ትልቁ ችግር ያለው ከውድቀት ከአለመማር እንጅ ከመውደቁ ላይ አይደለም ! – ጠገናው ጎሹ

June 9, 2019
ጠገናው ጎሹ

  1. እንደ መግቢያ

አርቲስት/አክቲቪስት ታማኝ በየነ “በትግል ሂደት ወቅት መውደቅና መነሳት ያለ ነው። አሁንም ብንወድቅም አቧራችን አራግፈን መነሳታችን አይቀርም”  የሚለውን አጠቃላይ እውነት (general truth) እና አጠቃላይ  መርህ ( general principle) ሰሞኑን ኢሳት ውስጥ (በተለይ የዋሽንግተን ዲ.ሲው) የተከሰተውን እጅግ አስቀያሚና ልብ ሰባሪ ክስተት አስመልክቶ ባስተላለፈው መልክት በአፅንኦት ተናግሮታል ። የችግሩን  ምክንያት ሲገልፅ ደግሞ  ኢሳት “የበጀት እጥረት” ከአጋጠመው ቆየት ያለ  መሆኑንና “ከለውጥ” ወዲህ ደግሞ እየባሰ መምጣቱን ለማሳየት ሞክሯላ ። በመጨረሻም   የተከሰተውን ችግር ከአገር ቤት ሲመለስ በጥሞና ለመወያየትና ተገቢውን ለማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እስኪፈጠር  ድረስ ሁሉም ወገን ችግሩን ከሚያባብስ ሁኔታ ተቆጥቦ እንዲጠብቀው  ተማፅኗል።   ይህ መልእክት በአጠቃላይ እውነትነትና  መርህ ደረጃ  ሲታይ  ትክክል  ወይም ተገቢ ነው።

በሌላ በኩል ግን  ለምንና እንዴት? ለነማን ሲባል እና በነማንስ ነው እንዲህ አይነት የኢሳትን አንፃራዊ ሚዛናዊነት ፣ ነፃነትና ተአማኒነት የማጎሳቆል ጨዋታ መጫወት የተፈለገው?  የሚሉ ጥያቄዎችን  ማንሳት  በጣም ትክክልና ተገቢ ነው።  እንዲህ አይነት ጥያቄዎች በተነሱና ግልፅና ቀጥተኛ ሂሳዊ አስተያየቶች በተሰነዘሩ  ቁጥር ግልፅነትና ገንቢነት ባለው አኳኋን በማስተናገድ  ተገቢውን ከማድረግ ይልቅ “የልዩነት አራጋቢዎችና የግጭት ፈጣሪዎች ጫጫታ ነው” የሚለው እጅግ ጋግርታም አስተሳሰብ ወደ ክፉው አዙሪት ይዘፍቀናል እንጅ በአሸናፊነት እንድንወጣ ጨርሶ አይረዳንም (አያግዘንም) ።

የምንነጋገረው ስለ ገሃዱ ዓለም ፖለቲካ ከሆነ እንኳን ለእንደኛ አይነት ካለበት ዘመን ሁለንተናዊ የሥልጣኔ ግሥጋሴ ጋር በአካል (existence) እንጅ በፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እጅግ ወደ ኋላ ለቀረ  ማህበረሰብ  በአንፃራዊነት ጉልህ ሥልጣኔና ግልፅነት የሚታይበት ማህበረሰብ ውስጥም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አፍራሽ የሆኑ አስተሳሰቦችና ወሬዎች   ይኖራሉ ። ማድረግ የሚቻለው በተቻለ መጠን ተቀባይነታቸውን ፉርሽ የሚያደርግ እውነተኛ መረጃን ለህዝብ በወቅቱና በብቃት ማድረስ እና የማህበረሰብን (የአገርን) ደህንነት ቀይ መስመር የሚያልፉትን ደግሞ በተጨበጠ፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት ባለው አግባብ ተጠያቂ ማድረግ ነው።

ፖለቲከኞቻችን ከራሳቸው ልክ የሌለው ውድቀት የተነሳ የሚከሰተውን (የሚፈጠረውን) እጅግ አስከፊ ኩነት ሁሉ ከእነሱ ውጭ ባለውና  ለሥልጣናችን ያሰጋናል በሚሉት ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ እያመካኙ (እየዘፈዘፉ) የዘመናዊ  ፖለቲካ እውቀትና ባህል ማይም (illiterate) የሆነውን መከረኛ ህዝብ ግራ እያጋቡ “ከእናንተ በስተቀር መዳኛ የለኝም” ብሎ እንዲያምን የማይሞክሩት ሙከራ የለም ።

ከሰሞኑ የምንታዘበው የኢሳት ትርምስም ከእንዲህ አይነቱ እጅግ የዘቀጠ የፖለቲካ ጨዋታ ጨርሶ ነፃ አይደለም ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ከወደ አዲስ አበባ ያየነውና የሰማነው ጨርሶ ይሉኝታና የሂስ ሥነ ምግባር የጎደለው የፖለቲከኞች ትርክትም ለዚህ የዘቀጠ የፖለቲካ ጨዋታ ቀጥተኛ  ማሳያ ነው ። ( የአቶ ኤፍሬም ማዴቦን የተሌቪዥን መስኮት ቃለ ምልልስ ያስታውሷል) ።

አለመታደል ወይም እርግማን ሆኖብን ሳይሆን እንደመልካም ዜጋ የእየአንዳንዳችንን ውስጠ ህሊና (inner soul) ለእውነት እና ለጋራ ዓላማ (ግብ) እውን መሆን ተገዥ እንዲሆን ለማድረግ በሚያስችል አኳኋን ፍቃደኛና ዝግጁ ሆኖ እንዲገኝ ባለመስቻላችን “የህዝብ ዓይንና ጆሮ ነው ፤ ህዝብም የህልውናውና የስኬቱ ዋስትና ነው” የምንለው ኢሳት ለኢህአዴግ የተሃድሶ ፍርፋሪ እራሳቸውን አሳልፈው በሰጡ ፖለቲከኞች እና አድር ባይነት ወይም አጎብዳጅነት በተጠናወታቸው  አንዳንድ  ጋዜጠኞች ምክንያት አሁን እየታዘብን ካለነው አስቀያሚ የውድቀት ጠርዝ ላይ  ቢደረስ ከቶ የሚገርም አይሆንም ።

በዚህ አኳኋናችን የምንመኘውን (የምንፈልገውን) እና እንደዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው በነፃነትና በኩራት መኖር የሚያስችለንን እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት እውን ማድረግ ይቻለናል ? የሚለውን እጅግ ከባድ ግን መመለስ ያለበትን ጥያቄ በትክክል ለማስተናገድ በእጅጉ እንቸገራለን ። በቅንነት ለሚያስተውል የአገሬ ሰው አሁን የምንገኘው  በእንዲህ አይነት አስቸጋሪ የተቃርኖ (paradoxical) ሁኔታ ውስጥ ነው ። በአንድ በኩል የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ያስፈልጋል እያሉ የመጮህና  የማስጮህ ፣ በሌላ በኩል ግን እንደ ኢሳት የመሰሉና በአንፃራዊነት ህዝብን  በኢንፎርሜሽን ምንጭነትና የነፃ ሃሳብ ማንሸራሸሪያነት የሚያገለግሉ መገናኛ ብዙሃንን የሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ሰለባ የማድረግ ክፉ ተቃርኖ (paradox)  ውስጥ ነው የምንገኘው ።

የዚህ ክፉ አዙሪት ልክፍት ሰለባነት በዚህ  ብቻ የሚቆም አይደለም ። “ኢህአዴግን በተሃድሶ ከተዘፈቀበት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ነፃ አውጥቼ ተአምር ሰሪ አደርገዋለሁ” የሚል ቅዠት ውስጥ በሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቃላት (የሰበካ) ዲስኩር ምርኮኛ በመሆን  ለዘመናት የጮሁለትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና መሥረታ  ጩኸት  በዜሮ የማባዛት አባዜ  ሰለባ የሆኑ  አክቲቪስቶች ጉዳይም ከባድ ጥያቄ ቢያስነሳ ትክክልና ተገቢ አይደለም ብሎ ለመከራከር የሚያስችል የሞራልም ሆነ የፖለቲካ ብቃት የለም። ለዚህ እውነትነት የኢትዮጵያ ህዝብ ለአንድ ዓመት ከመጣበትና አሁንም እየኖረበት ካለው መሪር እውነታ በላይ የሚነግረን ሌላ አስረጅ ፍለጋ  እርቆ መሄድ አያስፈልገንም።

ወደ ኢሳት ልመለስና ከሥራ አሰናብተናል ባዮችን  ሃላፊነትና ተግባር ግልፅ ሳያደርግ በደፈናው “በበጀት እጥረት ምክንያት እነ እገሌን ከሥራ አሰናብቻለሁና ገናም አሰናብታለሁ” ከሚለው አካል (የግለሰቦች ስብስብ) የሰማነውና እየሰማን ያለነውም የዚሁ ክፉ የአስተሳሰብ አዙሪት ውላጅ ነው ።

ነፃና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን የአምባገነኖችን የከፋና የከረፋ የፖለቲካ ሥርዓት ለህዝብ በማጋለጥ፣ በማሳወቅና ግንዛቤ በማስረፅ እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ባለው አስተዋፅኦ  ምክንያት ከህግ አወጭው፣ ከሥራ (ህግ) አስፈፃሚው እና ከህግ ተርጓሚው  ቀጥሎ እንደ አራተኛ የመንግሥት አካል (branch of government) ተደርጎ ይታያል ። መንግሥት የተሰጠውን የህዝብ  ሥልጣንና ተግባር ተጠቅሞ  ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ አንዱን ሌላኛው የሚቆጣጠርበት  (check and balance) ሥርዓትን  ጤናማነት ወይም መታወክ  ለራሱ ለመንግሥት  በማሳወቅ ተገቢው የእርምት ወይም የማሻሻያ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ያስችላል።  ህዝብም ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኝና የቅርብ ክትትል እንዲያደርግ የማስቻሉ ሚና  የእውነተኛና የነፃ ሚዲያን የግድ አስፈላጊነት (indispensability ) ያረጋግጣል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጦርነት ጋንግስተሮች!!! ጦርነት ሲኦል ነው!!! የጦርነት ሚሊየነሮች ትርፍ!!! ሰንደቅ-ዓላማው ዶላሩን ይከተላል፣ እናም ወታደሮቹ ሰንድቅ ዓላማውን ይከተላሉ!!!

ይህ አይነቱ እጅግ ሰፊና ጥልቅ አመለካከትና ተግባራዊ እይታ የሚነግረን አንድ ትልቅ እውነት አለ። በቅንነትና በደፋርነት ለማዳመጥና ለመቀበል ፈቃደኞችና  ዝግጁዎች ከሆን ።   ስለ ኢሳት መጠናከር ወይም መዳከም ስንነጋገር ስለ የአገራችን ዴሞክራሲያዊነት እጣ ፈንታ እየተነጋገር መሆኑን ጨርሶ ልንዘነጋው አይገባም ።

ታዝበን እንደሆነ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በአፍላው የለውጥ አራማጆችን የማስመሰል ሆይ ሆይታ ተልእኮ ከተወጣ በኋላ ተመልሶ በኖረበት አዙሪት ውስጥ ገብቶል ። የዜና እውጃውና የዜና  ትርክቱ  በአብዛኛው   ከፍተኛ ፣ ድንቅ፣ ልዩ ፣ ታሪካዊ ፣ አስገራሚ ፣ አስደማሚ ፣ ትክክለኛ አቅጣጫ አስቀማጭ ፣ ንግግረ መልካም ፣ የልማት ኮከብ፣ የፕሮጀክት አፍላቂ ፣ ድንበር ተሻጋሪ ባለ ራዕይ ፣ የሃይማኖት መሪዎችን አስታራቂ ፣እንደ ክርስቶስ በተዘጋው በርም ቢሆን ዘልቆ ገብቶ መካሪ ፣  በየሃይማኖቱ አውድ ታዳሚ ፣ ከሰው ሳይሆን ከሰማይ ክብርና ሞገስ የተቀባ ፣ ወዘተ የሚል አይነት ክፉ አዙሪት ውስጥ ተመልሶ ተዘፍቋል ። ጋዜጠኛውም የእለት ዳቦውን የሚሰጠውን የመንግሥት ባለሥልጣን ስሜት እየለካ ስለሚናገርና ስለሚፅፍ የሙያውን ምንነትና እንዴትነት ከውስጠ ሰብእናው አውልቆ ጥሎታል ወይም ተሳስቶ እንኳ እውነት እንዳይናገር ወይም እንዳይፅፍ በአንደኛው የአእምሮው ጓዳ ቆልፎታል ።

እናም አገር  በዚህ አስቀያሚ  ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ነው አንጡራ የፖለቲካ ነፍሳቸውን ለኦዴፓ/ኢህአዴግ የተሃድሶ ፍርፋሪ አሳለፈው የሰጡ ፖለቲከኞችና የአድርባይነት (የአጎብዳጅነት) ክፉ ባህሪ የተጠናወታቸው ጋዜጠኛና አክቲቪስት ተብየወች ኢሳትን ከቤተመንሥት ፖለቲካ ጋር በቅርብ የሚወዳጅበትን ሁኔታ ማመቻቸታቸውን እየነገሩን ያሉት ። ከሁሉም የሚያመው ደግሞ የህዝብን የማወቅ ወይም የግንዛቤ ችሎታ የናቁበት ግብዝነታቸው ነው ። አዎ! “ለቤተ መንግሥት ፖለቲከኞችና  ” ለአዲሱ ኢሳት” መወዳጀት አይምቹም የምንላቸውን ባልደረቦች  ለማስወገድ የተጠቀምንበት ምክንያት  የበጀት እጥረት ነውና አትንጫጩ “  ለማለት ድፍረት ያገኙበት አካሄድ በእጅጉ ህሊናን ያቆስላል ።

  1. 2. በምክንያትነት እየተነገረ ያለውየበጀት እጥረትን” ጉዳይ በተመለከተ ግልፅና ቀጥተኛ ጥያቄ መጠየቅ የትክክለኛ መፍትሄ ፍለጋ አካል ነውና ለማሳያነት ያህል አስተያየቴን ከጥያቄ ጋር እያያዝኩ ልግለፅ፦
  • በእውነት ከተነጋገርን በታማኝ የተማፅዕኖ መልእክትና በሌሎችም የሠራተኛ ስንብት ብይን ሰጭ  የኢሳት ባልደረቦች የሚቀርበው ምክንያት ቀደም ብለን ከሰማነውና ከታዘብነው ኢሳትን የለውጥ አራማጅ ለምንላቸው ፖለቲከኞች በገፀ በረከትነት የማቅረብ አስቀያሚ እውነታ ጋር እንዴት ይጣጣማል?

የኢሳት ሚዛናዊነትና ገለልተኝነት ፈተና ላይ እንደሚወድቅ ምልክት በግልፅ ማየትና መስማት የጀመርነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተቀዋሚ ነኝ የሚለውን ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነኝ  የሚለውን ሁሉ ወደ አምልኮ በተጠጋ አድናቆት ባስረገደው  (እጥፍና ዘርጋ ባስደረገው)  የአሜሪካ ጉብኝቱ ወቅትና ወደ አገርቤትም ከተመለሰ በኋላ ኢሳትን ኢሳት ካደረጉት ባለደረቦች ለይቶ  ግለሰቦችን በስም እየጠራ   ያሞካሸ (እርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ የተጫወተ) እለት ጀምሮ  እኮ ነው ።   ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም ጠቅሶ ካሞገሳቸው የኢሳት ባልደረቦችና ምናልባትም ወደፊት ለዚህ ሙገሳ በእጩነት ሊይዛቸው ከሚችሉ ተጨማሪ ባልደረቦች ውጭ ያሉና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ባልደረቦች  እንደ ባለሙያም ይሁን እንደ ኢትዮጵያዊ ፅዕኑ የሆነ  እውነትን የማሳወቅ መርህና የተግባር አቋም ያላቸው  መሆኑን ከራሱ የፖለቲካ ሰብዕና አንፃር በሚገባ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም።

ለዚህ ነው በየመድረኩና በየአጋጣሚው ስለሚዲያ በሚያደርገው ዲስኩር ውስጥ  ስም በቀጥታ ባይጠቅስም ተአምራዊውን የለውጥ ወይም የሽግግር ሥራየን የሚያደናቅፉ የሚል ማስፈራሪያ አዘል መልእክት ለማስተላለፍ የሞከረውና አሁንም የሚሞክረው። በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደግሞ ጀዋር መሃመድን የመሰሉ አክራሪ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ነጋዴዎች የሚቆጣጠሩት ሚዲያ እዚያው ቤተመንግሥቱ አጠገብ መርዙን ሲረጭ ለምን? ብሎ ሳይጠይቅ የአገርና የወገን ጉዳይ ያሳስበናል በሚሉ  ቅንና ጠንካራ የኢሳት ባልደረቦች ላይ ማነጣጠሩ ነው ።

በሚመራው ገዥ ቡድንና መንግሥት የተግባር ውድቀት ምክንያት በርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ ፣ እጅግ ብዙዎቹ ለአካል ለአእምሮ ጉዳት ሲዳረጉና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ  በገንዛ ሃገራቸው የደሃ ጎጇቸው ከያዘችው ቁሳቁስ ጋር በዶዘር ተደምስሳ ሜዳ ላይ ሲወደቁ እግዚኦ ብለው የጮሁትንና እውነቱን ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም ያሳወቁትን ድንቅ የኢሳት ባልደረቦችን ለምን ተናገራችሁብኝ በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ የሚል የአገር መሪ/ጠቅላይ ሚኒስትር ከእርሱ ጋር ትሽሽት የጀመሩትን ተቀዋሚ ተብየ ፖለቲከኞች ተጠቅሞ (proxy) ኢሳትን ተጨማሪ የመንግሥት ልሳን ለማድረግ የሚደረገው ክፉ ዘመቻ ግቡን እንዲመታ ይፈልግም ብሎ መከራከር  የለየለት ፖለቲካ እምቦቃቅላነት (naivety) ነው።(የጌዴዎንና ጉጅን ጉዳይ ልብ ይሏል)

  • አዎ ! በእውነት ስለእውነት ከተነጋገር አንዳንድ ጋዜጠኞች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የተለየ እውቅና ከማግኘታቸውም  በፊት የህወሃት የበላይነት መወገድንና አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎችን ለለውጥ ሂደት መሳካት  እገዛ የሚያደርጉ ሳይሆን እንደ ግብ የማስተጋባት አቀራረብ (አስተሳሰብ) ይታይባቸው እንደነበር ግልፅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ልብ ብሎ ስለተገነዘበላቸው ነው ኢሳት ውስጥ ሌላ ጋዜጠኛ እንደሌለ በሚመስል ሁኔታ በስም እየጠራ ያሞካሻቸው ። ከዚያ በኋላ ነው እነዚህ ጋዜጠኞች  አንድና ሁለት እያልን በለውጥ አራማጅነት በምንጠራቸው ፖለቲከኞች የለየለት ድክመት (ውድቀት) ምክንያት ህግና ፍትህ የባለጌ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች መጫወቻ ሲሆንና ህዝብም በአስከፊ ሰቆቃ ውስጥ ሲወድቅ እያዩና እየሰሙ  ሰንካላ ምክንያት በመደርደር  እነዚህኑ ፖለቲከኞች ሸንጣቸውን ገትረው  ወደ መከላከሉ ጠቅልለው የገቡት ። ህግ ሲጣስ ፣ ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሥ ፣ በሽዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በግፍ ሲገደሉና ለአካል ጉዳተኝነት ሲዳረጉ ፣ የፖለቲካ ትግልን አሻፈረኝ ያሉ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ነጋዴዎች ከግለሰብ እስከ ባንክ ዘረፋ ሲሰማሩ ፣ ወዘተ መንግሥት የለም ወይ? ሲባል “አይ የባሰ ቀውጢ እንዳይፈጠር መታገሥ ስላለባቸው ነው” የሚል እጅግ የዘቀጠ መከራከሪያ  ያቀርቡ የነበሩና ዛሬም ከዚያው ክፉ ልክፍት ማገገም የተሳናቸው ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ናቸው ኢሳትን ሌላው “የለውጥ አራማጅ” ፖለቲከኞች የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሊያደርጉት የሚቃጣቸው ። ይህ አስተያየቴ እንኳን ለተተችዎች ለአንዳንድ የዋህ ወገኖችም አልመች እንደሚላቸው እረዳለሁ ። መሪር ቢሆንም ሃቅ ነውና ሌላ የተሻለ አገላለፅ የለኝም።
  • እውን በኢሳት ዳይሬክተርነት እያገለገለ ያለው አርቲስት/አክቲቪስት ታማኝ በየነ ሳያውቀው ነው እንዴ ይኸ በሸፍጥ የተለወሰ (የተቦካ) እርምጃ የተወሰደውና እየተወሰደ ያለው ? ይህ ሆኖ ከሆነ በተወሰኑ ግለሰቦች (ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች) የሚካሄደውን የሸፍጥ ጡዘት ያሳያል። ካልሆነ ግን የአክቲቪስት ታማኝ ተማፅዕኖ ግልፅነትና ተአማኒነት የጎደለው  ይሆናል ማለት ነው። ቢያንስ ግን ችግሩ እዚህ እስከ ሚደርስ ድረስ ከህዝብና በተለይም ከደጋፊ ህዝብ ከመደበቅ ወይም ሲደብቁ ዝም ብሎ ከማየት የሃላፊነት ጉድለት መሸሽ የሚቻል አይመስለኝም ። የምንነጋገረው ስለእውነተኛ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ከሆን ።  ለዚህ ነው የተማፅዕኖው ክብደት ሚዛን ለማንሳት አቅም የሚያጥረው እና ተቀባይነትም ይኑረው ወይም አይኑረው በችግሩ ዙሪያ የሚወራውን (የሚባለውን) በደፈናው “ከንቱ ጫጫታ ስለሆነ  የትም አይደርስም” የሚለው ብዙም የማያስኬድ የሚሆነው ።
  • ለሚከሰቱ (ለሚፈጠሩ) ፈታኝ ሁኔታዎች ከህዝብ ጋር በግልፅነትና በቀጥተኛነት ተመካክሮ ገንቢ የሆነ የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ለምንድን ነው ነገሮችን እንደምንም አሾልከን ለማሳለፍ በምናደርገው  ሙከራ ሂደት ችግር (ተቃውሞ) ሲገጥመን ልፍስፍስ (ሽባ) ምክንያት እየደረደርን ህዝብን  በእመነኝና አትመነኝ  ተማፅዕኖ የምናስቸግረው ወይም ግራ የምናጋባው?
ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሁለቱ ታላላቅ ዕቅዶች” ክፍል 3 (ዮፍታሔ)

 

  • ምክንያቱ በእውን የበጀት እጥረት ከሆነና በዚህም ምክንያት ኢሳትን ኢሳት ለማድረግ የበኩላቸውን  ጉልህ አስተዋፅኦ  ያደረጉትንና ወደፊትም የበለጠ እንዲሆን የሚያደርጉትን ባልደረቦች እስከማሰናበት  የሚያደርስ ስለመሆኑ  የኢሳት የጀርባ አጥንት ነው  ለምንለው ማህበረሰብ (ህዝብ) በወቅቱና ግልፅነትን በተላበሰ አኳኋን  ለመግለፅ ለምንና እንዴት  አልተቻለም ወይም አልተፈለገም ?
  • ቅንና ጠንካራ የኢሳት ባልደረቦችን ከሥራ ለማሰናበት ምክንያት ነው የተባለው የበጀት ጉዳይ  እውነት ከሆነ ለምን የፋይናንስ አያያዝንና  አጠቃቀምን ሁኔታ በሂሳብ ሰሌዳ ግልፅና ግልፅ በማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ደጋፊ ኢትዮጵያውያን የሚችሉትን እንዲያደርጉ አልተደረገም?   ግልፅነትንና ተአማኒነትን በተላበሰ አኳኋን የድጋፍ  የጀርባ አጥንት ነው  ለምንለው ህዝብ ግልፅ ቢሆን ኖሮ ለእነዚህ “ተሰናባች” ቅንና ጠንካራ የኢሳት ባልደረቦች  ሲሆን በዘላቂነት ካልሆነ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ክፍያ (ደመወዝ) መክፈል አይችልም ነበር እንዴ? ቅንነትና ግልፅነት ቢኖር ኖሮ ወይም ምክንያቱ ከሸፍጠኝነት የሚነሳ ባይሆን ኖሮ ይህ ይቻል እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ህወሃት/ኢህአዴግ  በሚሊኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከመከረኛው ህዝብ አፍ እየነጠቀ ኢሳትን  በተደጋጋሚ ከአየር ላይ ሲያወርደው ተመልሶ እንዲነሳ በማድረግ  እዚህ እንዲደርስ ያደረገ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ  ህዝብ (ኢትዮጵያዊ) ቅንና ጠንካራ  ባልደረቦች በክፍያ እጥረት ምክንያት ከሥራ ውጭ ሊሆኑ ነው ሲባል እንዴት ዝም ይላል ተብሎ ይታሰባል? እናም ጉዳዩ የበጀት ሳይሆን የለየለት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ የንግድ ሸፍጥ ነው ። አዎ! ታዲያ ዛሬ ኢሳትን ኢሳት እንዲሆን የበኩላቸውን ያልተቆጠበ ጥረት የሚያደርጉትን ባልደረቦች ከሥራ ማሰናበትን ጨምሮ የኢሳትን እጣ ፈንታ እንወስናለን የሚሉትን ሰዎች ከፖለቲካ ሸፍጠኝነትና ልክ ከሌለው የግል ወይም የቡድን ፍላጎት አራማጅነት ውጭ በሌላ የተሻለ አገላለፅ መግለፅ የሚቻል አይመስለኝም ።

 

  1. ወድቆ መነሳት እንዴት?

 

  • “ውድቀት የስኬት ወላጅ ናት (failure is the mother of success)” የሚለው አጠቃላይ እውነት (general truth) የሰው ልጅ እንደሰው መኖር ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ የኖረና ወደፊትም የሰው ልጅ እንደሰው  መኖር እስከ ቀጠለ ድረስ ጊዜ የማይሽረው ሆኖ ይቀጥላል ። ይህ ሲባል ግን ስኬታማነት የግድ ከውድቀት ይገኛል ወይም ስኬታማ መሆን ውደቅትን ግድ ይላል ማለት እንዳልሆነ ከምር ልብ ማለት ያሻል ። ልክ በሌለው የእራስ የአስተሳሰብ ድንቁርና እና የተግባር ስንኩልነት መላልሶ እየወደቁ “ውድቀት የስኬት መንገድን ይወልዳልና እየወደቅን አቧራ ልሰንና አራግፈን እንነሳለን” የሚለውም እንዲሁ ከምር   ልብ ማለትን ይጠይቃል። ለስሜታችን የሚመቸውን የተስፋ ወይም የይሆናል ቃለ አፅንኦት በደምሳሳውና በተለምዶ የንግግራችን ማጣቀሻና ማድመቂያ ከማድረግ አልፈን ካልሄድን በስተቀር መላልሶ ከመውደቅ ክፉ አዙሪት ለመውጣት የሚቻለን አይሆንም ። ለዚህ ነው አጠቃላይ የሆነውን እውነት ወደ እራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ አውርደን ወደ ተግባር የሚተረጎም እውነታ ካላደረግነው በስተቀር ከባዶ አፅንኦተ ቃልነት አያልፍምና ልብ እያልን እንራመድ ማለት ትክክል የሚሆነው።
  • ለነገሩ ስለ ራሳችን በእውነትና  በግልፅነት ከተነጋገር በመጀመሪያው አብዮት (1960/70ዎቹ) ያጋጠመንን እጅግ መሪር ተሞክሮ በትምህርት ሰጭነቱ ተጠቅመን ከወደቅንበት በቅጡ (ትርጉም ባለው አኳኋን) አቧራችን አራግፈን ለመነሳት ባለመቻላችን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን እርስ በርስ የሚያናቁርና የሚያናክስ መርዙ በቀላሉ ሊወገድ በማይችል  የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ የፖለቲካ ማንነት ሥርዓት ሥር ቆይተናል ። አሁንም በእጅጉ የጎደለንን የቤት ሥራ በአግባቡና በወቅቱ ለመሥራት ባለመቻላችን ለመነሳት ያኮበኮበው እኛነታችን መሬት ላይ ከመንፏቀቅ አላለፈም ። ይህ ደግሞ ለዘመናት ስለ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ስንጮህ ብንኖርም ለዚህ የሚያበቃ አማራጭ ሃይል ለማዘጋጀት ባለመቻላችን ጠንቀኛ መርዙን ሳያራግፍ በተሃድሶ ስም የመሪነቱን ሥልጣን ይዞ የቀጠለው ሥርዓተ ኢህአዴግ ሰለባ ከመሆን የሚመነጭ (የመነጨ) ነው። ታዲያ ለማስመሰል ትንሳኤ ሳይሆን ለእውነተኛ  ትንሳኤ የሚያበቃ የፖለቲካ ምንነትና ማንነት ባልፈጠርንበት ሁኔታ  “አቧራችን አራግፈን እንነሳለን!” የሚለው እንዴት ሆኖ ነው አሁን ከምንገኝበት የእኛነት እውነታ ጋር የሚገጥመው?  ኢሳትን አሁን እየገጠመው ያለው ፈተናስ ከዚህ ክፉ አዙሪት ተነጥሎ ለብቻው የተንጠለጠለ ነው ወይ? እናም በመሬት ላይ ካለው መሪር እውነታ ጋር ያልተናበበ የሞራል ፉከራ ወንዝ የሚያሻግር አይሆንምና ልብ ማለት ጥሩ ነው ።
  • በራሳችን የለየለት የሸፍጥና ቅንነት የጎደለው ባህሪና ድርጊት ምክንያት መላልሰን እየወደቅን ብንወድቅም አቧራውን አራግፈን እንነሳለን እያሉ መፎከር ከቶ የትም አያደርሰንም። አለማድረስ ብቻ ሳይሆን ስሜትም አይሰጥም ። ትናንት የሄድንበት መንገድ የውድቀት መሆኑን እያወቅን ያን መንገድ እንደዚያ እንዲሆን ያደረገውን መሠረታዊ ምክንያት መርምረን የስኬት መንገድ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ሳንሠራ ተመልን በዚያው መንገድ እየሄደንና መላልሰን እየወደቅን “ብንወድቅም አቧራ ልሰንና አራግፈን መነሳታችን አይቀርም!” የሚለው ፉከራችን አጠቃላይ የሆነውን እውነት እንጅ የእኛን ተጨባጭ አኳኋን ጨርሶ አይነግረንም ።   ለመሆኑ በምን አይነት አሳማኝ ምክንያትና ስንት ጊዜ ነው እየወደቅንና  አቧራ እያራገፍን መነሳት ያለብን ? ደግሞስ ተነስተን በቅጡ ሳንራመድ በራሳችን ልፍስፍስነት ተመልሰን እየወደቅን “መውደቅ ያለ ነውና ሲሆን ዛሬ ካልሆነ ነገ መነሳታችን አይቀርም”  የሚለው ምን ስሜት የሚሰጥ  ትርጉም ይኖረዋል ?
  • ልክ የሌለውን የግል ወይም የቡድን ጋግርታም ሸፍጠኝነትና ጠማማነት ታግለን በማሸነፍ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን መንገዳችንን ሁሉ የውድቀትና የመከራ
ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁለቱ አርበኞች ሳይጋጩ እንዲኖሩ | ገለታው ዘለቀ

ከአደረገብንና አሁንም የተሃድሶው ፍርፋሪ ተመፅዕዋች ሆነን እንድንቀጥል  ለማድረግ እያዘጋጀን (እያለማመደን) ካለው  ሥርዓተ ኢህአዴግ ሥር እየተንደፋደፍን “ብንወድቅም እንነሳለን!” የሚለው መፈክራችን ለልጆች መደለያነት ከሚነገር ተረት አያልፍም ።

መልኩን (ቅርፁን) ቀይሮ የቀጠለው ሥርዓተ ኢህአዴግ የፖለቲካ ሽባነት የፈጠረውና እየፈጠረ ያለው ኢሰብአዊ የሆነ ምስቅልቅል የምፅዋት ለማኝነታችን ስፋትና ጥልቀት በእጅጉ የከፋ አድርጎታል ። የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች በተሃድሶ ስም ለብዙ ዓመታት የኖሩበትን ሥርዓተ ፖለቲካ እስከ ጠንቀኛ መርዙ ይዘውት በመቀጠላቸው ያስከተለውና እያስከተለ ያለው አጠቃላይና ሁለንተናዊ ቀውስ አስከፊነት  በስፋትም ሆነ በድግግሞሽ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በሚያሳዝን ሁኔታ ልክ እንደማነኛውም ችግር እየተለመደ መጥቷል ። ይህ ደግሞ ለምንመኘው የሥርዓት ለውጥ እጅግ ትልቅ አደጋ ነው።በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ እንደሚል ዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደሰውም ያሸማቅቃል ።

እኛም የዚህ ሁሉ መከራና ውርደት ዋና ምንጭ (ምክንያት) የሆነውን ሥርዓተ ኢህአዴግን ለማስወገድ በሚቻልበት ቁም ነገር (አጀንዳ) ላይ ከማተኮር ይልቅ ገድለውና አስገድለው፣ አካል አጉድለውና አስጎድለው እና የሚሊዮኖችን መጠለያ ጎጆ በማፈራረስ ሜዳ ላይ ወርውረው “ከፈለጋችሁ ምፅዋዕት እየለመናችሁ እንደምታደርጉ አድርጓቸው” ሲሉን “እንኳን ለወገን ለማነኛውም ሰው የነፍስ አድን ምፅዕት እንለምናለን ። ነገር ግን እናንተ የመከራና የውርደት ዶፍ እያወረዳችሁ እኛም ምፅዋዕት እየለምን በፍፁም ልንቀጥል እንደማንችል ከምር ተረድታችሁ ለእናንተም ሆነ ለወገን ወደ እሚበጀው ህሊናቸሁ ተመለሱ” ለማለት ድፍረት እጥተን  የምፅዋዕ መለመኛ ኮሮጇቻችን ሞሉ ወይስ ጎደሉ እያልን ፋይዳ የሌለው ጭንቀት እሹሩሩ እንላለን ። ይባስ ብለን “የለውጥ ሃይል የምንላቸው ፖለቲከኞችን ማገዝ ነው እንጅ መቃወም ጥሩ አይደለም” በሚል እጅግ የዘቀጠ የፖለቲካ ሰብዕና ቀውስ ውስጥ ተዘፍቀናል ። ታዲያ ብንወድቅም አቧራችን አራግፈን የምንነሳው በምን አይነት  የፖለቲካና የሞራል  ተአምር ነው ?

4.ማጠቃለያ

አዎ!እንኳን  ከነፃነትና ከፍትህ ጋር የተያያዘ የትግል ሂደት ማነኛውም ማህበረሰብአዊ መስተጋብር እስከ መውደቅ የሚያደርስ ፈተና አለበት። ዋናው ከውድቀት ተምሮ ሲሆን ጨርሶ ላለመድገም ካልሆነ ግን ላለመደጋገም ከፍተኛ ጥረት የማድረግ ጉዳይ እንጅ ያለመውደቅ ጉዳይ አይደለም። የአወዳደቁ ሁኔታ ሥራን በሃቀኝነት ለማከናወን በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚከሰት ነው ወይስ ከግል ወይም ከቡድን ፍላጎትና ጥቅም በሚመነጭ የሸፍጠኝነት ባህሪ ? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። በእውነት መነጋገር  ካለብን ይህ የኢሳት ውድቀት የመነጨው በሁለተኛው ምክንያት ነው።  የበጀትና ሌላም የአሠራር ሰበብ መደርደሩ የባሰ ሸፍጠኝነትን ያጎለብታልና የሚሻለው ሃቀኝነትና ሥልጣኔ የተሞላበት የመፍትሄ ፍለጋ አካሄድና ውሳኔ መሆኑን አውቆ ጥረት ማድረግ ነው።

የኢሳትም ሆነ ሌሎች እጅግ በርካታ አስከፊ ኩነቶች ኢህአዴግ ከህገ መንግሥት ተብየው  ጀምሮ መሠረታዊ ከሆነ ባህሪዎቹ ፣ ከመንግሥትና የካድሬ መዋቅሮቹ ፣ ከበሰበሰው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነት ከሚመነጩ አሠራሮቹ ፣  ከበርካታ ወንጀለኛ ፖለቲከኞቹና ካድሬዎቹ ፣ በአክራሪ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ የፖለቲካ ከተለከፉ  ድርጅቶችና መሰል ወዳጆቹ ፣ ወዘተ ጋር በሚመራው የፖለቲካ አውድ ሥር እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ በፍፁም የሚታሰብ አይደለም ። አንዳንድ ወገኖቸ ኢህአዴግ ተዋህጀ  ኢትዮጵያዊ ስም ልለጥፍ ነው” የሚለውን እንደትልቅ የለውጥ ማሳያ ሲናገሩ እሰማለሁ ። እንዳሉት ቢሆን እንዴት መልካም ነው። ግን ይህ ተስፋ እንዲህ በቀላሉና በአጭር የጊዜ ስሌት ጨርሶ እውን ሊሆን አይችልም ።

ሊሆን የሚችለው ይህን መከረኛ ህዝብ በቅርፅ (ለስሜት የሚመች ስያሜ በመለጠፍ) እያደነዘዙና ከዋናው ጥያቄ እያስወጡ አገዛዝን ማስቀጠል ነው ። ይህን ለማጀብ ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉትን ጨምሮ “አዲሱ ኢህአዴግ” የሰላም እጁን ዘርግቶ ወደ አገር ቤት ያስገባቸው ተቀዋሚ ተብየ ፖለቲከኞች ዝግጁዎች ናቸው። ይሀንንም በየመደረኩና በየአጋጣሚው “የእኛ ዓላማና ፍላጎት የለውጥ አራማጅ የኢህአዴግ ፖለቲከኞችን መቃወም ሳይሆን ማገዝ (መደገፍ) ነው” በሚል እያረጋገጡ ናቸው። ይህ ሁሉ የሚነግረን ለእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ የሚደረገው ትግል ገና ብዙ እንደሚቀረው ነውና ይህኑ መሪር እውነታ ተረድቶና ተቀብሎ ተገቢውን ማድረግ ግድ የሚል መሆኑን ነው ። እንዲያም ሲሆን እዚያም እዚህም ኢሳትን እንዳጋጠመው አይነት ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ መፍትሄ የሚያገኙት ።

መልካሙን ሁሉ እየተመኘሁ አበቃሁ !

 

1 Comment

  1. Ethiopians need to sue EPRDF for selling public properties since 1991.

Comments are closed.

Share