—————-
ብዙ ጸሃፊዎች ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የተለያዬ ሀሳብ ያራምዳሉ::እኛ በእግዚአብሄር ቃል እንደሚያምን ሰዉ ግን እግዚአብሄር ህሊና ዉስጥ ያለዉ ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነዉ ብለን እናምናለን::
ስለሆነም የኢትዮጵያዊነት የአስተምህሮታችንም ሆነ የህሳቤአችን እንዲሁም የኢትዮጵያዊ ማንነታችን ማጠንጠኛ መሰረቱ የእግዚአብሄር ቃል የሚገኝበት መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ነዉ:: ስለ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ስናስብ ምርኩዝ የምናደርገዉ የእግዚአብሄር ቃል መሆን አለበት::
ኢትዮጵያዊ ማንነት ምንድነዉ? ኢትዮጵያዊነትስ ምን ማለት ነዉ? መገለጫዉስ? የሚሉትን እና ተያያዥ ጥያቄዎችን መጽሃፍ ቅዱስ በአስገራሚ ሁኔታ አፍታትቶ አቅርቦታል::
ክፍል 1:- ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ምንድን ነዉ?
—————————-
– ኢትዮጵያዊ እግዚአብሄር በአንደበቱ ህዝቤ ያለዉ ህዝብ ነዉ:: ማንነቱም የእግዚአብሄር ልጅነት ነዉ::ትንቢተ አሞጽ 9፥7 እንዲህ ይላል::”የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር፡፡” ይሄም አስገራሚ ነገር ነዉ::ለምን ቢሉ : ኢትዮጵያዊ ማንነት በእግዚአብሄር ዘንድ የታወቀ እና የተመሰከረለት ማንነትን ነዉ ማለት ነዉ። እናም እግዚአብሄር ልጄ ብሎ ከገለጸዉ ኢትዮጵያዊ ማንነት በላይ ሌላ ማንነት ለኢትዮጵያዊ ሰዉ ማንነት የለዉም::
– እግዚአብሄር ኢትዮጵያዊዉን ልጄ ነዉ ሲል የተናገረለት ህዝብ ክርስቲያኑን ብቻ ነዉ ብሎ መጠዬቅም ይገባል:: ብዙዎችም እንደሚጠይቁ ይታወቃል:: መልሱም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንጂ እስላም ወይም ክርስቲያን አላለም:: ግዚአብሄር ኢትዮጵያዊ ሲል ሙስሊም ወይም ክርስቲያን አላለም::ሲጀምር እግዚአብሄር ኢትዮጵያዊ ልጄ ሲል የኢትዮጵያን ሰዉ ሁሉ የጠራዉ ከክርስትናም ከእስልምናም እምነት በፊት ባለዉ ዘመን ዉስጥ ነዉ:: በብሉይ ኪዳን ማለት ነዉ::
እናም እግዚአብሄር “የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ የ እግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ የተናገረዉ ለክርስቲያን ወገን ብቻ ነዉ ብሎ የሚያስብ ካለ እራሱን ያርም::
-እግዚአብሄር ኢትዮጵያዊን ህዝቤ ልጄ ያለዉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነዉ። በህዝቡ መሃከል ያሉ ጥቂት ልዩነቶችንም (አንዳንድ የቋንቋ እና የባህል ልዩነቶችን ደግግሞ) አንድ የነብር ቆዳ ላይ እንዳሉ የቀለም ልዩነቶች መስሏቸዋል። ነብሩ አንድ እንደሆነ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብም አንድ የ እግዚአብሄር ህዝብ መሆኑን እግዚአብሄር በመጽሃፍ ቅዱስ አስረግጦ ተናግሯል::
እግዚአብሄርን የሚያምነዉም ወገን ወይም የማያምነዉም(ዛፍ የሚያምነዉ:ቃልቻ የሚያምነዉ: ጣኦት የሚያምነዉ እግዚአብሄር የለም የሚለዉ) ኢትዮጵያዊም ሁሉ የእግዚአብሄር ልጅ ስለተባለ የእግዚአብሄር ልጅ ነዉ::
ይሄን ሁሉም ሚስጢር ትንቢተ ኤርምያስ 13፥23 እንዲህ ያብራራዋል ‘በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? “:: እናም ኢትዮጵያዊነት ሰዎች በፈቃዳቸዉ ሊለዉጡት የማይችሉት ማንነት ነዉ::
ይሄም የሆነዉ ኢትዮጵያዊነት በእግዚአብሄር ህሳቤ ዉስጥ ያለ ነገር ስለሆነ ነዉ::ኢትዮጵያዊነት ቃል ነዉ:: ከቃልም የእግዚአብሄር :: “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” የተባለለት ቃል:: ይሄን ጥያቄ ደጋግሞ ማሰብ ይገባል::እግዚአብሄር “ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን” ሢል ምን ማለቱ ነዉ?
ክፍል 2:- የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር
————————–
ኦሪት ዘፍጥረት እንደሚያብራራዉ ጥንታዊዉ የኢትዮጵያ መልከአምድር ከገነት ጋር ያለዉ ቁርኝት እና ትስስር በዘፍጥረት 2፥13 በደንብ ተገልጿል:: እንዲህም ሲባል ተብራርቷል::
እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር።
የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤ ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል።የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው። መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 1፥38 ደግሞ “ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት።” ይላል ::
ክፍል 3:- ኢትዮጵያ የእግዚአብሄርን ምልክት በምድር ላይ የሚጠብቅ: የእግዚአብሄርን ጥንታዊ ስራዎች የማይክድ: የእግዚአብሄርን በዓላት በጥንቃቄ የሚያከብር ህዝብ ነዉ ኢትዮጵያ የእግዚአብሄርን ምልክት ምልክቱዋ ታደርጋለች: የእግዚአብሄርንም ማደሪያ ታከብራለች: የእግዚአብሄር ቅዱሳን በአላትንም ታከብራለች : ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሄር በምድር ላይ ታላላቅ ታምራት ያደረገባቸዉን ቀናት ታስባለች::
የእግዚአብሄርን መታሰቢያ ለማሰብም ህግ ሰርታላቸዋለች:: በሰባት እግዚአብሄር አብርሃም ቤት የገባበትን: በ19 እግዚአብሄር ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ዳንኤልን ያዳነበትን : በ16 ለእመቤታችን ምህረትን የሰጠበትን : በ12 ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ ወዳጆቹን የታደገበትን: በ27 ክርስቶስ ኢየሱስ ለአለም ህዝብ ቤዛነት የተሰዋበትን: በ29 ክርስቶስ ኢየሱስ ለአለም ድህነት የተወለደበትን: እንዲሁም እያንዳንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ የተበሰረበትን: የተጸነሰበትን በአጠቃላይ እግዚአብሄር ልዩ ልዩ መልአክትን እና ቅዱሳንን እየላከ በክንዱ አለምን ያዳነበትን : እግዚአብሄር በክንዱ ምህረት ያደረገባቸዉን ቀናት ታስባቸዋለች:: ታከብራቸዋለች::
በመዝሙር 74 እንደተነገረዉ “አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ” እንደተባሉት ወገኖች ኢትዮጵያ የ እግዚአብሄርን በዓል ለመሻር አትራወጥም::
በመዝሙር 74:14 አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። የተባለላት ሀገር ነችና ምግብ የተባለ የሆድ ነገር ሳይሆን የመንፈስ ምግብ ነዉና የእግዚአብሄር መታሰቢያዎቹን : ከጥንት ጀምሮ በምድር ላይ ያደረገዉን ቸርነቱን እንዲሁም የእግዚአብሄር የአምልኮ ቤቱን እና ምልክቱን ታከብራለች:: ለአለምም ታሳዉቃለች:: ወደፊት የሚመጡ ኢትዮጵያዉያንንም በየትኛዉም አለም ቢኖሩ ወይም ምንም አይነት ቋንቋ ቢናገሩ ወይም ምንም አይነት ሞያ ቢኖራቸዉ የእግዚአብሄርን ነገር በምድር ላይ ማክበር እንዲሁም ለዓለም ማሳወቅ ስራቸዉ ሆኖ ይቀጥላል::ለምን እና እንዴት ቢባል ኢትዮጵያዊ በእግዚአብሄር አንደበት ልጄ የተባለ ህዝብ ስለሆነ ነዉ::
መዝሙር 74 ላይ የተነገረዉን አስተምህሮት በጥንቃቄ ከዚህ ዘመን ተጨባጭ አለም አቀፍ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ መመርመር ይገባል:: ህጻናትም ሆኖ አዋቂዎችም ይሄን እንዲረዱት ማሳወቅ ይገባልም::
“ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥ ሁልጊዜም በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ። ጠላቶችህ በበዓል መካከል ተመኩ፤ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ። እንደ ላይኛው መግቢያ ውስጥ በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥ በመጥረቢያ በሮችዋን ሰበሩ። እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት። መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ። አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ።
ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም። አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ሁልጊዜ ያቃልላልን? ቀኝህን በብብትህ መካከል፥ እጅህንም ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ? እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። ”
ይሄም ሲብራራ ሰይጣን ሰዉን በልዩ ልዩ ስልት አሳቦ ማሳሳት ስለሚወድ አንዳንዱን የአለም ክፍል በነጻ አስተሳሰብና ነጻ የሀይማኖት ፍልስፍና አሳቦ ባዶዉን አስቀርቶታል:: ቤተክርስቲያናት እንዲዘጉ አድርጓል::
ቤተክርስቲያኖችን ወደ ዳንስ ቤት ካስቀየረ ብሁዋላ ዛሬ በርካታዉ የአለም ክፍል አለም የርኩስ መንፈስ መፈንጫ ሆኗዋል:: ቤተክርስቲያንናትን መጀመሪያ አያስፈልጉም በሚል ፍልስፍና የክርስቶስ አማኝ ክርስቲያኖችን በግዴለሽነት ልባቸዉን ካደነዘዘ ብሁዋላ: በነጻ አስተሳሰብ አሳቦ የክርስቶስ ምልክት : መስቀልና የእግዚአብሄር መታሰቢያ ቀናትን ከምድር እንዲደመሰሱ ብዙ የሀሰት አስተምህሮቶች ተነዝተዋል::
ከእነዚህ ሀሰተኛ አስተምህሮቶች ዉስጥ ሰዉ የእግዚአብሄርን በአላት ካከበረ ሰነፍ ይሆናል የሚል ነዉ:: ዛሬ እግዚአብሄር በብዙ የአለም ክፍል ክርስቲያኖች አዕምሮ የ እግዚአብሄር ጥንታዊ ስራዉ መታሰቢያዎች እንዲወገዱ ሆነዋል:: እንዳይታሰቡ ተደርጓል:: ኢትዮጵያ ግን ከላይ በመዝሙረ ዳዊት 74 እንደተባለላት የእግዚአብሄርን ምልክት ምልክቱዋ ታደርጋለች: የእግዚአብሄርንም ማደሪያ ታከብራለች: የእግዚአብሄር ቅዱሳን በአሉትንም ታከብራለች : ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሄር በምድር ላይ ታላላቅ ታምራት ያደረገባቸዉን ቀናት ታስባለች:: የኢትዮጵያ ሰዉም ይሄን ነገር በምድር ላይ ይተገብራል ለአለምም ያሳዉቃል::ህጻናት ወይም አዋቂዎች ይሄን ሚስጢር እንዲረዱት ማድረግ እና ተግቶ ማስተማር ይገባል::
ክፍል 4:- ኢትዮጵያዊ የእግዚአብሄር ካህናት ለሙሴ መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲሁም የስራ አመራር ክህሎት ያስተማሩ ናቸዉ
ኦሪት ዘጸአት ም. 4 እንደሚያብራራዉ የሳጲራ አባት ካህኑ ዮቶር እግዚአብሄርን የሚያመልክ ሰዉ ነበር::ይሄም ካህን ለሙሴ የማኔጅመንት/ስራ አመራር/ ጥበብን እና መንፈሳዊ ሚስጥራትን ይገልጽ ነበር::
“የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ።
እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፦ ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው። ሙሴም አማቱን፦ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው። የሙሴም አማት አለው፦ አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም።
አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው። አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው።
በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል። ይህንም ብታደርግ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል። ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ። ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶም አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ።”
ክፍል 5:- ኢትዮጵያዉያንን የክርስቶስ ኢየሱስን መወለድ እግዚአብሄርን እያመለኩ በተስፋ ሲጠብቁ የነበሩ እና በ34ዓም ቀድመዉ ክርስቲያን የሆኑ ህዝቦች ናቸዉ
የሃዋርያት ስራ ም 8 ከቁጥር 27 ጀምሮ ያለዉ አስተምህሮት አስደማሚ ሚስጢራትን ይገልጻል:: እንዲህም ያትታል::
“የጌታም መልአክ ፊልጶስን፦ ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው። ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን፦ ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው።
ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና፦ በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። እርሱም፦ የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?
ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ፦ እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፦ እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፊልጶስም፦ በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና።”
ይሄ ታሪክ በ34 ዓም የተከናወነ ነዉ::
እዚህ ታሪክ ዉስጥ ጃንደረባዉ እግዚአብሄርን የሚያመልክ ሰዉ እንደነበረ በግልጽ ተቀምጧል::እንዲሁም እግዚአብሄርን እያመለከ ኢየሱስ ክርስቶስን በተስፋ ይጠብቅ እንደነበረ የሚያብራራዉ ክፍል ደግሞ ያነብ የነበረዉ መጽሃፍ የክርስቶስን መወለድ እና ሞቱን የሚያትተዉን የትንቢት ክፍል ነበር::እየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል የነበረዉ የ እምነት ፍጥነትም ታላቅ እና ፈጣን ነበር::ማንልባትም በአለም ታሪክ ዉስጥ እንዲህ በፍጥነት “ጃንደረባውም፦ እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፊልጶስም፦ በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።” የሚል ዉብ እምነት ይገኛል::
ጃንደረባዉ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መጥቶ ክርስትናን በፍጥነት አስተምሮ በርካት ህዝብን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ወገን አድርጎታል::
አንዳንድ ስህተተኛ የሆኖ ጸሃፊያን ኢትዮጵያ ክርስትናን በ4ኛዉ ክፍለ ዘመን ተቀበለች ሲሉ ይሰብካሉ::እዉነቱን ግን መጽሃፍ ቅዱስ በሚገባ አብራርቶታል::ኢትዮጵያ ቀዳማዊት ሚስጥራዊት የክርስቶስ ባለሟል ነች::
ክፍል 6: ሌሎች የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች
—————–
-በመጽሃፍ ቅዱስ ተብራርቶ እንደተገለጸዉ የኢትዮጵያዊ ቁመቱ እና መልኩ የታወቀ ነዉ:: ይሄንንም ህጻናት ወይም አዋቂ ወገናቸዉ ኢትዮጵያዉያንን እንዲወዱ እና ኢትዮጵያን በልባቸዉ እንዲስሏት ማስተማር ይገባል::
-ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያዉያን በመንፈሳዊዉ አለም የስነ ከዋክብት ቀማር ህሳቤንም አዉጠንጣኝ እና ከሌላዉ አለም የተራቀቀ ባለ እዉቀት ናቸዉ:: ለማጣቀሻም በመዝሙረ ዳዊት 148 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት::መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት። የሚለዉን እና በተለይም በቁጥር 3 ላይ “ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ፥ አመስግኑት።”
የሚለዉን ቃል ኢትዮጵያዉያን ከአንድ ሽህ አመታት በፊት በመዝሙር አንደምታ የተነተኑበት እና ያስረዱበት መንገድ እጅግ የተራቀቀ እና የስነ ከዋክብት እዉቀታቸዉ እጅግ እረቂቅ መሆኑን የሚያሳይ ነዉ::
ክፍል 7:- የአለም ታላላቅ ሰዎ ህሳቤ ስለ ኢትዮጵያ
-ግሪካዉያን ኢትዮጵያዉያን እንደ አማልክት ቆንጆ የሆኑ እና ቆዳቸዉ ጥቁር ህዝቦች ናቸዉ ሲሉ ይገልጿቸዋል::
-በርካታ የጥቁር ህዝብ መብት ታጋዮች (የጥቁር አሜሪካዉያን ነጻነት ታጋዮች እና የአፍሪካዉያንን የዲሞክራሲ ተምሳሊት በመባል የሚታወቁት ማንዴላ) እንዲሁም ጃማይካዉያን ኢትዮጵያን የሰዉ ልጆች የነጻነት ተምሳሌት ናት በማለት ይገልጿታል::ኢትዮጵያ በማንም ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ስለሆነችም እንደ ነጻነት መንፈስ መቀስቀሻ አድርገዉ ይጠቀሙባታል::
– አንዳንድ ጸሃፊዎችም ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያንን ብዙ መጥፎ ነገሮች የሚያሰራጩ አሉ::እንዴዉም አንዳንድ ቡድኖች ኢትዮጵያ የሚለዉን ቃል ከመጽሃፍ ቅዱስ ለማስፋቅ የሚሰሩም አሉ::
ሆኖም አንድ እዉነተኛ ኢትዮጵያዊ እና እግዚአብሄር ኢትዮጵያዊ ልጄ ነዉ የሚለዉን ሀሳብ የሚቀበል ሰዉ ከሁሉም በፊት ማወቅ እና መረዳት ያለበት እርሱ የ እግዛኢብሄር ልጅ እንደሆነ ብቻ ነዉ::የ እግዚአብሄር ልጅነቱን ለማሳጣት ዲያቢሎስ በልዩ ልዩ ጸሃፊያን እና ቡድኖች በኩል ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ዘመቻ በሚያደርግበት ጊዜ በእግዚአብሄር ቃል የሚያምን ሰዉ አይናወጥም:: ለእግዚአብሄር ቃል ታምኖ ይቆማል እንጂ::
ህጻናት ወይም አዋቂዎች ከልጅነታቸዉ ጀምረዉ ይሄን ሚስጢር በደንብ ተረድተዉ ከብዙ አቅጣጫ በሚመጡ አስተምህሮቶች እንዳይወናበዱ ማድረግ የቤተሰብ ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ታላቅ ሀላፊነት ነዉ:: ሰንበት ትምህርት ቤት በዚህ ረገድ ቀዳሚዉ ረድፍ ላይ ትገኛለች::
ክፍል 8:- የሰዉ ልጅ አንድነት እና የክርስቲያኖችን ሁሉ አንድነት የማሰብ መርህን ሳይረሱ እግዚአብሄር ኢትዮጵያ የሚለዉን ታላቅ ማንነት ማወቅ እና ማክበር ይገባል ሲባል ሊታወስ የሚገባዉ እዉነታ
ወደ ሮሜ ሰዎች 3፥22 በስፋት እንደሚያብራራዉ “እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤” ይላል እንዲሁም 10፥12 ደግሞ “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤” ሲል ሁላችን አንድ መሆናችንን ይሰብካል::
እናም እግዚአብሄር ልጄ ስለሚለዉ ኢትዮጵያዊ ማንነት ስናስተምር እና ስናብራራ ከሌላዉ የአለም ማህበረሰብ የተለዬን መሆናችንን በማጉላት ለመለዬት ለመነጠል እና ለመኮፈስ አይደለም::ከዚያ ይልቅ እንደ ክርስቲያን “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው” የሚለዉን የኢየሱስ ክርስቶስ መርህ በመከተል በጥቁር : በነጭ ወይም በሌላዉ የሰዉ ዘር መካከል ልዩነት እንደሌለ ማስረዳትም የክርስቲያን ጥበቡ ሊሆን ይገባል::ኢትዮጵያን ግን እግዚአብሄር ልጄ ሲል በቃሉ ጠርቶታል እና ይሄንንም የ እግዚአብሄር ህሳቤ በማክበር ኢትዮጵያዊ ምንነትና ማንነትንም ጠንቅቆ ማወቅ እና መላበስም ተገቢ ነዉ::
=============================
መደምደሚያ:- ኢትዮጵያዊነትን የሚዋጋዉ የርኩስ መናፍስት ሀይል ማን ነዉ? ለምንስ ኢትዮጵያን ይጠላል?
—————————————
መልሱ ቀላል ነዉ::የ እግዚአብሄር መንፈስ አብሮት የሆነ ማንኛዉም ሀይል በቀላሉ መርምሮ መረዳት ይቻላል::ከላይ የተነሱትን ነጥቦች እስከ መጨረሻዉ ያነበበ የ እግዚአብሄር መንፈስ ያለበት ወገን ኢትዮጵያዊ በመሆኑ በደስታ ልቡ ይዘላል::የርኩስ መንፈስ ተሸካሚዎች ግን ከላይ የተቀመጠዉን የኢትዮጵያዊነት ሚስጢር ሲያዉቁ ዋይ ብለዉ ያብዳሉ::
የመድሃኒዓለም ሀይል ከኢትዮጵያዊነት እና ከኢትዮጵያዊ ጋር ነዉ