በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም (መሳይ መኮንን)

እየሆነ ያለው ልብ ይሰብራል። ውስጥን ይረብሻል። በጽኑ ያሰጋል። ከዋሻዋ ማዳ ጭል ጭል ብላ ትታየን የነበረችው ብርሃን እየደበዘዘች መሆኗ ነገን እንዲያስፈራ ሆኗል። ደመ ነፍስነት አሸንፎኛል። በህወሀት ዘመን ውስጤ ሊገባ ዳር ዳር ሲል የነበረው የምጽአተ ኢትዮጵያ ፍርሃት ዘንድሮ ሁለመናዬን ሲቆጣጠረው ይሰማኛል። ‘’ ኢትዮጵያዬ የቃልኪዳን ሀገር ናት። ጠፋች ሲሏት ከወደቀችበት ተነስታ እንደጸዳል የምታበራ፡ ቀብርናት ብለው ሲፎክሩ በተአምርና በጥበብ ሊቀብሯት ያሰፈሰፉትን ቀብራ ተዝካራቸውን የምትበላ፡ ፈጣሪ አስር ጊዜ ጥሎ አስር ጊዜ ያነሳት፡ ፈሪሃ እግዚያብሄር ባደረባቸው ልጆቿ ትጋት፡ በአበው ጸሎትና ምልጃ በእሳት ተፈትና ወርቅ ሆና በመውጣት ተደጋጋሚ ታሪክ ያስመዘገበች፡ የዜማና ቅኔ ምድር፡ የሰማዕታት መኖሪያ፡ የታላላቅ ነገስታት መናገሻ፡ የኢልማ አባ ገዳ ምድር፡ የኩሽና የሴም ህዝብ የፍቅር ትስስር የተገለጠባት፡ የሁለቱ እምነቶች የመቻቻል ሀገር፡ . . . . . ኢትዮጵያ!’’

ተራ ፉከራ እየሆነብኝ ነው። አፍ ላይ የሚንከባለል፡ ወደ ልብ መዝለቅ አቅቶት ምላስ ላይ የሚንተከትክ ባዶ ሽለላ። አሁንስ ተስፋችን ማን ነው? ከ100ዓመታት በፊት በቀኝ ገዢዎች የተጠነሰሰው የኢትዮጵያ መፈራረስ በራሷ ልጆች እጅ እውን ሊሆን ተቃርቦ ይሆን? የጽንፈኞች ጩኸት ምነው በረከተ? የአዋቂዎች ዝምታና አርምሞ እንዴት ያስፈራል? ሰው ገድሎ የሚፎክር፡ አንገት ቀልቶ የሚሸልል፡ ክብሩን የሰው ልጅ ገላ ተልትሎ አደባባይ ወጥቶ የሚንጎማለል ወጠጤ፡ ጢቦ፡ መንጋ፡ የበዛባት ሀገረ ኢትዮጵያ አሁንስ ተስፋዋ ማን ነው?

በህወሀትና በሻዕቢያ ምርኮኞች የተመሰረተው የትላንቱ ኦህዴድ የዛሬው ኦዲፒ ሀገር የመምራት እድሉን እያጨናገፈ ነው። በጽንፈኞች እስከ አፍንጫው ተይዟል። መሀል አዲስ አበባ ተቀምጦ መንጋውን ለእርድ የሚያሰማራን ጎረምሳ በፍትህ ማስታገስ አቅቶት በየመድረኩና በየአደባባዩ ይለማመጥ፡ ያሽሞነሙን ጀምሯል። የኦሮሞን ህዝብ አይን የወጋ፡ የተቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ የመኖር ህልውና አደጋ ውስጥ የከተተን ጽንፈኛንና መሪውን ‘’ብሌናችን፡ ዓይናችን’’ ዓይነት ነጠላ ዜማ ለቋል። በአንዳንድ የኦዲፒ አመራሮች ሲቀነቀን የነበረው አምልኮተ ጽንፈኛ ተስፋ ባደረግናቸው፡ የለውጥ ሞተር ብለን በምስጋና ባደመቅናቸው መሪዎች ሲደገም አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚሰማ ድንጋጤ ውስጥ ከመግባት ውጪ አማራጭ የለም። ኦዲፒ ጽንፈኞችን መለማመጥ ለምን መረጠ? የጽንፈኞችን ይሁንታ ለማግኘት የስንት ኢትዮጵያዊ ህይወት መቀጠፍ አለበት? ኦዲፒ ሀገር መምራቱን ረስቶ በጽንፈኞች ዜማ ዳንኪራ መምታቱ ከምን ያደርሰው ይሆን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዐብይ አሕመድ የድርድር ተውኔትና የደመቀ መኮንን ሚና - መስፍን አረጋ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦዲፒን ህመም ማስታመሙን መርጠዋል። በፓርላማ የተናገሩትን ሀረር ላይ መቀልበሳቸው የጽንፈኞቹን የጥፋት ግስጋሴ ማስቆም እንዳልቻሉ እየነገሩን ነው በሚል ተርጉሜዋለሁ። የአቶ ለማ የአብረን እነሰራለን ጥሪ ለቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የመርዶ ያህል ክው አድርጎ የሚያስቀር አስደንጋጭ መልዕክት መሆኑ ግልጽ ነው። ለካንስ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ‘’ዓይናችን ነው’’ ፉከራ፡ የአቶ ሽመለስ አብዲሳ ‘’ወንድማችን ከጎንህ ነን’’ መልዕክት፡ የአቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ‘’መወድሰ ጽንፈኛ’’ ንግግር፡ የጭሮ ከተማው ከንቲባ ‘’የምንከተለው እሱን ነው’’ ዲስኩር፡ የየግለሰቦቹ የግል አቋም አልነበረም። ወይም አንዳንድ ነገሮችን በቅንነት ማየት እንደሚመርጡት የዋሆች ‘’የአፍ ወለምታ’’ አይደለም። የኦዲፒ ድርጅታዊ አቋም እንጂ።

ኦዲፒ ከተገደሉት ይልቅ ገዳዮችን እያባበለ ነው። ተበዳዮችን ወደ ጎን ገፍቶ ግፍ ፈጻሚዎችን እየተለማመጠ ነው። አንገታቸው ከተቀሉት ዘንድ ኦዲፒ መሄድ አልፈለገም። መጠጊያ አጥተው በቤተክርስቲያን ከተጠለሉት ይልቅ ካራና ገጀራ ከያዙት ጋ ጉባዔ መቀመጥን መርጧል። የለውጥ መሪዎች ብለን ተስፋ ያደረግንባቸው ሰዎችም የኦዲፒ የሰሞኑ ግርግር አካል መሆናቸውን አረጋገጥንና አንጀት ውስጥ በሚያቃጥል ፍርሃትና ስጋት ገባን። አዎን! ፍትህ አፈር ከድሜ በልታለች። የህግ የበላይነት መቃብር ላይ ህገወጦች ዳንኪራ እየጨፈሩ ነው። ከእንግዲህስ ተስፋችን ማን ነው?

በእርግጥ በኢትዮጵያ ተስፋ አልቆርጥም። በመቃብር አፋፍ ላይም ተስፋ እንዳለ ውስጤ ይነግረኛል። በሞት ጥላ ተይዞ የሚሄድም ስለመኖር ተስፋ ያደርጋልና እኔም በዚህ ድንግዝግዝ ዘመን ስለኢትዮጵያ ተስፋ መቁረጥ አልፈለኩም። ዶ/ር አብይ የገቡበትን ቅርቃር እረዳዋለሁ። የሀረሩ አስደንጋጭ መልዕክታቸው ከልባቸው የወጣ፡ አምነውበት የተናገሩት ነው ብዬ ባላምን እመርጣለሁ። ኢትዮጵያን ለማዳን ፍላጎቱም፡ ቁርጠኝነቱም አላቸው የሚለውና ለወራት አብሮኝ የዘለቀው እምነት አሁንም እንዲከዳኝ አልፈልግም። የመጣውን ቅዝምዝም ጎንበስ ብሎ ለማለፍ በሚል እየጎመዘዛቸው ያደረጉት ነው የሚል አቋም መያዙ ይበጀኛል። ንጉስ ዳዊትም እኮ አትብላ የተባለውን እንጀራ የቀመሰው ወዶ አልነበረም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመደራጀት መብት ግዴትም አለበት (ይገረም አለሙ)

አዎን! ሊነጋ ሲል ይጨልማል። በአስፈሪ ነጎድጓዳማ ሌሊት ሲጥ ተደርጋ በተያዘችው ኢትዮጵያ መንጋቱ አይቀርም። በዚህ አስጨናቂ፡ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኜም ስለኢትዮጵያ መልካም ነገር አስባለሁ። ኢትዮጵያ ትድናለች!

4 Comments

  1. ኣንተም አንደ ኣቢይ ኣህመድ ህዝቡን አያዘናጋህ መሆኑ የገባህ ኣትመስልም ፥ አባክህ በዚህ ፕሮፖጋንዳህ ኣሁንም ህዝብን ኣታዘናጋ የአስካሁኑ ይበቃሃል

  2. ተስፋህ እንደ ወሸላህ እንደተንጠለጠለ ትሞታታለህ እንጅ የነፍጠኛ አባቶችህ ኢትዮጵያ ተመልሳ አትመጣም። እንዳልነበረች ሁናልሃለች።

  3. መሳይ፤ አናፋህ አናፋህና ኤርትራ ስትሄድ ዝም አልክ። ግድ የለህም መሳይ፤ ኦሮምያ ሲሄድም ትለምደዋለህ። ቸሩ እግዚአብሔር ላንተና ካንተ ጋር ለሚያላዝኑት (ሙሾ ለሚያወርዱት) ሲሳይና ወንድማገኝ ብርታቱን ይስጣችሁ።

    በነገራችን ላይ፤ ወንድማገኝ ኦሮሞ ጋ የመጣዉና የጨቆነዉ ነፍጠኛ የአለቃ ተክለወልድ ነፍጠኞች አይደሉም።

    ወያኔን የመሣሪያ ብዛት አያድነዉም ብሎ ሲፎክር የነበረዉ ጄኔራል ሲሳይ አገና ዛሬ ደግሞ መሣሪያ ስላለዉ የአብይን መንግሥት ማንም አይገልብጥዉም ይላል፤ እናቱ ትገልበጥና። እነኝህ እሳቶች ምንም ሳያዉቁ እናዉቃለን እያሉ የኢትዮጵያን ችግር እያባባሱ ነዉ።

Comments are closed.

Share