June 3, 2019
15 mins read

ወይ የኢሣት ነገር! ጊዜ ደጉ ስንቱን ያሳያል? – ግርማ በላይ

“ተማምለን ነበር እንዳናንቀላፋ፤ ተኝተሸ ተገኘሽ መተማመን ጠፋ፡፡” ብሎ የገጠመው ጎረምሣ እውነት ብሏል፡፡

በኢሣት ዙሪያ ሰሞኑን የሚወራው ደስ አይልም፡፡ በመልካም ጓደኛሞች መካከል መጥፎ መንፈስ የገባ ይመስላል፡፡ በኢሣት መንደር የተነሣው አቧራና ጭስ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ጠቡ አደባባይ እየወጣ ነው፡፡ የጠቡ መንስዔም ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ ሰንጎ የያዛት የዘረኝነት አገዛዝና እርሱን እንደግፍ አንደግፍ በሚሉ ኃይሎች መካከል የፈለቀ ቁርቋሶ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ያም አለ ያም አለ በመጨረሻ እውነት ማሸነፏ አይቀርም፡፡ በጎመን የደለሉት ሆድ ጉልበት ሆኖ አቀበት ሲያወጣ፣ መጣ የተባለው የይስሙላ ዴሞክራሲም ሕዝብን አዋህዶ ሀገር ስትለማ በቅርቡ ልናይ ነው፡፡ የአጋሰሶች ዘመን ሊያልቅ ሲል፣ የከሃዲዎች አበቅቴ ሊጠናቀቅ ዳር ዳር ሲል፤ የሌሊት ወፎች የጨለማ ዘመን ሊያበቃ ጎህ ሲቀድ ምልክቱ ብዙ ነው፡፡ እንዲህ ብዬ መግቢያየን ልጨረስ፡፡

ኢሣት መፍረስ አልነበረበትም፡፡ ያፈረሱት እነማንም ይሁኑ ትንሽ መታገስ ነበረባቸው፡፡ ሊያውም ለብዙ አሠርት ዓመታት በሚገባ በሠለጠኑበት ነጭ ውሸት በታጀበ ዲስኩር፡፡ ሀፍረትን ሸጠው የበሉ ናቸው፡፡ ከወያኔ የሚያንሱት አራት ኪሎን በግልጽ ባለመያዛቸው ብቻ ነው፡፡ የጅብ ችኩል ነው የሆኑት፡፡ በሀገራችን የፈጠጠው እውነት አፍራሾቹ እንደሚሉት የሚያዝናና ሳይሆን ከሕወሓት ዘመንም የከፋ ቆፈናም መሆኑን ለመገንዘብ ከአዲሱ አገዛዝ ጋር በጥቅም ትስስርና በድውይ ዓላማ ቁርኝት አለመጠመድን ብቻ ይጠይቃል፡፡ የሁላችንም ትግል አንድን ጎሣ በሌላ ለመተካትና በኮፒ/ፔስት ዘረኝነትን ለማንገሥ ሳይሆን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነበር – ለጊዜው ምኞታችን ሁሉ በነበር ባይቀር፡፡ ይሁን ግዴለም፡፡ “በቅሎ ገመዷን በጠሰች” ቢሉ “ማሰሪያዋን አሳጠረች” እንዲሉ ነው፡፡ እንጂ ምድረ ዘረኛና እስስት ለማንም ቢያጎበድድ ነፃነት እንደራቀች ትቀራለች ማለት አይደለም፡፡

የኢሣት ምርጥ ጋዜጠኞች ከኢሣት መባረራቸው እውነት ከሆነ የሚባረሩበትን ምክንያት ለማወቅ ብዙ ምርምርን አይጠይቅም፡፡ ሊሆን የሚችለው አሽቃባጭነትና አጎብዳጅነት ነው፡፡ ሊሆን የሚችለው ድርጅታዊ ሽርሙጥና ነው፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ አንጋፋ ዜጎችና እንደግል ንብረታቸው የሚቆጣጠሩት ድርጅታቸው ለአዲሶቹ አህዲዳዊ ወያኔዎች ካደሩ ወዲህ ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ናቸው፡፡ ሆድና ጥቅም ሰውን ስንትና ስንት ጊዜ እየሠራ እንደሚያበላሸውም በእግረ መንገድ እየተረዳን ነው፡፡ የት ይደርሳሉ ብለን በጉጉት እንጠብቃቸው የነበሩ ምሁራንና ለሀገር ተቆርቋሪ ይመስሉን የነበሩ ዜጎች ምናልባት በትግሉ መራዘም ምክንያት ተስፋ ከመቁረጥና ከመሰላቸት የተነሣ ሊሆን ይችላል ሃሳባቸውን በመቀየር ወደተግማማ አሠራር እየወረዱ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ እነዚህ የመርገምት ፍሬዎች እጅግ በቀለኛና ሸፍጠኛ ናቸው፡፡ የሚጠሉትን ለመበቀል የሚጓዙት ርቀት ከፈጣሪያቸው ከወያኔ ቢብስ እንጂ አያንስም፡፡ ይህ የመበቃቀል አዙሪት አንድ ቦታ ላይ ካልተበጠሰ ይሄ ሰሞኑን በኢሣት ጋዜጠኞች ላይ የተፈጸመው ደባና ተንኮል በሌላ ሥፍራና ሁኔታ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ነገረ ሥራችን ከዝንጀሮ ቆንጆ የመምረጥ ሆነና ዐረፈው፡፡ በተቃዋሚውም ሆነ በመንግሥት ጎራዎች የሚታዩት ፊቶች ሁሉ አንድ የመሆናቸው ምሥጢርም የሀገራችን ፖለቲካ መረገሙንና ሊያንሠራራ አለመቻሉን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ክፉኛ ተረግማለች፡፡ ፖለቲከኛ እንዳይወጣላት በተለይ ትልቅ እርግማን አለባት፡፡

የሰው ዐይን መጥፎ ነው፡፡ እነዚያን መሰል ድንቅ ዜጎች የሰው ዐይን ገባቸውና ኦህዲድ ሥር ተነጥፈው ሲርመጠመጡ ማየት አንጀትን የሚበላ የዘመናችን ዘግናኝ አውነት ሊሆን ቻለ፡፡ የአንዳንድ ሰው መጨረሻ በርግጥም ያሳዝናል፡፡ ይህ በሌላ በኩል የሚያሳየው አነሳሳቸውም ላይ ግርታና ያላወቁት የግል ችግር የነበረባቸው መሆኑን ነው፡፡ ዕድሜ ሰጥቶኝ መጨረሻውን ብቻ ያሳየኝ፡፡ ወይ ሀገር! አገር ሲያረጅ ጃርት ማፍራቱ ለካንስ እውነት ነው፡፡ ወያኔ በአምሳሉ ቀፍቅፎ የተወልን ድርጅቶች የማያሳዩን ተዓምር ላይኖር ነው፡፡ በስመ አብ!

አማራ ጠሎቹ እነዚህን መሰል የከንቱ ትውልድ አብነቶች አካሄዳቸው ባጭር ካልተቀጨ በሀገርም ሆነ በንጹሓን ዘጎች ላይ የሚያስከትሉት አደጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ተሰሚነታቸውን፣ የሚችሉ ደግሞ ከግል ገንዘባቸውና ከሕዝብ የሚሰበስቡትን ሀብትና ጥሪት፣ በጥቅሉ መላ አቅማቸውን በመጠቀም የሚያደርሱት ጉዳት አንዳንዴ ሊቀለበስ የማይችል ሊሆን ይችላልና መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ እልከኞች ናቸው፤ የደምና የሥልጣን አራራ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ለመግደልና ለማስገደል ወደኋላ አይሉም፡፡ ዕብሪተኞች ናቸው፡፡ ትምክህተኞችም ናቸው፡፡ በዝቅተኝነት ስሜት የሚሰቃዩ በመሆናቸው ሲንጠራሩ የሰማያትን ግንቦች ሊያፈርሱ ይደርሳሉ፡፡ ብዙዎቹ ሃይማኖት የሚባል ነገር አያውቁም – አላቸው የሚባሉትም ለማስመሰል እንጂ አስተምህሮውን በተግባር አያውሉትም፡፡ የበቀለኝነታቸውና የእልኻቸው መንስዔ ሞራላዊና ባህላዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ዕሤቶች ከውስጣቸው ተንጠፍጥፈው መውጣት ነው፡፡ ከነዚህ ጋር ጦርነት መግጠም ልፋት ነው፤ ከዶንኪሾቶች ጋር ገጥሞ ማን ሊያሸንፍ?ይህንንም ስል አይሸነፉም ለማለት አይደለም፡፡ እነሱን ለማንበርከክ በነሱ መንገድ መጓዝ አይገባም፡፡ ልዩ ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ግን ጊዜ ነው፡፡ ጊዜ እንኩቶ ያደርጋቸዋል፤ ይጠራርጋቸዋልም፡፡

ዘረኝነት መጥፎ የአስተሳሰብ ልምሻ ነው፡፡ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ቢማርና ዶክተር ፕሮፌሰር ቢሆን በዚህ በሽታ አእምሮው ከተሽመደመደ ሌት ከቀን የሚያውጠነጥነው ጥፋትን እንጂ ልማትን አይሆንም፡፡ እነ አቶ ፀጋየ አራርሳንና መሰል የዚህ ደዌ ልክፍተኞችን በዋቢነት ማየት በቂ ነው፡፡ እየተሰቃዩ ያሉት በዚህ ደዌ ነው፡፡

የኢሣት ነገርም ከዚሁ ከሚጠነባ የዘረኝነት ሥነ ልቦናዊ በሽታ ጋር የተያያዘ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አማራ ሲባል ከስም አጠራሩ ጀምሮ ደማቸውን የሚያንተከትክባቸው ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አማራን ለገንዘብ ማሰባሰቢያነትና ለትግል ማስኬጃ መናጆነት እንጂ ወደ ሀብትና ሥልጣን እንዳይጠጋ ለማድረግ ከገዢዎች ጋር በኅብረት እንደሚሠሩም እናውቃለን፡፡ እንጂ ኦህዲድን በአንቀልባ ለማዘልና ከሕዝብ ጋር ተጣልቶ ኢሣትን ለመበተን የሚያበቃ ሀገራዊ ድባብ በአሁኑ ወቅት ጨርሶውን የለም፡፡  ዶክተር አቢይንም ሆነ ኦነግንና ኦህዲድን በአንቀልባ አዝለው የመዞር መብታቸው በመሠረቱ የተጠበቀ ነው፡፡ በሀገር ቁስል ግን እንጨት የመስደድ መብት ፈጽሞ የላቸውም፡፡  ይህ ነገር ጊዜ ቢፈጅም ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ሊረዱት ይገባል፡፡ በማፍረስና በመበተን የሚታወቁ ግለሰቦች አደብ ቢገዙ ከተጨማሪ የካርማ ጽልመት ራሳቸውን ሊታደጉ ይችላሉና ዘመድ ወዳጅ ካላቸው ይምከራቸው፡፡ እናጠፋዋለን ብለው የተነሱት አማራ እንደሆነ አይጠፋም – ዕርማቸውን ያውጡ፡፡ የሚጠሉት የሚመስሉት በዓላማና በግብር ግን የሚመሳሰሉት መለስ ዜናዊ ራሱ በመርፌ ማምከንን ጨምሮ ብዙ ቢለፋም አማራን ሊያጠፋ አልተቻለውም – ቀድሞ ራሱ ጠፋ እንጂ እንዲያውም፡፡

ይልቁናስ ለነሱም መዳን ትልቁ ምክንያት የሚሆነው እርሱ ነው – አማራው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ነው ታዲያ፡፡ ኢትዮጵያዊነትንና አማራነትን ለመለያየት የሚደረገው የባንዳዎችና የግብረ አበሮቻቸው እልህ አስጨራሽ ትግል ጉልበቱን ጨርሶ ሲከስም ኢትዮጵያዊነት አፈሩን አራግፎ ከተቀበረበት ይነሣል፡፡ ያም ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሠገሠ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይላት እንዲህ መንቀዥቀዥና ግምባር መፍጠር ምሥጢሩ ውስጣቸው የዚያን ወርቃማ ዘመን መምጣት እየነገራቸው እንደሆነ በስድስተኛው ስሜት መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኢሣት ዕውቅ ጋዜጠኞች ይህን ነገር አትናደዱበት፡፡ ለበጎ ነው፡፡ ይሁዳ ክርስቶስን በ30 ብር እንደሸጠው አስታውሱ፡፡ ሊያልቅ ሲል ብዙ ነገሮች እንደሚበለሻሹም ተገንዘቡ፡፡ ይልቁናም ምንም ሳትበሳጩና እልህ ውስጥ ሳትገቡ ሌላ የሚዲያ አውታር መሥርቱ፡፡ ይቻላል፡፡ ነባሩን ኢሣት የሚያስንቅ ሌላ ጣቢያ መገንባት ይቻላል፡፡ ነባሩን ኢሣት ባለጊዜዎቹ ‹ተንበርካኪዎች› ይፈንጩበት፡፡ ሲፈልጉ ኢቲቪ ቁጥር ሁለት ይበሉት፡፡ ሲሻቸው ኦኤምኤን  ቁጥር ሁለት ይበሉት፡፡ ከነሸጣቸውም ኦቢኤን ቁጥር ሁለት ያድርጉት፡፡ እሱ የማንኛችንም ራስ ምታት አይደለም፡፡ ሥራ ግን መሠራት አለበት፡፡ መሸነፍ የለም፡፡ “የኢትዮጵያ ሬዲዮና ሣተላይት ቴሌቪዥን” (ኢርሣት – ERSAT) ብላችሁ ብታቋቁሙ የምትችሉ ይመስለኛል፡፡ ማንኛውንም ነገር ሞክሩ፤ አንዱ ይሳካል፡፡

የፈሰሰ አይታፈስም፡፡ ማፍረስ የለመደም አይመለስም፡፡ “መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል” እንዲሉ ነውና ከመነሻቸው ጀምሮ ሲያፈርሱና ሲበትኑ ከኖሩ ሰዎች ምንም ደግ ነገር እንደማይጠበቅ ተረድታችሁ ራሳችሁን በሌላ መልክ አደራጁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ እንደሚቆም ደግሞ በጭራሽ አትጠራጠሩ፡፡ መከዳት ዕጣው የሆነው ይህ የተገፋ ሕዝብ ሁሉንም ምሥጢር ያውቃልና ችግሩን ስለሚረዳ ፊት አይነሳችሁም፡፡ ይቅናችሁ፡፡

4 Comments

  1. ዘረኝነት መጥፎ የአስተሳሰብ ልምሻ ነው፡፡ አንድ ሰው የፈለገውን ያህል ቢማርና ዶክተር ፕሮፌሰር ቢሆን በዚህ በሽታ አእምሮው ከተሽመደመደ ሌት ከቀን የሚያውጠነጥነው ጥፋትን እንጂ ልማትን አይሆንም፡፡ yes you said it. but your article also smell ethinocenter ethinocenter(amhara amhara). ESAT should have change it’s gear. Only opposition doesn’t mean loyalty to the people. by the way I am amhara by father and mother, I was ESAT advocate and I live by my sweat.I’m not shrud and I hate shrudness

  2. Dear Girmay,
    This is digital world. Why you write too long introduction. I could not read and understand; mainly because of it is very long like the of Rome. May you condense to the point and re-write so that everybody understands you.

    Regards,

    • Biru, kehulet gets belay endemin lasatrew? jemro saynageru mechem makom aychalim.

  3. Ato Girma you sound that your are ‘NIKIR” Zeregna first treat yourself from
    This disease before you talk about others business how dare are you blaming
    This respectful and very thoroughful Journalist who pay the maximum Altimat
    Price in prison for you narrow minded and TIMKEHITENGA
    ETHIOPIA means AMHARA and vise versa what kind stupid mentality is this?
    while the world is coming together and one in so many aspects
    I saw from your article your hatriate and I smell it from far get help my Dear b/c
    Really ur are sick.

Comments are closed.

Previous Story

  <<ሁሌም ቢሆን ከእውነትና ከመርህ ጋር እናቆማለን። -  ከኢሳት ዲሲ ስቱዲዮ ጋዜጠኞች የተሰጠ መግለጫ

Next Story

“እኛ ና እነሱ” የወቅቱ ” የዘረኝነት መደብ ” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop