የዝንጀሮ ቆንጆ! (በላይነህ አባተ)

ጊዜው ተገልብጦ ታቹ ላይ ሆነና፣
መልከ-መልካም ጀግና ቆንጆ ሴት ተወና፣
ተዝንጀሮ መራጪ ሆነ ሰው ተላላ፡፡

ተመቀመጫው ላይ ጠባሳ ተሌለው፣
የዝንጀሮ ቆንጆ እንዴት ይመርጣል ሰው?

የዝንጀሮ ታሪክ አመልም ተሌለው፣
እንዴት በግመር ፍቅር ከንፎ ይሄዳል ሰው?

ተዝንጀሮ መንጋ ቆንጆ ሲፈልጉ፣
ብዙ ጂላጅሎች ወደ ገደል ገቡ፡፡

ዝንጀሮ መረጣ ሲወጡ ሲወርዱ፣
የካቡትን ሁሉ እንደ ገደል ናዱ፡፡

ያልታደለ ገላ ያልተባረከ ነፍስ፣
በዝንጀሮ ቆንጆ ተለክፎ እንደ አንከሊስ፣
እንደ በላዬ ዘር እርስ በርስ መናከስ፡፡

ተሰው ልጅነቱ ታልወጣ በእርግማን፣
በዝንጀሮ ቆንጆ እንዴት ሰው ይጣላል?

በዝንጀሮ ቆንጆ ምርጫ ሲታገሉ፣
ባውሬ እየታደኑ ታንቀው ይበላሉ!

ያያቶችን ብሂል ቀጥ ብለህ ተከተል፣
ተዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል፡፡

ገደል ተንጠልጥለህ ዝንጀሮ መረጣ፣
በድድ ተመናከስ እንደ ጅል ባላንጣ፣
እንደ አንበሳ ነብር ግባ ወደ ጫካ፡፡

ባራት እግር ቆመህ እንደ ከብት እንሰሳ፣
ተዝንጀሮ ቆንጆ መምረጡን ተውና፣
ቀጥ ብለህ የምትሄድ ሰው ሁን እንደገና!

በላይነህ አባተ ([email protected])
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.