ዘንድሮ የሚሥተዋለው የፓለቲካ ትኩሣት ከመደበኛው በላይ መሆን በእጅጉ ያሣሥበኛል ።    (ሰው ዘ ናዝሬት )

ዘንድሮ፣ዘንድሮ፣ዘንድሮ
የሥንቱ ተወርቶ የሥንቱ ተነግሮ፡፡ ዘንድሮ!
       ወሎ በማደሩ ተዋሐደንና
       መጥፎ ከደህና ጋር ተማታብንና
      ብዙ ዓመታት አልፈው ዛሬ ነቃንና
      ያስቀን ጀመረ ግራ ገባንና፡፡
አዝማች
      በዛኛው ተገርመን ጥቂት ሳንቆይ
     የዚህኛው መባስ አያስቅም ወይ
     ይህ ሁሉ ነገር ሥንት ዘመን ኖሮ
     በጣም ያስገርማል ጉድአየን ዘንድሮ፡፡
አዝማች
    ብዙ ዓመት በድብቅ ሲጎዝ ከረመና
    ዘንድሮ ላይ ሲደርስ ሸክሙ አጋደለና
   ተዘረክርኮ ወድቆ በግልፅ ብናየው
    የዘንድሮን ነገር ዘንድሮ አወቅነው፡፡
  “ዘንድሮ ”  የተሰኘው የጥላሁን ገሠሠ ምርጥ የሥልሳዎቹ  መጨረሻ  ዘፈን ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ከግጥሙ  እንደተገነዘባችሁ አምናለሁ፡፡
   ዛሬ ላይ   ሆኜ የጥላሁን ገሠሠን ዘፈን ስሰማ በአሁኑ ወቀት ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት እጅግ በጣም የሳስበኛል፡፡
    ትኩሳት የበሽታ ምልክት ነው ።አንድ የታመመ ሰው በሙቀት መሳሪ መለኪያ የሰውነቱ ሙቀት የለካል፡፡ሙቀቱ ከ37 ዲገሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ከሆነ በሰውነቱ ውስጥ በምርመራ የሚደረስበት በሽታ እንዳለ ያመላክታል፡፡
    በወቅቱ የትኩሳቱ መንሰኤ ተውቆ ህክምና ካለገኘ፣ ትኩሳቱ እየጨመረ የህመምተኛው ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይታወቃል፡፡ ትኩሳቱ ከ39  ዲግሪ ሴንቲግሬድ  በላይ ሲሆን ህመምተኛው መቃዠት ይጀምራል።  እንደሁም  የፖለቲካ ትኩሳት ከመደበኛ ልኩ በላይ እየሆነ ከሄደ የሚቃዡ ፖለቲከኞችን እዛና እዚህ እንደሰካራም ሲቀበጣጥሩ እናገኛቸዋለን።
   ዘንድሮ  የፖለቲካውን ትኩሳት ከፍ እና ዝቅ የሚያደርጉ እዛና እዚህ ሥለበዙ ሀገር እና ህዝብ በትኩሳቱ ወላፈን እየተገረፉ ነው። ግርፋቱ ለሥቃይ፣ለሞት እና ለሥደት እየዳረጋቸው ነው።
     እንሆ አሁን በዚህ ወቅት  ደግሞ ትምህርትን ለመማር በፌደራል መንግሥቱ ዩኒቨርሥቲ እየተማሩ ያሉ በአሸባሪ ኃይሎች የፖለቲካዊ ትኩሳት ጨማሪነት እየታወኩ ነው።  የፊደራል ዩኒቨርሥቲዎች በፊደራል መንግሥት እሥከልተጠበቁ ጊዜ ድረሥ ግጭቱ ይዳፈናል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይጠፋም።
   በዘፈኑ ተምሳሌትነት እንኳን ዘንድሮን ብንገመግም ዘንድሮ፣በአይናያችን ያላየነው ምን  አሥዳሳች እና አሳዛኝ ነገር አለ ?! …እንደዘንድሮስ ከቶሥ በጆሯችን  ያልሰማነው ምንሥ ቀፋፊ እና  አሥደሳች ወሬስ ይገኝና?!… ዘፈኑ ከሚጠቅሰው ከ1967 ዓ/ም ግብታዊ “ሥር ነቀል “ለውጥ ግርግር፣ሥቃይ እና የእርሥ በእርሥ እልቂት ረዢም ጊዜ በኋላ ፣እንሆ ” ዘንድሮ ” ከመቼውም ጊዜ በላይ የሞት ድግሥ ደጋሾች እና ” ግጭትን የኃብት ማፍሪዬ ያደረጉ አሥመሳይ ፓለቲከኞች” ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲረቃቸው ሌት እና ቀን የማጋጨት ሴራ  ሲነድፉና እና ቦታ እና ሥልት በመቀያየር እንደሁኔታው አመችነት መላው ኢትዮጵያን በማተራመሥ ላይ ይገኛሉ።
     እውነት ነው፣ ዘንድሮ የሥንቱ ተነገሮ፣የሥንቱሥ ተወርቶ ያልቃል።ቴክኖሎጂ ያፈላቸው ቴሌቪዢኖች ፣ህዝብን፣ማሳወቅ፣ማሥተማር፣ማዝናናት እና ህግን አክብረው ከማሥከበር ይልቅ ፣ ” ሰው ውሻ  ሲነክሥ  ” ለማሳየት ፣ያልታረሙ ሥድ ንግግሮችን ፣ቆዳ ማወደዶችን፣ሰው ሰውነቱን ዘንግቶ በግብዝነት ሲመፃደቅ እና  በሥሜት በመገፋፋት በአፉ  ሞርተር  ያለሃፍረት በአምሳየው ሰው ላይ ሲተኩሥ ያሳያሉ።
   አንዳዶቹ፣  የጠጅ ቤት እንካሰላንትያዎችን ጭምር  ለመድረክ በማብቃት ፣ሰዎች በሥህታቸው እንዲገፉ ያደርጋሉ።…
      በየክልሉ የተቋቋሙ የፀጥታ ጠባቂዎች እና ጥቂት ፓሊሶችም፣ከህግ ይልቅ ለቋንቋ ይወግናሉ።እናም የሀገሪቱን ህግ ሳይሆን ቋንቋ የተባለን ጣዖት ለመጠበቅ ደሞዝ እንደሚከፈላቸው በማመን በክልላቸው ባሉ የፊደራል ዩኒቨርሥቲዎች ግጭት ሲነሳ እንኳ ለቋንቋው ተናጋሪዎች ዘብ ሲቆሙ ተሥተውለዋል።ቋንቋቸውን የማይናገረውን የማሪያም ጠላት አድርጎ ማየት በራሱ ውጉዝ ተግባር ነው።
       በየዩኒቨርሥቲው ያሉ ተማሪዎች ሁሉ  ሰው ሆነው ሳለ ሰውነታቸውን ዘንግተው የራሳቸውን ቆዳ በማዋደድ ፣ “እኛ ቋንቋ እንጂ ሰው አይደለንም ። ” የሚሉትን ልክናችው በማለት ወደ ከ17 ኛው ክ/ዘ ጀምሮ እሥከ 20 ኛው ክ/ዘ በሀገራችን ወደነበረው  ጭፍን ጥላቻ እና ጭፍን ፍቅር  ፣ በ21 ኛው ክ/ዘመንም መወሥድ ሤጣናዊ ተግባር ነውና ልናወግዘውና “ይበቃል!” ልንል ይገባል።
   የዛሬዋ ኢትዮጵያን በዚህ ዘመነኛ ፣ የዓለም ህዝብ በቴክኖሎጂ አማካኝነት በተቀራረበበት  21ኛው ክ/ዘመን  ጭፍን ፍቅር እና ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ግለሰቦች ተቦድነው፣ፓርቲ ነኝ ብለው ፣በመንግሥት እውቅና አግኝተው ሀገር ምድሩን ሲያጋጩ እና በግጭት ውሥጥ ተንደላቀው ሲኖሩ ሳይ በእጅጉ አዝናለሁ።
     ለግጭት እና ለሸበር በዋናኛነት የሚጠቀሙበት  መሳሪያ ቋንቋ እና ዘር መሆኑ ደግሞ የበለጠ ያሳዝነኛል ። ዘንድሮ፣ ቋንቋ እና ዘር ሰዎችን   ማፋለጫ  መሣሪያ ” የሆነበት ሀገር የእኛ ሀገር ብቻ ነው።
   ይህንን በመገንዘብ ፣የደነዘዙትን ከድንዛዜያቸው ለመፈወሥ፣ግጭትን የሀብት ምንጭ ያደረጉትን   “ይበቃል !” ለማለት ኢህአዴግ  እንዲፈርሥ አሻጋሪው የለውጥ ኃይል መወሰኑ እንደታላቅ የምሥራች እወሥደዋለሁ።  በእውነቱ ሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጋ ከምር የሚያሳትፍ ፓርቲ ለመመሥረት አሻጋሪው የለውጥ ኃይል መወሰኑ እና ወደተግባር መግባቱ የሚያሥመሰግነው ነው። ።የፓርቲውንም ሥያሜ “የብልፅግና ፓርቲ” ብሎ መሰየሙ አሻጋሪው የለውጥ ኃይል በኢትዮጵያ ድህነት መቆጨቱን አመላካች ነው።
         እርግጥ፣  ለእኔ እና ለመሰሎቼ  የብልፅግና  ፖርቲ በአሥራአንደኛው ሰዓት በኢሕአዴግ  ማህፀን ውሥጥ መፈጠሩ  አላሥገረመንም።  የብልፅግና ፓርቲ ወደፊት ጥቅማችንን ሊያሣጣን ይችላል በማለት የሚሰጉ ግን መገረምን ሳይሆን ድንጋጤን ፈጥሮባቸዋል።
      ከእነዚህ ይልቅ በእጅጉ የሚገርመው ህወሓት  “ብልፅግናን አልፈልግም።ዘላለም ዓለሜን ነፃ አውጪ ተብዬ በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተደላድዬ መቀመጥ ነው። የምፈልገው።” ማለቷ ነው። ?!  ወይሥ   የብልፅግና ፓርቲ ምሥረታ ለህወሓት   አሥደንጋጭ እና እንደእናት ሞት የተቆጠረበት ምክንያት ሰበቡ ህወሃት በአሥተሳሰብ የጃጁ ግለሰቦች እየመሯት ሥለሚገኙ ነውን?! ።
     ህወሃት ወጣቶችን በፓርቲው  ከፍተኛ  አመራር  ደጃፍ  አላሥደርሥም ብላ ፣የሰው እንጂ፣የመልአክት ሥብሥብነቷን ዘንግታ፣ ሥትሞዘዝ ፣ ጃጅተው ሥልጣን አለቅም እንዳሉት ቀኃሥ እጣ ፈንታዋ እንዳይሆን  አሥራአንደኛው ሰዓት ከመጠናቀቁ በፊት ብታሥብበት መልካም ነው።
  ህወሃት  የግለሰብ ሥብሥብሥብነቷን ረሥታ እና ሰዎች በባዮሎጂ በተራ በተራ መሞታቸውን እና በአዲሥ ትውልድ መተካታቸውን ዘንግታ እንደኃይለሥላሴ በድዴ እገዛለሁ ብላ መሟዘዞ  ህወሓት የሞተቺው  መለሥ ሲሞት እንደነበር ዛሬም ሥላልገበት ይመሥለኛል።
    መለሥን የተኩት ” ኢየሱሳዊው ”  ሰው፣  ከ2007 ዓ/ም    ጀምሮ እሥከ 2010  ዓ/ም እየከፋ  የመጣባቸወን  ህዝባዊ ተቃውሞ መቋቋም አቅቷቸው  በተጨማሪም፣ እንደመለሥ  ንጉሥ አልነበሩም እና ለእኛ ግልፅ ያልሆነልንን መንግሥታዊ ችግር መቋቋም ሥላልቻሉ   ፣  ” ጠ/ሚርነቱ ይቅርብኝ፣ከችግሩ አካልነት ይልቅ የመፍትሄው አካል መሆን ይሻለኛል  ።”  በማለት ሥልጣናቸውን ሲለቁ ነበር ህወሃት  የሞተቸው። ይህንን እንኳ ዛሬ ላይ ሆና አሮጊቷ አላመነችም።
   ይህ ሁኔታ አንድ ለጥቅሥ የሚበቃ ፣ የአንድ ሰካራም ታሪክን አሥታወሰኝ። እንሆ !
    —ሰውየው ተጠንቅቀው በሚሄዱበት ጭቃማ ጠባብ መንገድ ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ ሲሄድ ፣በሥካሩ ሰበብ  አሥሬ እየወደቀ እየተነሳ ፣”ይህቺን የወዳል!…ይኽቺን ይወዳል !”እያለ ከኋላው ያሉትን መንገደኞች አላሳልፍ አለ።በዚህ ሰካራም የተበሳጨው ከኋላው ሆኖ ማለፍያ መንገዱ የተዘጋበት፣ ሰው፣ ሰካራሙ ለአሥረኛ ጊዜ ወድቆ  “እቺን ይወዳል !” ብሎ ሊነሳ ሲውተረተር ትከሻውን ተጭኖ መሬት ላይ በጀርባው አሥተኛውና ፣”ወዳጄ ጭቃውን ከወደድከው እንዳሻ ተከባለልበት ።እኛ ግን  እንዳናልፍ መንገድ አትዝጋብን “በማለት ፣መንገደኞቹ እየተራመዱት እንዲያልፉት አደረገ።—
      አሮጊቶ  ህወሃት በሌኒን ሥም፣በማርክሥ ሥም፣በቼ ጉቬራ ሥም፣በሆቺሚኒ ሥም፣በአጠቃላይ በግራ ፓለቲካ ሥም ፣ ድሮ በሚባል ዘመን ሥትምልና ሥትገዘት ኖራ  ለዘንድሮ በቅታለች።
  ህወሓት እርሶም አርጅታ መሥራቾቿም በተፍጥሯዊ  ሞት እና በእርጅና  ተራ በተራ እየተለይዋት ነው። ያልሞተው ሥያሜዋ በቻ መሆኑን ግን አንዳንድ የዋሆች ከቶም አልተገነዘቡም። በአረጀ እና ባፈጀ ዘመንን በማይሻገር ሥም ፣  ዛሬም አለው ማለት  ፣ ለጊዜ፣ለቦታ ና ለሁኔታ   ደንታ ቢሥነትን ያሳያል። ይህ እንዝላልነት ደግሞ ዋጋ ያሥከፍላል። (  ወያኔ የተባለው  ሥም ከ1936 ጀምሮ፣በቀዳማይ ወያኔ  የተፈጠረ ሥም  እንጂ ፣ በ 27 ዓመት የተፈጠረ ሥም እንዳልሆነ ታሪክ ይመሰክራል።)
     27 ዓመት ሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነው፣በመላው  ሀገር እንደፈለጋቸው የሥልጣንን ኳሥ ሲጠልዙ ከርመው፣ ለጥቂት የሥልጣን አጋሮቻቸው ብልጽግናን አውርሰው፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ድህነትን አጎናፅፈው ፣ በገሃድ እየታዩ ፤ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒሥቴር   አብይ አህመድ ፊት አውራሪነት፣ “በህዝብ መነገድ ይብቃ።ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ይኑር።ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት በእኩልነት ይታይ። ፍትህ እና ዴሞክራሲ ከምር በሀገር ይሥፈን።በውሥጥም በውጪም ያሉ ኢትዮጵያውያን በዜግነታቸው ኮርተው ፣ይኸቺን  ውብ ሀገራቸውን አበልፅገው ይበልፅጉ።
        “ብልፅግናን  ለዜጎች ለማላበሥ በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ።”የሚሉም   በአዲሱ የብልፅግና ፓርቲ አባል ሆነው የበኩላቸውን ሀገራዊ ግዴታ ይወጡ። … ” ሲባል፣  የብልፅግና ፓርቲ የሚመሰረተው በሕወሓት መቃብር ላይ ነው ! ” ብሎ ለያዥ ለገራዥ ማሥቸገር እጅግ አሥነዋሪ ተግባር ከመሆኑም በላይ የትግራይን ህዝብ ካለማወቅ የመነጨ ነው።የትግራይ ህዝብ እንደ ሰው እና እንደህዝብ ብልፅግናን እንጂ፣ጦርነትን፣ርሃብንን እንዲሁም ጉሥቁልናን ከቶም አይመኝም።
      የህወሓት ኢህአዴግን ሥብሥብ ብልፅግና ፓርታን ለመቀላቀል ያለመፈለጉን በመግለጫው  ሥሰማ ፣”ሲጀመር የበለፀገ ቡድን ለምንድነው ገና ወደብልፅግና ከሚጎዝ አዲሥ   ፓርቲ ጋር የሚቀላቀለው? በትግራይ ውሥጥ መሽጎ ፣በትግሪኛ ተናጋሪው ሥም እየነገደ እሥከዕለተ ሞቱ በድሎት መኖር እየቻለሥ ምን ቅብጥ አድርጎት ነው  ህወሃትን በማፍረሥ  መሞቱን የሚያውጀው? ከባለአምሥት ኮኮብ ዘወትሮዊ ኑሮውሥ ፣ለደሃው የትግራይ ህዝብ ብልፅግና ብሎ ለምን ይፋታል???” ነው ያልኩት በምፀት።
    እውነት ነው ፣ሰው ከምቾት ህይወት ይልቅ ተራ ህይወትን አይፈልግም። በሣይንሥ ግን እጅግ የተቀናጣ የምቾት ንሮ አይደገፍም። ሰው በራሱ ላይ ህመምን የሚያመጣው በቅንጦት ብዛት ነው ይላል ሣይንሱ።  ይሁን እንጂ ፣ረብጣ ብር የሚከፍሏቸው ጠባቂዎች ያሏቸው የህወሓት  ንጉሶች የአምሥት ኮከብ ህይወታቸውን እንደዋዛ ማጣት አይፈልጉም።እናም የገዢነት  ዕድሜያቸውን ለማራዘም ዛሬም  የክልሉ ነዋሪ የሆኑትን ፣ ዜጎች ፣በፈጠራ ወሬ   በማሸበር ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ወገኑን እንደጠላት እንዲያይ  ለማድረግ እየጣሩ ነው። ይሁን እንጂ ህዝብ እንደህዝብ ማንንም አይጠላም።ህዝብን ከህዝብ የሚያጣሉት በህዝብ ሥም የራሳቸውን ሀብት ለማካበት የሚፈልጉ ናቸው።
    ትላንት በገዢ መደቦች አማካኝነት፣ የቋንቋ ፓለቲካ በኢትዮጵያ በመሥፈኑ ዜጎች የጎሪጥ እንዲተያዩ መደረጉ አይካድም።ይህንን ያደረጉ እና የተባበሯቸው እኛን በቋንቋ አሣውረው ሀገሪቱን ሙልጭ አርገው በመበዝበዝ ከበርቴ መሆናቸው ሀገር ያወቀው ፣ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው።
      ዘንድሮም  አንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ሌላውን ቋንቋ ተናጋሪ ሊያጠፈ እንደተነሰ ፣ ባላሰለሰ ፕሮፓጋንዳ በማሳመን ህዝብን ከህዝብ ፣”በድብቅ ሴራ” እሳት ውሥጥ ገፍትሮ ለመማገድና እና በነሱ መሥዋዕትነትም “በምላሱ ጤፍ እየቆላ ” የግል ሃብቱንም እያከማቸ ፣የቤተሰቡን ኑሮ፣ እረፍት እና  መዝናኛውን  ውጪ አገር አድርጎ ለመኖር ዛሬም የሚያልም የዋህ የህወሓት ካድሬ  መኖሩ ያሥገርመኛል።ይህ እኮ የራስ ዜጋን በአፓርታይዳዊ አገዛዝ   እየገዙ ሺዓመት ለመንገሥ መጣር ነው።
    የሮዴሺዋ መንግሥት  የአፓርታይድ አገዛዝን በቀለም ልዩነት አገዛዝ ነበር የምናውቀው።በኢትዮጵያ  ደግሞ ለ27 ዓመታት የቋንቋ አፓርታይድ ነግሦ እንደ ነበር  አንዘነጋም።  ዛሬም ሰው ወይም ዜጋ   ከኢትዮጵያዊነት  ይልቅ  በቋንቋው ብቻ መኩራቱን እንዲቀጥል የሚፈልጉ፣ ዜጋና ሀገር እንዲወድምና ኢትዮጵያ ከሶርያ የከፋ ውድቀት ውሥጥ እንደትገባ የሚፈልጉ አሉ።
    ትላንት የነበረው አፓርታይድ መሰል አገዛዝ ዘንድሮ ማክተም ይኖርበታል። ያለፉት ሃያሰባት ዓመታት በቋንቋ ሰዎችን ከመከፋፈል እና ልዩ ጥቅም ከመሥጠት አንፃር፣ በኢትዮጵያ ውሥጥ የአፓርታይድ ሥርዓት ነበር ብይ አምናለሁ። መገለጫውም ዜጎች በክልል አጥር ውሥጥ በአንድ የቋንቋ  የበላይነት እንዲኖሩ መገደዳቸው ነው።ዜጎች   በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ዜጎች በቋንቋ ምክንያት ብቻ፣ በእውቀታቸው ሥራ አያገኙም ነበር። “ሁሉም ዜጎች በሁሉም ክልሎች በእኩል ተወዳድረው ሥራ ሊያገኙ ይገባቸዋል። ” ብሎ ያምናል ይህ ፀሐፊ።
       በአዲስ አበባ መሥተዳደር የወጣውም ” የአምሥትሺ ሥራ አጦች የክፍት ሥራ ማሥታወቂያ” ለአዲሥ አባባ ነዋሪ ብቻ መደረጉ ተገቢ ብቻ ሳይሆን አፓርታይዳዊ ነው ብሎ ያምናል። ይህ ድርጊት በመለሥም በኃይለማርያምም ጊዜ በአዲስ አበባ ከቶም  አልተፈፀመም። …
       ይህ ድርጊት ወንዝ አያሻግረንም እና  ከህዝብ አሥተዳደር ሥራዎች ባሻገር ያሉ  ሙያዊ ሥራዎች ሁሉ ፣በሁሉም ክልሎች ለሁሉም ምሩቃን እና ሙያተኞች  በሙሉ ክፍት የሥራ ማሥታወቂያ ወጥቶ፣ ያለአድሎ እና ጉቦ ኢትዮጵያዊያን ሥራ ፈላጊዎች በሙሉ በመላ ሀገሪቱ በክፍት ሥራ ማሥታወቂያዎች  ተወዳድረው ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ በእውነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደምንኖር እና እኛም ሥልጡን እንደሆንን  ማረጋገጫ ይሆናልና ለሥልጣን የሚፎካከሩ ፓርቲዎች በትምህርት ፓሊሲያቸው ይህንን ጉዳይ እንዲያቀነቅኑ  በመምከር ፅሑፊን እቋጫለሁ  ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔና ይሉኝታ አይተዋወቁም (አንተነህ መርዕድ)
Share