ወንጀል እና ህግ ፣ እውነት እና ውሸት በብሄረሰቦች ነፃነት ዘመን (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ
ሰኔ 2011

በብሔረሰብ ተቆርቋሪ ስም የሰው ህይወት በግልፅ እና ስውር ማጥፋት ፣ ባንክ በጠራራ ፀሐይ መዝረፍ ፣ የህዝብ እና አገር ጥሪት ያለ ሰነድ ማራቆት ፣ ህዝብን ከአፅመ ርስቱ ማፈናቀል ፣ መዋሸት ፣ ስም ማጉደፍ ፣ በፈጠራ እና ግምት ላይ የተመረኮዘ ማነሳሳት ብሎም የሲቪሉን ህብረተሰብ ዕለታዊ ህይወት በመንጋ ጥቃት ማተራመስ… እነኝህ ሁሉ እንበለ ህግ ድርጊቶች ወንጀል መሆናቸው እንደቀረ ያህል ስር እየሰደዱ እየተንሰራፉ መምጣታቸው ግልፅ ይመስላል። የህዝብ ዕለታዊ ህይወት ይፋ ባልተደነገገ የብሔረሰብ ነፃ አውጪዎች የፖለቲካ ፕሮግራም እየተመራ ባለበት ሁኔታ በፓርላማ ፀድቋል የተባለውን የተፃፈውን ህግ ሥራ ላይ ማዋል እንዳልተቻለ እኛም እነሱም (ወያኔ/ኢህአዴግ) አምነው የተቀበሉት ጉዳይ ነው።

በብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት ስም ፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ነን ያሉ ወገኖች ያፀደቁትን የራሳቸውን ህገ መንግስት ማክበር ማስከበር ያልቻሉበት እንቆቅልሽስ ምን ይሆን… ዛሬ ኢትዮጵያን ከመሀል እስከ ሁሉም ማዕዘናት ወጥሮ የያዛት ችግር እንደ አገር በህግ የመተዳደር ወይንም በብሔር ብሔረሰብ ነፃ አውጪ ፕሮግራም ጥላ ሥር በህልውና ለመቀጠል የመቻል ጥያቄ ሆኗል። “… መሆን አለመሆን” ነው ጥያቄው…

የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች ፕሮግራማቸውን ለመተግበር ዘር እየቆጠሩ በሚያካሄዱት አንተ ትብስ የጥድፊያ እንቅስቃሴ ተፅፎ ህግ የተባለውን ሰነድ ሲጨፈልቁ እንደማይጠየቁ ዋስትና የተሰጣቸውም ያህል ይሰማኛል። ከዚህ መሳ ለመሳ ፖለቲካዊ የድርጅት ስም የሌላቸው ግን የብሄረሰብ ‘ተቆርቋሪ’ ስብስቦችም ግዛታችን ነው በሚሉት አጥቢያ ያሻቸውን ጥቃት ሲፈፅሙ ማየት የተለመደ ነገር ሆኗል… ኤጀቶ ፣ ፋኖ ፣ ቄሮ ፣ ባልደራስ… ሁሉም ወያኔን ለመጣል ባንድ ወይንም በሌላ ሂደት በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ተሰልፈው የነበሩ ግን በወያኔ ውድቀት ማግስት ራሳቸውን በየአጥቢያቸው አድራጊ ፈጣሪ አድርገው ባልተፃፈ ህግ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወትን እንምራ የሚሉ ናቸው። ህገወጥ ትርምስ በመፍጠር ረገድ የቅርፅ እንጂ የይዘት ልዩነት የላቸውም። ወያኔን ለማንበርከክ ሲባል የታለመ አደራጃጀት እና ስልት እንደ ዘላቂ የማህበረሰብ መተዳደሪያ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ግቡን አሳክቶ ወደሚቀጥለው የተረጋጋ እና የተሻለ ዘመን ሊያደርሰን ይገባል —

ዛሬ እውነትን ከውሸት ለመለየት መለኪያው ጉዳዩን በብሔር ብሔረሰብ መነፅር ማየት ግድ ብሏል – አንድን አሰቃቂ ድርጊት ወንጀል ነው ወይስ አይደለም ፣ ያሰጠይቃል ወይስ አያስጠይቅም ብሎ ለመናገር ክህግ አንፃር ሳይሆን ከብሔር ብሄረሰብ ተቆርቋሪነት እና ማንነት አንፃር መቃኘት ቀዳሚ ስፍራ ተስጥቶት እከሌ ከእከሌ በማይባል ደረጃ የህግ እና የህጋዊነት አሰራር ድምጥማጡ እየጠፋ ነው… ክልል እና ሳጥን – ከዚያ ሳጥን ውጪ ማሰብ አይቻልም።

ኢትዮጵያን እያተራመሳት ያለው ህገ መንግስት በሚባል ሰነድ ያለመገዛት ብቻ ሳይሆን በምትኩ በዘረኞች እና ስግብግቦች ምናብ እና መልካም ፈቃድ ውሎ ማደር ብቸኛው አማራጭ ሆኖ የቀረበበት ሁኔታ መስፈኑ ነው። ይኼ ላለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት የደረጀ እና የደነደነ ብሎም እስካሁን የዘለቀ … እንደ ባህል እንደ ዘይቤ ስር የሰደደ ዝንባሌ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዕውን እንደሚባለው የትግራይ ሕዝብ በወያኔ አገዛዝ ተጠቃሚ አልሆነም?

በሌላ በኩል በዘረኛው የፖለቲካ ቅኝት ውስጥ የተጧጧፈውን መደዴ ቡድናዊ ዘረፋ አጋጣሚ እንደ አመቺ በመጠቀም ብልጣ ብልጥ ነን የሚሉ ስለ አገርም ስለ ብሔር ብሔረሰብም ደንታ የማይሰጣቸው ጮሌዎች ግርግሩን ተቀላቅለው የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ በሚል ለከት የለሽ ሌብነት መካሄዱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ያንድ ጅምበር ሚሊየነሮች ኢትዮጵያዊም ብሔረሰባዊም አይደሉም – እንደ ጨዋታው አውድ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ሌላ ጊዜ ብሔረሰባዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ለነሱ ፋይዳ ያለው ጉዳይ ቁጥጥር ፣ ህግ እና ስርዓት በሌለው ትርምስ ውስጥ ገንዘብ ማግበስበስ ነው። ከየት አመጣኸው ብሎ የሚጠይቅ ተቋማዊ ፣ ህጋዊ እና ሙያዊ ስርዓት አለመኖሩ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ከአገሪቱ ነባራዊ እውነት ጋር ጨርሶ የማይጣጣም ህይወት ይኖራሉ። ወንጀል በብሄረሰብ መጋረጃ ሲጋረድ – ከመጋረጃው ጥላ ሥር የሚካሄደው መጠነ ሰፊ ህገወጥነት ቃላት ሊገልፁት ከሚችሉት በላይ አስከፊ ይሆናል። ትርምስ አትራፊ ሆኖ ያገኙ ስግብግቦች አገር ከተረጋጋ ተጠያቂነቱ አይቀሬ መሆኑን ከማንም በላይ ያውቃሉ… እና ትርምሱን ለማስቀጠል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።

ባለፈው አንድ ዓመት የወያኔ ፍጹማዊ ዘረኛ አገዛዘ በስብሶ ወድቋል በሚል መንፈስ በአዲስ ህብረ ብሄራዊ እና አገራዊ መንፈስ ለለውጥ የተነቃቃው ዜጋ ሳይቀር መልሶ በዚህ የገለማ የዘር ቅኝት ውስጥ ተዘፍቆ አንዱ በሌላው ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት ዘሩን ተመርኩዞ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መቀጠሉን እያስተዋልን ነው። አንዳንዱ የህግ ዋስትና በመጥፋቱ ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ በመሰለው መንገድ ሲነጉድ ነገርግን ትርምሱን እያደመቀ መሆኑን መገንዘብ ተስኖታል። በትርምስ የሚያተርፉት አተራምሰው ሥልጣን ላይ የወጡ የቀን ጅቦች ብቻ ናቸው።

ያለንበት ዘመን የደረስንበት የማህበራዊ መገናኛ ዕድገት ደረጃ ለበሬ ወለደ ወሬ እና ውሸቶች በቅጽበት መሰራጨት አመቺ መደላደል ሆኗል – እንደምናየው ውሸት በብርሀን ፍጥነት ይሰራጫል ፣ ይተቻል ፣ ይታመናል የተግባር መርህ ሆኖ መንጋ ይቀሰቅሳል… ያነሳሳል።

በዚህ ሰሞን ባህር ዳር ከተፈጠረው ዱብ ዕዳ ጋር ተያይዞ ከታዘብነው ትንሿን ምሳሌ እዚህ ላንሳ – ዶ/ር አቢይ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው ባህር ዳር ላይ ሆኖ ነው ተባለ። ሰውየው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር እንደመሆኑ ለሥራው ቅልጥፍና ሲል በፈለገበት ያገሪቱ ክፍል ቢገኝ ለምን እንግዳ አነጋጋሪ እንደሚሆን አልገባኝም… በወሬ ምንጭነት ሻምፒዮን ለመሆን የሚሽቀዳደሙ የማህበራዊ መገናኛ አራጋቢዎች እየተቀባበሉ ጉዳዩን በሰዓታት እና ደቂቃዎች እያወራረዱ ትንተና ሰጡበት… ከዚህ መንደርደሪያ በመነሳት አቢይ እዚያው ሆኖ የሹማምንቱን ግድያ ሲያቀነባብር ነበር የሚለው ዘገባ ወትሮም በምናውቃቸው የጥላቻ አራጋቢዎች መሰራጨት ቀጠለ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ላለባት ጨዋታ ተጫዋቾች ተመረጡ

በማግስቱ ይኼ መረጃ ፍፁም ትክክል አለመሆኑን በውቅቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመቀበል አራት ኪሎ በስፍራው ተገኝቶ የነበረ ጋዜጠኛ ‘የለም አዲስ አበባ ከቢሯቸው ሆነው ነው…’ ቢል ማን ይስማው። ጭራሽ ሴራ ተደግሶ ነበር የሚሉን ተንታኞች ጋዜጠኛውን የሴራው ተዋናይ አድርገው ፈርጀውታል –

እና በንደዚህ አይነቱ የወሬ እና ውሸት ቅብብሎሽ ዕለታዊ ኑሯችንን እንመራለን። ድሮ አሉባልታ ካንዱ ወደሌላው የሚተላለፍው በቡና ወይንም መሸታ ቤት ብቻ ነበር ፤ ዛሬ በረቀቀው ቴክኖሎጂ አሉቧልተኛው ሁሉ ተጥዶ የመሰለውን እንደ ሰደድ እሳት በሚያሰራጭበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው – የሀይማኖት ነቢይ ነን እንደሚሉት ካራቲስቶች የፖለቲካ ሀሁ ያልቆጠሩ ማይማን ገደብ የለሽ አሉባልታቸውን ሲነሰንሱ ውለው ያድራሉ። አብዛኞቹ ምንም ዓይነት ሀላፊነት የሌላቸው እና የማይሰማቸው ሆነው ሳለ ግን የብሄር ብሄረሰብ ስም አንጠልጥለው ጦር ያውጃሉ… ፍለጠው ቁረጥው ይላሉ።  መዘዝ እንዳለው ሊያጤኑ የሚችሉበት ህሊና ባይኖራቸውም ተጠያቂነቱ ውሎ አድሮ መምጣቱ እንደማይቀር እንኳ የሚያሳስባቸው ዘመድ የሌላቸው ወፈፌዎች ይመስሉኛል።

ለዘራቸው እጅግ ቀናኢ ነን ያሉ ወታደሮች እና መኮንኖች በነሱ የዘር ማንጠሪያ ተለክቶ ‘ለስላሳ’ ብለው በኮነኗቸው አለቆቻቸው ላይ የወሰዱት የሰሞኑ ወታደራዊ ጭፍጨፋ የደረስንበትን አገር የማጥፋት አዘቅት ጎላ አድርጎ ያመላከተ ሌላ አስረጂ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ላይ በደረሰው ክፉ አጋጣሚ ምክንያት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የታየው ሰጥ አገባ የብዙዎች ታዋቂ ግለሰቦችን አመለካከት አድማስ ጭምር ገሀድ ያጋለጠ ነው። እገሌ እገሌ ማለቱ ጠቃሚ ባይሆንም ዙፋኗ ላይ የተደላደለችው ንግስት ውሸት ምን ያህል ግዛቷን እንዳስፋፋች ግን አረጋግጠናል። አይደለም አንድ ሰፊ የአገር አካል የሚያስተዳድር የመንግሥት ሀላፊ ቀርቶ የአንድ ወረዳ አስተዳዳሪ ተኩሶ መግደል ትልቅ ወንጀል ነው። የተያዘው ሰጥ አገባ ይህን አሰቃቂ ፀረ አገር ወንጀል የፈፀሙ ወገኖችን ከወዲሁ እስከ ማሞካሸት እና ተግባራቸውን ማሽሞንሞን ምን የሚሉት እንደሆነ አይገባኝም። ሰው ወድቋል ፣ ከፈተኛ ሀላፊነት ላይ የተቀመጡ ሹማምንት በሥራ ገበታቸው ላይ ሳሉ በጥይት ተደብድበው ሞተዋል — ድርጊቱ አደባባይ ላይ በማን አለብኝነት የተፈፀመ የጭካኔ ተግባር ነው… ሊወገዝ ሊኮነን ይገባዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ እውነት የሚባል ነገር ደብዛው እየጠፋ ነው – መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የመጀመሪያው ሰው አዳም ከኤደን ገነት ከተሰጠው ክብር እንዲባረር የተደረገው እባብ የተሳሳተ መረጃ ስላቀበለው ነበር። ‘እግዚአብሔር በለስ እንዳትበላ ያለህ እንደሱ በገናና ዙፋን ላይ እናዳትቀመጥ ብሎ ነው…’ የሚል መረጃ እባብ አቀበለው። ውሸት ማሰራጨት ፣ ሰውን በተንኮል ማሳሳት የተጀመረው ገና ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ ነው። ውሸት አብራን ኖራለች መዘዟም የከፋ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክብር እንክርዳድ ተዘርቶበት ስንዴ ሆኖ ለበቀለ ትውልድ!!! – ተስፋየ ኤልያስ

በለስ ስትበላ እንደ እግዚአብሔር በዙፋን ላይ ትቀመጣለህ የሚለው የእባብ ውሸት ዛሬ ‘አቢይን ካስወገድክ የምትመኛትን የጥንቷን የጠዋቷን ኢትዮጵያ ትጎናፀፋለህ” ወይንም ‘አምባቸው መኮንን ከጠፋ አማራ ‘ሙሉ ክብሩን ይጎናፀፋል” የሚል ፐሮፓጋንዳ የሚያሰራጩትን ዋልታ ረጋጭ ፖለቲከኞች ይመስለኛል… ልክ እንደ አዳም ዘመን እባብ የበለሱን ታሪክ ይደግሙልሀል። እባቦቹ አቢይን ስንብላው ከዙፋኑ ላይ በሙሉ ክብር እንቀመጣለን ነው የሚሉን… እነደ አዳም የሚከተለውን ዘላለማዊ ውርደት ልብ የሚለው ጠፍቷል።

ህብረተሰቡ እንደ አባታችን አዳም አንድን ጉዳይ እውነት ነው ውይንስ ውሸት ብሎ መጠየቅ የዘነጋበት ዘመን ላይ ነን – ስለ አንድ ተጨባጭ ጉዳይ አቋም ለመውሰድ የጉዳዩን እውነተኛ ምንጭ በጥሞና ለመመርመር ፍላጎትም የለውም – በዘር ቦይ ኮለል ብሎ የተነዛውን የወሬ አምቡላ ግጥም አድርጎ ተግቶ ለተግባር ይንቀሳቀሳል… በውሸት ትርክት ላይ ተመርኩዞ ሀውልት (አኖሌ) ይገትራል… እውነት ክብሯ ተገፏል ፣ ራቁቷን ቀርታለች… እንዲያውም ሞታለች… ውሸት በበኩሏ የብሄር ብሄረሰብ አበጋዞችን እና ስግብግብ ዘራፊዎችን ፍላጎት ለማርካት ስትል ዙፋን ላይ ተቀምጣለች። ውሽት ፣ ሌብነት… ገንዘብ ብዙ ገንዘብ ፣ ስልጣን እና ምቾት ያተርፋሉ… በመንጋ ተከታይ ይታጀባሉ…

ኢትዮጵያ አሳሳቢ አደጋ ላይ የወደቀችው ወያኔ አገሪቱን ተቆጣጥሮ በዘር ግንድ የተመለመሉ ታማኝ ሎሌዎቹን በመላ አገሪቱ ለዘረፋ ካሰማራበት ወቅት ጀምሮ ነው – ከዚህ አደጋ የሚታደጓት ደግሞ የራሳቸው ውስን አጅንዳ ያላቸው ከአንድ ወይንም ሁሉት ብሔረሰብ የመጡ አበጋዞች ወይንም ነፃ አውጪዎች አይደሉም –

ግን ዜጎች ለዘለቄታው እንዳይፈናቀሉ የምንሻ ከሆነ ፣ የህዝብ ሀብት ሀላፊነት በተሰጣቸው የብሔር ብሔረሰብ ሹማምንት በጠራራ ፀሐይ እንዳይዘረፍ ፣ ወያኔ ባሰመረው የክልል አጥር ድንበር ተብሎ ወንድማማች ዜጋ መተላለቁ እንዲያበቃ የምንፈልግ ከሆነ ያለን አማራጭ ያልጎበጠ ያልተጠመዘዘ ህግ እንዲገዛን ማረጋገጥ ብቻ ነው። ይኼ በጨዋ ደንብ ጠረቤዛ ዙርያ ተቀምጦ ከሀይማኖት መሪዎች ፣ ከሁሉም ማዕዘን በሁሉም ማህበራዊ ዘርፍ ድምፅ ሊያሰሙ የሚችሉ ዜጎች የተካተቱበት የሰከነ ውይይት እና ምክክር አድርጎ በሚቀየስ ብልሀት የሚፈታ ችግር ነው። ለዚህ ደግሞ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የአቢይ አህመድ መንግሥት ያሳያቸው በጎ አዝማሚያዎች እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰዱ የሚገባ ይመስለኛል።

አገር በሏላዊነት በህልውና መቆሙን ፣ መኖሩን ከሚያረጋግጡት ቀዳሚው ጉዳይ በተፃፈ ህግ እና ያንንም ህግ ያላንዳች ጉብጠት እና ጥምዘዛ ተግባር ላይ የሚያውሉ ተቋማት ከመኖራቸው ላይ ነው። በህግ የማይገዛ ህብረተሰብ ውሎ አድሮ የከፋ ዋጋ የሚያስከፍል አዘቅት ውስጥ ቢገኝ አይገርምም ለማለት ነው።

ጥያቄው አገር “መሆን አለመሆን” ነው።

 

 

1 Comment

  1. “ኢትዮጵያ አሳሳቢ አደጋ ላይ የወደቀችው ወያኔ አገሪቱን ተቆጣጥሮ በዘር ግንድ የተመለመሉ ታማኝ ሎሌዎቹን በመላ አገሪቱ ለዘረፋ ካሰማራበት ወቅት ጀምሮ ነው”?? ዉሸት! Ethiopia is like the Tower of Pisa – based on a bad foundation! The current generation is fed with ‘3000 years’ fake history! Even the intellectuals could not agree on some common true history! Fake history, fake pride, fake (copied) politics only to fill own stomach!
    At times, what some Habesha ‘scholars’ talk or write, forces me to question if these people really know Ethiopia and its inhabitants. They seem not to know even the Amhara people they claim to be sole advocates of the people’s interests.

Comments are closed.

Share