አልበዛም ወይ መፋዘዙ???
****************************
የአማራ ክልልን የሚያስተዳድረው ብአዴን/አዴፓ የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በሚፈልገው ግራ ቀኝ የማየት ነገር ላይ የሚቀረው ብዙ ነው።ፓርቲው የህወሃት የስነ-ልቦና ማኮላሻ ለበቅ ያልገረፈው፣ከራስ መተማመኑ ያልተፋታ፣ወቅቱ የሚፈልገውን አይነት ሃሞተ ኮስታራ አመራር ማስገባት ግድ ይለዋል። ይህ የሆነ አልመሰለኝም።
የስልጣን ጥም ብቻ ህዝብን ታዳጊ መሪ አያደርግም። በአዴኖች ክልሉን የመምራቱን ስራ በትርፍ ጊዜው እንደሚሰራ ሰው ከልባቸው የያዙት አይመስልም፣ክልሉ ያንዣበበበትን አደጋ በሚመጥን መንገድም ዝግጁነት ያንሳቸዋል።ከልባቸው የሚሰሩበት የስልጣን ሽኩቻውን፣በዘር ተቧድኖ መራኮቱን ነው።
በቅማንት ስም የሚደረገው የህወሃት ረዥም እጅ ማጠር ያልቻለው በከፊል በብአዴን ፍዝ አካሄድ ነው።ክፉ ሰዎች የሚመሩት ጎረቤት ይዞ አጥርን ማጠባበቅ ግድ ነው።ስለማይጠቅም እንጅ ለእጅ አዙር ጦርነቱም ቢሆን እዛም ቤት እሳት እንዳለበት ኮስተር ብሎ ማሳወቅ ደግ ነው።ይሉኝታ ቢስን አካል ለመገዳደር አንዳንዴ ይሉኝታ መጣልም ያስፈልጋል።
ብአዴን በሰሞኑ መግለጫው ኮስተር ለማለት ቢሞክርም በበኩሌ ያልተመቹኝ ነገሮች አሉ። በመግለጫው ውስጥ የሰሞኑን ደም መፋሰስ ያመጡት “የአሮጌ ዘመን ቁማርተኞች”
፣”የሁከት ነጋዴዎች፣”የጥፋት ሃይሎች”፣ “የአሮጌው ዘመን ቆሞ ቀሮች”፣”የህዝባችንን ደም ሲመጡና የነበሩ መዥገሮች” ናቸው የሚሉ ሾላ በድፍን የሆኑ፤ ለችግሩ መፍትሄ በማምጣት ረገድም መዋጮ የሌላቸው ሃሳቦችና ተጠቅሰዋል።
ይህ ባለጋራን በስሙ ለመጥራት የሚያሽኮረምም የበአዴን ህመም መነሻው ሃያ ሰባት አመት በህወሃት ቤት በባርነት የቆየበት ሀንጎበር ነው። ህወሃት እንደ በአዴን ስነልቦናውን የሰለበው ፓርቲ የለም።ክፋቱ የራሱ መሰለብ ሳይሆን የሚወክለውንም ህዝብ ብአዴን በሚመዘንበት ቀሊል ሚዛን ማስመዘኑ ነው። ህወሃት ብአዴንን በሚያይበት ንቀት ነው የሚያስተዳድረውን የአማራ ህዝብም የሚያየው።
ብአዴን ከላይ የጠቀስኳቸውን ሾላ በድፍን የሆኑ አነጋገሮችን ሲጠቀም ማንን እየተናገረ እንደሆነ ግልፅ ነው።ሆኖም ይህን ሊያስብለው የቻለው መረጃ ካለው ግልጥልጥ አድርጎ ማውጣት እና ጥፋተኛንም በስሙ ጠርቶ በስራው እንዲያፍር ማድረግ ያስፈልጋል።ይህ ብቻ ግን አይበቃም። ተግባር ያስፈልጋል! ብአዴን በተግባር የክልሉን ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ ተመዞ የማያልቅ መዘዝ ይመጣል።
እኔን የሚያሰጋኝ ነገር ቋጠሮ ያለው እዚህ ላይ ነው።ህወሃት ብአዴንን በሚያይበት የንቀት አይኑ የአማራን ህዝብም ያያል።ስለዚህ ድሽቃ አስታጥቆ ገዳይ ይልካል።ይህ የተደጋገመበት ህዝብ ደግሞ ከሞት የሚያድነኝ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስት ስለሌለ ራሴ በራሴ ልወጣው ብሎ ተቧድኖ የመልስ ምት የጀመረ ዕለት ለሁለቱ ክልሎች ቀርቶ ለሃገር የሚተርፍ እሳት ከሰሜን ሊነሳ ይችላል።
ስለዚህ የፌደራሉ እና የአማራ ክልል መንግስት የነገሩን አደገኝነት ተረድተው የክልሉን ህዝብ ሊቆጣጠሩት በሚችሉበት የክልል ልዩ ሃይል እና የመከላከያ ሰራዊት ጣምራ ጦር መጠበቅ አለባቸው።ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህዝቡ ራሱን ለማዳን ከተነሳ ጠመንጃውን የሚያዞረው ሊገድለው በመጣው ቅጥር ባለድሽቃ ገዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ተሸክሞት በኖረው አይረቤው ብአዴን ላይም ነው። ብአዴን እና የፌደራል መንግስት የአማራ ክልልን ፀጥታ ማስጠበቅ ባልቻሉ ቁጥር ህዝቡን ወደዚህ አደገኛ አማራጭ አየገፉት እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል።
ይህ ደግሞ ለሁሉም አደጋ ነው። መንግስት የአማራ ክልል ጉዳይ በማይቆጣጠረው ሃገሬ ታጣቂ እጅ ከመግባቱ በፊት ተው ሲለው በሚመለስ ፣በሚቆጣጠረው የመከላከያ ሃይል ክልሉን በተጠንቀቅ ቢያስጠብቅ ጥሩ ይመስለኛል።
የአማራ ክልልን ጉዳይ ለማራገብ ሲሆን ብቻ ከዘራቸው ውጭ ሰው እንዳለ ትዝ የሚላቸው እንደ ኦሮሞ ብሄርተኞች ከነ ሚዲያቸው እና ፕ/ሮበየነ ጴጥሮስ አይነት አጓጉል ቼ ጉቬራዎች ደግሞ ከዚህ ምን ሊያገኙ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ውስጥ እንደገቡ አይገባኝም – ያው የአማራ ጥላቻቸውን ተንፈስ ከማድረግ ውጭ። የጥላቻን እሳት፣ የዝቅተኝነትን ህመም ተንፈስ ለማድረግም ደግሞ ሌላ መለስተኛ መንገድ መፈለግ እንጅ ሃገር የሚያናውጥ ነገር መነካካት ጥሩ አይሆንም።