September 2, 2019
ጠገናው ጎሹ
የአገራችን ሁኔታ በዘርፈ ብዙና ከባድ ፈተና ውስጥ ከወደቀ ብዙ ዘመን ተቆጠረ ። ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚዊ ፣ማህበራዊ ፣ ባህላዊ፣ ሞራላዊ ፣ ሥነ ምግባራዊ ፣ ሥነ ልቦናዊና መንፈሳዊ (ሃይማኖታዊ) እሴቶቻችንን እያደር ከመዝቀት አዙሪት ለመታደግ ያለመቻላችን እንቆቅልሽ በእጅጉ የማያሳስበውና የማይቆጨው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ቅን የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
ለግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን (ከ1966 -እስከ አሁን) ከሆነውና አሁንም እየሆነ ካለው እጅግ አስከፊና ሁለንተናዊ ፈተና ከምር ተምረን በአይነቱም ሆነ በይዘቱ እስከአሁን ከመጣንበት እጅግ እኩይ ሥርዓተ ፖለቲካ እና አሁንም እየሄድንበት ካለው የሸፍጥና የሴራ ተሃድሶ ፖለቲካ አውጥቶ ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞኬራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግረን የጋራ መድረክ፣ ራዕይ ፣ስትራቴጅ ፣ ፓሊሲ፣ እቅድ እና ተግባራዊ እርምጃ እውን ለማድረግ ከሚያስችል አስተሳሰብና አካሄድ ላይ ያለመገኘታችን እንቀቅልሽ እጅግ አስከፊ ገፅታና ይዘት እየያዘ ቀጥሏል ። የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ወርቃማ እሴቶች በማጥፋት በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ የሚመሠረቱ መንደሮች ፈላጭ ቆራጭ ገዥዎች እንሆናለን በሚል ክፉ ቅዠት የተለከፉ ፖለቲከኞችና አክቲቪሰቶች ነን ባዮች ሃይማኖታዊ እምነትንና ቋንቋን ወደ ለየላቸው የፖለቲካ መሣሪያነት በመለወጥ ዘመቻ ላይ ተጠምደዋል ።
በሸፍጥ ፖለቲካና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉ ኢህአዴጋውያንም ጉልቻ እየለዋወጡ “በንስሃ ተጠምቀናልና አታስቡ!” ሲሉን “ይሁን ወይም አሜን!” እያልን ከዚህ ዘርፈ ብዙና እጅግ ከባድ አገራዊ ፈተና በአሸናፊነት ለመውጣት ይቻለናል ብሎ ማሰብ ፈጣሪ ለትልቅ ዓላማ የሰጠንን አእምሯዊና አካላዊ ብቃት (ችሎታ) ማራከስ (እርካሽ ማድረግ) ነው የሚሆነው። ለነገሩ ፈጣሪም እንዴት ሊረዳን እንደሚችል በእጅጉ የተቸገረው በዋናነት ከራሳችን በሚመነጨው ልክ የሌለው ውድቀታችን ምክንያት እንጅ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ሰባኪዎች ወይም መምህራን ታላቁን መፅሀፍ ሲፈልጉ ለምህረት (ለመፅናኛነት) ሳይፈልጉ ደግሞ ለጥፋት (ለማስፈራሪያነት) በሚያመቻቸው ሁኔታ እየተረጎሙ ሊነግሩን እንደሚሞክሩት በመከራም ውስጥ ሆኖ “ተመስገን!” የሚለው የአገሬ ህዝብ ከሌሎች የዓለም ህዝቦች ሁሉ ኅጢአቱ የከፋና ለዚህ አይነት ቅጣት የሚያበቃው ሆኖ አይደለም። ሰባኪዎቻችን በእራሳቸው አእምሮ ውስጥ የሚፈጥሩት አምላክ ካልሆነ በስተቀር ከብቁ ህሊና እና አካል ጋር ሰውን የፈጠረ እውነተኛና የእውነት አምላክ ይህን አያደርግም።
አባት ለልጁ እንደ ሰው ሆኖ መኖር የሚያስችለውን ሁሉ ከአባታዊ ምክር (ትምህርት) ጋር ያለምንም ስስት ሰጥቶት በልጁ ድንቁርና ወይም ክፉ ስንፍና ወይም የተበላሸ ማህበራዊ መስተጋብሩ ወይም የፍቅርና የሰላም ባህሪ እጦት ፣ ወዘተ ምክንያት ከእራሱ አልፎ የሌሎችን ህይወት ቢያበላሽ ተጠያቂው እርሱ እራሱ ብቻ ነው። “አይ እግዚአብሔር እኮ እንደ ሰው አይደለምና የፈለገውን ያህል ብንሰንፍና ብንበላሽ አይጨክንም” የሚል ሃሳብ እንደሚቀርብ እረዳለሁ። አዎ! ፈጣሪ ጨካኝ አይደለም ። እኛ ግን እኛን ከፈጠረበት ጥሮ ግሮ በነፃነትና በፍቅር የመኖር ዓላማ ውጭ ከመጠን ባለፈ ስንወጣ ጭሆታችንን ትርጉም አልሰጠው ብሎ ዝም ቢለን የሚገርም ወይም የሚያሳዝን ሊሆን አይችልም። በእኔ አረዳድና እምነት በእውነት ስለእውነት መነጋገሩ እያስፈራን ካልተቸገርን በስተቀር በአገራችን ለዘመናት የሆነውና አሁንም እየሆነ ያለው ይኸው ነው ። የሁሉም ሃይማኖቶች መሪዎችና አስተማሪዎች ብርቱ ፈተናዎች ከሆኑት አንደኛው የሚመነጨው ከዚሁ የደካማነት አዙሪት ነው።
የበፊቱ ህወሃት/ ኢህአዴግ የአሁኑ ኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞችን የምናስተናግድበት ሃይማኖታዊ እይታችን በእጅጉ የተንሸዋረረ ነው። ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ጥርሳቸውን ነቅሎ ያሳደጋቸውን የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ተሃድሶ በሚሉት ማደንዘዣ አቡክተው እየጋገሩና እያከፋፈሉ አደንቁረው ሲገዙት የኖሩት መከረኛ ህዝብ የእነርሱን መከራና ውርደት አሸካሚነት በአብሮነትና በፈጣሪው ድጋፍ ታግሎ ነፃነቱን እንዲያረጋግጥ ከማገዝ ይልቅ ሁሉን ነገር “የፈጣሪ ፈቃደኝነት ባይታከልበት ነው ” በሚል የለየለት የድንቁርና አዙሪት ውስጥ እየዳከረ እንዲኖር ማድረግ የበጎች/የህዝቦች እረኝነትን ጨርሶ አያመልክትም።
የስሜታዊነት ፈረስ እየጋለብን ልብ አላልነውም እንጅ የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞች ገና ሥልጣነ መንበራቸው ላይ በቅጡ ሳይቀመጡበት በጠቅላይ ሚኒስትራቸው አማካኝነት በየሃይማኖቱ ልዩ ልዩ አውዶች ላይ በእንግድነት (በተጋባዥነት) ሥነ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በዋና ተዋናይነት ሃይማኖቱንና ፖለቲካውን እየቀላቀሉ ሽር ጉድ ያበዙት ለዚሁ ርካሽ የፖለቲካ ንግዳቸው ሲሉ እንደነበር (እንደሆነ) ግልፅ ነበር ። የሃይማኖት መሪዎችም የለውጥ አራማጅ ተብየ ፖለቲከኞችን የተቀበሉበት አኳኋን ከኖረበት መከራና ውርደት አስከፊነት የተነሳ የእውነት ለውጥ መስሎት የለውጥ አራማጅ ተብየወችን እጅግ በተሳከረና ግልብ በሆነ ስሜታዊነት ከተቀበለው የዋሁ የአገሬ ሰው ሁኔታ የተሻለ ሳይሆን በእጅጉ የወረደ ነበር።
“የኢትዮጵያዊነት ሱሰ ነው” ትርክታቸውን ክርስቶስ የተናገረው እስኪመስል ድረስ ከሊቅ ተብየ እስከ እንደ እኔ አይነቱ ተራ ሰው በዘወትር መፈክርነት ሲያስተጋባ ሸፍጠኛ የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች ከአደባባይ በስተጀርባ ሲሸርቡት የነበረው ሴራ ይኸውና ዛሬ ካለንበት እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ጥሎናል ። አዎ! “የዘመናችን ሙሴዎች” ብለን ያሞካሸናቸው የለውጥ አራማጅ ተብየዎች እንደ ጃዋር መሃመድ በመሰሉ እኩይ ፍጡራን የስትራቴጅና የታክቲክ መሃንዲስነት እና ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው በተቀበሏቸው ኦነጋዊያን አስተባባሪነት እየታጀቡ መከረኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለምንምና ለማንም ወደ ማይበጅ ሁኔታ ውስጥ እየገፉት ይገኛሉ ።
የሃይማኖት መሪዎችም የለውጥ ሐዋርያት መሪው (የጠቅላይ ሚኒስትሩ) “የአስታራቂነትና የሙሴነት” “ውለታ” ስለከበዳቸው አገርና ወገን በአክራሪ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች እና የገዥውን ፓርቲና የመንግሥቱን መዋቅርና አሠራር በሚዘውሩ ፖለቲከኞች ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ምስቅልቅላቸው ሲወጣ ሌላው ቢቀር የተለመደውን የመግለጫ ድርሰት አዘጋጅተው ሳያስነብቡን ወይም ሳያሰሙን በርካታ ወራት ማስቆጠራችውን ልብ ይሏል ። ይኸውና ዛሬ የአብያተ ክርስቲያናት ጥቃትና ቃጠሎ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከ1990ዎቹ ጀምሮ የነበረ መሆኑን እየጠቀሱ የፈተናውን ክብደትና አደግኝነት ይነግሩናል። ምነው በወቅቱ ትርጉም ላለው የመፍትሄ ፍለጋ አልተረባረባችሁ ? ተብለው ቢጠየቁ የሚሰጡት መልስ በተለመደ ሰበብ ድርደራ የተሞላ ከመሆን አያልፍም ።
አሁንም ምንም ያህል ይዘግይ የፈተናውን አደጋ (ቤተ እምነቶችን የማውደምንና አገልጋዮቿን የመግደልን) የእብደት ዘመቻ ማሳወቁና እንዲቆም መጠየቁ ተገቢ ነውና እሰየው ነው ።
ችግሩ ግን የዚህ አይነቱን በብልሹ ፖለቲካ የተቦካንና ሥራ ላይ እየዋለ የሚገኝን እጅግ አስከፊና አደገኛ ጨዋታ ፖለቲከኞች ለእራሳቸውም ሲሉ ለጊዜው ጋብ እንዲል (ሰላም የሰፈነ እንዲመስል) ሲያደርጉት የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች (አስተማሪዎች) ተመልሰው ከፖለቲከኞች ጋር የመላላሳቸው ወይም ደግሞ በአድርባይነት ውስጥ የመዘፈቃቸው አባዜ ነው።
ለዚህ ነው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ጨርሶ ታጥቦ በማይጠራ ሁኔታ የተዘፈቀው የያኔው የህወሃት/ኢህአዴግና የአሁኑ የኦዴፓ/ኢህአዴግ ሥርዓተ ፖለቲካ መሠረታዊ በሆነ የለውጥ አካሄድ በእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስአልተካ ድረስ ለዘመናት ከዘለቀው አስከፊ አዙሪት ጨርሶ መውጣት አይቻልም ብሎ መከራከር ትክክል የሚሆነው።
በተለምዶ እንደምንለው አለመታደል ሆኖብን ወይም የሃይማኖት ሰባኪዎች እንደሚሉን እግዚአብሔር ሊቀጣን ፈልጎ ወይም ሰይጣን ሹክ ብሎንና አሳስቶን ሳይሆን ፈጣሪ እንደሰጠን የብቁ አእምሮና የአካል ባለቤትነት ለመኖር ባለመቻላችን (ባለመፈለጋችን) ዛሬም እንደ ግለሰበም ይሁን በሙያ ፣በፖለቲካ ፣ በሲቪል ፣ በሃይማኖት ተቋም (ድርጅት) እንደታቀፈ (እንደሚሳተፍ) ዜጋ እና በአጠቃላይ እንደ ህዝብ ከዚህ ክፉ አዙሪት ለመውጣት ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እየሆነልን (እየተሳካልን) አይደለም ። በየ ሚዲያው ፣ በየ አደባባዩ ፣ በየ አዳራሹ ፣ በየ አውደ ምህረቱ (በየ ቤተ እምነቱ) ፣ ባገኘነው አጋጣሚና ቦታ ሁሉ ከመደስኮርና ከማስደስኮር ካልዘለለ ክፉ ልማዳችን ወጥተን ወደ መሬት ወርዶና ህይወት ዘርቶ አገርን (ወገንን) በእውን የሚታደግ የመፍትሄ ሃሳብን ወደ ተግባር የሚለውጥ የአስተሳሰብ ልዕልና እና ድርጃታዊ ሃይል እውን ለማድረግ አልቻልንም (አልፈለግም)።በአሳዛኝ መልኩ !
ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቆ የኖረውን ምንነታቸውንና ማንነታቸውን በንስሃ እንዳነፁት የሚነግሩን (የሚያደነቁሩን) የገዥው ቡድን ፖለቲከኞች ጥርሳቸውን ነቅለው ካደጉበት የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍት ጨክኖ መላቀቁ አልሆንላቸው ብሎ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ አክራሪነት ልክፍተኞችን (እብዶችን) አቅፈውና ደግፈው በተቃራኒው ግን መብታቸውን የጠየቁና የሚጠይቁ ንፁሃን ዜጎችን ሰብአዊ መብት በለመዱት ተውኔታዊ ዘዴ ማጎሳቆሉን ቀጥለውበታል።
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ትርጉም ባለውና ተፅዕኖ በሚያሳድር አኳኋን በህግ አምላክ! ለማለት የሞራል ግዴታና ለሰብአዊ መብት ፀንቶ የመቆም አርበኝነት ወኔ የተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች የቤተ እምነቶች ጥቃትና የንፁሃን አገልጋዮቻቸው መጎሳቆልና መገደል ለምን ይገርማቸዋል ? ይሁ ሁሉ ሲሆን አልሰማሁምና አላየሁም በሚል አይነት ወይም “ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አላቃተኝም ፤ ግን የባሰ አገር ትፈርሳለች ብየ ነው ” የሚልና ስሜት አልባ የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣኑን በተረከቡ ማግሥት የሃይማኖቶች መሪዎችን “በክርስቶስ መልእክተኝነት” እንዳስታረቁና እፁብ ድንቅ ሰላምና ፍቅር እንዳስገኙ በእነዚሁ የሃይማኖት መሪዎች አይደል እንዴ ገድሉ ሲነገርላቸው የነበር? ታዲያ ምነው ዙሪያ ጥምጥሙን እየዞሩ በደፈናው የእሮሮና የማስጠንቀቂያ ንግግር ከማዥጎድጎድ እኒያን “ታላቅ አስታራቂ” ጠቅላይ ሚኒስትር “ምነው ቃልዎና የመሬቱ እውነት ተነጣጥለው ወደቁ? “ ብለው አይጠይቁ?
መሪሩን እውነት እየሸሸን ያንኑ ምርኮኛው ያደረገንን በውሸት ምንነትና ማንነት እራሳችንን የመሸፋፈንን ክፉ ልማድ የሙጥኝ ካላልን በስተቀር ሃቁ ይኸው ነው።
የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ተብየዎች በፖለቲካው ሥርዓት ብልሹነት ምክንያት ከልክ ያለፈው የኑሮ ጉስቁልና ናላውን ያዞረውን ወጣት ትውልድ ቄሮና ኤጀቶ በሚል ቅርፀ ቢስና ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ሥር አሰልፈው ትእዛዛቸውን እንዲቀበል እያደረጉና እጅግ አደገኛ በሆነ የስሜታዊነት ፈረስ እያስጋልቡ ከዓለማዊው አውድ አልፎ የሃይማኖታዊ እምነት አውዶችን ከአገልጋዮቻቸው ጋር በእሳት እስከ ማጋየት የደረሰ እብደት ውስጥ ዘፍቀውታል ። ታዲያ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች የምድሩንና የሰማዩን ዓለም ግንኙነት ትርጉም ባለውና ተፅዕኖ በሚያሳድር ሁኔታ ለዚህ ትውልድ በግልፅና በቀጥታ ማስተማርና መምከር ለምንና እንዴት ተሳናቸው?
የአክራሪ ወገኖች እብደት በሸፍጠኛ የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች በቀጥታም ይሁን ከበስተጀርባ በሚጎነጎን ሴራ እየተደገፈ ከተለመደው እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ አልፎ የኢትዮጵያ የሚል ቅፅል ያለውን ነገር ሁሉ እንደ ጠላት ፈርጆ ወደ ማጥፋት ደረጃ ተሸጋግሯል ።
ታዲያ ይህን እኩይ አስተሳሰብና አካሄድ ሠርቶ በማሳየት አርበኝነት ባልታጀበ የምህላ ወይም የእግዚኦታ አዋጅ እንዴት መቋቋም ይቻላል ? መሪር በመሆኑ ለመቀበል ቢቸግረንም ተያይዘን ከመጠፋፋት ዘላቂነት ባለው አኳኋን መዳን ካለብን ከፊታችን የተደቀነው እውነት ይኸው መሆኑን አውቆ የሚበጀውን ማድረግ ከቶ አማራጭ የለውም።
ከሰሞኑ የአማርኛ ቋንቋን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መልክ ለማስያዝ በትምህርት ሚኒስቴር ተብየው በኩል የቀረበውን “ፍኖተ ካርታ” በሚመለከት የሆነውን ሁሉ በቅንነትና በአገራዊ ቁጭት ለታዘበ የአገሬ ሰው የውድቀታችን ቁልቁለት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ መረዳት አይሳነውም ።
የለውጥ አራማጅ ተብየውን አቅጣጫና ስትራቴጅ ቀያሽነቱን በይፋ የሚነግረንና እጅግ አደገኛ ሰብእና የተጠናወተው ጃዋር መሃመድ ማስጠንቀቂያ በሰጠ ማግሥት አንድ በሚኒስተርነት ደረጃ ላይ የሚገኝና በትምህርት ደረጃውም ባለ ዶክትሬት ነኝ የሚል ባለሥልጣን “ፍኖተ ካርታው ከምክረ ሃሳብ (ከምክር ቢጤ) የሚያልፍ ዓላማና ይዘት የለውምና አትጨነቁ” በሚል “ለማስተካከል (ግልፅ ለማድረግ)” በእጅጉ ሲጨነቅ ከማየት የበለጠ ምን አይነት የውደቀት ውድቀት ይኖራል ? ከዚህስ የባሰ ትውልድን የመግደል የውድቀት ውድቀት የትኛው ነው?
ይህን ትውልድ ገዳይ አስተሳሰብና አካሄድ መዋጋት ለፖለቲከኞች ብቻ የሚተው ሳይሆን የየትኛውም የሃይማኖት መሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያሳስበው መሆን አለበት። የመግባቢያ ቋንቋቸው ተደበላልቆባቸው ይሠሩት የነበረው ሥራ ሁሉ ትርጉም አልባ ሆኖባቸው የተቸገሩትን ሰዎች ታሪክ ታላቁን መፅሐፍ በየሰበካው አደባባይና በየአውደ ምህረቱ በዋቢነት የሚጠቅስ ሰባኪ በዚህ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእኛው የእራሳችንን አሳዛኝ ሁኔታ በትኩረትና በድፍረት ማስተማር ካልደፈረ ሌላ ምን ሊደፍር እንደሚችል ለመረዳት ያስቸግራል ።
አዎ! ተገቢና ገንቢ የጋራ የመፍትሄ ሃሳብ እውን ማድረግ ተስኖን ስንደፋደፍ በእኩይ ፖለቲካዊ ባህሪና አድራጎት የተለከፉት የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ነን ባዮች የማመዘን ህሊናውን ጨርሶ በሳተው ጃዋር መሃመድ አዝማችነት “የኢትዮጵያ የሚል ቅፅል ያለበት ተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነት በኦሮሚያ ውስጥ ድራሹ መጥፋት አለበት” የሚል አደገኛ ዘመቻ ሲነደፉና ቀመር ሲያወጡ ቆይተው ይኸውና ወደ ተግባር መግባታቸውን እየነገሩን ነው። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ክፉ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍታቸውን የሚጋሩትን ሸፍጠኛ የለውጥ አራማጅ ተብየ ፖለቲከኞችን በመተማመን የመሆኑን ጉዳይ መሬት ላይ እየሆነ ካለው ሃቅ በላይ የሚነግረን የለም ።
ምንም እንኳ የሰሞኑ መግለጫና አቤቱታ ተገቢ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያኗ እራስ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የአክራሪ ጎሰኞች ሴራ ዛሬ በድንገት የተጀመረ አለመሆኑን እያወቀ በወቅቱ ምንም ሳይል ሸፍጡና ሴራው የዛሬ ሳይሆን የቆየ ነውና መንግሥት አንድ ይበለኝ ማለቱ ችግሮቻችንን የምንፈታበት መንገድ ሁሉ እየተንሸዋረረ እንዳስቸገረን ይነግረናል ።
ይህ “ከእኔ የእምነት አይነትና ከእኔ ማህበረሰብ አባል ውጭ በእኔ ቀየ (መንደር) ምን ትሠራለህ (ትሠሪያለሽ) ?” በሚል እራስን በራስ (ወገንን በወገን) የማሳደድና የመግደል እጅግ አስከፊ እብደት በእጅጉ የማያሳስበው ቅን ልቦና እና አመዛዛኝ ህሊና ያለው የየትኛውም ሃይማኖት መሪና ተከታይ የሚኖር አይመስለኝም ። አዎ! የየትኛውም ሃይማኖት ተቋም ለጊዜው የዚህ ክፉ ልክፍት ቀጥተኛ ሰለባ አይደለሁም ብሎ ሊያስብ ቢችልም በሁለት ምክንያቶች እውነት አይሆንም ፦ ሀ) ሃይማኖትን ለፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም የሚደረግ ጨዋታን በጋራ ማስቆም ካልተቻለ በየተራ መጠቃቱ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው ፤ ለ) የሃየማኖት መሪና አስተማሪ ነኝ/ነን እያልን የሌላው መሠረታዊ የእምነት መብት ሲጨፈለቅ ለምንና እንዴት? ብሎ አለመጠየቅና ከተበዳይ ጎን አለመቆም በራሱ እናምንበታለን የምንለውን እምነት ዋጋ (value) ያሳጠዋል ። ፖለቲካዊውንም ሆነ ሃይማኖታዊውን ህይወታችንን ዘመናት ካስቆጠረበት አዙሪት መታደግ ያልሆነልን የአንደኛውን ወገን ጥቃትና ህመም ሌላኛው ወገን ከቃላትና ከአዞ እንባ አልፎ ሊሰማው ባለመቻሉ (ባለመፈለጉ) ነውና።
በየዜናዎቻችን (በየወሬዎቻችን) እወጃ እንኳ ቢያንስ በዚህ ወይም በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ወይም የዚህ ወይም የዚያ ጎሳ አባላት ኢትዮጵያውያን የሚል ሳይሆን ይህን ያህል አማራዎች ወይም ኦሮሞዎች ወይም ትግሬዎች ወይም ኦፋሮች ወይም ጉሙዞች ወይም አኟኮች ወይም ሲዳማዎች ወይም ወላይታዎች ወዘተ ተዋከቡ፣ ታሠሩ፣ ተገረፉ፣ ተፈናቀሉ ፣ ተገደሉ ከሆነና የህዝቡም አስተሳሰብ (ሥነ ልቦና) በዚሁ አስቀያሚ ብቻ ሳይሆን አደገኛ የፖለቲካ ቅኝት ከተቃኘ ዓመታት ተቆጠሩ።
ታዲያ በዚህ አኳኋናችን የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች (እብዶች) ሰለባ ብንሆን ለምን ይገርመናል ? ከጎሳ/ከዘር ፖለቲካ በሚነሳ ግርግር እናተርፋለን የሚሉ እኩያን ወገኖችን በህግና በአገር ደህንነት አግባብ አደብ ከማስገዛት ይልቅ ከመጋረጃ በስተጀርባ የጨዋታ ሜዳውን የሚያመቻችላቸው የገዥ ቡድን ባለበት ሁኔታ ከነችግሮቿም ቢሆን በኢትዮጵያ ታሪክና በጎ ትውፊቶች ላይ ግዙፍና ጥልቅ አሻራ ያሳረፈችው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጥቃት ኢላማ ብትሆን ለምን ይገርመናል?
አሁንም ከመማርና ከመማማር ይልቅ መደናቆሩና መናቆሩ እየገነነ በመምጣቱ የእራሳችን ማጥፊያና መጠፋፊያ ከሆነው አስከፊ የፖለቲካ ጨዋታ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን ስለ ዴሞክራሲ ፣ ስለፍትህ፣ ስለ የእምነት ነፃነት፣ ስለ ሰላምና መረጋጋት፣ ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስንደሰኩር ጨርሶ ሃፍረትና ይሉኝታ የለንም ። ታዲያ እኛ የውድቀት ውድቀት ተምሳሌቶች ብንሆን ለምን ይገርመናል ? ለምንና እንዴትስ ያሳዝነናል ? በማንና ለማንስ ነው የምናዝነው?
አዎ! ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የሸፍጥና የመከራ መፍለቂያና ማከፋፈያ ሆኖ የዘለቀውን ሥርዓተ ኢህአዴግ ከሞት አፋፍ መልሰው በሸፍጥና በሴራ በተበከለ ንስሃና ተሃድሶ ስም እንዲቀጥል ያደረጉ የፖለቲካ ተውኔት ተዋንያንን በቃችሁ ብሎ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን የሚያስችል አማራጭ ሃይል ከመሆን ይልቅ ተቀዋሚ ተብየ ሁሉ የተውኔቱ ሰለባ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ከአስከፊው አዙሪት መውጣት እንዴት ይታሰባል ? እንዴትስ ይቻላል? ለዚህ አይደለም እንዴ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች የኢትዮጵያዊነት (የዜግነት) ፖለቲካን ከማጥቃት አልፈው የኢትዮጵያ ስም የታተመባትን የሃይማኖት ተቋም ካላጠፈን ብለው ያዙንና ልቀቁን ወደ እሚል እብደት የተሸጋገሩት ?
እንደ ሃይማኖት ተቋምም የአንዱ የአምልኮ ቤት ወይም ሥፍራ እስከ አገልጋዮቹ እንደ አልነበር ሲሆን ቆሞና ዝም ብሎ የሚያይ የሃይማኖት መሪና ተከታይ ካለ እምነቱ ጨርሶ የውሸት ነው ፤ ወይም ሃይማኖታዊ ተልእኮውንና ግዴታውን እንደማነኛውም የዓለማዊ ኑሮ ማሸነፊያ ዘዴ አድርጎታል ማለት ነው። ታዲያ እያየነውና እየሰማነው ያለነው ክፉ ነገር ሁሉ እንዴትና በየት በኩል ሊቆምና በበጎው ነገር ሁሉ ሊተካ ይችላል?
በእውነት ከተነጋገርን የአንዱ መቃጠል ለሌላው የመስፋፋትና የመጠናከር እድል የከፈተለት የሚመስለው አይኖርም ብሎ መከራከር የሚያሳምን አይመስለኝም ። ልባችን እያወቀው ስሙን ለመጥራት ካልፈራን (ወኔው ካልከዳን) በስተቀር ከፊታችን ያፈጠጠውና ያገጠጠው መሪር ሃቅ ይኸው ነው። “እኔንና የእኔ የሆነውን ሰውና ነገር እስከ አልጎዳ ድረስ ለሌላው ምን አገባኝ” የማለት ብቻ ሳይሆን በሌላው መከራና ኪሳራ የእራስን ልክ የሌው እኩይ ዓላማና ፍላጎት የማስፉፉትና የማጠናከር ልክፍት የፖለቲካው ብቻ ሳይሆን የሃይማኖቱም ብርቱ ፈተናችን ነው።
ለዚህ ነው የአገራችን የየሃይማኖቶች መሪዎችና አስተማሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪ በሰጠው ምድር (አገር) ላይ እንደ ሰውና እንደ ዜጋ ተከብሮ የመኖር ነፃነቱን በሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥዎች እየተነጠቀ የመከራና የውርደት ተሸካሚ ሲሆን ተሸክመነዋል በሚሉት ሰማያዊ ተልእኮ አነሳሽነትና ተነሳሽነት በአንድ አዳራሽ ወይም አደባባይ በጋራ ሲመክሩና የጋራ መፍትሄ ሲዘይዱ የማናያቸው (የማንሰማቸው) ። ይህ ባይሆንማ ሃይማኖትን መጫወቻ ካርድ በማድረግ ላይ የሚገኙትን የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችን ከእብደታችሁ ተመለሱ ብለው ሲገስፁ ለመስማትና ለማየት በታደልን ነበር።
እናም የሚሻለው እራስን ከመሸንገል ይልቅ እውነቱን በእውነት ተጋፍጦ ከዚህ ክፉ ደዌ ቢቻል ጨርሶ መላቀቅ ካልሆነ ደግሞ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ አገርን እንዳልነበር ሳያደርግ የሚበጀውን ተገባራዊ ሥራ ሠርቶ መገኘት ነው።
አወንታዊና ዘላቂ መፍትሄ በእውን የምንፈልግ ከሆነ የክፋታችን አስከፊነት የደረሰበትን አደገኛ ጠርዝ ቆም ብሎ ማሰብንና ተገቢውን ማድረግን ይጠይቀናል ።
ነገራችን ሁሉ የቃጠሎው ዋነኛ ምክንያት የሆነውንና እንዳይድን ሆኖ የተበከለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ ከህዝብ፣ በህዝብና ለህዝብ በሆነ ሥርዓተ ፖለቲካ ከመተካት ይልቅ ቃጠሎው በተከሰተ ቁጥር እግዚኦ! ማለት ሆኗል። ይህን አይነቱ እግዚኦታ ደግሞ እራሳችንን ለማታለል በእራሳችን ጭንቅላት ውስጥ የምንቀርፀውን ፈጣሪ ካልሆነ በስተቀር የእውነተኛውንና የእውነቱን አምላክ ትኩረትና ድጋፍ አይስብም። ምክንያቱም እውነተኛው አምላክ ሰው አድርጎ ሲፈጥረን በዚች ምድር ላይ ለመኖር የሚያስችለንን ረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል የሰጠን ጥረታችንን እንዲያግዝ እየጠየቅን (እየፀለይን) ጥረንና ግረን በነፃነት እንድንኖር እንጅ ሌት ተቀን እያለቀስን (እግዚኦ እያልን) እንድንኖር አይደለምና ።
በእውነት ከተነጋገርን ሁለመናችን የፈጣሪና የፍጥረቱ (የሰብአዊነትና የአንድ አገር ልጅነት) ሳይሆን የየጎሳችን/የየዘራችን/የየቋንቋችን እንደሆነ በህገ መንግሥት ተደንግጎ ፣ በፖሊሲ ተነድፎ እና በመዋቅር ተዘርግቶ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የዘለቀ ነው። በአሁኑ ሥርዓተ ኦዴፓ/ኢህአዴግ ሥርዓተ ሥር ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን በየክልልና በየጎሳ ተከፋፍሎ (ተቀራምቶ) አትድረሱብን እኛም አንደርስባችሁም ለማለት የሚያዘጋጅ አስከፊ ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል ። የዚህ ሁሉ ልክ የሌለው ዝቅጠት ምክንያት የሆነውን የኢህአዴግን የፖለቲካ ነቀርሳ ከሥረ መሠረቱ አስወግዶ መሠረታዊና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ሊያስደርግ የሚችል የጋራ ጥረትና ውጤት እውን እስከ አልሆነ ድረስ ለዘመናት ከዘለቅንበት ክፉ አዙሪት ጨርሶ መውጫ የለንም።
ለዚህ ነው የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች (ሰባኪዎች) ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀሙባቸው ከሚወረገረጉ (ከሚቅበዘበዙ) ፖለቲከኞች ጋር አብረው እጥፍ ዘርጋ የማለታቸውን እጅግ ደካማ ወይም የወረደ ባህሪ በቅጡ መፈተሽ አለባቸው ማለት ትክክል የሚሆነው ።
እንደማነኛውም ማህበረሰብ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አለመግባባቶችና ግጭቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከጥንተ ታሪክ ጀምሮ በአንድ ወይም በሌላ መልክ አብሮ የዘለቀውን ህዝብ በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምስቅልቅሉን ካላወጣነው በሚል ያዙንና ልቀቁን የሚሉ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች እብደታቸው ከመቸውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ አደገኛ እየሆነ መጥቷል ። የፖለቲካው አውድ በሚፈልጉት መጠንና ፍጥነት አልቀጣጠልላቸው ሲል በቀላሉ ለማቀጣጠል ያስችሉናል ያሏቸውን የሃይማኖታዊ እምነት አውዶች (ተቋማት) ኢላማዎቻቸው በማድረግ ዘመቻ ላይ ተጠምደዋል። ይህን ማድረጋቸው ግን ያሳዝን እንደ ሆን እንጅ ጨርሶ የሚገርም አይደለም።
ለዚህ አባባሌ (አገላለፄ) ዋነኛ ምክንያቶችን ልግለፅ ፦
1) የግልም ይሁን የቡድን ፍላጎታቸውን በትክክለኛው አስተሳሰብና አካሄድ እውን ለማድረግ ጨርሶ የማይፈልጉና የማይችሉ ሁሉ የሚመርጡት እናተርፍበታለን ብለው የሚያምኑበትን የመተራመስና የማተራመስ መንገድ የመሆኑ ጉዳይ ፈተናውን እጅግ ዘርፈ ብዙና ከባድ አድርጎታል (ያደርገዋል) ፤ ለስሜታዊነት እጅግ ቅርብና በቀላሉ ሊቀጣጠሉ የሚችሉ ጎሰኝነትንና የሃይማኖት እምነት ልዩነትን ዒላማዎቻቸው የማድረጋቸው ጉዳይ ደግሞ ፈተናውን እጅግ ከባድና አደገኛ ያደርገዋል ወይም አድርጎታል።
2) ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደውን ትክክለኛ አስተሳሰብና አካሄድ እንከተላለን በሚሉ የተቀዋሚ ሃይሎች (ወገኖች) በኩል ደግሞ የእኩይ ፖለቲካ ሃይሎችን እብደት በሚመጥን ደረጃ ለመታገልና ድል ለማድረግ በሚያስችል አኳኋን ፀንቶ የመቆሙ ሁኔታ እያደር ከመጠንከር ይልቅ እየተልፈሰፈሰ የመምጣቱ እንቆቅልሽ ለዘመናት የዘለቀው ችግር ከአንዱ ዘርፍ ወደ ሌላው እየተዛመተ ፈተናውን ዘርፈ ብዙና እጅግ መሪር አድርጎታል (ያደርገዋል)። ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች (ስብስቦች) “እውን ሳናደርገው ጨርሶ እረፍት የለንም” ሲሉት የነበሩትን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማሸጋገር ተልእኮና ዓላማ በሸፍጥ ፖለቲካ ለተበከሉና በእራስ ገደብ የለሽ ፖለቲካዊ ዝና ( unlimited political self-aggrandizment) ፍለጋ ለሚቃዡ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች በገፀ በረከትነት ማስረከባቸው ዴሞክራሲያዊት አገር እውን የማድረጉን ትግል እጅግ ከባድ ያደርገዋል (አድርጎታል)።
እናም ከመሪርነቱ የተነሳ ለመቀበል ብንቸገርም ይህ የለውጥ ብልጭታ በሸፍጠኛ የኢህአዴግ ፖለቲከኞችና የተቀዋሚ ድርጅት መሪዎች ነን በሚሉ ፖለቲከኞች የለየለት በእራስ የመቆምና የመተማመን ወይም የአድርባይነት (የአሽቃባጭነት) ቀውስ ምክንያት ፈተናው ከመቅለል ይልቅ እየከበደና እየተወሳሰብ ቢሄድ የሚያስገርመን አይሆንም ። የአሳዛኝነቱ ህመም ግን ብርቱ ነው ።
3) “የዘመናችን ሙሴዎች” በሚል እጅግ የወረደ ግንዛቤና አመለካከት የተቀበልናቸው “ኢህአዴግን አዳሽ” ፖለቲከኞች የአድናቆታችን ድምፅ ገና ከየጆሮዎቻችን ታምቡሮች ሳይጠፋ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ተውኔታቸው እራሱን ግልፅ በማድረግ አገር አተራማሽ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችን ከመታገሥ አልፈው ድጋፍ እየሰጡ በተቃራኔው ግን ይህን የሸፍጥና የከሃዲነት ፖለቲካ በሰላማዊ መንገድ የሚተቹትንና የሚታገሉትን ንፁሃን ዜጎች ያማሳደዱንና የማፈኑን እርምጃ የመቀጠላቸው አባዜ ፈተናውን ዘርፈ ብዙና እጅግ አሳሳቢ ከማድረግ አልፎ የታየውን የለውጥ ብልጭታ ለአሳዛኝ ክሽፈት ቢዳርገው ከቶ የሚገርም አይደለም ።
4) አይነተኛ ከሆኑ የመማርና የመመራመር ጠቀሜታዎች አንዱ ከእራስ አልፎ ለአገር (ለወገን) እና በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚጠቅም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ማስቻሉ ነው። ይህ በጎ የባህሪ ለውጥ ደግሞ ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምን (የሚሰለጥን) የትውልድ ቅብብሎሽ ሰንሰለትን (ድልድይን) ይፈጥራል።
እኛ ግን እንኳን ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን ቅደመ አያቶች እና አያቶች ሳይማሩና ሳይመራመሩ ያቆዩልንን አገር እና ድንቅ ቁሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ ፣ ሞራላዊ ፣ወዘ እሴቶች የማጥፋት ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሳችን የመጠፋፋት እጅግ አስከፊ ባህሪ እና ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀን ዘመን እንቆጥራለን ። በዚህ አስከፊ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን ስለ ስልጣኔና ስለዴሞክራሲ ስንደሰኩር ጨርሶ አናፍርም። ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ብለን የምንጠራቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የበጎ ባህሪ ማበልፀጊያዎች ሳይሆን በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞች (መሪ ተብየዎችን ጨምሮ) ክፉኛ የተበከሉ (የተለከፉ) ወጣቶች መደባደቢያና መጋደያ ሲሆኑ ከማየት የከፋ በትውልድ ላይ የሚፈፀም ወንጀል የለም።
የአንድ አገር (ማህበረሰብ) አስከፊ ውድቀት የሚገለፀው ለሚያጋጥሙት ፈተናዎች ሁሉ በእውቀትና በክህሎት ሊያግዘው የሚችለው (የሚገባው) ትውልድ እራሱ የውድቀት (የቀውስ) ሰለባ ሲሆን ነው። አዎ! በጎሳ/በዘር/ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ክፉኛ የተለከፉ (ያበዱ) ወገኖች ይህን ወጣት ትውልድ ነው ቄሮ፣ኤጀቶ፣ ፋኖ፣ ወዘተ በሚሰኙ ቅርፀ ቢስና ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች አደራጅተው በአገሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በእራሱ እጣ ፈንታ ላይም አስከፊ ውሳኔ እንዲወስን አይዞህ ግፋ የሚሉት።
5) ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸውና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ብዙ የተነገረላቸው ብቻ ሳየሆን በራሳቸው የእለት ከእለት እውነታዎች ናቸው ። በመሆናቸውም ለአሁኑ ከዚህ በላይ ማለት አስፈላጊ ሆኖ አላገኘሁትም። እናም የማልፈው ብዙ ሰው ብዙ ጥያቄና አስተያየት በየአእምሮው ውስጥ ቢመላለስበትም በሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና አገልጋዮች ዙሪያ በግልፅና በቀጥታ መነጋገርን ወይ እንደ ነውር ወይም እንደ ቅስፈት ወይም እራሱን ፈጣሪን እንደ መዳፈር በመቁጠር ወይም ደግሞ ምን አገባኝ በሚል ደካማ አመለካከት ምክንያት ዝምታን ወደ እሚመርጥበት ጉዳይ ነው።
በቅድሚያ አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ ። ምንም እንኳ አስተያየቴ ይበልጥ የሚያተኩረው መሠረታዊ ቀኖናዋንና ትውፊታዊ እሴቶቿን በወግ አጥባቂነት ሳይሆን እንደ አንድ አንብቦና አዳምጦ መረዳት እንደሚችል ዜጋ ተከታይ ስለሆንኩባት የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነት ቢሆንም ሌሎች የክርስትና ክፍሎችም ሆነ የእስልምና እምነት መሪዎችና አገልጋዮች አሳሳቢ ከሆኑ ድክመቶች (ውድቀቶች) ነፃ ናቸው ማለት እግዚአብሔር የማይወደውን ውሸት መዋሸት ነው የሚል አረዳድ እንዳለኝ ግልፅ ይሁንልኝ። ምናልባት ደረጃው ይለያይ እንደሆን እንጅ ከደሙ ንፁ የሆነ የለም (አይኖርም) ለማለት ነው ።
ወደ ዚያው ልለፍ፦
በመሠረቱ የሃይማኖት ተቋማት እንደ እየእምነት ቀኖና እና የአስተምህሮት መርሃቸው (religious dogma and doctrine) ተልእኳቸውን ለመንፈሳዊውም ሆነ ለዓለማዊው ህይወት በሚበጅ ሁኔታ እስከተወጡ ድረስ በየትኛው ማህበረሰባዊ መስተጋብር ውስጥ የሚኖራቸው በጎ (የተቀደሰ) ሚና እና ተፅዕኖ ፈፅሞ የሚያጠያይቅ አይደለም ።
በሌላ በኩል ግን ተቋማቱ እንደ ተቋማት ሳይሆን የተቋማቱ መሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ ሃላፊዎችና አገልጋዮች ከተልእኳቸው የሚመነጨውን ሃላፊነትና ግዴታ ተወጥተዋል ወይ? (እየተወጡ ነው ወይ? ) ብሎ መጠየቅና ሂሳዊ አስተያየትን መግለፅ የእምነት ተቋማትንና መሪዎቻቸውን እንደ መዳፈር መውሰድ ጨርሶ ትክክል አይደለም (አይሆንም)። ከፍ ሲልም የድንቁርና አስተሳሰብ ነው።
የሃይማኖትንና የመንግሥትን (የፖለቲካን) አላስፈላጊ መተሻሸት (ግንኙነት) በግልፅና በቀጥታ ወይም አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት በማይሽኮረመም አኳኋን በሁለቱ ተቋማት ውስጥ ተዋናይ የሆኑትን ወገኖች ( ከፓትርያርክ እስከ ታችኛው አካል እና ከጠቅላይ ሚኒስትር እስከታችኛው ባለሥልጣን/ካድሬ) መተቸት ተቋማቱን በደምሳሳው እንደ መተቸት ወይም እንደ ማጎሳቆል አድርጎ መመልከት ወይም መተርጎም ጨርሶ ትክክል አይሆንም ። ከፍ ሲልም ስሜት አይሰጥም ።
ድህረ ገፅ ላይ እንዳነበብኩት የየሃይማኖቱ ተወካዮች የተወከሉበት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ (inter religious Council) ራዕይ (vision) እንዲህ ይላል ፦”To see a developed Ethiopia where religious communities and their institutions stand together for peace, love, justice, human dignity, mutual respect, tolerance, and religious equality “ (“የየሃይማኖቱ ማህበረሰቦችና ተቋሞቻቸው ለሰላም፣ ለፍቅር ፣ ለፍትህ፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለመከባበር፣ ለመቻቻል፣ እና ለሃይማኖት እኩልነት በአንድነት በመቆም የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት።”) ሲያነቡት እንዴት ያስጎመዣል! መሬት ላይ እየሆነና እየተደረገ ካለው መሪር ሃቅ ጋር ለማመሳከር ሲሞከር ግን ማሳዘን ብቻ ሳይሆን እንዴት ህሊናን ይፈታተናል! እንዴት ልብን ያቆስላል! እውን ይህ ግዙፍና ጥልቅ ራዕይን ከምር የተሸከመ የሃይማኖት ተቋማት አካል (ምክር ቤት) ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው ? የሚል አግራሞትና ቁጭት የተቀላቀለበት ስሜት ይፈጥራል። እናም በፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታዊ ህይወታችንም የገጠመንና እየገጠመን ስላለው ልክ የሌለው ዝቅጠት ከእንዲህ አይነት መሬት ከተዘረጋ መሪር እውነታ በላይ የሚነግረን ከቶ የለም።
ሌላው ቢቀር የአንዱ የእምነት ተቋማት ፣ አገልጋዮችና ተከታዮች የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነትን እና የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካን የሥልጣን ጥም ማስፈፀሚያቸው ለማድረግ የሚቃዡ ወገኖችን በግልፅና በፀና የጋራ አቋም በማውገዝ አደብ እንዲገዙ ለመንገር ፣ እና እንዲሁም በየተዋረዱ ሥልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ከዚህ የባሰ ክፉ ነገር ምን እንደሚጠብቁና ለምንና ለማንስ እንደቆሙ ለመጠየቅ ወኔ የሌለው ሃይማኖታዊ ምክር ቤትን እንዴት መግለፅ እንደሚቻል መልሱን የአገርና የወገን ጉዳይ በእውን ለሚያስባቸው ወገኖቼ እተወዋለሁ ። የዚህ ምክር ቤት አባላት በወረቀት ላይ አስፍረው ግድግዳ ላይ የሰቀሏቸውን የራዕይ ሃይለ ቃሎች ቀና ብሎ በጥሞና ከልብ ቢያነቧቸው ምን እንደሚሉ አላውቅም ።
የአቤ ጎበኛ አልወለድም ለሰብአዊ መብት መከበር እና ለነፃነትና ለፍትህ መስፈን ፀንቶ በመቆሙ ምክንያት ግፈኛ ገዥዎች በጥይት ደብድበው ሊገሉት ሲዘጋጁና መናገር የሚፈልገው ካለ መናገር እንደሚችል ሲጠይቁት ” እያንዳንዱ ሰው በዓለም ላይ የሰዎች መልካም ኑሮ ጠላት ያሆነው ክፋትና የሰው ዘር መልካም ነገር መሠረት የሆነው ደግነት ሲዋጉ መኖራቸውን ይወቅ ። የሰውን መልካም እድል ያበላሹትም ከክፋት የሚመነጩ ጠንቆች ናቸው ። ሰዎች እራሳቸውን ከክፋት ነፃ ማድረግ ቢያቅታቸው ለመጥፎ ሥራቸው ሃላፊ ሆኖ እንዲወቀስ ሰይጣን የተባለውን ስም ያቀርባሉ ። መልካም እንሥራ ስትሉ ሰይጣን መጥቶ የከለከላችሁ መቼ ነው? ሰይጣንስ መጥቶ ክፉ ሥሩ ያላችሁ መቼ ነው? ከሰይጣን የሚከፉት ክፉ ሰዎች ናቸው። በስምም አታምልኩ። የክርስቲያንነት ፍሬ ክርስቲያንነት የሚያዛቸውን መልካም ነገሮች መፈፀም እንጅ በስም ክርስቲያን መባል አይደለም። …” ይላቸዋል።
በማስቀጠልም ለሰብአዊ መብት መከበር እና ለነፃነትና ለፍትህ መስፈን ሲታገልና ሲያታግል፣ በግፈኛ ገዥዎች ሲንገላታ እና በመጨረሻም የግፍ ፍርድ ሲፈረድበት ግፈኛ ገዥዎችን ለምንና እንዴት ? ብለው ለመጠየቅ ወኔው ለከዳቸውና በጥይት ተደብድቦ የሞትን ፅዋ መጎንጨቱን ለማየት ወደ ተገኙት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ቄሶች በንዴት ዘወር ብሎ ” እናንት የተረት ቄሶች! ሰው ነፍሱና ሥጋው ሲለያዩ ብዙ ሙግት አለበት የምትሉትና ሰውን የምታስፈራሩበት ተረት ከንቱ መሆኑን ተመልከቱት ። እኔ አሁን ግንባሬን ወይም ደረቴን በጥይት ስመታ በደቂቃዎች ውስጥ እሞታለሁ ። እንግዲህ እናንተ በፃእዕረ ሞት ላይ ከመልአከ ሞት ጋር ይደረጋል የምትሉትን ረጅም ጥያቄና መልስ (ኢንተርቪው) መቼ ላደርገው ነው? እንዲያው ሁላችሁም ህዝብን ስታደነቁሩ ፣ስታስፈራሩና ስታስጨንቁ መኖርን ስለፈጠራችሁ እግዚአብሔር ብላችሁ ተው” የሚል የመጨረሻ መልእክቱን ይነግራቸዋል ።
ይህን መሪር ሃቅ በመጨራሻው ሰዓት ከመናገሩ በፊት የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደበት ለፍርድ አስፈፃሚዎች የመቃብሩን ጉድጓድ ሌሎች ምስኪኖችን ከማድከም እራሱ እንዲቆፍር ይፈቅዱለት ዘንድ ሲጠይቃቸው ፈቀዱለትና “ከየትኛው አይነት ቤተ ክርስቲያን መቀበር ትፈልጋለህ ?” ሲሉት ከህዝቡ መካከል የነበሩት የልዩ ልዩ ቤተ ክርስቲያን ቄሶች እየጮሁ ሁሎችም “ይህ አረመኔ ስንት ቅዱሶች ባረፉበት የእኛ መካነ መቃብር አይቀበርም” ሲሉ ” እናንተ ዋሾዎች! እየሱስ ክርስቶስ ‘ለቀበሮዎች ዋሻ ፣ ለወፎች ጎጆ አላቸው ፤ ለሰው ልጅ ግን እራሱን የሚያስጠጋበት ቤት የለውም’ ብሎ ነበር። አሁንም ለእናንተ ለቀበሮዎች በድን የተፈቀደው ዋሻ ለእኔ የማይፈቀድ ሆነ ። ለእኔስ ስንት ውሸታሞችና አጭበርባሪዎች ከተቀበሩበት ቦታ ይልቅ ንፁሁ ሜዳ የሻለኛል” በሚል መሪር እውነት እንደሞገታቸው ይነግረናል ።
በመጨረሻም የእርሱ እጣ እንዳይገጥማቸው (እንዳይጠብቃቸው) አጥብቆ ለሚያስብላቸው ህፃናትም በሥነ ግጥም ፦
እኔስ ይኸው አረፍሁ መገላገሌ ነው ከዚህ ዓለም ጣጣ ፣
ወዮለት ለህፃን ወደ ዚች ክፉ ዓለም ገና ለሚመጣ ።
እናንተ ህፃናት እውነትን ይዛችሁ እንግዲህ ወደ ፊት የምትወለዱ ፣
ምንም የማታውቁት የጥንት መምጫችሁን
ደግሞ የማታውቁት የት እንደምትሄዱ፣
እንዴት ልንገራችሁ መራራ መሆኑን
የዚህ ዓለም ጣጣ መዘዙና ጉዱ፣
እኔስ ምንም አልቻልሁ ! ሳትፈቅዱ ሳትወዱ ፣
እናንተው መጥታችሁ እናንተው ፍረዱ።” ይላቸዋል ።
በእውነት ከተነጋገርን ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን (ከ1960ዎቹ ) በኋላም አሁን የምንገኝበት መሪር ሃቅ የባሰ እንጅ ከቶ የተሻለ አይደለም ። “የግፍና የውርደት ቀንበራችሁን መሸከም በቃኝ” የሚለውን ንፁህ ዜጋ ሁሉ አስበውና ተዘጋጅተው በግፍ አገዛዛቸው ሰንሰለት የሚጠረንፉትንና በጨካኝ ሰይፋቸው የሚሰይፉትን ገዥ ቡድኖች “እንዲህ አይነቱ እኩይ ባህሪና ተግባር ጨርሶ በሰይጣን የሚመካኝ አይደለምና በአምሳሉ ከፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር ላይ ሰንሰለታችሁንና ሰይፋችሁ አንሱ” ለማለት የተሳነው የሃይማኖት ምክር ቤት፣ መሪ ወይም ሰባኪ ወይም ፓስተር ወይም መምህር ወይም ቄስ ወይም ሼህ ሁሉንም እኩይ ባህሪና ተግባር ጠቅልሎ ሰይጣን ለተባለው ስም በማሸከም ፖለቲከኞችን (ገዥዎችን) “እነሱ እኮ አይደሉም ፤ ሰይጣን ነው የሚጫወትባቸው (የሚያሳስታቸው) “ በማለት ከንፈር ያስመጥጥላቸዋል ፤ እግዚኦ! በሉላቸው ያሰኝላቸዋል። አዎ! አሁንም በእውነት ስለ እውነት መነጋገሩ እያስፈራን መስሎና አስመስሎ በመኖሩ (መኖር ከተባለ) ክፉ ልማድ እንቀጥል ካላልን በስተቀር እፊት ለፊታችን ያፈጠጠው መሪር ሃቅ ይኸው ነው።
እናም በዚህ ረገድ ሲገጥመን የኖረውና አሁንም እየገጠመን ያለው ፈተና በፖለቲካውና በሌሎች ዘርፎች ከገጠሙንና እየገጠሙን ካሉ ፈተናዎች የቀለለ ነው ለማለት የሚያሰኝ አሳማኝ ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሃይማኖታዊ እምነት ከሞራል፣ ከሥነ ምግባር፣ ከሥነ ልቦና ፣ እና በአጠቃላይ ከውስጠ ነፍስ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ የሚሸከመው ተልእኮና ሃላፊነትም በዚያው ልክ ስፋትና ጥልቀት ያለው ነው ። ለዚህ ነው አገራችን የሁለት አንጋፋና ታላላቅ (ክርስትና እና እስልምና) ሃይማኖት ተቋማት ባለቤት የመሆኗን ያህል በለውጥ ስም ጭቆና እና ግፍን እያፈራረቁ በንፁሃን ዜጎቿ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ የሚያወርዱት ገዥዎችን ደፍረው የሚገስፁ፣እና አማኙንም “ዝም ብለህ እግዚኦ በል “ ከማለት ይልቅ “ከእግዚኦታህ ጋር ግፈኛ ገዥዎችን ለማስወገድ እና ነፃነትንና ፍትህን ለመጎናፀፍ ብቸኛው መፍትሄ በአብሮነት፣ በማይዋዥቅ የጋራ ራዕይ ፣ በማይናወጥ የጋራ መርህና ፅዕናት መታገል ግድ ነው” ብለው ለማስተማር የሚደፍሩ የሃይማኖት መሪዎችንና አስተማሪዎችን (ሰባኪዎችን) ፈልጎ ማግኘት ብርቅየ የሆነብን።
ፖለቲከኞችም በአንደ በኩል “ንስሃ ገብተናልና እመኑን” የሚል ድንቅ ዲስኩር እየደሰኮሩ በሌላ በኩል ግን ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተዘፍቀው ከኖሩበት ክፉ የሸፍጥ ፖለቲካ ልክፍት መውጣት አቅቷቸው ያን የለመደባቸውን የጭቃ ጅራፍ ከየአለበት እየመዘዙ መሠረታዊ መብታቸውን በጠየቁ ንፁሃን ዜጎች ላይ ሲያሳርፉ ማየት በእጅጉ ልብ ይሰብራል። እናም ይህ ሁሉ ግፍ ለምንና እንዴት? ብሎ ከምር የሚቆጣ ብቻ ሳይሆን ንፁሃንን ለመታደግ እውነተኛ ክርስቶሳዊ ተልእኮውን የሚወጣ ( የሚያከናውን ) የሃይማኖት መሪና አስተማሪ (ሰባኪ) ፈልጎ ለማግኘት ከመቸገር የከፋ የሃይማኖታዊ እምነት ፈተና የሚኖር አይመስለኝም።ቃለ እግዚአብሔርን ማነብነቡና ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት መባሉ በቂ ነው ካላልን በስተቀር ።
ለነገሩ ንስሃ አንዳች አይነት ረቂቅ ሚስጥር ሳይሆን ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ጥሮና ግሮ እንዲኖር በመሆኑ እና ለመኖርም በሚያደርገው የኑሮ ግብ ግብ ሂደት አውቆም ይሁን ሳያውቅ ስህተትን ደጋግሞ ከመሥራት ልማድ ለመውጣት ያግዘው ዘንድ ከፍጡራን ሁሉ ለይቶ የሰጠው እራስን የማረም ዘዴ ነው ። ሌላ ምንም አይነት ረቁቅና ለተለዩ ሰዎች ብቻ የሚገለፅ ሚስጥር አይደለም። ሰይጣን የሚለው ስምም ከስህተት ለመማር የሚሳነው የሰው ልጅ ክፉ ባህሪ ሌላው መጠሪያ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምትሃታዊ ወይም ከሰው ልጅ ምንነትና ማንነት ተነጥሎ የሚኖርና ሲፈልግ እላያችን ላይ ጉብ ብሎ የሚጋልበን ነገር አይደለም ። ለዚህ ነው በሃይማኖት መሪዎች ቡራኬ የተቸረው የፖለቲከኞች ንስሃና ይቅር በሉን ባይነት ብዙም ሳይራመድ የፖለቲካ ሸፍጥና ቅሌት ሰለባ የሆነው።
የሃይማኖት ተቋማት ክርስቶስ የምድሩን ከሰማዩ ዓለም እየነጣጠለና ጨርሶ ተአምራዊና የማይጨበጥ እያደረገ በማስተማር “ከዚህ መውጣት ኅጢአት ነው” ብሎ ያወጀ በሚመስል ሁኔታ የዋሁን አማኝ ህዝብ እግዚኦ ከማለት ውጭ መፍትሄ እንደሌለ ሲሰብኩት (ሲያደነቁሩት ማለት ሳይሻል አይቀርም) መስማትና ማየት ስለሰማያዊውም ሆነ ስለምድራዊው ህይወት ቅን አመለካከት ያለውን የአገሬ ሰው ግራ ቢያጋባው ከቶ አይገርምም።
ይህ ብቻ አይደለም ። በየቤተ እምነቱ (ገዳማትን ጨምሮ) በበረሃ መናኝነትና በፈዋሽነት ወይም በሰባኪነት ወይም በመምህርነት ወይም በትንቢት ተናጋሪነት ስም የሚተወነው የለየለት ተራ ተውኔት የቅን አሳቢና እውነትን ፈላጊ የአገሬ ሰው ህሊናን ቢፈታተነው ከቶ የሚገርም አይሆንም ። ሊገርመን ሳይሆን ሊያሳስበን የሚገባው የየሃይማኖቱ ቤተ እምነቶች (ተቋማት) የእንዲህ አይነት የለየለት ተራ የግል ዝና ማስተዋወቂያና የኑሮ ማሻሻያ ተውኔት አውዶች ሲሆኑ ለምንና እንዴት ? ብሎ ለመጠየቅና ለመረዳት የሚደፍር ወይም የሚፈልግ መልካምና እውነተኛ አማኝ ዜጋ ፈልጎ ማግኘት ቀላል ያለመሆኑ ጉዳይ ነው።
ከአንዳንድ የበቃን መምህራንና ባህታዊያን ነን ከሚሉ ወገኖች የሚሰማውና የሚታየው “የተአምራዊ ፈዋሽነት” ተውኔትና ትርክት ለእውነተኛዋ ቤተ እምነትና ለእውነተኛው አምላክ መሠረታዊ ምንነትና ማንነት ጨርሶ የሚጠቅም አይደለምና ልብ ሊባል ይገባዋል። ይህ አይነት ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴ በእጅጉ የማይመቻቸው ብቻ ሳይሆን ቅስፈት ያስከትላል ብለው የሚሰጉ እጅግ በርካታ ቅን ወገኖች እንደሚኖሩ በሚገባ እረዳለሁ ። መልሴ ግን በገሃድ ስለሚታየው መሪር እውነት ሃሳብን መግለፅ የሃይማኖት መሪዎችንና መምህራንን ከመዳፈር ወይም ካለማክበር ጋር አያይዞ የሚቀየም ወይም የሚቆጣ የእውነት አምላክ የለምና አትጨነቁ የሚል ነው። እውነተኛውን አምላክ ቅር የሚያሰኘው ወይም የሚያስቀይመው እውነቱን አለመናገር ነውና ።
ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር በተስፋና በአስጨናቂ ሥጋት እየተወጠረ በአእምሮና በሥነ ልቦና ቀውስ ነውጥ ክፉኛ የሚመታውን የዋህና መከረኛ ህዝብ ሃይማኖታዊውን ትምህርት ከገሃዱን ዓለም እውነታ ጋር ትርጉም ባለው ሁኔታ እያገናኙ እና ከምር ከሆነ የእባክህ አግዘን ! ፀሎት ጋር እያዋሃዱ በማስተማር ከዚህ አዙሪት የሚወጣበትን መንገድ ከማሳየት ይልቅ በሃይማኖታዊ እምነት ስም “በተውኔታዊ የፈውስ” ትርክት የባሰ ግራ ማጋባት ቢያንስ ሞራላዊ ውደቀት ነው ። ከፍ ሲል ደግሞ ኅጢአት እንጅ ፅድቅ አይደለም። ለእራሳችን “ተውኔተ ፈውስ” በእራሳችን አእምሮ የምንፈጥረው አምላክ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ አይነቱን ተውኔት እውነተኛው አምላክ ባርኮ ይቀበለዋል የሚል እምነት የለኝም ።
“እንዲህ አይነቱ ተውኔት ለቤተ እምነት (ለእግዚአብሔር አገልግሎት) የሚውል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስለሚጠቅም የተቀደሰ ነው” የሚል መከራከሪያ ካለ ደግሞ ጨርሶ ሃፍረተ ቢስ የሆነ ስህተት ነው።
ለመሆኑ የተሸከሙትን የክርስቶስ መስቀል ከፍ አድርገው ለአገሩም ሆነ ለእምነቱ ቀናኢ የሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘመናት በመከራና በውርደት ቀንበር ሥር የገዙትንና አሁንም ከጎሳ/ከዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍት መላቀቅ ተስኗቸው አገርን ምስቅልቅሉን እያወጡ ያሉትን ገዥዎችና ሌሎች ፖለቲከኞች “ጠብቁልኝ ያለንን በጎችን (ህዝቦችን) ልቀቁልንና በነፃነትና በፍትህ ይኑሩ!” ለማለት ወኔ የሌላቸው መምህራንና ባህታዊያን ነን ባዮች በየትኛው መንፈሳዊ አቅማቸውና ችሎታቸው ነው ኑንና እንፈውሳችሁ የሚሉት?
በእውነት እየተነጋገርን ከሆነ እጅግ እኩይ በሆነው የጎሳ/የዘር/የመንደር ፖለቲካ ማንነት እብደት ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ቤተ እምነት ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ጉዳት (በደል) በእጅጉ የከፋ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም።
ይህ ከደመነፍስ እንስሳት ባህሪና ተግባር በእጅጉ የወረደ አስተሳሰብና ድርጊት የሃይማኖቱን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የማነኛውንም ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ቅን ኢትዮጵያዊ ህሊና በእጅጉ የሚፈታተን ከባድ ፈተና ነው። በሌላ በኩል ግን ይህ ለምን ሆነ ? የሚለውን ፈታኝ ጥያቄ ከእራስ እያሸሹ በደል ለሚፈፅመው አካል ወይም ሰይጣን ለሚባለው ስም ብቻ ለማሸከም የሚደሰኮረው ስብከትና የሚነበነበው ቃለ ነቢብ ለምድሩም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው የሰማያዊው ዓለም ህይወት የሚጠቅም አይደለም ።
ለምን? ቢባል ቃል ከመሪሩ የገሃዱ ዓለም እውነታ ጋር ተዋህዶ የሚጨበጥ ህይወትን ካልወለደ ጨርሶ ትርጉም የለውምና ነው። እኛም ከዘመናት የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት ከተቸገርንባቸው ከባድ ፈተናዎች አንዱ ይኸው ነው ። በማጥፋትና በመጠፋፋት የጎሳ/የዘር/የቋንቋ/የሃይማኖት ማንነት የተለከፉ ወገኖችን አደብ የሚገዙ ከሆነ እንዲገዙ ለማድረግ አሻፈረኝ የሚሉ ከሆነ ደግሞ ለህዝብ መብት መከበርና ለአገር ደህንነት ሲባል በህግ አግባብ የሚያስተናግድ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አምጦ መውለድን ግድ ይለናል ። ይህ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ እራስን ከእግዚኦታ ፀሎት አልፎ መሬት ላይ ለሚታይ ሥራ በአርአያነት ማቅረብን ይጠይቃል ። ይህን ሆኖና አድርጎ መገኘትን እየሸሸን አስከፊ ችግር በገጠመን ቁጥር የማሳሰቢያና የማስጠንቀቂያ መግለጫ ማዥጎድጎድና የምሬት ጩኸት ማስተጋባት የህመምን ስቃይ ለጊዜው ከማስታገሥ አያልፍም ።
እስኪ ልብ እንበል!
ለስንት ዘመን መሬት ላይ ያለውን መሪር ሃቅ እየሸሸን ባዶ የፖለቲካና የሃይማኖት ዲስኩርና ትርክት ስንደሰኩርና ስንተርክ ኖርን ?
ስንት ጊዜስ በዴሞክራሲ ማልንና ተገዘተን?
ስንት ጊዜ ድርጊት አልባ በሆነ የተለምዶ ፀሎትና እግዚኦታ ፈጣሪን ና ውረድ እያልን አስቸገርን ?
ስንት ጊዜ በመከረኛው ህዝብ ስም ድርጊት አልባ ወይም አጭበርባሪ የሆነ የመልካም አስተዳደርን የማስፈን መሃላ ፈፀምን?
ስንት ጊዜ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ስም ዘመርንና ቅኔ ተቀኘን?
ስንትስ ጊዜ ዘፈንና ፎከርን?
ስንት ጊዜ ጀግና እና አርበኛ መሪዎችንንና አያቶቻችንን ሆነን ታላላቅ ተውኔቶችን ተወን?
ስንት ጊዜ ህሊናን ጨምድደው የሚያስጨንቁ ሥነ ግጥሞችን አነበብን ወይም አስነበብን?
ስንትስ ጊዜ የሃይማኖት ተቋማትን ለእኩይ ፖለቲካ ሰለባነት አመቻችተን ሰጠን?
ስንት ጊዜ ከመጋረጃው ጀርባ ከግፈኞች ጋር እየዋልንና ከአድርባይነት ጋር ፍቅር በፍቅር እየሆን በፈረደበት የሃይማኖት አውደ ምህረትና አደባባይ ላይ እፁብ ድንቅ ዲስኩር ደሰኮርን ?
ስንት ጊዜ ግፈኛ ገዥዎችን በሃይማኖት የአርበኝነት ወኔ ገስፀን የስንት ንፁሃንን ህይወት ከቁም ስቃይና ከሞት ታደግን?
ስንት ጊዜ ተስማምተን ስንት ጊዜ አፈረስንና ፈራረስን ?
አዎ! ስለ የትኛውም ቤተ እምነት መጠቃትና መሳደድ አምርሮ መነሳት ከተገቢም በላይ ተገቢ ነውና የሰሞኑን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መሪዎችንና ተከታዮችን ቁጣና ምሬት አቃልሎ የሚያይ ቅንና ሰላም ፈላጊ ኢትዮጵያዊ የሚኖር አይመስለኝም።
የዚህ አግባብነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ በተዋህዶ ኦርቶዶክስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የክርስቲያን ሃይማኖቶችና የእሰልምና ሃይማኖት መሪዎች ላይ ጥያቄና ሂሳዊ አስተያየት መሰንዘር ግን ከተገቢም በላይ ተገቢ ነው ። በእውነት እየተነጋገርን ከሆነ ግልፅና ቀጥተኛ የሆኑ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በቅንነት ፣ በአስተዋይነት ፣ በመልካም አስተማሪነትና በገንቢነት ከማስተናገድ ይልቅ “እኔን/እኛን የደፈር ፈጣሪን የደፈረ ነው” የሚል አይነት ደምሳሳና ልፍስፍስ ምክንያት ማቅረብ ለምድሩም ሆነ ተስፉ ለምናደርገው የሰማይ ቤት ጨርሶ አይጠቅምምና ከተለመደ ልማድ በቀላሉ ለመውጣት ብንቸገረም የግደ መድፈር ይኖርብናል።
የፈተናው አስቀያሚነት ከአንድ ሃይማኖት የአስከፊ ጥቃት ሰለባ ከመሆን ወይም ካለመሆን ጋር ብቻ የሚታይ ሳይሆን የምንኖርበት ሥርዓተ ማህበረሰብ እና ሥርዓተ ፖለቲካ በጠና የታወከ መሆነን ከምር ከመገንዘብና ለዚሁ የሚመጥን የመፍትሄ እርምጃ ከመውሰድ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወይም የሌላን ሃይማኖታዊ ተቋም መጠቃትም ከዚህ መፍትሄ አዘል አስተሳሰብና አካሄድ ውጭ የሚታይ አይደለም ።
ዘርፈ ብዙነቱና አስከፊነቱ ይበልጥ እየከፋ በመሄድ ላይ ያለውን ዘመን ጠገብ ፈተና በመጣንበትና እየሄድንበት ባለው እጅግ የወረደ አስተሳሰብና አካሄድ ጨርሶ ልንወጣው አንችልም። የዚህ አይነት እጅግ አስከፊ ፈተና ዋናው መፈልፈያውና ማሰራጫው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ ተመሥርቶ ህዝብ እንደ ህዝብ ለዘመናት ተሳስሮ (ተጋምዶ) የኖረባቸውን ወርቃማ የማህበራዊ ፣ የባህል ፣ የታሪክ ፣ የሞራል ፣ የሃይማኖት ፣ ወዘተ ገመዶች ( social , cultural , historical , moral, religious , … fabrics) በመበጣጠስ የመከራና የውርደት አገዛዝን ሲያራምድ የቆየውና አሁንም በተሃድሶ ስም ጉልቾችንና የጉልቾችን አለቃ እያፈራረቀ የቀጠለው የቀድሞው የህወሃት/ኢህአዴግና የአሁኑ የኦዴፓ/ኢህአዴግ ሥርዓት ነው። ይህን መሪር ሃቅ ተቀብለን በየፈርጁ የምናደርገው ጥረት (ትግል) እንደተጠበቀ ሆኖ ዋነኛው የትግል ትኩረታችን ይህንኑ የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓተ ኦዴፓ/ኢህአዴግ በእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሥርዓት መተካት ላይ ማድረግን ግድ ይለናል ። ይህን ዒላማ እየሳትን የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞችና አክራሪ የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ልክፍተኞች መልሰው እያንሰራፉ መላልሰው የመከራና የውርደት ቀንበር ሲያሸክሙን በየተራ እየየና እግዚኦ እያልን የቁም ሞት የመሞቱን አስከፊ ልማድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እምቢ እንበለው!
ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ የሰብአዊና የዜግነት መብቶች እንዲከበሩ ከማድረግ (ከማስደረግ) እና አገርን እንደ አገር ከማቆየትና ለዜጎቿ የምትመቸ ከማድረክ አንፃር የሃይማኖት መሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ አገልጋዮች ያለባቸው ሃላፊነት እጥፍ ድርብ (ምድራዊና ሰማያዊ) ነውና ከምር እራሳቸውን ሊመረምሩና ተልእኳቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል።