ዳግማዊ ጉዱ ካሣ ([email protected])
እንደመግቢያ፡- ኢትዮጵያን የገጠሟት ነጋዴዎች የለዬላቸው የቀን ጅቦች እንጂ በፍጹም ሰዎች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያን የገጠሟት ፖለቲከኞችም መሠሪ ሆዳሞችና ጎጠኞች አንዳንዶቹም የውጭ ጠላቶቻችን ቀጥተኛ ወኪሎች እንጂ ስለሀገርና ሕዝብ የሚጨነቁና የፖለቲካ ሀሁንም የሚያውቁ አይደሉም፡፡ ከነዚህ ፖለቲከኞች ብዙዎቹ በትምህርት ሲወድቁና ሥራ ሲያጡ የኑሮ አማራጭ በማጣታቸው ብቻ “ዛሬ ከምሞት ነገ ልሙት” በሚለው የአጋሰሶች ፈሊጥ በመነዳት በቀላሉ ወደሚገባበት የፖለቲካው ጎራ ዘው የሚሉ ናቸው፡፡…
የራስህ ሕዝብ በሞትና በሕይወት መሀል ሆኖ እየተጨነቀ ባለበት ሰዓት አንድ ኩንታል ጤፍ 5000 ብር ሲገባ፣ ሦስት በሦስት የሆነች አንዲት ጭርንቁስ ክፍል በወር ከ2000 ብር የበለጠ ስትከራይ፣ ኑሮ እንደመንኮራኩር በየቀኑ ሲወነጨፍ … ባለሁለት ሽህና ከዚያም በታች የሚያገኙ የወር ደሞዝተኞች እንዴት ይኖራሉ ብሎ ቅንጣት የማያስብ መሪና መንግሥት ያለን ብቸኛ ሕዝብ እኛ ነን፡፡ በኮሮና ቫይረስ ተጨንቀን ተጠበን የምንገባበትን አጥተን ሳለ ገብጋባ ነጋዴዎች አንዲት ሎሚ ብር 10 እና 15 እንዲሁም አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት 200 እና 250 ብር ሲሸጡ ዝም የሚል መንግሥት ማንን እየመራ እንደሆነ መረዳት አይቻልም (እርግጥ ነው በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን ችግር ለመቅረፍ ውሱን እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ ይሰማልና ለነዚያ ዓይነቶቹ የሥራ ኃላፊዎችና የሥምሪት አባላት ምሥጋናየን ማቅረብ እወዳለሁ)፡፡ ሁሉም እንደፈለገው ሆኖ ኳስ አበደችን የመሰለ የጨረባ ተዝካር በኢትዮጵያ ገንኖ ይታያል፡፡ በኪነ ጥበቡ አለን እንጂ መንግሥት ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ በዚህ ላይ ነው ኮሮና ቫይረስ የመጣብን፡፡ በደምባራ ፈረስ ቃጭል ተጨምሮ፡፡ ቡሃ ላይ ቆረቆር፡፡ ዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፤ ሌላም ካለህ ጨምርበት፡፡ እኛም እንደዚህ ሆነናል፡፡
መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጨካኝ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊ ጨካኝ ነበር፡፡ መንግሥቱ ዐረመኔ ይሁን እንጂ ዐረመኔነቱ በዘርና በጎሣ፣ በሃይማኖትና በጎጥ መደቦች ያልተከፋፈለ ለሁሉም እኩል ነበር፡፡ አሁን ያለን ዘረኛ መንግሥት ግን ዕድሜ ለሕወሓትና ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ለአንዱ የእንጀራ ልጅ ለሌላው የሥጋ ልጅ እየሆነ ሀገርና ሕዝብ በመፍረስ አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ ግን አንፈርስም!
መንጌ በገብጋባ የበርበሬ ነጋዴዎች ላይ የወሰደውን የማያዳግም እርምጃ እናስታውሳለን፡፡ አካሄዱ ህገወጥና ጭካኔ የተሞላበት ቢሆንም ውጤቱ ግን ለሕዝብ አልጠቀመም ማለት አንችልም – ፈረንጅ እንዲህ ይላል – Little temper settles the dust. ሌላም ላክልልህ – Even the nicest people have their limits. አንዳንዴ ክፉ መሆን ባትፈልገውም እንኳን መልካም ነው፡፡ ስልሳ ሰው የጫነ አውቶቡስ አንድ ሰው ለማዳን ብሎ ስልሳ ሰው ገደል ሊከት አይገባውም፡፡ በተመሳሳይም ጥቂት ጅብ ነጋዴዎች ይከፋቸዋል ተብሎ ሰፊው ሕዝብ በቁሙ እንጦርጦስ ሊገባ አይገባምና አንዳንዴ እያመመንም ቢሆን ጨከን ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ ሀገርንና ሕዝብን ከተጨማሪ ጉዳት ከማዳናቸውም በላይ አስተማሪነታቸው የጎላ ነው፡፡ ችግሩ ግን ሕግ አስከባሪ ተብዬውም በራሱ ወይ በቤተሰቡ ስም በንግዱ ዘርፍ ከገባና የሌቦች ተባባሪ ሆኖ ከተገኘ ነው፡፡ ያ ዓይነቱ ጉዞ ተያይዞ ጥፋት ነው፡፡ ሕግ አስከባሪ ከሌቦች ጋር በጥቅም ከተሻረከና ሙስና ሀገርን ካጥለቀለቀ የሀገርና የሕዝብ ኅልውና ልክ እንደኛ እንዳሁኑ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ አሁን እኮ ሰው ገድለህ ብታመልጥ አንደኛ የሚከተልህ የለም፤ ሁለተኛ የሚከተልህ ቢኖር እንኳ የሙስና ድርሻውን ካንተ ወስዶ ፋይልህን መቼም እንዳይገኝ አድርጎ የሚቀብርልህ ኅሊናቢስ ሙሰኛ ነው፡፡ ሦስተኛ ወደየትም አቤት ብትል የሚሰማህ የለም (ሲጀመር አቤት መባያ ራሱ የለም)፡፡ ያለንበት ሁኔታ እኮ እኮ ያስጨንቃል ጎበዝ!
ጃዋር መሀመድን የመሰለ ዐረባዊ ኮሮኖና ቫይረስ እንደፈለገው ሲፈነጭ ማየት፣ በቀለ ገርባን የመሰለ ኢቦላ ቫይረስ እንዳሻው ትዳር ሲያፈርስ መታዘብ፣ ሕዝቅያስና ፀጋየ አራንሳን የመሰሉ ኢትዮ-ግብፃውያን ኤችአይቪዎች እንዳሻቸው ሕዝብን ሲያጋጩ ማየት ለእውነተኛ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የኅሊና ቁስል ነው፡፡ ወቅቱ ነው ብለን ፍርዱን ለጊዜና ለፈጣሪ ብንተውም የቁስሉ ጥዝጠዛ ግን ዕረፍት ነሣን፡፡ ስለሆነም ክፉም ቢሆን ያለፈን መናፈቅ ልናመልጠው ያልቻልነው የወቅቱ ፍርጃ ሆነብን፡፡
ኢትዮጵያችን በሰብአዊና ተፈጥሯዊ የኮሮና ቫይረሶች ተቀፍድዳ እዬዬ እያለች ነው፡፡ ፈጣሪ በአፋጣኝ ይድረስላት፡፡ እንዳንዳች ነገር የሚከረፋውና የሚጠነባው ዘረኝነት ላይ ይህ ቫይረስ ተጨምሮ ሀገራችን ዓለም ባፈራቻቸው ቋንቋዎች ልትገለጽ የማትችል ቅርጸ ቢስ ሆናለች፡፡
ለማንኛውም መንጌ ሆይ ወዴት ነህ! በሃሳብ ደረጃም ቢሆን የበደልኩህን ይቅር በለኝ፡፡ ካንተ የባሱ የእፉኝት ልጆች መጥተው አሣራችንን እያበሉን መሆናቸውን ሳትከታተል አትቀርም፡፡ አንተ አሁን አርጅተሃል፡፡ ሥልጣን ቢሰጥህ እንኳ እንደዚያ እንደዱሮው በመስቀል አደባባይ እየተገማሸርክ በቀይ ቀለም የተሞላ ጠርሙስም ከግድግዳ ጋር እያጋጨህ እንደማትገዛን ግልጽ ነው፡፡ ጊዜ ባለውሉ እንዲህ ነው፡፡
ይህን የጊዜ ባለውልነት ያልተረዱ ጎረምሦች ቤተ መንግሥትን በዘር ወር-ተረኝነት ተቆጣጥረው ፍዳችንን እያሳዩን ነውና ፈጣሪ ሆይ ቶሎ ድረስልን፡፡ አጋንንታዊነት በቤተ መንግሥት ብቻ ሳይወሰን ቤተ አምልኮቶችንም በግላጭ ተቆጣጥሮ ከሃይማኖትም፣ ከሞራል ዕሤቶችም፣ ከባህልም፣ ከዕውቀት አምባም አውጥቶናል፡፡ ሰው መሳይ በሸንጎ ከሆን ቆየት አልን፡፡ … በሁሉም የሰውነት መለኪያ ሚዛኖች ስንለካ ወርደንና ቀለን የለየለት እንስሳ ሆነናልና አምላክ ሆይ እንደገና ሥራን፡፡ እንደጠፋን እንዳንቀር ጀርባህን እንዳዞርክብን አትቅር፡፡
በነገራችን ላይ ከእንስሳትም እንዳነስን መጠቆሜ ስህተት መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት እንስሳት ከኛ ይበልጣሉና፡፡ አንድ እንስሳ ከጠገበና ካልደረሱበት ማንንም አይተናኮልም – አይነካምም፤ እንስሳ ከተፈጥሯዊ ተግባሩ አያፈነግጥም፡፡ የወንድ እርግብ ሚስት ሴት እርግብ ናት – ሊያውም አንድ ለአንድ በሚለው ሕግ ተመርተው፡፡ አንዲት ጉሬዛ የምታገባው መሰሏን ወንድ ጉሬዛ ነው፡፡ አውሮፓውያን ከእንስሳት ጋር እንዲጋቡ ህጋቸውን ማሻሻላቸውን እየሰማን አይደል ሰሞኑን? እኛ ሰዎች ስንባል እንግዲህ የተሰጠንን አንጎል በከንቱ በማዋል ከሰውነት ተራ የሚያወጡ ተግባራትን እየፈጸምን ከራሳችን ኅሊናም፣ ከተፈጥሮና ከእግዜሩም ተለያይተናል፡፡ መጥኔ ለሰው ልጅ! ግን ግን ለዚህም ሁሉ ይከፈለዋል – ክፍያውም ጀምሯል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ዓለማችን ትታደስና ሦሥት ዐይናማዎች በጉጉት የሚጠብቁት ወርቃማው ዘመን ይብታል፡፡ መንገድ ጠረጋው ነው ያለንበት፡፡ …