ዘመናችንን እንደገና እንዋጅ!  (በዮሴፍ ወርቁ ደገፋ)

ወድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ሁሉም በእርሱ በሆነው፣ ከሆነውም  እንኳ ኣንዳችም ያለእርሱ ባልተፈጠረው፣ በሀያሉ እግዚኣብሔር ስም እንደምን ሰነበቻሁ? በኣጸደ ስጋ ሳለን ለሰማይም ለምድርም የከበዱ ሁለቱ ዋና ጉዳዮች ያንጎዳጉዱናል። ኣንድም ነፍሳችን ጽድቅ ፍለጋ በውስጣችን ወደፈጣሪዋ ስትጮህ፣ ኑሮ ደግሞ በራሱ መንገድ ያወዛውዘናል።
መንፈሳዊውን ስንል፣ ማህበራዊውና ኢኮኖሚያዊው ይታገሉናል፣ የፖለቲካው ጣጣ ኑሮኣችንን ብርቱ ሰልፍ ያደርገዋል። በዚህም ለእግዚኣብሄር ክብር፣ ለራሳችንና ለሌሎች ሰዎች ሚዛናችንን ጠብቀን ለመኖር እንቸገራለን። ከሰዎች ጋር በፍቅርና ባንድነት መኖር እንዲሁ በቀላሉ አይመጣልንም።
ከእውነት ጋር መቆም መንፈሳችንን ጽኑ ስለሚያደርግ ነው እንጂ፣ ሀሰትና ክፋት በመንገሳቸው ህይወታችን ምንግዜም በትግል ላይ ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር መልካም ፍሬዎች እንዳይፈሩ የሚከለክሉ የስጋ ስራዎች በርካታ ናቸው። በፖለቲካው ቀርቶ በቤተ እምነታችን ውስጥ እንኳን ሀሰት እንጂ እውነት ቦታ የላትም።
ጠ/ሚር ኣቢይን እንደምሳሌ ብንወስድ  እግዚኣብሄርም ሰውም የሚወደውን መልካም ስራ ከመስራት ውጭ፥ ምን መጥፎ ስራ ስለሰሩ ነው ምድሪቱ ክፋት በክፋት የምትሆነው? በርግጥ ሰዎችን በማጋጨት፣ መከራና ሞት በማድረስ “ኑሮኣቸውን” የሚኖሩ ጥቂት የሰይጣን ኣገልጋዮች አሉ። ነገርግን የምድራችንን የመከራ ስፋትና ጥልቀት ስናይ መላው ሀገሬው በጥፋት ጎዳና ላይ የተሰለፈ ይመስላል።
ህያው መጽሀፍ ግን የመኖራችን ትርጉም ‘ለእግዚኣብሄር ክብር፣ ለሰዎችም በረከት መሆን’ እንዳለበት ይናገራል። ታዲያ እንዴትና እንዴት ተብሎ ነው ለሌሎች የሚተርፍ ህይወት ለመኖር የሚቻለው? በተለይም ዛሬ ሰው ማለት የጎሳ ኣባል ብቻ የሆነበት የዘረኝነት መንፈስ ኣገራችንን ክፉኛ ተጣብቶኣታል። ወንድም በወንድሙ ላይ ኣረመኔያዊ ጭካኔ ይፈጽማል። በመሆኑም ሰላምና በአንድነት መኖር በሀገራችን መሰረታዊ ህዝባዊ ችግር ሆኖኣል።
ጥበብ፣ አርቆ ማሰብና ማስተዋል ሰለጎደለን ነው እንጂ የችግሩ መንስኤ እኛው እንደሆንን፣ የመፍትሄው አካልም እኛው ነን። ግና ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዘላቂ ሰላም በምድራችን ለማምጣት አልተቻለንም። ከሁሉም በላይና በፊት ሰዎች ሁሉ እኩል መሆናቸውን እያወቅን ባለማወቅ በኣድሎና በኣግላይነት ቀንበር ታስረናል። ከጎሳችን ውጭ በሌላው ሰው ላይ ልባችን ደንድኖኣል፣ ያንዳንዱም በክፋት ሀሳብ ተወጥሮኣል (በርግጥ ሰው ከኣንድም ከሁለትም ከብዙ ጎሳዎችም ሊወለድ ይችላል፣ ነገርግን ጎሳ መርጦ የተወለደ ይመስል፣ ሰው ያለሀጢያቱ በጎሳው ምክንያት ብቻ ስለምን ይጠላል? ይሰደዳል? ይገደላል?) የራስንና ጎሳን ብቻ በ”መውደድ” ቀንበር የተነሳ ለሌላው ሰው ፍቅር በማጣት የጉስቁልና በሽታ የተያዘው በሚሊዮን ይቆጠራል።
ምን ይደረግ? አሁንም ትልቁ ተስፋችን እግዚኣብሄር ብቻ ነው፣ ከእግዚኣብሄር በታች እኛው ለእኛው ነው ያለነው። በእውነት ለሚሆን ፍቅርና ኣንድነት እሺ ብንል በሰላም ልንኖርና ልንባረክ፣ እንቢ ብንል ደግሞ ሰይፍ ሊበላን ተዘጋጅቶኣል። ስለዚህ ከእግዚኣብሄርም ከራሳችንም ጋር ታርቀን በመኖር ከመታዳደግ ውጭ ሌላ የሚበጅ ኣማራጭ የለንም፣ ካለም አቅርቡ። በዚህ የፍትህ መንገድ ብቻ ነው እኛም ሰው ሆነን ሌሎችንም ሰው ለማድረግ የሚቻለን።
‘ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ይጣላል’ በማለት መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚናገረን፣ በከንቱ ኖረን በከንቱ እንዳንሞት እንጠንቀቅ! ግትርነት ከንቱነት ከሚሆንብን ቀድሞውንም ኣለመፈጠር ይሻለናል! (እግዚኣብሄር ግን ሰውን ለከንቱነት አይፈጥርም፣ ነገርግን ሰው የአኣምሮ ችግር ከሌለበት በስተቀር ከንቱ የመሆን የግል ምርጫ ጉዳይ መሆኑ ነው ችግሩ)
ደግሞም ቅዱስ መጽሀፍ ስለት ‘ስለትን እንደሚስል ወንድም ወንድሙን ይሳል’ ይላል። በክፉት ሀሳብ ተገፋፍተን ከመውደቅ ይልቅ፣ መልካሙንም ሕጸጹንም ስራችንን ፊት ለፊት እያቀረብን፣ ለማፍረስ ሳይሆን ለመገነባባት እንተናነጽ። በዚህም የሰማዩን ብቻ ሳይሆን የምድሩንም ጊዜያዊ ጎጆ በጋራ በመስራት 100 ኣመት እንኳን የማትሞላ እድሜን ሰላም ሳንነፍጋት እንኑር!
ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? እንዲህ ይቻላል፣ ክርስቶስ ኢየሱስ 10ቱ ትእዛዛትን በሁለት ትእዛዛት ኣጠቃልሎኣቸዋል፣ ‘ፈጣሪ አምላክህን እንደራስህ ውደድ’ የምትለዋ የመጀመሪያ ዋና ትእዛዝ፣ እንዲሁም ሁለተኛዋና የመጨረሻዋ ትእዛዝ ደግሞ ‘ሰውን ሁሉ እንደራስህ ውደድ’ የምትል ስለሆነች፣ ይቻለናልና ኣንፍራ!
ነገርግን በፍቅር እና በአንድነት መኖር የሰማይ ያህል ርቆን ሳለ ‘ፈጣሪያችንን እንወዳለን!’ ብንል ራሳችንን እያታለልን ነው። ሌሎችን እያገለልንና እያሳደድን ፈጣሪ ከእኛ ጋር ሊሆን ፈጽሞ ኣይችልም። ለምን? እግዚኣብሄር ከክፋት ጋር ህብረት የለውምና። ያለ እግዚኣብሄር “ደስታ” እና “ሰላም” ያለን ቢመስለን እንኳን የውሸትና የለበጣ ወይም የግብዝነት ነው። ባጠቃላይ ሁለቱ ዋና ዋና ጉዳዮቻችን ዋጋ ቢሶች ከሆኑ በምድርም በሰማይም ዋጋ የለንም፣ ዘመናችንን በከንቱ መጨረስ ብቻ! ይሁንና ዘመናችንን ለመዋጀት እንደምንችል ኣሁንም መጽሀፍቅዱስ ያስተምራል! ዘመናችንን እንደኣዲስ እንዋጅ!!!
እግዚኣብሄር ከዚህ ያውጣን ማለት ብቻ ኣይበቃም! የእኛም ፈቃድኝነት መታከል ኣለበት! እግዚኣብሄር በእኛ መልካም ፈቃድ ላይ ብቻ ነው የሚሰራው!
መልካም ሀሳብና የቀና ልብ ይሁንልን! ኣሜን!
ተጨማሪ ያንብቡ:  ‘‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!!’’ በኒቆዲሞስ (ከሀገረ ኢትዮጵያ)
Share