እነሆ የዓለም ዓይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ አነጣጥረዋል

ዓለም ሁሉ ዕይታው ኢትዮጵያ ላይ ነው፤ ከፊሎቹ በክፋት፣ ከፊሎቹ ለጥናት፣ ከፊሎቹ እውነታውን ለመረዳት፣ ሌሎቹ ደግሞ በቅናት፡፡ ‹‹አንቺ ለዓለም ብርቅ የሆንሽ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠሸ ድንቅ ሚስጥር የት ነው ያለሽው?›› እያሉ ነው፡፡ ኩራት ውበቷ የሆነ፣ ለጠላት ያልተበገረች፣ ፈጣሪ በቃሉ ያጸናት አስርቱ ትዕዛዘትን ያሰፈረባትና ያሳረፈባት ኢትዮጵያ፤ ዓለም በንፍር ውኃ ጠፍታ ዳግም በኖኅ ዘር ስትለመለም ፍጥረታትም ሲበዙ፣ በፈጣሪ ዘንድ የተመረጠው ታላቁ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገር ነበር፡፡ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን እንዲመራና ወተትና ማር የምታፈልቀውን ምድር ከነዓንን እንዲያወርስ የተመረጠ ነብይ እንደነበር የሃይማኖት ድርሳናት ይመሠክራሉ፡፡

እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ አካባቢውም በደመና ተጋረደ፤ ፍጡር ሁሉ ፈራ ተጨነቀ ራደ፤ ሙሴ ግን ከእርሱ ጋር ይጋገር ነበር፡፡ በሲና ተራራ አናት ላይም የቃል ኪዳን ታቦት ተቀበለ፡፡ የእብራውያኑ ነብዩ ሙሴ የኢትዮጵያዊውን ካህን የዮቶርን ልጅ ሲጳራን ነበር ያገባው፡፡ ሕገ እግዚአብሔርን፣ ሥነ ምግባርና መልካም ትምህርቶችንም በሀበሻ ምድር ተምሯል፡፡

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከፈጠራት ከኤዶም ገነት የሚፈስሰው ታላቁና የተቀደሰው ወንዝ ግዮን የኢትዮጵያን ምድር ይከብባል፡፡ ኢትዮጵያም በገነት ፈሳሽ ወንዞች የተከበበች፣ በእግዚአብሔር የተመረጠች ቅዱሳን የሚኖሩባት፣ ጻድቃን የሚጠጉባት ጭቁኖች የሚመኩባት፣ ትቢተኞችም የሚያፍሩባትና አደብ የሚገዙባት ቅድስት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነት በዘመን እርዝማኔ፣ በቦታ መራራቅ የማይለወጥና የማይናወጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንደጋሻጃግሬ የሚያስከትሉት እንደመልካም ድል የሚመኩበት ኩራትና ተድላ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ነብይ ኤሪሚያስን ከጉድጓድ አውጥቶ ከሞት ያዳነው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አቤሜሌክ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ ለሰው እንደሚኖር ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ርኅራሄ፣ ድል፣ ዕድል፣ ታማኝነትና ሕይወት ነው፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበታተኑት ልጆቼ ቁርባኔን ያመጣሉ›› እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ኢትዮጵያውን የፈጣሪን መልካም ነገር የሚቀበሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለጥቁር ሁሉ ማሸነፍን ያስተማረች፤ እጇቿን ወደፈጣሪዋ ዘርግታ ለዓለም ምሕረትንና ሠላምን የምትለምን ድንቅ ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሕገ ልቦናን፣ ሕገ ኦሪትንና ሐዲስ ኪዳንን ያስተማረች ሀገርም ናት፡፡ ዓለም ከጨለማ ባልተላቀቀባት ጊዜ ብርሃን የነበረባት ሀገር ናትም ይላሉ ሊቃውንት፡፡

የሰው ልጅ ሳይሰለጥን፣ ጥበብ በዓለም ሁሉ ሳይስፋፋ፣ ስልጣኔ በወንዞች አካባቢ ተወስኖ በነበረበት ዘመን ቀድማ የሰለጠነች፤ አስቀድማ የተጠበበች፤ ደንጋይን እንደ ጭቃ ቅርጹን ገርተው ድንቅ ኪነ ሕንጻዎችን የሚሠሩባት የብልሆች ብልህ ሀገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ቅድመ ልደት ክርስቶስ ከ1000 ሺህ ዓመት በፊት በሀገር ደረጃ የኦሪት ሕግን ተቀብላ ነበር፡፡ ፈጣሪ ያዘጋጃት፣ ሃይማኖት የተሰበከባት የፈጣሪ ሕግ ያረፈባት፣ ቅድስቲቱ ከተማ አክሱምም የመንግሥቱ መቀመጫ ነበረች፡፡

በ2550ዓ.ዓ ገዳማ የነገሠው ኢትዮጵስ አክሱማይ ሲራክ የተባለ ልጅ እንደነበረውና በዚያ ዘመን አካባቢ እንደተቆረቆረች ይገርላታል፤ አክሱም፡፡ በኢትዮጵስ ልጅ አክሱማይ ሲራክ ስም የተሰዬመች እንደሆነ ሲነገር በሌላ በኩል ደግሞ ‹አክሱም› የሚለው ቃል ‹‹ከአገውኛ የተወረሰ ነው›› ይባላል፤ ትርጉሙም ‹ውኃ ሹም› ማለት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከአክሱም ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው አሁን በከተማዋ አካባቢ የሚገኘው ‹ማይሹም› የሚባለው አካባቢ ይህን ታሪክ ያጠናክረዋል፡፡

አክሱም ለኢትዮጵያውያን የብዙ ነገር መነሻ ናት፡፡ የዓለም ዓይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዩ ካደረጋቸው ሚስጥር፣ ስለቀዳሚውና ስለሙሴ ጽላት በዚህ ጽሑፍ ትንሽ ለማቅረብ ወደድን፡፡ ከአባ ጴንጤሊዮን ተራራ ግርጌ ከንግሥተ ሳባ ቤተ መንግሥት አጠገብ፣ በንግሥተ ሰባ መዋኛ ገንዳ የተከበበችውና አያሌ ሚስጥራትን በውስጧ ያነገበችው አክሱም ከተማ ሚስጥርን በመያዝ የሚስተካከላት የለም፡፡ በአክሱም ከነገሡት አያሌ ነገሥታት መካከል ስሟ ከብሮና ገንኖ የሚጠራው ንግሥተ ሳባ (ማክዳ) ወይንም ንግስተ አዜብ ናት፡፡ ንግሥተ ሳባ እርሷ ነግሣበት በነበረበት ዘመን በኢየሩሳሌምም አንድ ታላቅ ንጉሥ ነግሦ ነበር፡፡ ንግሥተ ሳባ ስለ ኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማችው ታምሪን በሚባለው ነጋዴዋ አማካኝት ነበር፡፡ ‹‹የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የመጣላትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች›› እንዲሉ መጽሐፍ ቅዱስና ክብረ ነገሥት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአፍሪካ ቀንድ ጅኦ-ፖለቲካል ሽኩቻና ውልደተ ውክልና ጦርነት!!! የውኃውን ቁልፉ እንጫነው? የትኛውን ፈረስ እንጫነው? ፋኖ በአማራ ክልል በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ይጥራ!!!

ታምሪን ነጋዴ ነበር፤ 520 ግመሎችና 73 መርከቦች ነበሩት፡፡ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ንጉሥ ሰሎሞን ለጽላተ ሙሴ ማስቀመጫ ይሆን ዘንድ ሦስተኛ ቤተ መቅደሱን ሊሠራ ባሰበ ጊዜ ለመሥሪያ ዕቃ የሚያመጡለት ሀብታም ነጋዴዎችን ያፈላልግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያዊው ሀብታም ነጋዴ ከታምሪን ጋርም በዚህ ምክንያት ተገናኘ፡፡ ንጉሡም ቀዩን ወርቅ፣ ጥቁሩን የማይነቅዝ እንጨትና ሰምጴር የተባለውን ከዓረብ ሀገር ታምሪን እንዲያመጣለት አዘዘው፡፡ ታምሪንም ንጉሡ የፈለገውን ሁሉ አመጣለት፡፡ ንጉሥ ሰሎሞንም ለታምሪን የሚሻውን ሁሉ ከገንዘቡ አብልጦ ሰጠው፡፡ ብልሁ ነጋዴ ከሰሎሞን ጋር በቆዬባቸው ጊዜያት የሰሎሞንን ጥበብ ያስታውል ነበር፡፡ ወደሀገሩም በተመለሰ ጊዜ ከንጉሥ ሰሎሞን ያዬውን ሁሉ ለንግሥተ ሳባ ነገራት፡፡ ንግሥቷም ከነጋዴው በሰማችው ነገር ትደነቅና ወደ ሰሎሞንም ለመሄድ ሻተች፡፡

በመጨረሻም ከጥበቡ ለማዬትና ለመታዘብ ወደ ቅድስቲቱ ምድር ለመሄድ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ለምንገዷ የሚያስፈለጉ፣ ለንጉሡ የሚቀርበውን ገጸ በረከት እና ለመኳንንቱና ለመሳፍንቱ የሚሰጠውን ስጦታ ሁሉ አዘጋጅታ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ በኢየሩሳሌምም ብዙ ጥበብ ከሰሎሞን ተማረች፡፡ እርሱም ከንግሥተ ሳባ ብዙ ነገር ተመለከተ፡፡

በስጋዊ ፍቅርም ወደቁ፤ ንግሥቷም ከንጉሡ ፀነሰች፡፡ ነፍሰ ጡር ሆናም ንግሥቷ ወደ ሀገሯ ተመለሰች፤ ወለደችም፡፡ ስሙም ምኒልክ ተባለ፤ አድጎም ወደ ኢየሩሳሌም አባቱን ለመተዋወቅ ሄደ፡፡
ምኒልክ በአባቱ ዘንድ ተወደደ፤ ‹‹ይህን ልጄን በእየሩሳሌም አነግሠዋሁ›› ሲልም ንጉሥ ሰሎሞን ተሰማ፡፡ ምኒልክ ግን ከእየሩሳሌም ይልቅ በኢትዮጵያ መንገሥ እንደሚፈልግ አጥብቆ ተናገረ፤ በእስራኤላውያን በኩልም ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ቅሬታ ይቀርብ ነበር፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም መኳንንቱንና መሳፍንቱን አስጠርቶ ‹‹እነሆ አሁን የምነግራችሁን ስሙኝ፡፡ በቀኜም በግራዬም የምትቀመጡ መኳንንትና መሳፍንንት ሆይ! ልጄን ከልጆቻችሁ ጋር በኢትዮጵያ እንድናነግሠው ፍቀዱ፤ ልጆቻችሁም እንዲሁ አለቃ ሆነው በቀኝና በግራ ሆነው ይቀመጡ፤ እናንተ አማካሪዎቼ መኳንንትና መሳፍንት የበኩር ልጆቻችሁን እንሰጠው ዘንድ ፍቀዱ፤ በተወለደበት ንጉሥ ይሆናልና›› አላቸው፡፡ እነርሱም ፈቃዳቸው ሆነ፡፡

ለቅበዓ መንግሥቱን የሚጣፍጥ ሽቶ አዘጋጁ፤ ነጋሪት፣ እምቢልታ፣ እንዚራ፣መሰንቆና ከበሮ ተመታ፤ ቅድስቲቱ ከተማ በልዕልታና በደስታ ድምጽ ተመላች፡፡ ወደ ቤተመቅደሱም ውስጥ አስገቡት፡፡ በካህኑ በሳዶቅና የንጉሥ ሰለሞን የኃይል አዛዥና ካህን በሆነው በኢዮሳፍ ቅብዓ መንግሥት ተሰጠው፡፡ ከቤተ መቅደስም ወጣ፡፡ ስሙን ዳዊት ብለው ሰየሙት፡፡

ቀደማዊ ምኒልክ ከአባቱ ከሰሎሞን ጋር በኢየሩሳሌም ሦስት ዓመታትን ሲኖር በሊቀ ካህናቱ በሳዶቅ መምህርነት ሕገ ኦሪትን፣ ሕገ መንግሥትንና የእብራይስጥ ቋንቋን ተምሯል፡፡ ከንጉሡ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ የታዘዙ የእስራኤል የበኩር ልጆችም ከሀገራቸውና ከወገናቸው ይልቁንም ከታቦተ ጽዮን ተለይቶ መሄድ እጅግ አሳዝኗቸው ነበር፡፡ የካህናቱም ልጆች ለብቻቸው ተሰባስበው ‹‹ጽዮንን እንዴት ልንተዋት እንችላለን? ለእርሷም ተሰጥተናልና ምን እናድርግ?›› ብለው ተማከሩ፡፡

የካህኑ የሳዶቅ ልጅ አዛሪያስ ‹‹ታቦተ ጽዮንን ከመንበሯ ማንም ሳያውቅብን እንውሰዳት!›› የሚል ሐሳብ አቀረበ፤ ሁሉም ተስማሙ፡፡ የቤተ መቅደሱ ቁልፍ በአዛሪያስ እጅ የነበረ በመሆኑ ማድረግ እንደሚቻልም አመኑ፡፡ የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ለአብነትም ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ ለአዛሪያስ ደግሞ ታዬው በላዩም ላይ እንደ እሳት ምሰሶ፤ ወጣ በብርሃኑም ቤቱ ተመላ፣ አዛሪያስንም አስነስቶ ‹ቁም፣ ጽና፣ ወንድምህን ኤልማኖስን፣ አብሳን፣ መክሪምንም አንቃ፤ እነዚህን የጽላት እንጨቶች ውሰዱ፤ እኔም የቤተ መቅደሱን በሮች እከፍትልሃለሁ.፤የእግዚአብሔርንም ታቦተ ሕግ ውሰዳት፡፡ እኔም ለዘላለም ከእርሷ ጋር እንድኖርና በአያያዟም መሪ እንድሆንልህ ከእግዚአብሔር ታዝዣለሁ› አለው፡፡›› ይላሉ አበው፡፡ የተባሉትንም አደረጉ፡፡ ታቦተ ጽዮንን ከመንበሩ አንስተው ወደ አዛሪያስ ቤት አስገቧት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ውሉን የሳተ የትግል ጉዞ - ከእውነቱ ፈረደ   

ቀደማዊ ምኒልክ አባቱን ተሰናብቶ ወደ ሀገሩ ሊመለስ በዝግጅት ላይ በነበረ ገዜ የነበረውን ትርምስ እንዲህ ብለው ይገልጹታል፤ ‹‹ሰረገላዎቹ ሁሉ ተጫኑ፣ አለቆዎች ሁሉ ተነሱ፣ ነጋሪት ተመታ፣ ሀገሪቱም ጮኸች፣ ጎልማሶች ደነፉ፣ግርማም ጋረዳት፣ ጸጋም ከበባት፣ የእስራኤል ጀግኖችና የመኳንንቱ ልጆች ስለተነሱ ሽማግሌዎች ዋይ ዋይ አሉ፡፡ ሕጻናት ጮሁ፤ ባልቴቶችና ደናግላንም አለቀሱ፤ በእነርሱ ምክንያት ግርማዋ ስለተወሰደባት እንጂ ሀገሪቷ የምታለቅሰው ስለእነርሱ ብቻ አይደለም፤ ታቦተ ጽዮን እንደተወሰደች በግልጽ ባያውቁም በልባቸው አልሳቱም ነበርና እግዚአብሔር የግብጽን የበኩር ልጆች በገደለ ጊዜ እንደነበረው ዓይነት መሪር ለቅሶን አለቀሱ፡፡››
ንጉሥ ሰሎሞንም በሁኔታው ደነገጠ፡፡ የሚሄዱትን ሰዎች ግርማ ባዬ ጊዜም እንባው በክብር ልብሱ ላይ እስኪንጠባጠብ ድረስ አምርሮ እንዳለቀሰ አፈ ታሪኮች ያስረዳሉ፡፡ ሰሎሞንም ምኒልክ በመሄዱ የሀገሩ ግርማ ስለተገፈፈ የበኩር ልጆችንም ይዞ ስለተንቀሳቀሰ ‹‹ክብሬ አልፋለች፤ የመመኪያዬ ዘውድም ወድቃለች፤ ሆዴም ተቃጥላለች፤ ወዮልኝ›› አለ፡፡ ከ12 ነገደ እስራኤል የተውጣጣ በጠቅላላው 12 ሺህ (አንዳንድ ድርሳናት 40 ሺህ ይላሉ) ሕዝብ ምኒልክን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡

በእግዚአብሔር መልአክ መሪነትም ወደሌላኛዋ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ንጉሡን ተከትለው የመጡት ካህናት ምኒልክን ‹‹ሚስጥር ትችል እንደሆነ እንገርህ›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹እችላለሁ እስከ ዕለተ ሞቴም አልናገርም›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ፀሐይ ከሰማይ ወረደች፤ በሲናም ለእስራኤል ተሰጠች፡፡ ከሙሴ እስከ እሴይ ዘር ድረስ ለዓዳም ዘር ሁሉ መድኃኒት ሆነች፡፡ እነሆ በእግዚአብሔር ፈቃድ በአንተ ዘንድ ናት፤ እግዚአብሔርም አንተንና ሀገርህን ለቅድስቲቷ ለሰማይቷ ጽዮን አገልጋይ ትሆኑ ዘንድ መረጠ፡፡ የአምላክህን ትዕዛዝ ከጠበክ ለአንተም ከአንተ በኋላ ለሚመጣው ለዘርህም መሪ ትሆናለች፤ አንተ ብትሻ እርሷን ለመመለስ አትችልም፤ አባትህም ቢሻ አይችልም፤ እርሷ ወደፈቀደችበት ትሄዳለች እንጂ›› አሉት፡፡

ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ባዬ ጊዜም ደንግጦ ለፈጣሪው ምሥጋናን አቀረበ፡፡ ታቦተ ጽዮን መምጣቷ ሲሰማ በኢትዮጵያ ደስታ ሆነ፤ በኢየሩሳሌም ደግሞ ሐዘን ሆነ፡፡ ካህኑ ሳዶቅ ወደንጉሥ ሰሎሞን በተመለሰ ጊዜ ንጉሡ ሲተክዝ አገኘው፡፡ ንጉሡም ያስተከዘውን ለካህኑ ሳዶቅ ነገረው፡፡ ‹‹ንገሥተ ሳበ በመጣች ወቅት በሌሊት እንዲህ ዓይቼ ነበር፤ በእየሩሳሌም ዋልታ እንደቆምኩ በይሁዳ ሀገር ከሰማይ ፀሐይ ወረደች፤ እጅግም አበራች፤ ቆይታም ጠፋች፡፡ በሀገረ ኢትዮጵያ አበራች ፤ሁለተኛም ያቺ ፀሐይ ወደ አይሁድ አልተመለሰችም፡፡›› ካህኑ ሳዶቅ ይህንን እንደሰማ ደንግጦ ወደ ቤተ መቅደሱ ገሰገሰ፡፡ ወደ ቤተመቅደስም ገባ ታቦተ ጽዮን አልነበረችም፡፡ በድንጋጤ እንደበድን ሆነ፡፡ ንጉሡም በሰማም ጊዜ ተቆጣ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነም ስላወቀ አልቅሶ ዝም አለ፡፡

የእስራኤል ክብር ወደ ኢትዮጵያም መጣ፡፡ ታቦተ ጽዮንም በፈጣሪ ፈቃድ በግዮን ከምትከበበው ከቅድስቲቷ ምድር ለመቀመጥ ኢትዮጵያን መረጠች፡፡ ኢትዮጵያውያንም የዚህ ድንቅ ሚስጥር መቀመጫ እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡ ምኒልክ እናቱን ሲያገኝ ‹እልልል› ብላ ተቀብላ አነገሠችው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዲሲ 2013 - ክንፉ አሰፋ

ከእየሩሳሌም ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ወጥታ በኢትዮጵያ በምኩራብ ለብዙ ዓመታት ተቀምጣለች፡፡ ከታቦተ ጽዮን ጋር የመጡት እስራኤላውያንም በዚሁ ቀሩ፡፡ ክርስቶስ ያለው ቃል ሲደርስ በአዲስ ሕይወት አዲስ ኪዳን ተተካ፡፡ በ34 ዓ.ም በሐዋሪያው ፊሊጶስ አማካኝነት የአዲስ ኪዳን ክርስትናን ተቀበለች፡፡ በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አማከኝነትም ከሕገ ኦሪት ወደ ሐዲስ ኪዳን ተሸጋገረች ፡፡

አባ ሰላማ በኢትዮጵያ የተሾሙ የመጀመሪያው ጳጳስ ናቸው፡፡ የቀደመ ስማቸው ፍርሚናጦስ ነበር፡፡ አቡነ ሰላማ ቅዱሳት መጻሕፍ ከሰባ ወደ ግዕዝ እንዲተረገሙና የተስተካከለ የአጻጻፍ ስልት እንዲመጣም ታላቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያን ለ15 ዓመታት ያስተዳደሩት መንትያዮቹ አብርሃ ወአጽብኃ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ 12 ክፍል ቤተ መቅደስ በአክሱም ሠሩ፡፡ ቤተ መቅደሱ 72 ምሰሶዎች የነበሩበት አስደናቂም ነበር፡፡ ለ14 ዓመታት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ በአቡነ ሰላማ ተባርኮ ታቦተ ጽዮን ካረፈችበት መቅደሰ ኦሪት ወጥታ አዲስ ወደተሠራው ቤተ መቅደስ ገባች፡፡ በዓሉን ለማክበርም ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣ ሕዝብ ተሰብስቦ ነበር ይባላል፡፡ በእልልታና በዝማሬም ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡

የዓለምም ዓይን ይህን ሚስጥር ለማዬትና ለማወቅ ወደኢትዮጵያ ይመጣሉ፤ ነገር ግን ማዬት አይቻላቸውም፡፡ ኢትዮጵያም በፈጣሪ ጸናች፤ አትናወጥምም፡፡ ከታቦተ ጽዮን በኋላ በእርሷ አምሳል እየተሠራ በተለያዩ አብያ ክርስቲያናት ጽላት ይቀመጣል፡፡ አብርሃ ወአጽብኃ ያሠሩት ቤተ መቅደስ ከ600 ዓመታት በኋላ በዮዲት ጉዲት ዘመን ጠፋ፡፡ ንጉሡ አንበሳውድም ባለሰባት ቤተ መቅደስ አድርጎ ድጋሜ አሠራው፡፡ ጽዮንን ግን አስቀድመው አሸሽተዋት ስለነበረች በዮዲት ጊዜ በጠላት አልተነካችም፡፡ የንጉሡ አንበሳውድም ቤተ መቅደስ ድጋሜ በግራኝ አህመድ ዘመን ጠፋ፡፡ ንዋዬ ቅድሳቱና ታቦተ ጽዮን ግን አስቀድመው ከቦታው ተነስተው ነበርና አልተጎዱም፡፡

እስከ አጼ ፋሲለደስ ዘመነ መንግሥት ድረስም የአክሱም ቤተ መቅደስ እንደፈረሰች ቆዬች፡፡ አጼ ፋሲል የጎንደርን አብያተ መንግሥታት በሚስል ድንቅ ጥበብ ባለሦስት ቤተ መቅደስ በአክሱም አሠሩ፡፡ እርሳቸው ያሠሩት አስደናቂ ቤተ መቅደስም ዛሬ ድረስ ተውቦና አምሮ ይገኛል፡፡ በኋላም አጼ ኃይለሥላሴ በዘመናዊ አሠራር ሌላ ተጨማሪ ቤተ መቅደስ በድንቅ ሁኔታ አሠሩ፡፡ የቀደማዊ ኃይለሥላሴ ባለቤት እቴጌ መነንም ባለ አንድ ፎቅ ቤተ መቅደስ አሠሩ፡፡

ይህ ሁሉ ታሪክና ክብር ያላት ርዕሰ አድባራት ወገደማት አክሱም ጽዮን ማርያም ኅዳር 21 ቀን በየዓመቱ በታላቅ ክብር ትከብራለች፡፡ ስለምን ቢሉ ‹‹በዚህ ቀን ታቦተ ጽዮን ደራጎን የተባለውን ጣዖት የሰበረችበትን ቀን ለማሰብ፤ ቀደማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የገባበትና ንግሥተ ሳባም በደስታ ግብዣ ያደረገችበትን ለማሰብ፣ አብርሃ ወ ጽብኃ የመጀመሪያውን ባለ 12 ቤተ መቅደስ አሰርተው ታቦተ ጽዮንን ያስገቡበት ቀንም ስለሆነ ያንን ለማሰብ፣ በዮዲት የጥፋት ዘመን ጊዜ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ዝዋይ ደሴት ተሰደው የነበሩት አባቶች የተመለሱት በኅዳር 21 ቀን ስለሆነ ያን ለማሰብና ሌሎች አያሌ ሚስጥራትን ለማድረግ ኅዳር 21 አክሱም ጽዮን ማርያም በእልልታና በዝማሬ ትከብራለች›› ይባላል፡፡

እነሆም ዛሬም አክሱም ጽዮን እየከበረች ትገኛለች፡፡ ሚስጥሩን ለማዬት የሚጓጉ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ወደ አክሱም ተጉዘዋል፤ ታሪኩንም ያያሉ፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሚስጥር ነው፡፡ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ፡፡

‹ታቦተ ጽዮን በኢትዮጵያ› በሚል የተዘጋጀውን ዘጋቢ ፊልም፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከብረ ነገሥትና ታቦተ ጽዮንን ፍለጋ መጻሕፍትን በማጣቀሻነት ተጠቅመናል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 21/2012ዓ.ም (አብመድ)

3 Comments

  1. የኣኽሱም በወርቅ የተሰራው ቤተ ክርስትያንን ሁለቴ በጉዲት እና በግራኝ ከተቃጠለ በኋላ፣ ፋሲል ለጊዜው የወርቅ ቤተ ክርስትያኑ እንደገና እስኪነደቅ ጊዜ ድረስ ብሎ ይችን ጊዝያዊ ህንፃን አቆመ:: ከዚያን በኋላ ወደ ስልጣን የመጡት ሁሉ ፅዮንንም “ከትግሬን ማድቀቅ ነው” ኢላማቸው ጋራ ስለ አዳመሩት እንኳንስ የወርቅ ይቅርና ዞር ብለውም አላዩትም፣ ከሃዲዋ ወያነም ብትሆን በየአውስትራሊያው ባንኮች ምንትሴዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ባለቤት የሌላቸውን ህንፃዎችን ሁሉ ስታስገትር፣ ይሄንን ህንፃን ግን በብርጭቆ ወረቀት ከማስፈግፈግ በኋላ ኖራ እንኳን አላስለቀለቀችውም….! ሰዎች እስኪ ህንፃውን እማ እዩት..!

  2. This is deep and faith building spiritual jewel and thank you Mr.Tarko Kende “Kibur ታርቆ ክንዴ” I add the title Kibur because you deserve it. I am tired of garbage politics and am hungry for faith and spiritual historic narrations. It is like a movie when I read and the title and the narration”እነሆ የዓለም ዓይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ አነጣጥረዋል”.
    We have to be cautious to preserve our heritage and protect it. It is sad The woyanes or TPLF when they rob the wealth of the Country they don’t even think of renovation of the AKSUM CHURCH it is because they were only thinking for themselves not even for the people of Tigray and “OUR LADY ST. MARY of AKSUM TSION DOES NOT ALLOW MONEY THAT COMES ILLEGALLY FROM TPLF SHIFTAS IT IS A CURSED MONEY”.
    I LAUGH WHEN TPLF TALKS ABOUT RIGHTS OF PEOPLE AND THE RULE OF LAW YOU DONOT GET WHAT YOU DONOT PUT LEAVE ALONE TO THINK FOR ETHIOPIA TPLF DOES NOT CARE FOR PEOPLE’S RIGHT ONLY FOR THEMSELVES A BUNCH OF THIEVIES AND KILLERS.
    YOU WILL SEE WHAT AKSUM TIZION WILL DO TO THOSE OLD GUARD ROBBERS THEIR DAY ARE NUMBERED AND THEY DO NOT DIE QUICK THEY WILL HAVE TO SUFFER AND PROLONG THEIR MISERY.
    OUR DEAR LADY THE VIRGIN MARY OF AKSUM TSIZON WILL PROTECT THE EVIL EYES AND WILL ALLOW ONLY THOSE WITH LOVE, UNITY, PEACEFULL FREEDOM AND UDERSTANDING AND RESPECT FOR ONE ANOTHER.
    GOD BLESS ETHIOPIA.
    MUCHFUN A KASSA
    CANADA.

Comments are closed.

Share