የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተጨባጭ እውነታ ዋልታዎች ( ክፍል ፪ ) አንዱዓለም ተፈራ

አንዱዓለም ተፈራ – eske.meche@yahoo.com

ሐሙስ፣ ነሐሴ ፴ ቀን ፳ ፻ ፲ ፩ ዓ. ም.  (09/05/2019)

 

በዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያው ክፍል፤ የለውጡ እንቅስቃሴ ዋልታዎች በግልጽ እየወጡ መሄዳቸውን አመላክቻለሁ። የኒህም እንቅስቃሴዎች ማዕከሎች፤ አዲስ አበባና መቀሌ መሆናቸውን ገልጫለሁ። መቀሌ የከተመው፤ ለውጡ ተገቢም፣ ትክክል አይደለም ይላል። መሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በሀገራችን ላይ ያነገሠው ሕገ-መንግሥት መቀጠል አለበት ይላል። ለውጡን ያመጣውና ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሕዝቡ መካከል መከፋፈልን በመፍጠርና በማጋጋል፤ ሀገራችንን ለርስ በርስ መጠፋፊያ የዳረጋት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግምባር፤ ከፖለቲካ ፍልስፍናውና ከአስተዳደር መመሪያው ጋር፤ በመጥፎ ተግባሩ ተጠቅልሎ ይወገድ ብሏል። እኒህ ናቸው የሀገራችን የፖለቲካው ትግል ማዕከሎች። በዚህ በሁለተኛው ክፍል፤ የዳበረ ምሽግ ያለውን የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባርንና የአባሪዎቹን እንቅስቃሴ ወደ ጎን ትቼ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ በኩል ያለውን አቀርባለሁ።

አብዛኛውን ጊዜ በሀገራችን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ፤ እንደሌሎቹ ሁሉ በበደል ላይ ያተኮረና፤ እንዲህ ተደረግን በሚለው የተሽከረከረ ቢሆንም፤ መፍትሔውን በሚመለከት፣ ወደ የት መሄድ አለብን በሚለው ላይ ትኩረቱ ቀዝቃዛ ነው። የራስን ወገን አስተዋፅዖና ሚና በሚመለከት ጠለቅ ያለ ግልጥነት አይታይም። ይልቁንም የበደሉን ትክክለኛ ገጽታና የወገንን አሰላለፍ ከትግሉ ማዕከላዊ ምንነት አኳያ ማስቀመጡ ላይ ግልጥነት አይታይም። ይሄን የያንዳንዱን ታጋይ ድርጅት አነሳስና ታሪክ በመመርመር መታዘብ ይቻላል። የብሔር ጭቆና፣ የደንበር መካለል፣ የታሪክ አረዳድን ስናጤን በጉልህ ይታያል። አሁን ደግሞ የእያንዳንዱ ብሔር መሆንና የራሱን ክልልና አስተዳደር መመሥረቱ እሽቅድድም ተጧጡፏል። ደቡብ እየተከፋፈለ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ እያለ እየቀጠለ ነው። የት ላይ እንደሚያበቃ ልኬቱ አይታየኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቃሚ የትግል ግብአቶች

እያንዳንዱ ብሔር የራሱን ክልል አበጅቶና መሪዎቹን አስልቶ ሲተለተል፤ እኛ ኢትዮጵያዊ ነን! ከተለያዩ የትውልድ ሐረጎች የሚመዘዝ ማንነት አለን። ኢትዮጵያዊነታችን ከዳር እስከዳር የሚደርስ እንጂ፤ በአንድ ጠባብ ጎራ ውስጥ የሚሸጎጥ አይደለም! ያሉት ኢትዮጵያዊያን፤ ያለ ምድር፣ በአየር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ ማለት ነው። እንደ አክራሪዎች ከሆነ፤ በነሱ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሌላ ክልል ተወላጆች፤ ቦታውን ለቀው መሄድ አለባቸው። አለዚያ እንግዳ ሆነው በነሱ ፈቃድ መኖር ይችላሉ። ይሄም ሲሆን፤ መጀመሪያ የነሱ ፈቃድ፣ ቀጥሎ ደግሞ በማንኛውም የኅብረተሰብ ተሳትፎ ውስጥ የማይሳተፉ፤ ለዕለት ተዕለት ኑሯቸው እንኳን፤ የዚያን አካባቢ ቋንቋ ብቻ መጠቀም ግዴታቸው ነው። ይህ ነው የነሱ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት።

እዚህ ላይ የኦሮሞ ጽንፈኛዎችን እንመለክት። ኦሮሞ የኢትዮጵያ ዋልታ ነው። ገዥዎችንም ሆነ ተገዥዎች ወደኋላ ብንመረምር፤ ኦሮሞ ሀገር አቅኚ፣ ሀገር ግንቢ፣ ከሌሎቹ ጋር የኢትዮጵያ ባለቤት ነው። ይህ ሀቅ እያለ፣ እኛ ተወራሪ ነን! ዐማራ ቅኝ ገዝቶናል! በማለት የተጠቂ ሰለባ አቀንቃኞች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ለምን? ይሄን ወደጎን ልተወውና፤ የአሁኑ የሀገራችን የፖለቲካ ትግሉ መሽከርከሪያ በሆነው በለውጡ ምንነት ላይ ላተኩር። ከላይ እንዳመለከትኩት ይህ የለውጡ ሂደት ሁለት ሰፈሮችን አበጅቷል። ለውጡን ተቀብለን ወደፊት ለመሄድ፤ የለውጡ ወገን ሁለት ጉዳዮች አሉት። የመጀመሪያው ከለውጡ አንጻር ቆመው፤ ለውጡን ለማክሸፍ ከሚጥሩት ጋር ያለው ግብግብ ነው። ሌላኛው ደግሞ፤ የለውጡ ግብ ላይ መስማማቱ ነው። ለውጡ በግለሰቦች ላይ ያተኮረና ግኝቱ የነከሌ ነው የሚለው አፍራሽ እንደሆነ ጠቁሜያለሁ። ለውጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውጤትና ባለቤትነት ያለው ነው። ለውጡ የነበረው አስተዳደር ያደረሰውን በደል ተመርኩዞ የመጣ ነው። እናም መተካት ባለበት ላይ ስምምነቱ ሊኖረን ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በመደብ ትግል የሚያምኑ በመደብ ትግል ይደመሰሳሉ - ሸንቁጥ አየለ

አንድ መካድ የማንችለው ሀቅ አለ። የግድ መንግሥት መኖር አለበት። ይህ መንግሥት ደግሞ ኢሕአዴግ የተወልን መዋቅር ነው። ባሁኑ ሰዓት መንግሥት ሆኖ ሊንቀሳቀስ የሚችለው ይሄው ኢሕአዴግ ነው። ይሄንን በልመና ወይንም በድርድር በተግባር የሚተካው የለም። ኢሕአዴግ ይገዛናል፤ መግዛትም አለበት። ቦታውን በአየር ላይ በትኖ ሊሄድ አይችልም። መታወቅ ያለበት ግን፤ ይህ ክፍል ብቸኛ የለውጡ ባለቤት አለመሆኑ ነው። ተደርጎም መወሰድ የለበትም። ብቻዬን ላሸጋግራችሁ ነው! የሚለው አፍራሽ ነው። መነሻው ደግሞ ብቻየን ለውጡን አምጥቻለሁ ከሚል ነው። ይህ ትክክል አይደለም። ከፍተኛውን መስዋዕትነት ክፍሎ፣ ልጆቹን ገብሮ የታገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ለውጡን ያመጣው! የለውጡም ባለቤት! ስለዚህ፤ ለውጡ በትክክል ሕዝባዊነቱን አዝሎ፤ በሕዝቡ ታቅፎ ግቡን እንዲመታ፤ ሕዝቡ የሽግግሩም አካል መሆን አለበት።

ሕዝቡ የሽግግር መንግሥቱ አካል መሆን አለበት ስል፤ የተውጣጡ ልሂቃን ዘለው በሥልጣን ላይ ድርግም ይበሉ ማለቴ አይደለም። የለውጡን ማሽከርከሪያ ሃሳብ አጉልተን ስናወጣው፤ በዚያ ዙሪያ ያሉ ያልታቀፉ የትግሉ ክፍሎች ሲካተቱ፤ ሽግግሩን ሕዝባዊ አድርገው ያሳኩታል ማለቴ ነው። ይሄን የኛ ሀገር ተጨባጭ የፖለቲካ እውነታ በሚመለከት፤ ሽግግሩን የሚገዙ ሁለት ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው ለውጡን ፈላጊው የኢሕአዴግ ክፍል፤ ሀቀኛ፣ ግልጥና ቅን የለውጡ አካል ሆኖ መገኘት ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ በሕዝቡ በኩል ይሄን ተቀብሎ፤ በትክክል ለውጡን ከግቡ ለማድረስ፤ የሃሳብ ጥራትና ተሳታፊነት ይዞ መገኘቱ ነው። እኒህ ወሳኝ ጉዳዮች መስመር ከያዙ፤ ሽግግሩ በትክክል ይካሄዳል። የሚቀጥለው ምርጫም ትርጉም ያለውና ግብ መቺ ይሆናል። ለውጡን በሚመለከትና ለውጡን ፈለጊዎችን በሚመለከት፤ በመካከላችን ያለው ልዩነት፤ መሠረታዊ በሆነው በሀገር፣ በማንነትና በነጋችን መሆን የለበትም። ያለፈው ሥርዓት መፍረስ እንዳለበት ጥያቄ ሊኖር አይገባም። የሀገራችንን ወደ ዴሞክራሲያዊ አሰራር መንገድ መጓዝ፤ ለጥያቄ መቅረብ የለበትም። እንዴት አድርገን የምንፈልገው ቦታ እንደርሳለን? በሚለው ላይ የተለያዩ ሃሳቦችን ይዘን እንቀርባለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አመት በአል ሲቃረብ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል| በእውቀቱ ስዩም

በትክክል ለውጡን በምንፈልገው ውስጥ፤ ከአንድ ጫፍ እስከሌላው ጫፍ ድረስ የተለያዩ ፍላጎቶችን ያነገብን ግለሰቦችና ቡድኖች አለን። ነገር ግን፤ የግል ፍላጎታችን ወሰን አለው። መጀመሪያ ሀገራችን መኖር አለባት። የሀገራችን ዳር ደንበር መጠበቅ አለበት። የኛ ሀገር እንድንል የሚያስችለን ሀገራዊ ራዕይና ባለቤትነት ሊሰፍንብን ይገባል። ያ በሌለበት፤ በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል፤ የራሱ የሆነ ትርጉምና ግብ ነድፎ እንዳሻው ይነዳናል ማለት ነው። አሁን የተያዘው ሩጫ፤ ዋናውን የለውጡን ተቃዋሚዎች ትክክል ማስገባት ላይ ትኩረት መሥጠቱ ቀርቶ፤ ለውጡ የመጣበትን የመከፋፈል አባዜ አጉነን፤ የየራሳችንን ጎራ ማጠናከር ነው። ይህ ለውጡን ዋጋ ያሳጣዋል። ይልቁንም ለበለጠ መተላለቅ ይዳርገናል። በዚህ ላይ ደግሞ፤ እኛ ሳንታከልበት፣ የለውጡ ጠላት ሌት ተቀን እየሠራበት ነው።

ወደ የምንፈልገው የፖለቲካ ግብ፤ በአንድ ዝላይ አንደርስም። የሽግግር መንግሥቱ ተግባር ይሄን ማከናወን ነው። የሽግግር መንግሥቱ ምንነት፤ የሽግግሩን ሂደትና መድረሻ ግቡን ይወስነዋል። ስለዚህ፤ የሽግግር መንግሥቱ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ፤ ሕዝቡን በለውጡ ማዕከል ማካተት አለበት። ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ለውሃውም አይጠቅምም፤ እየተንጠባጠበ ያልቃልና! አዲስ አበባ የማን ናት? ይሄኛው መሬት የማን ነው? መታወቂያህ የት እንድትኖር ይፈቅድልሃል? እኒህ፤ እኛ ሳንሆን፤ የለውጡ ተቃዋሚዎች እኛን ለማዳከም የሚያነሷቸው ጉዳዮች ናቸው። አዲስ አበባም ሆነ ሐረር፤ ነዋሪዎቹ መርጠው በሚያስቀምጧቸው መሪዎቻቸው ፍላጎታቸውን ያሟላሉ። አሁን ለውጡን ፈር እናስይዘው።

Share