“ማንነት! ማንነት ማንነት !”የአላዋቂዎች ጩኸት – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

እኔ ማነኝ?ሰው ነኝ።ሰው ከመሆን ውጪ ፣ለሰው ሌላ ማንነት የለውም።
” ያላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋል።”
        የአእምሮ ልማት የሌሎች ልማቶች መሠረት ነው።
ሀገርን በፈጣን ዕድገት ለማሳደግና ልማቷም ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ በቅድሚያ የሰው አእምሮ በጠቅላላ ዕውቀት መልማት አለበት።በጥበብም መበልፀግ አለበት።
    በጠቅላላ ዕውቀት በመዳበር በወጉ ያለማ  ና በጥበብም ያልበለፀገ አእምሮ በአንድ አገር ውሥጥ እየበዛ ካልመጣ፣  ሰላምና ብልፅግና አይኖርም።ሁለ አቀፍ ዕውቀት ና ጥበብ የሌለው ፣ጥራዝ ነጠቅ ና አሥመሣይነት የተካነ  ዜጋ  ከበዛ ደግሞ  ተጠምዛዥ፣ተጎታችና፣ጥገኛ እየበዛ ይመጣል። ይህ ጥገኛም ፣የሌሎች ቡድኖችና ግለሰቦች መጠቀሚያ ነወ የሚሆነው።
     ከዚህ ነባራዊ ዕውነት  በመነሳት ፣ ጥቂት የማይባለው የሀገሬ አዲስ ትውልድ ባለፉት 28 ዓመታት  ከጥበብ በእጅጉ በመራቁ ራሱን እሥከ አለማወቅ ደርሷል።ከጥንት ፍጥረቱ ሰው መሆኑን ዘንግቷል። አገዛዙ ለራሱ እንዲመቸው የፈጠረው ከጥበብ የራቀ ሰውነትን የሚያሥክድ የማደናበሬ ሥልትም ሠምሯል።
    ይህ እኩይ ሥልቱም፣ከጥበብ በራቁ ፣”ሆድ ና ቁሥ የዚህ ዓለም አልፋና ኦሜጋ ናቸው።” ብለው በሚያምኑ ዜጎችም ተወድሷል ። ያውም ከደርግ የመሥከረም ሀለት ና ከላብ አደሮች ሰልፈ በተኮረጀ ና ዘንድሮ (ከ28 በኋላ)  ህዝብ ግዳጅ ስለሌለበት በተወው የተፅዕኖ የድጋፍ ሠልፍ እየታጀበ።
     ከእውነት መዝገብ እንደተረዳነው ና ዛሬ አፉን ከፍቶ ሊውጠን ካሠፈሠፈው ጨካኝ አፈሙዝ ተላቀን ሣንፈራ የምንናገረው ሃቅ እጅግ በጣም ብዙ ነው።
   ህወሃት  መራሹ ኢህአዴግ  ከደርግ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ጋር ተመሣሣይ የሆነ፣በከፍተኛ  አመራር ትዕዛዝ ሰጪነት  ከቀበሌ የሚነሣ ፣ በተጽዕኖ ና በጥቅም ላይ የተመሠረተ ፣በድራማ የተሞላ ፖለቲካ ነበር ሲያራምድ የነበረው።በዚህም ሰበብ ሰውነታችንን አሥረሥቶን ነበር።
   ሰው ልጅ፣  እውነት  ከሆነው የእሱነቱ መገለጫ ከሰውነቱ  ይልቅ፣ በብዙ ሺ ዓመታት የኑሮ ሂደት ሰው ቁጥሩ እየበዛ ሲመጣ ፣ህይወቱን ለማቆየት በተለያየ የዓለም ክፍል በመሰደዱ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ ከቀየውና ከአካባቢው በመለየቱ።(በምህንድሥና የተሠራ መንገድና  ድልድይ አይታወቁም ነበር ። ) በድንገት በደረሰበት ሀገር ና አህጉር   የፈጠረውን የተለያየ  ባህል ና ቋንቋ  በእኛ ሀገር ፣የፖለቲካችን ዋና መዘውር እንዲሆን በመደረጉ፣ ከጥበብ የራቁ ፣እና የገዛ ቤተሰባቸውን እንኳ በቅጡ ማሥተዳደር የማይችሉ ግለሰቦችን ወደአመራራ አምጥቷል።
    መለሥ ዜናዊም  አሥቀድሞ አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ እንደሚገላቸው በመገንዘቡ፣ በአብዘኛው፣ በዙሪያው የሰበሰበው ከጥበብ በእጅጉ የራቁትን ነው።
   አዲሱን  ትውልድ “ማንነትህ ቋንቋ ና ባህልህ ነው። ” በማለት ሰው ከተሰኘ የወል ማንነቱ ይልቅ ፣በባህሉ ሰበብ የሌለ የማንነት ትርጉም ላይ እንዲሞዘዝ በማድረግ   ከጥበብ እንዲርቅ ያደረገው ሆን ብሎ ፣ለራሱና ለቡድን አጋሮቹ፣ ሥኬት  ሲል መሆኑን ከዚህ እውነት ተነሥተን ልንመሠክር እንችላለን።
    ምሥክርነታችንም ከንቱ አይደለም። ህወሃት  መራሹ ኢህአዴግ በዚህ ድርጊቱ በ28 ዓመት ውሥጥ ከጥበብ የራቁ ጥቂት የማይባሉ ወላጆችና አሥተማሪዎች ፈጥሯል።  ከጥበብ የራቀው ወላጅ፣፣መምህር ና በተዋረድ ያለ ከጥበብ የራቀ የመንግሥት አካል ነው።(በቡድን ሰውን አልከሥም) ለዛሬው ህሊና ቢሥ ወጣት የጥፋት  ድርጊት ተጠያቂ የሚሆነው።
  በማሥተዋል፣አርቆ በማሰብ፣ማንኛውንም ሃሳብ በማዳመጥና አሉታዊና አወንታዊ ጎኑን በመመርመር፣ ከራስ አኳያ በህሊና ሚዛን በመመዘን ፣ ከግል ሥሜት ውጪ በመመልከት ብይን  የማይሰጡ፣ወላጆች፣መምህራኖች፣ፖለቲከኞች በበዙበት ሀገር፣መጥፎ ሱሱች በተሥፋፉበት ከተማ ና ገጠር ምን ዓይነት ትውልድ ሊበቅል እንደሚችል ይታወቃል።
      ዛሬ፣ዛሬ፣የቢራ ዓይነት ብዛቷል።የአሥረሽ ምቺው ቤት ተበራክቷል።በከተማና በገጠር ጥቂት የማይባል ወጣት በሱስ ደንዝዞል።ይህንን ሃቅ መካድ አይቻልም።
     ዛሬ እኮ ” ባልወልደውም ልጄ ነው።”ብሎ ለጠፋው በግ ተቆርቋሪ አዛውንት የበዛ አይደለም።
  አንድ ወጣት  ዩኒቨርሥቲ ገብቶ ፣ሌሎች በዕውቀት ልቀው ጥበባቸውን ለመላው ዓለም የተውትን ምሁራን ትምህርት ከየመጸሐፋቸው እየቀዳ ፣ አእምሮውን በማልማት እሱም እንደእነሱ ጥበበኛ መሆን ሲገባው “መንገድ በተጣለ በማይረባ ቆሻሻ ሃሳብ እና ፍሬ ቢሥ ነገር… “በቃየል መሰል  ደነዝ አእምሮ” ወንድሙንየሚገድል  ከሆነ፣ እንዲህ አይነት ህሊና የሌለው ሰው የዕብዶች መታከሚያ ሆስፒታል እንጂ ዩኒቨርስቲ መገኘት አልነበረበትም። አለመታደል ሆኖ ግን እብዱን ተማሪ ብቻ ሳይሆን እብዱን ፖለቲከኛ ና ከታች እሥከ ላይ ያለውን ውሳኔ ሰጪ አካል አእምሮ ጤነኝነት አረጋግጦ ወደሥራ እንዲሰማራ የጤንነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት የሚሰጠው የለም። አፍሪካ ውሥጥ ጠመንጃ ያላቸው ጥቂት ደፍር ጓዶች ካሉህ በተጨቋኙ እና በደሃው ህዝብ ሥም ሥልጣን ትይዛለህ።ህዝብም እንደ ኢዲያሚን ፣እንደቦካሳ፣እንደ ጋዳፊ፣ ወዘተ።ወዘተ።ያጨበጭብልሃል።ዓመት ሳይሞለህ ግን ፣ለዳቦ ፈላጊው፣የወስፋቱ ጩኸት አላሥተኛው ላለው ምሥኪን ህዝብ ያለህን ንቀት ታሳያለህ።”…ዝም በሉና ተገዙ።እኔ ከእናተ ጫንቃ የምወርደው በባዮሎጂ ወይም በሌላ  ባለጊዜ ( ባለጠመንጃ ) በአፈሙዝ   አሥገዳጅነት ብቻ ና ብቻ ነው።” ትላለህ እንደአልበሽር ሙባረክ፣  ቡታፍሊካ…።
   የዛሬዋ ኢትዮጵያ  በአፍሪካ ከምናውቀው በጠመንጃ ሥልጣንን ዘላለማዊ የማድረግ መንገድ ለመውጣት ፣ እየታገለች የምተገኝ ሀገር ናት።በግንባር ቀደምትነት ለውጡን የሚመሩ ግለሰቦችም ፣የመከላከያ ና የፍትህ ተቋሙን በማጠናከር አንዳችም ድራማ የማይታይበት ምርጫ እንዲካሄድ ለማድረግ ቀና ደፋ እያሉ ነው።ሆኖም ግን ከምርጫ በፊት በቀበሌ በክ/ከተማ፣ በዞን ና ክልል የተዘረጋውን  የካድሬ ስብስብ ፣ ማፍረስ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።ሥፍራውንም በጥበብ በተሞሉ የማዘጋጃ አገልግሎት ሰጪዎች  መተካት፣ ያሥፈልጋል።
    በካድሬነትም ይሁን በአባልነት ሥልጣን የተሰጣቸውን አንስቶ ፍፁም ሙያተኛ ተኮር የሆነ አገልግሎት ሰጪ ፣በየአገልግሎት ዘርፉ መመደብ እና ለፖለቲካ ሰራተኞቹም እንደቀድሞ ሥራቸው ተገቢውን ቦታ በመሥጠት የፖለቲካ ና የምርጫ ምህዳሩን ማሥፋት ከወዲሁ “አብይ መራሹ መንግሥት “ሊያተኩርበት ይገባል።
   እነዘህ ማሥተካከያዎችን” አብይ መራሹ መንግሥት” (ገዢው ፖርቲ ኢህአዴግ የማልልበት አንድ ሺ አንድ ምክንያቶች አሉኝ ) እሥካላሥተካከለ ጊዜ ድረሥ    ከትግራይ እሥከጋምቤላ ፤ ከሞያሌ እሥከ ኦጋዴን፤ከደንቢዶሎ እስከ መተማ የተፎካካሪ ፖርቲዎች ኡ!ኡ! የዴሞክራሲ ያለህ ” የሚል  ጩኸት ገዝፎ መሰማቱ አይቀርም።ምርጫው እንደሚጭበረበር ፣ኮሮጆውም በሐሠት መራጭ ድምፅ እንደሚሞላ ከወዲሁ መገመት አይከብድም።
   ያለአንዳች ጥረት ና ግረት በሥልጣን ተጠቅመው ፣ በመሬት ሽያጭ ና በተቀነባበረ የባንክ ብድር ፣ ዓይናችን እያየ ከአጠገባችን እንደሮኬት የተተኮሱ ፣ መኖራቸውን በምንገነዘብበት ሀገር፣ዛሬም እንደትላንት ባለ የምርጫ ቦርድ መዋቅር ምርጫ እሥከ ቀበሌ ለማድረግ ከታሰበ ምርጫው እንደሚጭበረበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
  እርግጥ ነው፣አጭበርባሪው ነገ ሌላ ሥም፣ወይም የቀድሞውን ኢህአዴግ ይዞ የሚመጣው ብቻ አይሆንም።
   ለእውነት የመሞት እሴታችን በተሸረሸረበት ሀገር እና ከጥበብ የራቁ  ና ሰው መሆናቸውን የዘነጉ ሰዎች በበዙበትም ሀገር አጭበርባሪ  እንደሚበዛ ይታወቃል። ከጥበብ የራቀ አእምሮ ሲበዛ እንኳን ለምርጫ ፣ ለሀገር ህልውናም አሥጊ ነው። ከጥበብ የራቀ አእምሮ   “ከጅብ ቆዳ እንደተሰራ ከበሮ ሁሌም ፣ ለእኔ!ለእኔ !…” ሥለሚል፣የሀገር ዕድገት ፀር መሆኑ ይታወቃል።
     አሁን እያስተዋልን ያለነው የሀገር ዕድገት ፀርነት እየተስፋፋ የመጣው የዜጎች እእምሮ እንደዜጋ ለኢትዮጵያ እንዲያስብ የሚያስችል አእምሮአዊ ልማት ሳናሰልስ ባለማካሄዳችን እና መልካሞችን ባህላችንን በባዕዳኑ መጥፎ ባህል ወረራ በማጣታችን ነው።
   በዚህ የባህል ወረራ ሰበብ በከተሞቻችን፣ወጣቶቻችንን በአካልም ሆነ በአእምሮ የሚገነቡ ጅምናዚዬሞች ና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች  ሳይሆኑ ፣ መጠጥ ቤቶች፣ጭፈራ ቤቶች፣ጫት መሸጫ ና ሺሻ ማስጨሻ ቤቶች በመበራከታቸው ምክንያት ፣ ሱሰኞች እና አመንዝራዎች፣አጭበርባሪዎች እና ሌቦች፣ቀማኞች እና
ዘራፊዎች ፣ ከቀን ወደቀን እየተበራከቱ መጥተዋል።
    ጥቂት የማይባለው ከጥበብ የራቀው ፣በፍላሎት የሚተከተከው ጎረምሳ፣( ከተሜ ና ባለአገር  )፣ ባለማወቅ አስገዳጅነት እና ዘር ላይ ባጠነጠነ የመሰሪ ሰዎች ቅስቀሳ እና የውጪ እጅም ባለበት ሤራ ፣ በጠባብ ሀገረኝነት እና አግላይነት  ጎራ እየተሰለፈ ነው።ይህ ጎራ የግብዞች ጎራ ነው።ይህ ጎራ  የሥሥታሞች  ጎራ ነው።ሠልፉም ፣ የትዕቢተኞች  ሰለፈ ነው።
    ከታሪክ እንደምንረዳው፣ይህ ሰልፍ ፣ትላንት አውዳሚ ሃሳብን ብቻ የሚሰብክ ፣ የማያመዛዝን  ህሊና በሌላቸው ከጥበብ በራቁ  ፣”ከራሥ በላይ ነፋሥ።” በሚሉ ቅጥረኞች የሚመራ ነበር።…
   በነዚህ ከጥበብ በራቁ   ሰዎች የጥፋት ሰልፍ ምክንያት ሰው፣ሰውን(አምሳያውን ወይም ራሱን) በሰውነቱ ሳይሆን በዘሩ ና በብሔሩ እንዲመለከት ሥለተደረገ በጭካኔ ያለህግ ወይም ያለፍትህ ሰው እንደ አውሬ፣ በደመ ነፍሥ ሰውን በደቦ ጨፍጭፎ ገሏል።
   ይህንን   ውጉዝ የሆነ  ድርጊት ከጀርባ ሆነው የሚቆሰቆሱት፣ የዘር ፣የጎሣንና የቋንቋን ፖለቲካ እሳትን  የሚያረግቡ ናቸው። በዚህ ዘመነኛ ዓለም ፣ ሰው በአፍ መፍቻ  ቋንቋው ሣይሆን ከአፍ መፍቻ ቋንቋው ውጪ ሢናገር ፣የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆነ ከሳቁበት ጅሎች ናቸው።ልክ የእራቱ ወጥ ሲተከተክ የሽሮውን ድንፋታ አይቶ እንደሳቀው ጅል ሰው ነው አሥተሣሠባቸው።ደግሞም ከጥበብ በእጅጉ የራቁ እንደመሆናቸው ከእኩይ ምግባራቸው በኋላ እንኳ አይፀፀቱም።
    እንደዚህ ዓይነቶቹ ናቸው ለሚኖሩበት ማህበረሰብና  ለሀገር  አደገኞቹ።…  እኩይ ድርጊት እንዲከሰት በብርቱ ቆሥቁሰው ፣አሣዛኝ እና አሠቃቂው ድርጊት ከተፈፀመ በኋላ፣ ዳር ቆመው  “ከደሙ ንፁህ ነን።…” የሚሉ…።አይገርሙም።በነሱ ቅሥቀሳ አይደለም እንዴ  የዋሆቹ  የሞት ሰልፍ  የተሰለፉት???
     የእነዚ በመሰሪነታቸው የሚታወቁ የሴራ ፖለቲካ አራማጆች ሰልፍ ” የቅስፈት ሰልፍ ” እንደሆነ ግን  አዳሜ አያውቅም።ሄዋኔም አታውቅም። በዚህ እጅግ አስቀያሚና ሞት የፊት መሪ በሆነበት ሰልፍ፣በሚያሳዝን መልኩ አለማወቅ ያወራቸው ሰዎች በብዛት ተሰልፈው ሳይ በእጅጉ እፈራለሁ።ምክንያቱም በዚህ ሰልፍ ሰውነትን ፈፅሞ የረሳ፣ወደአውሬነት የተለወጣ(ሰው ከጥበብ ከተለየ ወደእንሥሣነት መዝቀጡ አይቀርምና) ገጀራ፣ቆንጨራ፣ዶማ፣መጥረቢያ፣አካፋ፣ወዘተ የያዘ አቅለ ቢሥ ፣ሰው ይታየኛል።
     ይሄ አቅለ ቢሥ  የሞት ፊትአውራሪ፣ እንደ እንሥሣ በአንድ ዓይነት ዕውቀት የተሞላ እና ፣ልክ ግዳዩን እንዳገኘ እሱን ገድሎ መብላት እንደሚያሥደሥተው አውሬ በውስጡ  የሚንቀለቀል፣ ፍላጎቱን  ማሳካት እንጂ  የንፁሐን ደም እንደጎርፍ ቢፈሥ ከቶም አይበርደውም። …
 ይህ ሰልፍ፣አስቀያሚ እና ራሱ የሞት አጋፋሪ በግንባር ቀደምትነት የሚመራው ሠልፍ  ከመሆኑም በላይ፣ሂትለራዊ ነው።ሁቷዊ ነው።(የሩዋንዳ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ ያካሂዱትን  ጭፍጨፋ ያስታውሷል)በዚህ ሁቱአዊ ሰልፍ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ፣ ሰው መሆናቸውን ፈፅሞ የዘነጉ የአእምሮ ህሙማን ናቸው። ፍጥረታቸው እንኳን ከሥነ ህይወት አንፃር ከሌላው ሰው ጋር ተመሳሳይ መሆንን አይቀበሉም።ለእነሱ ፣ሰው የሚባለው አምሳያቸው አይደለም።በቋንቋና በተወሰነ ባህል እንዲሁም በመልክ የተለዩ በመሆናቸው ከሌላው ዜጋ ወይም ሰው፣የሚሻሉ ምርጦች እንደሆኑ ያስባሉ። እናም አልማዞች ነን።ወርቆች ነን።…ሌላው ሰው ግን በሮሮ ነው።ሰው አይደለም።በማለት በትምክህትና በትዕቢት ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በነእሱ ዐይን ሌላው ዘር፣ጎሳና ብሔረሰብ
…ጎዶሎ ነው።እናም ሞት ይገባዋል።(በርዋንዳ የሆነው ይሄው ነው።የተገደሉት ቱትሲዎች ሰዎች ሆነው ሳለ በረሮች ናችሁ ተብለው ነው።
    በጠባብ ጎሠኝነት ና ዘረኝነት  ሰልፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ፣ሌሎች ብሄሮችን በጅምላ ግለሰቦችን በተናጥል አኮስሰው ማየት እና ለትውልዳቸው ይህንኑ መስብክ የዘውትር ተግባራቸው ነው።
   አእምሯቸው  በጥበብ ሥለአልማ እና አጠቃላይ ዕውቀትን ሥላአልገበየ ከእነሱ በተቃራኒ የቆመውን ሲገድሉ ዝንብ ወይም በረሮ እንደገደሉ እንጂ “ራሳቸውን እንደገደሉ” አይገነዘቡም።እነዚህ  በጠባብ   ጎሠኝነትና ዘረኝነት  የናወዙ ሰዎች እያጠፉ ያለው ህይወት የሰው ህይወት ነው። ሰው እንደመሆናቸውም የራሳቸውን ህይወትም ነው እያጠፉ ያሉት።ግን ይህንን አይገነዘቡም።ምክንያቱም አእምሮአቸው አለማም።ጥበብ አልባ ነው።
       አእምሮአቸው አለማም ስል፣ዲግሪዎች የሏቸውም።የዕውቀት ደሃ ናቸው።ማለቴ አይደለም።እንደውም ትምህርት ቤት ደጀፍ ያልደረሱት ከአንዳዶቹ ባለድግሪዎች በመቶ እጥፍ የሻላሉ። ምክንያቱም በጥበብ የተገነባ አእምሮ አላቸውና!!
    እውነት ነው።የሰውን ልጅ ሁሉ በማፍቀር ወደር የሌላቸውን የገጠር ኗዋሪዎች በየትም የሀገራችን ክፍል ብንሄድ በብዙ ቁጥር እናገኛቸዋለን። ሆኖም የቀለምን ተምህርት የዘለቀው  ምሁር ነኝ ባይ ምክራቸውን ሰሚ ጆሮ የለውም።በቀለም ተሟልቷል።” ተምሯል” ሥል አእምሮው ለምቷል ማለቴ አይደለም።
የቀለም ትምህርት መማር ብቻውን አእምሮን አያለማም።ከህይወት፣ከሀገር፣ከተለያዩ ዓለማዊና መንፈሳዊ መፀሐፍት፣ከመገናኛ ብዙሃን  እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎችና ከኃይማኖት አባቶች ወዘተ።የምናገኘው ዕውቀት ነው ጠቢብ የሚያደርገን። አእምሯችንን  የሚያለማው።የቀለም ወይም የሙያ ትምህርቱ እንጀራ ለማግኛ ነው የሚረዳን።
     እናም  ፣የዜጎችን አእምሮ ለማልማት እና ከጠባብ ብሔርተኝነት ለማውጣት ፣የመንግሥት ሚና የአንበሳውን ድርሻ መያዝ እንዳለበት አምናለሁ። ግን የቱ መንግሥት?? ወደፊት  ከምርጫ በኋላ  የሚመጣውን  መንግሥት ማለቴ ነው።
     ለማንኛውም ፣ ከምርጫ በኋላ  ጥበብ በምድሪቱ ይነግሥ ዘንድ ፣ ዜጎች አእምሯቸው እንዲለማ ፣ከጫት ቤትና ከመጠጥ ቤት ይልቅ መፀሐፍት ቤት እና ወጣቶች አካላቸውን አእምሯቸውን የሚያጎለብቱበት ሥፍራዎች እንዲበዙ ሁኔታቸውን ማመቻቸት የሚችል ፣ ኢትዮጵያ እንዲኖራት እመኛለሁ።
     ምኞቴ በዚህ አያባራም።በጥበብ የተሞሉ አባላትን አቅፎ፣ አያሌ ገንቢ ሥራዎች በመሥራት ዜጎች በጥበብ እንዲሞሉ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ዜጎች ሁሉ ፣የወል መጠሪያቸው ሰው እንጂ ቋንቋ ያለመሆኑን    እና ዜጎች ሁሉ ፣ የአንድ ሉአላዊ ሀገር ባለቤት መሆናቸውን ተገንዝቦ፣ በሀገራቸው የግዛት ክልል ሁሉ ፣ ያለሥጋት ተዘዋውረው መሥራት እንዲችሉ የማደረግ ብቃት ያለው ና የሐብት ክፍፍሉን ሚዛናዊ የሚያደርግ  ፖለቲካ ፓርቲ ኢትዮጵያ እንዲኖራት እመኛለሁ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  የሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት የአራተኛ መደበኛ ስብሰባ የአቋም መግለጫ

1 Comment

  1. Senseless!
    የሚገርመው፣ ብዙዎች ስሜታቸውን ብቻ ለመግለጽ ከችሎታቸው በላይ የሆነና ራሳቸው በቅጡ ስለማያዉቁት ነገር፣ መላ ቅጡ የጠፋው ብዙ ገጽ ይዘከዝካሉ! እድሜ ለኢንተርነት፣ ገጽ ለመሙላት ወይም ተመልካች ለመሳብ ብቻ ጥሩ አርዕስት ተሰጥቶት ይለጠፋል። ይህ የመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ጽሁፍም ከነዚህ ገለባዎች አንዱ ነው!

    @አዲሱን ትውልድ “ማንነትህ ቋንቋ ና ባህልህ ነው። ” በማለት ሰው ከተሰኘ የወል ማንነቱ ይልቅ ..@ ብሎ criticize ለማድረግ ይሞክራል! ለማህበራዊ ሰው ቋንቋና ባህሉ የማንነቱ መገለጫዎች ካልሆኑ በሁለት እግር መሄዱ ብቻ ነው እንዴ “ሰው” የሚያሰኘው? ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል እና ሌሎች ማህበራዊ እሴቶች ከሌሉት “ሰው” መባሉ “ከብት” ተብሎ ከሚጠራው እንስሳ የሚለየው ለመጥሪያነት የተጠቀምንበት ቃል ብቻ ነው የሚሆነው!

    እንኳን ሰው፣ እንስሳ እንኳ ማንነት አለው። አንዱ በሬ ከሌላው በሬ የተለየ ዐመል አለው። በመልክም በቁመናም በዕድሜም ይለያያሉ። ነጭ ሰው፣ ቢጫ እና ጥቁር የሰው ዝርያዎች አሉ። ከዚያም ወረድ ብሎ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በስነ ልቦና እና የመሳሰሉትን የሚጋሩ የሰው ልጆች ስብስቦች አሉ። በዛሬው ዐለም ደግሞ፣ በፖለቲካ የተደራጁ፣ ከዚያም አልፎ የራሳቸውን ልዑላዊ ሃገር የመሰረቱ፣ ወይም ለመመስረት የሚጣጣሩ ህዝቦች አሉ።

    ለራሳችሁ የተሸዋረረና በጭንቅላቱ የቆመ የፖለቲካ አስተሳሰብን አመንክዮአዊ ለማስመሰል ብቻ ከተፈጥሮአዊ ህግጋት ዉጪ ባዶ ቃላትን በማዥጎድጎድ ምሁር ለመምሰል አትጣሩ! ከእንስሳት ተራ ወጥታችሁ ማንነት ያለው “ሰው” ሁኑ!

Comments are closed.

Share