ፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጄንሲ
ለሃያ ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያራቁት ቆየ:: ዛሬም ቀጥሎበታል::
መንግስት የት ሄደ? ሕዝብስ ምን ይላል??
በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ በግለሰቦች ሲመዘበር በኢትዮጵያ ሕግ የለም ወይ? ወይም የኢህአዴግ ሰዎች ዛሬም ዘረፋቸውን አላቆሙም ወይ ያስብላል::
ምክንያቱም ግለሰቦች የመንግስትን ስልጣን ከላይ እስከ ታች የሚያወርድ ወይም ከታች እስከ ላይ የሚያወጣ የሙስና መሰላል ወይም ሰንሰለት አበጅተው በየደረጃው በረቀቀ ስልት መንግስትን ሲመዘብሩት ቆይተዋል:: እነሆ ዛሬም እየመዘበሩት ይገኛሉ::መንግስት መሥሪያ ቤቱን ሲያዋቅር የኤጀንሲው ተልዕኮ፣ራዕይና እሴቶችን በመቅረጽ ነበረ::
እነሱም አንደኛው የኤጄንሲው ራዕይ ነው::
”የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓትና አፈፃፀም ትራንስፎርም የሚያደርግ ተቋም ሆኖ መገኘት::”ይላል:: ነገር ግን መቶ በመቶ የተጻፈውና የሚሠራው አራምባና ቆቦ ነው::
ሁለተኛው የኤጄንሲው ተልዕኮ ነው::
እሱም “ዘመናዊ የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት፣የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በዘላቂነት በመገንባት፣ ቁጥጥርና ክትትልን በማጠናክር የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ፍትሃዊ ፣ ቀልጣፋ ፣ ውጤታማ እንዲሆን ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፡፡” የሚል ሲሆን ለዚህ ሁሉ ወርቃማ ቃላት ተቃራኒ ሆኖ የመንግስትን ንብረት የሚመዘብር: የሚበዘብዝ: የሚዘርፍ: የሚሰርቅ: የሚያጭበረብር: የሚያታልል: የሚያወናብድ: ከውጭ ሌቦች ጋራ ተሻርኮና ተመሳጥሮ ኢትዮጵያን የሚያራቁት መሥሪያ ቤት ቢኖር ይህ ኤጄንሲ ነበር:: ዛሬም ነው::
ይህ ኤጄንሲ “የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት” የሚለውን ወደ ጎን በመተው የመንግስትን ግዥና ንብረትን እንዴት ወደ የግል ይዞታነት እንደሚቀየር እና ግለሰቦቹም እንዴት እንደሚበለጽጉ የሚሠራ መሥሪያ ቤት ነው:: ይህ ኤጄንሲ “የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ዘላቂነት በመገንባት” እያለ የግለሰቦችንና የዘመዶቻቸውን የኑሮ አቅም እንዴት መገንባት እንደሚቻል የሚሠራ ኤጄንሲ ነው::
ይህ ኤጄንሲ “በፍትሃዊነት: በቀልጣፋነት: በውጤታማ: በግልጽነት እና በተጠያቂነት” ስም የሚፈጽማቸው ሙስናዎች ተራራ አክለው በግለሰቦች አቅም የሚገፉ ሊሆኑ አልቻሉም:: በዚህ ዙሪያ አደገኛና ውስብስብ ኔትዎርክ አለ:: ጸረ ሙስና ኃይሎች የሚድያ እና የፕሬስ ተቋማት የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች ጭምር የተሳተፉበት አልፎ ተርፎም በቦርድ ሊቀመንበርነትና በቦርድ አባልነት ጭምር እጃቸውን ብቻ ሳይሆን እግራቸውንም ጭምር ያስገቡበት የመከበሪያና የበመልጸጊያ ሥፍራ ሆኖ ለዓመታት ሲያግለግል ኖሯል::
ይህ ኤጄንሲ ተጫራቾችን በማጉላላት ሆን ብሎ መረጃዎችን በመሸንሸንና በመሰንጠቅ ለወጥመድ እንዲሆን በማድረግ በጨረታ ሂደት ውጣ ውረድ ውስጥ ተጫራቾችን በማስወገድ ጨረታውን ለሚፈልጉት የቤተሰብ እና የቤተዘመድ ድርጅት እንዲያሸንፍ በማድረግ ቢሊዮን ብር ከመንግስት ካዝና ወደ የግል አካውንት እንዲገባ የሚደረግበት ኤጄንሲ ነው::
የዚህ መሥሪያ ቤት ቀልድ ደግሞ በእሴት ስም የሚያሾፈው ነገር ነው::
የመሥሪያ ቤቱ እሴቶች ይልና……../
1.ለውጥና መልካም አስተዳደር ለውጤት:
2.የህዝብ አገልጋይነትን መላበስ፣
3.ትኩረት ለዘመናዊ የግዥና ንብረት አስተዳደር ሙያዊ ልቀት፣
4.ቡድን ሥራ ለውጤታማነት፣ትኩረት ለባለብዙ ዘርፍ፣
- ፍትሀዊነት፣ቅንነት፣ ታማኝነት፣ እና ተጠያቂነት እንዲኖር ተግቶ መስራት በማለት በመሥሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ ያሰፍራል:: ማጭበረብሪያ ቃላቶች ናቸው:: ማታለያ እሴቶች ::
ከእራሱ ከመሥሪያ ቤቱ የውስጥ ጠቋሚዎች እንደተረዳነው ከሆነ የመስሪያ ቤቷ ዳይሬክተር የሆኑት የህወኃቷ ወይዘሮ ጽዋእ አንዴ ከድህነት የሚያላቅቅ ገንዘብ በእጄ ከገባ መሥሪያ ቤቱ ምን ያደርግልኛል እያለች ሙስና ዓላማዋ እንደሆነ በተደጋጋሚ እንደምትገልጽ ነው:: እንዲያውም ወይዘሮዋ ወደ መሥሪያ ቤቱ ከመጣች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሊየነር ተርታ እንደገባች እና መንግስት ቢያባርራትም ደንታዋ እንዳልሆነ ትፎክራለች:: ምክንያቱም ይላል ጠቋሚያችን ምክንያቱም ከወይዘሮ ጽዋእ በፊት የነበሩት አለቆች ወይም ዳይሬክተሮች በሙሉ በሀብት ተጨማልቀው ልጆቻቸውን በአሜሪካ: በአውሮፓ: በጃፓን ሲያስተምሩ በውጭ አገሮች የባንክ አካውንት ከፍተው ቋሚና ተንቀሳቃሽ ሀብት እንዳፈሩ ትናገርና እኔም ይህንን ዕድል መጠቀም እፈልጋለሁ ትላለች:: ስትናገርም የመንግስት ኃላፊነት እንደምሰማትና ግዴታም እንዳለባት ከቁብም አትቆጥርም:: መንግስት እና ሕዝብ ይጠይቀኛልም አትልም:: ዛሬ ቢሊዮን ገንዘብ ዘርፋ ነገ ጠዋት ብትባረር ደስታዋ ነው::
ይህ ልምድ የተገኘው ከሃያ ሰባት ዓመታት የህወኃት ብልሹ አሠራር ነው:: ስለሆነም ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት የስንዴ ግዥ ጨረታ በማውጣት 73ተጫራቾች ድርጅቶችን ተቀብሎ ሲያበቃ በሆነ ባልሆነ: በዘዴ በብልሃት አድርጎ 11 ድርጅቶችን ብቻ አስቀርቶ: ሌሎችን የውኃ ሽታ አደረጋቸው:: ቀጥሎም ከአሥራ አንዱ ድርጅቶች መካከል እህትማማች የሆኑትን ሦስት ድርጅቶችን መረጠ:: አንደኛ: ሁለተኛ እና ሦስተኛ የወጡ ተጫራቾች በማለት::
ቀጥሎ አንደኛና ሁለተኛ ያስቀመጣቸውን ድርጅቶች በተለያየ ቴክኒክ በማስቀረት ሶስተኛ ደረጃ ያለውን ድርጅት በመምረጥ 47 ሚሊዮን ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቀውን ድርጅት እንዲያልፍ ተደረገ:: ለምን ከተባለ ከተነቃ አይቀር በአንድ ዝግ በልጽጎ ለመገላገል የቆረጠ አመራር ስለሆነ ነው:: ለመውጣትም ጭምር ስለታሰበ ነው::
በዚያ ላይ ይህ ሦስተኛ ወጣና አሸነፈ የተባለው ድርጅት በሎንደን የወያኔ ተሻራኪ የነበረ ድርጅት ነው:: እስከዛሬ ድረስ ጨረታውን አሸንፏል እየተባለ ቢሊዮን ብር ይከፈለዋል:: ነገር ግን አንድ ከረጢት ስንዴ አቅርቦ አያውቅም:: በተደጋጋሚ ይህ ድርጅት ያለጨረታ በሾርት ሊስት የግዥ ዕድል ተሰጥቶታል:: ይህ ድርጅት በእንግሊዝ አገር በየዓመቱ ፈቃዱን እየዘጋ በየዓመቱ በአዲስ መልክ ፈቃድ እያወጣ ከአፍሪካ መሪዎችና ባለስልጣናት ጋራ ህኖ አፍሪካን ማራቆት የለመደ ልማደኛ ድርጅት ስለሆነ በውጭ አገር ለሙሰኞች አካውንት በመክፈትና ድርሻቸውን እዚያው በውጭ አገር እንዲቀር የሚያስተባብር ድርጅት ነው እየተባለ የሚጠረጠር ኩባንያ ነው:: ስለዚህ መንግስት እየተዘረፈ ነው:: ሕዝብ እየተመዘበረ ነው:: ሕግ እየተረገጠ ነው:: ፍትህ የለም:: መልካም አሰተዳደር ከቃል አልዘለለም::