በኢትዮጵያ አሁን ለሚታየው ውጥንቅጥ መፍትሄው ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም (ድጋፌ ደባልቄ)

ድጋፌ ደባልቄ
ጁላይ 12፣ 2019

በኢትዮጵያ አሁን ለሚታየው ውጥንቅጥ መፍትሄው ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም

  • ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ዲሞክራሲ የለም ሊኖርም አይችልም:: ዲሞክራሲን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመገንባት የሚያስችሉ ተሰፋ ሰጪ ሁኔታዎች ግን አሉ፡፡በመሆኑም ለውጡን ተከትሎ የዲሞክራሲ ስርአትን በተቋማዊ መልክ ለመገንባት የሚያስችሉ መሰረቶች እየተጣሉ ነው፡፡
  • በአንድ አገር የዲሞክራሲ ምህዳር አለ ብሎ ለማለት ቢያንስ ሁለት መመዘኛዎች መሟላት አለባቸው፡፡ አንደኛው ዲሞክራሲን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚተገብሩ የሚጠብቁና የሚከላከሉ ተቋማት መኖር፡፡ ሁለተኛው በማህበረሰቡ ውስጥ የዲሞክራሲን መሰረታዊ ባህርዮች የሚያንፀባርቅ ባህል (ዲሞክራሲያዊ ባህል) መታየት ሲጀምር ወይንም መኖር ናቸው፡፡
  • ያለነበት ወቅት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህልና የፖለቲከኞቹን ግልብና የረዥም ጊዜ ራእይ የሌለው አስተሳሰብና አመለካከትን በግልፅ መመርመርና መፍትሄ መሻት የሚያስፈልግበት ነው፡፡

 

መግቢያ

ለበርካታ አስርተ አመታት በአገራችን በተለያዩ የርዕዮተ አለምና ምናባዊ ቅርፆች ሲንገታገት የቆየው የዲሞክራሲ የፍትህ የእኩልነትና የነፃነት ትግል አሁን ካለበት ተስፋን ከሰነቀና ስጋትን ከቋጠረ እርከን ላይ ደርሷል፡፡ ይህንን ትግል እዚህ ደረጃ ላይ ለማድረስ ደግሞ በተለያዩ ወቅቶችና የትግል ሜዳዎች ወጣቶች አዛውንት ገበሬዎች ሰራተኞች በጥቅሉ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ወገኖቻችን ከህይወት እስከ አካል መጉደል ከግርፋት እስከ ስደት የሚደርስ ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ የተከፈለው መስዋዕትነትና በዚህም ሂደት ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ፈተናዎች ተደምረውና በትውልድ ድምፅ ታጅበው ከግብ እናደርሰው ዘንድ ይጣራሉ ይሞግቱናልም፡፡ ይህ ጥሪ ሁላችንም የዚህች አገር ጉዳይ ያገባናል የምንል ሁሉ ቀበቶአችንንና መቀነቶቻችንን አጥብቀን እንድንንሳ የሚጋብዝ ሲሆን ትግሉን ከግብ ለማድረስ ደግሞ የትግሉን ውስብስብነትና የተጋረጡብንን ፈተናዎች በሚገባ ነቅሶ ማውጣትና ተገቢ ስልት መቀየስ በእጅጉ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ በየጊዜው እየወደቀና እየተነሳ ለዚህ የደረሰው ዲሞክራሲን ባገራችን የማስፈን ትግል ከአምባገነናዊ ገዥዎች ጋር በተደረጉ ትንቅንቆች ከሞት ከእስርና ከስደት ጋር የተያያዙ በርካታና ለመንፈስ በእጅጉ የሚዘገንኑ መስዋእትነቶች አስከፍሏል፡፡ እነኚህ ጥቃቶች በኢሰብአዊነታቸውና በአሰቃቂነታቸውና እስራትን የአካል ጉዳትንና ሞትን ከማድረሳቸው አኳያ በተደጋጋሚ የሚነሱና ብዙ የተነገረላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእነኚህ የግፍ እምባዎች በስተጀርባ ጎልተው የማይነገርላቸውና  የማይነሱ  ነገር ግን በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ህመም ያደረሱ የጥቃት አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህም በሰነልቦና በስነ አእምሮ በሞራልና በስነ ምግባር ላይ የደረሱ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ያለፉትን ሃምሳ አመታት ብቻ ከግምት አስገብተን ብንመረምር እንኳን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የደረሰው መሪር ጥቃትና ያስከተለው መዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ይህም በመሆኑ ባገራችን ከግለሰብና ከቤተሰብ አልፎ የጋራ የስነ አዕምሮ ህመም (collective trauma)  ለመኖሩ በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡እነኚህ ምልክቶችም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ በባህል በስነምግባር በሞራልና በስነስርአት ባህርዮች በኩል ራሳቸውን ይገልፃሉ፡፡

በኢኮኖሚና በፖለቲካው በዳበሩ አገሮች እንዲህ ያለ ግፍ የተፈፀመበት ሰው ቀርቶ ግፉ ሲፈፀም በርቀት የተመለከተና የታዘበ እንኳን ለስነ አእምሮ ጉዳት ( trauma) ተጋልጧል በሚል የስነ ልቦና ምክርና የህክምና ድጋፍ ይቀርብለታል፡፡ እርግጥ ነው ባገራችን ይህንን አይነቱን የጤና መታወክ በሚመለከት በቂ የሙያተኛም ሆነ ተቋማት አለመኖር ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ስር የሰደደና የተንሰራፋ ለመሆኑ በግል በማህበረሰብና በመንግስት ተቋማት ደረጃ ዕውቅና ያለመሰጠቱ በራሱ ለችግሩ የተቀናጀ ትኩረት እንዳይሰጥ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ያገራችንን የተወሳሰበና የተቆላለፈ የፖለቲካ መሰናክል ለመሻገር ደግሞ ለዚህ አይነቶቹ ችግሮች ትኩረት መስጠትና ተገቢ መፍትሄ መሻት የሁሉንም ዜጎችና ተቋማት ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ በአስተሳሰቡ በምናቡና በራእዩ ጤናማ ያልሆነ ማህበረሰብ ምንም እንኳን በቁጥር አናሳ ቢሆን የሚያሳድረው በጎ ያልሆነ ተፅእኖ ግን ኢምንት ነው ብሎ መገመት ስህተት ነው፡፡ የተጓዝንበት የፖለቲካ ጎዳና የተወልንን ፍርስራሽና ጉድፍ ጠርገን ካሳደረብን የመንፈስ የሰነ ልቦናናን የስነ አእምሮ ህመም አገግመን አስተሳሰባችንንና አመለካከታችንን ባዲስ መልኩ መቅረፅ ካልቻልን ለውጡን በምንፈልገው ፍጥነትና ብቃት ማስኬድ አንችልም፡፡

በውስጣዊ የለውጥ ኃይሎች የሚመራው  አገርን ወደ ተሻለ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስርአት የማሻገር የለውጥ ጉዞ ከተጀመረ በኃላ እንደ ማንኛውም በሰደት ሲባዝን እንደኖረ ትውልደ ኢትዮጵያ ወደ ምናፍቀው ወገኔና ትውልድ አገሬ ለመመለስና ከወዳጅ ዘመዶቼና ከአገሬ ህዝብ ጋር ለመገናኘት በቅቻለሁ፡፡ይህ በራሱ እንደ ትልቅ ፀጋ የምቆጥረውና ለዚህ እንድንበቃ መስዋትነት ለከፈሉት ሁሉ ምስጋና የማቀርብበት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አገር ቤት በቆየሁባቸው ወራቶች ውስጥም የአገራዊ ለውጡን ሙቀትና ቅዝቃዜ ተሰፋና ስጋት የማየት የማድመጥና የመታዘብ መልካም ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡

ለረዥም ጊዜ ሲወድቅ ሲነሳ የኖረው የዲሞክራሲ ትግል እልባት ሊያገኝ ወደ ሚችልበት አቅጣጫ መጓዝ መጀመሩ ተስፋየን አጎልቶታል፡፡ ይሁን እንጂ ለረዥም አመታት የተካሄደው የትግል ጉዞ የፈጠራቸው የተቆላለፉ ችግሮችንና የፖለቲካ ባህሉን ኃላ ቀርነት ሳስብ ደግሞ የስጋት መንፈስ ይፈጥርብኛል፡፡ ከዚህም የተነሳ የተጀመረው የለውጥ ሂደት በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል ወደ ሚል ድምዳሜ እንዳመራ አስገድዶኛል፡፡ በመሆኑ እነኚህን ውስብስብ ፈተናዎች እንዴ ነው አገራችን ተሻግራ ወደምንፈለገውና ወደ ምንመኘው ጎዳና የምታመራው?  በሚለው ሃሳብ ዙሪያ በሚቀጥሉት ጥቂት ገፆች መሰረታዊ ችግሮቹ ያልኳቸውንና የመፍትሄ ሃሳቦቹስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ከሙያዬና ከዜግነት የኃላፊነት ስሜት የሚመነጩ አስተያየቶችን ለማጋራት እሞክራለሁ፡፡ እነሆ የችግሮቹ ምንጮች ናቸው የምላቸውንና የታዘብኳቸውን አንኳር ሃሳቦች እንደሚከተለው ላቅርብ፡፡ በቅድሚያ ግን አንባቢዎቼ እንዲገነዘቡልኝ የምፈልገው ይህ ፅሁፍ በመደበኛ የጥናትና የምርመር ( empirical evidence) የተደገፈ ሳይሆን በማድመጥና በመታዘብ ( observation) ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመሆኑም በነኚህ ባገር ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ባሉ ጉዳዮች ላይ በሚገባ የታቀደና የተቀናጀ ጥናት አስፈላጊነትንም በዚሁ አጋጣሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

አበይት አገራዊ ችግሮችና መሰናክሎች

The function of education is to teach one to think intensively and to think critically. Intelligence plus character – that is the goal of true education.                                              

                 —Martin Luther King, Jr.                                                                                                           

የትምህርት ስርአቱ የፈጠረው የዕውቀት የብቃትና የሞራል ቀውስ

በየእርከኑ ያሉ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡት የትምህርት ጥራት ደረጃና አይነት ባብዛኛው ባንድ ወገን ርዕዮተ አለማዊና ፖለቲካዊ  አመለካከትና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ የተነሳ የትምህርት ተቋማቱ እውቀት የሚገበይባቸው ሳይሆኑ ካድሬ የሚፈለፈልባቸው ተቋማት ሁነው ቆይተዋል፡፡ ይህ ያንድን ወገን የፖለቲካ ደቀ መዝሙር ማፍራትን አላማውና ግቡ አድርጎ የተቀረፀ ስርአት የትምህርትን መሰረታዊ መርህና ትርጉም ያልተከተለ ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት በተለይም የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ኃላፊነት ለማስተማር በራቸውን ከፍተው የተቀበሉዋቸውን ተማሪዎች ጥናትና ምርምራቸውን ለማከናወን ምን ማሰብ እናዳለባቸው ሳይሆን እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው ነው አቅጣጫ ማመላከትና መቅረፅ የሚኖርባቸው፡፡ የጥልቅ ሃሳብን (critical thinking) ብቃት ማዳበር ከእነዚህ ክትምህርት ከሚገኙ ውጤቶች ውስጥ አንዱና ዋነኝው ነው፡፡ ይህንን ከማድረግ ይልቅ የእትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያተኮሩት እንደ ካድሬ ማሰልጠኛ ተማሪዎች ምን ማሰብ እንዳለባችውና ከዚያም ጋር ተያይዞ ሊገኙ የሚችሉ ንዋያዊ ጥቅሞች ላይ ማተኮርን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በወጣቶቹ በሚኖሩበት ማህበረሰብና ባገሪቱ ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሷል፡፡ለአንድ ግለሰብ ማህበረሰብና አገር እንደ አእምሮአዊ መነፅርና ሞራላዊ አቅጣጫ ማመልከቻነት ሊያገለግሉ የሚችሉ እንደ ፍልስፍና ማህበራዊ ሳይንስ እና ሌሎችም ከእነኚህ ጋር የተያያዙ የትምህርት አይነቶች በቁጥርም ሆነ በጥራት ደረጃ ያሽቆለቆሉ በመሆናቸው በተመራቂዎች ላይ ለሚታየው የሰነ ምግባር የሞራልና የብቃት ችግር ከፍተኛና አጥፊ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

ለምሳሌ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የምህንድስና ዘርፍ “ ተመራቂዎች” ባሉበት አገር ዛሬም ድንች ብዙም ምርምርና ጥናት በማይጠይቀው መላጫ (peeler) ሳይሆን በቢላዋ ነው የሚላጠው፡፡ ቡናን ለአለም ያበረከትች አገር ዛሬም በአገር ደረጃ የኤሌክትሪክ መፍጫ ማምረት አቅቷት ከሙቀጫ ወቀጣ አልወጣችም፡፡ የትምህርት ስርአቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረትና ቅድሚያ እንዲሰጥ ተደርጎ ነው የተቀረፀው ከተባለ የዚህ  አይነቱ ትምህርት ውጤት ማለትም የማህበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል አኳያ በምንድን ነው የሚለካው ? ከፍልስፍናውም ከሳይንስና ቴክኖሎጂው ያልሆነው ትውልድስ በምንድን ነው የሚካሰው? ይሄ በኔ ግምት በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግስት መዋቅሮች በሚገባ አጥንተው መልስ ሊሰጡበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ብዙዎች በተደጋጋሚ ሃሳባቸውን መሰንዘራቸው ቢታወቅም ጉዳዩ  ባገርና በትውልድ ላይ ካደረሰው ኪሳራ አኳያ ሊሰጠው የሚገባው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብና ለዚህም የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ መሰራት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ከአገር ህልውና ጋር የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ትምህርት የሚያጎናፅፈን  በርካታ የእውቀትና የአስተሳሰብ መነፅሮች አሉ፡፡ከእነኚህ ውስጥ ግን ዋነኛው አለምን ህይወትንና ሃላፊነትን የምናይበት ምናብ ነው፡፡አልፎም ከዚህ ጋር የተያያዙ (existential) ጥያቄዎችን የምናነሳበትን መንገድ ያስተምረናል፡፡ደስታ በምን ይለካል? ደስታ ከምን ይገኛል? በዚህ ምድር ላይ ስኖር ኃላፊነቴ ምንድነው? የህይወት ትርጉሙ ምንድነው? ሞራል ግብረ ገብነትና ስነ ምግባር ምንድናቸው? የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው? ወዘተ የሚሉትን እንድንጠይቅ ያነሳሳናል፡፡ ለእነኚህ ጥያቄዎች መልስ ፍለጋ በምናደርገው መባዘት ውስጥ ነው ማንነታችንን የምናገኘውና ለህይወትም ትርጉምና ኃላፊነትን የምንሰጠው፡፡ለእነኚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በምናደርገው መኳተን ውስጥ ነው በዝህች አለም ላይ በምንቆይበት አጭር ጊዜ ውስጥ ኃላፊነታችንንና ቦታችንን የምናገኘው፡፡ ይህንን በመሰረታዊነት ደረጃ በተማሪዎቹ አእምሮ ውስጥ ማስገባት ያልቻለ የከፍተኛ  ትምህርት ተቋም የዲግሪና ዲፕሎማ መፈብረኪያ እንጂ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመሆን መመዘኛውን አያሟላም፡፡ ትምህርት ትውልድ ይቀርፃል፡፡ ትውልድ ደግሞ አገር ይገነባል፡፡ በመሆኑም የትምህርት ተፅእኖ በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡

የሞራል ዝቅጠት – “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ

ያንድ ማህበረሰብ ሞራላዊና ሰነ ምግባራዊ መሰረቶች የሚቀረፁት በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንደኛው በቤተሰብና በማህበረሰብ  ሲሆን ሌላኛው በተቋማት ማለትም ትምህርት ቤቶች የኃይማኖት ተቋማት የበጎ ፈቃደኝነት ተቋማትና ( formal institutions) ነው፡፡ ከእነኚህ ተቋማት የሚገኘው በጎም ይሁን በጎ ያልሆነ የሞራልና የሰነ ምግባር ምሳሌነት በአጠቃላይ የማህበረሰብ ሞራላዊና ስነ ምግባራዊ ጤንነትም ሆነ ህመም ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የተቀመጡ የመንግስት ባለስልጣናት የኃይማኖት መሪዎች መምህራን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ታዋቂ የስፖርት ሰዎች በእለተ ተእለት ኑሮአቸው በሚያሳዩት የባህርይና የስነምግባር ማንነት ተፅእኖ ያሳድራሉ ፡፡ የእነኚህ ግለሰቦች ተፅዕኖ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ እጅግ ጠለቅ ያለ ነው፡፡ እነርሱን የመምስልና የሚያደረጉዋቸውን ሁሉ ለመቅዳት ወጣቶች ባለ ማወቅም ይሁን በማወቅ ( consciously and subconsciously)  ቢጣጣሩ የሚያስገርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ከመናገር ጀምሮ በእግሩ ቆሞ እስከ መሄድ ድረስ የሚማረው ከሌላው ሰው ነውና፡፡ በጎውንና መልካም መልካሙን ከሰው እንድ ምንቀስም ሁሉ ክፉውንና ጥፋቱንም እንዲሁ ከሌላ ሰው ነው የምንማረው፡፡

ይሁን እንጂ ባገራችን የኪነ ጥበብ ሰዎች ባብዛኛው የየራሳቸውን ተከታዮች ለማፍራት ጥቂት ቅኝቶችና ድራማዎች ከመወርወር የዘለለ ወጣቱን በስነ ምግባር ለመቅረፅ ያደረጉት ቀጥተኛ ጥረትም ሆነ የምሳሌነት ተግባር ከግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ የሙዚቃውም ሆነ የሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች መመዘኛ በማህበራዊ ኑሮ በሞራላዊ ንፁህነት ወይንም በሰነ ምግባራዊ ምሳሌነታቸውና አስተማሪነታቸው ሳይሆን ፍሬ ከርስኪ የሆነ ይዘታቸውንና መልእክታቸውን ባደመጠው ወይንም በተመለከተው ህዝብ ቁጥርና በተከፈላቸው የገንዘብ መጠን ነው የሚለካው፡፡ ከዚህም አልፎ በፖለተከኞች የቁማር ስራ ተከፋፍሎ ማህበራዊ አንደነቱና ግንኙነቱ የላላውን የተከፋፈለ ማህበረሰብ እንደ ንግድ ዕድል  ( business opportunity) በመጠቀም ከዚህ አገራዊ መከፋፈል ጥቅምና ዝናን ያተረፉም አሉ፡፡ የኪነ ጥበብ አንዱ ስራ አገሮችንና ህዝብን ማቀራራብ እንጂ መራራቁን እንደ አጋጣሚ ተጠቅሞ ማራገብ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያንና የኤርትራና የሰላም ግንኙነት ከማነሳሳትና እንዲዳብርም ከማድረግ ረገድ  በሁለቱም ወገን ያሉ የኪነ ጥበብ ስዎች በጎ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህ እሰየው የሚባልና በምሳሌነትም ሊጠቀስ የሚገባ ነው፡፡

ባገራችን በፖለቲከኞችና በህዝብ መካከል ግንኙነት (accessibility) የለም፡፡ በህዝብ ተመረጥኩ የሚለው ፖለቲከኛ በተመረጠ ማግስት ራሱን ከህዝብ ማራቅና መኮፈስ ህዝብን እንዲያገለግል ሳይሆን ህዝብ እንዲያገለግለው ሆኖ እንደተመረጠ ያስባል በተግባርም ያሳያል፡፡ ይህ ራስን ከጣራ ላይ አውጥቶ አልወርደም የሚለው አመለካከት ለወጣቱ ትውልድ የሚያስተላልፈው መልዕክት በእጅጉ የተዛባና ህዝብን ማገልገል ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማይገልፅ ነው፡፡ በረዥም ያገራችን ታሪክ ውስጥ የተፈፅመውና ዛሬም የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ታዲያን ወጣቱ ትውልድ የፖለቲካ ተምሳሌቶቹን የሚያገኘው ከየት ነው? ሌላው ባገራችን የፖለቲካ ሰውነት መታጀብን በጥሩ ቤት ውስጥ መኖርን መንደላቀቅንና ሌላውን ዜጎችን ወደታች ከማየት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወደፊት በፖለቲካ ለመሳተፍ   እዚህ ላይ አሁን ባገራችን እየተካሄደ ካለው የለውጥ ጉዞ ግንባር ቀደም መሪዎች ከሆኑት አንዱ ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ የጀመሩት ራሳቸውን accessible የማድረግና በዕለት ተዕለት ስራቸው ምሳሌ የመሆን ተግባራቸውን በእጅጉ እውቅና መስጠትና ማመስገን ተገቢ ነው፡፡

የሚታየው የሞራል ዝቅጠት መንስኤዎች በርካታ ቢሆኑም ዋነኛውኝ ከስርአት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባንድ ወቅት በመዲናይቱ ካነጋገርኳዋቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ ለምን አገር ቤት ውስጥ ንብረት አንደሌለኝና “እንደሌሎቹ” አፓርትመንት እንዳልሰራሁ ሲጠይቁኝ ለመለስኩላቸው መልስ የሰጡኝ ምላሽ  ክፉኛ ነው ያስደነገጠኝ፡፡ እኔ ያልኩት “አይ ወደ ፊት ሁሉም ነገር ስርአት ይዞ ማንም ከቤቱ ሳይፈናቀል ማንም የእርሻ መሬቱን ሳይለቅ ፍትሃዊ የሆነ መሬት ካገኘሁ ቤት እስራለሁ ስላቸው፡፡ “ አይ ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብሮ መዝረፍ እንጂ ጥግ ቁሞ ማየት ምን ይበጃል” ነበር ያሉኝ፡፡ እንዲህ አይነቱ የዘቀጠ አመለካከት ምን ያህሉን ማህበረሰብ እንደ ሚወክል የተጠና ቀጥር ወይንም መረጃ ባይኖረኝም ካነጋገርኩዋቸው ሰዎችና ከታዘብኩት እውነታ ተነስቼ ስገመግም ይህ አይነቱ አሳፋሪ ሃሳብ በእጅጉ የተንሰራፋ መሆኑን መታዘብ ችዬአለሁ፡፡

የሞራል ዝቅጠቱ የሚገለፅባቸው መንገዶች በንዋያዊ መልኩ ብቻ አይደለም

ዋሾነት ሌብነት ቅጥፈት አጭበርባሪነት የአሉባልታ ወሬ ማራገብ “ ተባለ” ና “ በሬ ወለደ” ን እንደ መሪ ባህርይ አድርጎ መታየት እንደ ማያሳፍርና እንደ ማያሸማቅቅ ድርጊት ሁኖ ማየት አንገት ያስደፋል፡፡ የትምህርት በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ዋነኛው ውጤት በመረጃና በማረጋገጫ (empirical evidence) ላይ የተደገፈ እውነትን መሻት ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ወሬንና አሉባልታን ሃሜትንና ሹክሹክታን ከእውነት ለይቶና አበጥሮ መለየት ያለማወቅ ብቻ ሳይሆነ ይህንኑ ያልተረጋገጠ “ በሬ ወለደ” ማራገብ ሙያቸው ያደረጉ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያደረሰውና በማድረስ ላይ ያለው ጉዳት ከግልና ከቤተሰብ አልፎ አገርንም ያካትታል፡፡በምንም በማንም ላይ ተራምዶ “ ገንዘብ መስራት” በሚል ከሰብእና እርከን በእጅጉ ዝቅ ያለ የንዋይ ፍቅር በእጅጉ ተንሰራፍቷል፡፡ ሁሉም ነገር የሚሽከረከረው በገንዝብና በንዋይ ዙሪያ አድርጎ የማየት ባህል እንደ ወረርሽኝ ተንሰራፍቷል፡፡በግለሰብና በማህበረሰብ መካከል የሚፈጠር  ግንኙነት ንዋያዊ ( transactional) ከሆነ አንዱን ከሌላው የሚያስተሳሰሩ በሞራልና በስነ ምግባር ላይ የተመሰረቱ እንደ በጎ አሳቢነት ለሌላው ደህንነት መቆርቆር ታማኝነትና ( non transactional and value based)የመሳሰሉት ከጠፉ ክህደት ሌብንት ዋሾነት አጭበረባሪነት ይነግሳሉ፡፡ይህ ደግሞ በአገር ላይ ከውጭ ወራሪ ከደረሰ ጥቃት በላይ አደጋ ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡ አጉራ ዘለልነት  በእጅጉ ከመበራከቱ የተነሳና የፖለቲካው  መስመር የለቀቀ ጉዞ ተደምሮበት በተለያዩ ቡድኖች መካከል የሚካሄዱ ኳስ ጨዋታዎችን እንኳን ማካሄድ የማይቻልበት እውነታ ላይ ተደርሷል፡፡ አጉራ ዘለልነት (hooliganism) ከዘር ፖለቲካ ጋር ተዳቅሎ የፈጠረው ባህልና ወግ የለሽ መሆን አልፎ ከተራ የእግር ኳስ ደጋፊነትና ተቃዋሚነት ዘሎ የህግ የበላይነትን ያለማክበር አገራችን የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የባህልና የሞራል ቀውስ ውስጥ መሆንዋን በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለጥምር ጎሳ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን! - አገሬ አዲስ

ማድመጥ ያለብን ለተናጋሪው የምንሰጠውን መልስ እያሰብን መሆን የለበትም፡፡ ስናዳምጥ ማድመጥ ብቻ ነው ያለብን፡፡ ይህ ነው ማድመጥን ከመስማት የሚለየው አንዱና ዋነኛው መመዘኛ፡፡

ማድመጥ ሙቷል

ዘመኑ ያፈራቸው የማህበራዊ ግንኙነትና የመረጃ መለዋወጫ አውታሮች በርካታ በጎ ጎኖች ያሉዋቸው ቢሆኑም በተጓዳኙ ደግሞ አደገኛ ገፅታዎቻቸው መላውን አለም በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዳብረናል ብቁ ተቋማትንም ገንብተናል የሚሉትን ሳይቀር በእጅጉ እያስፈራና እያሰጋ ይገኛል፡፡ ከአገራችን ጋራ በተያያዘ መልኩ ግን ይህ ችግር በእጅጉ ቅጥ እያጣና መረን ለቅቆ ባብዛኛው ላገር ችግር መፍትሄ ማፈላለጊያ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ የችግሩ አራጋቢና አቀጣጣይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አሉባልታና ወሬ “ ሰበር ዜና” ለመረጃነት ቀርቶ ለተራ ወሬ እንኳን የማይበቃው ደግሞ “ ሰበር መረጃ” “ ጥብቅ መረጃ” እየተባለ በየማህበራዊ ሚዲያውና በዩቱብ ጣቢያዎች እጅግ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ማረጋጋጫና  ተዕማኒ ማስረጃ በሌለው መልኩ ይለቀቃሉ፡፡ እንዲህ አይነቱ ከመልካም ውጤት  ይልቅ ጥፋትን አብሮ መኖርን ከማዳበር ይልቅ መራራቅን ከፍ ሲልም ደም መቃባትን ሊያስከትል የሚችል አደገኛ አጉራ ዘለልነት ነው፡፡ ከመናገር ከመፃፍና ሃሳብን በነፃ ከመግለፅ ጋርም በምንም መልኩ ያልተገናኘ የጥላቻና የማናቆሪያ መልእክት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም ስያሜ ሊሰጠው አይችልም አይገባምም፡፡

ከዚህ ጋርም ተያይዞ የ “ አውቃለሁ” ባይነት መንፈስ በእጅጉ ከመንስራፋቱ የተነሳ ሁሉም ተናጋሪ ዙሪያው ሁሉ የፖለቲካ ተንታኝ መሆኑን መታዘብ ተለምዷል ፡፡ የሚገርመው የፖለቲካ “ተንታኝ” መኮኑ ሳያንስ አንድ ግለ ሰብ የወታደራዊ የቀጠናዊ የባህላዊ የኢኮኖሚያዊ የአየር ፀባይ የግጭት ባህርዮችን ተንታኝና መፍትሄ አቅራቢ ሁኖ ወይንም ሁና ማየትና ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የአገራዊ እውቀት ልክ ምን ያህል መቀጨጩን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን አውቃለሁ ባይነትና እኔን ብቻ አድምጡኝ ባይነት ምን ያህል እንደተንሰራፋ ያሳየናል፡፡ የማድመጥ ጥበብ ወይንም (the art of listening) ዛሬ ባለማችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከሚሰጡት ስልጠናዎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከማድመጥ ዕውቀት ስለ ሚገኝ ብቻ ሳይሆን ማድመጥ በውስጡ የያዛቸው በርካታ ፋይዳዎች ወይንም (qualities) ስላለው ነው፡፡ ከእነኚህም ውስጥ አክብሮት ( respect) ጥያቄዎችን የመጠየቅ ብቃት ማዳበር ለምሳሌ በስራ ውስጥ በሚገባ የሚያዳምጡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ሲችሉ በሚገባ ያልተከታተሉት ግን በስራ ውጤታቸው ደካሞች እንደ ሆኑ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ያሳያሉ፡፡ ማድመጥ የጥበብ መቅሰሚያ ክህሎት ብቻ ሳይሆን በራሱ ጥበብ ነው፡፡ ብርቱ አንባቢ ጎበዝ ፀሃፊ እንደሚሆን ሁሉ ጥሩ አድማጭም ጥሩ ተናጋሪና ሃሳቡን በሚገባ ለአድማጩ የማጋራት ብቃት ይኖረዋል፡፡ በዚህ ሁሉም ተናጋሪ በሆነበትና በጫጫታና በቁም ነገር በንግግርና በድንፋታ መካካል ያለው ልዩነት በጠፋበት ዘመን የማድመጥ ጥበበን መማርና ማዳበር   ያዳበረና በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ያግዛል፡፡

ዘመኑ ከፈጠረው ቴክኖሎጂዎች ጋር የተፈጠረው ቅርበትና ቁርኝት ሁሉ ወደ እውቀት አያመራም ወይንም እውቀትን አያጎናፅፍም፡፡ እንደውም ውጤቱ ወደ ተቃራኒው እየሄደ መሆኑን መታዘብ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው የዘመኑ የኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መረጃንና ለእውቀት መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ ሰነዶችን ላብዛኛው የአለም ክፍል ተደራሽ አድርጓል፡፡ ይህ በእጅጉ ሊወደስ የሚገባው ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ጥፋትን የሚሰብኩ ጥላቻን የሚኮተኩቱ ስነ ምግባርን የሚያዘቅጡ ወዘተ ሰነዶች በዚህ የዘመኑ ስልጣኔ ዱር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሞራልና የስነ ምግባር ልጓሞች በተመናመኑበት እውነታ ውስጥ የእነኚህ ሰነዶችን የጥፋት መልዕክት የሚያሰራጩና የሚተገብሩ ደግሞ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እመርታና የቴክኖሎጂ ለውጥ ያሳየበትና እንዯ ቀዴሞው እለታዊ ዜናዎችና መረጃዎች የሚገኙት ከተለመድው መገናኛ ብዙሃን ማለትም ከሬዴዮ ከቴሌቪዢንና ከህትመት ጋዜጦች ብቻ አይደለም። ይልቁንም የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች እንደ አሸን መፍላት ባንድ በኩል የመረጃ ልውውጥን ቅጽበታዊ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ የመረጃን ጥራትና እውነተኛነት ከጥያቄ ውስጥ አስገብቷል። በመሆኑም የህዝብ መገናኛ አውታሮች የአገርን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነትና መቀራረብ በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ  ሃላፊነት ይጠበቅባቸዋል።

መፍትሄው ምርጫና ፖለቲካ ብቻ አይደለም

ታዲያን ብዙውን ጊዜ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የለውጥ ጉዞ ስኬትና መሰናክል ሲነሳ ባብዛኛው እንደ መልስ ሁኖ የሚቀርበው የፖለቲካ መፍትሄ ነው፡፡ “ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ከተደረገ” “ የመናገር የመሰብሰብ የመፃፍ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ከተከበረ” ወዘተ ወዘተ የሚሉ ፖለቲካዊ የመፍትሄ ሃሳቦች ይደረደራሉ፡፡ ይህን እንደ መፍትሄ የሚያቀርቡት ደግሞ በፖለቲካ እውቀት እምብዛም ያልተካኑ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲካ ሙያችን ነው የሚሉና በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ የሚሳተፉም ይገኙበታል፡፡ ይህ የሚመጣው አንድም የአገሪቱን ችግር ከተለያዩ ማእዘናትና አቅጣጫዎች ማየት ያለመቻል ሲሆን ሌላው ውስብስብ ( complex)ችግሮችን በሚገባ የማጤንና ለችግሮቹም በቂ ምላሽ የሚሆን መፍትሄ ለማቅረብ ካለ መቻል የሚመንጭ ይመስላል፡፡ አዎ ለአገራችን ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ አንዱ ነው፡፡ይሄ ብዙም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ግን የተለመዶ (conventional ) የፖለቲካ እውነታ አይደለም፡፡ የአገር ህልውና በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በአገር ደረጃ የሚጋሩት የጋራ ራዕይ የላቸውም፡፡ አገራዊ ፖለቲካ ማለትም ምንድነው በጋራ የምንጋራው? ምንስ ነው በክልልና በሌሎች ደረጃ ባሉ የመንግስት አካላት የሚሰራው? የሚሉት ጥያቄዎች ግልፅና የማያሻማ መልስ አልተገኘላቸውም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የህግ የበላይነት አይከበርም፡፡ የኃላፊነት እርከኖች ( power centres) የቱጋ እንደሆኑ በግልፅ አይታወቅም፡፡ ተቋማዊ ያልሆኑ የራሳቸው አሰራርና “ህግ” ያላቸው ቡድኖች በእጅጉ ተንሰራፍተዋል፡፡ ይህ ውስብስብ ሁኔታ ባለበት (conventional) መደበኛ የፖለቲካ ሂደትን በመከተል ብቻ መጓዝ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ሰለዚህም ከፖለቲካዊው ራቅ ያለ አገርንና ህዝብን የሚያስቀድም  አልፎም የሚያረጋጋና ማህበረሰቦችን የሚያቀራርብ ( radical  approach shift) ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ይጠበቃል፡፡

በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ ኃይሎችና መሪዎቻቸው ለአገራዊ ሰላም ግንባታ ስራ በግልም ሆነ በድርጀት ደረጃ ፍላጎት ያለማሳየት

የአገራችን የፖለቲካ ባህል በእጅጉ ያልዳበረና የፖለቲካ የድርጅትን ከመፍጠርና ከማፍረስ በዙም ያልዘለለ የመንደር ልጆች ተሰባሰበው ለኳስ ጨዋታ እንደሚፈጥሩት ክለብ አንዴ ብቅ ብሎ ሌላ ጊዜ ደግሞ እርስ በእርስ በመናቆርና በተለያዩ ያልረቡ ምክንያቶች የሚፈርስ ነው፡፡ ሌላው የፖለቲካ ድርጅት ነን የሚሉ ኃይሎች ግልፅ የሆነ አገራዊ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አጀንዳ ሳይቀረፅ የሚመሰረቱ በመሆናቸው ከህዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የማይችሉና ባብዛኛው ከጅምሩ የተሽመደመዱ (dead on arrival) ናቸው፡፡ሌላው ላገራችን ፖለቲካ የማይላቀቅ ፈተና የሆነው በስልሳዎቹ የተጀመረው የአጥፊና ጠፊ የሳበው ጥለፈውና የሴራ ፖለቲካ ባህል ዛሬም በፖለቲከኞቻችን አእምሮ ውስጥ ስር የሰደደና ቅንነትንና ለአገር ቅድሚያ የሰጠ በጎ አሳቢነትን ያዳከመ እኩይ ባህል ነው፡፡ ዛሬ የአገር መሰረታዊ ህልውና እጅግ አሳሳቢና አደገኛ ሁኔታ ላይ ባለበት እንኳን “አለን” ለሚሉት የፖለቲካ አጀንዳ ከማሴርና  ከመሸረብ በስተቀር ዛሬ አገራችን ካለችበት እውነታ ስንነሳ ቅድሚያ ተሰጥቶት መሰራት ያለበት ዋነኛ ጉዳይ ምንድነው? ብለው ማሰብ እንኳን የተሳናቸው መሆናቸውን እንታዘባለን፡፡

ያው እንደ ቀድሞው አሰልቺ የሆነውን “ጭቆና” “ በደል” ወዘተ ተፈፅሟል በሚል ህዝቡ ከእነርሱ በተሻለ መንገድና በህይወት ልምዱ በሚገባ ያለፈበትን የፈተና ታሪክ እየደጋገሙ ከማላዘንና ከማሰልቸት በስተቀር የወደፊት አገራዊ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ  ራዕያቸው ምን እንደሚመስል አያብራሩም፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ እነኚሁ በተቃዋሚ ጉራ ተሰልፈናል የሚሉ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ላገራችን “ሰላም ያስፈልጋታል” ሲሉ ይደመጣሉ። ነገር ግን ከእነርሱ በሃሳብና በአመለካክት ይለያል የሚሉትን ሰው ” እንደምን አደርክ?” ለማለት እንኳን ፍቃደኝነታቸውን አያሳዩም። ታዲያን ተከታዮቻቸውስ የማንን ፈለግ ነው የሚከተሉት? ከፖለቲካና ከርዕዮተ አለም ልዩነት ባሻገር በሰውነት መቀራረብና (civic friendship) መፍጠር ካልተቻለ እንዴት ነው አገራዊ አንድነት መገንባት የሚቻለው፡፡ የሰለጠነ ፖለቲካ የሚኖረው የሰለጠነ ፖለቲከኛ ሲኖር ብቻ ነው፡፡

በሁሉም ጎራ ያሉ አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች በኩርፊያና በጠላትነት ፖለቲካ ጥርሳቸውን የነቀሉ በመሆናቸው ላገራችን ዘላቂ ሰላም ግንባታና አንድነት እንቅፋት ሁነዋል፡፡ ሰላም በቃላት ብቻ የሚደሰኮር በተግባር የማይገለጽ አብስትራክት ሃሳብ አድርጎ ማየትና ከመንፈሳችን አውጥተን በእለት ተዕለት ኑⶂችን ውስጥ ካልተገብርነውና ምሳሌ ሁነን ካላሳየን ስለ ተመኘነው ብቻ ወይንም ስላወደስነው ከሰማይ ዱብ የሚል አይደለም። ሰላም በቤት ከቤተሰብ ጋር በስራ ቦታ ከስራ ባልደረቦች ጋር ከጎረቤት ከማህበረሰብ ከወንዝ ማዶ ከሚኖረው ከሁሉም ጋር በተግባር የምናሳየው እንጂ በዲስኩር ብቻ የምንለፍፈው አይደለም፡፡

ሰላም በተግባር የሚገለፅ በአእምሮአችንና በሰነ ልቦናችን ውስጥ የሚዳበር የኑሮ መርህ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የአገራችን ፖለቲከኞች በጥሎ ማለፍና በሳበው ጥለፈው ተንኮል የተካኑ በመሆናቸው የአገርን ውስብስብና የተቋላለፈ ችግር አጢኖ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ የችግሩ ዋነኛ መንሰኤና አካል ሁነው ይታያሉ፡፡ከእነርሱ በሃሳብ በራእይና በብስለት የተሻለውን ከፍ ከፍ ከማድረና ላገር ልታበረክት ወይንም ሊያበረከት የሚችልበትን መንገድ ከማመቻት ይልቅ ጠልፈው የሚጥሉበትንና የሚያዋርዱበትን መንገድ ሲሸርቡ ያድራሉ፡፡ ለእነርሱ ፖለቲካ ሴራ ሴራ ደግሞ ፖለቲካ ነው፡፡  ይህ የሴራና የመጠላለፍ ፖለቲካ ዛሬ ለደረስንበት ውጥንቅጥ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ሁኖ ሳለ ይህንኑ መንገድ እየተከተሉ ላገር በጎ አሳቢ ነን ወይንም መፍትሄ እናመጣለን ማለት በራሱ የሚቃረን ሃሳብ ነው፡፡ እነኚህ ስለራሳቸው በእጅጉ የተጋነነና ጣሪያ የነካ(over inflated self-worth) ዋጋ የሚሰጡ ከእነርሱ የተለየና የተሻለ ሃሳብ አለው ወይንም አላት የሚሉትን እንደ አደጋ (threat) የሚያዩና የሚያገሉ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ አዳዲስና ገንቢ ሃሳቦች በፖለቲካ ሂደቱ ውስጥ መታየት አልቻለም፡፡ ከዚህ የተነሳም አዳዲስ አመለካከትና ራእይ ያላቸው በሰፊ ድንኳንና በመግባባት ፖለቲካ ላይ ፅኑና ቀና አቋም ያላቸው ወደ አመራር መምጣት አልቻሉም፡፡እንደ አዲስ አበባ ላዳ ታክሲ የፖለቲካ ምህዳሩን ሙጥኝ ብለው በመያዛቸው የፖለቲካ ባህላችን እነርሱ ከጣሉለት የተንጋደደ መሰረት መላቀቅ አልቻለም፡፡ ይህንን ተገንዝበው ለአገርና ለህዝብ ሲሉ  ቆም ብለው ባህርያቸውን አካሄዳቸውንና ስልታቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ችግር ከፖለቲካዊ መፍትሄ የዘለለና የማህበራዊ የሰነልቦናዊ የሞራላዊ የስነ ምግባራዊና የመንፈሳዊ ባህርይ ያለው( spiritual)ችግር ነው፡፡እነኚህን ችግሮች በሚገባ መገንዘብና የሚመጥናቸውን መፍትሄ መሻት በእጅጉ አስፈላጊ የሚሆንበትም ምክንያት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ከግቡ ከማድረስና ከማሳካት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡ለምሳሌ የህግ የበላይነት መከበር የሚረጋገጠው በመንግስት የህግ አስከባሪ ተቋማት ጥንካሬና ብቃት ብቻ አይደለም፡፡ የዜጎች ህግን የማክበር ባህል በህግ የበላይነት መስረፅ ላይ አብይ ድርሻ አለው፡፡ዜጎች በህግ አግባብ መብታቸውን መጠየቅና ማስከበርን ወደ ጎን ትተው በሁከትና በአምባጓሮ ጎዳና መጓዝ ከመረጡ በህግ አስከባሪዎችን ህግን በሚጥሱ መካከል የሚፈጠረው ችግር የራሱ የሆነ ቀውስ ይዞ ብቅ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የሰላምን ምሰሶ ከመሰረቱ ስለ ሚያናጋው ለተጀመረው ለውጥ ትኩረት ሰጥቶ የመስራት አቅምን ያሰናክላል፡፡

“It’s a journalist’s job to be a witness to history. We’re not there to worry about ourselves. We’re there to try and get as near as we can, in an imperfect world, to the truth and get the truth out.”                                                                                 Robert Fisk

“የጋዜጠኛ ኃላፊነት የታሪክ ምስክር መሆን ነው፡፡ ጋዜጠኞች ወደ መስክ ( የጦርነት አውድማን )ጨምሮ ለመዘገብ ስንሄድ ስለ ራሳችን ደህንነት ለመጨነቅ አይደለም፡፡ የምንስማራው በዚህች ምሉእ ባለሆነች አለም በተቻለን መጠን ለእውነቱ ቅርበት ለማግኘትና እወነቱንም ላለም እንዲዳረስ ለማድረግ ነው፡፡”

ሮበርት ፊስክ

ማነው ጋዜጠኛ?

ጋዜጠኝነት አክቲቪስትነትን ይጨምራል ወይ? አክቲቪስቲስ ጋዜጠኛ መሆን ይችላል ወይ? ልዩነትና አንድነትስ ይኖራቸው ይሆን? “ጋዜጠኛ” ነን ባዮችስ ቦታቸው የት ነው? የሚሉት ጥያቄዎች በመላው አለም በእጅጉ እያጠያየቁና የጋለ ክርክርም እያሰነሱ ይገኛል፡፡ይህ ለጉዳዩ መልስ ለማግኘት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የተጧጧፈ ክርክርና ውይይት በኢትዮጵያም ውስጥ እየተካሄደ ነው፡፡ ጉዳዩን በይበልጥ ያወሳሰበው ደግሞ የደረስንበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚዲያ ስራን በየትም ቦታና ጊዜ ማንም ሊከውነው የሚያስችል ዘመን ላይ መሆናችን ነው፡፡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ቢዚህ ጉዳይ ላይ እየተካሄድ ወደ ውይይቱና ክርክሩ ዘልቀን ከመግባታችን በፊት እስቲ የአክቲቪዝምና የጋዜጥኝነት (journalism) ን ትርጉም ለመቃኘት ብንሞክር በጉዳዩ ላይ መሰረታዊ ጭብጥ እንድንይዝ ሊያግዝ ይችላል ፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ የተጀመረው በ1400 ክፍለ ዘመን ቢሆንም ከፍተኛ እመርታ ያሳየው ግን በ1600ኛው ክፍለ ዘመን በጀርመን አገር የህትመት መሳሪያዎች መፈጠርን ተከትሎ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው በዘመናችን ለምናየው በተለያዩ ቲክኖሎጂዎች ተደግፎ የሚቀርበው የጋዜጠኝነት ሙያ መሰረቱ የህትመት ( print journalism) ነው፡፡ከዚያ በመነሳት ነው ዛሬ ካለበት የባለብዙ ዘርፍና ስርጭት አውታር ሊዳብር የቻለው፡፡ ዛሬ ጋዜጠኝነት በህትመት ከሚቀርብ ጋዜጣ አልፎ በቴሌቪዥን በሬድዮ በኢንተርኔት ወዘተ በመሰራጨት ዜናንና መረጃን ከማድረስ ረገድ በፍጥነትም ሆነ በብዛት ከከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‎የአንድ ጎልማሳ ገንዳ ወግ‎

ይህ ወደ ሰባት መቶ አመት የሚጠጋ ታሪክ ያለው ሙያ በረዥም ሂደት ወስጥ ያለፈና ከዘመኑ የሳይንስና ቲክኖሎጂ ለውጥ ጋር ራሱን እያጣጣመ  አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ሙያው የተለያዩ ቅርንጫፎችንም እያበጀ ዛሬ ፖለቲካን ብቻ ሳይሆን  ኢኮኖሚን የአየር ሁኔታን ወታደራዊ ሁኔታዎችንና አሰላለፎችን ሃይማኖትን ወንጀልንና ባህልንና ስነ ጥበብን ወዘተ የሚመልከቱ ዘገባዎችንና ምርምሮችን የሚያጋራ ሁኗል፡፡ለእያንዳንዱም ዘርፍ በሙያው የሰለጠኑ ጋዜጠኞች ተመድበው ሲሰሩ እናያለን፡፡ጋዜጠኝነት የራሱ የሆነ የሙያ ደንብና ስርአት ያለውና አንድ ሰው “ ጋዜጠኛ” ነኝ ሲል ሊከተላቸው የሚገባቸው የተፃፉና እንደ የሃገሩ የተደነገጉ ስነ ምግባርንና ሙያን የሚገዙ ደንቦች አሉ፡፡ ከተፃፈው ህግ ባሻገር ሙያው ራሱ ለራሱ የግድ የሚለው ሙያዊ ፍልስፍናና መርህ አለው፡፡ከእነኚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛው እውነትን መሻትና ያንን በማስረጃ የተደገፈ እውነት ለህዝብ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ የውጊያ አውደ ውሎንም ይሁን የመንደር ወንጀልን ወይንም የፖለቲካ  ዜናን  በተመለከተ የሚቀርቡ ዘገባዎች በእውነት ላይ ካልተመሰረቱና በ”ተባለ”ና በ “በሬ ወለደ” የሚነገሩ ከሆነ ሙያውን ዝቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአገርና በማህበረሰብ ላይ አደጋን ይደቅናሉ፡፡ከዚህ ባሻገር አንድ ብቁ ጋዜጠኛ ተአማኒነትን ፅናትን ጠርጣሪና አጣሪነትን ጥናትና ምርምር የማድረግ ብቃትን ንቁ አእምሮና የተላበሰች በምትሰራበት ቋንቋ የተካነች መሆን ለስራው ጥራትና ጥልቀት ወሳኝ ነው፡፡

ከዚህ ተነስተን  ማን ነው ጋዜጠኛ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንሞክር የሚከተለቱን መልሶች እናገኛለን፡ አንደኛ ለሙያው አክብሮት ያላት፡፡ ሁለተኛ በአሉባልታ በወሬ በተባለና በመረጃ የተደገፈ እውነት መካካለ ያለውን ልዮነት የማበጠር ብቃት ያላትና እነኚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት ከራስዋ ጋር ቃል የገባች ሙያዊና ስነ ምግባራዊ ብቃቷን ሰንቃ ያለመታከት እውነቱን ለማግኘት ያለመታከት የምትሰራ ናት ጋዜጠኛ የሚለውን ኃላፊነት መሸከም የምትችለው ፡፡

የውጊያ አውደ ውሎንም ይሁን የመንደር ወንጀልን ወይንም የፖለቲካ  ዜናን  በተመለከተ የሚቀርቡ ዘገባዎች በእውነት ላይ ካልተመሰረቱና በ”ተባለ”ና በ “በሬ ወለደ” የሚነገሩ ከሆነ ሙያውን ዝቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በአገርና በማህበረሰብ ላይ አደጋን ይደቅናሉ፡፡ ከዚህ ተነስተን  ማን ነው ጋዜጠኛ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንሞክር የሚከተለቱን መልሶች እናገኛለን፡ አንደኛ ለሙያው አክብሮት ያላቸው፡፡ ሁለተኛ በአሉባልታ በወሬ በተባለና በመረጃ የተደገፈ እውነት መካካለ ያለውን ልዮነት መገንዝብ የሚችሉና እነኚህን ኃላፊነቶች ለመወጣት ከራሳቸው ጋር ቃል የገቡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ዛሬ ባገራችን  ውስጥም ሆነ ካገር ውጪ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተሰልፈናል የሚሉ ባብዛኛው እያሳዩ ያሉት ባህርይ  ግን በእውነተኛ የጋዜጠኝነት መርህ ላይ የቆመ ሙያዊ ክህሎት ሳይሆን የወረደና የዘቀጠ የመንደር አሉባልታንና ወሬን “ዜና” “ ሰበር ዜና” “ ጥብቅ መረጃ” በሚል ሽፋን ማህበረሰብን ከማህበረሰብ ጎረቤትን ከጎረቤት የማባላት ስራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጋዜጠኝነት ሳይሆን በማንኛውም አገር በህግ የሚያስጠይቅ የወንጀል ስራ ነው፡፡

በተለያዩ የአለም ክፍሎች ጋዜጠኞች በአንድ የማህበራዊ ጉዳይ ላይ ብቻ እያተኮሩ ስራቸውን ማከናወንም እየዳበረ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ የአየር ሁኔታ ዘጋቢዋ ሰለ ኢኮኖሚ አትተነትንም፡፡የወታደራዊ ዘርፍ ዘጋቢው ጤንነትን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ገብቶ አይፈተፍትም፡፡በተሰለፉበትና በተካኑት የሙያ ቅርንጫፍ እውቀታቸውንና ብቃታቸውን ያዳበራሉ አንጂ ሁሉን እናውቃለን  በሚል ባንዱም በሚገባ ሳይካኑ ግልብና መሰረት የሌለው እውቀት ይዘው አይቀሩም፡፡ይህ የሙያ ብቃትን የማዳበርና በተሰለፉበት ዘርፍ የማያቋርጥ ትምህርት ለመማር መዘጋጀት እወቀትን ከማዳበር ባሻገር የተጣራ መረጃ ለህዝብ ከማቅረብ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ዲግሪና ዲፕሎማ ማግኘት የትምህርት መጀመሪያ እንጂ ፍፃሜ አይደለም፡፡ ሰው መማርን የሚያቆመው በዚህች ምድር ላይ የመኖር ዘመኑ ሲያበቃ ብቻ ነው፡፡ዛሬ በአገራችን  ውስጥም ሆነ ካገር ውጪ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተሰልፈናል የሚሉ ባብዛኛው እያሳዩ ያሉት ባህርይ  ግን በእውነተኛ የጋዜጠኝነት መርህ ላይ የቆመ ሙያዊ ክህሎት ሳይሆን የወረደና የዘቀጠ የመንደር አሉባልታንና ወሬን “ዜና” “ ሰበር ዜና” “ ጥብቅ መረጃ” በሚል ሽፋን ማህበረሰብን ከማህበረሰብ ጎረቤትን ከጎረቤት የማባላት ስራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጋዜጠኝነት ሳይሆን በማንኛውም አገር በህግ የሚያስጠይቅ ነው የወንጀል ስራ ነው፡፡

ከላይ ባጭሩ ለመዘርዘር እንደተሞከረው የአገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያለውና በመሰረታዊ የእውቀት ምሰሶና የአስተሳሰብ ምናብ ላይ የተመሰረተ ጥልቅ ትምህርት ( deep education) መስጠት ባለመቻለቸው ተመራቂዎች ወደ ስራው አለም ሲሰማሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ይቸገራሉ፡፡ይህም በመሆኑ የስራቸው ይዘትና ጥራት ከጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ከሙያ ዝግጅት ማነሰና ጥራት ማሸቆልቆል ጋር የተያያዘ ችግር በተደጋጋሚ በሚሰጥ ስልጠና ሙያተኞቹ ራሳቸው የተሻለ ሁኖ ለመገኘት በሚያደረጉት ጥረት ከሚያዩት ከሚታዘቡትና ከሚያነቡት በሚያገኙት እወቀት ሊሻሻል የሚችል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጋዜጠኝነት መፃፍ ማንበብና መናገር የሚችል ሁሉ ወይንም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመመረቅ ብቻ የሚሸከሙት ኃላፊነት አይደለም፡፡

የምድር ቤት “ጋዜጠኞች”

የዘመናችን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮት በብርቱ ከጠቀማቸውና ካናወጣቸው የሙያ ዘርፎች አንዱ የጋዜጠኝነት ሙያ ነው፡፡ ባንድ ወገን የመረጃና የዜና አቅርብቶን በፍጥነትና በጥራት ለአለም ከማድረስ አኳያ ቴክኖሎጂው ያስገኘው እመርታ በእጅጉ የሚደነቅ ሲሆን የመረጃ ጥራትንና እውነተኛነትን በተመለከተ ደግሞ የራሱን የሆነ ችግር ይዞ መጥቷል፡፡በተለምዶው ጋዜጠኝነት ፈቃድ (licence) የተመዘገበ የስራ ቦታ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የመንግስት አካላት ለሚያወጡት ህግና ደንብ የሚገዛ አልፎም የራሱ የመተዳደሪያ ደንብ ያለው ወዘተ ያለው ተቋም ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ግን ከዚህ በላይ ለተዘረዘሩት ውስጣዊና ውጫዊ ህጎች በፍፁም የማይገዙና ለሚያሰራጩት “ ዜና” “ሰበር ዜና” “ ሰበር መረጃ” ምንጭ የማይጠቅሱና የእነርሱን ያልተረጋገጠ “ ሰበር ዜና” ተከትሎም ለሚደርሰው አደጋ ሃላፊነትን የማይወስዱ የምድር ቤት ጋዜጠኛች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ይህ እውነታ ባገራችን ላይ በእጅጉ ጎልቶ ከመታየት ባሻገር ለፖለቲካ ውጥንቅጡና በየጊዜው እየተካረረ ለመጡት ግጭቶች አስተዋፅኦ አለው፡፡

የእነኚህ በተለይም ካገራችን ጉዳይ ጋር በተያያዘ “ ሰበር ዜና” እያሉ በዩቱብ በፌስ ቡክና በሌሎች የድረ ገፅ አውታሮች የሚሰሩ የምድር ቤት ጋዜጠኖች ዋነኛ መነሻ የተረጋገጠ መረጃ ማቅረብ ወይንም ህዝብን ማገልገልና ማስተማር ሳይሆን በተቻለ መንገድ “ሰበር መረጃ” በሚል ሰውን እያማለሉ ወደ ድረ ገፃቸው ማምጣትና የእነርሱን ገፅ በጎበኘው ሰው ቁጥር የሚያገኙትን ገቢ ለማሳደግ ነው፡፡ ኃላፊነት የጎደለው አንዳንዴም በወገን ለወገን መጨራረስና ደም መፋሰስ የንዋይ ትርፍ ለማግኘት መሞከር ቀደም ባሉት ገፆች ለመግለፅ እንደ ተሞከረው ከሞራላዊና ከስነ ምግባራዊ ዝቅጠት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይህ አየነቱ “ ጋዜጠኝነት” እንደ እትዮጵያ ባሉና ሁሉን ያካተተ የዲሞክራሲ ስርአት ለመገንባት በሚንገታገቱና ወሬ እንደ ሰደድ እሳት የመሰራጨት ልምድ ባለበት አገር ውስጥ የሚያስከተለው መዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ተጠያቂነት የሌለው የምድር ቤት “ጋዜጠኝነት” አገርንና ህዝብን ወደ ከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ መፍትሄውም እንደ ተለምዶው “ መንግስት  አንድ ነገር ማድረግ አለበት”ብለን የምንተወው ሳይሆን ሁላችንም በግላችን እንዴት ይህንን አጥፊ መድረክ መታገል እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ምን ማድረግ እንችላለን? በቅድሚያ የእነኚህን የምድር ቤት “ጋዜጠኞች” ድረ ገፆችን ለይቶ ማወቅና ድረ ገፃቸውን ያለመጎብኘት፡፡መረጃ ለሌሎች ከማስተላለፍ በፊት ምንጩን ማረጋገጥና ያልተረጋጋጠ የአሉባልታና የ” ተባለ” ወሬ ለሌሎች ያለማስተላለፍ፡፡ ከዚህ ባሻገር በዲያስፖራው ውስጥም ሆነ ባገር ውስጥ እንዲህ ያለ ያልተረጋገጠ ዜናና የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ለይቶ ማወቅና መምከር ሲያልፍም ተደማጭነት ማሳጣትና የሚመለከታቸው የህግ አስከባሪ አካላትም እንዲያውቋቸው ማድረግ፡፡

አክቲቪዚም ምንድን ነው?

አክቲቪዝም በአለማችንም ይሁን በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ዘመናዊ (contemporary activism) በተለያዩ አገሮች በተለያየ ቅርፅና መልክ ይታወቃል፡፡ከእነኚህ ውስጥም የ1960 ዎቹ አሜሪካ የሚነገርለት አዲሶቹ ማህበራዊ ንቅናቄዎች (new social movements) ዋነኛው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኢክቲቪዝም ስርወ ታሪክ በጣም ራቅ ያለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፡፡ በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው በአክቲቪዝም የተቀነባበረው አመፅ “የባሮች አመፅ” በመባል የሚታወቀውና 6000 ባሮች የተሳተፉበት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1ኛው ክፍለ ዘመን (1st century BC(E) ) በሮማውያን ዘመን ነው፡፡ በአገራችንም ከ1960 ዎቹ ጀምሮ ፖለቲካ ተኮር የሆነ አክቲቪዚም ሲካሄድ ኖሯል፡፡ይህ ረዥም ታሪክ ያለው ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህን ከመሻት የሚመንጭ የጋራና የግል የትግል ስልት በተለያዩ የአለም ክፍሎች አገራችንንም ጨምሮ ተተግብሯል በመተግበር ላይም ይገኛል፡፡ በየጊዜው ከሚነሱት አዳዲስ ማህበራዊ ትኩረቶች በመነሳትም ዘርፉን እያሰፋ በርካታ ጉዳዮችን እየሸፈንና ተመሳሳይ ችግሮች የሚያሳስባቸውን በማሰባሰብ የታወቀ ድምፅን በግልና በጋራ የማሰማት የትግል ስልት ሁኗል፡፡

በመሆኑም ዛሬ አለማችንን በከፍተኛ ደረጃ እያሰጋ የመጣውን የአየር ሁኔታ ለውጥ በተመለክተ ባለም ዙሪያ የተቀናጀ የአክቲቪዝም ዘመቻ ይከናወናል፡፡ በኢኮኖሚ ፍትህ በሴቶች መብት በሚዲያ ነፃነት በልጆች መብት በአዛውንቶች መብት በእንሰሳት መብት ወዘተ ዙርያ በርካታ የአክቲቪዝም ዘመቻዎች ይካሄዳሉ፡፡ በመሆኑም ማህበራዊ ፍትህና ለውጥ በማምጣት ረገድ አክቲቪዝም ትልቅ ድርሻ ተጫውቷል አሁንም በመጫወት ላይነው፡፡ይሁን እንጂ ሁሉም አክቲቪዝም ለቀናና ለበጎ ነገር ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ አክቲቪዝም ለብዙሃኑ መልካም ውጤት ለማሰገኘት የሚካሄድ የትግል ስልት የመሆኑን ያክል ለጥቂቶች የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነትም ይከናወናል፡፡በአገራችን አብዛኛው የኢክቲቪዝም ትኩረት ፖለቲካዊ እንደ መሆኑ ሌሎች የአክትቪዝም ዘርፎች ጎልተው አይታዩም፡፡ ለምሳሌ አሁን አለማችንን በእጅጉ እያሳሳበ ያለውና ለኢትዮጵያም ታላቅ ፈተና የደቀነው የአየር ሁኔታ ለውጥ በአገራችን በተጠናከረና ሰፋ ባለ መልኩ የአክቲቪዝም ስራ አይሰራበትም፡፡

 

አክቲቪዝምና የጋዜጠኝነት ሙያ

አንዳንዶች ጋዜጠኝነት በተፈጥሮው የአክቲቪዝም ባህርይ አለው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የለም ጋዜጠኝነት ከአክትቪዝም ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ነገር የለም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ጋዜጠኞች በማንኛውም ጉዳይ ላይ ከአክቲቪዝም በእጅጉ ርቀው ነው ሙያቸውን መወጣት ያለባቸው እንጂ ሁለቱን መቀላልቀል ሙያውን ተአማኒነት ያሳጣዋል የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡ መልሱ ቀላልና በጥቁርና ነጭ በማየት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ መልሱ ህግን የሙያ ብቃትን የሙያው የስነ ምግባርና የመተዳደሪያ ደንብን ማህበራዊ ኃላፊነትን ማካተት ይኖርበታል፡፡በጋዜጠኝነት ሙያ የሰለጠኑና የተካኑ አክቲቪስቶች ይኖራሉ፡፡ለጋዜጠኝነት የሙያ የህግና የስነ ምግባር ደንብ የማይገዙና  በዚህም የማይጠየቁ አክቲቪስቶች ግን ጋዜጠኛ ነን ቢሉ አግባብ ያለው አይሆንም፡፡ጉዳዩ የብቃት ብቻ ሳይሆን የህግና የስርአት ነው፡፡አክቲቪስቷ ከሌሎች ጋዜጠኞች የተሻለ የሙያ ብቃት ሊኖራት ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን አክቲቪስቶች ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር የሚቀራረብ ስራ መስራት የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለቆሙለት አላማ መፃፍ ዘገባ ማቅረብ በፎቶና በቪድዮ የተደገፉ መረጃዎችን ማሰራጨት ወዘተ የሚንቀሳቀሱበትን አገር ህግና ስርአት ባልጣሰ መልኩ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ጉዳዩ ችግር ሊፈጥር የሚችለው አክቲቪስቱ ጋዜጠኛ ነኝ ወይንም በጋዜጠኝነት ጥላ ስር ዘገባውን ካቀረበ ነው፡፡ ሌላው የመልእክቱ ይዘት ነው፡፡መልእክቱ ህግን የሚጥስ በቀጥታ የማህበረሰብን ሰላም የሚያናጋ ከሆነ ግን ከህግ ጋር የተያያዘ ነውና መልሱን የሚሰጠው በህግ አግባብ ይሆናል፡፡

ዜጋ ጋዜጠኛ ( citizen journalist)

ዜጋ ጋዜጠኛ በመባል የሚታወቀው ከዘመኑ የኢንፎርማሽን ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ብቅ ያለ አዲስ የጋዜጠኝነት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ባብዛኛው የሚያተኩረው ዜጎች ስለ በአካባቢያቸው ማለትም በሚኖሩበት ከተማ ሰፈር ወይንም የገጠር መንደር ውስጥ ስለሚያሳስቡቸውና ኑሮአቸውን በቀጥታ በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ሪፖርትና ዘገባ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡በዘርፉ የተሰለፉ ዜጋ ጋዜጠኞች ባብዛኛው localized በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ቢሆንም አንዳንዴ ከመንደር ጉዳይ አልፎ ሰፋ ያሉና ከአገራዊ ጉዳዮችን የተያያዙ ጉዳዮችን ያነሳሉ፡፡ ከዚህ ዘርፍ ጋር በተያያዘ የሚነሱት ጥያቄዎች የተአማኒነትና ዜናንና መረጃን አብጠለጥሎ የማጣራት ብቃትና አቅም ማጣት ናቸው፡፡ የዜጋ ጋዘጠኞች አብይ የሚባሉ የዜና አውታሮች ትኩረት የማይሰጡዋቸውን ጉዳዮች በማንሳት እንዲደመጡና መልስ እንዲያገኙ ያግዛሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን አብዛኛው ትኩረታቸው በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ ሁኔታዎችን ሰፋ አድርጎ የማየት ፍላጎት አያሳዩም፡፡መፍትሄውም ከዚህ ሰፋ አድርጎ ከማየት ሊመንጭ እንደሚችል ማየት ይቸገራሉ፡፡

በታሪክ ውስጥ እናዳየነው በየዘመኑ የሚፈጠሩ አዲስ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶች በጎና የሰው ልጅ ኑሮን ከማሻሻል ረገድ የሚወደሱ ናቸው፡፡ ባንፃሩ ደግሞ ይዘው የሚመጡት መዘዝና ጣጣ ይኖራል፡፡ ባለንበት ክፍለ ዘመን በመካሄድ ላይ ያለው  የኢንፎሜሽን ቴክኖሎጂ አብዮት በመላው አለም መረጃን ከመለዋወጥና እውቀትን ከማንሸራሸር አኳያ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ውጤት አስገኝቷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የጥፋት የጥላቻና የወንጀል ድርጊቶች በዚሁ መጠን በእኩልና በፍጥነት ማሰራጨትን አስችሏል፡፡ የቴሌቪዚን ጣቢያ ለመክፈት የሚያስፍለጉት የቢሮ የቁሳቁስና የገንዘብ አቅም በዛሬው የቴክኖሎጂ እውነታ እምብዛም አያስፈልጉም፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ከመኖሪያ ቤቱ ሁኖ የጋዜጠኝነት እውቀትና ብቃት ሳይኖረውና ሙያው የሚጠይቀውን ደንብና ስርአት ሳይከተል “ ዜና” “ መረጃ” ማሰራጨት ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በመላው አለም አጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ይህ የሃሰት ጋዜጠኝነት ባገራችንም ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ሲሆን ለሰላምና መረጋጋትም እንቅፋት እየሆነ መጥቷል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ አጀንዳ አክቲቪስቶች ራሳቸውን “ጋዜጠኛ” ብለው ከመሾም ባሻገር ይህንን መድረካቸውን በመጠቀም አገርን ህዝብን ያምሳሉ፡፡ ይህ ሁለቱንም የመሆን አባዜ ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ የመናገር የመፃፍ መብቶችን በማይተላለፍ መንገድ በቶሎ ፈር ሊበጅለት ይገባል፡፡

ምን እናድርግ? መፍትሄው ምንድን ነው?

ሰላም ስለተመኘነው ወይንም በመዝሙር በግጥምና በድራማ ስላወደስነው ብቻ አይገኘም፡፡ ሰላም ሚስጥራዊ (abstract) ሳይሆን በእለት ተእለት ውሎአችን የምንኖረውና በተግባር የምናሳየው የህይወትና የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡

ሰላም ብቸኛው መንገድ ነው

‘ማፍረስ ቀላል ነው መገንባት እንጂ’ እንዲሉ ሰላም ከጦርነት በላይ ከፍ ያለ ስራንና የሞራል የመንፈስ የስነ ልቦናን የፈጠራንና የቀናነትን ጉልበት በጥምረት አዋህዶ መስራትን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ሰላምን መገንባት ጦር ከመስበቅና ሰራዊት ከማሰማራት ያለፈ የረዥም ጊዜ ስራ ነው፡፡ ሰላም ልበ ቀናነትን አስተዋይነትን ሆደ ሰፊነትንና ይቅር ባይነትንም ይጠይቃል፡፡ይህም በመሆኑ የመሪዎች ብቃትና አስተዋይነት ባብዛኛው የሚለካውና የሚወደሰው ጦርነት በማወጅና ውጊያ በመምራት ብቃታቸው ሳይሆን ሰላምን እርቅን መቀራረብንና መቻቻልን ለማስፈን ያለመታከት በመስራታቸው ነው፡፡ ለዚህም የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕርዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ማህተማ ጋንዲ የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ይስሃቅ ራቢን ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ ምንም እንኳን ጦርነት በተለምዶ ጀግንነትን የሚያጎናፅፍ ቢሆንም ትልቁና ይበልጡንም ዋጋ ያለው ሰላምን ለማስፈንና ከሰላም የሚገኙ በረከቶችን ህዝብ እንዲቋደስ ከማድረግ ነው የሚገኘው፡፡ በመሆኑም መሪዎች ከጦርነት ከማወጅ  ይልቅ ሰላም ከማስገኘት አኳያ በተጫወቱት ሚና ትልቅ ክብርና እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኦሮሙማው የፋሽስት መንግሥት ጋር ድርድር አይሞከር፤ ለፋሽስቶች ድርድር ጠላቶቻቸውን አዘናግቶ ማጥፊያ መሳሪያ ነውና!!

ሰላም ‘ወልዶ ለመሳም ዘርቶ ለመቃም’ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የሰው ልጆች ፍላጎት መሳካት ቁልፉና ዋነኛው ነው፡፡

በመሆኑም ጠቀሜታው እጅግ የላቀና አገርንና ህዝብን ከመሰረቱ የሚለውጥ ነው፡፡ ይህም በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎችና ጊዜያት አለማችን በሰላምና በጦርነት በግጭትና በመቀራረብ መሃል ያሉ ጉልህ ልዩነቶችን አሳይታለች፡፡ ይህንን በተመለከተ አንድ ምሳሌ እንመልከት፡፡ የሁለተኛው የአለም ጦርነት በጥምረቱ ኃይልና ( ሶቭየት ህብረትን ጨምሮ) በስሩ በተሰለፉ ከመላው የሰው ልጅ ዘር ተውጣጥቶ በተመሰረተው ሰራዊት በናዚዎች በፋሽስቶችና በተስፋፊዋ ጃፖን ተሸናፊነት ሲደመደም  ለድህረ ጦርነቱ የአለም ወታደራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ አሰላለፍ/ ስርአት ይበጃሉ ያሉዋቸውና ውሳኔዎችን አስተላለፉ።

ከእነኚህ ውሳኔዎች አንዱ በጀርመንና በጃፖን ላይ የተጣለው የወታደራዊ የሰው ኃይልና መሳሪያ ግንባታ ማዕቀብ ነው። ይህ ማዕቀብ መንፈሱ ” የአለም ሰላምን ለማረጋጥ”  የሚል መሪ ሃሳብ ነዉ። አልፎም እነኝህ ሁለት አገሮች ዳግም አንሰራርተውና ተጠናክረው በአለማችን ላይ ተፅዕኖ የማደረግ አቅማቸውን ቢቻል ለመወሰን ካልሆነም ደግሞ ለመግታት ነበር። ይሁን እንጅ ሁለቱ አገሮች ይህንን ማዕቀብ እንደ ዕድል በመጠቀም ትኩረታቸውን ወታደራዊ ባልሆኑ ጥናትና ምርምሮች በማተኮር ባጭር ጊዜ ውስጥ በጦርነት የፈረሱት አገሮቻቸውን ገንብተው ዛሬ በአለማችን በኢኮኖሚ በማህበራዊውና በአጠቃላይ በኑሮ እርከን አንቱ ከሚባሉት አገሮች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈው እናገኛቸዋለን።ይህንን እንደ ምሳሌ ወስደን ባገራችን የሰላም ሸማ በመሸመን ሰላምን በመዝሙር በድራማ በስነ ግጥም ብቻ የምናወድሰው ሰይሆን ከዕለት ተዕለት ውሎና አዳራችን ጋራ ተሰናስሎ ሰላም በተግባር ባህላችን ይሆን ዘንድ የአስተሳሰብ የባህልና የሥነ ትምህርት ለውጥ ማድረግ የግድ ይሏል።

አገራችን የጀመረችው ዘርፈ ብዙ የለውጥ ጉዞ ዜጎችን በሰፊው ያስደመመ ከመሆን ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሰላም ተስፋን ያሰረጸ ነው። ይህ በአገራችን ውስጥ የፖለቲካ ነጻነትን የኢኮኖሚ ፍትህንና ማህበራዊና አገራዊ አንድነትን ለማስፈን የተጀመረው ጉዞ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ማህደር ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚገባው ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያገባናል የምንል ባገርም ሆነ ካገር ውጪ ያለን ዜጎች በቀና መንፈስና በጽናት የጉልበት የእውቀትና የገንዘብ አስተዋጽ ማበርከት ወቅቱ ከሚጠይቃቸው ኃላፊነቶች አብዩ ነው። ለረዥም ዘመናት አገራችን ኢትዮጵያ ከተጓዘችበት ማህበራዊ ውጥንቅጥና ስር የሰደደ የፖለቲካ ነጻነት መታጣትና የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነት የተነሳ ይህ ባገር ውስጥና በውጭ ከፍተኛ ተሰፋ የተጣለበት የለውጥ ጉዞ እነኚህን ስር የሰደዱ ችግሮች ለመፍታት ያጫረው ተሰፋ ግዙፍ ሲሆን ይህንንም የማሳካት ኃላፊነቱ የመንግስት ወይም የተቋማት ብቻ ሳይሆን የሁለም ዜጎች ሊሆን ይገባል።

በተጨማሪም የሰላምን ባህል ከመገንባትና ከማጠናከር አኩያ ባህላዊ የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት እሴቶቻችንን ወደ ፊት በማምጣት በተግባር እንዱተርጎሙና አንድ ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ያለውን የባህሌ እስቶችና ልምዶች በማጋራት ሂደቱን ራሱን መቀራረብንና አብሮ መኖር እንዲያገለግሉ ማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። የዚህ የሰላም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መቋቋም በመጀመሪያነቱ ታሪካዊ ሲያደርገው በመርህና ከሚያከናውናቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች አኩያ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራስዋ አልፋ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት የሚያሳይ ነው። ዘላቂ ሰላምን በአገራችንና በአፍሪካ ቀንድ ለማስፈን ባለ ብዙ ዘርፍ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ብዙም አከራካሪ አይደለም። ይህም የሚመነጨው ኢትዮጵያ ከራስዋ ጥቅም ባሻገር በቀጣናው ካለባት ታሪካዊ ስትራጄያዊና ጂዎ ፖለቲካዊ ኃላፊነት የሚመንጭ ነው። ይህ ስራ በትምህርት በባህል በኪነጥበብና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና በሌሎች አግባብ ባላቸው ዘርፎች በሰፊው መከናወን ይኖርበታል። ለዚህም ስኬት አገራችንን ያላትን የሰው ኃይል በአግባቡና በትክክለኛው ቦታ በማሰማራት መጠቀም አስፈሊጊ ብቻ ሳይሆን የግድም ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያም በረዥም ዘመን ታሪኳ ውስጥ የጦርነት ውድመትና ጥፋት ካደቀቋት አገሮች አንድዋ ሁና ቆይታለች። ከዚህ የጦርነትና የጥፋት አባዜ በመውጣትም ዘላቂና ተቋማዊ  የሰላም ግንባታ ስራዎች መልክ በያዘና በተቀናጀ ሁኔታ መከናወን ይኖርባቸዋል። ሰላም መተኪያ የሌለው የሁሉም የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ስኬት መሰረትና ቁልፍ መሆኑንም ዋቢ ያደረገ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ያስፈልጋል። በመሆኑም በግለ ሰብ በቤተሰብ በማህበረሰብና ከፍ ሲልም በአገር ደረጃ ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራ በተቀናጀና በታቀደ መልኩ መተግበር ይኖርበታል። አገራችን በረዥም ዘመን ታሪኳ ውስጥ የጦርነት ውድመትና ጥፋት ካደቀቋት አገሮች አንዷ ሁና ቆይታለች። ከዚህ የጦርነትና የጥፋት አባዜ ለመውጣትም ዘላቂና ተቋማዊ  የሰላም ግንባታ ስራዎች መልክ በያዘና በተቀናጀ ሁኔታ መከናወን ይኖርባቸዋል። ሰላም መተኪያ የሌለው የሁሉም የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ስኬት መሰረት ቁልፍ መሆኑንም መሰረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ጠቃሚ ነው።

የመፍትሄ ሃሳብ  # 1

በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈናል የሚሉ ፖለቲከኞች በግላቸው ( individual/leaders symbolic act)ና በድርጅቶቻቸው ውስጥ የሰላምና የእርቅ ቡድን በማቋቋም ላገሪቱ ያላቸውን የሰላምና የአብሮ መኖር ራዕይና ንድፍ በግልፅ ማስቀመጥና በተግባርም ማሳየት፡፡ የዚህን እቅድ አፈፃፀምም በማያሻማ ሁኔታ ከፖለቲካ ስሌት በራቀ መንፈስ ማስቀመጥ፡፡ይህንን ሃሳባቸውንም በመንግስት ደረጃ ላሉ የሰላም ተቋማት ማጋራት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰላም አሁን ባገራችን ካለው ሁኔታ አንፃር በትርፍ ጊዜ ስራነት የሚታይ ሳይሆን ቅድሚያ ተሰጥቶት መሰራት የሚገባው በመሆኑ ትኩረታቸውን ወደዚያ ቢያደረጉ መልካም ነው፡፡ በመጨረሻም ስራቸውን ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ የሰላም ተቋማት ጋር ማቀናጀትና አብሮ መስራት፡፡

የመፍትሄ ሃሳብ # 2

ባገራችን ያሉ የሬድዮ የቴሌቪዥንና የህትመት የዜናና የመረጃ አውታሮች በአገራዊ ሰላም ጉዳይ ላይ ቋሚ ፕሮግራሞች ነድፈው የአገር ሽማግሌዎችን የሰላም ግንባታ ባለሙያዎችንና የሃይማኖት አባቶችን በጋራ በማቅረብ በሚገባ የታቀደና የተዘጋጀ ውይይት ሳይሆን ዳይሎግ እንዲያደረጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡ ይህንንም በማድረግ ሰላምን በሃሳብ ደረጃ የምናወራው ብቻ ሳይሆን በተግባር ምን መደረገ እናዳለበት በግልፅ ማስቀመጥ፡፡

የመፍትሄ ሃሳብ # 3

ዲያስፖራው አሁን ባገራችን ለተፈጠረው ለውጥ ያበረከተው አስተዋፆ ቀላል እንዳለመሆኑ ይህ የተጀመረው መልካም ጉዞ ከግብ እንዲደርስ ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት አለበት፡፡ ይህም እገዛ በሙያ በገንዘብና በሌሎች በተለያዩ መልኩ ነው፡፡ ከእነኚህ ውስጥ አሁን አገራችን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር ግን የተወሰኑ የዲያስፖራ አባላት የሚረጩትን የሃሰትና ማህበረሰብን ከማህበረሰብ የማባላት እኩይ ድርጊት ከመግራት ረገድ በየሃገሩ የሚገኘው ዲያስፖራ ምን ማድረግ እንዳለበት መወያየትና የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ አገራዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የመፍትሄ ሃሳብ# 4

ባገር ውስጥ የተፈጠረውን የለውጥ አጋጣሚ በመጠቅም በተቃዋሚነት በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ወደ አገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ ጀመረዋል፡፡ ይህ በጥቅሉ መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወደ አገር ቤት ለመግባት ባደረጉት እሽቅድምድም በውጪ ያሉ ደጋፊዎቻቸውንና አባላቶቻችውን የሚቀጥለው የዲያስፖራ ተሳትፎ  ምን መሆን እንዳለበትና ዲያስፖራው በምን መልኩ ተደራጅቶ ትግሉ ከግብ እንዲደርስ እቀድ ሳያዘጋጁና ሳያሳውቁ ሄደዋል፡፡ ይህንን አባላትንና ደጋፊዎችንን በትኖ የመሄድን ሁኔታ ተከትሎ ዲያስፖራው ግራ ከመጋባቱ የተነሳ ቀድሞ ሰለ አገራዊ አንድነት ያቀንቅንና አስተዋፅኦ ያበረከት የነበረው ወደ ጎሳ ፖለቲካ በማዘንበል የብሄር ድርጅቶችን ከመቀላቀል ባሻገር በየማህበራዊ ሚዲያው የአሉባልታና የክፍፍል መልእክቶችን በሰፊው ያሰራጫል፡፡ ይህ በእጅጉ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን አደገኛም በመሆኑ ዲያስፖራውን አግባብ ባለው መልኩ ማደራጀትና ከጥላቻና ከከፋፋይ ሴራዎች እንዲርቅ ማድረግ ለነገ መባል የለበትም፡፡

ማጠቃለያ

አሁን ያለንበት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በአስተሳሰብ በሳይንስ በቴክኖሎጂና በሌሎችም የተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ፈጣን ለውጦች የሚካሄዱበት ነው። ይህ ዘመን የሰው ልጆች አእምሮአቸውን የፈጠራ ችሎታቸውን ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ደዌን ለመፈወስ  በሰው ልጆች መካከል ያለውን የጊዜና የቦታ ልዩነትና ርቀት ለማጥበብ የሰው ልጅ ኑሮ ካለፈው የተሻለና ምቹ እንዲሆን በጋራና በተባበረ መንፈስ የሚሰሩበት ዘመን ነው። ከዚህ ሁኔታ በተጓዳኝ ደግሞ የብሄረኝነት መንፈስ በእጅጉ ጉልቶ የሚታይበትና ባንዳንድ አካባቢዎች መሰረቱን ከ1930ዎቹና 40ዎቹ ጋር ያያያዘ የፋሽስታዊነት መንፈስና ባህርይም የሚታይበት ዘመን ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኃላ የተፈጠረው አለማቀፋዊ የፖለቲካ ወታደራዊና ስትራቴጅያዊ አሰላለፍ በመዋዥቅ ላይ ብቻ ሳይሆን አዲስ የፖለቲካ የኢኮኖሚና ወታደራዊ አስላለፍ ማቆጥቆጥ ጀምሯል፡፡ ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ አገራዊ የስትራቴጂ ቦታ ምንድንነው የሚለውን በሚገባ መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከዘመኑ የእውቀትና የስልጣኔ ማእድ ተቋዳሽ ትሆን ዘንድ መሰረታዊ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ማድረግ የግድ ነው፡፡ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ እንደ መሰረት አድርጎ መያዝ ያለበትም ለሰላምና ለአብሮ መኖር ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ላይ ነው፡፡ የኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክሉ ከኔ ባላይ አዋቂ የለም እኔ ከሌለሁበት ያገር ጉዳይ አያገባኝም ከሚለው ተራና ደካማ አስተሳሰብ ወጥተን አዲስና ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ለውጥ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የታገልንለትና የምንታገልለት የዲሞክራሲ ስርአት ላገራችን የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ኑሮ ፍቱን መድኃኒትና ችግሮችዋም በነው እንዲጠፉ የሚያስችል የፖለቲካ ስርአት ነው ብለን በእርገጠኝነት መናገር አንችልም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ባለ ስርአት ውስጥ አገራችን ኑራ አታውቅምና፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ግን ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ እናዳየነውና ያገራችንን የታሪክ የባህል የኢኮኖሚና ሌሎች መመዘኛዎች ላይ ሁነን ስናሰላ የዲሞክራሲ ስርአት ብዙዎቹን ጥያቄዎቻችንን መመለስ የሚያስችል ስርአት ነው፡፡

ባገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ በእጅጉ ተስፋን ያጫረና የአገራችንን እውነተኛ ትንሳኤ ሊያመጣ የሚችል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከተፈጠረውና እየተፈጠረ ካለው የለውጥ መሰናክል አኳያ ነገሮችን ቅደም ተከተል የማስያዝ (prioritizing) ችግር እንዳለበት ይታያል፡፡ ይህንን ችግር ለመፈታት መንግስትም ሁኔ በተፎካካሪነት ተሰልፈናል የሚሉ ኃይሎች አካሄዳቸውን እንደገና መፈትሽና የትኞቹን ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ መገምገም ይኖርባቸዋል፡፡ ብሄራዊ ምርጫ አስፈላጊነቱ ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ ምርጫውን ለማካሄድ የሰላምና የፀጥታ ዋስትና ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ተቋማዊ ብቃት ወዘተ መመቻቸታቸውንና ለዚያም መኖር የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቻውን ከወዲሁ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምርጫ የሚያስፈለገው የምርጫ ኮሮጆና የምርጫ ታዛቢዎች መኖር ብቻ አየደለም፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ሚፈለገው የዲሞክራሲ ጎዳና ታመራ ዘንድ የፖለቲካ መሪዎች በአስተሳሰብም ሆነ በአካሄዳቸው መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በስልሳዎቹና በሰባዎቹ አመለካከት የዛሬይቱን ኢትዮጵያ መረዳትና መምራት አይቻልም፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች በአደረጃጀታቸው በሚመሩበት መርህን ካገርና ከህዝብ ጋር ስለ ሚኖራቸው ግንኙነት ስር ነቀል የአስተሳሰብ እመርታን(radical shift in thinking )ማድረግ ካልቻሉ ከመንደር ስብስብነት አልፈው ባገር ጉዳይ ላይ ገንቢሚና መጫወት አይችሉም፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰልፈናል የሚሉ ደግሞ በቅድሚያ የሙያውን ትርጉም ኃላፊነትና የሰነ ምግባር መርህ በሚገባ ማጥናትና መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሙያው እጅግ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በየመንደሩና በየሻይቤቱ ከጓደኞቻችን ጋር የምናወራውን ወሬ ማይክሮፎን ስንይዝ መድገም ጋዜጠኝነት አይደለም፡፡ ለሙያው ክብር መስጠትና ያለመታከት እውነቱን ቆፍሮ ማወጣትና ለህዝብ እንዲደረስ ማድረግ የእውነተኛ ጋዜጠኛ ዋና መመዘኛ ነው፡፡

ሁላችንም መገንዘብ ያለብን አንድ እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ዲሞክራሲ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም:: ዲሞክራሲን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለመገንባት የሚያስችሉ ተሰፋ ሰጪ ሁኔታዎች ግን አሉ፡፡በመሆኑም ለውጡን ተከትሎ የዲሞክራሲ ስርአትን በተቋማዊ መልክ ለመገንባት የሚያስችሉ መሰረቶች እየተጣሉ ነው፡፡ ሌላው በአንድ አገር የዲሞክራሲ ምህዳር አለ ብሎ ለማለት ቢያንስ ሁለት መመዘኛዎች መሟላት አለባቸው፡፡ አንደኛው ዲሞክራሲን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚተገብሩ የሚጠብቁና የሚከላከሉ ተቋማት መኖር፡፡ ሁለተኛው በማህበረሰቡ ውስጥ የዲሞክራሲን መሰረታዊ ባህርዮች የሚያንፀባርቅ ባህል (ዲሞክራሲያዊ ባህል) መታየትና ማቆጥቆጥ ሲጀምር ወይንም ሲኖር ነው፡፡

ለኢትዮጵያ አንድነት ቆሜአለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ አኳያ ፍልስፍናውንም ሆነ መርሁን መቅረፅ ያለበት ይህንን እውነታ መሰረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡ለኢትዮጵያዊነት ለቆመ ሁሉ ከዚህ ሌላ መሪ አጀንዳ ሊኖር አይገባም፡፡ኢትዮጵያዊነት አንዱ የሚሰጠው ሌላው ደግሞ እንደ ድርጎ የሚቀበለው አይደለም፡፡ለኢትዮጵያዊነት መፅናትና ለኢትዮጵያ መከበር ዘመናትን ያስቆጠሩ በአለም ፊት የተመሰከረላቸው መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ይህንን መስዋእትነት ደግሞ የከፈሉት ያንድ መንደር ያንድ ሰፈር ወይንም ብሄር አባላት ሳይሆኑ በአራቱም ማእዘናት የሚኖሩ የተለያየ ኃይማኖት የሚከተሉ የተለያየ የዘር ግንድ ያላቸው አባቶቻችንና አያቶቻችን ናቸው፡፡የእነርሱ ደም ዘርና ሃይማኖት መንደርና ሰፈር ከተማና ገጠር ሳይለይበት ከዚህች አገር አፈር ተቀላቅሏል፡፡

ሁላችንም ኢትዮጵያዊነትን የተረከብነው ከዚህ መስዋእትነት እንጂ ከዘመኑ ፖለቲከኞች ወይንም በየማህበራዊ ሚዲያው አካኪ ዘራፍ ከሚሉና ራሳቸውን የኢትዮጵያዊነት ባለአደራ ሰጪና ከልካይ አድርገው ከሚያስቡት አይደለም፡፡ስለሆነም ኢትዮጵያዊነታችንና ኢትዮጵያን የማስከበርና የመጠበቅ ኃላፊነታችን የአያቶቻችን አደራ እንጂ ከማንም የሚሰጠን ትእዛዝ ወይንም በጥቂቶች ቸር አሳቢነት የሚለገሰን ስጦታ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቅርቡን ዘመን ሰቆቃ ስናስብ ዘር ኃይማኖት ቋንቋ ሳንለይ አብረን ታግለናል፡፡ አንድ ላይ በጠባብ ክፍል ውስጥ ታጉረናል፡፡አብረን ተጠምተናል፡፡ አብረን ተርበናል፡፡አንድ ላይ ተገርፈናል የተገርፍንበት ፌሮ በሁላችንም ደም ቀልሟል፡፡ ሁሉንም ማህበረሰብ የሚወክሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሰንሰለት ተቆራኝተው አንድ ላይ በጥይት ተደብደበዋል፡፡ በአንድ ጉድጓድም ተወርውረዋል፡፡ እነርሱም እንደ አያቶቻቸው አንድ ላይ ወድቀዋል፡፡ ይህንን እውነት ላንዲት ሰከንድ እንኳን ቢሆን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡

ከፍ ባሉት ጥቂት ገፆች በርካታ ጉዳዮችን ለማንሳት ሞክሬአለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በቂና ዝርዝር መልስ ቀርቧል የሚል እምነት የለኝም፡፡ነገር ግን በእነኚህ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት ውይይትና ክርክር እንዲሚያስፈልግ ምንም ጥያቄ የለውምና ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው አካላትና ግለሰቦች መድረክ በማዘጋጀት በሰፊው ይመክሩበታል የሚል ተሰፋ አለኝ፡፡

በመጨረሻም አገራችን ለፈተና አዲስ አይደለችም።አብዛኛው የታሪኳ ምዕራፎች በፈተና ቀለም የተጻፉ መሆናቸው መሰረታዊ የታሪክ ዕውቀት ላለው ሁሉ ግልጽ ነው። በእምባ በደም በስጋና በአጥንት የተከተቡ በርካታ የታሪክ ገጾች ያላት ከወደቀችበት ጠንክራ የምትነሳ  ከታመመችበት የምታገግም ጭለማን ገፍፋ ብርሃን የምትፈነጥቅ አገር ናት። ይህ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ግን አንዱ ላገር አሳቢና ሰራተኛ ሌላው ደግሞ ተቺና አብጠልጣይ ሲሆን ሳይሆን ሁላችንም ያገባናል ብለን በቀና መንፈስና ለዚህ የአገርና የአዲስ ስርአት ግንባታ የድርሻችንን ስናበረክት ብቻ ነው፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ደም መፋሳስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ወይንም በማስከተል ላይ ያሉ ግጭቶች መከላከልና አፈታትና ባለ ሙያ ነው፡፡

ገንቢ ሃሳብ አስተያየት ወይንም ጥያቄ ካልዎት በሚቀጥለው የኢሜይል አድራሻ ይላኩ፡፡

Digafie.debalke@gmail.com

Share