July 30, 2019
38 mins read

አህያየን የሰረቃት ሌባ – ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
[email protected]
ሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ/ም

አህያየን የሰረቃት ሌባ፤ ራሱ ደብቆ አፈላላጊየ ሲሆን አህያየን እንዴት ላገኛት እችላለሁ

ይህ አባባል ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ እየተሻገሩ ዘመን ካቌረጡት ከብዙ ክስተቶች አንዱ እንደሆነ አበው ይናገራሉ።

እኛ የኦርቶዶክስ ይማኖት መምህራን፤ “ለትውልደ ትውልድ ዘኢየኀልቅ ለዓለም ዓለም” ብሎ በሚደመድመው በየመንፈቀ ሌሊት በምናደርሰው ጸሎተ ኪዳናችን ትንሹንና ትልቁን ህዳጡንና መንጋውን ህብረተሰቡን አጠናቅሮ በመምራት ላይ ያለውን ተወራራሽ ምድራዊ መንግሥት እንቃኝበታለን። በአመጽም ሆነ በሰላም ቅብብሎሽ እየተፈራረቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሻገር ላይ ያለው ምድራዊና ጊዜአዊ መንግሥትም በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት እንደሚዋጥ እናስተምራለን።

ኢትዮጵያውያን መተርጉማን ይህን ሐረግ ከመሳሰሉት ምንባባት በመነሳት፤ እንደ እኛ በቅኝ ግዛት ሳይወረር በኖረ ሕብረተ ሰብ የሚነገሩት በብራና ባይጻፉም ተረቶች ወይም ፈጠራዎች አይደሉም። ባንድ ትውልድና ዘመን ተከስተው ዘመናትን እየተሻገሩ በቅብብሎሽ የመጡ ናቸው“ እያሉ ነግረውናል። ”አህያየን የሰረቃት ሌባ፤ ራሱ ደብቆ አፈላላጊየ ሲሆን አህያየን እንዴት ላገኛት እችላለሁየሚለው ክስተት በጽሑፍ ባይቀረጽም በቃል ንግግር ቅብብሎሽ በየትውልዱ የሚደርስ ነው። ይህን የመሳሰሉ ክስተቶች ከረዥም ዘመን በኋላ ባዲሱ ትውልድ ላይ ሲወድቁ፤ አዲሱ ትውልድ ለመቀበል እየከበደው ተረት ይመስሉታል። ግን ቅርጻቸውን፤ ይዘታቸውንና ትርጉማቸውን እየቀያየሩ በየትውልዱ የሚከሰቱ አማናውያን ናቸው ይላሉ።

“ለትውልደ ትውልድ ዘኢየኀልቅ ለዓለም ዓለም” በሚለው ምንባብ ላይ የተመሰረተው ሐተታ እንደሚጠቁመን፤ ቀዳማዊው መንግሥት በደሀራዊው መንግስት እየተዋጠ በሚሻገር እንደ ኢትዮጵያ በመሰለ ኅብረተሰብ የሚነገሩ አፈታሪኮች ካለፈው ትውልድ አካል ጋራ አይቀበሩም። ከማይቀበረው ታሪክ ጋራ በትኩረት ሊጠኑንና ሊመረመሩ የሚገባቸው ናቸው። የቀደሙ አባቶቻችን በግል አካላቸው በመቃብር ቢወሰኑም፤ ባወረሱን አካላቸውና በሰሩት ታሪካቸው በነገሩን ትንግርታቸው ሕያዋን ናቸው።

መተርጉማን አባቶች፤ የቀደሙትን ክስተቶች ተቀባዩ ትውልድ በሰከነ አዕምሮ ቢቃኛቸው በዘመኑ የሚገጥሙትን ጎጅና ጠቃሚ ክስተቶችን ለይቶ በመገንዘብ እራሱንና አገሩን እንዲጠብቅ ይረዱታል እያሉ ይነግሩን ነበር።

የዚህችን ልፋፍ ጽሑፍዋና ሀሳብ መጨበጥ ይረዳ ዘንድ “አህያየን የሰረቃት ሌባ፤ ራሱ ደብቆ አፈላላጊየ ሲሆን አህያየን እንዴት ላገኛት እችላለሁየሚለውን በመጀመሪያ እንድንቃኘው እፈልጋለሁ።

አህያው የተሰረቀችበት ባላገር እየፈለገ ባካባቢው መዞር ጀመረ። ያህያዋን ዱካ አገኘ። ዱካዋን ተክትሎ ሲሄድ አህያውን የሰረቀ ሌባ ካሰረበት ጫካ ደረሰ። ሌባው ሲመሽ ፈቶ

ለመውሰድ ባካባቢው ቆሟል። የአህያዋ ጌታም አህያየ ጠፍታኝ በመፈለግ ላይ ሳለሁ ፋናዋን አግኝቼ እየመራኝ እዚህ ደርሻለሁ። ምናልባት አይተሀት ከሆነ ልትነግረኝ ትችላለህ? ወንድሜ“ ብሎ ሌባውን ጠየቀው። ሌባውም መለሰና ቀኑን ሙሉ ሳር ሳጭድ ከብቶችንም ሳሰማራ ከዚህ አልተለየሁም፤ አህያ ግን አላየሁም አለው። በመፈለግ ላይ ያለው ያህያዋ ጌታም ከዚህ የደረስኩት የምታየውን ፋናዋን እየተከተልኩ ነው አለው ። ሌባውም

አንድ ሰው በቅሎ እየነዳ በዚህ አልፏል። የምትከተለው ፋና የበቅሎዋ እንጅ የአህያዋ አደለም። ይልቅስ እየመሸ ነውና ጅብ እንዳይሻማህ ወደ ሌላ ቦታ እንድትፈልጋት

እመክርሀለሁ አለው። ያህያዋ ባለቤት ሰውየውን ተጠራጥሮ ቆሞ በመተከዝ ላይ ሳለ፤ አህያው ጠፍታው በመፈለግ ላይ መሆኑን ያወቀ አቋርጦ በመሄድ ላይ የነበረ የጎረቤት ሰው

አህያህን አገኛሀት?” ብሎ የአህያዋን ጌታ ጠየቀው። ያህያዋ ባለቤትም፦ አፈላላጊየ አህያየን የሰረቃት ሌባ ሲሆን፤ እንዴት ላገኛት እችላለሁ? ብሎ መለሰለት።

የዚህች ጦማር መነሻና መድረሻ ተሰርቃ የጠፋቸውን አህያ እያማከለ የዛሬይቱን ኢትዮጵያን የሚገልጽ ስለሆነ፤ ባህያዋ ዙሪያ የሚሸከረከረውን ከላይ የተገለጸውን ሀሳብ እንጨብጠው። አህያይቱን ከባለቤቱዋ ሰርቆ፤ እንዳያገኛት ወደ ጫካ ወስዶ ካሰራት በኋላ፤ በመፈለግ ላይ ያለውን ባለቤቷን በምክርም በተግባርም ለመርዳት የቀረበው ሌባ ምንኛ ክፉ ሸፍጠኛ እንደሆነ ሳንረሳ ወደሌላ ክስተት እንሻገር።

በሁለት በሶስት ምስክርነት ነገር ሁሉ ይጸናል እንዲል መጽሐፍ፦ የዘመናችንን ሸፍጥ ለመረዳት የአራት ሌቦችን ክስተቶች ካህያዋ ሌባ ጋራ ደምረን እንመልከት። ባንድ ወቅት በሀገራችን ሌቦች በዙ፤ ሌብነታችሁን ተው ቢባሉ አልተውም። በረቱ ጉረኖው እየተከፈተ ኮርማው ሰንጋው የበጉ የፍየሉ ሙክት እየተዘረፈ ህብረተሰብ ታመሰ። ጸሐይ በጠለቀች ቁጥር ህብረተ ሰቡ እንቅልፍ አጣ። የረዥም ዘመን ታራካዊና ባህላዊ ሂደት ያለው ኅብረተ ሰብ ለገጠመው ችግር መፍቻ ይፈጥራልና፤ ሌባውን ዘራፊውን ከመካከሉ ለይቶ ላካባቢው ጎበዝ አለቃና ፋኖ የሚጠቁምበት ባንዳንድ ቦታ እውስ ፤ በሌላ ቦታ አውጫጭኝ አፍስርሳታም የሚባል ዘዴ ነበረው።

ዘዴው ቢኖርም ዘዴውን በመጠቀም ሌቦችን ከኅብረተስ መካከል ለይቶ ለሚመለከተው ጎበዝ አለቃና ፋኖወች ለማቅረብ ህብረተ ሰቡ የሚቸገርበት ወቅት አልፎ

አልፎ ይከሰት ነበር። ሌባው በአውጫጭኙ ከተጠቆመ በኌላ የጎበዝ አለቃው ርምጃ ከመውሰድ ቢዘገይ፤ ሌባው የጠቋሚውን ቤት ከማቃጠል፤ ሌላም አደጋ ከመፈጸም ስለማይመለስ ለመጠቆም ህብረተ ሰብ ይሰጋ ነበር።

የህብረተሰቡን ጭንቀት የተረዱ የቅኔ መምህር ሰረዝ የሚባለውን የቅኔ አይነት ዘዴ በመጠቀም ኅብረተ ሰቡን ለመርዳት ወሰኑ። የቅኔ መምህሩ ሰረዝ በሚባለው ፈሊጣዊ ቅኔያቸው የሌቦችን ስሞች ወደ አረፍተ ነገር ገልብጠው መናገር ነበረባቸውና የቅኔውን ፈሊጥ ፋኖወችና የጎበዝ አለቆች ብቻ አስቀድመው ተረድተው ቅኔውን በሚዘርፉበት በዚያችው ሰአት ሌቦችን እንዲይዟቸው መከሩ።

የቅኔው ምሥጢር በሌቦች ስሞች ላይ የተመሰረተ ስለሆነ አስቀድመን የሌቦችን ስም ብናውቅ፤ የባለ ቅኔውን ፈሊጥና ችሎታ፤ ኅብረተሰባችን ያለፈበትንም ውጣ ውረድ በግልጽ እንድንረዳው ያደረገናል፤ የልፋፏንም የጦማሯንሙሉ ሀሳብ እንድንጨብጥ ያግዛናል። ሌቦች አራት ነበሩ። 1ኛው አቶ ጀንበር ፤ 2ኛው አቶ ቢተው፤ 3ኛው አቶ በዛ 4ኛው አቶ ለማ ይባሉ ነበር።

የቅኔ መምህሩ በህዝብ መካከል ቆመው፦ ወገኔ ያገሬ ህዝብ ሆይ ስማብለው በመጀመር ሰረዛዊ ቅኔያቸውን ቀጠሉ። “እንደምታውቁት ሌባው ከቀድሞ ይልቅ እጅግ ለማ

  • ቁጥሩም ባዛ እንጅ ሲቀንስ አላየንም። ለኅብረተሰባችን መልካም ሊሆን ይችል የነበረው ሌባው ባይለማ፤ ቁጥሩ ባይበዛ መስረቁንም ቢተው ነበር። ችግራችንን የባሰ ያከፋው ሳያሰልስ ጀንበር በሰረቀ ቁጥር ለአውጫጭኝ ስራ መፍታታችን ነው። ይህ ሁሉ በመካከላችን እያለ የቀደመ ሰላማችንና መረጋጋታችን እንዴት ልናገኝ እንችላለን ብለው በመናገር ምሁራዊ፤ ክህነታዊና ዜግነታዊ ሐላፊነታቸውን ተወጡ።

በዚያ ዘመን የተከሰቱት አቶ በዛ፤ አቶ ቢተው፤ አቶ ለማ፤ አቶ ጀንበር የሀገርና የወገን ጠንቆች ነበሩ። በዚህ ክስተት ዘመናችንን ስለካበት ቁም ነገር ለመስራት ከሚታገሉ ከጥቂት ወገኖች በቀር፤ ያለበዛ የጥፋት አካል የለም። የቆሞሱ፤ የሰባኪው፤ የጳጳሱ፤ የቄሱ የዲያቆኑ የአክትቪስቱ የዶክተሩ ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም። በዚያው ላይ ደግሞ መላከ እገሌ፤ ሊቀሊቃውንት እገሌ፤ መጋቢ እገሌ፤ መምህር እገሌ በማለት ራሱን እየሰየመ በህዝብ ፊት የሚቆመው እንደዚህ ዘመን የበዛበት የለም።

ይህችን ዓለም ጠልቻታለሁ በውስጧ ካለውም ንብረትና ሁለንተናዋ ተጸይፌ ሸሽቻለሁ ብሎ የመነኮስ ጳጳስ የሁለት የሶስት ቪላ ጌታ ሆኖ ሳለ፤ “ዓለሙም ንብረቱም ሁሉም አላፊ ነውና ይህችን ዓለም አትውደዱ” የሚለውን አዋጅ በአውደ ምህረት ላይ ሲናገር ሀፍረት የማይሰማው ከሆነ፤ ሰባኪው ኃያላን መስለው የሚታዩትን የሚያወድስ፤ የተሳሳተ መርኌቸውን የማይነቅፍና ህሊናቸውን የማይጎንጥ ከሆነና ህሊናውንም ክዶ የወቅቱን ህዝባዊ ፍዘትና ትርምስ በመጠቀም መንፈሳዊነት በተላበሰ ሸፍጡ በብዝበዛው ላይ ካተኮረ፤ ፤ አክትቪስቶች ኢትዮጵያዊነትን ከጭንቅላቱ እያወጡ፤ ኢትዮጵያን እንዲበታትን፤ እርስ በርሱ

እንዲማታ በሚያደርግ ሸፍጥ መንፈሱን የሚያሰክሩት ከሆነ፤ ያችን ኢትዮጵያ እንዴት ላገኛት እችላለሁ? እያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመተከዝ ላይ ነው።

ትካዜው ሀሳቡና ጭንቀቱ ከላይ ከተዘረዘሩት ብቻ የሚመነጭ አልሆነም። አታለለን አፈዘዘን አደነዘዘን በማለት ሕብረተ ሰባችን የሚታዘበው አካላት እየበዙ ናቸው። በመብዛት ላይ ካሉት ክስተቶች አንዱና ዋናው ዛሬ ኢትዮጵያ አገራችን በምትመራበት ሕገ መንግሥት ውስጥ የተሰነቀረው ሸፍጠኛው አንቀጽ ነው። ይህ ህገ መንግስት የአማራውን ህልውና እና ኢትዮጵያዊነቱን የካደ፤ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር ሲሰዋለት ከነበረችው ከእናቱ ኢትዮጵያ ነጥሎ መጻተኛ ያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያን እንዴት ልናገኛት እንችላለን እያለ የወቅቱን መንግስት በመጠየቅ ላይ ነው።

የአማራውንና የቀሩትን ህዳጣን ጎሳወች ህልውና የካደው ህገ መንግሥት ለሀገራችን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሊሆን የሚችለው፤ ለየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ከመሆን እንዲታቀብ የሚያስጠነቅቅ እንደሆነ ይናገራል። ያማራውን ህልውና የካደው ሕገ መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ከማነኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እንዲገለል የከለከለበት ምክንያት፤ አባል ከሆነበት ፓርቲ አንድ ሰው ተከሶ ቢቀርብ በማዳላት ፍርድ እንዳያዛባ ነበር። ለህጉ መከበር ጥብቅና ቆሚያለሁ የሚለው መንግሥት፤ የህገ መንግስቱን ማስጠንቀቂያ ገሸሽ አድርጎ፤ የራሱ አባል የሆነውን ግለ ሰብ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቦታ ሰይሟል። ሕገመንግሥቱም፤ ሕግ አስፈጻሚው ምንግሥትም፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉም፤ ሁሉም በአማራው ኅብረተሰብ ዘንድ አህያዋን ሰርቆ ጫካ ካሰረው አፈላላጊ የተለዩ ሊሆኑለት አልቻሉም።

ጠቅላይ ምኒስተሩ ህገ መንግስቱ የማይቀበለውን ግለሰብ በጎናቸው ያሰለፉት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፤ እራሳቸው የሚፈጽሙትን ሁሉ ተግባር ከመደገፍ በቀር አማራጭ የለውምና፤ በሳቸው መንግሥት የሚከሰስውንና የሚወቀስውን ጥፋተኛ እንኳ ቢሆን ህብረተ ሰብ ባይቀበለው የማን ሀላፊነት ነው

ጥጋቡ ባየ የተባለ ወጣት በዚህ ንቃተ ህሊና እየታገዘ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ጠቅላይ ምኒስተሩ ተቀብለው ሕገመንግሥቱንም፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንም በህገ መንግሥቱ ላይ ያለውን የራሳቸውንም አቋም ማስተካከል ሲገባቸው፤ ጥጋቡ ባየን አድነው ማሰራቸው፤ ኅብረተሰቡ፦ ጠቅላይ ምኒስቴሩንም፤ ዓቃቤ ሕጉንም፤ ሕገ መንግሥቱንም፤ የጠፋችውን እንስሳ ደብቆ አስሮ ለማፈላለግ የቀረበውን ሰው መሰላችሁን ቢል፤ ኅብረተሰቡን ተሳሳትክ ለማለት ሞራል ያለው ማን ሊሆን ይችላል

በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ መቅሰፍት በጀነራል አሳመነው ላይ መደፍደፉን ኅብረተሰቡ ተጠራጥሮ፤ በገለልተኛ አካል ይጣራ እያለ ያቀረበውን ጥያቄ መንግሥት ከመቀበል ውጭ ምን አማራጭ ይኖረዋል

ነፍሳቸውን ይማርና ጀነራል አሳመነውን የጠቀስኩበት ዋና ምክንያት፤ በቁሜ የሰማሁት እኔ ልቅርና፤ እስከ ዓለም መጨረሻ የሚተካካው ትውልድ የማይረሳውና ሲቀባበለው የሚኖረው “እናንት የሃይማኖት አባቶች እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሁኑእናንት ሽማግሎችም” ብለው ያስተላለፉት መልእክት ትኩረቴን ሰለሳበው ብቻ ነው። ራሳቸው ሰወችን ይግደሉ፤ ራሳቸው በሰው ይገደሉ፤ የማውቀው ነገር ስለሌኝ፤ ልፈርድባቸው ወይም ላስፈርድባቸው አይደለም። ሁሉን ለሚመረምር ለሰማያዊው ኃያሉ እግዚአብሐርና ለምድራውያን ታሪክ ተመራማሪወች ትቼ ትኩረቴን ወደ ሳበው ኑዛዜያቸው እሻገራለሁ።

“እናንት የሃይማኖት አባቶች እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሁኑእናንት ሽማግሎችም እንዲሁ ብለው ያቀረቡትን ቃለ ኑዛዜ፤ ኅብረተ ሰቡ ደጋግሞ እንዲፈትሸው ከዕለት ወደለት ጫናው እያከበደው ነው። ህብረተ ሰቡ የተፈጸመውን ስህተት በጀነራል አሳመነው ላይ ፈጥኖ ከመደፍደፍ ቢያዘግምም፤ ጀነራል አሳመነው “እናንት የሃይማኖት አባቶች እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሁኑእናንት ሽማግሎችም እንዲሁብለው የተናገሩትን እያሰበ፦ክቡር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በተገደሉበት ወቅት፦ ልዑል ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት

”አሁን ለምን ሞተ ለምን ተቀበረ

ክፉ ለክፉ ቀን ይሆን የነበረ“ ብለው ያወረዱትን ምሾ በማንጎራጎር፤ ለጀነራል አሳመነውና ለሞቱት ሁሉ ወገኖች እያዘነና እየተከዘ ነው።

በአጸደ ሥጋ የሉም እንጅ ለጀነራል አሳመነው የማቀርብላቸው ጥያቄ ነበረኝ። በአጸደ ሥጋ ሆነው ባይመልሱልኝም፦ “ግብኢ ውስተ እረፍትኪ” ተብላ ወደ አጸዷ ለተሸኘችው ነፍሳቸው፤ አንች ነፍስ አንች ነፍስኧረ አንች ነፍስ እያልኩ ጥያቄየን አቀርብላታለሁ። በሥጋዘመንሽ የነበረው የሃይማኖት አባትነት ከአቡነ ጴጥሮስ አባትነት ጋራ የማይገናኝ መሆኑን ለመረዳት እንዴት አቅም ተሳነሽ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ለህዝብ ተላልፎ ሊሞት ይቅርና በየቅጽሩ የተጠጋውን አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑ ምነው ዘነጋሽበመጽሐፍ ላይ ያለውን ስንደብቅ እያየሽ፤ በመሬት ላይ ያለውን የምንደብቅ ያህያዋ አፈላላጊወች መሆናችንንስ እንዴት ሳትገነዘቢ ቀረሽ ። አንች ነፍስ ሆይ በሥጋሽ ወራት በነበርሽበት ጊዜ ትኩረትሽን በዘመኑ ባለው የሃይማኖት አባትነት ላይ ብቻ ሳትወስኝ፤ “እናንት ሽማግሎችም እንዲሁ” በማለት የዘመኑን ሽምግልና የገረፍሸው በንቀት ነበር። ወይስ ከዘመንሽ ሽምግልና የጠበቅሽው ቁምነገር ነበረሽ

ቅዱስ ጳውሎስ “ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ሰወች ላይ፤ ለመፍረድ እኔ ምናገባኝ እግዚአብሔር ይፍረድ፤በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት ላይ ሰወች ላይ አትፈሩድምን

1ኛቆሮ 5፡12_13) ሲል በሰጠኝ መመሪያ በሃይሞኖት አባትነት ላይ ብቻ የተሰማኝን በመናገር እወሰናለሁ። ይህን ስል በተልእኮየ ላይ የትኩረት ቅድሚያ ለመስጠት እንጅ፤ በዕድሜየ ክልል መጋለጥ ስለማልፈልግ ሽምግልናው አይመለከተኝም ብየ መዋሸት አልፈልግምና ከዚህች ጦማር በኋል ሽምግልናውንም ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ጀነራል አሳመነው “እናንት የሃይማኖት አባቶች እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሁኑብለው የተናገሩትን ቃል፤ ጠቅላይ ምኒስትር ዓቢይም እኮ “ስንሳሳት ገስጹን” ብለው ደጋግመው ነግረውን ነበር።

በዚህ ዘመን የምንገኝ እኛ ግን ”ከመ ንፍታህ ዘኢይትፈታህ“ እያልን በየቀኑ በከንፈራችን የምናስተጋባው ጸሎተ ኪዳናችን እንደሚያስገነዝበን፤ የሕብረተ ሰብ አቅም እንዳይፈታው አድርጎ የሕብረተ ሰብ ጠላት የተበተበውንና የቋጠረውን ሸርና ሸፍጥ እንፈታ ዘንድ የሚያስችለንን ከመለኮት የተሰጠንን እውቀት እምነት ጥበብንና ኃይል ረሳን። እየፈረሰ የሚያፈርስ ምድራዊ መንግስት ፍረሱ ሲሉን የምንፈርስ፤ ተለያዩ ሲለን የምንለያይ፤ ተጣሉ ሲለን የምንጣላ፤ ታረቁ ሲለን የምንታረቅ ሆነናል። ጠቅላይ ምኒስሩ “ስንሳሳት ገስጹን” እያሉ ደጋግመው የየነገሩን፤ ነግሬያችሁ ነበር ለማለት እንጅ የኛን ምንና ማንነት ሳይውቁ ቀርተው አይመስለኝም።

ጀነራል አሳመነውን የመሳሰሉ አልፎ ሃጆችም ሆኑ ጠቅላይ ምኒስተር ዓቢይን የመሳሰሉ ቆመው ተመልካቾች፤ በይፋ በመላው ህብረተ ሰብ መካከል የተናገሩትን ሳናደርግ ቀርተን የአህያ አፈላላጊወች ቢሉን አይደለንም ለማለት ምን ሞራል ይኖረናል

አቡነ ጴጥሮስን መምሰል አለመቻላችን እና ጠቅላይ ምኒስትር ዓቢይም “ስንሳሳት ገስጹን” ብለው የጠየቁንን መፈጸም ያቃተንና የአህያ አፈላላጊውን ባህርይ ለመከተል የመረጥንበት ምክንያታችን ምንድነው መንግሥት ተጣላ ሲልህ ተጣላ፤ ተለያይ ሲልህ ተለያይ፤ የተጣላህበትን የተለያየህበትን ችግር ሳታስወግድና ሳትፈታ ዝም ብለህ ታረቅ ሲልህ፤ ታረቅ የሚል ትምህርት ሊቃውንት አላስተማሩኝም።

ሲኖዶስ ሲከፋፈል ተከፋፈል፤ ሲክድ ካድ ሲያምን እመን የሚል ትምህርትም መምህሮቼ አላስተማሩኝም። ይልቁንም ለነገረ መለኮቱ እራሱን ላስገዛው ሁሉ ራስህን አስገዛ፤

ለጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን ክብርና ልዕልና ጥብቅና ቁም”ህሡ ሰላማ ለብሄር እስመ በሰላመ ብሄር ይከውን ንብረትክሙ” ማለትም፦ ህይወታችሁ ኑሯችሁ መንፈሳችሁ አካላችሁ አንድነታችሁ በጤና መኖር የሚችለው አገር ሰላም ሲሆን ነውና ለኢትዮጵያ ሰላም ቅድሚያ ትኩረት ስጥ“ ለሚለው ትእዛዛቸው እራሴን እያስገዛሁ፤ በዘመኑ ውሽንፍር በመናወጥ ላይ ያለው አዲሱ ትውልድ ቢሰማኝም ባይሰማኝም፤ በኛ ባህርይና አቅመቢስነት ጥንታዊት ቤተክርስቲያናችንን እየለካ እንዲህ ነበር እንዴ በማለት ከቤተ ክርስቲያኑ እንዳይርቅ እናገራለሁ።

በዘመኑ ትምህርት ከእውነቱ አድማስ ለመድረስ የሚረዱ premiss እና reason የመሳሰሉ የሀሳብ መሰላሎች እንዳሉ፤ ከዘመኑ ፖለቲካ ቀመር በፊት የነበረችው ቤተ ክርስቲያናችንም ከእውነት ወደብ ላይ ለማድረስ የሚያግዙ ብዙ ተመሳሳይ የሀሳብ መስላሎች እስመአኮኑ እና አምጣነ“ የመሳሰሉትን አስረጅወች ቀምራ ነበር።

ምናልባት ያባቶቻችንን የጻድቃንንና የሰማእታትን ትውፊት የማይቀበሉ ወገኖች መንገድም ቀመርም እኔ ነኝ የሚለው ኢየሱስ ብቻ ነው ይሉን ይሆናል። አባቶቻችን እሱማ

ምን ጥር ጥር አለው ይሉና፦ ራሱ ኢየሱስ በፍካሬው፦ ኢየሱስ ኢየሱስ እያሉ ያአህያ አፈላላጊ ሰባኪወች በስሙ እንደሚወሩን ያስጠነቀቀንን በዘጋንባት ቅጽበት ባአህያ አፈላላጊ ሰባኪወች እንደምንወረር አባቶቻችን ደጋግመው ነግረውን ነበር።

የከክርስቶስ ትምህርትና ምሳሌ ካአህያ አፈላላጊ ሰባኪነት የሚታደገን በባእዳን ቀመር ሳንጠለፍ ”በዙሪያችን እንደደመና ያሉልን“ የራሳችን አባቶች ቀምረው በሰጡን ኢትዮጵያዊ ስነ ሕሊና መተርጎም ስንችል ብቻ እንደሆነ ነግረውናል።

አዱሱ ትውልድ እራሱን እንዲቃኝ ካዳዲስ ክስተቶች ጋራም እንዲያገነዘብ የሚገጥሙትን ጎጅና ጠቃሚ ክስተቶችን ለይቶ እየተረዳ በፊቱ የሚጋረጡበትን ፈታኝ ክስተቶች እየሰነጠቀ እንዲሻገር፡ የሚረዳው ስለሆነ ኢትዮጵያዊነት ስነ ሕሊና እንድናቀብለው አደራ ብለውን ነበር።

ይሁን እንጅ በዚህ ዘመን ላይ ያለን የሃይማኖት አባቶች የተቀበልነው አደራ መስዋዕት የሚያስከፍል መሆኑን ጠልቀን ሳንገነዘብ ክብሩንና ጥቅሙን ብቻ በማየት ራሳችንን ያሰለፍን በመሆናችን እውነቱን ሰዋሪወችና ደባቂወች ከአህያዋ አፈላላጊ ሌባ የተሻልን ሆነን አልተገኘንም። አህያይቱን ከባለቤቱዋ ሰርቆ፤ በጫካ ውስጥ ካሰራት ባኋላ፤ “ጅብ እንዳይሻማህ ወደ ሌላ ቦታ ፈልጋት” በማለት አቅጣጫ እያሳተ ወደ ጅቦች መንጋ የመራውን አፈላላጊ ያአህያዋ ሌባ ሆነናል።

ኢትዮጵያን ከወራሪ ጅቦች ሲታደግ ከኖረው ከቀደመው የሃይማኖት አባትነት እጅግ ርቀን በተቃራኒው መሰለፋችን ህዝባችንን እጅግ እጅግ በጣም እጅግ በማሸማቀቅ ላይ ነን። “The sheep of Ethiopia delivered from the hyenas of the west by the doctrines

of st. Cyril the great” ማለትም፦ኢትዮጵያ በምዕራቡ ጅብ ከመበላት የተረፈችው በታላቁ በቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት ነው” እያሉ የጻፉት እነ Iris Habib el Masri የዘመናችንን የሃይማኖት አባትነት ቢመለከቱት ምንኛ ይታዘቡን ይሆን እያልኩ በመሸማቀቅ የእኔም ሰውነት ደቀቀ።

አባቶቻችን ከንቱ ውዳሴ የማይሹ፤ ታሪካዊ ውለታም የማይረሱ በመሆናቸው Habib የተናገሩትን እንዳለ የተቀበሉ አልነበሩም። የቅዱስ ቄርሎስን ትምህርት በመጠቀም ኢትዮጵያን ከወራሪ ጅቦች ያዳኑበትን ያባቶቻችን ያተረጓጎም ክሂሎት ለማሳየት ለምሳሌ ያህል ከቄርሎስ ትምህርት ይህችን እጠቅስለታለሁ። “ንህነሰ ንተሉ ሥርአተ ወህገ ከመ ክርስቶስ አምሳሊነ እንዘ አምላክ ውእቱ ናሁ ኮነ ስብአ ወኢወጽአ ግሙራ እምስብሀተ መለኮቱ ። ወለእመኒ ኮነ ውስተ ክፍል እምነ ፍጡራን ውእቱሰ ይትሌዐል ላዕለ ኩሉ ፍጥረታት። እንዘ ሐጋጌ ሕግ በመለኮቱ ናሁ

ኮነ መትሕተ ሕግ ወነበረ በዘቦቱ ሐገገ ” (ቄርሎስ ሃ. ም .70፡ቁ 4

ማለትም፦እኛስ ምሳሌያችንን ክርስቶስን በመከተል ለሰብአዊ ስርአትና ህግ እንገዛለን፤ ምሳሌያችን ክርስቶስ ሰውም ቢሆን ከመለኮታዊ ባህርይው ፈጽሞ አልተለየም። በለበሰው ሰውነቱ ሰባዊ ባህርይ ቢካፈልም ከፍጡራን በላይ ነው። ከፍጡራን በላይ በሆነው መለኮቱ ሕግ ሰሪና ሰጭ ሲሆን ደግሞ ራሱ ለሰራውና ለሰጠው ህግ ተገዥ ሆነ” ብሎ ቅዱስ ቄርሎስ የተናገረውን፤ ሊቃውንት አባቶቻችን ከብሄራዊ ነጻነት ጋራ አዋህደው እና ከሰብአዊ ማንነት ጋራ አገናዝበው በህብረተ ሰቡ ህሊና በማስቀመጣቸው እንደሆነ የታሪክ ምስክሮች ይናገሩላቸዋል።

የቄርሎስ ትምህርት ብቻማ ለብሄራዊ ነጻነት በቂ ቢሆን፤ መጽሐፉን በየቋንቋቸው ተርጉመው የሚያነቡ ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን ለምን አገራቸውን ከወረሯቸው ጅቦች እንዲያተርፉበት አልረዳቸውምየራሱን የቄርሎስን ህዝብና አገር ለምን ከጅብ አላዳነውም እያሉ እነ የኔታ ቢረሳው ይጠይቁና ”የቄርሎስ ትምህርት ሊሰራ የሚችለው ኢትዮጵያውነትን ከመሰለ ስሜት ጋራ ሲዋሀድ ብቻ ነው“ እያሉ ይመልሱታል።

ያም ሆነ ይህየሃማኖትን አባትነትን ደብቀን የመዝረፊያና የግል ክብር ማስጠበቂያ ያደርገነውን የዘመናቸውን የሃይማኖት አባቶች፤ አቡነ ጴጥሮስን እንድንሆላቸው የሻቱት ጀነራል አሳመነው በጣም ተታለው እንደነበረ ተገነዘብኩላቸው።

ወገኔ ኢትዮጵያዊ ሆይከሕንጻወች ጋር ክርስቲያኖችን በሚያቃጥሉት አረመኔወች በነጃዋር ላይ ርምጃ ላለመውሰድ የሚያቅማማ መንግሥት “አዲስ አበባ የመላ ኢትዮጵያ ኅብረተ ሰብ ናት፤ መላው ኢትዮጵያዊ ኅብረተሰብም የአዲስ አበባ ነው” በማለታቸው ብቻ በእነ እስክንድ ነጋ ላይ ጦርነት እያወጀ፤ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞትም ኢትዮጵያዊ“ ብሎ የነገረንን ቃል ብቻ በማመን፤ በሸፍጥና በጥላቻ አርሮ በተኮማተረው በእነ ጃዋር ጭንቅላት ውስጥ የታሰረችውን ኢትዮጵያን እንዴት ልናገኛት እንችላለን ይቆየን

በተረፈ ኃያሉ እግዚአብሄር በኢትዮጵያና በህዝባችን ላይ የሚካሄደውን ግፍና መከራ እንዲያቆምልን እየተመኘሁ፦ ጀነራል አሳመነው “እናንት ሽማግሎች በምድር ላይ ያለውን እውነት ተናገሩ” ባሉት ርእስ እንገናኝ እያልኩ እሰናበታችኋለሁ።

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop