ግርማ በላይ ([email protected])
ማን እንደሆኑ ብትጠይቁኝ “እግዜሩና ባላንጣው ዲያቢሎስ” ብዬ ላልነግራችሁ ለራሴ ቃል አለብኝ፡፡
ምድርን ብቻ ሣይሆን ይህችን ዓለም እስከዝግንትሏ እንዳሻቸው የሚያሽከረክሯት ሁለት ኃይላት አሉ፡፡ በምጡቃን ምሁራን አገላለጽ positive and negative energies ቢባሉ ያስኬዳል፡፡ ተቃራኒ ኃይሎች ናቸው፡፡ በብዙዎች ሃይማኖቶች ደግሞ በዘመነኛ አጠራር “ፈጣሪ” ወይም በተለመደው የኔያዊ ልለው በሚቻለኝ ቅቡል አጠራር “እግዚአብሔር” በሚል በተሰየመውና ሰይጣን ተብሎ በሚጠራው የርሱ ተቃራኒ አፍራሽ ኃይል መካከል የሚካሄደው ግብግብ አሁን አሁን ለይቶለት በትንቢት የሚታወቀውን የመጨረሻውን ቀን የተቃረበ አስመስሎታል – የምን መምሰል – በራችን ላይ ነው እንጂ! መጽሐፉ ስለዚህ መጨረሻ ቀን የሚናገረው ሁሉ አንድም ሳይቀር ተፈጽሟልና የዘመኑ ፍጻሜ ደጃችን ላይ ነው፡፡
እግዚአብሔር የሚተኛ ሆኖ በጊዜ ዕጦት ምክንያት ግን የዕንቅልፍ ሰዓቱ ተዛብቶ የሚቸገር ቢሆን ዋና ተጠያቂዋ ኢትዮጵያ ልትሆን እንደምትችል በበኩሌ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ ይህች አገር ለፈጣሪም ፈተና ሳትሆን አትቀርም፡፡
ሰይጣን በከፊል የመናዊ ወዳጁ በጃዋር መሀመድ አማካይነት የሰውነትን አካለ-መጠን ወስዶ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት – ሊያውም የለውጡ ሞተር የሚባለው የቲም ለማ የአክራሪ ኦሮሞ መንግሥት መሬት ወድቆ ተንበርክኮ ለምኖት መጥቶልን – ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ እየሠራ የሚገኘውን ጀብድ ስንመለከት ዕብደታችንን ለነገ ቆጥበን በመታዘብ ላይ የምንገኝ ዜጎች – ሁሉ ነገር ተዘበራርቆብንና አገራችን ኢትዮጵያ ሲቀርቧትም ሲርቋትም የምታቃጥል ነዲድ እሳት ሆናብን በከፍተኛ አግራሞታዊ ጭንቀት ተውጠን ተቀምጠናል፡፡ የምትደንቅ ሀገር ናት፡፡ ይህ እንግዲህ ዋናው የሰይጣን መገለጫ ነው፡፡ በሌሎች ዓለማት የነበረውንና ያለውን ሥራ ሁሉ እርግፍ አድርጎ ትቶ በነጃዋር በኩል ዲያብሎስ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በነፃነት የሚፈልገውን ሁሉ እያከናወነ እንደሚገኝ መጠራጠር በኑፋቄነት ያስፈርጃል፡፡ በጌታዋ የተማመነች በግ ደግሞ እንኳንስ ላቷን መላ ሰውነቷን ከቤት ውጭ ብታሳድር የሚነካት የለም፡፡ “አቢይ አባቱ ዳኛ፣ ጃዋር ልጁ ቀማኛ” የሆኑባት ኢትዮጵያም ነገረ ሥራዋ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነና ወያኔን ልንናፍቅ አንድ ሐሙስ ብቻ ቀርቶናል – ሊያውም በህግ ጥላ ሥር በነበሩ ምሥኪን ዜጎች ላይ ሶዶማዊነትን ያካሂድ የነበረ የኢሉሚናቲ ልዑክ የሆነውን ወያኔ! ወያኔን የሚያስመሰግን ነገር ይመጣል ብዬ እንኳንስ በውኔ በህልሜም አላሰብኩም ነበር፡፡ ታሪክ ግን ቀልደኛና ግፈኛ ነው፤ መልካም ጦርነት ልጅ ጃዋር!
በሌላ በኩል በስምንት መቶ ብር ደሞዝ የአራት ሽህ ብር ጤፍ እየገዛ፣ በአንድ ሽህ ብር ደሞዝ የሦስት ሽህ ብር አንዲት መናኛ ክፍል ቤት እየተከራዬ፣ በ1200 ብር ደሞዝ ስድስት ልጆቹ “አንዳችም ነገር ሳይጎድልባቸው ‹ዝንጥ› አድርጎ እያስተማረና ለቁም ነገር እያደረሰ”፣ በ1500 ብር ደሞዝ የ90 ብር ዘይትና ከቤቱ መሥሪያ ቤቱ የ1000 ብር የትራንስፖርት ወጪ እየሸፈነ፣ በ500 ብር የጡረታ ገንዘብ ከነአሮጊት ሚስቱ በኪራይ ቤት ውስጥ በየቀኑ ለሚመጣለት አንድ ሊትር ወተት በወር 800 ብር ከፍሎ ተንደላቅቆ እየኖረ፣ በ2500 ብር ወርኃዊ ደሞዙ የ20 ብር ጃምቦ ድራፍት አምስቷን በቀን ጎንጨት እያለ … የሚኖረው ዜጋ ሌላ ሌላው ሁሉ ይቅርና በዚህ የኢኮኖሚ ቀውስ ብቻ በአንድ አዳር ተፋጅቶ አለማለቁ ሲታሰብ በርግጥም ፈጣሪም እንበለው አላህ ወይም እግዚአብሔር ከነሠራዊቱ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አነሁልሎናል ወይም ልባችንን አደንድኖታል ወይም በተዓምር ያኖረናል ማለት እንጂ በጤናማ ኅሊናና አእምሮ ሊታሰብ የሚችል እውነት አይደለም፡፡
ከሕዝቡ ቁጥር 99.9 በመቶው ከአፍ እስካፍንጫችን ማሰብ የማንችል የተማርንም ያልተማርንም ማይማን እንድንሆን ወያኔና አለቆቹ ፈርደውብን ከእንስሳትም ባነሰ የንቃተ ኅሊና ደረጃ በምንገኝበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት፣ 99.99 በመቶው መተዛዘንን ዕርም ብለን እንደ ጅብና ዓሣማ ሆዳችንን ብቻ አስፍተን እርስ በርስ የምንበላላ ሆነን ስናበቃ ፖለቲካውም ሆነ ንግዱ፣ ማኅበራዊ ተራክቦውም ሆነ ሃይማኖታዊ የማስመሰል አስተምህሮውና ስብከቱ ሁሉ ሰው ሰው የማይሸትና ከሞራልም ከባህላዊ ዕሤቶችም ከወግና ልማድም በራቀ መልክ ሙስና ተንሰራፍቶ ሥጋችንን የመቦጫጨቅ ያህል ኅሊናችንን ስተን እየተፋጀን በምንገኝበት ወቅት እግዜር ባይጠብቀን ኖሮ ይህ የበሸቀጠ ማኅበረሰብኣዊ ግንኙነት አንድ ደቂቃም በሕይወት ሊቆይ ባልቻለ ነበር፡፡ ያላወቁን “እየኖሩ ነው” ይሉን ይሆናል፡፡ እኛ ራሳችንም አልገባንም – ሌሎች ታዛቢዎቻችንም አልገባቸውም እንጂ ከሞትን ቆየን – ቀብሩን ግን ዕድሜ ለቄሮ እያቀላጠፈልን ነው፡፡ ለዚህ ያበቁን ሕወሓቶች ግን ልጅ አይውጣላቸው፡፡ ቢሞቱም የገሃነመ እሳት ወራሾች ይሁኑ፡፡ ለነገሩ ከዚያ ውጪ ያላቸው ዕድል በዜሮና በአንድ መቶኛ መካከል የሚዋልል ነው – ፍራቻየ በክፋታቸው ብዛትና መራቀቅ የተነሣ ሰይጣንም ተጠይፏቸው አልቀበልም እንዳይላቸው ነው፡፡ የነዚህኞቹ ገልቱዎች ነገር ግን ያስቀኝም ይዟል፡፡ ወይ አለማፈር! አለመማር እኮ በራሱ ምንም አይደለም፡፡ ሀፍረትን አለማወቅ ነው ትልቁ የሰው ልጅ ጠላት፤ ከጓደኛህ ጠባሳ መማር አለመቻል ነው ዋናው መረገም፡፡ “አታምር ወይ አታፍር” የሚባለውስ ለዚህም አይደል?
ለማንኛውም በተለይ አሁን አሁን በጣም እየገረመኝ መምጣቱን መግለጽ ይኖርብኛል፡፡ ሰኞን ማክሰኞ ሆና ሳያት እጅግ እደነቃለሁ፡፡ በዕብድ ማኅበረሰብ ውስጥ የምኖር እየመሰለኝም መንገዴን ሁሉ – ውዬ መግባቴን ሳይቀር – እጠራጠራለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገሬ ሀገሬ አልመስልህ እያለችኝ መቸገር ከጀመርኩ ቆየሁ (ይታያችሁ – ሥነ ጥበብና ኪነ ጥበብ፣ ትምህርት፣ ቋንቋ፣ ሰብኣዊነት፣ ርህራሄ፣ ብሔራዊና ሀገራዊ ስሜት፣ አመዛዛኝ ኅሊና… ሁሉ ሞተው ወይም በጣር ላይ ሆነው እንዴት ሰው አይጨነቅ? (“ምን መዓት ያወራል” የምትለኝ ልጅ ግን ደህና ነህ? እንዴነህ?))፡፡ … ብቻ አለ አይደል … የሆነ እንግዳ ፍጡር የሆንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ ተወልጄ ያደግሁባት አትመስለኝም፤ አዲስ አበባም ማለትም ፊንፊኔ’ራ 40 ዓመታትን ያህል የኖርኩባት የልጅ ልጆችንም ያየሁባት አልመስልህ ብላኛለች፡፡ ከአስተዳደጌ ያፈነገጡ እጅግ ብዙ ነገሮችን ስለማይ በማንነት ጥያቄ ውስጥ መዳከር የዘወትር ጭንቀቴ ሆኗል፡፡ ይህ የአሁኑ ፖለቲካችንና ብዙኃኑ እኛ ዘይትና ውኃ መሆናችንን ስታዘብ እነዚህ ከሕዝቡ አጠቃላይ ቁጥር 0.09 እንኳን ይሆናሉ ብዬ የማልገምታቸው ግን ኃይልና ገንዘብ እንዲሁም የውጪዎቹ ፀረ – ኢትዮጵያ ኃይላት ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚሰጧቸው ከየትኛውም ጎሣ የወጡ ብልሹና ሆዳም ሰዎች የት ሊያደርሱን እንደሚችሉ በማሰብ እጨነቃለሁ – በጭንቀት ምክንያት ሌሊት ብዙም አልተኛም፤ እውነቴን ነው – ሞትን በሚያስመርጥ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የምገኘው (ፈጣሪን የምትወዱ፣ ፍጡሩንም ትወዳላችሁና በርሱ ይሁንባችሁ ነገን አይ ዘንድ እንድትጸልዩልኝ በዚህች አጋጣሚ ላስቸግር – በእርሱ መንግሥት ትንሽና ትልቅ፣ አንድና ብዙ የለምና አደራችሁን!)፤ ዱሮን የማላውቅ የዘመኑ ወጣት ብሆን ኖሮ ዕድለኛ በሆንኩ – ወይንም እንደነአባጫላና ገመዳ አእምሮየን በዘረኝነት ልክፍት ያሽመደመድኩ ገልቱ ብሆን ኖሮ – ኦ! ይህስ በአፍንጫየ ይውጣ “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድኩ!” ብዬ ልጸጸት ኋላ? (ይቅርታ – የአፍ ወለምታ ነው)፡፡ የሆኖ ሆኖ ዝምታ መጥፎ ነው፤ ፍርሀትም ይሁን ከፍርሀት እምብዝም የማይለይ ትግስት መጥፎ ነው – አሞራን ሊበሏት ሲሉ ስሟን ጅግራ እንዲሉ ዓይነት፡፡ ገደቡን ያለፈ ቸልተኝነት ራስን ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ትውልድንም ሊያሳጣ እንደሚችል የተረዳ ሰው ስለመኖሩ አላውቅም፡፡…. በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሲታይ አቅሉን ስቶ ለገንዘብ ሲራወጥ እንጂ ጤናማ የሰውነት እንቅስቃሴ ሲያምርህ የሚቀር የክት ብርቅ ነገር ሆኗል፡፡ ሰው የሰውነት ባሕርያቱን ሲነጠቅ ምን እንደሚመስል ለመረዳት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፡፡ በሥውር ቦታዎች ሠልጥኖና በጭነት የአይሱዙ መኪናዎች ተጭኖ በአንድ ማዕከላዊ ዕዝ በሚነዳ የሜንጫ መንጋ ንጹሓን ሰዎች በሃይማኖታቸውና በዘራቸው ምክንያት ሕጻን ሽማግሌ ሳይባሉ አንገታቸው እንዴት እንደሚቀላ ለመታዘብ፣ መንግሥትና ሽፍታ በምን መልክ ተስማምተው ሀገርን ምድረ በዳና ቆፈን በቆፈን እንደሚያደርጉ ለመመልከት፣ ሀገርን በሁከት ማመስ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ ሊያደርግ የሚችል ክፍለ ዘመናዊ ዕንቆቅልሽ መሆኑን ለማየት፣ የተማረና ያወቀ ዜጋ ነፍሱን ከወንበዴዎች ጠብቆ ለነገ ለማቆየት እንዴት እንደሚሽቆጠቆጥ ለመገንዘብ፣ ቀን ሰጠን ያሉ የሰይጣን ቁራጮች አእምሯቸውን ተነጥቀው ከእንስሳትም በታች ሆነው እንዴት እንደሚክለፈለፉ ለማየት… አሁኑኑ ወደ ኢትዮጵያ መግባት፡፡ ያኔ ደንግጠህ ወዲያውኑ ትፈተለካህ፡፡ የእኚህ የሼህ ሁሴን ጂብሪል ትንቢት ግን ምነው ብዙ ደጅ አስጠናን? እ…?