልበት ምልክት ነው። ለዚህም ነው የማንኛውም ሃገር ሰንደቅ አላማ በየመንግስት ቢሮዎች፣ ክብረ በአላት፣ የስፖርታዊ ውድድሮች፣ ሁሉም አይነት ሰልፎች፣ እና አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የሚታየው። ይህ በመሆኑም ሰንደቅ አላማ ቢቻል በሁሉም ካልሆነም ባብዛኛው በአገሩ ዜጎች ተቀባይነት ሊያገኝ መቻል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ስናይ ግን ውጥንቅጡ የወጣ የህዝብ እይታ ነው ያለው። አንዳንዱ ሰንደቅ አላማየ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ሆኖ መሃሉ ላይ ኮከብ ያለበት ነው ይላል። ሌላው አይ የኔ ሰንደቅ አላማ ኮከብ የሌለው ምን አልባትም የአንበሳ አርማ ያለበት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ነው ሲል ይገልፃል። ከኒዚህ ውጭ ያለ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሰንደቅ አላማየ ፖለቲክ ድርጅት እንደ አርማ እየተጠቀመበት ያለ ምስል ነው ይላል። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ግጭቶች እየተከሰቱ የሰው ህይወት ሲቀጠፍና ንብረት ሲወድም ይታያል።
አራተኛው ደግሞ የፌደራል መንግስትን የስራ ቋንቋ በሚመለከት እየተነሳ ያለው አተካሮ ነው። እንደሚታወቀው የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አማርኛ ባብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለሚነገር የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል ህገመንግስታዊ እውቅና አግኝቷል። ይህ መሆኑ አንዳንዶቹን ለሴራና ለቁማር ፖለቲካ ቢያነሳሳም አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ግን እንዳስማማ ይታመናል። በሌላ በኩል ተጨማሪ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋዎች ያስፈልጋሉ ወይስ አያስፈልጉም የሚለው ጥያቄ ጎልቶ እየወጣ ነው። ይህን በተመለከተ በአንድ ወገን ያሉ ሃይሎች የፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋዎች መብዛት የህዝብ ለህዝብ መቀራረብን በማጎልበት የሃገር አንድነትን ሊያጠናክር ስለሚችል የሃገሪቱ ህገመንግስት በሚፈቅደው መሰረት ተግባራዊ መደረግ አለበት ይላሉ። በሌላ ወገን ደግሞ የፌዴራል መንግስት ቋንቋዎች መብዛት የሃገር አንድነትን ሊያላላ ስለሚችል መፈቀድ የለበትም የሚሉ አሉ። ከዚህ ጎን ለጎንም በባህሎቻችን ዙሪያ ቡድን ለይተን ስንነታረክ እንደምንውል የታወቀ ጉዳይ ነው። አሁን አሁንማ ጭራሽ በየቦታው ጥቃት በሚደርስባቸው ዜጎች ዙሪያ ሳይቀር አንድ ላይ ማዘንም እየተቸገርን መጥተናል።
ታዲያ በምን እንግባባ ያገሬ ልጆች???
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት ከፍ ሲል በተገለፁትና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለመግባባት የተቸገርንበት ምክንያት ምንድነው በሚለው ላይ ትንሽ ነገር ልበል። በእኔ እምነት ላለመግባባታችን እንደ ዋነኛ ብልት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት የአመለካከት ፅንፈኝነት ነው ብየ አስባለሁ። ፅንፈኝነት ሃይማኖታዊ፣ ብሄራዊ፣ ፆታዊ፣ እንዲሁም አገራዊ ሊሆን ይችላል። ፅንፈኛ የሆነ አስተሳሰብ በባህሪው ምክንያታዊ አይደለም። ሁልጊዜም የኔ፣ ለእኔና በእኔ በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ባህሪው ደግሞ የሌሎችን መብት፣ ፍትሃዊ ጥቅምና ፍላጎት እንዲያስተናግድ አይፈቅድለትም። ለምሳሌ ማንም ሰው ወይም ቡድን የኔ ብሄር ቋንቋ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን እፈልጋለሁ ብሎ ቢነሳ መብት ነውና ሊከለከል አይችልም። የኔ ብቻ ሳይሆን የሌላ ብሄር ቋንቋ እንዲሁ የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን እታገላለሁ ቢልም መብት ነው። በዚህ ዙሪያ የሚነሳን ፍላጎት፣ ፍትሃዊ ጥቅምና ህጋዊ መብት ፅንፈኛ አስተሳሰብ ነው ብሎ መፈረጅ አግባብነት አይኖረውም። የኔም ሆነ የሌላ ብሄር ቋንቋ የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የምታገለው በሌላው ቋንቋ ውድቀትና መዳከም ላይ ነው ብሎ መዶለትና ይህን ለማስፈፀም መንቀሳቀስ ግን ፅንፈ-ብሄር የሆነ ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል።
በሌላ በኩል መሬት ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመካድ ሌሎች የብሄር ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ መሆን የለባቸውም፤ ስለሆነም በዚህ መልክ የሚቀርቡ ጥያቄዎች የሃገርን አንድነት ይጎዳሉና ውድቅ መደረግ አለባቸው የሚል አስተሳሰብ ካለም ፅንፈ-ሃገር የሆነ ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በሌላ አነጋገር ሁለቱም የፅንፍ አስተሳሰቦች አድሃሪያን፣ጎታችና የውድቀት መሰረቶች ናቸው ብየ አምናለሁ። ስለሆነም ሁለቱም ፅንፍ አስተሳሰቦች በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች መገራት አለባቸው። ይህን ማድረግ በተለይ የመሃል/ለዘብተኛ ፖለቲካን (Liberal Politics) በመከተል ሃገር እየመራሁ ነው ለሚለው ብልፅግና ፓርቲ እጅግ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው ብየ አምናለሁ። ለዚህ ደግሞ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ባልሆነ መንገድ ተግባራዊ አድርጎ ስላጠለሸው እንጅ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መርሆዎችን በሚገባ መተግበር እንደመፍትሄ ቢወሰድ በተሻለ መንገድ ሊያግባባን ይችላል የሚል እሳቤ አለኝ።
በ’ኔ እይታ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ማለት ለራስ ጥቅም ብቻ መቆም አይደለም። ሁሉም ለኔ፣ የኔና ከኔ በላይ ላሳር ማለትም ሊሆን አይችልም። ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ማለት ለራስ ብሄር ፍትሃዊና አግባብ ያለው ጥቅም በመቆም የሌሎቹም ፍትሃዊና ተገቢነት ያለው ጥቅም እንዲከበርላቸው መታገል ማለት ነው። በተጨማሪም ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሲባል የራስን ተገቢ የሆነ ጥቅም ከማስከበር አልፎ ያለአግባብ መጠቀም የሚፈልግን የራስንም ሆነ የሌላን ብሄር አባል አምርሮ መታገልን እንደሚያበረታታ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ሲሆን መከባበርና አብሮ መኖር እየጎለበተ መምጣቱ አይቀርም። በዚህ መንገድ እየጎለበተ የሚሄድ መከባበርና አብሮነት ሲኖር ደግሞ ውህደቱ ይጠነክርና አገራዊ እሳቤው እየጎለበተ ይሄዳል። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን የማጎልበት ያለማጎልበት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ሊያግግባባን ይችላል ብየ የማስበው ለጊዘው ያለኝ ምክረ-ሃሳብም ይህንኑ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እሳቤ አጠንክሮ መያዝ ነው።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ሃገራዊ የሆኑ ውይይቶችና ምክክሮች በሰፊው ሊካሄዱ ይገባል። የምክክርና የውውይት መድረኮቻችን ሁሉንም ካልሆነም አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ መጥቀም የሚችሉ ሃሳቦችን የምናመነጭባቸው እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በነዚህ ውይይቶች ላይ ከፍ ብየ በተቀስኳቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻል ከሆነ እመርታዊ ለውጥ (Breakthrough) ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በምክክርና በውይይት ያልተፈቱትን ደግሞ የሃገሪቱን ህጎች ተጠቅሞ መፍትሄ መፈለግን እንደ አንድ የመግባቢያ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። ይህ ሁሉ ሆኖ ልዩነቶች የማይታረቁ ከሆነ እንደየአግባቡ የሚመለከተውን ህዝብ ባሳተፈና ከተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ የሚካሄዱ ህዝበ-ውሳኔዎችን (Referendums) በመጠቀም አለመግባባቶችን የመፍታት አቅጣጫን ከመከተል ውጭ ሌላ አማራጭ የሚኖረን አይመስለኝም።
ቸር እንሰንብት!!!