ምሕረት ዘገዬ (አዲስ አበባ)
እንደየሰው ቢለያይም ሀገር በመፈራረስ ጠርዝ ላይ እያለች ዝም ማለት አያስችልም፡፡ ምንም ለውጥ ባናመጣ ቢያንስ የሚሰማንን የምንናገር ዜጎች ልንወቀስ አይገባም፡፡ ተያይዘን ልንጠፋ ከአንድ ክረምት ያነሰ ጊዜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ብዙዎች እንደዘመነ ኖኅና ሎጥ በፈንጠዝያና በቸበርቻቻ ባህር ሰምጠው ግዴለሽ ሆነው ሲታዩ ወዴት እየሄድን እንደሆነ በእጅጉ ያሳስባል ብቻ ሳይሆን ክፉኛ ያስጨንቃል፡፡ የደርግ መንግሥት በወያኔና በሕዝብ የዝምታ ዐመፅ እየተንኮታኮተ ባለበት የመጨረሻዋ ሰዓት ግንቦት 18 እና 19 1983ዓ.ም መርካቶ ሄደው የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሶፋ የሚገዙ ሚኒስትሮችና ታላላቅ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንደነበሩ በጊዜው ሰምተናል፡፡ ከማግሥቱ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ግን የነዚያ ሰዎች ቤት ከርቸሌ ነበር – ሊያውም የታደሉት፡፡ ብዙዎቻችን ስለነገው ጉዳያችን ላለማሰብ ምን እንደሚያሳውረን አይገባኝም፡፡ የአሁኑ ሁኔታ ደግሞ ከመቼውም የባሰ አስጨናቂ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠረውና ከመንግሥት ጀርባ ያለው አሰለጥ ኃይል በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሚነዳ ሣይሆን በፈግጠው ፈግጪው የብተና መንፈስ የሚዘወር የፀላዔ ሠናያት ስብስብ ነው፡፡ ያ ነው እጅግ የሚያሳስበን፡፡ ብርጭቆ ከወደቀ ያለመሰበር ዕድሉ አነስተኛ ነው፤ ከተሰበረ ደግሞ ለመጠገን ያለው ዕድል በዜሮና በአንድ መቶኛ መካከል ነው – ሊያውም የፈጣሪ እገዛ ከተጨመረበት፡፡
ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ትናንት አንዱ እንዲህ አለኝና አስደመመኝ፡፡ ግን ሰሚ ጠፋ ታዲያ፡፡
“አየህ ምሕረቴ! አውሮፓና አሜሪካ ዜጎች መበለሻሸት ከጀመሩ ብዙ ዘመናት አለፉ፡፡ ሃይማኖትና ጨዋ የሚሰኝ ሞራላዊ ዕሤት ተቀብረው ሰዎች ወደ እንስሳነትና ከዚያም የወረደ ብልሹ ማንነት ወርደዋል፡፡ ለምሣሌ የሶዶማውያንን ሁኔታ ላጫውትህ፡፡ ጌይና ሌዝቢያን ስለሚባሉት፡፡ እነዚህ ብዛት ያላቸው ዜጎች ልጅ አይወልዱም፡፡ በተመሳሳይ ፆታ ልጅ ስለማይወለድ፡፡ የልጅ አምሮታቸውን የሚወጡት ከአፍሪካና መሰል ሀገራት የማደጎ ልጆችን ወስዶ በማሳደግ ነው፡፡
የሚወስዷቸውን ልጆች ሲያሳድጉ ታዲያ እንደነሱ ዓይነት ባሕርይ እንዲኖራቸው አድርገው ነው፡፡ ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ያን ለኛ ሰይጣናዊ የሆነ ዕኩይ ጠባይ እንዲለማመዱት ያደርጋሉ፡፡ ከነሱ ፊት ይሳሳማሉ፤ ይተሻሻሉ፡፡ በጥቅሉ አይሆኑ መሆንን እየሆኑ የሚያሳድጓቸውን ሕጻናት በነሱ ፈለግ ቀርጸው ያሳድጓቸዋል፡፡ እነዚያ ልጆች ወደ ጤነኛው ማኅበረሰብ ወጥተው ጤናማ ግንኙነትን ሲመለከቱ ካደጉበትና እንዲሆኑ ከሰለጠኑበት የጌይና የሌዝቢያን ባሕርያት ውጪ ስለሚሆንባቸው ለነሱ መጥፎ የሚሆነው ጤናማው ግንኙነት እንጂ ሸፋፋው አይደለምና እነሱም እንዳሳዳጊዎቻቸው ይሆናሉ፡፡ ለነሱ ትክክለኛ መስሎ የሚታያቸው ያ በአሳዳጊዎቻው የተለማመዱት የሚቀፍና የሚዘገንን ኢሞራላዊ ልምምድ እንጂ ጤናማው የማኅበረሰብ ግንኙነት አይደለም፡፡ ወደው አይደለም ማለት እንችል ይሆናል፡፡ ግን በዚያ መልክ ስለተቀረጹ ለራሳቸውም ሆነ ለማኅበረሰቡ የሚያስትሉት ጉዳት ከባድ ነው፡፡ ከነዚህ ዓይነት ከምንጫቸው ከተበላሹ ዜጎች ደግሞ ምንም ዓይነት ደግ ነገር መጠበቅ አይቻልም፡፡ እነዚህን ብልሹ ወገኖች በሥርዓትና በአግባብ በመነጠል ጉዳት እንዳያደርሱ ማድረግ ብቻ ነው ዋናው መፍትሔ፡፡ ገባህ?”
እንዲህ ሲለኝ በንግግሩና በተመሳስሎኣዊው ገለጻው (አናሎጂው) ተደመምኩ፡፡
አዴፓም የተጣባው ችግር ይህን መሰል ነው፡፡ ስለዚህ ሰፊው የአማራ ሕዝብና በተለይም ወጣቱ ልዩ ሥልት ቀይሶ ይህን በወያኔና በተተኪው ኦህዴድ የተበለሻሸ የምግባረ-ቢሶች ድርጅት ጠማማ አካሄድ ማስተካከል አለበት፡፡ ሀገር ተረካቢው ወጣት በወያኔ ሤራና ሸር ከተዘፈቀበት የሱስና የዓላማ ቢስነት ቋጠሮ በአፋጣኝ ወጥቶ ሀገራዊ ራዕይ ይላበስ፡፡ የነገይቱ ኢትዮጵያ ይበልጥ የምትጠቅመውም ሆነ የምትጎዳው እርሱን ነውና፡፡ አዴፓ ተብየዎቹ ግን ልክ እንደእስካሁኑ ሁሉ በጀመሩት የአሽከርነት ጠባያቸው መንጎድን ምርጫቸው ካደረጉ መላውን የአማራ ሕዝብ ባወጣ ቸብችበው የነሱንም ወረደ መቃብር ማቃረባቸው አይቀርም፡፡ እንደ አቃቂ የጋሪ ፈረስ ዐይናቸውን በወያኔና በምትኩ ኦህዲድ ተሸብበው በብልግናቸውና በክህደታቸው ከቀጠሉ የሚያስከትሉት ጉዳት ዘመን አይሽረውም – ምልክቶቹንም ከወዲሁ እያየን ነው፡፡ … አማራ ንቃ!! የመቀበሪያ ጉድጓድህን ለሚቆፍሩ የታሪክ ጠላቶችህ በር አትክፈት፡፡ በሠርጥና በጎጥ እየተከፋፈልክም ጠላት በቀደደው ቦይ አትፍሰስ፡፡ የትም ይኑር፣ የትኛውንም ሥልጣን የየትኛውም ጎጥና ሸጥ ሰው ይያዘው አማራ አማራ ነው፡፡ ወሎና ጎጃም፣ ሸዋና ጎንደር የአስተዳደር መለያ ሃሳባዊ ወሰን እንጂ ለንዑስ ዘረኝነት ሊዳርግ አይገባም፡፡ ወንዘኝነት ከአማራ የከፍታ ደረጃ በታች ነውና አያምርበትም፡፡ በዕውቀትና በችሎታ ይሁን እንጂ ሁሉንም ሥልጣን የቅምብቢት ወይም የአቸፈር ወይንማ ሰዎች ቢይዙት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ኮታ አጥፊ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ያጠፋት አንዱ ኮታ ነው – ሊያውም ቀደም ሲል ወያኔ አሁን ደግሞ ኦህዲድ ከላይ ሆነው የሚዘውሩት ጥርስ አልባ የኮታ ሹመት፡፡ ዐይናችን ይከፈት፡፡
ኦነግና ኦህዲድም ዕድሜ ለወያኔ እያሉ አንሻፎ የፈጠረላቸውን የትሮይ ፈረስ አዴፓን በመጠቀም ይህን ታላቅ ሕዝብ መቀመቅ እንደሚከቱት መታወቅ አለበት፡፡ ሰሞኑን ባሕር ዳር ላይ ተፈጸመ የተባለው ግድያና ዕልቂትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የአማራን ሕዝብ እንደናቁት በግልጽ ያስመሰከሩበት ክፍተታችን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የማን እጅ እንዳለበት ወደፊት ታሪክ የሚያወጣው ቢሆንም ብዙ ነገሮችን መጠራጠር ግን ይቻላል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው መጯጯህ አይደለም፡፡ የሚጮህ ምንም አይሠራም፡፡ የሚሠራ አይጮህም፤ የፕሮፓጋንዳ ጋጋታም አይሻም፡፡ የንግግርን መጥፎ ጎን እያየነው ነው፡፡ ልጆቻችንን (እንደተባለው እርስ በርስም ይሁን በእጅ አዙር በሌላ ኃይል) ያስጨረሰብን ይሄው “እንዲህ እናደርጋለን/አናደርግም” የሚባል የወሬ ቱማታ ነው፡፡ አንዳንዴ በርግጥም ዝምታም ወርቅ ነው፡፡ መናገር በሚያስፈልግ ወቅት ልንነግረው ለሚገባን አካልና ለሚመለከተው ሰው ብቻ እንናገር፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ ነው፡፡ ብልኃት የሚጎድለው ስሜታዊ ንግግር ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ከፕሮፌሰር አሥራትና ቀጥሎም ከኢንጂነር ዶክተር ቅጣው እጅጉ የማይረሳ ትምህርት ቀስመናል፡፡ “ሙያ በልብ” ትልቅ አባባል ነው፡፡ ይህን ሁሉም ይረዳና በሞረሽ እየተጠራራ የተደቀነብንን የአደጋ ጊዜ ለማለፍ እንሞክር – ማለፉ የማይቀረው ጨለማ ዘመን ብዙ መስዋዕትነት እንዳያስከፍለን እንጠንቀቅ፡፡ በአማራ ላይ የተቀሰሩ ጣቶችና የተሰበቁ ጦሮች ተቆጥረው አይዘለቁም፡፡ ሴትዮዋ “ዕድሌ ሆኖ ፈሴ ይሸታል” ያለችው ወድዳ አይደለም፡፡ አማራው “አገሬ፣ አገሬ” በማለቱና ለአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራው ቆላ ደጋ ተንከራትቶ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር የአፍሪካ ኩራት የምትሆን አንዲት አገር በመፍጠሩ በክፉ የሚያዩት የውጭ ሀገር ጠላቶችና የሀገር ውስጥ ተባባሪዎቻቸው እንደአሸን ይፈሉበት ይዘዋል፡፡ በ“ጠላቴ ጠላት” መርኅ ከወዲያ ከወዲህ እየተጠራሩ እስትራቴጂያዊ ኅብረት በመፍጠር አማራን ለማጥቃትና ከዚያም በኋላ የመጨረሻውን ዘውድ ለመጫን ራስ በራሳቸው ለመፋጀት የቋመጡ ኃይሎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ የአማራው አስተዋይነት የሚፈተነው አሁን ነው፡፡ ጉራና ጩኸት፣ ስድብና ዘለፋ፣ የቃላት ጦርነትና የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ በዚህ ዘመን እምብዝም አይጠቅምም፡፡ አጉል ጀብደኝነትና ባልተቀናጀ መልኩ በተናጠል የሚገለጥ እልኸኝነት በልባምነትና በመዋቅራዊ ቅርጽ ተለውጦ ጥቅም ላይ ካልዋለ ጎጂ ነው፡፡ ጠቅላላ ዓለም አቀፋዊ ብዛታቸው አሥራ ስምንት ሚሊዮን የማይሞሉ ጸዮናውያን ዓለምን የሚያንቀጠቅጡት በምን ሁኔታ ውስጥ አልፈውና ለምን በዓላማም ቆመው እንደሆነ ለመረዳት ሩቅ ሳንጓዝ የትናንቶቹን የሕወሓት አባላትን በምሥጢር በመጠየቅ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ነው ብዛት ዋጋ የለውም የምልህ – ብልጥነትና ብልኅነት፤ አይበገሬነትና ከፋም ለማም የዓላማ ጽናት እንጂ፡፡
እናም ዋናው ቀድሞ መገኘት ነው፡፡ ዋናው በኃይል ሚዛንም ይሁን በአደረጃጀትና በብስለት በልጦ መገኘት ነው፡፡ ብዛት ብቻውን ደግሞ ወንዝ ከማያሻግር ጊዜያዊ የሥነ ልቦና እርካታ በዘለለ ምንም አይፈይድም፡፡ ስለሆነም አማራውን ለማንቃትና ለማደራጀት፣ ከኢትዮጵያዊነቱ ሳይፋታ ኅብረቱን አጽንቶ ለአንዲት ሀገር ምሥረታ እንደቀድሞው ሁሉ እንዲዋደቅ ማንቃት፣ ማስታጠቅና ማደራጀት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ ደግሞ ከፍ ሲል በመግቢያችን እንደተገለጸው በመጥፎ አስተዳደግ የተበከለውን አዴፓን ማመን ለአደጋ ሊዳርግ ይችላልና ጠንቀቅ ማለት አይከፋም፡፡
ሀብትና ሥልጣን የሚሠሩበት ጊዜ አለ – አሁን ግን ዋጋ የላቸውም፡፡ በአንድ ብልጭታ የክብሪት እሳት ዐመድ ለሚሆን ሀብትና የገንዘብ ክምችት የምትራወጡ ወገኖች ራሳችሁን መርምሩና ወደ ኅሊናችሁ በቶሎ ተመለሱ፡፡ ያ ይደርሳል፡፡ አሁን ወቅቱ አገርን የማዳን ዘመቻ የሚቀድምበት ነው፡፡ በአንድ ጀምበር በሚቀር የሥልጣን ሽኩቻ ተጠምዳችሁ በከንቱ የምትጃጃሉም አደብ ግዙ፤ ከነአምባቸውና ምግባሩም ተማሩ፡፡ ከዚህ በላይ ምን ማለት ይቻላል? ምንም፡፡