የዛፎች የህልውና ተጋድሎ – በላይነህ አባተ

የዛፎች የህልውና ተጋድሎ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

አብዛኛው የዓለም ታሪክ የአጥፊና የጠፊን የሞት ሽረት ትግል ከትቦ የያዘ ስንክሳር ነው፡፡ የዚህ ስንክሳር አካል የሆነችዋ ዕልም የምትባለዋ የዛፎች አገር ታሪክም ዛፎቿ ላለመጥፋት ከአጥፊዎች ጋር ያደረጉት ተጋድሎ ታሪክ ነው፡፡ ይህቺን የዛፎች አገር በተለያዬ ጊዜ የቅዠት ሰዎች ሊደፍሯት ቢሞክሩም ጥቅጥቅ ደኗ ስለሚያስፈራና አንበሶችና ነብሮችም ስለሚኖሩባት ሳትደፈር ትኖር ነበር፡፡ የቅዠት ሰዎች ዕልምን በእሳት ሊያቃጥሉ ደጋግመው ቢሞክሩም በዕልም ምድር ደረቅ ስላልነበረና ዝናብም ስለማይጠፋ የማቃጠሉ ተንኮል ሳይሳካ ቀረ፡፡ የድንጋይ ዘመን ሲገባደድና ባልጩት በብረት መሳርያ ሲተካ የቅዠት ሰዎች ዕልምን በምሳር ለመድፈር የስለላ ጉንጉን መጎንጎንና መረብ መዘርጋት ጀመሩ፡፡

 

የቅዠት ሰዎች የስለላ መረብ በይበልጥ የተዘረጋው ከጠማማ ዛፎች ዙሪያ ነበር፡፡ ጠማማ ዛፎች ቀጥ ብለው መውጣትና መቆም ስለማይችሉ ቀጥ ያሉት ዛፎች “ጎባጦች፣አጎብዳጆችና አጎንባሾች” እያሉ ይንቋቸው ነበር፡፡ ጠማማ ዛፎች በፈንታቸው ቀጥ ያሉ ዛፎችን እንደ ረጅሟ የአለቃ ገብረሃና ሚስት ወይዘሮ ማዘንጊያ ሽቅብ እያዩ “ሥራቸውን ቢቦድሱት ማየትና መስማት የማይችሉ ቀውላሎች!” እያሉ ይሰድቧቸው ነበር፡፡ ይኸንን በጠማማና በቀጥተኛ ዛፎች መካከል ያለውን ቅራኔ የቅዥት ሰዎች በዘረጉት የሥለላ መረባቸው አጠኑ፡፡ በጥናታቸውም የዕልም አገር ሳትደፈር የኖረቸው በዛፎች ትብብር በተለይም ደግሞ በቀጥተኛ ዛፎች ቀጥ ያለ አቋቋም፣ አስፈሪነትና ግርማ ሞገስ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ በዚህ ግንዛቤም ጠማሞችን ከቀጥተኞች አጣልተው ጠማማዎቹን ከጎናቸው የሚያሰልፉበትንና ቀጥተኞችን የሚያጠፉበትን ሰነድ አረቀቁ፡፡ “ቀጥ ያሉ ዛፎች እናንተን ጠማሞችን እንኳን እንደ ዛፍ እንደ ደን አካልም አይቆጥሯችሁ፡፡ እንደ ደን አካል ስለማይቆጥሯችሁም አፈሩን፣ አየሩንና ፀሐዩንም ተቆጣጥረው በአካል እንድትጣመሙና እንድትቀጭጩ አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት ዓይን ለዓይን ሳይሆን ዝቅዝቅ እያዩአችሁ ይኖራሉ፡። መንፈሳችሁንም እንደ ጥጥ አሳስተውና በራስ የመተማመን ሥነ-ልቡናችሁን እንደ ሙክት ፍሬ ሰልበው እንደ ኩምቢ አቀርቅራችሁ ምድርን ብቻ ስታዩ እንድትኖሩ አስገደዷችሁ” እያሉ ያለመታከት ሰበኳቸው፡፡

 

የቅዠት ሰዎችን ስብከት የሰሙ እድሜ ጠጋብ ጠማማ ዛፎች “ይህንን ዛፍን እርስ በርሱ የሚያጋጭ መሰሪ የባዕድ ስብከት አትስሙ! ተቀጥተኛ ዛፎች የበለጠ የቅዠት ሰዎች ዘመድና ወዳጅ ሊሆኑን አይችሉም፤ በመካከላችን ያለውን ችግር ራሳችን እንፈታዋለን” ብለው ለግላጋ ዛፎችን እያስተማሩ ለብዙ ዓመታት የቅዠትን ሰዎች ተንኮል አከሸፉ፡፡ ዳሩ ግን ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የቅዠት ሰዎች ያላሰለሰ ስብከት የጠማማ ዛፎችን ልብ እንደ ልጃገረድ ማሽኮርመምና ማማለል ቻለ፡፡ አሽኮርማሚዎቹ የቅዠት ሰዎች “ከጠማማ ዛፎች የምንፈልገው ትንሽ እርዳታ ነው፡፡ ከጎበጡት ቅርንጫፎቻችሁ የተወሰኑትን ብትለግሱን ቀጥ ያሉ ዛፎችን አጥፍተን የዕልምን ምድር የጠማማ ዛፎች ምድር እናደርጋታለን፡፡ ሥሟንም ከዕልም ዛፎች አገር ወደ የጠማማ ዛፎች አገር እንቀይረዋለን” ብለው ሲሰብኳቸው ጠማሞች ቀጥ ያሉ ዛፎች እንደ ዳይኖሰር ጠፍተው የዕልም ምድር በጠማማ ዛፎች ስትሸፈንና ሥሟም የጠማማ ዛፎች አገር ሲሆን ታያቸውና ጎባጣ ቅርንጫፎቻቸውን ለቅዠት ሰዎች ለማበርከት እንደ አዲስ አባባ የስኳርና የዘይት ሰለፈኞች ተራ ለማያዝ ተሽቀዳደሙ፡፡ ይኸንን የጠማማ ዛፎች እሽቅድድም የተመለከቱ የቅዠት ሰዎችም ከጎባጣ ቅርንጫፎች የሚጠርቡትን እጀታ ከምሳር አጋብተው የዕልምን ዛፎች ሲከተክቱ፤ በዚህ ክትከታ ምክንያትም ቀጥተኛና ጠማማ ዛፎች ተጣልተው እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ፤ በዚህ የመተላለቅ ግርግርም የደኑ አውሬዎች ደንበረው ሲጠፉና አውሬዎች ሲጠፉም የዕልምን ምድር እንደልባቸው ሲጠቀሙ ታያቸውና ተደሰቱ፡፡

 

የቅዠት ሰዎች ጎባጣ ቅርንጫፎችን ከጠማማ ዛፎች ተረከቡና “የተደበቀው ውበታችሁ እንዲወጣና እንድታምሩ ጠርበን ቅቤ እንቀባችሁ” በሚል ማተላለያ እየጠረቡና ቅቤ እየቀቡ እጀታ ሰሯቸው፡፡ እጀታ ከሰሯቸው በኋላም “የበለጠ ለማስጌጥና ዘመናዊ ለማድረግ” በሚል መሸንገያ ምሳሮችን እንደ ሎቲ ሰኩባቸው፡፡ እጀታዎች ምሳሮች እንደ ሎቲ ሲሰካባቸው ከዛፎች ባህል እጅግ ራቁና እንደ አካላቸው ሁሉ የመንፈስ ጉብጥናም ተጠናወታቸው፡፡ የመንፈስ ጉብጥና ስለተጠናወታቸውም የሚያብረቀርቁትን የምሳር ሎቲዎች ስላንጠለጠሉ ከጥንታዊ ዛፍነት ወደ ዘመናዊ ብረትነት የተቀየሩ መሰላቸው። የቅዠት ሰዎች ዛፎችን ለመቁረት ሲሄዱ በትከሻቸው ሲሸከሟቸው ያከበሯቸው መሰላቸው፡፡ እንደ እጀታዎች ጠማማ ዛፎችም እጀታዎችን ከቅዠት ሰዎች ትከሻ ሲመለከቱ “እውነትም የቅዠት ሰዎች ለጠማማ ዛፎች ክብር ያላቸው፤ ለፍትህ የቆሙና ጠማማ ዛፎችን ከቀትተኛ ዛፎች ጭቆና ለማላቀቅ ከሰማይ የወረዱ መላእክት” አሉና ሰገዱላቸው፡፡

 

የቅዠት ሰዎች በጠማማ ዛፎች መሪነት ከእጀታ በተሰካ ምሳር ቀጥ ያሉ ዛፎችን እየገነደሱ የመርካቶ ዘራፊ ጂዶ እንደመታው ነጋዴ መዘንደብ ሲጀምሩ በዕልም ምድር ድንጋጤና ውዥምበር ተፈጠረ፡፡ ውዥንብሩ እየጠራ ሲሄድ ዛፎች በተናጥል በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከቅዠት ሰዎች እየወደቁ ወገባቸውን ሰበሩ፣ ከፊሎቹም የምሳርን ጥርስ አዶለዶሙ፣ ሌሎችም እጀታዎችን እየታገሉ ሰንበር በስንበር አደረጉ፡፡ በዚህ ትንቅንቅ ልባቸው እንደ ቅቤ የቀለጡና ውሀ ሲመጡና ኦክሲጂን ሲፀዳዱ ኖረው አፈር ለመሆን የወሰኑ መሐል ሰፋሪ ዛፎች ደሞ “ጊዜ እስኪያልፍ ያባትህ ባርያ ይግዛህ!” በሚል የጡርቂዎች ፈሊጥ ከጠማማ ዛፎች ተመሳስለው መከራን ለማለፍ ማንነታቸውን ለመቀየር መጉበጥ ጀመሩ፡፡ በአደባባይ ቀጥተኛ ዛፎች እንደሆኑ ለመናገር ተቸጋገሩ፡፡

 

ከብዙ እልቂት በኋላ ቀጥተኛ ዛፎች በምስጢር ተሰባሰቡና “በምን ምክንያት ለእልቂት በቃን፣ ማንስ ፈጀን? እንዴትስ ራሳችንን መከላከል አቃተን” እያሉ መወያየት ጀመሩ፡፡ ከፊሎቹ “ያስፈጁን ከራሳችን የወጡ ጠማማ ዛፎች ናቸው!” እያሉ ሲቆጩ ከፊሎቹ ደግሞ “አህያውን ቢፈራ ዳውላውን! እኛን የፈጁን የቅዠት ሰዎች ጠፍጥፈው የሰሯቸው ምሳሮች ናቸው!” እያሉ ተከራከሩ፡፡ የቀሩትም “ቀንደኛ ጠላቶቻችን የቅዠት ሰዎች ናቸው!” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጡ፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ቀጥ ያሉ ዛፎች መግባባት ስላልቻሉ ግጪት ተፈጠረና በአንድነት መቆም ተሳናቸው፡፡ ይኸንን የቀጥተኛ ዛፎችን የአቋም መፈረካከስ የተመለከቱ ጠማማ ዛፎችም “ቀጥ ብለው መሄድ የማይችሉ ጠማሞች እያሉ ሲተርቱብንና ሲሰድቡን ኖረው ዛሬ እነሱ ቀጥ ብሎ መሄድ አቃታቸው፡፡ እንደ ውልክፋ እየተወላከፉና እንደማገር እየተወናገሩ ገመናቸውን ማሳየት ጀመሩ ኪ..ኪኪ..ኪኪኪ..” እያሉ ሳቁ፤ተሳለቁ፡፡

 

የቅዠት ሰዎችም ይህንን የዛፎችን ትርምስና ብጥብጥ ተጠቅመው አንበሶችና ነብሮችን አቅፈው በመያዝ የዕልምን ምድር አስክብረዋት የኖሩትን ዛሬ ቀን ጥሏቸው በአንድነት መቆም ያቃታቸውን ዛፎች መጨፍጨፉን ቀጠሉ፡፡ የሚጨፈጨፉት ዛፎችም “እኔ አለቃ ልሁን፤ እኔ ልምራ” በሚሉ ፉክክሮችና “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ ይመልሰዋል” በሚል አጉል ተስፋ ተተብትበው በተናጥል ማለቁን ቀጠሉ፡፡ አንዱ ቡድን “የኔ ትግል ስልት ፍፁም ነው!” ሲልና ሌላው የዚህን ቡድን ሥልት አጣጥሎ የራሱን ሥልት ፍፁምነት ሲሰብክ ብዙ የዛፍ ልጆች ተጨፈጨፉ፡፡ አንዱ ዛፍ ከሩቅ ተገንድሶ ሲወድቅ ሌላው “ተኔ እስኪደርሱ አምላክ መፍትሔ ያመጣል” ሌላውም “እኔን እስኪያገኙኝ አንበሶችና ነብሮች የቅዠትን ሰዎች ይለቅሟቸዋል” እያለ እንደ ፀጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ የማይነጋ ህልም ሲያልም በብዙ ሺ እሚቆጠሩ ዛፎች አለቁ፡፡ በዛፍ ቡድኖች አለመግባባት፣ በመሐል ሰፋሪው ብዛትና ራስን የመከላከል ድክመት የዕልም ምድር እንደ በደኖ ገደልና እንደ ጋንቤላ ሜዳ በሬሳ ተሸፈነች፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ እጀታዎችም በጭፍጨፋው ብዛት አንገቶቻቸው እየተቀሉ ከምድጃ ተማገዱ፡፡ አያሌ ምሳሮችም ጥርሳቸው ረግፎ አዷማ እየተሰሩ አፈር መብላት ጀመሩ፡፡

 

አንገቶቻቸው የተቀሉ እጀታዎች ከእሳት መጣላቸውን የሰሙ ጠማማ ዛፎች “አገልግሎታችን ሲያልቅ መጨረሻችን ገሀነበ እሳት መሆኑ መሆኑን መች አወቅን” እያሉ ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ የቅዠት ሰዎች ግን “አንድም እጀታ ከእሳት አልተጣለም!” ሲሉ ሙልጭ አርገው ካዱ፡፡ በቅዠት ሰዎች አጪበርባሪነት፣ አረመኔነትና በጠማማ ዛፎች ክህደት የበገኑ ቀጥተኛ ዛፎች የአልሞት ባይ ተጋዳይ ተጋድሎ ቀጠሉ፡፡ እንደ ዋንዛ ያሉ ጠንካራ ዛፎች የእጄታን ጭንቅላት መተርከክና አንገቱን መቅላት ጀመሩ፡፡ እንደ ቁጥቋጦ ያሉ ዘዴኛ ዛፎችም ወፈጥና ድንጋዮችን በቅጠሎቻቸው ሸፍነው ካጠገባቸው የበቀለን ቀጥ ያለ ዛፍ የሚጨፈጭፍ ምሳር ጥርስ መሰባበር ጀመሩ፡፡ እንደ አጋምና ቀጋ ያሉ ተናዳፊዎችም የቅዠት ሰዎችን ቆዳ በመገሽለጥና አይናቸውን በማፍሰስ ታገሉ፡፡ ዳሩ ግን እነዚህ ዛፎች የሚያደርጉት ተጋድሎ የተናጥል ስለነበር አንዱ እጀታ ሲቀጭ ሌላው እየተተካ፣ አንዱ ምሳር ጥርሱ ሲረግፍ ሌላው ጥርሳም እየተተካ፣ አንዱ የቅዠት ሰው ዓይኑ ሲፈስ ሌላው ስስታም ዓይኑን ይዞ ከች እያለ ዛፎች ለድል አልበቃ አሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፋኖ ሩሲያ ይዝመት፡ የአብርሃም ሃኒባልን ታሪክ ይድገም

 

ለድል አልበቃ ያሉበትን ምክንያት ለመመርመርና የትግል ስልት ለመቀየስ አስተዋይ ዛፎች መጀመርያ ምስጢራዊ ውይይት አደረጉና ቀጥለው ጠቅላላ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ወቅትም የተለመደው ጭቅጪቅ ተጀመረ፡፡ ሰብሳቢው ሾላ “አለም ከተፈጠረች ጀምሮ ታፍረንና ተከብረን ተኖርበት ምድር እንዴት ልንጨፈጨፍ ቻልን?” ብሎ ጥያቄውን ሳይጨርስ “ምን ጥያቄ አለው! ያስጨፈጨፈን የራሳችን ጠማማ ነው?” አለ ዋንዛ  በንዴት! የተናደደውን ዋንዛ የጎሪጥ እያዬ ኮባ የተባለው ተክል “አህያውን ቢፈራ ዳውላውን! የቅዠት ስዎች እኛን እንዲያጠፋ የጠፈጠፉት ምሳር ተቀምጦ የራሱን ወገን ይወቅሳል” አለ፡፡ ዋንዛም ኮባን በንቀት እያዬ “ተናግረህ ሞተኻል! ጥርሳሙ ምሳር ወገን ተምትለው ጠማማ ዛፍ ወሲብ ባይፈጥም አቅሙን ተየት ያመጣው ነበር! ” ሲል ወጠረ፡፡ “አቅሙን የሚያገኘውማ ተጠማማው ዛፍ ሳይሆን ተቅዠት ሰዎች ነው” አለ ኮባን የደገፈው እንሰት፡፡ በኮባና በእንሰት ክርክር ያልረካው የስብሰባው መሪ ሾላ “ኮባና እንሰት የምታስቡት በቅጠላችሁ ይመስለኛል! የእኛው ጠማማ የቅዠት ሰዎችን እጆችና የምሳርን ቀለበቶች ባያገናኝ የቅዠት ሰው አቅም በምን ታምር ወደ ምሳር ተላልፎ ምሳር እኛን እንዲከትፍ ያበቃው ነበር?” እያለ እንደ ፊዚክስ ሳይንቲስት የጉልበትን ወይም ኃይልን ከአንዱ ቁስ ወደ ሌላው የመፍሰስን ሂደት አስረዳ፡፡ ይህ የጉልበት ወይም ኃይል ፍሰት አገላለጥም ቀለም በደም ሥርም ሆነ በአፍ ቢሰጣቸው  ከማይገባቸው እንደ ብሳና ካሉት ዛፎች በቀር ሁሉንም ቀጥ ያሉ ዛፎችን ልቡና አረካ፡፡ ልቡናቸው በመርካቱም የጠማማ እንጨት ክህደትና አስፈጅነት እንደ መስተዋት ቁልጭ ብሎ ታያቸውና ቅርንጫፎቻቸውን እያፋጩ “ጠማማ ይሰበር! ባንዳ ይቀልጠም! ከሀዲ ይቃጠል!” እያሉ መፈክር አሰሙ፡፡

 

በጠማማ ዛፍ ክህደት፣ አስፈጅነትና ቀንደኛ ጠላትነት በተደረሰው ስምምነት ያልተደሰተ የገዴ ማደርያ ዛፍ “ጦርነት ውስጥ ከምንገባ የተወሰነውን የዕልም ክፍል አስረክበን በእርቅ ብንፈታውና ሰላም ቢሰፍን ይሻላል” ብሎ ሳይጨርስ “አንተን ብሎ ገዴ ዛፍ! ገድህ ይጥፋ! የምታስረክበው አካባቢ ያሉት ዛፎች ወንድሞችህ አይደሉም? ወንድሞችህን በጎባጣ እንጨት፣ በምሳርና በቅዠት ሰዎች አስፈጅተህ አንተ በሰላም ልትኖር ታስባለህ! ሆዳም! የቅዠት ሰዎች በከርስህ እየገዙህ ስንት ዘመን ትኖራለህ? ወንድሙን በክህደት የሚያስበላ ከፈጣሪ፣ ከፍትህና ከታሪክ የተጣላ እርጉም ነው!” አለ ዋንዛ ቅርፊቱ በላብ ወርዝቶ፡፡ በዋንዛ አቋም የረካው ዘንባባ “አንዱ በይ ሌላው ተበይ ሆኖ ሰላም የለም!” ብሎ ለዋንዛ ያለውን ድጋፍ ተናግሮ ሳይጨርስ በዘንባባ ንግግር የተገረመው በለስ “አንተም ዘንባባ! አንተም ሰላምን በመስበክ ፋንታ ለጦርነት ድጋፍ ሰጠህ? ስምንተኛው ሺ የደረሰ መሰለኝ! የሰላም ምልክትነትህ የት ደረሰ?” አለ፡፡ ዘንባባም በለስን ዘቅዝቆ በትዝብት እያዬ “ዕፀ- በለስ! እንደልማድህ ለማሳሳት ታልሆነ ያልኩትን አጥተኸው አይመስለኝም፡፡ ቀበሮ በግ መብላቱን ታላቆመ፤ ዓለም ተተፈጠረች ጀምሮ ለበላው በግ ካሳ ካልከፈለና ሥንሐ ታልገባ በግን ተቀበሮ ተስማማና ሰላም ፍጠር ብትለው እንዴት ሊሰማህ ይችላል? የምታውቀው እባብ ሲነድፍህ እግርህን ዘረጋግተህ ስጠው እሚል ቃል ተየትኛው መጣፍ ተጥፏል? ሰይጣን ቀኝ ፊትህን ሲመታህ ግራህን ስጠው የሚል ትዕዛዝስ የትኛው አምላክ አስተላልፏል?” በሚሉ ጥያቄዎች አፋጠጠው፡፡

 

በዚህ ጠንከር ያለ ክርክር ግራ የተጋባው ብሳና “አምላክ ሆይ! ደብቀን የያዝናቸውን አንቦሶችና ነበሮች አስነስተህ የቅዠትን ሰዎች አጥፍተህ እኛንም እርስ በራሳችን ተመናከስ አድነህ በሰላም አኑረን” ብሎ ወዠቦ እንደ ገፋው ቅርንጫፎቹን ዘቅዝቆ ለእግዞታ ከምድር ተደፋ፡፡ ብሳናን ለእግዞታ ሲደፋ ያየው ዋንዛ “ድፍት ያርግህ ብስናታም! አንበሳ ነፃ ያውጣን እያልክ ነጋ ጠባ ትደፋለህ! ዛፍን ነፃ ማውጣት ያለበት ራሱ ዛፍ ነው! በሞግዚት ነፃነቱን ያገኘ ፍጡር ባለም የለም! በሞግዚት ነፃ አውጣኝ ብትለውም እግዜር አይረዳህም! ሲያምርህ ይባጅ!” ሲል ተቆጣ፡፡ የዋንዛውን ሐሳብ የደገፈ አንድ እጣን “አምላክ ስሜን በከንቱ አታንሱ ብሏል! ያምላክን ስም በከንቱ እያነሳችሁ በየጎዳናው አትደፉ! አምላክ እርዱኝ አረዳለሁ አለ እንጅ እንደ ዱባ ተዘርፍጣችሁ ወይም እንደ አልጌ እየተንፏቀቃችሁ የነፃነት ሸማ አከናንባችኋለሁ አላለም! ቁርጥህን እወቅ በፍርሃት እየራድክና በስስት እየተዘፈክ ነፃነት አታገኝም!” አለ፡፡ እጣን ንግግሩን እንደ ጨረሰም የብሳና አጉል ፀሎትና ሃይማኖታኛነት እንደ ዛሬ ዘመኑ ጳጳሳትና አቡን ልቡን ስላቃጠለው በንዴት እፍ..እሁ.. ብሎ ጪሱን እንደ ሲጃራ አቦነነው፡፡

 

ውይይቱ መፍትሔ ወደ መፈለጉ ሳይሆን ወደ ግጭት እያመራ መሄዱን የተገነዘበው ዋርካ ቅርንጫፎቹን እንደ ንሥር ክንፍ እርግፍ-እርግፍ አደረገና “እንደማመጥ…እንደማመጥ” አለ፡፡ ፀጥታ ሲሰፍንም “ዋንዛ እንዳለው ራሳችንን ነፃ ማውጣት ያለብን ራሳችን ነን! በሞግዚት ነፃ የወጣ ተመልሶ መገዛቱ አይቀርም!” ሲል የዋንዛን ሐሳብ አጠናከረ፡፡ ንግግሩን በመቀጠልም “ጠላቶቻችን እጀታም፣ ምሳርም፣ የቅዠት ሰዎችም ናቸው፡፡ በደረጃ እናስቀምጥ ከተባለ እጀታን ያህል ጠላት የለንም! ምክንያቱም ምሳርና የቅዠት ሰዎች ባዕዳን ስለሆኑ የሚፈረጁት በጠላትነት ብቻ ነው፡፡ ጠላት ደሞ ጠላቱን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ እጀታ ግን ከዛፍ የተወለደ የወገን ከሃዲ ነው፡፡ ስለዚህ እጀታ የሚፈረጀው በጠላትነት ብቻ ሳይሆን በከሀዲነትም ነው፡፡ እጀታ ከሃዲም ጠላትም ነው!” ብሎ ሳይጨርስ አብዛኛው ዛፎች ቅርንጫፎቻቸውን በአዎንታ እያወዛወዙ ለብዙ ደቂቃዎች “እጀታ ከሃዲም ጠላትም ነው! ከሃዲም ጠላትም ነው! ከሃዲም ጠላትም ነው!” እያሉ መፈክር አሰሙ፡፡

 

በሌላ በኩል ደግም አንዳንድ ድሮ ጠማማ የነበሩ ነገር ግን በቅርቡ በአካባቢ ተፅዕኖ የተቃኑ ዛፎች መፈክር በሚያሰሙት ዛፎች አጉረመረሙ፡፡ ባጉረመረሙት የድሮ ጠማማ ዛፎች የበሸቀው ወይራ ብድግ አለና “እነዚህን የድሮ ጠማሞች ተመልከቱ! ተጣሞ የነበረ እንደገና መጉበጡ አይቀርም! የተፈጥሮ ህግ ነዋ! በጠበልና በጠሎት ቢያድኑትም የቅዠት ሰው ድንግልናውን ወስዶ ያጣመመው ዛፍ ተመልሶ መጣመሙ አይቀርም! እንኳን እርሱ ቅጥዩም ይጣመማል! ጠማማ ቀና፤ ከሀዲም ታማኝ ወልዶ አያውቅማ! አይደለም እንዴ?” ብሎ ፊቱን ወደ ዛፎች ሲያዞር “ትክክል! ወይራ! ወይራ! ዋንዛ! ዋንዛ!” አለ አብዛኛው ዛፍ በጭብጨባ ፡፡ ጭብጨባው ጋብ ሲልም በአገኘው ድጋፍ የተደሰተው ወይራ ” እጀታ ጠማማ ነው፡፡ እጀታ ከሀዲ ነው! እጀታ ባንዳ ነው፡፡ ከሀዲንናና ባንዳን የምንገላገለው ወፌ ቆመች በማለትና በመለማመጥ ሳይሆን ሥሩን መንግለን ዘር እንዳይተካ ከምድር ስናጠፋው ብቻ ነው! ኦሁሁ.. ጨርሻለሁ” አለ፡፡ የዋርካ፣ የዋንዛና የወይራ ክርክር እጀታ ቀንደኛው የዛፎች ጠላት መሆኑን አሳዬ፡፡ በጠማማ ዛፎች በተለይም በእጀታ ክህደት የብዙ ዛፎች ልቦች ቆሰሉና እንባቸው ከቅጠሎቻቸው እንደ ዝናብ ወረደ፡፡ የዛፎች እንባ የወረደባቸው አንበሶችና ነብሮችም ዛፎች የሚያነቡበትን ምክንያት መመርመር ጀመሩ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተዋሕዶ አብዮት መቀልበስ፤ ሐይማኖትና መንግስት ወይስ ሐይማኖትና ፖለቲካ?

 

የዛፎች ውይይት በማግስቱም በዋርካ የስብሰባ መሪነት ቀጠለ፡፡ በእጄታ ከሀዲነት፣በእጀታ አረመኔነትና በእጀታ እርጉምነት አዝነው ያደሩ ዛፎች አንጋታቸውን ደፍተው የተመለከተው አባሎ ተነሳና”ወገኖቼ በሐዘንና ትካዜ ራሳችሁን አትጉዱ! ጊዜ ይፍጅ እንጅ ለሁሉም በሽታ መድኃኒት ይገኝለታል” ብሎ ሳይጨርስ “የካህን ሚስት ሰለጠንሽ ቢሏት መጣፍ አጠበች! አንተ ደሞ ቁስልና ምች አክም እንጅ ስለ ትግል ምን ታውቃለህ?” ሲል ቀጋ አባሎን አንጓጠጠው፡፡ “ወይ ተፈጥሮ! ድሮም የቀጋ ሥራ መጎተት ነው! እስቲ ሐሳቡን አስጨርሰው!” አሉ የአባሎ ጓደኞች ዳማ ከሴና ግራዋ፡፡  “ያይጥ ምስክሯ ድንቢጥ” አለ ዳማ ከሴና ግራዋ በመድሀኒትነታቸው ጓደኞች መሆናቸውን የሚያውቀው ቀጋ፡፡ እንደ ቀጋ ሸብቦ በመያዝ የሚታወቀው ጠሮም “ትክክል! እውነትም ያይጥ ምስክሯ ድንቢጥ” ሲል የቀጋን ሐሳብ ደገፈ፡፡

 

ዋርካ አሁንም ስብሰባው ወደ መፍትሔ ሳይሆን ወደ አበልጃዊ ቡድን ውዝግብ መሄዱን ተረዳና “ጎበዝ! ይህንን የማይጠቅም ቡድናዊ ወይም ዝምድናዊ ክርክር ተውና ወደ ቁም ነገሩ እንግባ! ለመሆኑ ከፊታችን የተደቀነብን ትግል የመኖርና ያለመኖር የህልውና ትግል መሆኑን ስንቶቻችን ተረድተናል? የህልውና ትግል የጓደኛን ወይም የዘመድን ሐሳብ  በጓደኝነት ወይም በዝምድና ብቻ መደገፍ ከዳር አይደርስም፡፡ የህልውናችን ትግል ከዳር እሚደርሰው በተግባር የሚተረጎም የረቀቀ የጋራ የትግል ስልት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ የጋራ የትግል ሥልትም የሚተለመው ሁላችንም የየራሳችን ተሰጥኦና ሙያ ማበርከት ስንችል ነው፡፡ የጥፋት አዋጅ ታውጆብን መጓተቱና መጋጨቱ መጥፋታችንን ያፋጥናል እንጅ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ስለመፍትሔ ስንወያይም አባሎ ለሁሉም በሽታ መድሐኒት ይኖረዋል የሚል ጥሩ ሐሳብ ጀምሮ ስለነበር ሐሳቡን እናስጨርሰው” ብሎ እድሉን መልሶ ለአባሎ ሰጠው፡፡

 

አባሎም የመናገር እድሉን ደግሞ ስላገኝ ዋርካን አመስግኖና የልጃገረድ ዛፎችን ቀልብ ለመሳብ ችብሃ የመሰለ አርንጋዴ ቅጠሉን እርገፍ እርገፍ አድርጎ እንደ መልካም የክብር ካባ አሳይቶ “የሕክምና የመጀመርያው ደረጃ በሽታን በተለያዬ መንገድ ማወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደረጃ መድሃኒቱን መፈለግ ነው፡፡ በትናንትናው ስብሰባችን በሽታዎቻችን አውቀናል፡፡ በሽታዎቻችን እጀታ፣ ምሳርና የቅዠት ሰዎች መሆናቸውን አውቀናል፡፡ በሽታዎቻችንን ካወቀን ቀጥሎ መወያየት ያለብን ቀድመን የትኛውን በሽታ እናክም ወይም እናስወግድ ነው፡፡ የምሳርን ጥርስ ማርገፍ?  ከራሳችን የወጣን ጠማማ ባንዳ መቀለጣጠም? ወይስ የቅዠት ሰዎችን መተናነቅ?” ብሎ ሐሳቡን ሳይጨርስ ዋንዛ ብድግ አለና “መዥገር በጉያችን ይዘን እንደልባችን መራመድ አንችልም! ወጥመድ ገብቶብን ራሳችንን መከላከል አንችልም! መዥገሩም ወጥመዱም ጠማማው እንጨት እጀታ ነው! መጀመርያ መንቀል ያለብን መዥገርን! መጀመርያ መቀልጠም ያለብን እግር ብረትን! መጀመሪያ ማጥፋት እጀታን! መጀመርያ ከሀዲን! መጀመርያ ባንዳን!” አለ ባንዳውን ደፍተራ ታዬን አርባ እንደ ገረፈው በላይ ዘለቀ እየፎከረ፡፡ የዋንዛ ፉከራ የነሸጠው ሸንበቆ አንዴ ወደ ፊት ሌላ ግዜ ወደ ጎን መልሶ ደሞ ወደ ኋላ እየተንጎራደደ “ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው፤ አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው” ብሎ አቅራራ እንደ ሞላ ሰጥ አርጌ፡፡

 

በሸንበቆ ቀረርቶና በዋንዛ ፉከራ ልቦቻቸው የሸፈቱ ዛፎች ቅርንጫፎቻቸውን አንዴ እንደ እናት አልቢን፣ ሌላ ጊዜ እንደ በልጅግ፣ መልሰው እንደ ረጅም ሚንሽርና ጓንዴ እየቀሰሩ ፎከሩ፡፡ አንደኛው “እምቢኝ- እምቢ አሻፈረኝ፤ ጠማማ አራቂ እንደ አገር ቋጥኝ!” ሲል ሌላው ተከተለና “አውሬው የዛፎች ራስ፤ ሰባብሮ እሚጥል የምሳርን ጥርስ” ሲል አሁንም ሌላው ፋኖ “የዛፎች አውራ የዛፎች ገደል፤ የቅዠትን ሰው ወገብ እሚሰብር” እያለ ፎከረ፡፡ በአበባ ያጌጡ ሴት ዛፎችም “እውነት ነው!” እያሉ የሚፎክሩ ፋኖ ዛፎችን ለማበረታታት አበባ አበረከቱ፡፡ እንደ ሎሚ፣ ብርቱካንና እንኳይ ያሉ ቆነጃጅት ዛፎችም የፎካሪዎችን ደረት በፍራፍሬዎች እየመቱ በፋኖቹ የተማረኩ መሆናቸውን አመለከቱ፡፡

 

የዛፎች ቀረርቶና ፉከራ በረድ ሲል እንቆቆ የተባለው ተክል “ምንትስ ምንትስ” ብሎ እንደ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ለብዙው የማይገባ ቅኔ ተቀኘና መልሶ በቀላል ቋንቋ “ለጠላት ደረጃ በማውጣት ጊዜንና ሐይልን ማባከን አይገባንም፡፡ ከፈጣሪ ጋር እኛ የተክል ዘሮች ሶስቱንም ጠላቶች ባንዴ የመጋፈጥ ብቃት አለን፡፡ ለምሳሌ እስካሁን በተናጥል እንደተደረገው ሸንበቆና ቀርቀሃ ፋኖዎችን በቀረረቶና በሽለላ ቢቀሰቅሱ፤ እነዋንዛ የእጀታን አንገት እንደ አጥንት ቢቀለጥሙ፣ እነቁጥቋጦም ወፈጥን እንደ ፈንጅ ሸፍነው የምሳርን ጥርስ እንደ ሸክላ ቢሰብሩ፣ እነ ሰርዶና ጠሮ የቅዠት ሰዎችን እግሮች እየዘረጠጡ እንደ ፍሪዳ ቢጥሉ፤ እንደ ባህርዛፍና ዋርካ ያሉ ግዙፍ ዛፎች ደግሞ ከቅዠት ሰዎች ወገብ እንደ ናዳ ቢወድቁ፤ ቀጋና አጋምም የቅዠት ሰዎችን ቆዳ እንደ ልጥ ቢገሸልጡ፤ እነበርበሬ የቅዠት ሰዎችን ዓይን ቢያደናብሩና ጋሬጣዎችም ከተደናበሩት እግሮች ቢሰኩ፣ እንደዚሁም አባሎና ግራዋ የቆሰሉ ወገኖቻችንን ቢያክሙ፤ እነስንጥር እጨትም ስብራትን ቢጠግኑ፤ እነ እጣንም በጠሎታቸው ቢረዱ የህልውናችን ትግል ተሳክቶ ከበፊቱ ክብራችን ማማ ባጭር ጊዜ ተመልሰን እንወጣለን፡፡ ” ሲል አስተማረ፡፡ “እውነትም ስምን መላክ ያወጣዋል! ማሻሪያው እንቆቆ የሚያሽር የትግል ስልት አፈለቀ” እያሉ አብዛኛው ዛፎች በእንቆቆ የጦር ሥልት ተደምመው ቅርንጫፎቻቸውን እያፋጩ “እንቆቆ…እንቆቆ…እንቆቆ..” እያሉ ለሁለት ደቂቃዎች እስክስታ አወረዱ፡፡

 

እስክስታው ጋብ ሲልም አንድ የእጣን ሊቀጠበብት “እሽዋ…እሽዋ..” እያሰኘ እንደ እጣን ማጨሻ ቅርንጫፎቹን እርግፍ እርግፍ አርጎ አካባቢውን አጠነና “አንድም ሁለትም ሆናችሁ ተገኙ በመካከላችሁ እገኛለሁ ብሏል ፈጣሪ” ብለው ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ በመቀጠልም “እንደዚህ ዓይነት የመደማመጥና የመረዳዳት መንፈስ በመካከላችን ሲፈጠርና እኛም ስንረዳው እርሱም ይረዳል፡፡ ፈጣሪ ግፈኞችን ያንበረክካልና እኛም ስንጥርና ስንረዳው ሳንደርስባቸው የደረሱብንን የቅዠት ሰዎች ያንበረክክልናል፡፡ ስናጎርሳቸው የነከሱንን ጠላቶች ያመነዥክልናል፡፡ እኛን ለማጥፋት የተጠፈጠፈውን የምሳርን ጥርስ ይሰርብርናል፤ የከሀዲዎችን ክንድም ያዝልልናል፡፡ በእኒህ መረን በለቀቁ አርመኔዎችም አንበሶችና ነበሮችን ሊለቅባቸው ይችላል፡፡ ሳንሄድባቸው ለመጡብን፣ ሳንነካቸው ለነኩን፣ ሳንወስድባቸው ለወሰዱብን፣ ባበላናቸው ላስታወኩብንና ባጠጣናቸው ለሸኑብን ማዕበልና ጎርፍ ሊያወርድ ይችላል፡፡ ስብሰባችን ፍሬአማ ነበርና እቅዳችንን ከዳር ያድርስልን፡፡ የስብሰባውን መንፈስና የትግሉን ስልት ለመላው የዛፍ ፋኖዎች በጪሳችን ለማዳረስ እኛ እጣኖች ሌተ ተቀን እንሰራለን” ብለው ሀላፊነትን ሲወስዱ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡

 

እጣኖች ቃል በገቡት መሰረት የዛፎችን ውሳኔ በጪሳቸው በዕልም ምድር አሰራጩ፡፡ የምድር ዛፎችም አቅማቸውና ሙያቸው በሚፈቅደው መንገድ የሞት የሽረት ትግል ለማደረግ ተዘጋጁ፡፡ ይህንን የዛፎችን አመጥ የተረዱ ጠማማ ዛፎች ለእጀታዎች አደረሱ፡፡ እጀታዎችም ለምሳሮችና ለቅዠት ሰዎች አሳወቁ፡፡ የዛፎችን ቁርጠኝነትና ጥንካሬ የተረዱ አንዳንድ እጀታዎች ባለቀ ሰዓት ፋኖ ለመባል ከቅዠት ሰዎች እጅ እያመለጡ ከዛፎች ሥር እንደ ዱላ እየወደቁ ተደበቁ፡፡ እነዚህ እጀታዎች ያጠለቁትን ምሳር “ጉርንቦውን አንቀን ማርከን አመጣነው!” እያሉ በዛፎች ዘንድ ጀግና ለመምሰል የባጡን የቆጡን ቀባጠሩ፡፡ እነዚህን እጀታዎችን የታዘቡ ዛፎች ግን ጥርሳቸውን ነክሰው የትዝብትና የለበጣ ሳቅ እንደ ፍልጥ ፈገግ አሉ፡፡ አንዳንድ ዛፎች ግን “በሰሩት ሥራ ተፀፅተው ወገናቸው ለመርዳት ተመጡ ቅርጫፎቻችን ዘርግተን እንቀባላቸው!” ሲሉ ዋንዛ ቅርንጫፎቹን እንደ መንጋጋ አፋጨና ” እምንቀበላቸው እስከ ዛሬ ለቀጯቸው የዛፍ ልጆች ተጠያቂው ማን ሆኖ ነው? የቅዥት ሰዎች ድንግልናቸውን የወሰዱት ጠማማዎች ተመልሰው ወገን ሊሆኑ እንደማይችሉ አልተስማማንም ወይ?” ብሎ ፍሬውን አጉረጥርጦ ሲጠይቅ እንቀበል ያሉ ዛፎች መልስ አጡና አንገታቸውን ደፉ፡፡

 

የዛፎችን ትግል መሰናዶ በስለላ መረባቸው የተረዱ የቅዠት ሰዎች በበኩላቸው የራሳቸውን የፍልሚያ እቅድ አሰናዱ፡፡ ለዚህ እቅድ ማስፈፀሚያም ብዙ ተጨማሪ ምሳሮች ጠፍጥፈው ሰሩ፡፡ የዶሎዶሙትን ምሳሮችም በእሳት እያጋሉ ሳሉ፡፡ አንዳንድ እጀታዎች በቀላሉ ስለሚሰበሩ የምሳሮችን ሶስት እጥፍ እጀታዎችን ጠርበው አዘጋጁ፡፡ የዱር አውሬዎችን በመስጋትም ውሾቻቸውን አሰለጠኑ፡፡ ከጠማማ ዛፎች በተላጠ ልጥና ከቅርንጫፎቻቸው በተገኘ ደጋንም ቀስቶች ሰርተው የቀስት ውጊያ ተለማማዱ፡፡ መሪዎቹ የወረራውን ቀን በሚስጢር ይዘው የቅዠት ሰዎች በነቂስ በጦርነቱ እንዲሳተፉ ጥሪና ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  መኪና አሳዳጅ ውሾች! - በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

 

የዕልም ዛፎች ባላሰቡት ቀን የቅዠት ሰዎች በሰሜን በኩል የዕልምን ምድር ወረሩ፡፡ የቅዠት ሰዎች እጀታ ውስጥ በገባ ምሳር የገደል ማሚቶው “ዱዋ…ዋ.. ዱ..ዋ” እስከሚል ከዳር ጀምረው ቀጥ ያሉ ዛፎችን መቁረጥ ጀመሩ፡፡ የዚህ ቆረጣ የመጀመርያ ሰለባ የሆነው ዋንዛ እየቆረጠው ያለውን እጀታ “አንተ ጠማማ ባንዳ የቅዠት ሰዎች ዘራችንን ለማጥፋት በጠፈጠፉት ምሳር ገብተህ ወገኖችህን ስታስጨርስ ህሊናህን አይቆነጥጥህም?” ሲል ጠየቀው፡፡ የተጠየቀው እጀታም “ይኸው በእጄ ወድቀህም ለኻጭህን ማዝረብረቡን አትተውም፡፡ እንደ ዛፍ መኖር ከፈለክ መጀመርያ ይኸንን ጠማማና ባንዳ እያልክ የምታዝረበርበውን ልኻጪህን መጥረግ አለብህ” ብሎ ሳይጨርስ ወይራ ግንዱና ሥሩ ተገታተረና የዚህን እጀታ አንገት ቀላው፡፡ ይኸንን እጀታ ይዞት የነበረው የቅዠት ሰው ሌላ እጀታ ሊተካ ዘወር ሲል የአጋም እሾህ ዓይኖቹን አፈሰሰና ከጥቅም ውጪ አደረገው፡፡

 

የቅዠት ሰዎች ወረራ በመላው ዕልም ሲሰማ ሸንበቆና ቀርቀሃ በመረዋ ድምፃቸው እያቅራሩና እምቢልታ እየነፉ ዛፎችን ቀሰቀሱ፡፡ ይህ ወኔ ቀስቃሽ ሽለላ የነሸጣቸው እንደ ዋንዛ ያሉ ዛፎች ሥራቸውንና ግንዳቸውን እያጠነጠኑ እጀታን መቀልጠም ቀጠሉ፡፡ ዋርካዎች፣ ግራሮች፣ ባህር ዛፍቾና ሌሎችም ግዙፍ ዛፎች በመደዳ ከተሰለፉት የቅዠት ሰዎች እየወደቁ ወጋባቸውን ቀጩ፡፡ ቁጥቋጦ፣ ችፍርግና ሌሎችም አጫጭር ዛፎች ድንጋዮችን በቅጠላቸው እየሸፈኑ ቀጥኛ ዛፍ ሊጎረድሙ የተዘረሩን የምሳር ጥርሶች አረገፉ፡፡ በርበሬ የቅዠት ሰዎችን ዓይኖች በደም ነክሮ ሲያደናብርና ጋሬጣም በተደናበሩት እግር እየተሰካ የቅዠት ሰዎችን በእንፉቅቃቸው አስኬዳቸው፡፡ ጠሮና ሰርዶ የቅዠት ሰዎችን ጥልፈው እያጋደሙ ጭንቅላታቸው በድንጋይ እንዲፈረካከስ አደረጉ፡። አጋምና ቀጋ የቅዠት ሰዎችን ቆዳ እየገሸለጡ ደም እንዲንዠቀዠቃቸውና በህመም እንዲያቃስቱ አደረጉ፡፡ የቅዠት ሰዎች የደም ሽታና ሲያቃስቱ የሚያሰሙት ድምፅ አንበሶችና ነብሮች ከእንቅልፋቸው ቀሰቀሳቸው፡፡ የነቁት አንበሶችና ነብሮች ወደ ሸተታቸው ደምና ወደ ሰሙት የጣር ድምፅ እየተሳቡ መጡ፡፡ አንበሶችና ነብሮች እየተጎማለሉ ሲመጡ በቀስት ውጊያ የሰለጠነ የቅዠት ሰው በአንዱ ነብር ግንባር ቀስት ተከለበት፡፡ ቀስቱ የተተከለበት ነብር በንዴት እንደ አቦ ሸማኔ ተወርውሮ ከባለቀስቱ ተዋጊ ተኮፈሰበት፡፡ ሌሎች ነብሮችና አንበሶችም የቅዠትን ሰዎች እያሳደዱ መዘንቸር ጀመሩ፡፡ በዚህ ትንቅንቅ ወቅት ሰማዩ እንደ በር ተበረገደና በዕልም ምድር ታይቶ የማይታወቅ ዶፍ ወረደ፡፡ እንኳን ወንዞች ሜዳው በጎርፍ ተጥለቀለቀ፡፡ ከዕልም ተክሎች ተጋድሎ፣ ከአንበሳና ነብሮች መንጋጋ የተረፉት የቅዠት ሰዎች ከወንዝና ከባህር እየሰመጡ አለቁ፡፡ ብዙዎቹ በጎርፉ ተጠርገው እንጦረጦስ ገቡ፡፡ የቀረቱም ከወንዞች ከሐይቆችና ከባህሮች እንደ ኩበት ተንሳፈፉ፡፡ ምሳርና እጀታም ደለል ወስጥ ተቀበሩ፡፡ ከሰባት ሳዕታት የመረረ ተጋድሎ በኋላ ድል በዕልም ዛፎች ሥር ገባች፡፡ ሸምበቆዎችና ቀርቅሃዎች በስሜት አቅራሩ፤ ፋኖዎችም ያለማቋረጥ ፎከሩ፡፡ ስንጥር እንጨቶች ስብራት መጠገኑን፤ አባሎ፣ ዳማከሴና ግራዋም ቁስለኞችን ማከሙን ቀጠሉ፡፡

 

በድል ማግስት በትግሉ የተሰውትን ተክሎች ለማስታወስና ድላቸውንም ለመዘከር ተክሎች በነቂስ አደባባይ ወጡ፡፡ የዛፎችን የተጋድሎ ታሪክ ይዘግብ የነበረው ፓፒረስ ዛፍ ወደ መድረክ ወጥቶ “የሰማእታት ተጋድሎ ፍሬ በማፍራቱ እንኳን ደስ አለን!” ሲል አደባባዩ ልቅሶ፣ ደስታ፣ ሳቅና ጭብጨባ በተቀላቀለበት ጫጫታ ተናጋ፡፡ ጫጫታው ታገስ ሲልም “የተክሎች የህልውና ተጋድሎ ባለም ታይቶ የማይታወቅ ጀግንነትና ትብብር የታየበት ነበር፡፡ የተጋድሎውን ዝርዝር ታሪክ ተጠርዞ ሲወጣ ታዩታላችሁ፡፡ አንዳንድ አዋቂ ነን ባዮች በእኛና እኛን ሊያጠፉን በተነሱት ጠላቶች መካከል የተነሱት ግጭቶች “በውይይትና በዕርቅ” ይፈታሉ እያሉ ይደሰኩሩ ነበር፡፡ በቃሉ የሚረጋ ባለማተብ፣ በሽምግልናና በእርቅ የሚያምን ሲኖር ውይይት ሊሰራ ይችላል፡፡ ዓይናቸውን በጨው የታጠቡ እንደ ቅዠት ስዎች ያሉ ስግብግብና አረመኔ ጠላቶች ሲነሱ ውይይት ሰርቶ አያውቅም፡፡ በጠላት እጅ ከተጠፈጠፈ እንደ ምሳር ካለ ግዑዝ ጋር መደራደር አይቻለም፡፡ ከጠላት አብሮ የራሱን ወገን ከሚገልና ከሚያስገድል እንደ እጀታ ካለ እርጉም ባንዳ ጋር እንኳን መነጋገር ፊት ለፊት መተያየትም አይቻልም፡፡ ለእንደነዚህ ዓይነት የሳጥናኤል ተከታዮች የሚገባቸው ቋንቋ ጉልበት ብቻ ነው፡፡ ሳጥናኤል ፍጡራን በማበጣበጥ፣ ከሀዲዎችን በገንዘብና በስልጣን በመደለልል ተንኮል ተክኗል። ዳሩ ግን ሳጥናኤል ፍቅርና ሰላምን ሲወድ መቼ ታይቶ ያውቃል? ሳጥናኤል በቃል፣ በሽምግልናና በእርቅ በየትኛው ዘምን አምኖ ያውቃል?” ብሎ ሲጠይቅ “አምኖ አያውቅም!!” አለ አደባባዩን ጢም ያደረገው ዛፍ አገር በሚያናጋ ድምጥ፡፡ ድምጡ ሰጥ ሲልም “እንደ አለመታደል ዓለም በአብላጫው ስትገዛ የኖረቸው የሳጥናኤልን መንፈስ በሚተገብሩ ጉልበተኞች ነው፡፡ ዛሬም የምትገዛው በእነዚሁ ጉልበተኞች ነው፡፡ ነገም የምትገዛው በተመሳሳይ ጉልበተኞች ነው፡፡ ስለዚህ በዓለም ጉልበትን ጥለው ባይምሮ መሳርያ የሚጠቀሙ፣ ለእውነተኛ ፍትህና እኩልነት የሚታገሉ ፍጡራን እስከሚፈጠሩ ከመጥፋት ለመዳን ያለን አማራጭ ጉልበታችን ነው፡፡ ዛሬ ጉልበታችን የቅዠት ሰዎችን፣ ምሳርንና እጀታን ድባቅ መቶ ከመጥፋት እንዳዳነን ነገም የሚያድንነን ጉልበታችን ነው፡፡ ጉልበታችንና አንድነታችን ማጠንከሩን እንቀጥል፡፡  ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ” ብሎ መድረኩን ለአባ እጣን አስረከበ፡፡

 

አባ እጣን የተጨማደደ ቅርፊታቸውን እንደ ካባ ደርበው ወደ መድረኩ ወጡና “ለእኛ ክብር ሲሉ ያለፉትን ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን! እኛንም እዚህ ስላደረስን አምላክ የተመሰገነ ይሁን” ሲሉ “አሜን! አሜን! አሜን” እያለ ታዳሚው እንባውን አፈሰሰ፡፡ እንደ ታዳሚው ሐዘን የጎረሰ ደስታ የለበሱት አባ እጣንም ንግግራቸውን በመቀጠል “እግዚአብሔር እርዱኝ እረዳለሁ ባለው መሰረት ስለረዳነውም ረድቶናል፤ ታምሩንም አሳይቶናል፡፡ የእኛን ጉልበትና ትብብር እንደ ብረት አጠንክሮልናል፡፡ የጠላትን ክንድ እንደ ቅራሪ አቅጥኖልናል፡፡ አንበሳና ነብርን ተእኛ አሰልፎልናል፡፡ የቅዠት ሰዎችን የሚጠርግ ዶፍና ጎርፍንም አውርዶልናል፡፡ ቀጥተኛ መስመር የመከተልንና ወላዋይ ያለመሆንን ጥቅምም አሳይቶናል፡፡ አምላክ ከወላዋይ ጋር አብሮ አይቆምም፡፡ እግዚአብሔር ሁለት ልብ አይፈልግም፡፡ ለእግዚአብሔርና ለሳጥናኤል መገዛት አይቻልም፡፡ እግዚአብሔርና ሳጥናኤል ዘወትር ጦርነት ላይ ናቸው፡፡ የጦርነት ሜዳቸውም የሰው ልብ ነው፡፡ ሰው ልቡን ለሳጥናኤል ሰጥቶ እየካደ፣ የሰውን ሐብት እየተመኘ፣ እየሰረቀ፣ እየተስገበገበ፣ እርስበርስ እያጋጨ፣ እያመነዘረ፣ እየመቀነ፣ እየገደለና እያሰቃየ እጁን ለፈጣሪ ቢዘረጋ ከየትኛው ሰማይ እሚኖር እግዚአብሔር ይሰማዋል? በዘረፈውና አጭበርብሮ ባካበተው ገንዘብ የአምልኮት ሥፍራ ቢሰራ የትኛውን አምላክ ሊያታልል ይችላል? አምላክ ቀናተኛ መሆኑን አበክሮ ነግሮናል፡፡ ተእርሱ በቀር ሳጥናኤልንም ሆነ የሳጥናኤልን ጣኦቶች ገንዘብና ስልጣንን እንዳናመልክ አስጠንቅቆናል፡፡ ስለዚህ ሙሉ ልባችንን ለእግዚአብሔር ሰጥተን፤ ትስስራችን አጠንክረን፣ በሙያችን ተሰልፈን፤ ከሀዲና ባንዳን ተጉያችን እንደ መዥገር ነቅለን ለፍትህና ለነፃነት ተታገልን እግዚአብሔርም እንደ ዛሬው አብሮን ይቆማል፡፡ ተማመንታትና ሁለት ልብ ተመሆን አውጥቶ ለድል ያበቃን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ዳግመኛም እርስ በርሳችን አጋጪቶ ሊያጠፋን ተሚነሳ ጠላት ይጠብቀን፤ የሰማእታትን ነፍስ ይማር” ብለው ንግግራቸውን ሲጨርሱ ሁሉም ዛፎች “አሜን፤ አሜን፤ አሜን፡፡” እያሉና የተጨፈጨፉትን ወገኖቻቸውን እያሰቡ በቅርንጫፎቻቸው ተቃቅፈው እንባቸውን ከቅጠሎቻቸው እንደ ነሐሴ ዝናብ አወረዱ፡፡

 

ጥር ሁለት ሺ አስር ዓ. ም.

Share