ከዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ወዲህ የተጋጋመው የሲዳማ ልሂቃን የክልል ጥያቄ ማጠንጠኛ የአዋሳ ከተማ ባለቤትነት ጉዳይ ነው፡፡ላይ ላዩን ‘ክልል ባለመሆናችን ማንነታችን ተጨፈለቀ’ የሚሉት የሲዳማ ልሂቃን ዋናው ጥያቄያቸው የደቡብ ብሄረሰቦችም ሆኑ የፌደራሉ መንግስት ተባብሮ ያሳመራትን አዋሳ ከተማን የግላቸው ማድረግ ነው፡፡የእነዚህ ልሂቃን ጥያቄ የሲዳማ ክልል ጥያቄ ከመሆን ይልቅ “የአዋሳ ጥያቄ” ቢባል የልሂቃኑን እውነተኛ መሻትም ሆነ የነገሩን ውስብስብነት ይበልጥ ይገልፀዋል፡፡
የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ የአዋሳን የባለቤትነት ነገር በውስጡ ባይሸጉጥ ኖሮ ነገሩን መፍታቱ ለማዕከላዊው መንግስትም፣ ክልሉን ለሚመራው ደኢህዴንም ይህን ያህል አዳጋች አይሆንም ነበር፡፡የሲዳማ ልሂቃንም በክልል ጥያቄው ላይ ይሄድን ያህል አክርረው ባልሄዱ ነበር፡፡ሌላው ነገሩን ያወሳሰበው ጉዳይ እንደ ጃዋር እና ፀጋየ አራርሳ ያሉ አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሲዳማ ልሂቃንን እጋለቡ ሊያስፈፅሙ የሚፈልጉት ራሳቸው ጠባብ ብሄርተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡
የሲዳማ ልሂቃን አዋሳ ከተማን መናገሻው ያደረገ የሲዳማ ክልል ምስረታ ጥያቄ አቶ መለስ በህይወት እያሉም ጀምሮ ይጠየቅ የነበረ ቢሆንም የተጋጋለው ህወሃት ከስልጣን ከተባረረ በኋላ ነው፡፡ጥያቄው ረዘም ያለ ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም እልባት ያላገኘው ለምንድን ነው? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ አንስቶ መመርመር ያስፈልጋል፡፡
ምክንያት አንድ
የሲዳማ ልሂቃ የክልል እንሁን ጥያቄ መልስ ያላገኘበት የመጀመሪያው መሰረታዊ ምክንያት ጥያቄው ራሱ በሃገራችን ያለው ኋላቀር የዘር ፌደራሊዝም እና የዘር ፖለቲካ የወለደው፣በገሃዱ ዓለም በተግባር ለመተርጎም የሚያስቸግር ስለሆነ ነው፡፡ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ መስተጋብር አንድን መሬት መቼ እዛ ምድር ላይ የተገኘ፣ማን የተባለ ዘር ባለቤት መሆን እንዳለበት ቁርጥ አድርጎ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ከዚህ ባሻገር የሆነ ዘር ባለቤቱ ነኝ የሚለው ምድር እግዜር እንደሰራው ያልተቀመጠ፣ ይልቅስ በዘር ፌደራሊዝሙ የመሬቱ ባለቤት ተደርገው የማይቆጠሩ፣መጤ የሚባሉ ሰዎች ብዙ ዘመናትን ባስቆጠረ የተባበረ ጥረት ያለሙት መሆኑ ነው፡፡
ሃገራችን የምትመራበት ኋላቀር የዘር ፖለቲካ/ፌደራሊዝም ደግሞ በመሬቱ ላይ በተለያዩ ዘሮች ብዙ ተለፍቶበት የመጣውን ልማት እና ኢንቨስትመንት ካመጡ ሰዎች ይልቅ እግዜር በሰራው መሬት ላይ ዝም ብለው ለተቀመጡ ሌሎች የሃገር ባለቤትነት የሚሰጥ፣ልማታዊ ነኝ እያለ ከልማት ጋር የማይተዋወቅ ስርዓት ነው፡፡በዚህ ምክንያት ይህ ኋላቀር የዘር ፖለቲካ/ፌደራሊዝም በዘራዊ ሽንሸናው የሆነ መሬት ባለቤት ናችሁ ያላቸው ወገኖች ባለቤት ነን በሚሉት መሬት ላይ የተሰራውን ልማት፣የተለፋውን ልፋት ከመጤፍ ሳይቆጥሩ “እኛ ባለቤት ነን፤ እናንተ ግን መኖር ትችላላችሁ”ይላሉ፡፡
አዋሳን ማዕከሉ ያደረገ የሲዳማ ክልል የሚጠይቁ የሲዳማ ልሂቃን የአዋሳ ባለቤት መሆናቸውን ጠቅሰው በሚከራከሩ ጊዜ አዋሳ የለማችው የደቡብ ብሄርብሄረሰቦች መዲና በመሆኗ፣በሁሉም ብሄረሰቦች በጀት እንደሆነ ክርክር ሲቀርብላቸው “የመሬቱ ባለቤቶች እኛ ነን፤ ልማት የምትሉት ነገር የጣራ እና ግርግዳ ነገር ነው፣ወጭውን አስልተን እንከፍለችኋለን” ሲሉ ከዘር ፖለቲካው ፍርደ-ገምድልነት የሚቀዳ መልስ ይሰጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ነገሩ እውነት የጣራ እና ግርግዳ ጉዳይ ከሆነ ከተማዋን ላለሙ በክልሉ የሚገኙ ሃምሳ ምናምን ብሄረሰቦች “የጣራ እና ግርግዳ” ክፍያ ሲከፍሉ ለስንቱ ስንት ይደርሳል ብለው፣ በምን መንገድ ሊከፍሉ እንዳሰቡ ለዘር ፖለቲካኛ ጥያቄ ማቅረብ በድንጋይ ተወግሮ መሞትን ያስከትል ይሆናል እንጅ መልስ የሚኖረው ነገር አይደለም፡፡የሆነ ሆኖ የሲዳማ ልሂቃን የክልል ጥያቄየቸው እንዲመለስ የሚፈልጉበት መንገድ በሁሉም ብሄረሰብ ብዙ የተለፋባትን አዋሳ ከተማን ለእነሱ አዲስ የሲዳማ ክልል ብቻ ሸልሞ አዋሳን ያለማው ሌላው የደቡብ ህዝብ የጣራ እና ግርግዳ ሂሳብ ከእነሱ ተቀብሎ የሚሄድ ከሳሪ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ላይ የጣራ እና ግርግዳውን ክፍያ ከየት አምጥተው እንደሚከፍሉትም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡
የሲዳማ ልሂቃን ሌላው የደቡብ ክልል ህዝብ የአዋሳ ባለቤትነት ድርሻውን እንዳይጠይቅ መከራከሪያ ብለው የሚያመጡት ነገር “አዋሳ ከተማ የለማችው በራሷ ገቢ ነው” የሚል ግንዛቤያቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል መልስ ነው፡፡ ለዚህ ክርክራቸው ማጠናከሪያ አድርገው የሚያቀርቡት ነገር ከተማዋ ከፌደራል መንግስት እና እንደ ዓለም ባንክ ካሉ ተቋማት የምታገኘውን ገቢ መጥቀስ ነው፡፡ ይህ ይረዳናል ብለው የሚያመጡት ክርክር የአዋሳ ባለቤት ነኝ በሚለው የሲዳማ ዞን ያልለማች ይልቅስ የፌደራሉ መንግስት አግባብቶ በሚያመጣቸው ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ዳረጎት ያደገች፣ፌደራል መንግስት ለእድገቷ የተበደረው ሰማይ ጠቀስ እዳ የማያጣት ከተማ መሆኗንም ጭምር ነው፡፡ይህ ደግሞ የከተማዋን ባቤትነት ከአንድ ጎሳ ይልቅ ወደ ፌደራል መንግስት የሚጠቁም ነው፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው ክርክራቸው ባፈነገጠ ሁኔታ ደግሞ የሲዳማ ዞን የሚያመርተው የጫት እና የቡና ሃብት ከተማዋን ለማልማት አቅም እንዳለው፣ሲዳማ ዞንም ከሌላው የደቡብ ክልል ዞኖች ላቅ ያለ የተፈጥሮ ሃብት እንዳለው የሚያወሱት ነገር ነው፡፡ይህም ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የሲዳማ ቡና እና ጫት ቀርቶ ሃገራችን ከሁሉም ክልሎቿ ወደ ውጭ የምትልከው ቡና፣የቅባት እህል፣ቆዳ ሌጦ፣ቅመማቅመም፣የቁም ከብት፣ስጋ ሆነ ሌላ ምርት ሁሉ ተደምሮ የሚያመጣው ገቢ ወዴትም የሚያደርስ ላለመሆኑ ምስክሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አንድ ሳምንት ዶላር ላለመላክ ሲያምፅ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ማጣፊያ የሚያጥረው መሆኑ ነው፡፡ከሁሉም በላይ ዝናብን ጠብቆ በገበሬ ጓሮ የሚበቅል ቡናም ሆነ ሌላ የግብርና ምርት ገቢ እንዲህ የሚያዝናና አለመሆኑ ነው፡፡የዓለም የቡና ገበያ አኪር ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ላቲን አሜሪካ ሃገራት የገባ መሆኑን መረጃ ማገላበጥ ከሲዳማ ገጠራማ ቦታዎች በእጅ ተሸምጥጦ የሚመጣ ቡና አዋሳን እዚህ እንደማያደርስ ለመረዳት ያስችላል፤ቅዠት በሚመስል ሁኔታ ራስን በአጉሊ መነፅር ከማየትም ይታደጋል፡፡የሲዳማ ዞን የተፈጥሮ ሃብት በደቡብ ተወዳዳሪ የሌለው ተደርጎ ለሚቀርበው አስቂኝ ነገርም ሌላው የደቡብ ክልል ይቅርና በትንሹ ወደ አርባምንጭ ጎራ በሉና ከአንድ ትንሽ መንደር ለሃገር የሚዋጣውን ምርት ተመልከቱ ከማለት ውጭ ብዙ ድካም የሚፈልግ ነገር አይደለም፡፡
ምክንያት ሁለት
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ያልቻለበት ሌላው ምናልባትም ዋናው ምክንያት ጥያቄው ክፉኛ ከአዋሳ ከተማ ባለቤትነት ጋር የተጣበቀ መሆኑ ነው፡፡ የሲዳማ ልሂቃን የክልልነት ጥያቄ ዋና ዓላማው እነሱ እንደሚያወሩት የራስን ቋንቋ እና ባህል ማሳደግ እና ራስን በራስ ማስተዳደር ቢሆን ኖሮ በሲዳማ ዞን ካሉት ከተሞች በአንዱ(ለምሳሌ ይርጋዓለም፣በንሳ፣ሃገረሰላም፣አለታ ወንዶ) ዋና ከተማቸውን አድርገው ክልል የመመስረት ትግላቸውን እውን ማድረግ የሚችሉበትን አማራጭም ያቀርቡ ነበር፡፡ ነገር ግን ለሲዳማ ልሂቃን ይህ የማይዋጥ ብቻ ሳይሆን ሊሰሙት የማይፈልጉት ነገር ነው፡፡አዋሳን ማዕከል ማድረግ ካልቻሉ ሲዳማ የሚባል ክልል ዛሬውኑ እውን የሚሆን ቢሆን እንኳን በፍፁም የሚፈልጉት ነገር አይደለም፡፡ከዚህ መረዳት የሚቻለው ነገር የሲዳማ ፖለቲከኞች ዋነኛ ጥያቄ በብዙዎች ድካም ያማረችውን አዋሳ ከተማን የግል ማድረግ መሆኑን ነው፡፡ይህ ደግሞ የራስን ብቻ ከማየት የመጣ አጉል እሳቤ ነው፡፡
ሌላው የሲዳማ ልሂቃን ያልተረዱት ወይም ሊረዱት የማይፈልጉት ወሳኝ ጉዳይ አዋሳ ከተማ የሲዳማ ዞን አካል ያልሆነች ይልቅስ በከተማ አስተዳደር የምትመራ ከተማ መሆኗን ነው፡፡በ1995 ዓም በደቡብ ክልል ምክር ቤት በወጣ አዋጅ አዋሳ ከተማ በራሷ የከተማ አስተዳደር የምትመራ፣ ተጠሪነቷም ቀጥታ ለክልሉ መስተዳድር እንዲሆን ተወስኖ በዚሁ ሁኔታ እየተዳደረች ያለች ከተማ እንጅ በሲዳማ ዞን ውስጥ ያለች ግዛት አይደለችም፡፡ይህ አዋጅ የታወጀው ደግሞ ራሳቸው የሲዳማ ተወላጅ የክልል ምክርቤት አባላት ባሉበት ጉባኤ ነው፡፡ስለዚህ ጥያቄያቸው ህጋዊ ስለመሆኑ ህገመንግስት አስታከው የሚከራከሩ የሲዳማ ልሂቃን የከክልል ጥያቄያቸው ሲዳማ ዞን በአሁኑ ወቅት የሚይዘውን ቆዳ ስፋት ብቻ ያማከለ ሊሆን ይገባል፡፡እንጅ የሲዳማ ልሂቃን አዋሳን ስለለፈለጓት ብቻ በዞኑ ውስጥ የማትገኝን ከተማ ለሞት በሚያደርስ ሁኔታ መመኘት ህጋዊነት አይደለም፡፡
አማካሪዎቻቸው የኦሮሞ ልሂቃ አዲስ አበባ የኦሮሞ የተፈጥሮ ዕርስት ነች እንደሚሉት አዋሳም የሲዳማዎች የተፈጥሮ ዕርስታችን ነች የሚሉ ከሆነ ደግሞ በ1995 የአዋሳን የከተማ አስተዳደርነት አስመልክቶ በደቡብ ክልል ምክርቤት የወጣውን አዋጅ በሌላ የክልል ምክርቤት አዋጅ አስሽረው መሆን አለበት፡፡የደቡብ ክልል ምክር ቤት አዋሳ ለሲዳማ ትገባች እኛ በየፊናችን አዲስ ዋናከተማ እንገነባለን የሚል የቂል ውሳኔ የሚያሳልፍና አዋጅን በአዋጅ የሚሽርላቸው ከሆነ ምኞታቸው ይሰምራል ማለት ነው፡፡
አዋሳ በታሪክ የሲዳማ እርስት ነች የሚለው እሳቤ መነሻው ኦሮሞዎች አዲስ አበባ የኦሮሞ ተፈጥሯዊ እርስት ነች ከሚሉት ነገር ጋር ተመሳሳይ የሆነ፣ ከተጨባጭ ሃቅ ይልቅ ስነ-ልቦናዊ መሻቱ የሚበዛ ነገር ነው፡፡በዚህ ተመሳስሎሽ ሳቢያም ነው እንደ ጃዋር እና ፀጋየ አራርሳ አይነት የኦሮሞ አክቲቪስቶች የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አማካሪ ሆነው ብቅ ያሉት፡፡የሲዳማ ልሂቃን ሲዳማ ክልል መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ ትክክለኝነት ለማስረዳት በንጉሱም ሆነ በደርግ ዘመን የሲዳሞ ክፍለሃገር የሚባል ግዛት ከመኖሩ ጋር አቆራኝተው ሲያቀርቡት ይደመጣል፡፡ሆኖም የዛ ዘመኑ የሲዳሞ ክፍለ ሃገር የአሁኑን የሲዳማ ፣ወላይታ ፣የጌዲኦ ዞኖች፣የአማሮ ልዩ ወረዳን አካሎ ወደታች በመውረድ ከአሁኑ የኦሮሚያ ክልል ያቤሎን ጨምሮ የተዘረጋ ሰፊ ግዛት ነበር፡፡ዋና ከተማውም በንጉሱ ዘመን ይርጋዓለም ከተማ በኋላም በራስ መንገሻ ስዩም ቆርቋሪነት ወደ አዋሳ የተዛወረ ነው፡፡የሲዳሞ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ ወደ አዋሳ ከመዛወሩ በፊት የአሁኑ የአዋሳ ከተማ መሬት የከብት መጋጫ ሜዳ እና የአራዊት መናኸሪያ ጫካ ነበር፡፡የየትኛው ዘር ከብቶች ይግጡበት ነበር ወደ ሚለው ስራ ፈት ጥያቄ እንሂድ ከተባለ ደግሞ ጉጂም፣ጌዲኦም አዋሳ ላይ ከብቶቼን አሰማርቻለሁ ይላል፡፡
አዋሳ ጫካነቷ እየጠፋ ከተማ እየሆነች ስትሄድ ደግሞ ከተማዋን ከመቆርቆር ጀምሮ እስከማሳደጉ ድረስ በአቅራቢያው የሚገኙ ብሄረሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች ምናልባትም ከሲዳማ ተወላጆች በበለጠ ተሳታፊ እንደነበሩ እድሜ የጠገቡ ከተማዋ ተፀንሳ ስታድግ በአይናቸው ያዩ አረጋዊያን የሚናገሩት ነው፡፡ከዚህ ታሪካዊ ዳራ የምንረዳው አዋሳን የሲዳማ ብሄር ብቻ ንብረት የሚያደርጋት ታሪካዊ አመክንዮ እንደሌለ ነው፡፡ አዋሳ በንጉሱ ዘመን የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት፣ በደርግ ዘመን የሲዳሞ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ የነበረችበትን ወቅት ተጠቅሶ የባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ በዚህ ወቅት አዋሳ የወላይቶችም፣የጌዲኦዎችም፣የአማሮዎችም ቦረና እና የጉጂ ኦሮሞዎችም ዋና ከተማ ነበረችና እነዚህ ህዝቦችም የባለቤትነት ጥያቄ የማንሳት ታሪካዊ መብት አላቸው ማለት ነው፡፡
የአሁኑ የሲዳማ ዞን ብቻ አዋሳን ዋና ከተማው አድርጎ እንደ መንግስታዊ አስተዳደር የተዳደረበት የታሪክ አጋጣሚ የለም፡፡ስለዚህ አዋሳ የሲዳማ ንብረት ነች የሚለው የአሁኑ የሲዳማ ልሂቃን ክርክክር ብቸኛው መደገፊያው አዋሳን የከበባት የሲዳማ አርሶ አደር ስለሆነ ለእኛ ትገባለች የሚለው የደመነፍስ ክርክር ነው፡፡ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደመጣም የአሁኑን የደቡብ ክልል ለአምስት ክልሎች በሸነሸነ ወቅት ሲዳማ፣ጌዲኦ እና አማሮ በክልል ሰባት ስር ተካለው አዋሳን ዋና ከተማቸው አድርገው፣ ክልሎ ተጨፍልቆ የደቡብ ክልል እስኪባል ድረስ ቆይተዋል፡፡ በዚህኛው የታሪክ አንጓም ቢሆን የአዋሳ ባለቤትነት የጌዲኦ እና አማሮም ተጋሪነት ያለው ነገር እንጅ የሲዳማ ህዝብ ብቻ የሚሆንበት አመክንዮ አይኖርም፡፡
ኢህአዴግ ወደስልጣን ከመጣ በኋላ በእጅጉ ማደግ የጀመረችው አዋሳ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆናም የሲዳማ ዞን ደግሞ መቀመጫ ነች፡፡የሲዳማ ልሂቃን በአዋሳ ከተማ ላይ አይናቸውን እንዲጥሉ ያደረጋቸው ነገር እነሱ ከተማዋ በታሪክ የእኛ ነች ከሚሉት ማስረጃ አልቦ ጉዳይ በተጨማሪ አዋሳ ከተማ የሲዳማ ዞን መቀመጫ መሆኗም ነው፡፡የሲዳማ ዞን መቀመጫ እንድትሆን የሆነውም አቶ መለስ አዋሳ ላይ አይኑን የተከለውን የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ያቀዘቀዙ መሏቸው ባመጡት መላ ነው፡፡ ይህ ግን ጭራሽ ጉጉታቸውን ጨመረው እንጅ አላስታገሰውም፡፡
የራስን ምኞት ብቻ ተከትሎ ለሚሰግረው የሲዳማ ሊሂቃን ጥያቄ ጥሩ ከለላ የሆነው ደግሞ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የደቡብ ክልልን የስልጣን ቁንጮ ተቆናጦ የያዘውን የርዕሰ መስተዳድርነቱን ቦታ (አንድ ጊዜ አቶ ሃይለማርያም ጣልቃ ከመግባታቸው ውጭ) የሲዳማ ልሂቃን ብቻቸውን የተቆጣጠሩት መሆኑ ነው፡፡በአዋሳ ከተማም ሆነ በደቡብ ክልል የመንግስት መዋቅር ላይ በርከት ብለው የሚገኙት የሲዳማ ልሂቃን እጅ በክልሉ መክበዱ ሌሎችን የክልሉ ብሄረሰቦች ባይትዋርነት እንዲሰማቸው ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በ1995ቱ አዋጅ “ሰባ ሰላሳ” የሚባል ቀመር በአዋሳ ከተማ አስተዳደሩ ላይ እንዲተገበር ሆኖ ነበር፡፡
በዚህ ቀመር መሰረት በአዋሳ ከተማ ላይ አይናቸውን የጣሉት የሲዳማ ልሂቃ በከተማ አስተዳደሩ ላይ የሰላሳ ፐርሰንት የስልጣን ቅርምት እንዲኖራቸው እና የተቀረው ሰባው ፐርሰንት በሌሎች ብሄረሰቦች እንዲያዝ የሚደነግግ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ለሲዳማዎች የሰላሳ ፐርሰንት የስልጣን ይዞታ የሚሰጠው አካሄድ ለሲዳማዎች ያደላ ነው በሚል ከሲዳማ ውጭ ያሉትን የደቡብ ልሂቃን ያስደሰተ አልነበረም፡፡የባሰው ሲመጣ ግን በአዋሳ ከተማ አስተዳደር በዛ የተባለው የሲዳማዎች የሰላሳ ፐርሰንት የስልጣን ይዞታ ወደ መቶ ፐርሰንት ተጠግቶ ለስሙ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ የተባለውን የአዋሳ ከተማ አስተዳደር የሲዳማ ልሂቃን እንዳሻቸው ያደርጉታል፡፡በዚህ ምክንያት የድሬዳዋ ህዝብ 40-40-20 በሚል የስልጣን ድልድል ሳቢያ ተጎዳን ብሎ ሲያምፅ የሰማ ሰሞን የአዋሳ ህዝብ “እኛ በመቶ ፐርሰንት የሲዳማ ገዥዎች ወድቀን በድንጋይ ተገድለን እሳት የሚለቀቅብን ምን እንበል?” እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡በአጠቃላይ በደቡብ ክልል የሲዳማ ፖለቲከኞች የደቡብ ክልል ህወሃቶች ተደርገው የሚወሰዱ እበልጣለሁ ባዮች ናቸው፡፡
በአዋሳ ከተማ የሚኖር በንግድ፣በኢንዱስትሪ፣ኢንቨስትመንት እና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው ከተሜው እና ባለሙያው መደብ የመኖሪያ ቤት መስሪያ አጥቶ በኪራይቤት እየኖረ ከአዋሳ ከተማ ውጭ በአንዱ የሲዳማ ዞን ገጠር የሚኖር የሲዳማ ተወላጅ አዋሳ ከተማ ከአንድ በላይ ቦታ ተመርቶ ሁለቱን ሸጦ ሶስተኛው ላይ ቤት ይሰራል፡፡በከተማ አስተዳደሩ መዋቅር ላይ ሁሉ ያሻውን ነቅሎ የወደደውን ይተክላል፡፡የከተማ አስተዳደሩ የስራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ በህግ በተደነገገበት ሁኔታ “ኤጀቶ” የተባሉ (ከሲዳማ ገጠራማ ቦታዎች መጥተው አዋሳ ከተማን የሚያምሱ) ጎረምሶች በደቦ ወጥተው በከተማዋ ውስጥ በአማርኛ የተፃፈን የግልም ሆነ የመንግስት ድርጅቶች በመግቢያ በሮቻቸው ላይ ስማቸው የተፃፈባቸውን ባነሮች ሁሉ ሲቀዱ፣ ሲሰብሩ በሲዳማ ዘረኛ ካድሬዎች የሚዘወረው የክልሉም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ መንግስት በዝምታ ያያል ወይም ያበረታታል፡፡በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ ቀርቶ በአዋሳ ከተማ የሚገኙ ነገር ግን በፌደራል መንግስት ስር ናቸው የሚባሉ እንደ አዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተቋማት ጭምር በሲዳማ ልሂቃን ከመዘወር አልፈው ኤጀቶ የተባለው የሲዳማ ጎረምሶች ስብስብ የሚያሾራቸው ሆነው አርፈዋል!
በደቡብ ክልልዋና ከተማ አዋሳ የሲዳማ ልሂቃን ሶስት ነፍስ አላቸው፡፡አንደኛው እና ዋነኛው የክልል ርዕስ መስተዳድርነቱን ይዘው የክልለሉን ፀጥታ ሃይል ጨምሮ ሁሉን የሚዘውሩበት ነው፡፡ይህን ስልጣን ተጠቅመው ኤጄቶ በሚል ስም ለሚንቀሳቀሰው ጎረምሶች ቡድን ድጋፉን ይሰጣል፡፡ይህን ለማረጋገጥ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተብለው ተቀምጠው እንደ ኤጀቶ የሚናገሩት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ለተለያዩ መገናኛብዙሃን የሚሰጡትን ቃለ-ምልልስ ማዳመጥ ነው፡፡ሁለተኛው ነፍሳቸው የአዋሳ ከተማ አስተዳደርን መንግስታዊ መዋቅር ጠቅልለው ይዘው የከተማዋን ሁለመና የሚያሾሩበት ነገር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በከተማዋ መሃል አናት ላይ የቆመው ሃውልት ካዘለው መልዕክት እና ምስል ጀምሮ በከተማዋ የሚታየው ነገር ሁሉ ከደቡብ ክልልነት ይልቅ የሲዳማ ክልልነት ዝንባሌ ያለው ነው፡፡ሶስተኛው ነፍሳቸው በአዋሳ ከተማ በተቀመጠው የሲዳማ ዞን መቀመጫ አማካይነት የክልሉን ዋና ከተማ አዋሳን የሲዳማ ዞን ከተማ ብቻ ለማስመሰል የሚሰሩት ስራ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ በመጣ ቁጥር የአዋሳ ህዝብ ሳይወድ በግድ ገንዘብ እንዲያዋጣ፣በየንግድ ቤቱ በር ላይ የዘመን መለወጫ መልካም ምኞቱን በባነር አሳትሞ እንዲለጥፍ ግልፅ ባልሆነ ግዳጅ ይገደዳል፡፡የመልካም ምኞት ባነር መለጠፍ በዓል አክብረው በሚመለሱ የሲዳማ ጎረምሶች የድርጅቱን እቃ ከመሰባበር ለማዳን የሚደረግ መከላከያ እንጅ በየ አመቱ መጤነቱ እየተነገረው የሚሰደብበትን፣ከገጠር በመጡ ጎረምሶች የሚዋከብበትን በዓል ለማክበር ውስጣዊ መሻት ኖሮት አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ አዋሳ ሲዳማ ላልሆነው ኢትዮጵያዊ የማትመች ከተማ ከሆነች ሰንበት ብላለች፡፡ይህን ነገር ለማስቀጠል የሲዳማ ዘረኛ ልሂቃን እና ካድሬዎች ምን እየሰሩ እንደሆነ ይህን ለመግታት ክልሉን የሚመራው ደኢህዴን እና የፌደራል መንግስቱ እንዲሁም የአዋሳ ህዝብ ሊወስዳቸው ስለሚገቡ እርምጃዎች ሃሳቤን ለማጋራት በሚቀጥለው ሳምንት እመለሳለሁ፡፡