ሃምሌ 9 ቀን 2011 ዓም(17-07-2019)
የሚፈልጉትንና የሚሹትን በቅጡ አለማወቅ የተለያዬ አቋምና ውሳኔ ላይ ያደርሳል።ወይም በአግባቡ ሳያጤኑ በችኮላ የደረሱበት ውሳኔ የዃላዃላ ከጸጸት ላይ ይጥላል።በፍቅርና በጠብም የኸው አይነቱ ችኮላ የማታ ማታ ጸጸትን ይወልዳል።ለዚያም ነው ነብሱን ይማረውና ታዋቂው ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም ሲል ያቀነቀነው።በዚሁ ላይም አልቆመም እፍፍ ያሉት ፍቅር የያዙት ቸኩሎ ፣ይገነፍልና ያቃጥላል ቶሎ ሲል ጨምሮበታል።
ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም።በአለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በተለይም ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት ወዲህ በአገራችን ፖለቲካ ዙሪያ የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ በአገር ውስጥና ውጭ አብዛኛው ሕዝብ በተለይም እውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለውጥ መጣ ብሎ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ቡድን በተለይም ኮሎኔል ዶር አብይ አህመድንና አቶ ለማ መገርሳን በሚናገሩት ዲስኩር ተማርኮ ከሰውነት ደረጃ አውጥቶ ከሰማያት አማልክት ባልተናነሰ ደረጃ አስቀምጦ ሲያመልክባቸው ታዝበናል፤ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህም ወደ ነበሩበት ማንነት ፊታቸውን ሲያዞሩ ግራ በመጋባት ተገልብጦ ዓይናችሁ ላፈር ሲላቸው ለመስማትና ለማዬት በቅተናል።በዚህ የመገለባበጥ አዙሪት ላይ የተጠመደው ህብረተሰብ ለወደፊቱም ከዚህ አይነቱ ጅዋጅዌ ይላቀቃል ብሎ መገመት ስህተት ይሆናል ፤ስለሆነም ከዚህ አይነቱ አባዜ የሚላቀቅበትን መንገድ መጠቆም ተገቢና አስፈላጊ ነው።
ከላይ በጥላሁን ገሰሰ የዘፈን ስንኞች የተገለጸው መልእክት ሊገነዘብ የሚችል አይምሮ ላለው ሰው ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆን ነበር።ለዚያ ግን አለመታደል ሆኖ እንደ ቀላል ነገር ተመልክተን ሳንጠቀምበት ቀረን።ለመጣ ለሄደው በምናዬው ሳይሆን በምንሰማው ዲስኩር ብቻ የሰውን ማንነት እየፈረጅን ለመታለል ችለናል።
ደርግ ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም ብሎ አገራችንን የደም አሸንዳ አድርጓት አለፈ፣ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ የብሔር እኩልነት እስከ መገንጠል ድረስ በሚል አገር አጥፊ መመሪያ አሁን ሕዝብ በሰላም የማይኖርበትና ኢትዮጵያም እንዳገር የማትቀጥልበትን አደገኛ ስልት እራሱ ባረቀቀው “ በሕገመንግሥት” ተብዬው ጸረኢትዮጵያዊነትን ቀምሮ አስቀመጠ።ብዙዎቻችን በቸልታ አለፍነው።
በደርግም ጊዜ ሆነ በወያኔ መራሹ አሁን ደግሞ በኦህዴድ(ኦዴፓ)ፊትአውራሪነትት በሰፈነው ጸረ ዴሞክራሲ አገዛዞች ላይ የተነሳውና አሁንም የሚነሳው የሕዝብ ጥያቄ ፣የሰብአዊና የዜግነት መብት እንዲከበር፣ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት የሚተጋና የሚሠራ ፣ሕዝቡን ማእከል ያደረገ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን፣አሁን ሕዝቡን እርስ በርስ የሚያጋጭና የሚያፈናቅል፣ያገርንም አንድነት አደጋ ውስጥ ያስገባው በጎሳ የተዋቀረው መንግሥትና የሚመራበት “ሕገመንግሥት”እንዲወገድለት ነው።ይህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄ ግን በስልጣን ላይ በወጡ አፈጮሌዎች እየተሸፋፈነ ሕዝብ የመከራ ቀንበሩ ሳይወርድለት፣የሚሻውንም ሳያገኝ፣ በግፍ ላይ ግፍ እዬተሰራ አሁን ላለንበት እንደ አንድ አገር ሕዝብ ላለመኖር ከሚቻልበት ወቅት ላይ ደርሰናል።
አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የኮሎኔል ዶር አብይ አህመድ መንግሥት ንጹሃን ዜጎችን በጎሳ ማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው እያሳደደ በመግደልና በማሠር ላይ ተሰማርቷል።ይህ እንደሚሆን ለማወቅ ቀላልና አመላካች እውነታዎች ነበሩ። እራሱ አብይ አህመድ የኢሕአዴግ መሪ እንደሆነና የኢሕአዴግን ሕገመንግሥት አክብሮ ለማስከበር እንደሚታገል በግልጽ ነግሮናል።ሰሞኑንም የኢሕአዴግን ሕገመንግሥት ያላከበረ የፖለቲካ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ብሎም ለምርጫ ለመቅረብ
እንደማይችል ነግሮናል።ቢንቀሳቀስ እርምጃ እንደሚወስድ ባይናገረውም በተግባር እያሳዬን መጥቷል።ከዚህ የበለጠ ግልጽነት ከዬት ይመጣል?ወይንስ ላለማገናዘብና የለም አንተ የተለዬህ ነጻ አውጭአችን፣ ሙሴያችን ነህ ለማለት አዚም ወረደብን።ታዲያ በኢሕአዴግነቱ በኢሕአዴግ አርጩሜ ቢቀጣን ፣እንደነባር የኦነግ አባልነቱስ ለኦሮሚያ ለተባለ አገር ምስረታ ደፋ ቀና ቢል ይፈረድበታል?በእኔ በኩል አይፈረድበትም።ለቆመለት ዓላማ እዬሠራ ነው።የቆምንለትን ዓላማ ያላወቅንና አቋም የሌለን እኛ ነን።በዲስኩር ለሚያማልለን ለመጣ ለሄደው እያጨበጨብን አምባገነን የምንፈጥረው እኛው ነን።የምንፈልገውን በቅጡ አውቀን ለዚያ በትጋት አለመታገላችን ዛሬ ለሚታዬው የመደገፍና የመቃወም ጅዋጅዌ አጋልጦናል፤ዓላማ ቢሶች አድርጎናል።በውሃቅዳ ውሃመልስ ድካም ውስጥ ከቶናል። የነውጠኞችና የጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎችና ቅጥረኞች ማላገጫ ሆነናል።ከኢሕአዴግ ሰፈር ለውጥና ዴሞክራሲ ይመጣል ብሎ ከመጠበቅ ሌላ ምን ጅልነት ይኖራል?ከዶሮ ወተት አይታለብም!
ኢሕአዴግና አባል የጎሳ ድርጅቶች የሚወገዱ እንጂ የሚወደዱ አይደሉም።አንዳንድ የዋሆች ወይም እያወቁ አድር ባዮች ፣አማራጭና ተቃዋሚ ሳይሆኑ በተፎካካሪነት ስም ለሚሰራው ድራማ እያጨበጨቡ ለመንግሥት አጃቢ ሆነው ሕዝብን ሲያጭበረብሩና ሲያወናብዱ ማዬት ለጊዜው የተሳካ ተውኔት ቢመስላቸውም ነገ የሚገቡበት ቀዳዳ እንደሚጠፋቸው ለመናገር ነብይ መሆንን አይጠይቅም።
ለእውነተኛ ለውጥና ለአገር አንድነት የምንታገል ኢትዮጵያውያን ያለን አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው።ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱትንና ያሰፈሰፉትን የውጭና የውስጥ ሃይሎችን ለመቋቋም የሚችል አንድ አገራዊ ሃይል ማቋቋም የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።ለዚያ ግንባታ የገንዘብ፣የሞራልና የእውቀት አስተዋጽኦ ማድረግ ከማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ ይጠበቃል።ያንንም አደራ የሚወጣ አካል መፍጠር የግድ ይላል።ለዚህ ተግባር የየበኩላችንን ለማበርከት ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፤በእኔ በኩል ዝግጁ ነኝ።
ይህንን ዓላማ በማድረግ አብረው ሊሰለፉ የሚችሉ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉት የሙያና የብዙሃን ድርጅቶች፣ አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የህብረተሰብ ተወካዮች የተሳተፉበት አካል መፍጠር ሲሆን ዓላማው የጎሰኞችን ሥርዓትና የነሱ መጠቀሚያ የሆነውን ” ሕገመንግሥት” ማሶገድና በኢትዮጵያዊነት ካስማ ላይ የቆመ፣አገራዊ ራዕይ ያነገበ፣አገር ለማረጋጋት የሚችል፣ ለቋሚ መንግሥት መንደርደሪያ የሚሆን ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የሽግግር መንግሥት መመስረት ነው።
የጠራ ዓላማና ጠንካራ አቋም ለዘለቄታ ድል ዋስትና ነው።
ኢትዮጵያ በአንድነት ለዘላለም ትኑር!!
አገሬ አዲስ