በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ/ም
ዓለማችን በቴክኖሎጂ ጥበብ እጅግ እየተራቀቀች ቢሆንም ፖለቲካን (የሕዝብ አስተዳደርን) በተመለከተ ግን እጅግ ወደ ኋላ እየሄደች ትገኛለች። ለዚህም ብዙ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል። ይሁን እንጂ አሁን ለተነሳንበት ርዕስ፤ አንኳር አንኳር ከሆኑት ጥቂቶችን ብቻ መጥቀስ በቂ እንደሚሆን እንገምታለን። በጣም የሚደንቀው ነገር ግን በዓለም ብዙ የታወቁ ዩኒቨርስቲዎችና ፕሮፌሰሮች እንዲሁም ፈላስፎች ቢኖሩም፤ ለሰው ልጅ የሚመጥን ፍትሀዊ የአስተዳደር ቀመር ግን ሊያቀርቡ አልቻሉም። ከዚህም የተነሳ በተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና ያገኙት 193 ሉዓላዊ አገሮች ሁሉም የየራሳቸውን ሕገ መንግሥት በማዘጋጀት እየተመሩበት ይገኛሉ። ይህም ዓለማችንን የአስተዳደር ላቦራቶሪ ማዕከል አድርጓታል። ለምን እንደዚህ ሆነ ብለን ስንጠይቅ እያንዳንዱ ሀገር 100% ጠንካራና ቁርጠኛ መሪ የማግኘት ዕድል አልገጠመውም ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል። በእርግጥ ዓለማችን ለሕዝብ የቆሙ ሰዎችን አላገኘችም ለማለት የሚያስደፍር ምክንያት ግን የለም።
እንዲህ እንድንል የሚያደርጉን የተለየያዩ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። ዶ/ር ካርል ማርክስ ከደህና ቤተሰብ ቢወለድም፤ አባቱ እንዴት ሀብታም ሊሆን እንደቻለና የትርፉን ምንጭ ሲያጠና፤ አባቱ ቱጃር ለመሆን የበቃው በሥሩ ላሉ ሠራተኞች ማግኘት ከሚገባቸው በታች ደመወዝ እየከፈለ እንደሆነ ደረሰበት። በሕግና በፍልስፍና የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዳገኘ በጋዜጠኝነት ሙያ ሥራ ጀመረ። ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም ግኝቱን በጋዜጣው ላይ ማስረዳት በሚጀምርበት ወቅት የፋብሪካ ባለሀብቶች በመተባበር ሊገድሉት ይፈልጉት ጀመር። ከዚያም ይኖርበት ከነበረው ጀርመን ሸሽቶ ወደ ፓሪስ ፈረንሳይ ተሰደደ። እዚያም በዚሁ አቋሙ በመጽናት የተለያዩ ጽሑፎችን በመሔቶችና በጋዜጦች በመጻፍ፤ ሠራተኞች ኑሯቸው ሊሻሻል ያልቻለው በአሰሪዎቻቸው በሚከፈላቸው ዝቅተኛ ደመወዝ እየተበዘበዙ መሆኑን ማስረዳት ቀጠለ። እዚያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዋቂ እየሆነ በመምጣቱ እነዚሁ የፋብሪካ ባለቤቶች ድራሹን ለማጥፋት ከፍተኛ ክትትል ያደርጉበት ጀመር። ከዚያም ሸሽቶ ወደ ብራሰልስ ቤልጂየም በመሔድ ከጓደኛው ከፍሬደሪክ ኤንግልስ ጋር በመሆን የኮሚኒስት ማንፌስቶ የተባለውን መመሪያ ጻፈ።
ዶ/ር ካርል ማርክስ አሁንም ለሕይወቱ ስለሰጋ እንደገና ሸሽቶ ወደ እንግሊዝ ተጓዘ። በእንግሊዝም የእሱ አድናቂና ጓደኛው የሆነው ፍሬደሪክ ኢንግልስ የአባቱን የጨርቅ ንግድ ኩባንያ ወኪል ሆኖ በዚያ ይኖር ስለነበር ለሕይወቱ አስጊ ባይሆንም ነገር ግን ‘አደገኛ ሰው’ በሚል በየትኛውም ኩባንያ ሥራ እንዳይሠራ እገዳ ተጣለበት። ከዚህም የተነሳ የዚህ ዓቢይ አስተሳሰብ ባለፀጋ የሆነው ታላቅ ሰው ሕይወቱ ግን በከፋ ድኅነት የታጀበ ነበር። ስለሆነም ኑሮው የሚደጎመው ወዳጁና የዓላማ አጋሩ የሆነው ፍሬደሪግ ኢንግልስ በሚሰጠው ድጋፍ እንደነበር ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲ በመግባትና በሎንደን የሚገኙ ቤተ መጻሕፍትን በማሰስ የዓለምን የአስተዳደር ታሪክ በማጥናትና የሕዝብን ፍላጎት በመመርመር የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪውን ወስዷል። ከዚያም በሎንዶን በሚኖርባት እጅግ በጣም ጠባብ ቤት የተለያዩ መጻሕፍትን በመጻፍና የተወሰኑ ሰዎችን በፈረቃ እየተቀበለ በከፍተኛ ምስጢር የደረሰበትን የአስተዳደር ጥበብና ጥልቅ ምስጢር ሲያስተምር ቆይቶ እንደ አንድ ተራ ሰው በማርች 24 ቀን 1883 ዓ/ም ሕይወቱ አልፏል።
የሕንዱ ማኅተመ ጋንዲም እንዲሁ የሕግ ትምህርት የተማሩ ሲሆን ስለ ሰው ልጅ እኩልነት ታላቅ ክብርና ቦታ የሚሰጡ ሰው ነበሩ። ነገር ግን በሥራ ምክንያት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው ሳለ እንግሊዞች በጥቁሮች ላይ ያደርሱት የነበረውን የዘር መድሎና ግፍ ማየት ስለሰለቻቸው ወደ ሕንድ ተመልሰው ሕዝብን ማስተማርና መቀስቀስ ጀመሩ። እንግሊዞች ‘ልናሰለጥናችሁ ነው የመጣን’ በማለት ያፌዙ ስለነበር፤ ‘ማንኛውንም ነገር እራሳችን በራሳችን ማድረግ ይኖርብናል፤ የውጭ እርዳታም ሆነ የፋብሪካ ውጤት አያስፈልገንም፤ ብቻ አገራችንን ለቃችሁ ውጡ!’ በማለት ለብዙ ዓመታት ሲታገሉ ቆይተዋል። በዚሁም በትግል ወቅት መሸመን ተምረው የሚለብሱትን ጨርቅ እራሳስቸው ይሠሩ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል።
በማኅተመ ጋንዲ ሲመራ የነበረው የሕዝብ አመጽ ፍጹም ሰላማዊ ነበር። እርሳቸውም ከወረቀትና ከእስክሪቢቶ ውጭ አይዙም ነበር። በኋላም አመጹ ቀስ በቀስ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ መላዋን ሕንድ በማዳረሱ ከእንግሊዞች ቁጥጥር ውጭ እየሆነ መጣ።
ስለሆነም እንግሊዝ በ ‘ከፋፍለህ ግዛ’ መርህ መሠረት ሕንድን ለማዳከም ሲባል ሰሜኑን የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑትን ፓኪስታን፤ ደቡቡን የሒንዱ ሃይማኖት ተከታዮችን ኢንድያ፤ ምሥራቁን ባንግላዲሽ፤ የሲሎንን ደሴት ሲሪላንካ በማለት አዳዲስ ትናንሽ አገሮችን ፈጠሩ። በሕንድና በፓኪስታን መካከል የእስልምና እና የሒንዱ ሃይማኖት ተከታዮች የሚኖሩበትን ቦታ ካሽሚር በማለት ሲሰይሙ፤ ለወድፊቱ የቁርሾ ምክንያት ይሆን ዘንድ በማሰብ፤ የታወቀ ድንበር ሳያካልሉ ተውት።
ቀጥሎም ሕንድ አሁንም ታላቅ አገር ስለሆነችባቸው እንደገና ወደ ሦስት አገር ማለትም ፑንጃብ፤ አንድራ ፕራዲሽ፤ እና ማድራስ በማለት ሊሸነሽኗት ዕቅድ ነበራቸው። ነገር ግን ትግሉ እጅግ እያየለ ስለመጣና ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ሳይወዱ በግድ ሕንድን ለቀው ለመውጣት ተገደዱ። ሕንድም ጁን 15 ቀን 1947 ዓ/ም ነፃነትዋን አወጀች። ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ አገሩን ነፃ ያወጣውን ማኅተመ ጋንዲ፤ናተራም ጎደሴ የተባለ አንድ ሕንዳዊ በአደባባይ ተኩሶ ገድሎታል።
በተጨማሪም 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆን ኦፍ ኬነዲ የተባለው ጎልማሳ፤ የአሜሪካንን የሥልጣኔ ደረጃ ከሌላው ዓለም ጋር በማነፃፀር፤ በተለይ የአፍሪካን እና የእስያን ሀገሮች ኋላ ቀርነት በመገንዘብ ‘እነርሱንም የመርዳት ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን፤ አሜሪካ ብቻዋን ተለይታ መጥቃ መሄዷ አግባብ አይሆንም፤ እኛም የደረስንበትን የሥልጣኔ ደረጃ ለእነዚህ ሀገሮች ማካፈል ይገባናል’ የሚል ታላቅ ራዕይ ሰንቆ ተነሳ።
ይህንንም ዕቅድ ለማሳካት ‘የሰላም ጓድ’ የተባለውን ድርጅት በማቋቋም የአሜሪካ ወጣቶች የሁለት ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማበርከት በዓባልነት እንዲመዘገቡ ጠየቀ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣት አሜሪካውያን ዓላማውን በመደገፍ ተቀላቀሉ። ከዚያም በዓለም ዙሪያ በአሉ የታዳጊ አገሮች ዘመቱ። እጅግ በጣም የሚገርም አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ጨምሮ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ነገር ግን እንዲህ ያለ ዓለምን ወደ ተሻለ ሥልጣኔ ለማሳደግ የሚያስችል ግዙፍ አስተሳሰብ ወደ ተግባር የለወጠን ታላቅ መሪ፤ እኩይ አስተሳሰብ በአላቸው ሰዎች ሴራ በጠራራ ፀሐይ፤ በኖቬምበር 22 ቀን 1963 ዓ/ም ሊ ሐርቬ ኦስዋልድ በተባለ አልሞ ተኳሽ በጥይት ተመቶ ተገደለ።
ከላይ የተጠቀሱትን ጥቂት ምሳሌዎች መነሻ በማድረግ ለምን እንዲህ ሆነ ብለን ሁኔታዎችን ስንመረምር ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነጥቦች ከሞላ ጎደል እንደ ዋነኛ ምክንያት ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ሀ) የበታችነት ስሜት፤ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ‘እግዚአብሔር ይማርህ!’ የማይባል ርቂቅ በሽታ ነው። የበታችነት ስሜት ያለበት ሰው እጅግ በጣም ፈሪና ተጠራጣሪ ስለሆነ ከሰዎች እኩል ወይም ደግሞ የተሻለ መስሎ ለመታየት ከተግባር ይልቅ ውዳሴ ከንቱን ይወዳል። በራስ መተማመን የሚታይባቸውን ሰዎች በአካባቢው እንዳይኖሩ ያርቃቸዋል። የመታወቅ አዝማሚያ ያላቸውን ደግሞ የበታችነቱ ቅናት ስለሚመዘምዘው የተለያዩ ሰንካላ ምክንያትን እየፈለገ ከሥራ ያግዳቸዋል፤ያሳስራቸዋል ወይም እስከነአካቴው ድራሻቸውን ያጠፋቸዋል። የበታችነት ስሜት ያለው ሰው በአጋጣሚ ወደ አገር መሪነት ሥልጣን ከመጣ ያች አገር ወዮላት።
እጅግ ለተዘበራረቀ የፖለቲካ፤ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቀውስ ትዳረጋለች። የፖለቲካው ሥልጣን በችሎታ ሳይሆን በጓደኛና በቤተሰብ፤ በአምቻና በጋብቻ እየተሰላ ይታደላል። ኢኮኖሚን በተመለከተ የንግድ ፈቃድና ተያያዥ ጉዳዮችም እንዲሁ በአወቅሁሽና በተወለድኩሽ ስለሚያዝ ሚዛናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት አይኖርም። በማኅበራዊውም መስክ እንዲሁ ነው። ፍትሐዊ የሆነ የፍርድ ሂደት አይኖርም፤ ይልቁንም በግልጽ የሚታይ አድልኦ እስከመፈጸም ይደረሳል።
ለ) ግለኝነት (ስግብግብነት)፤ ይህንን በተመለከተ ለእኛ ከማለት ይልቅ ለእኔ የሚለው ጎልቶ ስለሚወጣ ሠፊው ሕዝብ ለከፋ ምዝበራ፤ ችግርና እንግልት ይዳረጋል። በሥልጣን ዙሪያ ያሉት ቡድኖች ሕዝብን ከማገልገል በፊት የራሳቸውን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው ስለሚሠሩ የአገር ዕድገትና የሕዝብ የኑሮ ደረጃ፤ በመሻሻል ፋንታ እየባሰበትና እየተጎሳቆለ ይሔዳል። ግለኝነት፤ የአንድ ወቅት የአስተዳደር ችግር ብቻ ሆኖ አይቀርም። እንዲያውም ለቀጣዩ ትውልድ መጥፎ ባህልና የኑሮ ዘይቤ ተክሎ ያልፋል።
ሐ) ሥልጣን፤ ድንገት እንደ ሎተሪ የሚገኝ አጋጣሚ ነው። የእኛን ታሪክ ማየቱ ብቻ ይበቃል። ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ያለውን እንኳ ብንመለከት ልንረዳው እንችላለን። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዙፋናቸውን፤ በእቅፋቸው ላሳደጉትና በጣም አስተዋይና ብልህ ለነበረው የልጅ ልጃቸው ለልጅ ኢያሱ አውርሰው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ይሁን እንጂ በእንግሊዞች ሴራና የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ጎትጓችነትና እንዲሁም ሴራውን ባልተረዱ የሀገራችን ባለሥልጣናት ተከታይነት፤ በተደረገ ፀረ ልጅ ኢያሱ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሥልጣኑ በድንገት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ሲተላለፍ (መካን ስለነበሩ)፤ ደጃዝማች ተፈሪ መኰንን በዓልጋ ወራሽነት ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ እንዲይዙ ተደረገ። ቀጥሎም ሚያዝያ 23 ቀን 1921 ዓ/ም ንጉሥ ተፈሪ መኮንን ተባሉ። ንግሥቲቱ እንዳረፉም ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ/ም ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ተቀቡ።
ከዚያም በ1966 ዓ/ም በተቀሰቀሰው አገር አቀፍ አብዮት ወቅት፤ የነበረውን የሕዝብ አለመረጋጋት ተመልክተው ሀገር እንዳትፈርስ በማሰብ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ባስተላለፉት የመለዮ ለባሹ ተወካዮች ጥሪ መሠረት፤ የሦስተኛ ክፍለ ጦርን ወክለው የተገኙት ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በደርግ ሊቀ መንበርነት እንዲሠሩ በመመረጣቸው፤ ቀስ በቀስ ሥልጣኑን ጠቅልለው በመያዝ ከ1967 ዓ/ም ጀምሮ የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን በቅተዋል። የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመንም ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ/ም ባከተመ ጊዜ፤ አላወቁበትም እንጂ ጄኔራል ተስፋየ ገ/ኪዳን እስከ ግንቦት 20 1983 ዓ/ም ድረስ፤ ለአንድ ሳምንትም ቢሆን የመሪነቱ ዕድል አጋጥሟቸው ነበር።
የተገንጣይ አስገንጣይ ቅጥረኛ ቡድን መሪ የነበሩት መለስ ዜናዊም፤ የበታችነት ስሜት ከተጠናወተው፤ በተንኮል፤ በዘረፋና በዘረኝነት ከታጀበው ከነሙሉ ሰይጣናዊ አስተሳሰባቸው ጋር ሳያስቡት ወደ ሥልጣን መውጣታቸው አይዘነጋም። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሪዚዳንት፤ ቀጥሎም ሕገ መንግሥቱን በመለወጥ ሥልጣኑን በሙሉ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር በማዛወር፤ በፈጣሪ ቁጣ በድንገት ለሕልፈት እስከ ተዳረጉበት እስከ ነሐሴ 2004 ዓ/ም ድረስ ኢትዮጵያን በደም አበላ እያጠቡ፤ ሕዝብን በሰው ሰራሽ ረሃብ፤ እሥራት፤ ግርፋትና ስደት ሲያሰቃዩና ሲያስመርሩ መቆየታቸው አይረሳም።
የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ድንገትኛ ሞት በፈጠረው የሥልጣን ክፍተትና፤ ሊተካቸው የሚችል ቀድሞ የተዘጋጀ ሰው ካለመኖሩ የተነሳ፤ ለፖለቲካ ሽፋን ሲባል ብቻ በም/ጠቅላይ ሚንስትርነት ማዕረግ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት፤ ደካማውና ላንቲካው ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚገርም ሁኔታ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን በቅተዋል። በሥልጣን ዘመናቸው ግን እዚህ ግባ የሚባል ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም እንድ ጉዳይ ሳይሰሩ፤ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ብቻ ሳይሆን በብድር ያገኘችውን ገንዘብ ሁሉ፤ ጃርት እንደበላው ዱባ ሲያስመዘብሩ ቆይተው ከሥልጠን መልቀቃቸው ይታወሳል።
በየጊዜው በተፈጠረባቸው ከአቅም በላይ የሆነ ጫና፤ ወከባ እና አገሪቱን አማክሎ ማስተዳደር አለመቻል፤ የተነሳ ከኃላፊነት እንዲለቁ ሲገደዱ፤ በሚመሩት የኢሕአዴግ ድርጅት ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻና ውድድር ተከሰተ። ይህንን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት አራቱም እህት ድርጅቶች የየራሳቸውን ሰው ለውድድር አቀረቡ።
እንደሚታወቀው ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሠቃየ፤ ያስመረረና የዘረፈ ከመሆኑም በላይ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የአገሪቱን የአብሮ መኖር እሴት፤ ሲገዘግዝና ሕዝብን ከሕዝብ በመለያየት ሲያጋጭ የቆየ በመሆኑ፤ ከሕወሃት የሚወከለው ሰው እንደማይመረጥ ይታወቅ ስለነበር፤ ወያኔ ከደቡብ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ለቀረብው ሽፈራው ሽጉጤ ድምጽ ለመስጠት ወስኖ ወደ ስብሰባ መግባቱ አይዘነጋም።
ነገር ግን ሴራው የገባቸው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የክልል ሦስቱ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደግሞ፤ ቀደም ሲል በአደረጉት ስምምነት መሠረት፤ በአለቀ ሰዓት የአማራው ዕጩ አቶ ደመቀ መኮንን እራቸውን ከምርጫ በማግለል ድምፁን ለኦሮሞው ዕጩ ዶክተር ዓቢይ በመስጠታቸው ወያኔ ያልጠበቀው ዱብ ዕዳ ሽንፈት አጋጠመው።
በዚህም መሠረት ሳይታሰብና ሳይታለም በሕዝብ ዘንድ ምንም ዓይነት ዕውቅና ያልነበራቸው ወጣቱ ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ በአንድ ጊዜ ተወንጭፈው ወደ ከፍተኛው የሥልጣን ጣራ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን መንበር ተፈናጠጡ። ከዚህ የምንረዳው ሥልጣን ስለፈለጓት ብቻ ሳይሆን በሆነ አጋጣሚ እንደሎተሪ ዕጣ የሚረከቡት የሕዝብ ኃላፊነት መሆኑን ነው።
ለዚህ ዓይነት ሥልጣን የተቀቡት ብልሆችና አስተዋይ ሰዎች፤ እንደ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ሕዝብ የማስተዳደር ጥበብ እንዲሰጣቸው ፈጣሪያቸውን እየለመኑ፤ እንቅስቃሴያቸውንና ውሳኔያቸውን ሁሉ በጥሞና እየመረመሩ ይወስናሉ። ለሕዝባቸው ይራራሉ ፈጣሪያቸውንም ይፈራሉ፤ ለስማቸውም ይጨነቃሉ። ምክንያቱም ታሪካቸው እስከወዲያኛው ስለሚጻፍ በክፉ እንዳይነሱ በበጎ ተግባር ላይ ብቻ ይጠመዳሉ።
አስተዋይና ብልህ ካልሆኑ ግን በዘር፤ በአምቻ በጋብቻ፤ በአወቅሁሽ በጠቀምኩሽ፤ ሙስና ይተበተቡና የሥልጣን መባለግ ይፈጽማሉ። በዚህ ጊዜ ሕዝብ ይበደላል፤ፍርድ ይጓደላል፡ ፈጣሪ አምላክም ይቀየማል። ለጊዜው ቢመስልም ቀስ በቀስ ግን የመንግሥታቸው መዋቅር፤ ላይ ላዩ ያለ ቢመስልም ውስጥ ውስጡን ምስጥ እንደበላው እንጨት ሲቦረቦር ይቆይና አወዳደቃቸው አይምርም።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን በኢትዮጵያ በገሐድ እየታየ ያለው ይህንን መሰል አካሄድ ነው። ዶ/ር ዓቢይ ብዙ የተሳሳቱት ነገር አለ። ይሁን እንጂ እንደ እርሳቸው ስህተት የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከዛሬ ነገ ያርማሉ በማለት ቸኩሎ ፊቱን አላዞረባቸውም። ይህም ታላቅ ፀጋ ነበር፤ ነገር ግን በቸልተኝነትም ይሁን በአማካሪ ሸፍጥ የእትዮጵያን ሕዝብ ከቀን ወደ ቀን የበለጠ እንዲቆጣና እንዲርቃቸው የሚያደርግ ተግባር እየተሠራ መሆኑን ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው።
ሕዝብ ማፈናቀል፤ አለአግባብ መታወቂያ ማደል፤የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ማገድ፤ዘር ተኮር የሆነ ንጹሐንን አስሮ የማንገላታት፤ለሕዝብ ድምፅና አቤቱታ ጆሮ አለመስጠት፤ የጴንጤ ሃይማኖት ተከታዮች መረን በለቀቀ መልኩ ሕዝብን ሲያወናብዱ ችላ ማለት፡ በአንፃሩም የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሲዘረፉና ሲቃጠሉ ‘ዓይኔን ግንባር ያድርገው፤ የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ!’ ማለት ጥቂቶቹ ናቸው።
የሹመቱ ጉዳይማ ሕዝብ ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ነው። ዓይኑን ያፈጠጠ ጥርሱን ያገጠጠ ሆኗል። በችሎታና በልምድ ሳይሆን በዘር ሐረግና በደም ጥራት መለኪያነት እየተሠራ በመሆኑ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እየተሞላ ሲሆን ሌሎች ግን እየተገፉ መሆኑ በሠፊው ይነገራል። ይህ ሁሉ ስህተት እየተሠራ ሕዝብ ግን ዶ/ር ዓቢይ ‘በመጥፎ ሰዎች ተከበዋል እንጂ የእርሳቸው ሥራ አይደለም’ በማለት እርስ በእርሱ ይከራከርላቸዋል።
እሺ ይህንን የሕዝብ አመኔታ እንደጠንካራ ጎን እንውሰደው። ታዲያ ጃዋር መሐመድ፤ ፕሮፌሰር ተብየው ሕዝቄል ገቢሣ፤ በቀለ ገርባ እና ሌንጮ ለታ የተባሉ እበላ ባይ ቡድኖች፤ የዶ/ር ዓቢይን መንግሥት ለማጠናከር ማሳጅ እያደረጉ እንዳልሆነ ሕዝብ በገርምት ይታዘባል። እነዚህ ሰዎች ከሚገባቸው መብት በላይ ቀይ መስመር አልፈው ሄደዋል፤ ነገር ግን በቃ ያላቸው ደፋር ባለመኖሩ አሁንም ሕዝብን የማተራመስ፤መንግሥትን የማራከስና አገር የማፍረስ ተግባር ላይ ተጠምደው ሌት ተቀን በትጋት በመሥራት ላይ ናቸው።
ቀድም ሲል በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የጠፋው ሕይወትና የወደመው የሕዝብ ሀብት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ‘በዕንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ’ እንዲሉ በዚያን ጊዜ ዝም ስለተባሉ አሁን ደግሞ ለሁለት ሺህ ዓመታት የቆየችውን፤ በዓለም ከፍተኛውን የኦርቶዶክስ ምዕመን ቁጥር የምታስተዳድረው፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ የተሄደበትን እርቀት ማየት ብቻ በቂ ነው። ‘ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ!’ እንዲሉ ጉዳዩ ገና በሀሳብ ደረጃ ሳለ በእንጭጩ ማምከን ሲቻል፤ አብጦ አብጦ ከፈነዳ በኋላ መድኃኒት ፍለጋ መሯሯጡ ብልህነት ሊሆን አይችልም።
በተለይ የማዕከላዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እውነት የዶ/ር ዓቢይን መንግሥት መጠበቅ ይችላሉ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ‘የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም’ የሚል ይሆናል። አንድም ከፍተኛ ድክመት አለባቸው፤ ወይንም በሌላ ኃይል ተሸብልለዋል። ለዚህ ደግሞ ሕወሃት የተካነበት ስለሆነ መጠርጠሩ ተገቢ ይሆናል። ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ቢያንስ ዓላማቸው ምን እንደሆነ በአስቸኳይ ቃላቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ተገቢ ነው እንላለን። ካልሆነ ግን ድቡልቡሏ ኳስ ‘ሥልጣን’ መቼ፤ወደ የት፤እና ወደ ማን እንደምትወነጨፍ የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው።
መ) ፍርሃት፤ የበታችነት ስሜት አንዱ መገለጫ ነው። ፍርሃት ተፈጥሯዊ ስለሆነ በምክንያት ከሆነ ትክክልና ተገቢ ነው። ያለምክንያት ከሆነ ግን የአእምሮ ቀውስን ያስከትላል። ብዙ የዓለማችን አዳዲስ ድንቅ ፈጠራዎች በወታደራዊ ተቋማት ምርምርና ጥናቶች የተገኙ ናቸው። የሚሊታሪ ተቋማት ሁሌም በምክንያታዊ ፍርሃት የተሞሉ ስለሆኑ ጠላት በድንገት ተነስቶ እንዳያጠቃቸው ስጋት ስላለባቸው ቢቻል የበላይነቱን ለመያዝ አለበልዚያም ተገዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን እልክ አስጨራሽ ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ተገቢ ነው።
ነገር ግን የበታችነት ስሜት ከዚህ ለየት ያለ ነው። አንድ ባለሥልጣን ሰው የእኔን እኩልነት ሕዝብ አይቀበልልኝም ብሎ አንዴ ከደመደመ፤ እኩል ብቻ ሳይሆን የበላይም እንደሆነ በተግባር ማሳየት ይፈልጋል። እንዲህ ያለውን እርምጃ ሲወስድ ሕግ ስለማይፈቅድለት፤ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የግድ ሕጉን እየጣሰ ይፈጽማል። የዚህም አንዱ መልዕክት ምን ታመጣላችሁ ሕጉም ቢሆን በእኔ ላይ አይሠራም የሚል አስተሳሰብ ለማስተላለፍ ይጠቀምበታል።
ስለሆነም ከፍርሃቱ የተነሳ ሕዝብን ይጠላል፤ይጠራጠራል። የተለያዩ ጉዳዮችን ተቃራኒ ትርጉም በመስጠት ሕዝብን ያስራል፤ይገርፋል፤ ያሰቃያል፤ይገድላል። አንዴ መንፈሱ በበታችነት ፍርሃት ተሞልቷልና የበላይነቱን ለማስመስከር ሲል የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ በጭካኔ የተሞሉ ናቸው። ከዚህም የተነሳ የሕዝብ ኑሮ መሻሻልና የአገር ዕድገት፤ ይህን በመሳሰሉ እኩይ ተግባራት ስለሚተኩ ትኩረት ያጣሉ።
ሐ) ምቀኝነት፤ልምድ ችሎታና ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች ማራቅና በዝቅተኛ ቦታ ላይ እንዲመደቡ በማድረግ ማሠቃየት። ምክንያቱም ነገ ከነገ ወዲያ ሥልጣኔን ይቀናቀኑኛል በሚል ፍርሃት ማግለል፤ አእምሮው እየተረበሸም ካቃተው ወይም የሕዝብን ቀልብ የሚስቡና የሚከተላቸው ከሆኑ ደግሞ አስሮ ማሰቃየት ወይም በሐሰት ወንጅሎ እስከመጨረሻው መግደል ይሆናል።
ሠ) ሙስና ዓለማችንን በከፍተኛ ደረጃ እየተቆጣጠረ የመጣ መድኃኒት ያልተገኘለት ወረርሽኝ በሽታ ሆኗል። እንኳን በታዳጊ አገሮች ይቅርና በሠለጠኑ ሀገሮችም የሙስና ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ይገኛል። የበታችነት ስሜት በተጠናወተው መሪ ግን የሙስናው ሥራ እጅግ ዓይን ያወጣ ይሆናል። ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን በችሎታና በልምድ ሳይሆን በዘር፤ በቋንቋ፤በሃይማኖት በደም፤ በአምቻ፤ በጋብቻ እየተመዘነ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ይታደላሉ። እነዚህ ሰዎች ለአገር ዕድገትም ሆነ ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል የማይጨነቁ ናቸው። ይልቁንም እንደ አለቃቸው ሁሉ እነርሱም በሥራቸው የሚገኙ ቦታዎችን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲሁ በሙስና በታጀበ መዋቅር ይጥለቀለቃሉ። በዚህም የሀገር ዕድገት ይገታል፤ ፍርድ ይጓደላል ሕዝብም ይበደላል። የበታችነትን ስሜት ለመዘርዘር እንዲሁ በቀላሉ ሊጠቃለል አይችልም ግን ለዛሬው በቂ ነው እንላለን።
-//-