(አሸናፊ በሪሁን ከSeefar)
ወጣትነት ለሥራ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት ዕድሜ እንደመሆኑ፣ የአንዲት አገር ዕድገት፣ ለውጥና መሻሻል ወይም ለዚህ ተቃራኒ ውጤት በየዘመኑ ባለው የወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ የሚወሰን ነው። ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ትናንሽ ከተሞች የሚፈልሱ እንዲሁም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በተለያያ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ ከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያዎች ሆነዋል። የአገሪቱን ከተሞች ያጨናነቁ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮባቸዋል። በአገራቸው ሥራ አግኝተው የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት እየተጋለጡም ነው ።
በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑት ዜጎች ቁጥር 71 ከመቶ ነው። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ቁጥር ደግሞ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፥ ከእነዚህም ውስጥ በኦፊሴላዊ ግምት ብቻ የ16.5 በመቶ የሚያድግ የሥራ አጥነት እንዳለ ይነገራል። ምንም እንኳን ኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ነው ቢባልም በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው አዚህ አምራች ኀይል አቻ የሚሆን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ግን አልቻለም”።
በ2011 የወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የልማት ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው 77.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከሁለት የአሜሪካን ዶላር ባነሰ የገንዘብ መጠን ነው።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወጣቱን ጥም ማርካት እንዳልቻለ ይተቻል። በየአመቱም ሁለት ሚሊዮን አዲስ ስራ ፈላጊዎች ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአርባ በላይ ከሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችም በየአመቱ ከ150 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አገሪቷ ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን መፍጠር እንዳለበት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የስራ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡ ከባለፈው አመት ጀምሮም መንግስት የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የስራ ፈጠራ መነሻ የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ በጀት መድቧል። ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮችም ከበጀታቸው በመቀነስ በተመሳሳይ ሁኔታ በጀት በመመደብ ስራአጥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ነው ተብሎል፡፡
በቅርቡ ለፓርላማ አመታዊ ሪፖርት ያቀረቡት ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 11 ሚሊዮን በላይ ስራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከእኒዚህም መካከል ለ 3 ሚሊዮን ያህሉ በመጪው አመት ስራ ለመፍጠር መታቀዱን ይፋ አድርገዋል፡፡ የዕቅዳቸው አንዱ አካል ደግሞ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን ወደ አረብ አገራት መላክ ነው ፡፡ ለዚህም 50 ሽ የሚሆኑ ወጣቶችን በዚሁ ዓመት ወደ አረብ ሀገራት ለመላክ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ደግሞ 250 ሽ ወጣቶችን ወደ አረብ ሃገራት ለመላክ ዕቅድ ተይዞል፡፡ አነዚህ ወጣቶች በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ አገራት መላክ ከራስ አልፎ ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ ወጣቶቹ የራሳቸውን ዕውቀት ከማሳደግ ባለፈ ከሚገኙበት አገር በሚልኩት ገንዘብ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጅ ሽግግርና ያገኙትን ልምድ በማካፈል የአገራቸውን ኢኮኖሚ በመደገፍ የድህነት ምጣኔ ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋኦ ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪም በሚሄዱበት አገር የስራ ቦታ ክፍተትን በመሙላት ያግዛሉ። በውጭ የሚኖሩ ስደተኞች የአገራቸውን ባህልና ልዩ ምርቶች ለመላው አለም በማስተዋወቅም ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡
3 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው በሚልኩት ገንዘብ( Remittance) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 2010 ከሪሚታንስ 1 .9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያገኘች ሲሆን በ 2017 ገቢው ወደ 4.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ብሏል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሪሚታንስ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አለው፡፡ከውጪ የሚላከው ገንዘብ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 5% የሚሆነውን የሚሸፍን ነው፡፡በርግጥ ይህ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡ ለምሳሌ ላይቤሪያ በስደት በውጭ ከሚገኙ ተወላጆቿ የምታገኘው ገንዘብ ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርት 26 ነጥብ 7 በመቶውን ሲይዝ ሌሴቶም 18 ነጥብ 2 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ የሚላክላቸውን ዜጎች ከፍተኛ መሆኑ የኢትዮጵያ ከሪሚታንስ የሚጠበቀውን ያህል እንዳታገኝ አድርጎል ፡፡ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ሀገራት ቀዳሚዎቹ አሜሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣልያን ሲሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ የሚላከውም ከእነዚሁ አገራት ነው። ባለፈው 2017 ከአፍሪካ ናይጄሪያ 21 እንዲሁም ግብፅ 20 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ አገራት መሆናቸው የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል። ሕንድ 69 ቢሊዮን ዶላር፣ ቻይና 64፣ ፊሊፒንስ 29 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከሪሚታንስ ገቢ በማግኘት ከዓለም ከአንድ እስክ አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።ይህም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ከተሰማራ ሀገራቸው ከ’ሪሚታንስ’ ከፍተኛ ገቢ እንደምታገኝ በጥቂቱ ማሳያ ነው ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለመንግስት ከፍተኛ ራስ ምታት የሆነው የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም ዘረፈ ብዙ እና መጠነ ሰፊ የሆነ አማራጮችን መዘርጋት እና መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለም አሁን በአገሪቱ የሚታየውን መሰረታዊ የስራ አጥነት ችግር ከስሩ መፍታት ይቻላል፡፡