ህዳር 22 ቀን 2012 ዓም(02-12-2019)
ከስድስት ወራት በፊት ጉደኛው ኢሕአዴግ ሕዝቡን ለማጭበርበር የመሪ ድርጅቶቹን ስያሜ በመቀዬር የዴሞክራሲ ጭንብል አልብሶ ብቅ ባለበት ጊዜ የስም እንጂ የተፈጥሮ ለውጥ እንዳላደረገ፣ሊያደርግም እንደማይችል ከታሪክ ምሳሌዎችን በመጠቃቀስ ለማሳዬት ሞክሬ ነበር።በተጨማሪም የጎሳ ማንነቱን በዴሞክራሲ ጭንብል ጠቅልሎ አገራዊ መልክ ሊሰጠው እንደሚችልም ጠቁሜአለሁ። ዕድሜ ደጉ የተባለው ነገር አሁን እዬተከሰተ መምጣቱን ለማዬት ችለናል።ህወሃት ሲያሽከረክረው የነበረው ኢሕአዴግ በሕዝብ ትግል ተገፍቶ ለሌላው የኢሕአዴግ አባል ለሆነው፣የኢሕአዴግን ተክለሰውነት ለተሸከመው ለኦሮሞ ድርጅት መሪነቱን መስጠቱ የስልጣን መቀባበል እንጂ የስርዓት ለውጥ እንዳልሆነ ለማሳዬት ሞክሬ ነበር፤የተከሰተውም ያ እንደሆነ የማይካድ ሃቅ ነው።በተከታታይም አባል ድርጅቶቹን በዴሞክራሲ ጭንብል ኦዴፓ፣አዴፓ በማለት የተሰራው ትያትርም ከወራት ያለፈ ዕድሜ ስላላስቀጠለ ወደሌላው በመደመር ጫጫታ ወደታጀበው የብልጽግና ፓርቲ ወደሚል ስያሜ ተሻግሮ ለማዬት በቅተናል።ይህም ቢሆን በዛው የኢሕአዴግ ተክለሰውነት ማለትም የጎሳ ንኡስ ህዋስ(DNA) የተገነባ ፣ኢትዮጵያን በጎሳ ከፋፍሎ ብሔርና ብሔረሰብ፣ክልል በሚሉ ጊዜ ያለፈባቸው ከፋፋይ ትርክቶችን በነበረው ሕገ-ጎሳ አጅቦ ለመዝለቅ የሚደረግ የማጭበርበርና ዕድሜ ቀጥል ሙከራ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ኢሕአዴግ በሌላ መልክ የመቀጠል ሙከራ እንደሆነ ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል።ፈረንጆች ተመሳሳይ ሁኔታ ሲገጥማቸው (It is an old lady in a new dress) አዲስ ቀሚስ የለበሰች አሮጊት ማለት ሲሆን አዲስ ልብስ መልበሱዋ ማንነቱዋን እንደማይቀይረው ለማሳዬት የሚጠቀሙበት አባባል ነው። ወይም በስርዓት ዓይን ከታዬ የነበረው ስርዓት በአዲስ ስም ቢመጣ ማንነቱን አይስትም ለማለት ነው።እኔም በመጀመሪያው “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ” በሚለው ርዕስ ባቀረብኩት ጽሁፍ ይህንኑ ለማሳዬት ሞክሬ ነበር።ግን በመስቀል የደነቆረ….ሆነና ነገሩ ለመልእክቱ ትኩረት ሳይሰጠው ጭብጨባና ውደሳው ሸፍኖት
ቀረ።እንደኔ ጥርጣሬያቸውንና ስጋታቸውን የገለጹት ወገኖችም ለዴሞክራሲ እንታገላለን በሚሉት አስመሳይ ጋዜጠኞች በሚቆጣጠሩት ድረገጽና የሚድያ ዘርፎች ሳይቀር ድምጻቸው ታፈነ።አሁንም በመታፈን ላይ ነው።እነዚህን አፋኞችና አድመኞች ጊዜና ተግባራቸው ያጋልጣቸዋል፤ለጥቅም ያላደሩ እውነተኞች ቦታውን ሲይዙ የጋዜጠኛ ሙያ የተከበረ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።አሁንም ቁጥራቸው ቢያንስም ለእውነት የቆሙና የጋዜጠኝነት ሙያቸውን የሚወጡ እንዳሉ ለመመስከር እወዳለሁ።
የዚህ የብልጽግና ፣”ጽ”ን አውጥቶ የብልግና ፓርቲ መባሉ ተገቢ ይመስለኛል፤ አባላቱ እነዛው በጎሳ ከፋፍለው አገር ሲያምሱና ሕዝብ ሲጨርሱ የነበሩ የኢሕአዴግ ቤተሰቦች የተጠራቀሙበት የጥፋት ድርጅት ነው።አሁንም ብሔር ብሔረሰብ፣ክልልና ሕዝቦች የመሳሰሉትን ስያሜዎችና አመለካከቶች ከነ ሕገ-ጎሳቸው ይዘው የሚጉዋዙ ጎሰኞችን እንጂ የተለዬ አገራዊ እራዕይ የሚከተሉ ነጻና ተራማጅ ድርጅቶችን ያቀፈ አደረጃጀት አይደለም። የአሁኑም የብል “ጽ”ግና ፓርቲ የሚባለው ስብስብ የነበሩትን የጎሳ ድርጅቶችና አጃቢዎቻቸውን ያቀፈ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ የአማራ፣የኦሮሞ፣የትግሬ፣የደቡብ፣የሶማሌ፣የቤንሻንጉል፣የጋምቤላ፣የሲዳማ፣የአፋር…ወዘተ የብዙ አገራት ሕዝቦች በማስመሰል ለያይቶ የሚነጉድ የጥፋት ሰልፈኞችን ያግበሰበሰ እንጂ በኢትዮጵያዊነት ሽንጡን ገትሮ የሚከራከርና የነበረውን ዃላቀር ትርክት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን የሚጠዬፍና አሽቀንጥሮ የሚጥል አዲስ ድርጅት አይደለም።ተመሰረተ የተባለውን የብል “ጽ”ግና ፓርቲውንና ተከታዮቹን ሁኔታ ሳስተውለው በምኖርበት አገር ጋብቻ የፈጸሙ ሰዎች በሚጉዋዙበት መኪና ላይ “Just married”በሚል ጽሁፍ ስር በገመድ የታሰሩ ቆርቆሮዎችን እየጎተቱ በማስጮህ የሚሄዱበትን ትዕይንት መስሎ ታይቶኛል።ለመሆኑ የአንድ አገር ብልጽግና፣ሕዝቡን እርስ በርሱ በሚያናክስ፣ በዘረኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ በተበከለ ድርጅት ሊመጣ ይችላልን?ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ ፣ሌላው ቀርቶ የሰው ልጅ እንደ እንስሳ በጽንፈኞች መንጋ በድንጋይ እዬተቀጠቀጠ፣ በቆንጨራ እዬተፈለጠ፣ከኖረበት እዬተፈናቀለ፣ ንብረቱን እዬተዘረፈ፣የእምነት ቤቱ በእሳት እዬጋዬና እዬወደመ መቀጠሉን እንኳንስ ሊገታ ቀርቶ ፣ወንጀለኞቹን ለፍርድ ለማቅረብ ያልቻለና ፍላጎት የሌለው መንግሥት ነው።ይግረም ብሎም ለወንጀለኞቹና ወንጀሉን ለሚያቀነባብሩ ግለሰቦች የደህንነት ጥበቃ በማድረግ ተባባሪነቱን ያሳዬ ቡድን ነው።
ሁለተኛው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው ምርጫ ተብዬ ትያትር የሚደረገው ሽር ጉድ ነው።በዚህ የጅንጀሮ ቀንጆ በሚመስል ውድድር አሸናፊ ተብሎ ሊቀርብ የሚችለው ማን እንደሚሆነና ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ያው ኤኮኖሚውን፣ሚዲያውን፣የምርጫ ቦርዱን….የሚቆጣጠረው የጎሰኞቹ ቡድን ነው፤በምርጫ ስም ለመጭው አስር ዓመታት በሥልጣን ላይ ለመቆዬት ዋስትና እንዲኖረው የሚያደርግ ሂደት ነው።ከምርጫው በዃላ ግን በሥልጣን ክፍፍሉ ሳቢያ የሚመጣውን ቀውስ ሲያስቡት ይዘገንናል።
በኤኮኖሚም በኩል የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሰጠና ሊሰጥም ደፋ ቀና የሚል ሃይል በመሆኑ ካለፈው የህወሃት አመራር የተለዬ አያደርገውም።የአገሪቱን አንጡራ ሃብቶች/ተቋማት፣ ለም መሬቶችና ቁልፍ የከተማ ቦታዎችን በልማት ስም የሚቸበችብ መሰሪ ቡድን የተሰበሰበበት ስርዓት ነው።ገንዘቡ በምን ቦታ ላይ መዋሉ ለማይታወቅ ብድርና ዕዳ አገሪቱን አሳልፎ የሰጠና የሚሰጥ ቡድን የተጠራቀመበት ስርዓት ነው። የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ይልቅ ለአሸባሪዎች ከለላና ድጋፍ የሚሰጥ የወንጀለኞች ዋሻ የሆነ መንግሥት ነው።ታዲያ ከዚህ አይነቱ ስርዓት ምን አይነት ሰላም እድገትና ብልጽግና ይጠበቃል?
አሁን ላይ ደግሞ በመካከላቸው የሚፈጠረው የስልት ልዩነት የፖለቲካውን መመሪያቸውን ለመለወጥ የሚደረግ ግብግብ አድርጎ በመቁጠር አንዱን የመደገፍና ሌላውን የመቃወም ጅልነት በመንጸባረቅ ላይ ነው።አንዱ አክራሪ ሌላው ለዘብተኛ ሆኖ ቢቀርብም ያው ጎሰኛ ጎሰኛ ነው።የጎሰኛ መልካም የለውም።ጎሰኝነት ሲውል ሲያድር ፋሽዝምን ይወልዳል።
ስለፖለቲካ ድርጅትም ያለን ግንዛቤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሱዋል።የፖለቲካ ድርጅት የህብረተሰቡን ብዙሃን ወይም አንዱን ክፍል ጥቅምና መብት ለማስከበር በሳይንሳዊ እይታ፣ፍልስፍና (ርእዩተዓለም)የታጠቀ፣መርሃ ግብር ነድፎ የሚንቀሳቀስ፣እምነት በሚጣልባቸውና ያንንም በተግባር ባሳዩ መሪዎች የሚመራ ድርጅት እንጂ እንደ እድር በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በሆይሆታ የሚያቋቁሙት፣ ምግባረቢስና ሸፍጠኞች የሚሰገሰጉበት አይደለም።
አገራችንን ከዚህ አይነቱ መሰሪና አጭበርባሪ ስርዓት፣እንዲሁም በተቃዋሚ ስም ከሚከናወነው ከጭፍን ጥላቻና ቡድናዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴና አደረጃጀት፣ሌላው ተቃዋሚ በነጻነት ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሶ ሕዝቡን ቀስቅሶና አሳምኖ ለምርጫ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ለሚካሄድ የምርጫ ጨዋታና ለሚያመጣው አደጋ ያለው አንድና ብቸኛ ምርጫ የአገር ወዳዱን ሃይል ማጠናከር ብሎም በአገር ወዳዱ ሃይል የሚመራ ጊዜያዊ/የሽግግር መንግሥት መመስረት ነው።የሽግግር መንግሥቱም ተግባራት የሚከተሉት ይሆናሉ፣
1 በመጀመሪያ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ሊያስከብሩ የሚችሉትን ብሔራዊ ተቋማት ይገነባል።በጎሳ መልክ የተቋቋሙትን ወገንተኛ ተቋማትን፣የፖለቲካ ድርጅቶችንና እንቅስቃሴዎችን በሕግ ያግዳል/ያፈራርሳል።
- አሁን የሚሰራበትን ሕገ ጎሳውን በማገድ የአገርና የሕዝብን ልዑላዊነት የሚያስከብር፣በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና ይሁንታ የዳበረ ብሔራዊ ሕገ-መንግሥት እንዲረቅና እንዲጸድቅ ያደርጋል፤
- ጎሳና ቋንቋን መሰረት ያደረገውን የክልል አወቃቀሩን አፍርሶ ሕዝቡ በቅርበት በሚቆጣጠረውና በሚሳተፍበት የክፍላተሃገር አወቃቀር ይተካል፤የፌዴራል ስርዓቱም በዚያው መልክ እንዲዋቀር ያደርጋል።
- የሰላምና የሕግ መከበሩን ተከትሎ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና ለእውነተኛ ዴሞክራሲና የፖለቲካ ለውጥ የቆሙ ድርጅቶች የሚሳተፉበት አገራዊ ምርጫ እንዲደረግ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ምርጫውንም ተከትሎ ላሸነፈው የፖለቲካ ድርጅት ሥልጣኑን ያስረክባል።
እነዚህን ዓላማዎች በተግባር ሊገልጥ የሚችል የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሁሉም አገር ወዳድ የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዲያበረክት ወገናዊ ጥሪ አቀርባለሁ።
የሽግግር መንግሥት ይቋቋም! የታቀደው ምርጫ ይሰረዝ!!
ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!
አገሬ አዲስ