በግልፅና በቀጥታ ካልተነገርን የመከራው ፖለቲካችን ማቆሚያ አይኖረውም  – ጠገናው ጎሹ

June 23, 2019
ጠገናው ጎሹ

ደራሲ አቤ ጎበኛ ከዛሬ አርባ አምስት ዓመት በፊት ( ሐምሌ 1966) በማህፀኗ ውስጥ ሆኖ ምስኪን እናቱን “እውነት በሌለበት ዓለም ለመኖር አልወለድም” ብሎ የሞገታትን   ህፃን  ኢይዝራኤሎስ ብሎ በምእናቡ በሰየማት ደሴት አገር እንዴወለድ አደረገው። በዚችው በውጭ ወራሪዎች ስትገዛና ስትመዘበር ቆይታ ነፃነቷን ብታገኝም ከእራሷ ብልሹ አገዛዝ ነፃ መውጣት ባልቻለችው ደሴት አገር ሳይፈልግ የተወለደው ህፃን  ካደገ በኋላ ለነፃነትና ለፍትህ ሲሟገት እንደፈራውም በጎልማሳነት እድሜው  በግፈኛ አገዛዝ ባለሥልጣኖች ሞት ተፈረደበት ። ያስፈረዱበትና የፈረዱበት የግፍና የመከራ ባለሥልጣናት ህይወቱን በመቅጠፍ ልሳኑን እስከ ዘጉበት ድረስ ከንቱነታቸውን ተፀይፏል ። በቁም ያሉ ሬሳዎች (ሙቶች) እነርሱ እንጅ እርሱና እርሱን መሰል እልፍ አእላፎች  አለመሆናቸውን በቀጥታና ፊት ለፊት ሞግቷቸዋል ።  በዚህ ዋና ገፀ ባህሪ አማካኝነት የአስተዳደር በደልንና የፍትህ እጦትን አስከፊ ውጤት በግልፃና በቀጥታ ባሳየበት  “የአልወለድም” መጽሐፉ መግቢያ ላይ   የዚያች ጎዳና ላይ ለምኖ አዳሪና አልወለድም በሚል የሞገታት የማህፀኗ ህፃን ታሪክ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ታሪክ መሆኑን እንዲህ ሲል ይነግረናል ።

“አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በእግዚአብሔር መኖር በእውነት በፍትህ በቅንነት፣ እንዲሁም ለእነዚህና እነሱን ለመሰሉ ነገሮች መኖር አምኖ እስከቻለ ድረስ ወደ በጎው ነገር ለማምራት የሚጣጣር ህዝብ ነው ነገር ግን ይህ ቅንና መከረኛ ህዝብ ለዚህ በጎ ዝንባሌው የተከፈለው ዋጋ ህሊና በሌላቸው ዝቅተኛና ከፍተኛ ሹማምንት ተረግጦ መገዛትና እረኛ እንደሌለው በግ በሚንቀሳቀሱ ነጣቂ ተኩላዎች መበላት ነበር የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ቅን ጎዳና ለመመራት በተዘጋጀበት ጊዜ ቅን ዓላማውን ጠማማ ለሆነው የግል ፍላጎታቸው ለመሠዋት የተዘጋጁ አራዊት በየክፍሉ ተለቀቁበት።”

ይህን ህሊናን በእጅጉ ሰቅዞ የሚይዝ መሪር እውነት በቅንነትና በእውነተኛ የነፃነት አርበኝነት ስሜት ለመረዳት ዝግጁ ለሆነ የአገሬ ሰው ከዚያን ጊዜው ትውልድ በበለጠ ስለዛሬው የእኛነታችን ልክ የሌለው ውድቀት እየነገረን መሆኑን ለመረዳት የሚቸገርው አይመስለኝም ።

የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ልክፍት የተጠናወታቸው ከፍተኛና ዝቅተኛ ፖለቲከኞች (ባለሥልጣናት) ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሲያወርዱበት ከነበረው የመከራና የውርደት ዶፍ የተገላገለ መስሎት “የዘመናችን ሙሴዎች” በሚል ውዳሴ የተቀበላቸው የዋህ ህዝብ ጨርሶ ያልተነካውና በየፓርቲና በየመንግሥት አደረጃጀትና መዋቅር   ሥር  የሚተራምሰው የበታች ተኩላ ባለሥልጣን/ካድሬ  ሰለባ ከመሆን አልዳነም ።

ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ  በዘለቀው የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ሥርዓተ ፖለቲካ በተዋናይነት ወይም በረዳት ተዋናይነት ማገልገላቸውን በፀፀት የነግሩን እና የይቅርታ ቃላትን የደረደሩልን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ብዙም ሳይራመዱ ህወሃት/ኢህአዴግ በኦዴፓ/ኦነግ/ኢህአዴግ እንዲተካ የማድረጋቸው  ጉዳይ  ፖለቲካችን  ከተኩላዎች መቀያየር የዘለለ ብዙም  ትርጉም  እንዳይኖረው አድርጎታል ። አንዳንድ ለለውጥ እውን መሆን ያግዛሉ የሚባሉ አወንታዊ  እርምጃዎችን በማየት የአሁኑ ተኩላነት ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው ተኩላነት ይሻላል  የሚል የተሸናፊነት  መከራከሪያ ካላቀረብን በስተቀር መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይኸው ነው ።

ከአስከፊው የፖለቲካ ተሞክሮ መማርና የሚበጃውን ለማድረግ ባለመቻላችን ምክንያት በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ልክ የሌለው የግልና የቡድን ፍላጎት በእጅጉ የተጠናዎታቸው የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞች (ተኩላዎች) ነፃ የሆነ መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆናል በሚል በተስፋና በቅንነት የሚጠባበቀውን ህዝብ እየተፈራረቁ የመከራውና የውርደቱ ዘመን እያራዘሙበት መሆኑን በመሬት ላይ ካለው መሪር እውነታ በላይ የሚነግረን የለም ። አይኖርምም ።

ደራሲ አቤ ጎበኛ በመንገድ ላይ ኗሪ ምስኪን እናትና በማህፅኗ ውስጥ ሆኖ አልወለድም ብሎ በሚሞግታት ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ልጇ አማካኝነት ትቶልን ያለፈው ሥራ የሚነግረን በጥቂት እኩያን ፖለቲከኞች/ባለሥልጣናት/ተኩላዎች  ምክንያት  ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ ሰብአዊ መብት ፣ የዜግነት መብት ፣ እውነተኛ ሰላምና ፍቅር፣ የጋራ ብልፅግና ፣ ወዘተ በሌለባት አገር ከመወለድ አለመወለድን እንደሚያስመርጠን ነው። ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በኋላም እራሳችን በስፋቱም ሆነ በጥልቀቱ ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ማግኘታችን ከባድ እንቆቅልሽ ነውይበልጥ ልብን የሚሰብረው ደግሞ  ይህኑ እንቆቅልሽ ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ በራሱ ሌላ ከባድ እንቆቅልሽ  እየሆነ መምጣቱ ነው ። የአገሩ ጉዳይ ከምር ለሚያስጨንቀው ዜጋ እና በአጠቃላይ የረጅም ጊዜ የነፃነት ታሪክና አኩሪ ባህል አለኝ ለሚል ህዝብ  ከዚህ የከፋ  አንገት የሚያስደፋ የፖለቲካና ማህበራዊ ዝቅጠት የለም ። እናም እንዲህ አይነቱን አካሄድ በጥሞና ተረድቶ ተገቢውን እርምት ከማድረግ የተሻለ ምርጫ ጨርሶ  የለም ። አይኖርምም ።

አለመወለድን ያስመረጠንን ወይም የሚያስመርጠንን ክፉ አገዛዝ (ሥርዓት) በፅናትና በአብሮነት አስወግደን መወለድን በፀጋና በደስታ ተቀብሎ የሚያስተናግድ ሥርዓት እውን ከማድረግ የተሻለ መንገድ እንደ ሌለ ነው  አቤ ጎበኛ ከብዙ ዓመታት በፊት አምጦ በወለደው አልወለድም አማካኝነት የሚነግረን አልወለድም በሚል ምስኪን እናቱን የሞገተውን ህፃን  በህይወት እያለ የመብትና የፍትህ ተሟጋች ፣ በመጨረሻም የሞት ፅዋ እስከ ተቀበለበት ድረስ እውነትና እውነትን ብቻ ይዞ እንዲዘልቅ የሚያደርግ እጅግ ድንቅ ሰብእና ያለው  አድርጎ የመረጠውም ለዚህ ግዙፍና ጥልቅ መልክቱ ሲል  ነው ።

እንዲህ አይነት የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ህሊና የሚፈትኑ ፣ትውልድ ተሻጋሪና እጅግ ጥልቅ የሆኑ ሥራዎችን አምጠው የወለዱ በርካታ ብርቅየ ደራሲያን ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ማለትም በዚህ በተያያዝነው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እየሆንና እያደረግን ያለውነውን እጅግ አስከፊ ሁኔታ   ከመቃብር ተነስተው ቢታዘቡን ምን ይሉ ነበር? እኛስ ምን እንላቸው ነበር?

መልሱን የኖረበትንና አሁንም እየኖረበት ያለውን መሪር ሃቅ አሳምሮ ለሚያውቀው ህዝብ በተለይ ግን ተማርኩና ተመራመርኩ ለሚለው የህብረተሰብ አካል እተወዋለሁ ። አዎ!  በተለይ ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል  የእራሱን የምንነትና የማንነት ሃቅ   ከሌላው ብቻ ሳይሆን ከእራሱም እየደበቅና ከእራሱ ህሊና  እየሸሸ ደጋግሞ በቁም መሞትን የተለማመደው ይመስላል ። መንበረ ሥልጣን ላይ የሚወጡ ፖለቲከኞችም ይህንኑ ውድቀቱን አሳምረው ስለሚያውቁት በየአደባባዩና በየመሰብሰቢያ አዳራሹ ታዳሚያቸው በማድረግ በንግግራቸው የእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር መጨረሻ  ላይ ክንዱ እስኪዝል ያስጨበጭቡታል ።

አዎ! ሳይማር ያስተማረውን መከረኛ ህዝብ  አንቅቶና  አደራጅቶ ለእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ እንዲበቃ ማድረጉ ይቅርና ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር የእርሱነቱን የክብር ካባ አውልቆ ሥልጣን ላይ  የሚወጡ ፖለቲከኞችን “የለውጥ ሃዋርያ” ካባ የሚደርብ  ፣ ወይም በየመንደሩ  የፖለቲካ ክለቦችን ማራባትን እንደ ፖለቲካ ሥራ የሚቆጥር ፣ ወይም ደግሞ በእለት ነፍስ ማቆያ ዳቦው እያስፈራሩ የፖለቲካቸው ታጋች (political hostage ) የሚያደርጉትን ፖለቲከኞች እየፈራ አንደበቱን  የሚዘጋና ብእሩን የጠረጴዛው ማድመቂያ የሚያደርግ ምሁር ባለባት አገር  አሁን እንደምናየው አይነት እጅግ አስከፊ ክስተት ቢከሰት  ከቶ የሚገርም አይደለም ። አዎ! በዚህ  ህን አይነት የቁም ሙት መንፈስ መቀጠሉ ከምር ተሰምቶን እንደ ሰውና እንደ ዜጋ ተከብረንና ተከባብረን የምንኖርበትን እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ  ነገ ሳይሆን ዛሬ  ቆርጠን ካልተነሳን ሰሞኑን  የተፈፀመው አስከፊ ክስተት ተደጋግሞ እንደማይከሰት ምክንያትና ዋስትና  አይኖርም ።

እናም ከቀን ወደ ቀን እየከፋ በመሄድ ላይ ያለውን  ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ በሸፍጠኛና በሴረኛ ፖለቲከኞች ላይ ብቻ ማሳበብ የለየለት የምሁርነት ወይም የልሂቅነት ደደብነት ነው ። በተሻለ አገላለፅ ብገልፀው ደስ ባለኝ ። አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት መሽኮርመም ወይም ወኔ ማጣት እራሱን የቻለ የውድቀት ማሳያ እንጅ ከቶም የመፍትሄ ፍለጋ መነሻ መንገድ አይደለም  የሚል እምነት ስላለኝ የተሻለ አገላለፅ ፍለጋ አላስፈለገኝም።

በአማራ ክልል (ባህር ዳር) ከፍተኛ የክልል መስተዳድር ባለሥልጣናት ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ የአገሪቱ ኢታማጆር ሹም የተገደሉበት እና ኦዴፓ/ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ግድያውን መርተዋል ባላቸው ሜጀር ጀኔራል ላይ የግድያ እርምጃ የተወሰደበት የሰኔ 15 2011 ዓ.ምቱ ክስተት በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያሳስብ ክስተት ነው ። አዎ! የአንዲት አገር (የኢትዮጵያ) ልጆች የተገዳደሉበትና  የተጎዳዱበት ሁኔታ እንደ ሰውም ሆነ እንደ ዜጋ ልብ ያቆስላል። ሃዘንንም የከፋ ያደርገዋል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግብጽ በየአቅጫው ሩጫ ላይ ና - መሳይ መኮነን

ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ ከመጣንበት የበከተና የከረፋ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እየወጣን መሆኑን የሚያሳይ  ብርሃን ሊፈነጥቅ ነው ስንል  መልሶ እየጠቆረ ያስቸገረንን  የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ  ደመና የባሰ ከባድና አስፈሪ እየሆነ መጥቷል  ።

ምን ተደረገ ? ማን ምን አደረገ ? ለምንስ አደረገ? እንዴትስ አደረገ?  ምንስ ይደረግ? የሚሉ ጥያቄዎች ገለልተኛ በሆነና  ተአማኒነት ባለው አካል ተጣርተው(ተመርምረው)   ግልፅና ተአማኒ የሆነ መልስ ማግኘት እንዳለባቸው እና ጥፋተኝነቱ በነፃ የዳኝነት ሥርዓት የሚረጋገጥበት ግለሰብ ወይም ቡድን ተገቢን ፍርድ  ማግኘት እንዳለበት በጭራሽ የሚያጠያይቅ አይደለም ። መሆንም የለበትም ። በአወንታዊነት መልስ ለመስጠት በእጅጉ የሚያስችግሩ ጥያቄዎችን አድበስብሶ ማለፍ ግን የትናንትን አስከፊ ክስተት ከመድገም ወይም ከመደጋገም አያድንም ።

ለማሳያነትት ያህል ፦ 

  • የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች ነፃ የሆነና ተአማኒነት ያለው አካል እንዲቋቋምና ወደ ሥራው እንዲገባ  ለመፍቀድ የሚያስችል የሞራልና የፖለቲካ ልእልና አላቸው  ወይ ?
  • ሩበ መቶ ክፍለ ዘመን ተዘፍቀው ከኖሩበት የፖለቲካ አፈጣጠራቸውና ባህሪያቸው ለመውጣት ቁርጠኝነቱ በእጅጉ የሚጎላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ፍትህንና ርትዕን በማያወላዳ አኳኋን የሚያረጋግጥና ለፖለቲካ ሥልጣናቸው የማይመች የአጣሪ ቡድንና የማጣራት ውጤት በፀጋ ለመቀበል እና በአግባቡ ለማስተናገድ እንዴት ይቻላቸዋል ?
  • የኢህዴግ ፖለቲከኞች ሃላፊነታቸውንና ተጠያቂነታቸውን በግልፅነትና በአግባቡ ለመወጣት ይችሉ ዘንድ የሚያስገድድ የነቃና የተደራጀ ህዝባዊ ሃይል መፍጠር ባልቻልንበት  የፖለቲካ አውድ  ውስጥ  ነፃና ተአማኒ የአጣሪ አካል እንዴት እውን ለማድረግ ይቻላል  ?
  • በፖለቲካ ሸፍጥና ሴራ ሲጦዝ ቆይቶ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ስሜታዊነት የፈነዳው መግደልና መገዳደል በተፈፀመበት ቅፅበት (ገና የተተኮሰው ባሩድ ሳይበርድ) በቴሌቪዚዮን መስኮት ብቅ በማለት መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮብን አከሸፍነው የሚሉ ፖለቲከኞች ነፃና ተአማኒነት ያለው እውነትን የሚነግረንን አካል ለመቀበል  እንዴት ይቻላቸዋል
  • በተመሳሳይ ቅፅበት በግልፅና በሚገርም ሁኔታ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ጉዳዮችን በማስተላለፍ ህዝብን በእጅጉ ግራ ያጋቡ የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች (ባለሥልጣናት) የፖለቲካ ገመናቸውን በታትኖ እውነትን ለህዝብ የሚያሳውቅ  ነፃና ተአማኒ አካል  ተቋቁሞ የሚደርስበትን እውነተኛ መረጃ እና መደምደሚያ አስተያየት በፀጋ ( ያለምንም ሸፍጥ ወይም ቅሌት) ለመቀበል እንዴት ይቻላቸዋል ?   
  • የቤተ መንግሥታቸውን አካባቢ ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች  በኦነግ ተፅዕኖ ሥር በወደቀው የራሳችቸው ድርጅትና በአክራሪ ብሄረተኞች አራጋቢነት ሚሊዮኖች ከቀያቸው ሲነቀሉ ፣ በርካታዎቹ ለአካል ጉዳትና ለሞት ሲዳረጉ “አልሰማሁም ወይም ከንቲባ አይደለሁም” ሲሉ ቆይተው የወገን ጉዳይ የአሳሰባቸው ሚዲያዎች ጉዳዩን ለህዝብ በማሳወቃቸው ለምን አሳወቃችሁብኝ በሚል  ያዙኝና ልቀቁኝ የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት አይነት ገልተኛና ተአማኒ መርማሪ ሊያቋቁም ይቻለዋል?
  • አንፃራዊ የሆነ አገራዊ የፖለቲካ ረዕይና አጀንዳ አለን ይሉ የነበሩትን ጨምሮ በዘመነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተቀዋሚነት የለምና ወደ ተፎካካሪነት ተሸጋግራችኋል የተባሉ የፖለቲካ ድርጅት ነን ባዮች ጠቅልለው የኦዴፓ/ኢህአዴግ ተለጣፊዎች በሆኑበት አውደ ፖለቲካ ውስጥ ምን አይነት ነፃና ተአማኒ አካል ነው በፖለቲካ ሸፍጥና ፕሮፓጋንዳ የተመሰቃቀለውን ፖለቲካ ወለድ

አስከፊ መገዳደል በእውነትና በእውነት ብቻ አበጥሮ  ወደ  የገሃዱ ዓለም  የሚያመጣው?

  • ገና ከአሁኑ እጅግ ተራና  እርካሽ በሆነ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተጠመዱ ፖለቲከኞች የህግ የበላይነትና የፍትህ ሃያልነት የሚመሰከረበትንና ውሳኔ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ እንዴት ለማመቻቸት ይቻላቸዋል

 በበኩሌ ህወሃት/ኢህአዴግን ከተካው ኦዴፓ/ኢህአዴግ ለነዚህ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ  መጠበቅ ይችላል  የሚል  እምነት የለኝም። ክሰተቱ ከተከሰተበት ቅፅበት  ጀምሮ ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ ባለሥልጣንና ካድሬ ም የሚዥጎደጎደው የ መፈንቅለ መንግሥት ትርክት የሚያመላክተን ይህኑ አሉታዊ መልስ ነው ።  ቀድሞውንም “የፖለቲካ አመለካከታቸውና አካሄዳቸው አላማረኝም”  የሚሏቸውን ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን የመብት ተሟጋቾችንና የሚዲያ ባለሙያዎችን በማሳድድና በማሰር ዘመቻ ላይ የመጠመዳቸው ሁኔታ  የሚነግረንም ይህንኑ መሪር ሃቅ ነው።

  • ይባስ ብለው ለዓመታት እጅግ ዘግናኝ ግፍ ሲፈፅሙበት የነበረውንና እያሻሻልነው ነው የሚለትን የፀረ-ሽብር ህግ ተብየ በሚገርም ፍጥነት ከጠረጴዛ መሳቢያቸው መዝዘው የሽብርተኝነት ክስ መሥርተዋል ። ጉልቻ ብቻ የተቀየረለት የካንጋሮው ፍርድ ቤትም እንደለመደው ዜጎችን በቀጠሮ የማንገላታት ሥራውን ቀጥሏል። ታዲያ የዚህች አገር የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ መጫወቻ ሚዳነቷ የሚያበቃበት ጊዜና ሁኔታ እንዴት አያስጨንቅ ?

በህይወት የሌሉት የህወሃት/ኢህአዴጉ “ታላቅ መሪ” በግፍ የሚያስሯቸውን ወይም በቁጥጥር ሥር የሚያውሏቸውን ዜጎች በወንጀለኝነት ፈርጀው (ሰይመው) ህጋዊ ለማስመሰል ወደ ፍርድ ቤት ልከው በይፅና ያስወስኑበት የነበረው እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ  አሁንም ያንኑ መንበረ ሥልጣን  በተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስተርና ባልደረቦቻቸው እየተደገመ መሆኑን ከሚያደረጓቸው ንግግሮችና በፅሁፍ ከሚያስነብቧቸው መግለጫዎች በግልፅ መረዳት ይቻላል ።

 “ የተገዳደሉትና የተጎዳዱት ወገኖች  ለእርካሽ ፖለቲካችሁ እንደምታስወሩት  በመፈንቅለ መንግሥት ምክንያት   ሳይሆን የእናንተውን የውስጥ የፖለቲካ ደዌ በቅጡ ማድረግ ባለመቻላችሁና ነውና ይህን ተረድታችሁ ለአገር የሚበጀውን አድርጉ” የሚል ግልፅና ቀጥተኛ መልእክት እንዲደርሳቸው ማድረግ የግድ ነው ። ያለዚያ ዝምታ መፈቀር እየመሰላቸው ወደ ማንመለስበት ቀውስ ነው ይዘውን የሚነጉዳሉ ።

እንኳን ለእራስ ለሌላም የሚተርፍ የተፈጥሮና የሰው ሃይል ባለፀጋ የሆነች ምድር (አገር) በተለመደ የግልና የቡድን ፖለቲካ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ በሚያናቁረውና በሚያጋድለው በጎሳ/በዘር/በመንደር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ በተለከፉ ፖለቲከኞችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ምክንያት ዜጎቿን ከሰብአዊ ፍጡር በታች ከሚያውል አዙሪት ለመውጣት አለመቻሏ  በእጅጉ ህሊናን ያቆስላል ።

እናም ይህ አስከፊ ሁኔታ  እንደ ሚያሳስበው ተራ ኢትዮጵያዊ  ያለንበትን መሪር እውነት በግልፅና በቀጥታ መግለፅ አስፈላጊ ነው የሚል ፅዕኑ እምነት ስለአለኝ  እያስታመምን ወይም እያስመሰልን እንግለፀው ከሚሉት ጋርም  ጨርሶ  አልስማማም ።

እጅግ አስቀያሚ የሆነ  ፖለቲካ ወለድ ክስተት በተከሰተ ቁጥር  ለምንና እንዴት? የሚል መሠረታዊ ጥያቄና ማንሳትንና የሃሳብ ፍትጊያን ችግርን እንደ ማባባስ ወይም እንደ ፖለቲካዊ ነውር (political aggravation and taboo) የመቁጠር ይዘት ያለው ልፍስፍስ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አብረው የሚሄዱ ነገሮች አይደለም። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ከችግርነት አልፈው ወደ አስከፊ ውድቀት የሚወስዱ ፖለቲካዊም ሆነ ሌሎች ኩነቶችን በወቅቱና በተገቢው መንገድ (በግልፅነትና በቀጥታ) እና ውጤታማ በሆነ አቀራረብ ተነጋግረንና ተረድተን በትምህርት ሰጭነታቸው ካልተጠቀምንባቸው በስተቀር ለጊዜው እፎይ ያልን ቢመስለንም መልሰን መላልሰን መውደቃችን ከቶ አይቀርም ።  ፖለቲከኞቻችንም ይህን ልፍስፍስ አስተሳሰብ ስለሚያውቁት ለሸፍጥና ለሴራ ፖለቲካቸው ግብአትነት አሳምረው ይጠቀሙበታል ።

ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን እየፈራን ወይም ነገር እናባብሳለን እያልን ወይም አጎብዳጅነት (አድር ባይነት)  እየተጠናወተን  ወይም የምን አገባኝነት ክፉ ልክፍት ሰለባ እየሆን  እኩያን ገዥዎች ያስከተሉትን አገራዊ መከራና ውርደት ተሸክመን መዝለቃችን ትምህርት ካልሆነን ከምር እራሳችን መመርመር ይኖርብናል።  ዛሬም በስሜት ከመጋለብ የዘለለ የመረጃና የሃሳብ ልውውጥ እናድርግ ፣ ፖለቲከኞችንም በዚህ አቀራረብ  መነሻነት በቀጥታና በግልፅ እንሞግታቸው ከማለት ይልቅ  “ዝም በሉ ወይም አካፋን አካፋ አትበሉ” የሚል እጅግ ጋግርታምና  ከሰብአዊ ፍጡር በታች  ዝቅ የሚያደርግ አስተያየት እየተደጋገመ ይሰማል።

ህወሃት/ኢህአዴግ ሠራሹን ክፉ የፖለቲካ ቫይረስ ከምንጩ ማድረቅና ጤንነቱ የተዋጣለት ሥርዓተ ፖለቲካ መመሥረት ለእራሳቸው  ለልክፍተኞችም ፍቱን መድሃኒት ስለመሆኑ በግልፅ ፣ በቀጥታ ፣ በጥበብና  ገንቢነት ባለው አኳኋን ለመነጋገር (ሃሳብ ለመለዋወጥ) በእጅጉ የሚጨንቀው ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ ወይም ለመብት ቆሚያለሁ የሚል አክቲቪስት  ለምን አይነት የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርህና ግብ ቆሚያለሁ እንደሚል ለመረዳት ያስቸግራል ። በእንዲህ አይነት በተልፈሰፈሰና የተለጣፊነት አባዜ በተጠናወተው የፖለቲካ ሰብእና እውነተኛና ታሪካዊ ለውጥን እውን ለማድረግ  ከቶ አይቻልም ።

በእውነት ከተነጋገርን ሰሞኑን የተከሰተው አስከፊ ክስተት በአንድ በኩል  አንድ ዓመት ሙሉ በዓለም የመጀመሪያ ሪከርድ ባስመዘገብንበት ሁኔታ  የሚሊዮኖች ንፁሃን ዜገች ህይወት ምስቅልቅሉ ሲወጣና የገንዘብ ተቋማት (ባንኮች) እየተዘረፉ ለዚሁ እኩይ ተግባር ማስፈፀሚያ ሲውሉ  “ሃላፊነታችን በአግባቡ አልተወጣንም” በሚሉ እና በሌላ በኩል ደግሞ ከለመደባቸው  የአሽከርነት ፖለቲካ ጨክኖ ለመላቀቅ ወኔ በከዳቸው የአንድ ድርጅትና የአንዲት አገር ልጆች  መካከል የተፈጠረውን የሃሳብ ግጭት ገንቢና ወቅታዊ መፍትሄ ካለመስጠት የመጣ ነው። ይህም ይሁን ወይም ከዚህ የከፋ ምክንያት ይኑረው መፈንቅለ መንሥግት የሚባለው ግን ለከሳሽ ፖለቲከኞችም አሳፋሪ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያን ለመታደግ ፋኖን በጅምላ ማሳደድ በአስቸኳይ ይቁም -  አክሎግ ቢራራ (ዶር)  

አካፋን አካፋ ብለን መጥራት እየተሽኮረመምን ወይም በአላስፈላጊ ይሉኝታ እየተሸበብን ወይም የፈሪነት ፖለቲካን (political cowardliness) እሹሩሩ እያልን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግና ዘመናትን ያስቆጠረውን የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ደግሞ ወደ መማሪያ ታሪክነት ለመቀየር ከቶ አይቻለንም። አንፃራዊ የሆነ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ህዝብን አስተባብረው ከዚህ አይነት የፖለቲካ ደዌ ይገላግሉታል ሲባል እራሳቸውን ለተለጣፊነት ፖለቲካ አስረክበውት አረፉ ።    

ፖለቲከኞቻችን በራሳቸው የፖለቲካና የሞራል ውድቀት ምክንያት አስከፊ ክስተት በተከሰተ ቁጥር እውነቱን ተጋፍጦ የሚበጀውን ከማድረግ ይልቅ እጅግ ልፍስፍስ ብቻ ሳይሆን ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ይረዳናል የሚሉትን  የፕሮፓጋንዳ ተውኔት በመተወኑ ላይ የመጠመዳቸው ጉዳይ  የአስቀያሚው የፖለቲካ ታሪካችን ውላጅ  ቢሆንም  የሰሞኑ ተውኔት ደግሞ ከደረሰው ጉዳት በላይ ህሊናን ያቆስላል ።

ከአስከፊው ክስተት በፊት ምን እንደ ተደረገ ፧ ማን ምን እንዳዳረገ ፣ ለምንና እንዴት እንደ ተደረገ  እና በክስተቱ ወቅትና ከከስተቱ በኋላም  ማን ምን እንዳደረገ  ወቅታዊና የማያሻማ መረጃ በመስጠትና ትክክለኛና ተአማኔነት ያለው ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለዜጎች ሁሉ የሚበጅ መረጋጋት ከመፍጠር ይልቅ በእጅጉ የተሳከረ የፖለቲካ ተውኔት እየታዘብን ነው ።

ይህ አይነት በርካሽ የፖለቲካ ትርፍ እሳቤ የተበከለ አካሄድ እንኳን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ትርጉም ያለው ጊዚያዊ እፎይታንም አይፈጥርም ። በአንድ በኩል “በኦዴፓ የሚመራውን ኢህአዴግንና መንግሥቱን እያስታመምን እንራመድ” በሚሉ እና በሌላ በኩል ደግሞ  “የክልሉ ሥልጣንና ተግባር ብሎም የአማራ ህዝብ መብትና ደህንነት የቀይ መስመር እየተጣሰ ባለበት ሁኔታ እያስታመምንና እየታመምን ልንቀጥል አንችልም” በሚሉ  የአዴፓ ፖለቲከኞች መካከል  የጦዘ አለመግባባት እንደ ነበር እውነት ነው ።

ይህን  ተከትሎ የተከሰተውንና በኦዴፓ/ኦነግ እና በህዉሃት ፖለቲከኞች አራጋቢነት የተፈጠረውን ግድያና መገዳደል ከመቅፅበት በሜዲያ መስኮት ብቅ ብሎ “መፈንቅለ መንግሥት  ተሞከረብኝ” በሚል  ያዙኝና ልቀቁኝ ማለት ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።

በተለይ የመፈንቅለ መንግሥትን መሠረታዊ ባህሪያት (elementary chrachterstics) አንብቦ ለመረዳት ለሚችል ሰው የፖለቲካ ሀሁ ነውና የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞቻችን በዚህ ረገድ ህዝብን ግራ ከማጋባት የዘለለ ብዙም የተሳካላቸው አይመስለኝም ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም እንኳን  ከባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ነፃ ለመውጣት የሚያስችሉትን የፖለቲካ መሪዎች አምጦ መውለድና አሳድጎ ለዓላማው አስፈፃሚነት ከፊት ለፊት ማሰለፍ ባይችልም በስሙ እየማሉ ሥልጣን ላይ የወጡ ፖለቲከኞችን ሸፍጥና ቅሌት አሳምሮ ስለሚያውቀው ይህ የአሁኑን የመፈንቅለ መንግሥት ተውኔታቸውን በሚሉት መጠን አልተቀበላቸውም። ከወደ አገር ቤት በተለይ አማራ ብለው ከሚጠሩት የአገሪቱ ክፍል የሚሰማው የህዝብ ትዝበትም  የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው ። ይህ እምነት የማጣት ፈተና ደግሞ እንኳን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለተጨማለቀው ኢህአዴግ በአንፃራዊነት ከሸፍጥና ከወንጀል ነፃ ነኝ ለሚል የፖለቲካ ሃይልም ከባድ ፈተና ነው ።

እኛው እራሳችን የፈጠርነውንና ያጎለበትነውን ክፉ የፖለቲካ ማንነት አባዜ በየህሊና ጎዳችን ደብቀን የምንደሰኩረው ዲስኩር በፍፁም የትም አያደርሰንም ። ይልቁን በቀላሉ ወደ ማንመልሰው አዘቅት ከመውረዳችን በፊት የአውሬነት ባህሪያችንን በክርስቶስ አምሳል በተሠራ የሰብአዊነት ባህሪ ቁጥጥር ሥር ለማዋል አሁንኑ መወሰንና የሚበጀውን ማድረግ ግድ ይለናል ።

ረዘም ያለውንና በብሶት ፣ በእዘኑልን አይነት እና በማስፈራሪያ ቃላትና ሃረጋት ተዘጋጅቶ የተለቀቀውን የአማራ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ በጥሞና ላስተዋለ የአገሬ ሰው  ፖለቲከኞቻችን ምን ያህል በፍርሃትና በራስ የመተማመን ቀውስ ክፉኛ  እንደ ተጎዱ ለመረዳት አይቸገርም።  ሥልጣን ላይ እንዳለ የመንግሥት አካል  ለጊዜው የሚታወቀውን የችግሩን አነሳስ ፣ ያደረሰውን ጉዳት እና ብሎም ጉዳዩን  ነፃና ተአማኒነት ባለው አካል ለማጣራት እንደተዘጋጀና ህዝብም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ በአጭሩ ከመግለፅ ይልቅ “ያስገኘሁትን የድል ገድል ለማጠልሸት የሞከሩ ሃይሎች” የሚል አሰልች   ድርሰት ፅፎ አንብቡልኝ ወይም አዳምጡልኝ ማለት አሁንም ደግሞ  ከማሰልቸት በስተቀር ብዙም ፋይዳ የለውም ።

በሚገርም ሁኔታ የህወሃት የበላይነት አንጎበር ገና በቅጡ ሳይለቀው እራሱን በኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግና  መንግሥት የበላይነት ሥር ያገኘው አዴፓም በዛሬው እለት  ተመሳሳይ መግለጫ  አውጥቷል ። ለምን መግለጫ ወጣ የሚል የቂል አስተያየት የለኝም ። አስተያየቴ ምን አለበት  ከሰለቸ ፕሮፓጋንዳ ጋጋታና ድግግሞሽ በላይ የሆነ ቁም ነገርን የሚያስጨብጥ፣   የነገን ብሩህነት የሚሳይ እና ስኬትና ውድቀትን ለማመሳከር የሚረዳ ተጨባጭ ፍኖተ ካርታ ፣ ስትራቴጅና ፖሊሲ ለህዝብ ቢ ነግሩት  የሚል ነው ።  በዚህ መሬት ላይ የወረደ  ሥራ መሥራትን  የግድ በሚል ፈታኝ ወቅት እንዴት ወደመሬት በማይወርድ የመግለጫ ጋጋታና “የአቅጣጫ ማስቀመጫ ስብሰባ” እንጠመድ ? ነው አስተያየቴ ። አሁን አሁንማ መግለጫዎችና “የአቅጣጫ ማስቀመጫ ስብሰባዎች” አዳዲስ ሳይሆኑ ከፋይል እየተመዘዙ ቀንና አንዳንድ ወቅታዊ ቃላት ተስተካክሎላቸው  የሚሰራጩ ሆነዋል ።

የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች የገንዛ እራሳቸውን ክፉ የፖለቲካ በሽታ  በቅጡ ተረድተው ተገቢውን መድሃኒት ከመፈለግ ይልቅ የእርካሽ ፕሮፓጋንዳቸውንና  የፈሪ በትራቸውን በሰነዘሩ ቁጥር  እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አገርን ጨምረው ወደ ከባዱ አዙሪት የዘው ይነጉዳሉ ።  ከፈጣሪያቸውና ከታላቁ አለቃቸው ህወሃት  እየተቀበሉ  27 ዓመት ሙሉ በመርዘኛ አሉባልታቸውና  እና ፕሮፓጋንዳቸው  መከራና ውርደት ሲያከናንቡት የኖሩትን  ህዝብ ዛሬም የዚያው አይነት ክፉ ልክፍታቸው ሰለባ አድርገውት ቀጥለዋል።

አሁንም በእራሳቸው የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ  ጨዋታ የተፈጠረውን  አስከፊ መገዳደል  በአንድ በኩል   እጅግ በተሳከረና ሸፍጠኝነት በተጠናወተው አኳኋን ለማስተናገድ መሞከር እና በሌላ በኩል ደግሞ  መዋረዳችን አልበቃ ብሎ የአሉባሉታ ዘመቻ ተከፈተብን  “  እያሉ ያንኑ መከረኛ ህዝብ ግራ ያጋቡታል ።

የሚገርመው ደግሞ ህገ መንግሥታችን የሚሉትን የጥላቻና የመገዳደል ሰነዳቸውን  ጨምሮ  የበሰበሰውና የከረፋው መሠረታዊው  የኢህአዴጋዊ  አስተሰብ፣ አወቃቀር፣ አካሄድና አሠራር ባልተለወጠበት ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ  ገድላችን ላይ የተቃጣ መፈንቅለ መንግሥት” መሆኑን ሳትጠራጠሩ እመኑን  የሚለው አደንቋሪ ትርክታቸው ነው ።

የተፈጠረውን ክስተት እንኳን መፈንቅለ መንግሥት (coup d’etat)   የክልል   መንበረ ሥልጣን ግልበጣ ብሎ ለመጥራትም የሚያስችል ባህሪና አፈፃፀም እንደሌለው ሲሆን ተማርኩ ለሚል ሁሉ ቢያንስ ደግሞ የፖለቲካ ሀሁ (ጀማሪ ተማሪ) ለሆነ በጣም ግልፅና ቀላል ጉዳይ ነው።

በተለይ በሙያና በሥራ ልምድ ብዙ ተሞክሮ ያለውና እንዲሁም ከመፈንቅል ጋር በተያያዘ ተወንጅሎ ለዓመታት ወህኒ ወርዶ የቆየ ከፍተኛ ወታደራዊ ሰው ከስብሰባ ቢሮ ባልዘለለ ግድያ  ከሆነልኝ አገር  አቀፍ  መፈንቅለ መንግሥት ካልሆነም ግን የክልል መፈንቅለ ሥልጣን አድርጌ  ከማእከላዊው መንግሥት ጋር ተስማምቸ የክልል ገዥ እሆናለሁ ወይም የልአላዊት አማራ ክልል የመጀመሪያው ፕረዝደንት እሆናለሁ  የሚል እምነት ይኖረዋል ብሎ እንኳን ለማመን ለማሰብም ይከብዳል ። ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የጦር ሃይሎች  ኤታማዦር ሹሙን  በጠባቂው ማስገደል  ብቻ በቂ ነው ብሎ አመነና አደረገው የሚል ሲጨመርበት የፖለቲካ ተውኔቱን በእጅጉ አሳፋሪ ያደርገዋል ።

በሚገርም ሁኔታ አንዳንድ የውጭ አገር መሪዎችና ዲፕሎማቶችም በአጠቃላይ  ድርጊቱን ከማውገዝና ዝርዝሩን ለእኛ ለአገር ባለቤቶቹ ከመተው አልፈው  መፈንቅለ መንግሥቱ የተሞከረው የለውጥ ሂደቱን ማወክ ወይም መቀልበስ በሚፈልጉ ሃይሎች ነው የሚለውን ከእኛ በላይ የሚያውቁ በሚያስመሰል አኳኋን አስተጋብተውታል ።ይህም የእኛዎቹ ፖለቲከኞች “የተሳካ” ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ውጤት  መሆኑ ነው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቡነ ኤርምያስ ሆይ፣ ቤተክሲያን በክብር የደፋችልወትን ቆብ በክብር ያውልቁ! 

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በመግደልና በመገዳደል የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የኖሩት የኢህአዴግ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚና በአፅንኦት እንዲህ አይነት   አስከፊና አሳፋሪ ክስተት ገጥሞን አያውቅም ይላሉ ።

 “ባለሥልጣናት  እርስ በርሳቸው  በዚህ ሁኔታ ሲገዳደሉ  አጋጥሞን አያውቅም” ለማለት ከሆነ ትክክል ይሆናል ። ሚሊዮኖች የቁም ሰቆቃ ፣ እጅግ ብዙ ሽዎች ለግድያ  እና አያሌ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ለአካለ ስንኩልነት ሲዳረጉ የኖሩበትን የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ኢህአዴጋዊ የመከራና የውርደት ሥርዓትን ከዚህኛው ለማነፃፀር ከሆነ ግን ትክክል አይሆንም።  በሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎች ቃል የማይገልፀው አሟሟትና የቁም ሥቃይ መሳለቅ ነው የሚሆነው ።

በወቅቱ ቅን የሆነና ተገቢውን መፍትሄ የሚያስገኝ ጣልቃ ገብነት ያልነበረ በመሆኑ በመሠረታዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት የሌላቸው ነገር ግን በአካሄድ (ትእግሥት ያስፈልገናል እና ትግሥት ልኩን አለፈ) በሚሉ የአዴፓ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው ስንጥቅ የዚያን ክልል ተፅዕኖ ለማዳከም ከመጋረጃው በስተጀርባ የሴራውን ተውኔት ሲያዘጋጁ  ለነበሩ አካላት በር ከፍቶላቸዋል ።  የማእከላዊውን ሥልጣን በተቆጣጠሩት ኦዴፓ/ኦነግ እና እንዲሁም አኩርፎ መቀሌ ላይ ያዙኝና ልቀቁኝ በሚለው ህወሃት አራጋቢነት  የተፈፀመውን አስከፊ ክስተት ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ የሚሊዮኖች ሰቆቃ በላይ ማመን የሚያስቸግር አድርጎ በማሳየት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሞከር አይጠቅምም።

“አይተነው የማናውቅ ኢሰብአዊ ተግባር ነው” እያሉ ለዚሁ መከረኛ ህዝብ ሌት ተቀን የመርዶ ወሬ መደጋገም  ብዙም እርቀት አይወስድም ። አዎ ! ድርጊቱ ኢሰባዊና የሚወገዝ ነው ። “አይተነው የማናውቅ ኢሰባዊነት” የሚለው ትርክት ግን በህወሃት አሽከርነት ከመጣችሁበት የሩብ መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ መጠን የለሽ  አስከፊ  የመከራና የሰቆቃ እውነትነት አንፃር ሲፈተሽ እውነትነት የለውም ። ይህ የሰሞኑ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ያን የመከራና የውርደት ታሪካችሁንና አሁንም ከዚያው አዙሪት አለመወጣታችሁን በግልፅ የሚያሳይ  ነውና የሚሻለው  የሴራና  የቅሌት  ፖለቲካውን   እንደምንም ተቆጣጥሮ ለሁሉም የሚበጀውን ሆኖና አድርጎ መገኘት ብቻ ነው ። ይህ ደግሞ ከአፈጣጠሩ፣ ከእድገቱና ከተግባራዊ ማንነቱ የተበከለውን የኢህአዴጋዊ ሥርዓት መጠገን ሳይሆን ማስወገድን የግድ ይላል ። ኢህአዴግ ከነ መሠረታዊ መደላድሎቹ እንደ ሥርዓት እስከቀጠለ ድረስ እውነተኛ ሰላምና እድገት እውን ይሆናል ማለት ቀቢፀ ተስፈኝነት ነው ።የሰሞኑ መገዳደል የሚያስጠነቅቀንም ይህንኑ መሪር እወነታ ነው ።

እናም ነገር የተበላሸው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተጠናውቶን የኖረውን የፖለቲካ ካንሰር (ሥርዓተ ኢህአዴግ)  መሠረታዊ ፣ አስተማማኛና ዘላቂ በሆነ አግባብ  አስወግደን ጤናማ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እናደርጋለን  እያልን አጥብቀን የሰበክንለትን ዓላማ እርግፍ አድርገን ትተን ከሞት አፋፍ ተመልሶና ህወሃትን በኦህዴድ/ኦዴፓ የበላይነት ተክቶ  በተሃድሶ ስም የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ መጫወት ከጀመረው ኢህአዴግ ሥር ስንደፋደፍና ምን  እንታዘዝ ስንል ነው ።

ለዚህ የወረደ የፖለቲካ ሰብእና ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ለሆነ የኢትዮጵያዊነት (የዜግነት) ፖለቲካ ሥርዓት እውን መሆን ነፍሳችን (ህይወታችን) እንሰጣለን እያሉ ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ የተቀዋሚ ጎራ ፖለቲከኞች  የተለጣፊነትና የተሃድሶ ፍርፋሪ ምፅዋዕተኝነት ሰላባ  መሆን ትልቁን ድርሻ ይይዛል ።

እርግጥ ነው ኤርትራ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች (ቡድኖች) የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች ከኤርትራው ፕረዝደንት አቶ ኢሳኢያስ ጋር በፈጠሩት ቅፅበታዊ ፣ እጅግ  ስሜታዊነትና ውል አልባ ወዳጅነት ምክንያት ሁለት ምርጫ ነበራቸው ። ወይ ከፖለቲካው ጨዋታ ውጭ መሆን ወይም “ግቡና እኔ ላሸጋግራችሁ” የሚለውን ጥሪ ተቀብሎ መግባት ። ሁለተኛውን መርጠው ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ለማጣጣል መሞከር ትክክል አይሆንም ። ከገቡ በኋላ እጅግ ከተወሳሰበውና በሸፍጥ ከተለወሰው የኢህአዴግ የተሃድሶ (reform) ትርክትና አካሄድ ጋር የተጣበቁበት ሁኔታ ግን ለዓመታት ያገኙትን አንፃራዊ የፖለቲካ ቁመና በእጅጉ አኮስምኖታል ።

አስከፊ ሁኔታዎች  የዘወትር ዜና በሆኑባት አገር ውስጥ ብንናገር ነገር ማባባስና የለውጡን ሂደት ማደናቀፍ ስለሚሆን ማመልከቻ ቢጤ አዘጋጅተን ሰጥተናል  ወይም በውስጥ የግንኙነት መስመር አሳስበናል የሚል የተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ስብስብ ኢህዴግን በእንዴት አይነት ምርጫ አሸንፎ  እውነተኛ (መሠረታዊ) ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሊያደርግ እንደሚችል ለመረዳት ይቸግራል።

የዜግነት (የኢትዮጵያዊነት ) ፖለቲካ በእንዲህ አይነት እጅግ የተልፈሰፈሰና የተንሸዋረረ አስተሳሰብና አካሄድ እንዴት እውን ሊሆን ይቸላል የተልፈፈሰውና ወደ ተለጣፊነት ጠቅልሎ የገባው ተቀዋሚ ፖለቲከኛ  ዛሬ እያየነው ላለነው እጅግ አስከፊና አዋራጅ የመግደልና የማገዳደል ፖለቲካ የህግ ሳይሆን የፖለቲካና የሞራል ውድቀት ተጠያቂነት አለበት። ምክንያቱም ህዝብ በሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ሲከፋው አማራጭ አጥቶ መከራውን ሲቆጥር ከማየት የባሰ የፖለቲካ ውድቀት የለምና ።

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እኩያን ፖለቲከኞች በሰፊው በዘሩት፣ ተንከባክበው ባሳደጉትና በህገ መንግሥት ደረጃ  ደንግገው ሥራ ላይ ባዋሉት እጅግ አስከፊ የፖለቲካ አስተሳሰብና አጀንዳ ምክንያት ልጆቿ ገዳይነትንና  ሟችነትን በእራሳቸው መካከል እያፈራረቁ የቀጠሉባት የእናት አገር ኢትዮጵያ የደም እንባ ማቆሚያ ማጣቱ የሚያስከትለውን ህመም ለመግለፅ የሚያችሉ ቃላት የምናገኝ አይመስለኝም ።

አዎ!ለልጆቿ የሚሆነውን ነገር ሁሉ በእናትነት ጓደዋ ውስጥ ያላጣች እናት በተወሰኑ የእኩይ ፖለቲካ ልክፍተኛ ልጆቿ ( ኢህአዴጋውያንና ሰፊ ጎደዋን አፈራርሰን እንከፋፈል ባዮች) ምክንያት ለገዳይና ለተገዳይ ልጆቿ የደም እንባ የምታነባ እናት አኳኋን እንዴት ልብ አያደማ ? እንዴትስ አእምሮን አያናውጥ ?

ፖለቲከኞቻችን የመከራውና የውርደቱ  ምንጭ ወይም ምክንያት በዋናነት ከእነሱ የሚነሳ መሆኑን እያወቁ ከመፍትሄው እርምጃ እራሳቸውን በማሸሽ ባስከተሉት የፖለቲካ እብደት  የአንድ አገር ልጆች ገዳይና ሟች ሆነው እናት አገር የደም እንባ ስታነባ አብረው የአዞ እንባ እያነቡ  የመቀጠላቸው እጅግ አስከፊ የፖለቲካ ታሪካችን ብዙም ያስተማረን አይመስለኝም።

አንድ መሪር ሃቅን ግን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም ። አዎ! ሁሉም  ሟቾችና ተጎጅዎች ወይም በዚህ አስከፊ   ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎች  በእጅጉ የተበከለ ወይም የተመረዘ  ወይም ወደ ካንሰርነት የተለወጠ  የፖለቲካ ሥርዓት ሰለባዎች መሆናቸውን ማስተባበል  ከቶ አይቻልም  ።

የዚህ የተበከለ/የተመረዘ የፖለቲካ ሥርዓት ምንጩና እድገቱ ደግሞ በዋናነት ሌላ ሳይሆን የበላይ አለቆቹን እየቀያየረ (ህወሃት/ኢህአዴግን በኦዴፓ/ኢህአዴግ) ታድሻለሁ የሚለው ኢህአዴግ ነው ። እናም ዘላቂና አስተማማኝ  መፍትሄ የሚገኘው ይህን መሪር ሃቅ በዴሞክራሲያዊ  አርበኝነት ተቀብሎ በተሃድሶ (reform) ስም  እየማለና እየተገዘተ  የባሰ አዘቅት ውስጥ የሚዘፈቀውን ሥርዓተ ኢህአዴግ  ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ መስመር ማስገባት ሲቻል ብቻ ነው ።

ብዙን ጊዜ ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብ መንቃት ፣ መነጋገር ፣ መደማመጥ ፣ መተባበር፣ መደራጀት፣ አበሮነት፣ መከከባበር ፣ የህግ የበላይነት መከበር፣ የመንግሥት ሃላፊነቱን መወጣት ፣ የህዝብ ተሳትፎ ፣ ጠንካራ ተቀዋሚ ድርጅት ፣ ወዘተ ነው የምንለው ። አዎ! እነዚህንና መሰል ፅንሰ ሃሳቦችን በደምሳሳው ያስፈልጋሉ ማለት ብቻ ሳይሆን ወደ መሬት ሊወርድ በሚችል አኳኋን መግለፅና መተንተን አስፈላጊ ነው ። ከዚህ በላይ ግን ወሳኙ ወደ ተግባር የመተርጎሙ ጉዳይ ነው ። ለዚህ ደግሞ  የገዥዎችን በጎ ችሮታ እየተለማመጥኩ ወይም የመብት  መጨፍለቂያ መሳሪያቸውን ሃይልነት እየፈራሁ  ያለ ነፃነትና ያለ ክብር ለመኖር ፈፅሞ አልፈቅድም” የሚል ከእያንዳንዱ ግለሰብ ውስጠ ህሊና ሳያቋርጥ የሚመነጭ ቁርጠኝነት የግድ ነው። እያንዳንዱ የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚ የወገኑ መከራና ውርደት ተሸካሚነት እስአላከተመ ድረስ እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ጨርሶ የሚታሰብ አለመሆኑን ለእየራሱ አእምሮ  መንገርና ማሳመን ይኖርበታል ። ይህ ጥልቅ እራስን የመመርመርና በእውን ሰው ሆኖ የመገኘት ቁርጠኝነት ብቻ ነው እውነተኛ የነፃነት ቀን እንዲቀርብ የሚያደርገው ። እኛም ለዘመናት ከኖርንበት (መኖር ከተባለ) የመከራና የውርደት ፖለቲካ አዙሪት መውጣት ያቃተን ይኸው ውስጣዊ እሴት ስለጎደለን  ነውና የጎደለውን ለማሟላት በቁጭት እንነሳ ። ያለዚያ የመከራውና የውርደቱ ፖለቲካችን ማቆሚያ አይኖረውም ።

Previous Story

ገዳይ ደስ አይበልህ፤ ሟችም ብዙ አይክፋህ – ግርማ በላይ

Next Story

ወንጀል እና ህግ ፣ እውነት እና ውሸት በብሄረሰቦች ነፃነት ዘመን (ታሪኩ አባዳማ)

Latest from ነፃ አስተያየቶች

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት

የፋኖ አደረጃጀቶች አንጻራዊ ወሳኝነትና የእስክንድር ነጋ ወሳኝ ሚና

ጭራቅ አሕመድ ያማራን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ የተነሳው  በእስክንድር ነጋ ላይ ግልጽ ጦርነት እከፍታለሁ ብሎ በመዛት ስለነበር፣ ያ ማራ ሕዝብ ደግሞ ጭራቅ አሕመድን  ጨርቅ በማድረግ ቅኔያዊ ፍትሕ  (poetic justice) ሊሰጠው የሚገባው  በእስክንድር ነጋ መሪነት ነው።    ________________________________________ ያማራ ፋኖ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የቤታማራና የሸዋ

Share